September 22, 2023
38 mins read

የአብይ አህመድ አምባገነን አመራር- ከአልማዝ አሸናፊ (ዋዮሚንግ: አሜሪካ)

F6CiAX WsAAfelQ 1በቅድሚያ አምባገነንነት ማለት ምን ማለት ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠቴ በፊት : በኢትዮጵያ ውስጥ በድህነት ተወልጄ : በጉዲፈቻ ያሳደጉኝን አጎቴንና ባለቤቱን በቸሩ ፈጣሪ ስም አመሰግናለሁ:: ጥሩ ጭንቅላት ለግሶኝ በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በአዳሪነት ተምሬ የነፃ ትምህርት ዕድል በአሜሪካ እግኝቼ በመማር ዛሬ ላለሁበት ዕድሜና የኑሮ ደረጃ ላደረሰኝ አምላኬ ከፍ ያለ ምስጋና አቀርባለሁ:: በዚህም አጋጣሚ ለእኔ ትምህርት አስተዋፅኦ ያደረገው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለሆነ : ከ86 ጎሳዎች በላይ ያለው ይህ ሕዝብ ለትምህርቴ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሰጠኝ ስጦታ ሳላመሰግነው አላልፍም:: ይህንን የምልበት ምክንያት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ የተማሩ የዘመኑ ሊቆችና ፖለቲከኞች ያስተማራቸውን መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘንግተው በጎሳቸው አስተዋፅኦ ብቻ እንደተማሩ አድርገው የሌሎችን ጎሳዎች ውለታ ሲያሳጡና በጎሳዎች መሃል ጥላቻ በመፍጠር ሲያጋድሉና ሲያፋጁ ሳይ : እነዚህ ውለታቢሶች ጎሰኞችና ፅንፈኞች እንዴት ዝቃጮች እንደሆኑ መናገር ስለሚያስፈልግ ነው:: ሃቁ የማንኛውም ጎሳ አባል የተማረው በኦሮሞ : በአማራ : በትግሬ : በሱማሌ : በጋምቤላ: በወላይታ ወዘተ ኢትዮጵያውያን ተወላጆች አስተዋፅኦ ነው:: በአገር ውስጥም ሆነ በዲያስፓራ ያለው በኦሮሞ በትግራይ በአማራ ወዘተ ስም የሚነግደው የጎሳ ፖለቲከኛ : ንቃት ያገኘው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግብር ከፍሎ ባስተማረው ትምህርት ነው:: ዛሬ በዲያስፖራ ተመችቶት የሚኖረው የተሰደደው በኢትዮጵያዊነት ስም መሆኑን የማይገነዘብ ካለ : የሰው ዶማ ነው:: ጥገኛ ሆነን በምንኖርበት ባእድ አገሮች : ኦሮሞ : አማራ : ትግራይ : ወላይታ ወዘተ ስለሆንን በጎሳ ስም ጥገኝነት አልተሰጠንም:: ጥገኞች የሆንነው በኢትዮጵያዊነታችን ነው:: በኢትዮጵያ አምባገነን መንግስታት ሰብዓዊ መብቶቻችን ስለተገፈፉና ሕይወታችን ለአደጋ ስለተጋለጠ በመሰደድ ሕይወታችንን ያተረፍን ሰዎች ሕዝባችንን በጎሳ ፖለቲካ ሰላም ስናሳጣ ከጠላናቸውና ከምንጠላቸው የኢትዮጵያ አምባገነኖች በምን እንሻላለን?

ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ተጨናንቀው ባሉበት ወቅት እኛ በዲያስፖራ በምቾት የምንኖር የሕዝባችን መከራና ሰቆቃ ከመረዳት ይልቅ : በጎሳ ሕዝባችንን እየከፋፈልን ስናዋጋቸው ለምን ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይገባናል:: የሚሞቱት እንደኛ ሰዎች ናቸው:: እንሰሶች እንኳን የትኛው ዘራቸው እንደሆነ ያውቃሉ:: እንዴት ሰዎች ዘራችን የሰው ዘር መሆኑ ተሰናነን? የትግላችን ትኩረት በጋርዮሽ መሆን ያለበት በአምባገነን ስርዓት ላይ እንጂ : ጎሳን ከጎሳ ማጋጨት መሆን የለበትም:: ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተበደለው በየጊዜው እያስመሰሉና እያጭበረበሩ ስልጣን ላይ በሚወጡ አምባገነኖች ነው:: የአማራ ጎሳ : የኦሮሞ ጎሳ : የትግራይ ጎሳ : ወዘተ እርስ በርሱም ሆነ ሌላውን ጎሳ በድሎና ጎድቶ አያውቅም:: ለስልጣን ጥቅማቸው የጊዜው እምባገነኖች ጎሳዎችን ማባላትና ማፋጀት አንዱ ዘዴያቸው አድርገውታል:: እኛም የጎሳ ፖለቲካ አራማጅዎች በመሆን አምባገነኖችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመርዳት የተንኮላቸው ተባባሪ ሆነን እንገኛለን:: የመላው የኢትዮጵያ ጠላት እምባገነንነት መሆኑን እንገንዘበው::

ወደ ቅድመ ሃሳባችን ስናመራ :

አምባገነንነት በአንድ ወይም በጥቂት መሪዎች ስብስብ ከጥቂት እስከ ምንም ገደብ በሌለው የመንግስት ስልጣን የሚመራ የመንግስት አይነት ነው። በዚህ ስርአት ሶስት አይነት አምባገነን መንግስታት አሉ። ወታደራዊ መኮንኖች የሚቆጣጠሩት ወታደራዊ አምባገነን መንግስት : አንድ ፖለቲካ ፓርቲ ፍፁም ተቆጣጣሪ ሆኖ የሚመራው አምባገነን መንግስትና አንድ ግለሰብ ቆራጭ ፈላጭ በመሆን እንደ ግል ሀብት የሚያስተዳድረው አምባገነን መንግስት ናቸው። የ”ዶ/ር” አብይ አህመድ መንግስትም ከተመረጠበት ጊዜ ጀምሮ የአምባገነንነትን ጠባይ ቀስ በቀስ እያሳየ ይገኛል:: የዶ/ር ማዕረጉን በቅንፍ ያስቀመጥኩበትን ምክንያት አንባብያን ሊጠየቁ ይችላሉ:: ለዚያም መልሴ አምባገነን የፈለገውን ማዕረግ ለራሱ ይቅርና የሱን ፍላጎት ለሚሟሉ ዕውቀተ አልባዎች እንደፈለገው መስጠት ይችላል:: የዚህም ትዝብት ምስክርነት በምርኮት ጊዜውን ላሳለፈ ወታደር ለብርሃኑ ጁላ የፊልድ ማርሻልነት ማዕረግ የሰጠ አምባገነን የዩኒቬርስትን አስተዳደር በማስፈራራት የሰውን ፅሁፍ በመገልበጥ ለምን የዶክቶሬት ድግሪ ለራሱ ማግኘት አይችልም? አምባገነን መሪዎች ስልጣን ላይ የሚቆዩት ማን ፈቅዶላቸው ነው? የአምባገነን መሪ ዋናው መታወቂያው የሕዝብን ፈቃድ ጠይቆ ሳይሆን ያለውን የአገሪቱን ጦር ኃይል እንደ ግል ደህንነት ጠባቂ በመቁጠር በወታደራዊ ጉልበት ስልጣን ላይ መቆናጠጥ ነው:: አምባገነን መሪዎች ስልጣን ላይ የሚቆዩት የማህበረሰብ ሂደቶችንና የአገር ሕዝብን የስነ-ልቦና ተለዋዋጭነትን ለጥቅማቸው በማዋል ነው::

ከጥንት የአመራር ስርዓቶች ሥረመሰረቶች ጀምሮ ፣ አምባገነኖች : በባላባትነት ሆነ : ጎሳዎችን በመምራት ፣ ሃይማኖቶችን ወይም ድርጅቶችን ሆነ : አገሮችን በመምራት ሁልጊዜ ሕዝብን በማጭበርበር ሕዝቦችን እንወክላለን በማለት ወታደራዊ ኃይልን በመጠቀም ሥልጣን ላይ ለመቆየት የማያደርጉት ሻጥር የለም:: እኛ ሕዝቦችም ጠንካራና ጎበዝ ወደ ሚመስሉን ግለሰቦች በመሳብ የችግራችን መፍትሔ ይሆናሉ ብለን በመገመት መሲህ እድርገናቸው እምነታችንን እንጥልባቸዋለን:: እነዚህ አምባገነኖች ይህንን የሕዝብ እምነት በመጠቀም ለሕዝብና ለሀገር ደህንነት ማስጠበቂያ በሚል መሰረት የጦር ኃይልን ለስልጣናቸው ማስጠበቂያ ያደርጉታል። ይህም ወታደራዊ ኃይል የሕዝብ አካል መሆኑን መገንዘብ ተስኖት ለሕዝብ መቆም ትቶ ሕዝቡን ሲገድልና ሲጨርስ በተለያዩ በአምባገንነ አስተዳደር የሚመሩ አገሮች ውስጥ ተደጋግሞ ታይቷል:: እየታዩም ናቸው:: ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰፈነው የአብይ አህመድ አምባገነናዊ አስተዳደር ይህንን ብልሹ አካሄድ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል::

ያለፈው ታላቅነት ይታደሳል በሚል የተሳሳተ እምነትና በምናባዊ የአገር መረጋጋትና ጥበቃ ስሜት አንዳንድ ሕዝቦች ነፃነታቸውን እሳልፈው እንዲሰጡ አምባገነኖች በቀላሉ ያሳምነዋቸዋል:: በጥቅሉ ሲታይ የማህበረሰብ አለመረጋጋት ጊዜዎች ለአምባገነኖች አመራር ላይ ለመውጣት ሁሌም አመቺዎች ናቸው:: የኢኮኖሚ ውድቀትና ድቀት : ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ ትርምስ : አምባገነኖች እንደ አዳኝ (SAVIOR) እንዲታዩና ሁኔታዎች ሲፈቅዱ በመፈንቅለ መንግስት ወይም በሌላ መንገድ ስልጣን እንዲይዙ እድል ይሰጣቸዋል። የእነርሱ ህዝባዊ አራማጅነት የህዝቡን ሰፊ ክፍል ማታለያ ወጥመድ እንደሆነ ሁላችንም በደርግና በኢሐደግ አገዛዝ ዘመኖች ያየናቸው ናቸው:: አሁንም የአብይና የብልፅግና አስተዳደር ይህንን ሕዝብን ማጭበርበሪያ መንገድ በግልፅ እየተጠቀመበት መሆኑን ቀን በቀን በገሃድ እያሳየን ይገኛል::

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የተጋነኑ ቃሎቻቸው ሕዝብን ለማስገረም ከሚባለው ባዶ አነጋገር አይበልጥም። ታዲያ ሥልጣንን እንዴት ማግኘትና ማቆየት ቻሉ ብለን ስንጠይቅ : መልሱ የታወቁ ማህበራዊ ሂደቶችንና ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የስልጣን ጥማታቸውን.ያሳካሉ ነው:: የሀገር ፍቅር : የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጩኸታቸው ህዝቡ መስማት የሚፈልጋቸው ናቸው። ይህን የሚያሳኩት የማረጋገጫ አድልዎን (CONFIRMATION BIAS) መረማመጃቸው በማድረግ ነው:፡ ቀድመው የሚያምኑበትን ለማረጋገጥና ሕዝቦች እንዲቀበሉ ለማድረግ የሕዝቦችን የማመንን ፍላጎት በማፋፋም ረገድ እጅግ በጣም ጎበዞች ናቸው።

ለዚህም የአምባገነን የሽንገላ ንግግር ያለምንም ጥርጣሬና ጥያቄ ተቀባይነትን የሚያገኘው በሰው ልጅ እጅግ በጣም በተስፋፋው የማረጋገጫ አድልዎ (CONFIRMATION BIAS) ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ነው። ይህም ተቃራኒ መረጃዎችን ከቁጥር ሳናስገባ ሀሳባችንና ፍላጎታችንን የሚደግፍ ማስረጃ እንድንፈልግ ያስገድደናል። እንዲህ ዓይነቱ አድልዎ የዓለማችንን ውስብስብነት ቀላል ከማስመሰል በተጨማሪ ግብ ላይ ያላተኮረ የአስተሳሰብና የአመለካከት ስንኩልና መስሎ ሊታይ ይችላል:: አምባገነኖች በአስመሳይነት የተካኑ ስለሆኑ ይህንን ሁለንተናዊ የግንዛቤ አቋራጭ መንገድ ይጠቀማሉ።

አምባገነኖች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ለችግር ተጋላጭ የሆነውን የማህበረሰብ ክፍል ኢላማ ማድረግ ላይ ጥሩ ችሎታ አላቸው:: ሁልጊዜ በደንብ ያልተማሩትን ወይም በቂ መረጃ የሌላቸውንና ብዙውን ጊዜ ግራ በመጋባት በራስ የመተማመን ስሜት የማይሰማቸውን በሚፈልጉት የማሳመን ወጥመድ ውስጥ ከተው ሕዝብ ደግፎናል በማለት ስልጣን ላይ መውጣት የአምባገነኖች ትልቁ ሻጥር ነው። አምባገነኖች የህዝብን ቁጣና ብስጭት እንደገደል ማሚቱ በማስተጋባት ከተጎዳው ጋር ቆመናል በሚል ስነ-ልቦናዊ ሂደት ይጠቀማሉ:: ጉልበት ወይም አቅም የለንም ብለው የሚያስቡ ብዙ ሰዎች በጠንካራ ወንድ ወይም ሴት ውስጥ የራሳቸውን ነፀብራቅና በደከመውና በወደቀው ሀገራቸው ላይ የድል ተስፋን ያያሉ። እነዚህም እኛ ችሎታም ሆነ አቅም የለንም ብለው የሚያስቡ ራሳቸውን አሳንሰውና ጥለው ተፈጥሮ የሰጣቸውን እምቅ ችሎታና ኃይል መገንዘብ ተስኗቸው በቅዠት የተሞላ አስተሳሰብ ውስጥ የተዘፈዘፉ ናቸው:: አእምሮአቸው የግል አስተሳሰብ እንዳይፈጥር አምባገነኖች በሚረጩት የማጭበርበር ዲስኩር ይበረዛል።

የአምባገነኖች ሌላው የስልጣን መውጫ እቅድ የወቀሳና የውንጀላ ጨዋታ ነው፡: የማህበረሰቡ ጥፋት ምንም ይሁን ምን አምባገነኖች ተወቃሽ የሚሆነውን ፈልጎ በዚያ ላይ ሕዝብን በመቀስቀስና በስህተት መወንጀል ላይ እጅግ የተካኑ ናቸው። ከፋፍለህ አጥቃ የሚለውን ጥንታዊ የማጥቂያና የመከላከያ ዘዴን በመጫወት ስልጣን ላይ ይወጣሉ:: ከዚያም ያንኑ የሻጥርና የተንኮል መንገድ በመጠቀም ስልጣን ላይ ለመቆየት ሹር ጉድ ይላሉ:: ጉዳዮችን በቡድን በመለየት በውስጥና በውጪ ጠላት አንፃር በማስቀመጥ የውስጥ ጠላት ተብሎ የተፈረጀው የውጭ ጠላት ወኪል ነው ተብሎ በመወንጀል የውጭ ስጋቶችን አጉልተው ሕዝባዊ ፍራቻ የተሞላበት ውዥንብር እንዲስፋፋ ያደርጋሉ። ዛሬ ኢትዮጵያን የሚመራው የአብይ አህመድ ብልፅግና እየሰራ ያለው ይህንኑ ነው:: ከዚህም በተለይ እጅግ እፍረት በሌለው መንገድ አምባገነኖች በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚረዳቸው ሻጥራቸው የማይቋረጥ የእርስ በርስ ጥላቻ በዜጎች መሃል መፍጠር ነው:: የኦሮሞን ጎሳ በሌሎች ተጠልተሃል በማለት እያደናበሩት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ በመለየት ደጋፊው እንዲሆንና የአብይ እህመድን : የሽመልስ አብዲሳን : የአዳነች አበቤንና የኦሮማማን ፅንፈኞችን የስልጣን ጥማትን ማርኪያ መሳሪያ እያደረገው ይገኛል:: ትውልደ ኦሮሞ ያልሆነው የኢትዮጵያ ክፍል መጠንቀቅ ያለበት የኦሮሞን ሕዝብ በጎሳ ለይቶ በመውቀስና በመስደብ ለእምባገነኑ የኦዴድ ብልፅግና ፕሮፓጋንዳ መንገድ እንዳይከፍት ነው:: አብይና የኦዴድ ብልፅግና ስግብግቦችና የጥላቻ መርዝ እረጪዎች ሁለት ምላስ እንዳላቸው ደጋግመው አስመስክረዋል:: ይህም በኦሮምኛ ሲናገሩ መልክታቸው ኢትዮጵያን ለማሳደግ : አንድነቷን ለመጠበቅና ለማዳን ሳይሆን ኦሮሚያን የአፍሪቃ ትልቁ ኢኮኖሚና ሸገርን በኦሮሚያ የአፍሪቃ አንደኛ ከተማ ለማድረግ ያላቸውን ቅዠት በተደጋጋሚ አሰምተውናል:: በአማርኛ ሲናገሩ ኢትዮጵያውያን ነን:: ኢትዮጵያን ካለችበት ረመጥ (በድንቁርናቸውና በጎሰኝነታቸው ከከተቱበት) ውስጥ እናድናለን ነው::

እንደምታዩትና እንደምትሰሙት አምባገነኖች ራሳቸውን እንደ ፅኑ አገር አዳኝ (SAVIOR) አድርገው ያቀርባሉ። በቀላሉ ሲታይ ይህ ሻጥራቸው ሁለትዮሽ ሃሳቦች ያንፀባርቃል:: በአንድ በኩል እነሱ አገር አፍራሽ ናቸው ብለው ለሚያቀርቡት የውሸት ትረካ ተከታዮቻቸውን የመልካም ትግል አጋር ናችሁ በማለት ሲደልሉ ተቃዋሚ ናቸው ብለው የሚያስቧቸውን ሰዎች አለመታገስና ማጥፋትን ዋና ዓላማቸው ያደርጋሉ:: በአብይ አህመድ አምባገነናዊ አመራር ሂደት እነዚህን የከፋፍለህና የለያይተህ አመራርን አካሄዶች እናያለን:: በአንድ በኩል በጎሳና በፖለቲካ አመለካከት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ በአጋሮቹ በኩል ሲያራምድ : በተመሳሳይ በጎሳና በፖለቲካ አመለካከት ጠላት ብሎ የፈረጃቸውን በጦርነት ሊያጠፋቸው እየሰራ ይገኛል::

አምባገነኖች በውሸት የማሳመን ጌቶች ናቸው፡: አምባገነኖች ሰዎችን የማሳመንን ዋጋና ጥቅም ጠልቀው መማር ለስልጣን መውጫ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ቀድመው በመረዳት ለዘመናት ይዘጋጁበታል:: በውሸት ዲስኩሩ ማሰራጫ እርዳታ የተነሳ አምባገነኖች የሁሉም ሰው ህይወት አጠቃላይ አካል ይሆናሉ:: ያለእነሱ ሕዝብም ሆነ አገር አይሻሻልም : አይራመድም:: ያለእነሱ በረከት ብልፅግናም ሆነ ሰላም አይገኝም የማለት እምነት አላቸው:: ይህንንም በአገራችን ኢትዮጵያ በተለይም አብይ አህመድ ዛሬ ላለበት የስልጣን መቆናጠጥ እንዴት እንደሚዘጋጅ እንደነበረ ደጋግሞ በነገረን ትረካና በየቀኑ በሚለፈልፈው ልንገነዘብ እንችላለለን:: የሚገርመው ነገር አምባገነኖች ምን ያህል በከንቱ ስሜት ውስጥ ተዘፍቀው እንዳሉ ያለመገንዘባቸው ነው::

አምባገነኖች የስልጣን ዘመናቸውን ለማቆየት፣ ሁሉንም ዋና ዋና ሚዲያዎችን ማዕከላዊ በማድረግ መረጃን ይቆጣጠራሉ። ይህንንም ሃቅ ዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝብ ሚዲያዎች የሚባሉ የቴሌቪዥን : የሬዲዮና የፅሁፍ ሚዲያዎች እንዴት የብልፅግና የስልጣን ማራመጃ ልሳኖች እንደሆኑ በጋህድ እያየን እንገኛለን:: አወንታዊ ዜናዎች የአምባገነን ማድነቂያ ሲሆኑ አሉታዊ ዜናዎች የመንግስት ጠላቶችና አገር አጥፊዎች ተብለው የተፈረጁ አገር ወዳዶችና ዲሞክራሲ አራማጂዎች መገለጪያ ናቸው። የሚዲያ አውታሮቹ ብቻ ሳይሆኑ የሚዲያው ሰዎችና ጋዜጠኞች ገለልተኛ መሆን ትተው የአምባገነኑ አስተዳደር መሳሪያና አፈቀላጤዎች ሆነው ይገኛሉ:: ጥሩ ምሳሌ የምናደርገው እርግጠኛ ስሙን ማስታወስ የማልችለው የሕዝብ ሚዲያ የሆነው ሰራተኞች ለአዳነች አበቤ በቢሮዋ ሄደው አበባየሁሽ ማለታቸው ምን ያህል የአብይ አስተዳደር አምባገነንና አመስግኑኝ ባይ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል::

ይህ መሪ የዛሬ 5 አመታት በዓለም እየዞረ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ በማለት ሁላችንም ስናልምና ስንመኝ የነበረውን ኢትዮጵያዊነትን ሲሸጥልን ከርሞ ከሶስት ዓመት በሗላ ወያኔን አገር አጥፊ ነው በማለት ጦርነት ጀምሮ : አገር እናድን በሚል ጥሪ ኢትዮጵያውያንን አማራውን ጨምሮ በማሰለፍ ወያኔን ካሸነፈ በሗላ : አማራን ለመውጋት የወሰደው እርምጃ አባርቆበት የአብይን አስተዳደርንና የብልፅግናን አምባገነንነትን አጋልጦ እያሳየ ይገኛል::

ሌላው አምባገነኖች በስልጣን ላይ በመቆየት የስልጣን ጥማታቸውን ማርኪያ መንገድ : በምርጫ ወቅት የፕሬስ ነፃነትን በመገደብ የተቃዋሚዎችን የምርጫ ቅስቀሳ አቅም በመገደብና የተሳሳቱ መረጃዎችን ማለትም የውሸት ዜና (FAKE NEWS) በማሰራጨት የመጨረሻውን ውጤት መቀልበስ ወይም እነሱ አሸናፊ ሆነው መታየት ነው:: አምባገነኖች ማህበራዊ ማዕቀፎችንና እንደ ተቃዋሚ ሃይሎች የሚያገለግሉ ተቋማትን ለመገደብ ወይም ለማጥፋት ይሞክራሉ። ይህንን የአምባገነን የስልጣን መቆያ እርምጃ በአገራችን በአብይ ዘመን ባናየውም : በሚቀጥለው ምርጫ ወቅት አይከሰትም ብዬ ለመገመት አልደፍርም:: ጊዜው ደርሶ የአብይ ብልፅግና መንግስት ይህንን ዓይነት እርምጃ ካልወሰደና ዲሞክራሲያዊ አሰራርን በገሃድ ካሳየን ቀደም ብዬ ስሙን ስላጎደፍኩ በሁሉም ሚዲያዎች ታላቅ ይቅርታ እጠይቀዋለሁ:: እሱ ዲሞክራሲንና የሕዝብን ፍላጎት አክብሮ ከጠበቀ እንደ ታማኝ በየነ እሱ ሳይለምነኝ: እኔ ለምኜው ለይቅርታው በአሮጊትነቴ እግሩ ላይ እወድቃለሁ::

አምባገነንነት የባህሪዎች ውጤት ነው:: የባህሪያቸው ቅንብር ለአምባገነንነት የሚያበቃቸው ሰዎች ይኖራሉ። ብዙ ያለፉትና የዘመኑ አምባገነኖች ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛና ጤናማ ያልሆነ ራስን የማምለክ (NARCISSISM) ፍላጎት አለባቸው:: አንዳንዶንቹ ደግሞ በተጨማሪ በአእምሮ በሽታና (PSYCHOPATH) ሌሎችን ባለማመን በጥርጣሬ (PARANOIA) ተሞልተው ይሰቃያሉ። ለራሳቸው ከፍ ያለ ግምት ስለአላቸው የሌሎችን አድናቆት የማግኘት መብት ይሰማቸዋል:: ለዚህም የሌላቸውን ችሎታና ዕውቀት አለን : ያልተማሩትን ተምረናል በማለት የሌላቸውን የትምህርት ደረጃ ውሸት በተሞላበት ምስክር ወረቀቶችና ዲግሪዎች ሊያስመሰክሩ ይሞክራሉ:: በራሳችን አገር መሪ በአብይ አህመድ ሰሞኑን በተነሳበት የትምህርት ደረጃው ጥያቄ ይህን ራስን የመካብ ዝንባሌ ማየት ችለናል:: ይህ በውሸት ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ የአምባገነኖች ባህሪይ እንደሆነ ያሳሳስበናል::

በሰብዓዊነት መነፅር ስናይ : አምባገነኖች ግፈኞችና ጨቃኞች ለመሆናቸው ምንም አያጠራጥርም:: የሰው ሕይወት መጥፋት የማያሳዝናቸውና የማይቆረቁራቸው ናቸው:: የርኅራኄ ማጣት የጥፋተኝነት ወይም የፀፀት እጦታቸው እጅግ በጣም ተንኮለኛና ሊነገር የማይችል ግፍ እንዲፈፅሙ ያስችላቸዋል። ይህንን አስከፊ አረመኔነት በመንግስቱ ኃይለማርያም አመራር በተለይ በቀይ ሽብር ወቅት በአገር ቤት ውስጥ የነበሩት ፀረ-ደርጎች ያስታውሳሉ:: ዛሬም የአብይ አህመድ መንግስት በጦርነት ሰበብ የሚፈፅመውን የሕዝብ ፍጅትን አግባባዊ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ይመስላል:: በእርግጥም አብይ አህመድ ለሰው ሕይወት ርህራሄ ቢኖረውና ቢሰማው ኖሮ በአማራ ሕዝብ ላይ ያወጀውን ጦርነት “አንድ መቶ ሺህ ሰዎች አስጨርሰንም ቢሆን ጦርነቱን እናሸንፋልን” ባላለ ነበር:: ታድያ ለአምባገነኖች ተጠያቂው ማነው?

ምንም እንኳን አምባገነኖችን ስማቸውን ማጉደፍና መሳደብ ቀላል ቢሆንም፣ በብዙ መልኩ ወደንም ሆነ ተገደን ድርጊታቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመደገፍ እኛው ሕዝቡ ራሳችን ግፋቸውን እንዲፈፅሙ ያስቻልናቸው መሆናችንን ልንገነዘብ ይገባል። ለነገሩ አምባገነኖች ያለ ተከታዮች ሊኖሩ : ሊሰሩና ሊጠናከሩ አይችሉም። ጮክ ብለን ባንቀበልም ሌሎች ሰዎች ትክክልና ስህተት የሆነውን እንዲነግሩን ማድረጉ ይማርከናል። ነገር ግን የግል ሃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ሀሳብን በነፃነት ለመግለፅ ያለንን ችሎታና የዴሞክራሲ ሂደቶችን ያሰናክላል። ማወቅ ያለብን መልካሙ ዜና ግን አምባገነኖችን በድጋፋችን እንዲቆሙ እንደምናስችላቸው ሁሉ : ግፋቸው ሲበዛ እነሱን አሰናክለናቸው የመጣል ችሎታ እንዳለን እንደ ሕዝብ መገንዘቡ ነው። ይህም ሊከናወን የሚቻለው የአገርን ሕዝብ መብታቸውንና ግዴታቸውን ተረድተው የተቀበሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው መራጮች ስናድርግ ብቻ ነው::

በብዙ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በአቋቋሙ አገሮች የአምባገነንነት ማንሰራራት የምር ሥጋት እየሆነባቸው ነው። ይህም ሥጋት ሁለት አስቸኳይ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው:: በሂደት ላይ ያሉ አምባገነኖች ሊፈወሱ ይችላሉ? አምባገነኖች ስልጣን እንዳይይዙ ማድረግ እንችላለን? ለመጀመሪያው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ “አይሆንም” የሚል ስጋት አለኝ:: የታሪክ ልምዶችም ደጋግመው ይህንን አረጋግጠውልናል። ከክሊኒካዊ እይታ አንፃር ስንቃኘውም : አብዛኞቹ የሥነ ልቦና ባለሙያዎች አምባገነኖች (በሥነ ልቦና ባህሪያቸው) ሊታከሙ እንደማይችሉ ያምናሉ። ስለዚህ ወደ ስልጣን እንዳይወጡ እንዴት መከላከል እንደሚቻል ሁለተኛውን ጥያቄ ለመፍታት ብዙ ተቃዋሚ ኃይሎች ያስፈልጋሉ።

ለማዳን ከመሮጥ አስቀድሞ መከላከል ይሻላል እንደሚለው: አምባገነኖች ስልጣን ይዘው ሕይወታችንን ከማበላሸታቸውና ከማጥፋታችው በፊት የአባምገነንነት እምቅ ኃይላቸውንና ባህሪያቸውን ተረድተንና ተገንዝበን በመገኘት ለዲሞክራሲ ዘበኝነት መቆም ይኖርብናል:: አንዴ ስልጣን ከያዙ ከዚያ በሗላ ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ይተረትብናል። ይህንንም አቢይ አህመድና ብልፅግና ፓርቲ በማያዳግም ሁኔታ እያስተማረን ይገኛል:: የእምባገነንነት እምቅ ኃይሉንና ባህሪውን በሚገባ ደብቆ መጥቶ አታሎናል:: የተለያዩ አመለካከቶችን የሚያዳምጥና አሻሚ ጉዳዮችን በሚገባ ይዞ መቆጣጠር የሚችል ሕዝብ ውስጥ ጤናማ ዲሞክራሲ ቦታ ይኖረዋል:: እንዲሁም ምርጫ የእኔ ግዴታ ሳይሆን የሌሎች ጉዳይ ብሎ የሚያምነውን ሳይሆን ዕውቀት ያለውን: የተሰባሰበንና የተረዳውን መራጭ ሕዝብ ይመለከታል:: አምባገነኖች ወደ ፊት ስልጣን እንዳይዙ ለመከላከል ለነፃነት የሚቆረቆርና ለነፃነት ኃላፊነት የሚወስድ ህዝብ ይጠይቃል። በተጨማሪም መንግሥት : ርዕሰ መስተዳድሩ : ሕግ አውጪው አካል : ፍርድ ቤቶች : የዜና ማሰራጫዎችን መራጮች ነፃ ሆነው ዲሞክራሲ እንዲያድግና እንዲያብብ አፀፋዊ ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው።

ታዲያስ እንዴት ለተሻለ ዓለም እንታገል ብለን ስንጠይቅ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በሗላ እንደ እውሮፓውያን እቆጣጠር በ1940 የተሰራውን የቻርሊ ቻፕሊንን ፊልም እንድናስታውስ ያደርገናል:: በ 1940 The Great Dictator በተባለው ፊልም ላይ ቻርሊ ቻፕሊን አይሁዳዊ ፀጉር አስተካካይ ሆኖ በመጫወት ላይ እያለ የተሳሳተ ማንነት ባለው ሁኔታ የልበወለዳዊ ቶማይኒያን አገር ፈላጭ ቆራጭ ገዥ በመምሰል ተገዶ ናዚዝምንና (NAZISM) አዶልፍ ሂትለርን በምፀት አቅርቧቸዋል::

በፊልሙ መገባደጃ ላይ ቻፕሊን ህዝቡ ተባብሮ አምባገነንነትን እንዲታገል ንግግር ይሰጣል፡: “እናንተ : ህዝቦች : ይህንን ህይወት ነፃና ውብ ለማድረግ ኃይል አላችሁ:: ህይወትን አስደናቂ ትንግርት ለማድረግ : በዲሞክራሲ ስም ያለንን ኃይል እንጠቀም:: ሁላችንም በአንድነት እንሰለፍ:: አምባገነኖች ራሳቸውን ነፃ አውጥተው ህዝብን በባርነት ይገዛሉ። ዓለምን ነፃ ለማውጣት፣ ብሔራዊ መሰናክሎችን ለማስወገድ : ስግብግብነትን : ጥላቻንና አለመቻቻልን ለማስወገድ እንታገል።”

እንደ አለመታደል ሆኖ፣ እኛ ቻፕሊን ከገለፀው ዓለም ርቀን እንገኛለን። ብዙዎቹ የአሁን የዓለም መሪዎቻችን የዲሞክራሲ ሂደቶችን አደጋ ላይ ለመጣል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ጠባብ ብሔርተኝነት : የውጭ ዜጋ ጥላቻ : ስግብግብነትና የማይታሰብ ጥቃት በየቦታው ይታያሉ። ይህም ዛሬ በዓለማችንና በኢትዮጵያ አገራችን ያሉት ሰው በላሽ አምባገነናዊ ስርዓቶች በቻፕሊን የታሰበውን ዓይነት ዓለም ለማግኘት መጣርን የበለጠ ወቅታዊ ያደርገዋል።

አሳልፈን የሰጠነውን ነፃነት ከራሳችን በስተቀር ማንም አያስመልስልንም:: ለደህንነት ተብሎ ነፃነትን አሳልፎ የሰጠ ደህንነትም ሆነ ነፃነት አይገባውም:: ከሕዝብ የተጣላ አምባገነን : ሕዝብን ይገላል እንጂ አያሸንፍም:: ድል ምንጊዜም የሕዝብ ነው::

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

የኦህዴድ መራሹ ብልፅግና  መንግስት  በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በንጹሀን  ዜጎች ላይ እየወሰዳቸው ያሉ የነፃ እርምጃ  ግድያዎች  መንግስት ያሰበውን የፖለቲካ ግብ ያሳካለታል  ወይ ? በኔ አመለካከት እነዚህ የንፁሃን ዜጎች  የጅምላ ግድያዎች  በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላዎ (double edge sword) ናቸው:: ፩- መንግስት እያሰላው

 የኦህዴድ መራሹ ጅምላ ግድያዎች ስሌት (ሸንቁጥ- ከምዕራብ ካናዳ)

January 24, 2025
እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

Go toTop