የሽግግር መንግሥት፣ ምንነት፣ አስፈላጊነት እና ለስኬቱ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች  (ለወይይት መነሻ)

December 14, 2023

ባይሳ ዋቅወያ
*****
መግቢያ
በአገራችን እየተከሰተ ያለውን ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ቀውስን፣ ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት መፍትሔ ሊያገኝለት ባለመቻሉ ወይም ለማግኘት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ እሱን ተክቶ በአገራችን ሰላምና መረጋጋትን ብሎም አገሪቷን ከጥፋት ለማዳን የሚችል የሽግግር መንግሥት መቋቋም አለበት ብለው ዶ/ር አማረ ተግባሩና አቶ (?) ገለታው ዘለቀ ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ በቅርቡ ሁለት ጽሁፍ አቅርበውልን ነበር። ያው እንደ ተለመደው፣ በተቃዋሚዎች የሚዲያ መስኮቶች ያለ አንዳች መታከት ብቅ እያሉ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና መከፋፈልን ብሎም የእርስ በርስ ጦርነትን ለመቀስቀስ የማይሰንፈው የምሑር መኃይማን፣ የፖሊቲከኛና የአክቲቪስቶች ስብስብ፣ ዶ/ር አማረና አቶ ገለታው ባቀረቡት ሃሳብ ላይ አስተያየት ከመሰንዘር ተቆጥቧል። በኔ ግምት አገራችንን ለአደጋ የዳረጋትና እየዳረጋት ያለው፣ የኢትዮጵያ ምሑራን ዝምታና ታሪካዊ ቦታቸውንም ለጽንፈኛና መኃይም ፖሊቲከኞችና አክቲቪስቶች አሳልፈው ማስረከባቸው ይመስለኛል። የምሑራን ዝምታ በአንድ አገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በደንብ ለመረዳት ደግሞ፣ ምዕራብ አገራት የኢራን ምሑራንን ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ለመግታት ከማለት የኃይማኖት መሪውን አያቶላ ክሖሜኒን ከውጭ አገር አምጥተው ለሥልጣን ሲያበቁት፣ ምሑራኑ ያሳዩት የሚሰቀጥጥ ዝምታ ዛሬ ምንኛ አብዛኛውን ሕዝቦቿን እንደጎዳ እንዳለ ማየቱ በቂ ነው። ዛሬ ምሑሮቻችንም ብኩርናቸውን በመሸጣቸው፣ የፖሊቲካ መኃይማን መድረኩን ተቆጣጥረው ምሑሩን ራሱን መመርያ እየሠጡት ሲያስተዳድሩትና በመኃይምነታቸው ልክ አገሪቷን ወደ ገደል ሲገፏት በዝምታ እያየን ነው።

 

የሽግግር መንግሥት ለአገራችን ያስፈልጋታል ወይ? ከሆነስ በምን መልክ ይቋቋማል? ለማቋቋምስ የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ ወይ? ምን ዓይነት ቅድመ ሁኔታዎችስ ያሰፈልጋሉ? የሚሉ ተገቢ ጥያቄዎችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ዶ/ር አማረና ገለታው አንስተውታል። አዎ! አገራችን ታምማለች። ለበሽታዋ የሚስማማ መድኃኒት ካልተገኘ ደግሞ፣ መሞቷ አይቀሬ ይሆናል። ስለዚህ መታመሟ የሚያሳስበን ዜጎች ዝምታውን ሰብረን ለበሽታዋ ፍቱን የሆነን መድኃኒት በጋራ ፈልገን እንድናገኝ በቅንነት መወያየትና መስማማት አለብን። ሌላ ምርጫ የለንም! ጉዳዩ ደግሞ ለነገ የማይታደር ነው። በዚህ ውይይት መጨረሻ ላይ፣ የሽግግር መንግሥት መቋቋም ለበሽታዋ ፍቱን መድኃኒት ነው ብለን ካመንንበት ደግሞ፣ ለዚህ ፍቱን መፍኃኒት መቀመሚያ ይረዳን ዘንድ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ከሁሉም አቅጣጫ መመርመር አስፈላጊ ይመስለኛል። ለአንድ በሽተኛ የሚስማማ መድኃኒት ከመቀመም በፊት የበሽታውን ዓይነት በትክክል ማወቅ ያስፈልጋል ለማለት ነው። ሰፋ አድርጎ ከታየም፣ የበሽታው ዓይነት ብቻ ሳይሆን የበሽታውንም መንስዔ ማወቁ ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል። የበሽታውን ምንጭና የበሽታውን ዓይነት ለይተን ሳናውቅ ዝም ብለን ለታመመችዋ አገራችን አንዳች ዓይነት መድኃኒት ከሠጠናት ደግሞ፣ መድኃኒቱ በሽታዋንም ሊያስገረሽባት ይችላል። ስለዚህ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታና (በሽታዋን) እና ለዚህ ቀውስ የዳረጉንን ምክንያቶች (የበሽታውን መነሻ) በመጠኑም ቢሆን መዳሰስ (መወያየት) አለብን።

 

ይህን የውይይት መነሻ ጽሁፍ ለማቅረብ ያነሳሳኝ፣ የዛሬውን አገራዊ ቀውሳችንን በደንብ ተረድተው የመፍትሔ አቅጣጫ ለመቀየስ ይረዳ ዘንድ፣ በጣም ውስን ቢሆንም፣ የተለያየ አስተያየት ሲሰጡ ለነበሩና እንዲሁም ደግሞ፣ ሌሎች ጉዳዩ ለሚያገባቸውና ለሚያሳስባቸው፣ ግን ደግሞ እስካሁን ዝምታን ለመረጡ “አብላጫው ዝምተኛ” the silent majority በውይይቱ ለመሳተፍ የመስፈንጠርያ ርብራብ ይሆናቸዋል ብዬ ከማሰብ ነው። ስለሆነም፣ ለፖሊቲካ ሥልጣን ጥም መወጫ በየጽንፈኛው ሚዲያ ብቅ እያሉ ሰላምና አብሮነትን ሳይሆን ክፍፍልና ጥላቻን የሚሰብኩ ግለሰቦችና ቡድኖች በዚህ ውይይት ባይካፈሉ ደስ ይለኛል። ከተካፈሉ ደግሞ፣ የለመዱትን መልዕክቱን በቅንነት ለመረዳት ሳይሆን መልዕክተኛውን የመግደል ልምዳቸውን ወደ ጎን በመተው፣ በሠለጠነ መንገድ ሃሳብን በሃሳብ እየሞገቱ ለአገራችን ቀውስ መፍትሔ ፍለጋ በምናደርገው የጤናማ ውይይት ደንብ መገዛት እንዳለባቸው ካሁኑ እንዲገነዘቡ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

 

ወቅታዊው ያገራችን ሁኔታ

 

አገራችን፣ ምናልባትም በዘመናዊ ታሪኳ ውስጥ አስተናግዳ በማታውቀው ደረጃ መጠነ ሰፊ የሆነ ሁለንተናዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች። በቀውሱ ያልተለከፈ ክልልም ሆነ ግለ ሰብ የለም። የኑሮ ውድነቱ (ኤኮኖሚ)፣ የወንጀልና የሙስና መስፋፋት (ማኅበራዊ) እና በየክልሉ በመንግሥትና በአማጽያን መካከል ወይም የጎንዮሽ (horizontal) የእርስ በርስ ግጭት (ፖሊቲካዊ) የማያሳስበው ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት አያስደፍርም። የአገራዊ ችግሮቻችን ስፋትና ጥልቀት የትየለለ ስለሆነ በሙሉ ዘርዝሮ ለማቅረብ ጊዜም ቦታውም አይበቃም። ጥቂቶቹን በአጭሩ ለመጥቀስ ያህል ግን፣ የሕግ የበላይነት መጥፋትና የዜጎች ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት አለመከበር፣ ተነጻጻሪ የማይገኝለት የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት፣ የዜጎች የጎንዮሽ ግጭቶች መስፋፋትና ያስከተሉት መገዳደል፣ መፈናቀልና መሰደድ፣ የዔሊቱ፣ የምሁራን፣ የፖሊቲከኞችና የሚዲያው ጽንፈኝነት፣ ልዩነትን አቻችሎ አብሮ የመኖርና የመሥራት የፖሊቲካ ባሕል የማዳበር ልምድ አለመኖር የሚሉ ናቸው።

 

በያቅጣጫው የእርስ በርስ ጦርነት መከሰትትና ጦርነቱን ለማቆም መንግሥት የሚያሳየው ቸልተኝነት፣ ሚሊዮን ወጣቶች በሰሜኑ ትርጉም አልባ ጦርነት እንደ ቅጠል ረግፈው፣ እንኳን ባሕሉን የተከተለ የቀብር ሥነ ሥርዓት ይቅርና ለግማሽ ቀን እንኳ ባንዲራው ዝቅ ብሎ እንዲውለውበለብ ወይም ሐገር ዓቀፍ የኃዘን ቀን የማይታወጅበት የታሪክ ወቅት ውስጥ ነው ያለነው። በየተራ በሚያስተናግዳቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች ወቅት ስለሚካሄደው መጠን የለሽ ግድያና መፈናቀል፣ ሕዝቦቻችን ደግሞ የተቃውሞ ድምጽ ይቅርና በሰላም “ጦርነት ይቁም” ብለው እንኳ ደፍረው የማይናገሩበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው። ሁሉም በራሱ ሲመጣበት እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሆኖ፣ የኦሮሞው ሕዝብ መብት ሲጣስ የኔም መብት እንደ ተጣሰ እቆጥራለሁ ብሎ አማራው የማይነሳበት፣ ወይም የአማራው ሕዝብ መብት ሲጣስ የኔም መብት ተጥሷል ብሎ ኦሮሞው የማይነሳበት አገር ውስጥ ነው ያለነው። ብዙ ሕዝቦች፣ አንድ አገር ብሎ ነገር ውድ ሸቀጥ የሆነበት አገር!

 

ሌላው ትልቁ ችግራችን ብሎም ምሁሩንና ፖሊቲከኞቻችን የጋራ አቋም እንዳይኖራቸው የሚያደርገው ዓቢይ ጉዳይ ደግሞ በታሪካችንም ላይ ስምምነት አለመኖሩ ነው። አዎ! አገረ-ብሔር ለመመሥረት ባልቻሉ አገራት፣ በተለይም ባለፈው ታሪካቸው የብሔሮች መብት እኩልነት ባልተከበረባቸው አገራት፣ “በጋራ ታሪክ” ላይ አለመስማማት የተለመደ ነገር ነው። ለአንደኛው ብሔር ጀግና ተብሎ የሚወደስ ግለሰብ ለሌላው እንደ ጨፍጫፊ ገዳይ ይታያል። ለአንዱ የአገሪቷ ክብር መገለጫ ሆኖ የሚውለበለበው ብሔራዊ ባንዲራ ለሌላው ደግሞ የጭቆና ምልክት ሆኖ ይወገዛል። ይህ ዓይነቱ ክስተት በብዙ አገርታ የተከሰተ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ በላይ በተግባር የተተረጎመበት አገር ግን የለም ቢባል የተጋነነ አይመስለኝም። እንደኛው የብዙ ብሔሮች አገር የነበሩ አገራት ከኛ በኋላ ተነስተው አንድ አገር አንድ ሕዝብ አንድ ቋንቋ ብሎም አንድ አገረ-ብሔር መፍጠር ሲችሉ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች ግን ለዘመናት አንዳቸውም በአንዳቸው ውስጥ ሳይቀልጡ እንደ ውሃና ዘይት ጎን ለጎን ሲፈሱ የምናስተውለው ለምንድነው ብለን ጠይቀን መፍትሔ ለመፈለግ እንደ መትጋት፣ እንደው በደፈናው “ተዋድዶ ተከባብሮና ተጋብቶ አብሮ የኖረ አንድ ሕዝብ” የሚል ባዶ ተረት እየተጋትን ነው ያደግነው። እውነቱ ግን፣ አቶ አዲስ ዓለማየሁ ከ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ ስለ “ኢትዮጵያ ሕዝብ” ማንነት ለንጉሡ ባቀረቡት ሪፖርት በግልጽ ያስቀመጡት ስለሆነ እሱን ዘገባ ማንበብ ለዚህ ውይይታችን በጣም ይረዳል ብዬ እገምታለሁ።

 

ሕገ መንግሥቱን በተመለከተም እንደዚሁ በጣም የተለያዩ አስተያየቶች ይስተናገዳሉ። ሕገ መንግሥቱን የሚቃወሙና፣ ሲረቀቅ ጀምሮ ያልተካፈልኩበት ጸረ “የእኔ ብሔር” መንፈስ አለው የሚሉ ቡድኖች ያሉትን ያህል፣ “ሕገ መንግሥቱ በመታወጁ ምክንያት ለዘመናት ተነፍጎኝ የነበረው ማንነቴ ታወቀልኝ” የሚሉና ሕገ መንግሥቱ በምንም መልኩ እንኳን ሊሻር ይቅርና አንድም አንቀጽ እንኳ እንዲሻሻል አንፈልግም የሚሉ ብሔሮች ደግሞ አሉ።

 

የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት፣ መቼና እንዴት?

 

ከሰው ልጆች ተከታታይ የመንግሥታት አፈጣጠሮች ልምዶች እንደምናስተውለው ከሆነ፣ ከመንግሥታት አመሠራረት ሁሉ ዲሞክራሲያዊና ሁሉን ዓቀፍ የሆነ የሽግግር መንግሥትን እንደ ማቋቋም ከባድ ነገር የለም። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባለች ብዙ ብሔሮችን በምታስተናግድ አገር! የሽግግር መንግሥት በተለያዩ ሁኔታዎች ሊከሰት ይችላል። እስካሁን በብዙ አገሮች በተግባር የተተረጎሙት የሽግግር መንግሥታት የተፈጠሩት፣

 

ሀ) አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ሲወጡ የራሳቸውን መንግሥት አስተዳደርና ቢሮኪራሲ እስኪያዘጋጁ ድረስ፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውሳኔ ወይም ድጋፍ እና በአዲሱ አገር ፖሊቲከኞችና ምሑራን ስምምነት መሠረት፣ ሁሉን አቀፍ ምርጫ ተደርጎ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ፣ የሽግግር መንግሥት ይመሠረታል።

ለ) በውጭ አገር ወረራ ወይም በየእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የፈራረሰችን አገር፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረ ሰብ ድጋፍ ወይም በራሳቸው ተነሳሽነት፣ የደፈረሰውን ሰላምና መረጋጋት መልሶ ለማስፈን ከማለት፣ አገር በቀል ተፋላሚ ኃይላት፣ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው አንዳች ዓይነት የሽግግር መንግሥት ሊያቋቁሙ ይችላሉ።

 

ሐ) በየእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የመፍረስ አደጋ ያንዣበበባትን አገር መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ትግል ሂደት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በገዛ ፈቃዱ ሥልጣን ለማስረከብ፣ ወይም  ከተፋላሚ ኃይላት ጋር ሥልጣን ለመጋራት ሲስማማ፣ በመደበኛው ሁሉን ዓቀፍ ሕዝባዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ የሽግግር መንግሥት በሰላማዊ መንገድ ሊቋቋም ይችላል።

 

መ) በየእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የመፍረስ አደጋ ያንዣበበባትን አገር መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ትግል ሂደት ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በገዛ ፈቃዱ ሥልጣን አላስረክብም ወይም አላጋራም ሲል፣ መንግሥቱን በአብዮታዊ ዓመጽ የትግል ስልት አስወግዶ፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተደርጎ ሕዝባዊ መንግሥት እስኪቋቋም ድረስ አገሪቱን በጊዜያዊነት ለማስተዳደር ተብሎ የሽግግር መንግሥት ሊቋቋም ይችላል።

 

በኔ ግምት፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ከአራቱ ሴናሪዮዎች ውስጥ “ሀ” እና “ለ” የሚመለከቱን አይመስለኝም። ኢትዮጵያ እንደ አገር አለችና! “ሐ” እና “መ” ሴናርዮ ግን በቀጥታ ይመለከቱናል። አገሪቷ ባትፈርስም፣ ብሔራዊ ቀውሱ ከቁጥጥር ሥር መውጣቱ ለሕዝብም ለመንግሥትም ግልጽ ነውና!

 

መድረኩ ተፈጥሮ ውይይታችንን ስንጀምር፣ ለአገራችን ቀውስ መፍትሔ ለማግኘት መጠቀም ያለብንን የትግል ስልት ለመምረጥ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና በአገራችንም ባለፉት አምሳ ዓመታት የተካሄዱትን የመንግሥት አመሠራረቶችን ሂደት ወደ ኋላ ተመልሰን መገምገም ይኖርብናል። በኔ እይታ፣ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ከተደረገው ሕዝባዊ የትጥቅ ትግል ውጭ የተካሄዱት አብዮታዊ የትጥቅ ትግሎች ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ውጥረትን ለተወሰነ ግን ያስተነፍሱ እንደው እንጂ፣ ዲሞክራሲና ሕዝባዊ መንግሥትን አምጠው ወልደው አያውቁም። የትጥቅ ትግል በተፈጥሮው አውዳሚ ነው። የማንኛውም የትጥቅ ትግል ውጤት ደግሞ አንጻራዊ ንቃት፣ ትጥቅና ድርጅት ያላቸውን ጥቂት ቡድኖች ወደ ሥልጣን መንበር አመጡ  እንጂ፣ አብዮቱ በተከሰተባቸው አገራት ዲሞክራሲን አላሰፈኑም፣ ሕዝባዊ መንግሥትም እንዲቋቋም አልረዱም። የነቃና የተደራጀ ሕዝብን ያካተተ ሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመጽ ግን በትንሽ ኪሳራ አገራዊ ቀውስን ለመፍታት መንገድ ይከፍታል። ከታሪክ እንደምንማረውና እንደምንስተዋለው፣ በብዙ አገራት የተከሰቱት የነቃና የተደራጀ የሕዝብ ዓመጾች፣ ሁሉን ዓቀፍና ግልጽ ፍኖተ ካርታ ባላቸው የነቁ ፖሊቲካ ድርጅቶች ከተመሩ ዲሞክራሲን የማስፈን ዕድላቸው የሰፋ ነው። ሰላማዊው የቄሮ ትግል ያለ አንዳች የጥይት ድምጽ፣ የወያኔ መራሹን መንግሥት ሲያንገዳግድ፣ ግልጽ ፍኖተ ካርታ ያለው ሕዝባዊ ዓመጹን ሊመራ የሚችል የነቃና የተደራጀ ዝግጁ የፖሊቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ ሕዝባዊ ትግሉ ተፈላጊውን ውጤት ሊያመጣ ሳይችል ቀረ እንጂ፣ ሕዝባዊ ንቃትና ድርጅት ቢታከልበት ኖሮ ስኬቱ እርግጠኛ እንዲሚሆን አያጠራጥርም ነበር።

 

ስለሆነም፣ አንድ የፖሊቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ እውነተኛ ዲሞክራሲን እንዲወልድ ከተፈለገ፣ ገና ከጅምሩ፣ የሕዝቡን የመንቃትና የመደራጀትን ደረጃ እንደ አንድ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ አለበት ማለት ነው። በኔ ግምት፣ ከላይም ለማስቀመጥ እንደ ሞከርኩት፣ በዛሬው ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ ንቃትና ድርጀት፣ እውነተኛውን ሕዝባዊ መንግሥትን ለማቋቋም የሚያስችል ደረጃ ላይ አይደለም ባይ ነኝ። በዚህ ሁኔታ፣ ዛሬ እንዲቋቋም የምንፈልገው የሽግግር መንግሥት፣ ሕዝባዊ ሳይሆን በተወሰኑ ቡድኖች የሚቋቋም ኢሕዝባዊ መንግሥት ይሆናል ማለት ነው። ዶር/አማረና አቶ ገለታው ይህንን በምንም ተዓምር ሳናሙላው አመርቂ ውጤት ማምጣት የማንችልበትን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ መክተት ነበረባቸው። የአገራችን ነባራዊ የችግሮቻችን ካታሎግ የሚያሳየን ደግሞ፤ ሕዝባችን አለመንቃቱን ብቻ ሳይሆን ፖሊቲከኞቻችን ራሳቸው መሠረታዊውን የፖሊቲካን ሀሁ፣ ማለትም ተቃራኒ አስተሳሰብን አስተናግዶ የጋራ ግብን ለማሳካት አብሮ የመጓዝ ባሕልን በሚጠበቀው ልክ አለመላበሳቸውን ነው። የፖሊቲካ ንቃት ደረጃቸው ዝቅ ያለ ነው ማለቴ ነው።

 

ለሽግግር መንግሥት መቋቋም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች፣

 

የሽግግር መንግሥት፣ ዝም ብሎ እንደ ነጻ አውጪ ግንባሮች በወዳጅነትና “በሰፈር ልጅነት” ብቻ የተወሰኑ ግለሰቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተነሳሽነት የሚያቋቁሙት ተቋም አይደለም። የሽግግር መንግሥትን ለማቋቋም ሁለት የተለያዩ ግን ደግሞ ተጓዳኝ የሆኑ እርከኖች እንደ ወሳኝ ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ አለባቸዉ። የመጀመርያው እርከን፣ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለውንና ሁሉን አቀፍ የሆነውን የሽግግር መንግሥቱን አባላትንና ብሎም መንግስቱን ለማዋቀር የሚችል አንድ ራሱን የቻለና እሱም ልክ እንደ ሽግግር መንግሥቱ አባላት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተቋም ወይም ቡድን ማዋቀር ነው። ይህ ተቋም ወይም ቡድን፣ በጥቂት ግለሰቦች ጥቆማ ብቻ የሚመሠረት አካል መሆን የለበትም። በዚህ ተቋም ወይም ቡድን የሚቋቁመው የሽግግር መንግሥት ሁሉን ዓቀፍና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ የዚህ አዋቃሪ ኃይል ተዓማኒነትና ሁሉን ዓቀፍነት ቅድሚያ ሊሠጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ወደድንም ጠላንም፣ የሽግግር መንግሥቱን የሚያዋቅረውን ሁሉን ዓቀፋዊ ተቋም ወይም ቡድን ማዋቀሩ ለሽግግር መንግሥት መቋቋም የመጀመርያው እርከን ነው። ሁሉን አካታች የሆነው አዋቃሪ ቡድኑ ከተቋቋመ በኋላ የሚቀጥለው ሁለተኛው እርከን ደግሞ የአዋቃሪ ቡድኑ ቀጣይ ተልዕኮ የሆነውን ሁሉን አካታች የሆነውን የሽግግር መንግሥቱን አባላትን መልምሎ የሽግግር መንግሥትን ማቋቋም ነው።  በኔ ግምት፣ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው፣ ዛሬ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት ያለውን የሽግግር መንግሥትን የሚያዋቅር ቡድን ወይም ተቋም የመመሥረት ንቃቱና ብቃቱ፣ ብሎም ተስማምቶ የመሥራት ተስፋው አለን ወይ? ወይስ እፍኝ የማይሞሉ ፖሊቲከኞች ልክ እንደ ነጻ አውጪ ግንባሮችና ድርጅቶች፣ ማንንም ሳይወክሉ በራሳቸው ተነሳሽነት እንደ ጓደኛሞች ተመራርጠው አዋቃሪ ቡድኑን ብሎም የሽግግር መንግሥቱን ይፈጥራሉ? የሚለው ነው። ስለዚህ፣ ቁልፍ ጥያቄው፣ የሽግግር መንግሥቱን የሚያዋቅረውን ተቋም ወይም ቡድንን ማን ነው የሚያዋቅረው ይሆናል። አንድ የሆነ የአስፈጻሚነት ኃያል ያለው አካል መሆን አለበትና!

እንዲሁ ለማስታወስ ያህል፣ 19966 ዓ/ም፣ የተደራጀው ወታደራዊ ኃይል ነበር ታማኝ ግለ ሰቦችን መርጦ ጊዜያዊ ወታደራዊ (የሽግግር) መንግሥት ያቋቋመው። በ1991 ዓ/ም እንደዚሁ “የሚስማሙትን” መርጦ የሽግግር መንግሥቱን ያቋቋመው፣ ሕወሃት ነበር። ስለዚህ የሽግግር መንግሥትን አባላት የሚመለምል የአንድ የማስፈጸም ኃይል ያለው ቡድን መኖር የማይታለፍ ቅድመ ሁኔታ ነው ማለት ነው። የነዚህን ሁለት የለውጥ ሂደቶች ስናጤን፣ በዛሬው የአገራችን ሁኔታ የደርግን ወይም የወያኔን ሚና ተጫውቶ፣ ብቁ ናቸው የሚላቸውን “የሚስማሙትን” ኢትዮጵያውያኖችን መልምሎ የሽግግር መንግሥት አባላትን የሚሾም ኃይል ማን ነው? ይኸ ፈረንጆች የሚሊዮን ዶላር ጥያቄ የሚሉት ነገር ነው። ለዚህም ነው የሽግግር መንግሥትን የሚያቋቋመውን አዋቃሪ ቡድንና የሽግግር መንግሥቱ አባላትን ከመልመላችን በፊት፣ እነዚህን ሁለት ተጓዳኝ ተቋማትን ለማቋቋም የሚረዱ “የቅድመ ሁኔታዎች ዝርዝር – Cheklist) በግልጽ የምንወያይበት አንዳች ዓይነት የውይይት መድረክ ያስፈልገናል የምለው።

 

በውይይታችን ሂደት ከሁሉም በላይ ልዩ ትኩረት መሠጠት አለበት የምለው ዓቢይ ጉዳይ፣ የሕዝባችን የንቃት ደረጃ ዝቅተኝነት ነው። ለአንድ አገር ዕድገት፣ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና የሚጫወተውና የለውጥ ክስተት የማዕዘን ድንጋይ የሕዝቡ የንቃት ደረጃ ነው። ንቃት ማለት ደግሞ በፊደል ቆጠራ በሚገኘው ትምሕርት ብቻ ሳይሆን፣ መላው የማሕበረሰቡ አባላት ስለ ራሳቸውና በማሕበረሰቡ ውስጥ ስላላቸው ሚና ብሎም ከራሳቸው ማኅበረ ሰብ ውጭ ከሚገኙ ከሌሎች ማኅበረ ሰባ አባላት ጋር ተከባብሮ ግጭትን በሰላም በመፍታት አብሮ ለመኖር የሚያስችል በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸው ማለት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ዜጎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን መብትና ግዴታ በደንብ ጠንቅቀው ሲያውቁ ማለት ነው። መብትና ግዴታን ማወቅ ማለት ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉላቸውን የግልና የቡድን መብቶቻቸውን ጠንቅቆ ማወቅና እነዚህን መብቶች እንዳይጣሱባቸው ዘብ ቆሞ ለመከላከል መቻል ማለት ነው። ሰፋ ተደርጎ ሲታይ ደግሞ የራስን ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብትን በደንብ አውቆ የራስን ወገን ብቻ ሳይሆን የመላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ መብት መረገጥ እንደ ራስ መብት ረገጣ ቆጥሮ ለነዚህ መብቶች መከበር ከሌሎች ጋር ሆኖ ተደራጅቶ ጭቆናና ግፍን ለማስወገድ ሲታገል ማለት ነው። በዛሬው ያገራችን ሁኔታ፣ የማንነት ጥያቄ ከሁሉም በላይ ወሳኝ ሆኖ ፖሊቲከኞችና ምሑራን ጽንፍ ረግጠው ለየራሳቸው ወገን መብት መከበር ብቻ በሚታገሉበትና ይባስ ብሎም ሌላውን ሕዝብ እንደ ጠላት በሚቆጥሩበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሆኖ ጭቆናን እና የመብት ረገጣን ለመታገል ንቃቱና ድርጅቱ አለው ለማለት አያስደፍርም።

 

በኔ ግምት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የንቃት፣ የድርጅትና የትጥቅ ደረጃው በአገሪቷ እየተከሰተ ላለው ቀውስ አጥጋቢ መፍትሔ ሊሠጥ በሚያስችል ደረጃ ነው ለማለት ያስቸግራል። እንዲያውም፣ ከሌሎች አገር ሕዝቦች ጋር ሳስተያይ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ትሁት፣ ፈሪ፣ መንግሥትን “እግዜር ነው የሾመልኝ” ብሎ የሚያምንና፣ ማንኛውንም ዓይነት ችግር “እግዜር ያመጣውን እግዜር ይመልሰዋል” ከማለት ውጪ፣ ተፈጥሮ የሠጠውን ጭንቅላት ተጠቅሞ፣ ለመብቴ እሟገታለሁ ብሎ ደፍሮ ወደ አደባባይ የማይወጣና ሁሉን ነገር ችሎ የሚኖር ለአስተዳደር የሚመች ሕዝብ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። በሌላ አገር በዳቦ ወይም ስኳር ላይ መንግሥት ዋጋ ሲጨምር ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መንግሥትን መገዳደር የተለመደ ሲሆን በአገራችን ግን፣ እንኳን ዋጋ ተጨምሮ ይቅርና ዜጎች በአደባባይ ሲረሸኑ፣ ያለ ፍርድ በገፍ ሲታሠሩና ሲሰቃዩ እያየ አንዳችም ዓይነት ተቃውሞ ለማሰማት የሚያስችል ንቃትና ድርጅት ያለው ሕዝብ አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ የዘመናት ትግላችን ሕዝባችንን በተፈለገው ልክ ለማንቃትና ለማደራጀት ብሎም መብት ጠያቂ ሕዝብ ሊያደርጋቸው አልቻለም ማለት ነው። መንግሥትም ይህንን የሕዝቡን የንቃት ደረጃ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው በዘፈቀደ ሁሉን ነገር የሚጭንባቸው! ሕዝቡም እያጉረመረመ፣ ልጆቹ እንኳ ሲገደሉበት ዕንባውን እየረጨ ማቅ ለብሶ ድንኳን ጥሎ ለኃዘን ይቀመጣል እንጂ፣ ለራሱ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ሆ ብሎ በጋራ ተነስቶ ለሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍትሕን የመጠየቅ ንቃት የለውም ብል ከዕውነት የራቀ አይመስለኝም።

 

የሽግግር መንግሥትን ለማቋቋም የሚረዱ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማሟላት የባለድርሻ አካላት አስተዋጽዖ ምን መሆን አለበት?

 

በኔ ግምት በመጀመርያ፣ ደረጃ የሽግግር መንግሥትም ሆነ ሌላ ከዚህ ቀውስ የሚገላግለንን አማራጭ አስተዳደራዊ ተቋም ለመፍጠር የሚረዳ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀይስ፣ ብቃቱና ፍላጎቱ ባላቸው ዜጎች ትብብር የሚቋቋም አንድ የሆነ የውይይት መድረክ መፈጠር አለበት። ይህ የውይይት መድረክ፣ ባለ ድርሻ አካላት የተለያዩ ሃሳቦቻቸውን በሠለጠነ መንገድ ተወያይተውበት ሃሳብን በሃሳብ ሞግተው አንዳች ዓይነት ስምምነት ላይ ደርሰው አገሪቷን ከጥፋት የሚያድኑበትና ዲሞክራሲ ሰፍኖ ሕዝቦቿ የሰላም አየር የሚተነፍሱበት ምድር እንድትሆንና፣ ዲሞክራሲያዊ መንግሥትን ለማቋቋም የመጀመርያው እርምጃ እንዲሆን የሚረዳ አንዳች ዓይነት ፍኖተ ካርታ የሚያዘጋጁበት መድረክ መሆን አለበት። እንዲህ ዓይነቱ መድረክ በታሪካችን ውስጥ እምብዛም ያልተለመደና በተተገበረበትም ጊዜ አስፈላጊውን ውጤት ያላመጣ ቢሆንም፣ ዛሬ ግን አስፈላጊነቱ ከምን ጊዜውም በላይ የመኖርና ያለ መኖር ጉዳይ ያህል ሆኖ ይገኛል። የዚህ የውይይት መድረክ ተሳታፊዎች፣ የአገራችንን የግጭት ምክንያቶችን በውል የሚረዱና ተመሳሳይ ግጭቶችን ለመፍታት ዕውቀቱና ልምዱ ያላቸው (ባሕላዊና ሳይንሳዊ) ጽንፈኝነትና ወገንተኝነት የማያጠቃቸው የተለያዩ ብሔር ተወላጆች መሆን አለባቸው።

 

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች፣ በብሔር ማንነት ሰበብ ጽንፍ የረገጠውንና ብሎም ተከፋፍሎ ያለውን ምሁር፣ ኤሊቱን እና ፖሊቲከኞችን በተቻለ መጠን በአንድ መድረክ አሰባስቦ በአገሪቱ ጉዳዮች ላይ አንዳች የጋራ መግባባት እንዲኖር፣ በሁሉም ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ካልተደረሰ ደግሞ ባለመግባባታቸው ተግባብተው በሚያስማሟቸው ነጥቦች ላይ የጋር አቋም ይዘው፣ አገሪቷን ማዳንና ሕዝቦቻችንንም ሰላምና መረጋጋት በሠፈነባት አገር እንዲኖሩ የጋራ ትግል ለማድረግ ዝግጁ የሆኑ ግለ ሰቦች መሆን አለባቸው። የኢትዮጵያ ችግር ፈጣሪዎችና ከሌሎች ብሔር ተወላጆች ፖሊቲከኞቻን ምሑራን ጋር ከተስማሙ ደግሞ የዚያኑ ያህል ሰላም አስፋኞች ሊሆኑ የሚችሉ የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራይ ኤሊቶች፣ ምሑራንና ፖሊቲከኞች፣ ከነዚህ ሶስቱ አንዱን እንኳ ያላካተተች ኢትዮጵያ በሰላም ለመኖር እንደማትችል ተገንዝበው፣ የሥልጣን ሽኩቻቸውንና በማንነት ላይ ከተመሠረት ጽንፈኝነት ተላቅቀው፣ ሁላቸውም እኩል ዜጋ እንደ ሆኑና ማንም ብሔር ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ በውል ተገንዝበው፣ በጋራ ሆነው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋትን ሊያሰፍን የሚችል ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ለማቋቋም የሚረዳ የመፍትሔ አቅጣጫ ለመቀየስ በጋራ ለመሠለፍ የተዘጋጁ ግለ ሰቦች መሆን አለባቸው።

 

መደምደሚያ

 

ለአጭር ጊዜ ዓላማ ሳይሆን ለወደፊትም የሚከሰቱት ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት መብታቸውን እንዳይጥሱባቸው ሕዝቦቻችንን ማንቃትና ማደራጀት ተቀዳሚ የቤት ሥራችን መሆን አለበት። አለበለዚያ የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት ልክ እንደ ከዚህ በፊቶቹ፣ ለጥቂት ቡድኖች የፖሊቲካ ሥልጣን መጨበጫ መሣርያ ብቻ ሆኖ ይቀራል። በትክክለኛ መረጃ የተደገፈ ባይሆንም፣ ከአገራችን ሕዝቦች ከ75% በላይ የሚሆነው ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው። ስለሆነም፣ ሕዝቡን እናንቃና እናደራጅ ስል፣ ወጣቱን ትውልድ አንቅተን እናደራጅ ማለቴ ነው። እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ፣ እኛ ወጣቱን ትውልድ ወክለን ከምንጮህ እስቲ እነሱን እናደራጅና የራሳቸውን መብት ጠያቂ ሆነው ለራሳቸው መብት መከበር እንዲጮሁ እናድርግ። ለራሳችን የግል ፖሊቲካ ሥልጣን ጥቅም ብለን ያልሆነ ትርክት እየነገርናቸው ወደ ጥፋት ጎዳና አንምራቸው። ከሌሎች ብሔር ተወላጆች ጋር ሆነው ማንም ማንንም የማይበድልባትን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንዲገነቡ የቻልነውን ያሕል ሙያዊና ቁሳቁሳዊ ድጋፍ እንሥጣቸው። አዎ! ሕዝብን ማንቃትና ማደራጀት እጅግ በጣም አታካች ነው። ጊዜና ጉልበት ይጠይቃል። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት በተፈጥሮው መብት ጠያቂን ሕዝብ ስለማይወድ፣ የማንቃትና የማደራጀት ተልዕኮያችን ከመንግሥት ጋር እንደሚያጣላን ከወዲሁ መታወቅ አለበት። ይህንን ረጅምና አታክች ጉዞ ስናስብ ነው እንግዲህ ብዙዎቻችን ተሳክቶልን በዕድሜያችን ለማናየው ነገር ምን አለፋን ብለን ተስፋ ቆርጠን ማንቃትና ማደራጀቱን ችላ የምንለው። ወይም ደግሞ በተቃራኒው ሂደቱን አሳጥረን በኛው ዕድሜ እንዲሳካልን ሕዝቡን ማንቃትና ማደራጀቱን ትተን ትግሉንም ውጤቱንም  ለራሳችን ለማድረግ “እየታገልን” ያለነው! ከላይ እንዳልኩት፣ ይህ በስድሳዎቹ ሞክረን ከግብ ያላደረስነው እንቅስቃሴ ስለሆነ፣ ካለፈው ስሕተታችን ተምረን፣ የራሳችን ንቃት ብቻ ወሳኝ አለመሆኑን አውቀን፣ ሰፊውን ሕዝባችንን አንቅተን ለማደራጀት ፍኖተ ካርታ እናዘጋጅ። ሕዝባዊና ዲሞክራሲያዊ መንግሥትን ለማቋቋም ሌላ የተሻለ መንገድ በጭራሽ ሊኖር አይችልም።

 

በግሌ የሽግግር መንግሥት ያስፈልጋል አያስፈልግም የሚለው ሙግት እምብዛም አያሳስበኝም። ያለፉት ሁለት የሽግግር መንግሥቶቻችን የተቋቋሙት በሰፊው ሕዝብ ሰላማዊ ትግል የተገኘውን ድል፣ የተወሰኑ ከሰፊው ሕዝብ ይበልጥ የታጠቁና የተደራጁ ቡድኖች በሕዝብ ስም እየማሉ፣ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በጉልበት ገልብጠው ባካሄዱት አውዳሚ አብዮታዊ ለውጥ ስለ ነበር፣ ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል የሚል ሥጋት አለኝ። የኔ ምኞት፣ በታሪካችን አንድ ጊዜ ብቻ ሞክረነው አመርቂ ውጤት ያመጣውን፣ ማለትም አንዳች ጥይት ሳይተኮስ ለአርባ አራት ዓመት ተደራጅቶ ይገዛን የነበረውን የሕወሃት መንግሥትን ያንገዳገደውን፣ ሰላማዊውን የቄሮን ሕዝባዊ አመጽ የትግል ስልት እንድንሞክር ነው። ለሕዝባዊ ዓመጽ ስኬት ደግሞ የማዕዘን ድንጋዩ ሕዝባዊ ንቃትና ድርጅት ብቻ ነው። ሌላ አቋራጭ የለም። ሳያድለን ቀርቶ፣ ሕዝባዊ ንቃትና ድርጅቱን ሳናስቀድም፣ ዝም ብሎ “መንግሥት ይውረድ” እና በሱ ቦታ የሽግግር መንግሥት እናቋቁም ማለት በ1974 እና በ1991 ዓ/ም መንግሥት ሲገረስስ ወይም ሲዳከም፣ በማን እንደምንተካ በቂ ዝግጅት ባለማድረጋችንና የነቃና የተደራጀ ሕዝባዊ ኃይል ሳይኖር መንግሥትን ማፍረሱ፣ ነባሩን መንግሥት በአንድ ሕዝባዊ ባልሆነ መንግሥት ተክተን መራራ ብቅሉንም “ይጣፍጥሃል” ተብለን ሳንወድ በግድ እየተጋትን እንድንኖር ተደርገናል።

 

አዎ! የአገራችን ሁኔታ እጅግ በጣም አሳሳቢ በመሆኑ ሰላምና መረጋጋትን ሊያሰፍን የሚችል መንግሥት ማቋቋም አስፈላጊ ቢሆንም፣ ለችግራችን ዘላቂ መፍትሔ የምንመኝ ከሆነ ከሁሉ አስቀድመን ሕዝባችንን ለማንቃትና ለማደራጀት ልዩ ትኩረት መስጠት አለብን ባይ ነኝ። አንዳንድ ፖሊቲከኞች፣ ጥቂት የነቁ የማኅበረሰቡ አባላት ብቻ ጠብመንጃ ይዘው መንግሥትን ስለተገዳደሩና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሕዝቡን ለማስከተል ስለ ቻሉ ብቻ፣ “ሕዝቡ በሚገባ ነቅቷል” ሲሉ ይስተዋላል። ንቃት ማለት ደግሞ፣ ሕዝቡ ዝም ብሎ ስለ ወቅታዊው ቀውስ ስለተነገረው ብቻ  ጠብመንጃና ዱላ ይዞ በሆሆታ ጫካ መግባቱና መዝመቱ ሳይሆን፣ ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቱን ጠንቅቆ አውቆ፣ እነዚህን መብቶቹን ለማስከበር ቁርጠኛ ትግል ለማድረግ ሲደራጅ ብቻ ነው። በስድሳዎቹ ውስጥ፣ ወደውም ሆነ ተወናብደው ከደርግ ጋር ተባብረው የመኢሶንና የኢሓፓን አባላት ውድ ዋጋ ያስከፈሉት፣ የፖሊቲካ ድርጅቶቹ ራሳቸው ሊያነቋቸውና ሊያደራጇቸው ሲሞክሩ በነበሩ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ወዝ አደሮች መሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። የንቃትና ድርጅታቸው ጥንካሬ ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ለነሱ ነጻነት የሚዋጉላቸውንና ራሳቸውን አሳልፈው የሠጡትን ተራማጆችን መደገፍና ከነሱ ጋር ሆኖ ወታደራዊውን መንግሥት መታገል ሲገባቸው፣ ተራማጆቹን ምሑራን አሳልፈው በመሥጠት ለሞት ዳርገዋቸዋል። በኔ ግምት፣ ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ የንቃትና የድርጅት ደረጃ ከያኔው የተሻለ አይመስለኝም። የሕዝቡን የመንቃትና የመደራጀት ብቃት አሳንሶ ተስፋ ለማስቆረጥ ሳይሆን፣ ሕዝቡን ለማንቃትና ለማደራጀት ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው ፖሊቲከኞችና ምሑራን ታሪካዊ ሚናቸውን በሚፈለገው ልክ አልተጫወቱም ለማለት ነው።

 

በኔ ግምት፣ ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታና ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስፈልጉን ቅድመ ሁኔታዎች በአጭሩ ይህንን ይመስላሉ። የችግሩን ወርድና ቁመት ተረድተን ዘላቂ መፍትሔ መፈለጉ ደግሞ የሁላችንም ጉዳዩ ያሳስበናል የምንል ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ ሚና ነው ባይ ነኝ። ሃሳቤን በከፊልም ሆነ በሙሉ ሊቃወሙ የሚችሉ ግለ ሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከወዲሁ ለመገመት እችላለሁ። አያሳስበኝም! እኔ የሚሠማኝን ካየሁትና በልምድ ካገኘኋቸው ተሞክሮ ተነስቼ፣ “ሊሆን ይችላል” ወይም “መሆን አለበት” ብዬ ስሞግት፣ አለመግባባትንና የሃሳብ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ በመወያየት የመፍታት ብቃት እያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች  ዝምታን የመረጡ ቅን ዜጎች እንዳሉ ስለማምንና፣ ዝምታቸውን ሰብረው፣ የውይይት መድረኩን ለመፍጠር የበኩላቸውን አስተዋጽዎ ያድርጋሉ ብዬ ስለማምን፣ አሉታዊ ትችቶች ቢሠነዘሩም አያሳስበኝም።

 

አለመግባባትን መፍታት የሚቻለው በጉልበት ብቻ ነው ብለን ከያቅጣጫው የጦርነት ነጋሪት እየጎሰምን ሕዝባችንን እርስ በእርስ እያጫረስን፣ አገሪቷን ዛሬ ላላችበት አደጋ እንድትዳረግ አስተዋጽዖ አድርገናል። ስለዚህ፣ ሰላም ፈላጊውን ወገኖቻችንን አደራ ለማለት የምፈልገው፣ እስቲ ከሚዲያው ወከባ ራሳችንን ለጊዜው አግልለን፣ ሰከን ባለ መንፈስ፣ ችግሮቻችንን በቅንነት የምንወያይበት አንድ ሁሉን ዓቀፍ የሆን መድረክ እንፍጠር። አዎ! ሃሳብ መሠንዘር ቀላል እንደ ሆነ ይገባኛል። ቅንነት ካለ ግን  መድረኩን መፍጠሩም ያን ያሕል አዳጋች አይሆንም። ራሳችን መድረኩን መፍጠሩ ካቃተን ደግሞ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ አንዳንድ “ችግሮቻችንን በሠለጠነ መንገድ ብቻ መፍታት አለብን፣ የወላጆቻችንን ፈለግ ተከትለን አገራችንን ወደ ገደል አንምራት፣ ጦርነት ይቁም” ብለው በቲክቶክና በተለያዩ ሚዲያዎች ብቅ ያሉ የወጣቱ ትውልድ አባላት ስላሉ፣ እነዚህን ወጣቶች መድረኩን ራሳቸው እንዲፈጥሩ ማገዝም ሌላው ተገቢ አማራጭ ነው። እስቲ እነሱንም የምናጠናከርበትን ዘዴ እንፍጠር። ሰላምና ዲሞክራሲ የሠፈነባትና ሁሉም ሕዝቦቿ በሰላም የሚኖሩባት የነገዋ ኢትዮጵያ የነሱ ስለሆነች፣ ዛሬ የነሱ መጠናከር አገሪቷ ውስጥ ሰላም ተፈጥሮ ሕዝቦቻችን ችግሮቻቸውን በሰላም የሚፈቱበትን የመፍትሔ አቅጣጫ ለመቀየስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራልና በጥብቅ እናስብበት። የነገዋ ኢትዮጵያ የነሱ ብቻ ስለ ሆነች፣ በውይይታችን ሂደት ውስጥ የሚገባቸውን ታሪካዊ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ካሁኑ እናስብበት። በቸር ይግጠመን።

 

********

 

አዲስ አበባ፣ ኖቬምበር 2023 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com

1 Comment

  1. “አለመግባባትን መፍታት የሚቻለው በጉልበት ብቻ ነው ብለን ከያቅጣጫው የጦርነት ነጋሪት እየጎሰምን ሕዝባችንን እርስ በእርስ እያጫረስን፣ አገሪቷን ዛሬ ላላችበት አደጋ እንድትዳረግ አስተዋጽዖ አድርገናል” በይሳ አዘውትረህ እንደምትጽፈው ይህ ያንተ ማዘናጊያ ሃሳብ ነው። ወይ ጥርት አድርገህ በጋንዲ የተግል መንገድ በድሮን እየተደበድባችሁ፤በጨካኝ የኦሮሙማ ወታደሮች እየተፈለጣችሁ ካለቃችሁ በኋላ ነጻነት ይገኛል ነው የምትለን። ይህንን ከገዳ ስርአት ስለትማርን ለዛ እድል አንሰጥም። ጋንዲዝም የተሳካው እንግሊዞች ኦሮሙማ ስላልሆኑ ነው ሰው ሲበለት፤ ሲቀሰት፤ ሲገፈፍ ቁመው የማየት ስብእና የላቸውም። ደቡብ አፍሪካና የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶች ነጻ የወጡት እንግሊዛውያን ያላሰለሰ ጥረት በማድረጋቸውም ጭምር ነው ከናንተ ግን ያየነው መምህር ፋንታሁን ዋቄን ብቻ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

7778ioii7878
Previous Story

ሚናወቻቸውን የተለዋወጡት አቡነ ኤርምያስና አቶ ታየ ደንድአ

Fekadu Bekele Ethiopia 1 1
Next Story

የአንድ አገርና ህዝብ ዕድል ሊወሰን የሚችለው ከ2-5% በሚሆነውየህብረተሰብ ክፍል ብቻ

Go toTop