July 20, 2024
ጠገናው ጎሹ
በመሠረቱ እንኳንስ በእንደ እኛ አይነት ዘመን ጠገብ ፣ግዙፍ እና በእጅጉ አስከፊ በሆነ አጠቃላይ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ቀውስ በተመታና በመመታት ላይ በሚገኝ አገር ይቅርና በተወሰኑ የእቅድና የክንዋኔ ዘርፎች ፈታኝ ሁኔታ ወይም ቀውስ በሚያጋጥመው የትኛውም አገር ውስጥ ችግሩን ይፋ የሚያደርጉ መግለጫዎችን የመስጠት እና ከጅግሩ መውጫ የሚሆኑ አዋጆችን የማወጅ አስፈላጊነት የሚያጠያይቀን አይመስለኝም።
የእኛ የመጀመሪያው ውድቀታችን የራሳችንን እጅግ አስከፊና መሪር እውነታ በፅዕናትና በጥበብ ለመጋፈጥ እና ትክክለኛ ፍኖተ መፍትሄ አምጠን ለመውለድ ሲያቅተን ዙሪያውን እየዞርን የመግለጫና የአዋጅ ጋጋታ በማንጋጋት በሥልጣነ መንበር ላይ የሚፈራረቁ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የድንቁርና እና የመከራ ሰለባ ያደረጉትና እያደረጉት ያሉት መከረኛ ህዝብ እልህ አስጨራሽና ብቸኛ ነፃ መውጫ ከሆነው የዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ተጋድሎው የማዘናጋታችን አስቀያሚ የፖለቲካ ማንነታችን ነው።
መግለጫዎቻችንና አዋጆቻችን ወደ ተግባር ሊተረጎም ከሚችል የተግባር ውሎ ጋር ተቆራኝተው ፖለቲካ ወለድ መከራንና ውርደትን አስተማማኝነትና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ድል በመንሳት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሚወስደን ፍኖተ ግስጋሴ ላይ መሆናችንን እንዲመሰክሩልን ለማድረግ አለመቻላችን ያስከተለውና እያስከተለ ያለው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ዶፍ በራሱ ግልፅና ግልፅ መሆኑን የማይገነዘብ ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ወገን የሚኖር አይመስለኝም።
የመግለጫና የአዋጅ ጋጋትን በራሱ እንደ የስኬት መለኪያ እየቆጠርንና የዲስኩር ድሪቶ እየደረትን ከራሳችን አልፈን ሃሳብን ወደ ተግባር ከምንተረጉምበት የአእምሮና የአካል ፀጋ ጋር የፈጠረንን ፈጣሪ ጨምረን የማታለሉን እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ ማንነታችን ነገ ሳይሆን ከዛሬ ጀምሮ በቃን ማለት ይኖርብናል ። ይህንን ተገንዝቦና ከምር ተፀፅቶ ወቅታዊና ገንቢ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ወኔው የሚያጥረው ምሁር፣ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት ስለ ምን አይነት የሰላምና የፍቅር አገር እንደሚሰብክና እንደሚያውጅ ለመረዳት ያስቸግራል ።
በህወሃት የበላይነት እና ለአሽከርነት በፈጠራቸውና ባሰማራቸው ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደህዴን ተብየዎች አሽከርነት ለሩብ ምዕተ ዓመት የዘለቀው የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በኦህዴድ/ኦነግ የበላይነት እና የሰው ሥጋ ለባሽ አጋሰሶች በሆኑ ብአዴንና ደህዴን አሽከርነት ስሙን ብልፅግና በሚል የማጭበርበሪያ ስያሜ በመሰየም በመከረኛው ህዝብ ላይ የማታለያና የወዮላችሁ መግለጫና አዋጅ እያዥጎደጎደ ቀጥሏል ።
እርግጥ ነው አገርን ምድረ ሲኦል ያያደርጉና እያደረጉ ያሉት እኩያን ገዥ ቡድኖች መግለጫዎችንና አዋጆችን እንደ መደበኛ የማፈኛ ወይም የመቀጣጫ ወይም የማታለያ መሣሪያነት የመጠቀማቸው ጉዳይ ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ የመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን የምንገኝበት መሆኑ በእጅጉ ቢያሳዝንም የማይጠበቅ ግን አይደለም ።
በእጅጉ የሚያሳዝነውና ብርቱ ጥያቄ የሚያስነሳው የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ራሳቸው ግልፅ በሆኑና ባልሆነ የእኖር ባይነትና/የአድር ባይነት ልክፍት ምክንያት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የመከራና የውርደት ዶፍ አምራችና አከፋፋይ የሆነው የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ሰለባዎች ሆነው እያለ የሚያወጧቸው መግለጫዎችና የሚያውጇቸው አዋጆች ስሜት የሰጣሉ ወይ? የሚለው ነው ።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነት የበላይ አካል የሆነው ሲኖዶስ ከሐምሌ 22-28-2016 የአወጀውን የፀሎትና የምህላ አዋጅ ከሃይማኖታዊ እምነት መሠረታዊ ምንነትና እንዴትነት አንፃር ለመቀበል በፍፁም ባያስቸግርም ለብዙ ዓመታት እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሴረኛና ሸፍጠኛ ገዥዎች አደገኛ ተፅዕኖ ሥር ከወደቀው የሲኖዶሱ መሪር እውነታ አንፃር ግን ጥያቄ ቢነሳ የሚገርመው ወይም የሲኦል መንገድ የሚመስለው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ክርስቲያን ካለ እውነተኛ ክርስቲያንነቱን መመርመር ይኖርበታል።
አዎ! መሬት ላይ ተዘርግቶ የሚታየውንና የሚነበበውን ግዙፍና መሪር እውነታ እና ለዚህም የሃላፊነትና የተጠያቂነት ድርሻ ባለበት የበላይ አመራር (ሲኖዶስ) ላይ ሂሳዊ አስተያየት (ትችት) መሰንዘርን ፈጣሪን እንደ ማስቀየም፣ መሪዎችን እንደ መዳፈር ፣ ሃጢአትን እንደ መጋበዝ ፣ ሰላምን እንደ ማጣትና እንደ ማሳጣት፣ ፍቅርን እንደ ማርከስ፣ ወዘተ አድርጎ በማየት አካኪ ዘራፍ ማለት በፍፁም የትም አያደርስምና የሚሻለው የየራስን ህሊና ከምር መመርመር ነው።
የሃይማኖት ተቋሙ ዋና መንበረ ሥልጣን እና የእኩያን ፖለቲከኞች የቤተ መንግሥት መንበረ ሥልጣን እጅግ አስቀያሚ በሆነ ሁኔታ እየተደበላለቁ ለዘመናት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሃይማኖትን ጨምሮ መሠረታዊ መብቶቹ ለተረገጡበትና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ለመግለፅ በሚከብድ ሁኔታ እየተረገጡበት ያለውን የአገሬ ህዝብ በድርጊት በሚገለፅ ፀሎትና ምህላ ከማገዝ ይልቅ “ይህ ሁሉ የሆነውና የሚሆነው ኀጢአትህ ቢከፋ ነውና በየገዳሙና በየቤተ እምነቱ እግዚኦ በል” የሚል አዋጅ ማወጅ እና የአመራር ቅዱስነት አድርጎ ለማሳየት መሞከር ራስን ብቻ ሳይሆን ፈጣሪንም መሸንገል ነው የሚሆነው። አዎ! የመከራና የውርደት ዶፍ ዋነኛ ምክንያት ከሆኑት የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እየተሻሹ አገርና ሃይማኖት ፈተና ላይ ናቸውና ይህንን እንዲያስወግድልን እግዚኦ በሉ የሚል አዋጅን ያለምንም ጥያቄ መቀበል እንዴት ይቻላል? መጠየቅስ እንዴት ሃጢአት ሊሆን ይችላል?
አገርን ምድረ ሲኦል እያደረገ ያለው ገዥ ቡድን መሪ የሆነውንና በንፁሃን የግፍ አሟሟትና የደም እንባ የሚሳለቀውን ፣ የኦርቶዶክ ቤተ እምነቶችንና አገልጋዮቻቸውን የሰቆቃና የውድመት ሰለባዎች ያደረገውን፣ ለፈፀመውና ላስፈፀመው ፖለቲካ ወለድ ሰቆቃ ተሳስቶ እንኳ ለሆነው ሁሉ አዝናለሁና ይቅርታም እጠይቃለሁ የማይለውን እጅግ ጨካኝ (አረመኔ) ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየ (አብይ አህመድ) “ለአገር ልማት፣ ለሰላም መስፈን፣ ለህዝብ ደህንነት፣ ለቤተ ክርስቲያናችን ከበሬታ፣ ወዘተ እየቃተትክ (እየለፋህ) እንቅልፍ ማጣትህ ያሳስበናል” የሚሉ ጨካኝ ካድሬዎችን “ንፁህ” ኦሮሞነታቸውን አጣርቶ እና የጵጵስና ዩኒፎርም አጎናፅፎ አባላት ባደረገ ሲኖዶስ ከሚታወጅ የፀሎት፣ የፆምና የምህላ አዋጅ በአዋጁ የተጠቀሱትን በጎ ዓላማዎች እውን ለማድረግ እንዴት ይቻላል? ይህንን አይነት ወለፈንዲነት (paradox )የሚባርክና የሚቀድስ እውነተኛ ፈጣሪስ ይኖራል ወይ?
ለመሆኑ ከእረቂቅ የማሰቢያ አእምሮ እና ከሙሉና ብቁ የተግባር ማከናወኛ አካል ጋር ፈጥሮ በዚሁ ድንቅ ስጦታ አማካኝነት የእርሱን ድጋፍ እየጠየቅን ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ህይወት የሚበጅ ሥራ እንድንሠራ የፈጠረን አምላክ “ይህንን ሁሉ ድንቅ ስጦታ በአግባቡ ሳትጠቀሙበት እግዚኦ የምትሉብኝ ለምንድን ነው?” ብሎ ቢጠይቀን አጥጋቢ መልስ ይኖረናል እንዴ?
እጅግ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥዎችን በሃይማኖታዊ ሃላፊነትና የአርበኝነት አቋምና ቁመና በግልፅና በቀጥታ ለመገሰፅ እና አማኞችን (ምመናንን) ደግሞ “የዘመናት መከራና የደም እንባ (የመቃብርና የቁም ሙትነት) ፍፃሜ ያላገኘው እግዚኦታችንን እና የሰላምና የፍቅር አርበኝነታችንን (የተግባር ውሏችንን) ማቆራኘት ስላቃተን እንጅ ፈጣሪ እገዛውን ነፍጎ ሊቀጣን ስለፈለገ ፈፅሞ አይደለምና ይህ እንቆቅልሽ ይብቃን” ብሎ ለመናገር የሚገደው የሃይማኖት አመራር የሚያውጀው ድርጊት አልባ የፆም፣ የፀሎትና የምህላ አዋጅ ወደ የት ይወስደናል? የትስ ነው የሚያደርሰን?
እጅግ አያሌ አማንያንና ንፁሃን ዜጎች ለዓመታት የግፍ ግድያና የቁም ሞት ሰለባዎች ሲሆኑ እኩያን ገዥዎችን ፈራ ተባ እያሉ ከመማፀን እና “በፈጣሪ ያውቃል” ስም ከመሪሩ ሃቅ ከመሸሽ ያለፈ አቋምና ቁመና ያላስተዋልንበት ሲኖዶስ ያወጀውና ወደፊትም በዚሁ አቋሙና ቁመናው በሚያውጀው አዋጅ የሚስተጋባው እግዚኦታ ወደ የት እና እስከ የት ነው የሚወስደን?
ፀሎት፣ ምህላ ፣ እግዚኦታ እና ፆም ፈጣሪን በፈጣሪነቱ የምናመሰግንባቸው ፣ የምናስበው በጎ ሃሳብ እንዲሰምር እና የምናከናውነው ገንቢ ተግባር ውጤታማ እንዲሆን ፈቃዱንና እገዛውን የምንጠይቅባቸው ሃይማኖታዊ መሣሪያዎች (መንገዶች) እንጅ በራሳቸው (በዘልማድ ስለምንፈፅማቸው) የምድራዊውም ሆነ የሰማያዊ ህይወት ዋስትናዎች አይደሉም። በሌላ አገላለፅ ከተግባራዊ የህይወት ምንነት ተነስቶ ተግባራዊ ለሚሆን የምድራዊና የሰማያዊ ህይወት ስኬታማነት መሣሪያ የማይሆን የድርጊት አልባ ፆም፣ ፀሎትና ምህላ አዋጅ አደረግን ለማለት ካልሆነ በስተቀር ፈፅሞ ወንዝ አያሻግርም። “ፍቅር ከሌለኝ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው” በሚለው ታላቅ ሃይለ ቃል የምናምንና የምንግባባ ከሆነ የፍቅር ወይም የመፈቃቀር ምንነትና እንዴትነት ራስን ለመስዋእትነት እስከማቅረብ የሚደርስ ተግባራዊ ሰብእናንና ሃላፊነትን ግድ የሚል እንጅ የመግለጫና የአዋጅ ጋጋት ጉዳይ አይደለም።
የሚያጠያቀንና ሊያጠያይቀን የሚገባው የእኛ አገር የይታወቅልን መግለጫ እና ይህንን አድርጉና ያንን አታድርጉ የአዋጅ ጋጋታ ከእኛው ከራሳችን መላልሶ የመውደቅ አዙሪት ለምን አልታደገንም? የሚለው እጅግ ዘመን ጠገብና መሪር የሆነው የእኛነታችን ጉዳይ ነው። የየራስን የውስጠ ነፍስ የተቃርኖ እንቆቅልሽ (the very paradox within our inner souls) ከማንምና ከምንም በፊት ልባዊ፣ ጥልቅና ብሎም ትውልዳዊ አርአያነት ባለው ንስሃ (አስቀያሚና ተደጋጋሚ ውድቀትን ከምር በሚቀበልና ለእርምት ዝግጁ በሆነ አቋምና ቁመና) ከመፍታት ይልቅ በየገዳሙና በየቤተ ክርስቲያኑ “እግዚኦ በሉ” የሚልን አዋጅ ተቀብሎ የሚባርክ እውነተኛ አምላክ የለም ብሎ እውነት መናገርን እንደ ሃጢአት ቆጥሮ መዓት የሚያወርድ ፈጣሪ ፈፅሞ የለም።
ይህንን አይነት እጅግ አስቀያሚ እንቆቅልሽ ( ugly puzzle) ሁለገብ በሆነ የአርበኝነት አቋምና ቁመና በመፍታት የነፃነት፣የፍትህ፣ የሰላም፣ የእኩልነት እና የጋራ እድገት የሚረጋገጥባትና የሚከበርባት አገርን እና የሰማያዊውና የምድራዊው ህይወት በአንፃራዊነት የሚሰምሩበት ሃይማኖታዊ ተቋም እውን ለማድረግ እስካልተቻለን ድረስ የገዛ ራሳችንን እጅግ አስቀያሚና አሳፋሪ ወድቀት በፈጣሪ እያሳበብን እና ውጤት አልባ የፆም፣ የፀሎትና የምህላ አዋጅ እያወጅን የመከራውንና የውርደቱን ማንነት ይበልጥ እየተላበስነው እንቀጥላለን (መቀጠል ከተባለ) ።
የአምላክነቱ ባህሪ እንደ ተጠበቀ ሆኖ የሰው ሥጋ ለብሶ የሰው ልጀች ተስፋ ለሚያደርጉት ሰማያዊ ህይወት ዋስትናው በምድራዊ ህይወታቸው የሚሠሩት በጎ ሥራና የሚከፍሉት መስዋትነት የመሆኑን መሪር እውነት የቁም ሰቆቃንና የመስቀል ላይ ስቅላትን እስከ መቀበል ስለደረሰው ክርስቶስ እና ይህንኑ ተከትለው መከራና ስቃይ ስለተቀበሉ ሐዋርያትና ሌሎች ሰማዕታት የሚነግሩን (የሚሰብኩን) አብዛኛዎቹ የዘመናችን የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ሊቀ ሊቃውንት፣ ሰባኪያን የራሳቸውን የውድቀት አዙሪት ለምንና እንዴት ብለው ሳይጠይቁና ሳይመራምሩ እንደ እኩያን ገዥዎች እና እንደ ፋይዳ ቢስ ተቀዋሚ ቡድኖች (ድርጅቶች) የመግለጫና የአዋጃ ጋጋታ ሰለባዎች ሆነው የቀጠሉት ለምንና እንዴት ይሆን?
አሁንም ይህንን ዘመን ጠገብ ፣ ግዙፍ እና መሪር ውድቀታችን ፍፃሜ የምናበጅለት የሁሉም አይነት መሠረታዊ መብቶች የሚከበሩባት ዴሞክራሲያዊት አገር እውን ለማድረግ የየበኩላችን አስተዋፅኦ ስናደርግ ብቻ ነው።
ከሚታወቀው የፖለቲካ ችግርነት አልፎ እግዚአብሔር የሰጠን በህይወት የመኖር መብት ትርጉም ሲያጣ፣ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ለፀሎት ወጥቶ በሰላም የመመለስ ነገር ጭንቅ ሲሆን ፣ እንኳን በጨለማ በቀንም ወደ ቤተ እምነት ሂዶ አገልግሎት ለመስጠት የመቻል ጉዳይ የሞትና ወይም የሽረት ጉዳይ ሲሆን ፣ በገዳማዊነት በሰላም እየፀለዩ የመኖር ነገር ከባድ ፈተና ላይ ሲወድቅ ፣ በገዛ አገር ውስጥ በሰላም ለመንቀሳቀስ የመቻል ነገር ተረት ሲሆን፣ በአገር አቋራጭ መንገዶች ላይ በሰላም መጓዝ የሲኦል ጉዞ ሲሆን ፣ ወዘተ በፅዕኑ ሃይማኖታዊ መርህና አርበኝነት ገዥዎችን መገሰፅን እና እግዚኦታን ከተግባር ጋር እያዋሃዱ የመከረኛውን ህዝብ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ማገዝን እየሸሹ በምህላና በፆም አዋጅ ጋጋታ ሥር ራስን መደበቅ ሃጢአት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ነው?
እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!