እናትዋ ጎንደር እና አደይ ትግራይ፡- ለኢትዮጵያ ነጻነትና አንድነት!! – በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

‹‹እግዚኦ ቦኡ አሕዛብ ውስተ ርስትከ ወአርኮሱ ጽርሐ መቅደስከ ወርሰይዎ ለጎንደር ከመልገተ ዓቃቤ ቀምሕ››

(ደርቡሾች ጎንደርን ወረው ሕዝቡን በጨፈጨፉና አብያተክርስቲያናትን ባቃጠሉ ጊዜ የጎንደር ሊቃውንት ለትግራዩ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ከላኩት ደብዳቤ የተወሰደ)

ከሰሞኑን የፋኖ ታጣቂዎች በእስር ላይ የነበሩ የትግራይ ክልል ታጋዮችን ከእስር ቤት አስለቅቀው በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ መደረጋቸውን የሚዘግቡ ዜናዎችን ሰምተናል፡፡ ይህ ዜና የሁለቱን ሕዝቦች ጥብቅ የሆነ የታሪክ ትስስር፣ የሃይማኖትና የባህል መዋረስና እንዲሁም የአማራና የትግራይ ሕዝብ፤ ከጉራዕ እስከ ጉንደት፣ ከመቅደላ እስከ መተማ፣ ከአምባላጌ እስከ ዐድዋና ማይጨው… ወዘተ. ድረስ በደማቸውና በአጥንታቸው ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት የከፈሉትን መሥዋዕትነት የሚያውቁ ኢትዮጵያውያንን አስደስቷል፡፡

ታሪክ እንደሚነግረን፤ የዛሬን አያድርገውና የቀደሙ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት የፍቅርና የአንድነት ድርና ማግ ላይለያዩ በጥብቅ የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ የትግራይና የአማራ ሕዝብም በታሪኩ- በደጉም በክፉም ጊዜ ይህን የታሪክ ክብርና ኩራት የተካፈለ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ በውስጥ ጉዳያቸው አለመስማማትና ልዩነት ቢኖራቸውም እንኳ በኢትዮጵያ ነጻነት፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ መቼም ቢሆን ቃላቸው አንድ ነበር፡፡

ኢትዮጵያን እኛ በሕይወት ቆመን እያልን እንዴት ባዕዳን በግፍ ይወሯታል፤ ኢትዮጵያ ወይም ሞት፣ ነጻነት ወይም ሞት!! በሚል ጽኑ የቃል ኪዳን ውል በደማቸውና በአጥንታቸው የቆመች፣ ነጻይቷን ኢትዮጵያን አውርሰውናል፡፡ ይህን እውነታ የተገነዘቡት የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት ሲሳይ መንግሥቴ (ዶ/ር) ከጥቂት ሳምንት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ፤ ‹‹የአማራና የትግራይ ሕዝቦችን ግንኙነት ለማሻሻል የሚያስችል የመነሻ ሐሳብ›› በሚል አርእስት ባስነበቡት ጽሑፋቸው፤

የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ትስስር ከጥንት ጀምሮ እየጠበቀና ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየተወሳሰበ በመሄድ አገር በጋራ ከመመሥረትና ከመገንባት አልፎ ከቅርበታቸው የተነሳ ባህላዊ፣ … ምንም እንኳ አገር በመመሥረትም ሆነ መንግሥትን በማቋቋም ረገድ በሁለቱም ሕዝቦች የፖለቲካ ልሂቃን መካከል የተቀናቃኝነትና የተፎካካሪነት ሁኔታ የነበረና አሁንም ድረስ ያለ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ግን አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ እንደነበረም አይዘነጋም፡፡

የአገርን ዳር ድንበር ከወራሪ ኃይሎች በመከላከል ረገድም ይሁን የሕዝቦችን ነፃነት አስከብሮ ለማቆየት በተደረገ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ፣ የሁለቱም ሕዝቦችና ልሂቃን አሻራ ከፍተኛ መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ ከዚያም አልፎ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመልካም ጉርብትና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ማኅበራዊ ግንኙነት ፈጥረው አብረው የኖሩና አብረው የሠሩ ሕዝቦች መሆናቸው ሲታሰብም፣ በአማራና በትግራይ ሕዝቦች መካከል የሻከረ ግንኙነት ይፈጠራል ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ለምን ቢባል ሁለቱም ሕዝቦች በጋብቻ ተሳስረው ተዋልደው በቀላሉ ላይለያዩ ተዛምደዋል፡፡ ሲሉ ያወሳሉ፡፡

በርግጥም እነዚህ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነጻነት ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በጀግንነት የተዋደቁ ሕዝቦች በመካከላቸው ጠላትነትና መለያየት እንዲኖር የሚማስኑ መስሪዎችንና ከፋፋዮችን ማስቆም የሚቻለው የትናንትናውን የአብሮነት ታላቅ ታሪካቸውን በመዘከር፣ በመንገርና በማስተማር ነው፡፡ እስቲ ወጌን ፈር ለማስያዝ ያህልና ሐሳቤንም ያጠናክርልኝ ዘንድ ከሰፊው ታሪካችን አንድ ሰበዝ ልምዘዝ፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለምን ከምንወዳት አገራችን እንሰደዳለን? ክፍል 1 (በይበልጣል ጋሹ)

ጣሊያኖች በኢትዮጵያውያን ላይ ያላቸውን የበላይነት በመተማመን እንደሚሳካላቸው አምነው ነበር ‘ክተት ሰራዊት፤ ምታ ነጋሪት!’ ብለው ከሮማ ገሥግሠው ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጡት፡፡ ጣሊያኖች ይህን ሕልማቸውን ዕውን ለማድረግም ሲሉ በጥር 1885 ዓ.ም. መረብን ተሻገሩ፡፡ ራስ መንገሻን በቆአጢት ለመክበብ ቢፈልጉም ራሱ ሳይያዙ ወደ ደቡብ ሸሹ፡፡ ራስ መንገሻ ከደብረ ኃይላት እንደሸሹ ዜና የሚሆን ፉከራ ፎከሩ፡፡ እንዲህ ሲሉ… ቃሉም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ እንደ እሳት ተዛመተ፤

‘‘እሪ በሉ ለጎንደር ንገሩ፣

እሪ በሉ ለሸዋ ንገሩ፣

እሪ በሉ ለወሎ ንገሩ፣

እሪ በሉ ለጎጃም ንገሩ፣

መንገሻ ለቀቀ ተከፈተ በሩ፡፡’’

ሰሜን ኢትዮጵያ ሀገራችንን በተለያየ ጊዜ በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል ላሰቡና ለሞከሩ የውጪ ሀገራት ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች ሁሉ መግቢያ በር ነበር፤ ነውም፡፡ ግብጽ፣ ቱርክ፣ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የመውረርና የመቆጣጠር ሕልማቸው የተቀበረው ከሀገራችን የተለያዩ ግዛቶች በመጡ እምቢ ለነጻነቴ! እምቢ ለሀገሬ! ባሉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አባትና እናት አርበኞች ነበር፡፡ ጉንደት፣ ጉራዕ፣ ዶጋሊ፣ መተማ፣ አምባላጌ፣ መቀሌ፣ ማይጨው፣ ዐድዋ… የኢትዮጵያውያን የእምቢ ለነጻነቴ ተጋድሎ ፣ የነጻነት ችቦ ለዓለም ሁሉ ከፍ ብሎ የበራባቸው በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ደምና አጥንት የተዋቡ የነጻነታችን ዓርማና ኩራት ናቸው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም፤ የአማራንና የትግራይ ሕዝቦችን ለዘመናት የዘለቀና በኢትዮጵያዊነት ድርና ማግ የተጋመደ  አንድነታቸውን የሚመሰክር ሌላ የታሪክ እውነታ ልጥቀስ፤

ደርቡሾች ጎንደርን ወረው ሕዝቡን በፈጁት፣ ከተማውን በዘረፉትና በአብያተክርስቲያናትን በቃጠሉ ጊዜ የጎንደር ሊቃውንት በመግቢያ ላይ የጠቀስኩትን የሚከተለውን ድብዳቤ ጽፈው ለዐፄ ዮሐንስ ልከውላቸው ነበር፤

‹‹እግዚኦ ቦኡ አሕዛብ ውስተ ርስትከ ወአርኮሱ ጽርሐ መቅደስከ ወርሰይዎ ለጎንደር ከመልገተ ዓቃቤ ቀምሕ›› (‹‹አቤቱ ንጉሥ ሆይ፡- አረማውያን በምድርህን ወረሩ፣ ቤተ መቅደስህንም አረከሱ፣ ጎንደርንም አፈራረሷት፡፡››)

ይህ የጎንደር ሕዝብና ሊቃውንት የድረሱልን ጦማር/ደብዳቤ የደረሳቸው ዐፄ ዮሐንስ ዛሬ ነገ ሳይሉ ነበር ወደ ጎንደር የዘመቱት፡፡ ንጉሡ ከደርቡሾች ጋር በነበረው ውጊያም እንደ ተራ ወታደር በመካከል ገብተው ሲዋጉና ሲያዋጉ በመተማ ግንባር ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር ሲሉ ሕይወታቸውን የሠዉት፡፡ ዐፄ ዮሐንስ የጎንደር ሊቃውንት የይድረሱልን ጥሪ ሲደርሳቸው ይህ የጎንደር/የአማራ ሕዝብ ጉዳይ እንጂ የትግራይ ወይም የእኔ ጉዳይ ነው አላሉም እናም ከትግራይ ድረስ ገሥግሠው መጥተው ነው መተማ ላይ አንገታቸው የሰጡት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አስከፊው የአድርባይነት ደዌ እና ውጤቱ - ጠገናው ጎሹ

ዐፄ ዮሐንስ የግብጽንና ጣሊያንን ወረራ ኃይል ለመመከት ባወጡት ዐዋጅ ልሰናበት፤

ሀገሬ ሆይ ስማ…! መኳንንቶች፣ ወታደሮች፣ ሕዝቦቼ ስሙ፡፡ በመጋቢት 25 ቀን በምፅዋ መንገድ አቅንተህ ለጦርነት እንድትገሰግስ የኢትዮጵያ መንግሥት በጽኑ ያዝሃል፡፡ ወደፊት ገስግስ እንጂ ወደኋላ አትቅር፡፡ የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ ልብ አድረገህ ተመልከት ኢትዮጵያ የተባለች፡-

አንደኛ እናትህ፣

ሁለተኛ ዘውድህ ናት፣

ሦስተኛ ሚስትህ ናት፣

አራተኛ ልጅህ ናት፣

አምስተኛ መቃብርህ ናት!!

እንግዲህ የእናትን ፍቅር፣ የዘውድን ክብር፣ የሚስትን ደግነት፣ የልጅን ደስታ፣ የመቃብርን ከባቲነት እንደዚህ መሆኑን አውቀህ ነገ ከነገ ወዲያ ሳትል ተነሳ፡፡

 

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

 

5 Comments

  1. ደፍተራ እባክህን ሃምሳ አመት ሙሉ ተደስኩሮ ፍሬ ያላፈራ ነገር እንደ ሰነፍ ተማሪ ሌሎች ያሉትን አትድገም፡፡ ወንድ ተሆንክ እንደነ አቡነ ሚካኤልና ጴጥሮስ የካህን ፋኖ ሁን፡፡ አመስግናለሁ፡፡

  2. እያሸነፉ መምበርከክ አለ ትግሬ ለኢትዮጵያ አንድነት ምን አደረገ እስከዛሬ ድረስ ከውጭ ሀይሎች ጋር ሁኖ ሲወጋን ሲያስወጋን ነው የኖረው። የውጭ ጠላት ከዘገየ አዘናግቶ ገብቶ ህዝብን ወደ መከራ ድህነት ሰቆቃ መክተት ነው ይህ ነው የትግሬ ልዩ መገለጫው። አጼ ዮሀንስ በአማራና በአማራ እስላሞች ያደረሱትን ማስታወስ ያስፈልጋል ስሁል ሚካኤል መለሰ ዘራዊም የዚያ ተቀጽላዎች ናቸው ንጉሱ ልጃቸውን ቢያጋቧቸው አርደው ላኩላቸው እንደው ተትግሬን ጉዳይ እንኳን ተውን።

  3. የፈረንሳዪ የቀድሞ ዘመን ንጉስ Napoleon Bonaparte ስለ ፓለቲካ እንዲህ ብሎ ነበር። “In politics stupidity is not a handicap”. የሚገርም ነው አሁን ማን ይሙት ወያኔና የአማራ ህዝብ በምን አይነት የሂሳብ ስሌት ነው አንድ ግንባር የሚፈጥሩት? ግን ያው የሃበሻ የውሻ ፓለቲካ ጊዜ እየጠበቁ መነካከስ በመሆኑ የኤርትራው ሻቢያ የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በማለት ከብልጽግናው መንግስት ጋር አብሮ ትግራይን እንዳተራመሰው ሁሉ ይህ አሁን ተጀመረ የሚባለው የፋኖና የወያኔ ፍቅርም የተኩላ ለምድ ለብሶ በበጎች መካከል ለመሆን እንጂ ከዚህ ግባ የሚባል አንድነትን አያመጣም። የአማራን ህዝብ መከራ ጣራ ላይ ያወጣው ማን ሆነና? ተረቱ የወደቀን አንሳ፤ የሞተን አትርሳ ቢለንም እኛ ሁሉንም ዘንግተናል። ወያኔ በ 27 ዓመት የስልጣን ዘመኑ ያጠፋቸው ወገኖች በጣሊያን ዘመን ጀግኖች የነበሩ የቅርብና የሩቅ ቤተሰቦችን ጭምር ነው። ከአንድ ቤት ወንድም፤ እህት፤ እናትና አባት ሳይቀር ተገለዋል። ወያኔ ህብረት ያለው ከሳጥናኤል ጋር እንጂ ከሰው ልጆች ጋር አይደለም። ከሰው ጋር ቢሆንማ በከንቱ ወደ ሚሊዪን የሚጠጉ የትግራይ ልጆችን አስጨርሶና የአማራንና የአፋርን ህዝብ ለረሃብና ለመከራ አጋልጦ ዛሬ መቀሌ ላይ ባልተደበቀም ነበር። ስንቶች ናቸው እስከ ዛሬ ድረስ በስወርና በይፋ በወያኔ እስርቤቶች እየተሰቃዪ የሚገኙት? ይህን ያውቃሉ? ግራም ነፈሰ ቀኝ ጠበንጃ በሚመለክበት ሃገር ላይ አብረን እንረስ የሚል እንጂ እንግደልና እንገዳደል የሚል ጠፍቶ አያውቅም። ዘፈኑ፤ ቀረርቶው፤ አልፎ ተርፎም ተረትና ምሳሌው ያዙኝ ልቀቁኝ ለሚል ምቹ ነው። ይህም በመሆኑ ይኸው እልፍ ዘመን በመገዳደል ላይ እንገኛለን።
    ወሬን እየመነዘሩ በእኛ ላይ የሚነግድትን ሳይሆን የዓለምን የፓለቲካ አቲካራና አሰላለፍ ልብ ማለት ይጠይቃል። ፍልስጤሞች ተራቡ አለቁ ይሉና ይህ ግን ሙሉ እውነትነት የለውም። የተራበ ያለው በቻድ (የሱዳን ስደተኞች)፤ በሱዳን፤ በኢትዮጵያና በሌሎችም ሃገሮችን ነው። ግን የጥቁር ህዝብም መከራ ማን ዞር ብሎ ያየዋል? ማንም። አሁን ማን ይሙት ጋዛ ያለው መከራ በሱዳን ከደረሰውና ከሚደርሰው ይበልጣል? ግን እውነት ሞታለች። እኛም ደንዝዘናል። በቅርብ ከአረመኔው የኦነግ ሸኔ ሰራዊት እጇን ሰጠች ተብላ በፋና ቴሌቪዥን ቃለ መጠየቅ የተደረገላት ሴት ስትናገር “አማራን ገድለና፤ ኦሮሞን ገድለናል፤ እኛም እርስ በእርሳችን ተጋለናል”. የብሄርተኞች የነጻነት ፍልሚያ ራሱን የሚበላ ጭራቅ ነው። ስለዚህ እናትዋ ጎንደር አደይ ትግራይ አትበሉን። ወያኔ እያለ በምንም ሂሳብ የአማራና የትግራይ ህዝብ በሰላም አይኖርም። ፍትህ በሌለበት ምድር ሰላም አይኖርም። አሁን ኢትዮጵያና ኤርትራን በወደብ ሂሳብ ሊያጋጩ የሚጥሩ ሁሉ ቁጥራችን እንዲቀንስ የሚፈልጉ ለ 80 ዓመት ከአውራ ጣት አመልካች እጣት ትበልጣለች እያሉ ያጋደሉን የውጭና የውስጥ ተላላኪዎች ናቸው። ሞት ለሞት ፈላጊዎች ይሁን። በእኔ እይታ የሃበሻዋ ምድር ልትመለስበት ወደማትችልበት ማጥ ውስጥ ገብታለች። ለዚያ ይሆን ከዘመናት በፊት አንድ ገጣሚ እንዲህ ያለን።
    የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ
    ተቃጥሏል መሰለኝ ሸተተኝ ሃገሬ።
    ሁልጊዜ ሞት፤ ሁልጊዜ ረሃብና ጦርነት መቼ ነው የሚያቆመው? መቼ ነው ሰው በሰውነቱ የሚከበረው? መቼ ነው መሰደድና መታሰር፤ መገደል በዘርና በጎሳ መፈረጅ የሚቀረው? ወያኔና ብልጽግና የአንድ ሳንቲም አንድ ገጽታዎች ናቸው። ሳንቲሙ ላይ ስፍራ ጠፍቶ እንጂ ሻቢያም የክፋቱ ሁሉ ቁንጮ ነው። ፍትህ ለህዝባችን። ከመናጆ ፓለቲካ ራሳችሁን ጠብቁ!

    • “ወያኔ እያለ በምንም ሂሳብ የአማራና የትግራይ ህዝብ በሰላም አይኖርም።”
      ከላይ ካሰፈርከው የወሰድኩት ነው። ቁም ነገሩ በ “የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር” ነኝ ባይና በትግሬዎች መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ ላይ ነው። ዐማራ ሆኖ ከወያኔ፤ ማለትም ከ”የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር” ነኝ ባይ ጋር ምንም ዓይነት ኝኙነት ለማድረግ ከሚሰብክና ከሚፈልግ መጥዕንቀቅ ተገቢ ነው። ጸሐፊው በጎንደር ሕዝብና በትግራይ ሕዝብ መካከል ለማለት ይመስለኛል የፈለገው

      • እውነትም እስክ መቼ! እስከ መቼ ነው የትግሬ ሕዝብና ህዋት አንድ መሆኑ የማይገባህ? እስቲ ህዋት ያለነበረ፣ ህዋት ያልሆነ ወይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የማይደግፍ ሃምሳ ትግሬ ጥራ?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share