የአርሰናልን ማሊያ የለበሰው ጌዲዮን ዘላለም ትንሹ ፋብሪጋስ የሚል ቅጥል ስም አግኝቷል፤
በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ደግሞ ጀርመናዊ የሆነው ጌዲዮን ዘላለም በእግር ኳስ ያለውን ችሎታ የተመለከቱ የስፖርቱ ተንታኞች « አዲሱ ሴስክ ፋብሪጋስ » በማለት ያሞካሹታል።
የአስራ ስድስት ዓመቱ ጌዲዮን ዘላለም የሰሜን ለንደኑን ክለብ የተቀላቀለው ከሁለት ዓመት በፊት ቢሆንም ከትናንት በስቲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለክለቡ ከሃያ አንድ ዓመት በታች ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል።
የአርሴናል ከሃያ አንድ ዓመት በታች ከሊቨርፑል አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ቢሸነፍም በግል ጌዲዮን በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀሱን ነው ዘገባዎች ያመለከቱት።
የወደፊቱ የአርሴናል ተስፋ እንደሆነ የተነገረለት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጌዲዮን የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ሲሆን በአስራ ስድስት ዓመቱ በማሳየት ላይ በሚገኘው ምርጥ ብቃት ከወዲሁ ከቀድሞው የመድፈኞቹ አምበል ከነበረውና አሁን በባርሴሎና ከሚገኘው ሴስክ ፋብሪጋስ ጋር በመነጻጸር ላይ ይገኛል።
ጌዲዮን የተወለደው በጀርመን ሲሆን ለአገሪቱ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ተጫውቷል። ተጫዋቹ ባለፈው ሳምንት ለሰሜን ለንደኑ አርሴናል እግር ኳስ ክለብ መጫወት የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ በኋላ ክለቡ ከሊቨርፑል ጋር ባደረገው ጨዋታ ተሰልፎ የክለቡ የወደፊት ተስፋ መሆኑን ያመላከተ እንቅስቃሴ ማድረግ ችሏል።
ተጫዋቹ ለአርሴናል ታዳጊ ቡድን ሊመረጥ የቻለው ኑሮውን በአሜሪካ ባደረገበት ወቅት መሆኑም ታውቋል።
የጌዲዮን የቀድሞ አሰልጣኝ ማት ፒልኪንግተን ባለፈው ዓመት ተጫዋቹን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት « የጌዲዮን ሚዛን አጠባበቅ ፣ እይታውና በሜዳ ላይ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በእርሱ እድሜ በሚገኙ ተጫዋቾች ላይ የማይስተዋል ነው። ተጫዋቹን በአጭር ጊዜ በአርሴናል ዋናው ቡድን ውስጥ እናየዋለን » ብለዋል።