ይህንን ካልኩ በኋላ ብሄርተኝነትንና ብሄራዊ አንድነትን አጣምሮና አስታርቆ ሊሄድ ይችላል ብለው ያቀረቡት ቅርጸ መንግስት ብዙ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ልገልጽ ነው የዛሬው አነሳሴ።
የመጀመሪያው ነገር በአውኑ ከዘውግ እርሻና ከዘውግ ፌደራሊዝም እርሻ ላይ ለሁሉም የሚሆን መሪ ወይም አባት እናገኛለን ወይ? የሚለውን ጥያቄ በምናብ ሳየው እማይመስል ነገር ሆነብኝ። እርስዎ እንደሚሉት ዘውግ የስልጣን ምንጭ ሆኖ ሲያበቃ ፕሬዝደንት ግን ከዘውግ ውጭ በሆነ የምርጫ ስርዓት ይመረጣል ማለትስ ምን ማለት ነው? ከሁሉ በላይ ግን እሺ እርስዎ እንደሚሉት ፓርላማው፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤት ሁሉ በዘውግ የውክልና ቀመር ይመስረት፣ የፌደራል ስርዓቱም እንዲሁ ዘውግ ተኮር ይሁኑ እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ ታዲያ ለመሆኑ ፕሬዚደንቱ በየትኛው የመንግስት ውቅር ውስጥ ነው የብሄራዊ ማንነት መገለጫ የሆኑትን ጉዳዮች የሚያስፈጽመው? ፕሬዝደንቱ አስፈጻሚዎቹን ይዞ አስተዳደር የሚመሰርተው እኮ በዚያው በብሄር ፌደራል ስርዓቱ መዋቅር ላይ ነው። የፕሬዚደንቱ አስተዳደር የሚያድረው (dwell የሚያደርገው) በዘውግ የፖለቲካ ዩኒቶች ውስጥ ነው። ፕሬዝደንቱን ሁሉም ሰው የመረጠው ቢሆንም እንኳን ማስፈጸሚያ ማሽነሪዎቹ የዘውግ ማሽነሪዎች ናቸው። አሁን ያለው የትግሬ ፍርድ ቤት፣ የኦሮሞ አቃቤ ህግ፣ የወላይታ ፖሊስ፣ የእከሌ ባንክ…….. እየተባሉ የሚቋቋሙትን የመንግስት ማሽነሪዎችን ይህ ፕሬዚዳንት ከቶ እንዴት ሊያሽከረክረው ይችላል? ይህ ፕሬዝደንት በሁሉም ክልሎች አብላጫ ድምጽ ቢመረጥም ዞሮ ዞሮ የሚነዳው ያንኑ የብሄር ተኮር የመንግሥት ማሽነሪዎችን ነው።
ፕሮፌሰር መሳይ
አንድ ጊዜ ኢሳት ቴሌቪዥን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርቪው ነበረኝ። ጋዜጠኛው የብልጽግናን ውህደት ለምን ትነቅፋለህ የሚል ጥያቄ አይነት ጠየቀኝ። ኢህአዴግ ወደ ብልጽግና ተቀየርኩ ሲል የውነትም ተቃውሜ ነበር። የተቃወምኩበት ምክንያት ውህደቱ በመርህ ደረጃ ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ ስለሆነ ነው። አጠቃላይ የፌደራል ስርዓቱ በዘውግ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሳለ፣ ቅርጸ መንግስቱ በዘውግ ላይ የተመሰረተ ሆኖ ሳለ፣ ህገ መንግስቱ ዜግነትን እንደ የብሄር ልጅ አድርጎ የሚያይ ሆኖ ሳለ፣ ይህ መዋቅር ሳይለወጥ ውሁድ ፓርቲ መፍጠር ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያይል ነው። ውሁድ ፓርቲ የሚጫወትበትን የፖለቲካ መም (lane) ሳንዘረጋ፣ ወይም የፖለቲካ አስተዳደር ሳንዘረጋ በዘውግ ውቅር ላይ የዜግነት ፖለቲካ ጀመርን ማለት ስለማንችልና በሂደቱም የመዋቅር እገጭ እጓ ስላለው ነበር። የውነትም ብልጽግና ሃገራዊ ፓርቲ ሆንኩ የሁሉም ቤት ሆንኩ ባለ በማግስቱ የአማራ ብልጽግና፣ የኦሮሞ ብልጽግና፣ የወላይታ ብልጽግና …. እያለ ወደየዘውጉ መሮጥ ጀመረ። ይህ ችግር የመጣው ብልጽግና ውሁድ ፖለቲካን በማያስተናግድ የመንግስትት መዋቅር (government structure) ላይ ሄዶ ስለወደቀ ነው። የተዋሃደ የዜግነት ፖለቲካን በብሄር ፖለቲካና ፌደራሊዝም ሲስተም ውስጥ እናስፈጽማለን በሚል የተሳሳተ እርምጃ ውስጥ በመግባታችን የተፈጠረ ችግር ነው። ውህደቱ ከህገ መንግስት ማሻሻያና ከፌደራል ስርዓቱ ሪአሬንጅመንት መቅደም የለበትም ከሚል ነው የተቃወምኩት። ውህድ የፖለቲካ ጨዋታን በማያስተናግድ ሲስተም ላይ የብሄራዊ አንድነት ፓርቲ ስልጣን ቢይዝና በዚሁ ስርዓት ላይ የብሄራዊ አንድነት መርሆዎችን አንግቦ ልንቀሳቀስ ቢል ስርዓታዊ ሽብር ይፈጠራል።
ፕሮፌሰር መሳይ። እርስዎ የሚሉት የፕሬዝደንት ጽህፈት ቤትም የሚገጥመው ችግር ይሄ ነው። ፕሬዝደንቱ በዘውግ ምርጫ የመጡ አስፈጻሚዎችን ይዞ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የሚያስፈጽምበት መዋቅር አያገኝም። ስለሆነም ወይ ተንሳፎ ሜዳ ላይ ይቀራል፣ ወይም ይህንን ብሄራዊ አጀንዳውን በፖለቲካ ዩኒቶች መካከል ለማስፈጸም ሲጥር ከዘውጉ ራስ ማስተዳደር መርሆ ጋር ይጋጭና ሃገረ መንግስት ይናጋል። ስለዚህ ፕሬዝደንቱን በጋራ በመምረጥና አንድ ፕሬዝደንት በመሾም ብሄራዊ አንድነታችን ከዘውግ ማንነቱ ጋር እኩል አቻ ለአቻ እናራምዳለን ወይም ዘውግና ብሄራዊ ማንነት ይታረቃሉ የምንለው ጉዳይ በዚህ እርስዎ በሚሉት ቅርጸ መንግስት አይሰራም። የፕሬዝደንቱ ጽህፈት ቤት በጣም ቀጭን ይሆንና ዘውጌኝነትና የብሄር ፖለቲካ ጉልበታም ሆኖ ለሃገር አንድነት አደጋ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ከታች ከወረዳ ምክር ቤት እስከ ፌደሬሽን ምክር ቤት ድረስ ዘውግን የስልጣን ምንጭ አድርገን ስናበቃ ድንገት ተነስተን አንድ ፕሬዝደንት በመሾም ብሄራዊ ማንነትና የዘውግ ማንነት መሳ ለመሳ ሆነው ይቆማሉ የሚለውን አሳብ መቀበል አልችልም። ከሁሉም በላይ ይህ ቅርጸ መንግስት ቢተገበር ከፍተኛ የመርሆና የመዋቅር ግጭት የሚያመጣ ይመስለኛል። ከፍ ሲል እንዳልኩት የሀገሪቱ ዋና መተሳሰሪያ መርሆና ፓርላማ መገንቢያዋ ዘውግ ሆኖ ሳለ በሌላ በኩል አንድ ፕሬዝደንት ዘውግ ዘለል አድርገን በመምረጥ ዘውግንና ብሄራዊ ማንነትን በምንም አይነት እናቻችላለን ብዬ አላምንም።
ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ ፕሮፌሰር መሳይ። አንድ ሌላ በጣም ያሳሰበኝን ጥያቄ ልጠይቅዎ። ዘውግ የስልጣን ምንጭነቱን መቀጠል አለበት ሲሉ በመጀመሪያ የእርስዎ የዘውግ ብያኔ በየትኛው የብሄር ንድፈ ሃሳብ ወለል ላይ ነው የሚወድቀው? እርስዎ ኮንስትራክቲቪስት ከሆኑ “ዘውግ የስልጣን ምንጭ ነው” ሲሉ ለምሳሌ ኦሮሞ ውስጥ የኖረ አማራ ቋንቋውን ከቻለ ይህ አማራ መምረጥና መመረጥ ይችላል ማለት ነው። ኮንስትራክቲቪስቶች የሚሉት ብሄር ሰው ሰራሽ ስለሆነና ብሄርተኝነት ውጪያዊ ስለሆነ የሰው ልጅ ይህንን ውጪያዊ ልምምድ ከተለማመደው የዚያ ብሄር ተወካይ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። እርስዎ ይህንን የሚቀበሉ ከሆነ አንድ ሃረሪ ክልል ተወልዶ ያደገ ጉራጌ ለምርጫ ቀርቦ ቢመረጥ ሃረሪን ይመራል ማለት ነው። የመጀመሪያው ጥያቄዪ ዘውግ የስልጣን ምንጭነቱን ይቀጥል ሲሉ ዘውግን በዚህ በኮንስትራክቲቪስት አይን እያዩ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ አጠቃላይ ያቀረቡትን ቅርጸ መንግስት የበለጠ እንድመረምር ያደርገኛል።
ሁለተኛው ነጥብ እርስዎ ፕርይሞርዳያሊስት ከሆኑ ዘውግ የስልጣን ምንጭ ነው የሚሉት ብሄርን ከጥንታዊ ተፈጥሯዊነቱ ጋር አያይዘው ከሆነ ደግሞ ሌላ ከበድ ያለ ጥያቄ ያስነሳል። በዚህ ዶክትሪን አይን አይተው ነው ወይ ዘውግ የስልጣን ምንጭ መሆኑን ይቀጥል የሚሉት? ይህንን ንድፈ ሃሳብ ተንተርሰው ከሆነ ዘውግ የስልጣን ምንጭነቱን ይቀጥል የሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁለትና በላይ ብሄሮች የተወለደውን ህዝብ ምን ሊያደርጉት ነው? ይህ ህዝብ በቁጥሩ ከብዙ ብሄሮች ይበልጣል። እርስዎ ፕርይሞርዳያሊስት ከሆኑ በዚህ ባቀረቡት ቅርጸ መንግስት ውስጥ የሚፈጠረውን ከፍተኛ የዴሞክራሲ ደፈሲት አይተውታል ወይ? በቁጥር ከብዙ ብሄሮች የሚበልጠው ከተለያዬ ብሄር የተወለደው ህዝብ የሚገጥመውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የማህበራዊ መብቶች መሸርሽር እንዴት ያዩታል? ማለቴ ነው።
ከሁሉም በላይ ፕሮፌሰር መሳይ፣ ዘውግ የስልጣን ምንጭ መሆኑን ይቀጥል ሲሉ እርስዎ ዞሮ ዞሮ ኢንስትሩመንታሊስት ሆኑ ማለት ነው። ኢንስትሩመንታሊዝም የአንድ ሃገር የፖለቲካ መርሆ ሲሆን ደግሞ ማህበራዊ ሃብት እንደሚጎዳ ብሄራዊ ማንነት እንዴት እንደሚጠፋ፣ ዴሞክራሲ እንደሚጠፋ፣ የብሄሮች ባህሎች ኢንስትሩመንት ሲሆኑ እሴቶቻችን እንዴት እንደሚጎዱ ይታወቃልና ይህም ያሳስበኛል።
ስለሆነም የሃገራችን መካከለኛው መንገድና ብሄራዊ ማንነትንና የብሄር ማንነትን አቻችሎ ወደ ዴሞክራሲ ሊያራምደን የሚችለው ቅርጸ መንግስት ፖለቲካል ያልሆነ የባህል ምክር ቤትና በምርጫ የሚገነባ የእንደራሴዎች ቤት መገንባት የተሻለ ቅርጸ መንግስት ነው። ብሄርን ፖለቲከኛ አድርገን ኢንስትሩመንታሊስት ሆነን ከቀጠልን የምንሰብረው እቃ ይበዛል። ጣምራ ፌደራሊዝም የሚለው መጽሃፌ ላይ የሰራሁትን ቅርጸ መንግስት ከዚህ ኢሜየል ጋር አያይዤ ልኬልዎታለሁ። እስቲ ይመልከቱትና አስተያየት ይስጡበት ።
አክባሪዎ
ገለታው