ጎሰኛና ዘራፊ ስርዓት  ፋሽዝምና ሌባ ያመርታል!  ከኮሶ ዛፍ ላይ ኮሶ እንጂ  ወይን አይለቀምም

Abiy ahmed yሰኔ 25 ቀን 2016 ዓም(02-07-2024)

በሌሎች አገራት በእኛም አገር በኢትዮጵያ እንዳዬነው ስርዓት የህብረተሰብን አመለካከት ይቀርጻል።ተከተል መሪህን የሚባለው አባባልም የዚያ ማረጋገጫ ነው።እንዳለመታደል ሆኖ በዓለማችን በኢትዮጵያም ጭምር ከሰፈኑት ስርዓቶችና ሥልጣን ላይ ከተቀመጡት መሪዎች ውስጥ ለሕዝቡና ለአገራቸው መልካም  ሠርተው በመልካም የሚነሱ መሪዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው።አብዛኞቹ ሥልጣን ላይ የሚወጡት በጉልበት ሲሆን  ቅድሚያ የሚሰጡትም ለሥልጣናቸው ነው። በሥልጣናቸው ከመጣ ሕዝብ አይሉ አገር ገደል ቢገባ ደንታ የላቸውም።ታዲያ ከነዚህ አይነቶቹ መልካም አስተዳደር መጠበቅ ጅልነት ይሆናል።

እንደ ነገሩ ቢሆንማ መንግሥትና መሪ የሚያስፈልገውና የሚጠበቅበት ከራሱ ሥልጣን በላይ ለአገሩና ለሕዝቡ ሲያስብ፣የቀናና የሃቅ ምልክትና ምሳሌ መሆን ነው።ወንጀል እንዳይከሰት ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ብቃት ሲኖረው ነው።ድህነትንና ልዩነትን በማጥፋት እኩልነት፣አንድነትና  ሰላም እንዲሰፍን ሲተጋ ነው።የአገር ዳር ድንበር እንዳይደፈር ደፍሮ የመጣ ወራሪ ጠላትን መከላከል ብቻም ሳይሆን ድል ሲያደርግ ነው።የዚህ አይነቱ መሪ የኢትዮጵያ  ሕዝብ የሚናፍቀው ከሆነ ብዙ ዓመት አለፈው።በተለይም ላለፉት 50 ዓመታት የሰፈኑት አገዛዞች ይህንን መንግሥታዊ ቁመና ንደው አገርና ሕዝብ ትርምስ ውስጥ ብሎም ለመበታተን  አደጋ አጋልጠውታል።

መንግሥት የአንድ ሰው  ወይም በአንድ ጎሳ ወይም እምነት ላይ መሠረቱን የጣለ ቡድን ንብረት ከሆነ የፈላጭ ቆራች አገዛዝ ከመሆኑም በላይ ከቡድኑ አስተሳሰብ፣እምነትና ማንነት የተለዬውን ሁሉ  ከማጥፋት አይመለስም።ነጋ ጠባ ሲቆም ሲቀመጥ ሲተኛ ጭምር የሚያስበውና የሚያሰላስለው ሌላውን እንዴት እንደሚያንበረክክ፣ እንደሚያጠፋና የያዘውን አገዛዝ እንደሚያስቀጥል ብቻ ነው።ይህ አቋሙ ወደ ለዬለት ጭፍጨፋ ያመራና ፋሽስታዊ(የፋሽዝም) ስርዓትን ያሰፍናል።በሱ አስተሳሰብ የበከለውንና  የመለመለውን ደካማ የማህበረሰብ ክፍል የድርጊቱ ፈጻሚ  አድርጎ ይጠቀምበታል።ጎሰኛ አገዛዝ ፋሽዝምን ይወልዳል የሚባለውም ለዚያ ነው።

የስልጣን ሌላው ተመክኖ በሌቦች መዳፍ ላይ ከወደቀና  በዘረፋ ላይ መሰረቱን ከጣለ መንግሥት የተባለው ተቋም ሌቦች የሚጠቀጠቁበት ኩባንያ ይሆንና ያገር ሃብት ይመዘበራል፣ ሕዝቡንም በዚህ እርኩስ ተግባር ይበክለዋል።ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ በሚለው እኩይ ተግባር ያጠምቀዋል።ውድድሩ ሁሉ ማን ምን ያህል ዘረፈ የሚል እንጂ ማን ምን ያህል ሥርቶ አገኘ የሚል አይሆንም።ሠርቼ ላግኝ የሚል ቢኖርም የዘራፊዎች ኢላማ ከመሆን አያመልጥም።ሃብትና ንብረት ለመሰብሰብ አቋራጩ መንገድ ሌብነት ይሆንና የሚመሰገኑበትና የሚደነቁበት ሙያ ተደርጎ ይቆጠራል።የዘረፋው ቁንጮ የሆነው አገዛዝ በልዩ ልዩ አገልግሎት ስም የዘረፋ መንገድ ሲከፍት እሱን ተከትሎ  ሕዝቡን በቅርበት የሚዘርፈውም ወንበዴ  እንዲሁ ልዩልዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ የፈረደበትን ሕዝብ ያራቁተዋል። ይህም ዘራፊ ሥርዓት ሌቦችን ይፈለፍላል የሚለውን የመግቢያ እርእስ የሚገልጽና የሚያሳይ ነው።

አገዛዙ በተለያዩ ጊዜያት በልማትና በግብር  ስም የተለያዩ መመሪያዎችንና ደንቦችን እያወጣ  ሕዝቡን ሲመዘብር  የሰፈርና የመንገድ ሌባውም እንዲሁ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የዘረፋ ዘዴውን ይቀርጻል።በሁለት ወሮበሎች አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ሕዝብ አነሰ ሲሉ ተቀነሰ ወይም በእንቅርት ላይ ጆሮደግፍ ሆኖበት አቤት የሚልበት ቦታ ጠፍቶት አቤት ቢልም አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ ሆኖበት ሁሉንም ያጣ ለመሆን ተገዷል።በጫካ የሚርመሰመሰው  የስርዓቱ አካል የሆነው ባንዲት አሸባሪ  ቡድን የሚፈጽመውን ወንጀል ሁሉንም ለመጥቀስ ጊዜ ስለማይበቃ ብሎም የታወቀ ስለሆነ መግለጹ ለቀባሪው አረዱት ይሆንብኛል።በቂ  በቃልና በሰነድ የተደገፉ  የታሪክ ማስረጃዎች  ስላሉ ከማንሳት ተቆጥቤአለሁ።ሕዝባዊ ሥርዓት ሲሰፍን ዶሴው ተከፍቶ ሁሉም የሥራውን ያገኛል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ።

አገር አጥፊው የጎሰኞች አገዛዝ በሕግ ስም ባረቀቀው መመሪያ ቤት እያፈረሰ፣ ንብረት እዬዘረፈ  በማንነቱ እዬገደለና እያፈናቀለ ሲሄድ በከተማ ያለው የስርዓቱ ምርት የሆነው ሌባ በአደንዛዥ ስልቶች ተጠቅሞ የፈረደበትን ሕዝብ አግቶ መዝረፍና መግደሉን ቀጥሎበታል።ከሚሰሙት ዘዴዎችም ውስጥ ወደ ሥራው ወይም ወደ ቤተክርስቲያን /መስጊድ የሚሄደውን ዜጋ ቀርበው የማደንዘዣ ስልት ተጠቅመው ወደሚፈልጉት ቦታ ወስደው ደጎች ከሆኑ ንብረቱን  ከጣት ቀለበት ጀምሮ የወርቅ ጥርስ ካለውም አውልቀው መለመላውን ጥለውት ይሄዳሉ፤ከጨከኑም ይገሉታል።በሌላውም አሮጊቶችን በመላክ ሊዘርፉ ያሰቡትን መንገደኛ በሚያማልል መልኩ ምክንያቱም በአሮጊት የሚጨክን እንደሌለ ስለሚያውቁ ደብዳቤ አንብብልኝ ወይም ጻፍልኝ በሚል ልመና አዘናግተው ጭርንቁስ ሠፈር ውስጥ ወስደው ለሚጠብቁት ዘራፊዎች ያስረክቡታል።ያ የተራበ አውሮ ይመስል ለመዝረፍ ቆምጦ ይጠብቅ የነበረ የሰው አውሬ ለመርዳት አስቦ ከወጥመዳቸው የገባውን ቀና ሰው ተባብረው የሚፈልጉትን ወንጀል ይፈጽሙበታል።ተከተል መሪህን ማለትም እንዲህ ባለው መልኩ ይገለጻል።

የዘረፋው ሰንሰለት ከቤተመንግሥት እስከቤተ መቅደስ/መጅሊስ ድረስ በተዘረጋበት አገር በሰላም ውሎ መግባት የማይታሰብ ከመሆኑም በላይ ሰው ለሰው እንዳይተማመን፣እንዲፈራራና እንዲጠራጠር አድርጎታል።ይህ አይነቱ ከንቱ ምግባር በውጭ አገርም በተሰደደውና በሚኖረው ኢትዮጵያዊ በጥቂቶቹ  በኩል ሲንጸባረቅ ይታያል።ከሥርዓቱ ጋር ትስስር ያላቸው እራስ ወዳዶች ተሸክመው የሚንቀሳቀሱበት ቫይረስ ሆኗል። ለቁራሽ መሬትና ቤት ወይም ገንዘብ ሲሉ ወይም በጎሳ ማንነታቸው ወይም ከስርዓቱ መሪዎች ሃይማኖት ጋር የሚመሳሰል በተለይም የፕሮቴስታንት  ሃይማኖት ተከታይ ስለሆኑ(አንዳንዶቹን አይጨምርም)  ካለው ሥርዓት ጋር ወግነው የሚበጠብጡ ደካሞችና ሆድ አደሮች ከአገዛዙ ወኪል ከሆነው ኤምባሲ  በሚሰጣቸው መመሪያ ሲያወናብዱ ይታያሉ።ተለጣፊ ማህበርም በማቋቋም ለመከፋፈል ጥረት እያደረጉ ነው።

ያ በአንድ አገር ልጅነት ይተማመን ፣ለሚዋዋለው ውል ቃል ብቻ ይበቃል  ፊርማና ወረቀት አልሻም የሚል፣ በቤተሰብ ቀርቶ በጎረቤትና በከባቢ በብዙ የጋራ እሴት፣በእድር፣በዕቁብና  በማህበር ተሳስሮ ይኖር የነበር ማህበረሰብ አሁን ሁሉንም ያጣ ፣የመኖር ተስፋው የጨለመበት ፣ለመደማመጥ የማይችል፣ወኔው የፈሰሰና ተስፋ ቢስ ከሆነበት እንግዳ ዓለም ውስጥ ገብቶ ይገኛል።

በቅርቡ በኬንያ የታዬው አንድ ሳምንት ባልሞላው ዝግጅት የተካሄደው ሕዝባዊ እምቢተኝነት  በዳቦ ዋጋ ላይ የመጨመር ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን በፓርላማ እንዲጸድቅ  በታቀደ የመንግሥት አዋጅ ላይ  በመነሳት መንግሥቱን እንዳንበረከከና የታቀደው የሕግ እረቂቅ እንደተነሳ መሪውም ሕዝቡን ይቅርታ እንደጠዬቀ  አይተናል።የሌሎቹም አገር ሕዝብ እንዲሁ አድርጓል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ጭቆና፣ መገደል፣ መዘረፍ፣ መፈናቀል ብሎም አገር ለማጣት እዬተንደረደረ ለ50 ዓመት ያህል የመከራ ናዳ ሲወርድበት የተስማማው በሚመስል መልኩ  ከዳር ቆሞ ተመልካች ሆኗል።ለግፈኛ አገዛዝ መሪዎች እያጨበጨበ ከአንገት ይሁን ከአንጀት ግራ በሚያጋባ ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ውስጥ ተዘፍቆ የግፈኞችን ሥርዓት ከጫንቃው ላይ አውርዶ ለመጣል አልደፈረም፤የደፈሩትንም ይፈርጃል።

ከዚህ ቀውስና የጥፋት መንገድ ለማውጣት ጥቂቶች መስዋእትነት ከፍለዋል ፤እዬከፈሉም ነው።ሌላው አሳልፎ እዬሰጠ የነገው ተረኛ መሆኑን ዘንግቶት ተቀምጧል። በተቃዋሚውም ጎራ ውስጥ አንድነት ጠፍቶ የዓላማ ልዩነት ሳይኖረው በግለኝነት(Egotistical)ስሜት፣ በጎጥና በቡድን ህሳቤ ተጠምዶና ተከፋፍሎ  ለጠላት መሳሪያ ሆኗል።በተያዘው መንገድ መቀጠል ማለት ሕዝብ ተስፋውን እንዲቆርጥና ከትግል ሜዳ እንዲሸሽ ያደርገዋል። እራስንም ትውልድንም ለማያከትም ቀውስ መዳረግ  ብቻም ሳይሆን አገር አልባ ማድረግ ማለት ነው።የሰውን ልጅ  ከእንስሳት የሚለዬው ሰው ሆኖ እንደሰው የሚያስብ መሆኑ ነው።በሁለት እግሩ መንቀሳቀሱ ብቻ አይደለም።በሁለት እግሯ ከምትንቀሳቀሰውና ከምትታረደው ዶሮ የሚለዬው ግፍና በደልን፣ ኢሰብአዊነትን ሲጠዬፍና ሲያሶግድ ብቻ ነው።ለዚያ ካልበቃ ትልቅ ዶሮ መሆን ነው። ያለውን የጎሰኞችና ፣የዘራፊዎች ሥርዓት መንቅሎ ለመጣልና አገር እንዳገር፣ሕዝብም እንደ ሕዝብ በሰላም ፣በአንድነትና በእኩልነት ለመኖር በሚያስችለው ትግል ውስጥ መሳተፍ ሙሉ ሰው ያደርጋል።

የጎሰኞች ሥርዓት ያፈራው የፋሽስቶችና የዘራፊዎች ሰንሰለት ይበጠስ!

ኢትዮጵያና ሕዝቧ በነጻነትና በአንድነት፣በሰላምና በእኩልነት ለዘላለም ይኑሩ!!

አገሬ አዲስ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

191671
Previous Story

የጄኔራል ተፈራ ማሞ ፋኖን መቀላቀል እና የብልፅግና ድንጋጤ | በደቡብ ጎንደር ሚሊሻዎች ተደመሰሱ

191693
Next Story

አንድ ወጥ የፋኖ ዕዝ ተመሰረተ | ጀኔራሉ ከመግባታቸው የምስራች ተሰማ ባህርዳር በ4 አቅጣጫ ድል ጎንደር ታሪክ ተሰራ

Go toTop