የዝቅጠት፣ የሰብእና የህሊና እውርነት ጥግ! – ነአመን ዘለቀ

ተጠያቂነትና ግልጽነት የሌላቸው የጠ/ሚንስትሩ የቤተ መንግስት ግንባታና፣ የቅንጦት ፕሮጄከቶች 850 ቢሊዮን ብር (15 ቢሊዮን $) እንዲሰረዝ፣ የሚሊዮኖች ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት እንዲሟላ መሞገት፣ መታገል ያስፈልጋል። ለውጭ መንግስታት፣ ተቋማት መሞገት፣ ማቅረብ አለብን። አገዛዙ 2 ቢሊዮን $ ከአለም ባንክ ብድር ይለምናል፣ በአጻፉ ደግሞ በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ሚሊዮኖች በቂ ትኩረት አይሰጥም፣ በመቶ ሺዎች ያፈናቅላል፣ ለልመና ይዳርጋል፣ በየመጠለያው ያስርባል። በሌላ በኩል ደግሞ የ 15 ቢሊዮን ዶላር+ ቤተ መንግስት ግን ይገነባል። የዝቅጠት፣ የሰብእና የህሊና እውርነት ጥግ !

የውጭ ብድሮችና ኢኮኖሚያዊ እርዳታዎች ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ በውጭ የምንገኝ ሀገር ወዳዶች ሁሉ መታገል፣ መሟገት ወቅቱ የሚጠይቀው ሰላማዊ የትግል ስልቶች አንዱ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎች– ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ሰብአዊ መብቶች፣ፍትህ፣ የህግ የበላይነት- እንዲከበሩ እንዲረጋገጡ ተደራጅተን፣ ተናበን መሞገት መታገል አለብን።

የኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች-መጠለያ፣ ምግብ፣ ንጹህ ወሃ፣ መብራት፣ ለመሰረት ልማት- የብድሮችና የእርዳታዎች ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሆኑ መታገል፣ መሟገት የትግሉ አካል ነው፣
በጠ/ሚኒስትሩ አይዞህ ባይነት በኦሮሞ ብልጽግና መሪ ካድሬዎች የሚዘወረው፣ ኢ-ሕገ-መንግስታዊነት፣ጋጠ ወጥነት፣ ምዝበራና ሙስና፣ ሰፊ አፈና እና ሰብአዊ መብቶች ረገጣ፣ ነቀላና ፍንቀላ በአግባቡ ተሰንዶ፣ ለመንግስታት ለአለም አቀፍ ተቋማት ማቅረብ።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገኝበትን አስከፊና፣ አስቆጪና አሳዛኝ ሁኔታ ቁብ የማይሰጣቸው በኦሮሞ ብልጽጋና የሚጋለቡ የዲጂታል ካድሬዎች መራሩን ሃቅ እይዋጥላቸውም። እንደ አለቆቻቸው ሞራለ አልቦ ስለሆኑ እእምሮና ህሊና እከራይተው የተጻፈላቸውን ይለጥፋሉ።

ኢትዮጵያን ከመፍረስ የመታደግ ጥሪ!

“ለውጥ”ተብሎ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ  በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቀናነት ለማገልገል ጥረት አድርገዋል። በጦርነቱ ወቅት ከወገኔ ጋር ሞቸ አገሬን አድናለሁ ብለው ከሚኖሩባቸው አገራት ወደኢትዮጵያ በመሄድ አገራቸውን በቁርጥ ሰዓት አገልግለዋል። በዲፕሎማሲውና ሌሎች ዘርፎች ለአገራቸው በርካታ እገዛዎችን አድርገዋል። ይሁንና በለውጥ ስም የቡድንና የግለሰብና የቡድን ስልጣንና ጥቅምን ለማባከን ሲል ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው የሚያደርጉትን እገዛ በዜሮ እያባዛ አገርን ለማፍረስ እየሰራ ይገኛል። የሰላም ስምምነት በተደረገ ማግስት ሌላ ጦርነት ከፍቶ ህዝብን እያሰቃየ ይገኛል። በኃይማኖት ተቋማት እጁን አስገብቶ ለማፍረስ እየሰራ ነው። በአዲስ አበባና በአካባቢው በንፁሃን ላይ የሚፈፀመውን ዘግናኝ ወንጀል በከተሞችም የዘር ፍጅት ሊፈፀም እንደሚችል አስደንጋጭ ምልክት ነው። በእውር ድንብስና የራስን ቡድን ለመጥቀም ብቻ የሚያደርገው አካሄድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ምስቅልቅል ውስጥ አስገብቶታል። የራሱን ኢኮኖሚ ጥቅምና የገንዘብ ፍላጎት ለማሟላት አገራዊ ተቋማትን ባልተጠና መልኩ እየሸጠ ይገኛል። የመንግስት ሹማምንት በአገር ሀብት የቅንጦት ጥቅማጥቅም በሚጨመርላቸው በዚህ ወቅት ሰራተኛው ከዚህ ግባ በማይባል ገቢ የችግር ህይዎትን እየመራ ነው። የመንግስት የቅንጦት ድግስን በየጊዜው በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት ለህዝብ እየቀረበ፣ በርካታ ዜጎች ኑሮን መሸከም አቅቷቸው ጎዳና ላይ ወድቀዋል። በአገር ውስጥ የሚደረገው ጦርነት አልበቃ ብሎ የጎረቤት አገር ጋር ወደ ግጭት ለመግባት በየመድረኩ ፉከራዎች ተጧጡፈዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጢስ አባይ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ካምፕ በቁጥጥር ስር ተደረገ፥ ባህርዳር በየትኛው ሰዓት በህዝባዊ የፋኖ ሃይል....

የብልፅግና መንግስት በኢኮኖሚው፣ በግጭት፣ ዜጎችን በማሰቃየት፣ አገራዊ ተቋማትን በሴራ የማፍረስና ሌሎች አደገኛ አካሄዶች አገር ለማፍረስ እየሰራ እንደሚገኝ አረጋግጧል። ይህ የብልፅግና ተግባር አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሊታገሉት የሚገባ ሲሆን በውጭ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያንም ከብልፅግና ጋር ባለመተባበር  ብሎም ጫና በማድረግ አገርን ለማዳን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ይገኛሉ።  የብልፅግና መንግስት ለግልና ለቡድን ጥቅምና ስልጣኑ የውጭ ምንዛሬን አብዝቶ የሚፈልግበት ጊዜ ላይ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ይህን በመገንዘብ ተገቢውን እርምጃ የሚወስዱበት ጊዜ ነው።  ከውጭ እርዳታና ብድር ከሚያገኘው  ዶላር በቁጥሩ ከፍ ያለውን የሚያገኘው ከዳያስፖራው እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሁንና ይህ ሁሉ የውጭ ምንዛሬ የሚውለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለማያስፈልጓቸው ወሳኝ ጉዳዮች ሳይሆን ለብልፅግና መንግስት  የግለሰብና ቡድናዊ ጥቅምና ስልጣን ነው።

በአሁኑ ወቅት የአገርን ኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ ያስገባው ብልፅግና ብድርና እርዳታን እንዲሁም ከዳያስፖራው የማገኘውን ዶላር የሚጠቀምበት ለባለስጣናቱ ቅንጦት እንጅ ለወደቀው ኢኮኖሚ ማገገሚያ እንዳልሆነ በበርካታ መረጃዎች የተረጋገጠ ሀቅ ነው። በአርሶ አደሩ ማዳበሪያ፣ ለህፃናትና እናቶች መድሃኒት መግዥያ መዋል የነበረበት የውጭ ምንዛሬ ለባለስልጣናት ስልክ መግዥያ፣ ውጭ አገር ሄደው መታከሚያ፣ ለልጆቻቸቸውና ቤተሰቦቻቸው የውጭ ትምህርት  ወጭ የሚውል ሆኗል። በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መገንባት ሲገባ የብልፅግና ባለስልጣናት በእርዳታና ብድር በአገር ስም የተገኘን ገንዘብ በአሻጥር ወደ ውጭ አገር እያሸሹ እንደሚገኙም መረጃዎች አሉ። በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያ ጫና ሲደረግባት በዲፕሎማሲው ከመታገል አልፎ በጦርነቱ ምክንያት ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ በውጭ ምንዛሬ ወደ አገር በመላክ ሲያግዙ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እንደ ጠላት ተቆጥረው፣ በጦርነቱ ወቅት ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተቃራኒ ሆነው ኢትዮጵያን ሲወጉ የነበሩት ፀረ ኢትዮጵያ ተላላኪዎች ከየሚኖሩበት አገር ተጠርተው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተዝናኑና ጥቅማጥቅም እየተሰጣቸው ያለው ለአገር ኢኮኖሚ ማገገሚያ መዋል ከነበረበት የውጭ ምንዛሬ ተቆንጥሮ ነው። ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የሚላከው ገንዘው በንፁሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ለተከፈተው ጦርነት ጥይት መግዥያ፣ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ለማጥላላት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚሰራ የብልፅግና ፕሮፖጋንዳ እየዋለ ይገኛል። በጥቅሉ  የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ለቤተሰቦቹም ሆነ ለአገሩ የሚልከው የውጭ ምንዛሬ ለሚፈለግለት አላማ ሳይሆን ለስርዓቱ የአገር ማፍረስ ፕሮጀክት እየዋለ ይገኛል። የብልፅግና መንግስት ብር እያተመ በጥቁር ገበያ ጭምር ዶላር እየገዛ ኢኮኖሚውን ምስቅልቅሉን አውጥቶታል። ለአገሩ ህልውና፣ ለህዝቡ ደህንነት  የታገለ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ በትንሹ የብልፅግና መንግስት ለሚያደርገውን የአገር ማፍረስ በዶላር ባለማገዝ፣ ከፍ ሲል ደግሞ በዲፕሎማሲና ሌሎች ጫናዎች አገር አድን ትግል ማድረግ ይጠበቅበታል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በዛሬው ዕለት በናዝሬት ከተማ የማስተባበሪያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱን መክፈቱን አስታውቋል

አገር ወዳዶች ለህዝብና ለአገራቸው ብለው የሚልኩትን ገንዘብ ህዝብን መጨቆኛና አገር ማፍረሻ እንዲያደርግ የማይፈቅድ ከመሆኑም በላይ የሚላከው ዶላር ብልፅግና ያበላሸውን ኢኮኖሚ ከማዳን ይልቅ ይቀልጥ የከፋ እያደረገው የሚገኝ በመሆኑ ዳያስፖራው በቀናነት ለአገርና ለህዝቡ ብሎ የሚልከው ገንዘብ የዘር ጭፍጨፋና አገር ለማፍረስ ግብአት እንዳይሆን ደግሞ ደጋግሞ ሊያስብበት ይገባል። በቀጣይ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር የአፈፃፀም ሁኔታዎችን የምናቀርብ ሲሆን ለጊዜው ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ ለህዝባችን መፍትሄ ከማምጣቱ ይልቅ መጨፍጨፊያው፣ የአገር ኢኮኖሚን ከማገዙ ይልቅ የብልፅግናን የቡድን ማፊያ  አካሄድ አግዞ የአገር ኢኮኖሚን የሚጎዳ፣ ከህፃናትና እናቶች መድሃኒት፤

ከአርሶ አደሩ ማዳበሪያ መግዥያ ተመጥቆ ለጦርነትና የዘር ጭፍጨፋ መደገፊያ እያገለገለ መሆኑን በመረዳት ለአገርና ህዝባችን ማነቂያ ገመድ እንዳናቀብል እንድናስብበትና አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንድንወስድ አስፈልጓል። በጉዳዩ ላይ በርካታ አገር ወዳድና በሙያው የተካኑ ኢትዮጵያውያን ጭምር የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተዋቅሮ እየሰራ ሲሆን እጃችን ላይ ባለው በዚህ መሳርያ አገር እንዳይጠፋ፣ ህዝብ እንዳይጨፈጨፍ ጥንቃቄ አድርገን፣ አገር እያፈረሰ ያለውን የብልፅግና ኃይል ተገቢ ትምህርት ልይሰጥበት ይገባል።

2 Comments

  1. ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም! እውነት ይሄ ከአቶ ነአምን ነው? አይቃወሙ አይደለም፣ እንደው በሳቸው ደረጃ ያለ ሰው ተቃውሞውም ድጋፉም ከጥግ ጥግ ቢሆንብኝ ነው። ከመንግስት ወገን ስህተት/ጥፋትም ቢኖር [ደግሞም አለ!] በቅድሚያ ያላቸውን ግንኙነት ተጠቅመው “ምነው አቢይ? እንዲህ ነው እንዴ የተባባልነው?” ብለው ትንሽ ቢሞክሩ ጥሩ ነበር። አርገውትም ይሆናል፣ ግን አልነገሩንም። እንደው ለመሆኑ አቶ ነአምን በሚኖሩበት ሃገር ሥራቸው ምንድነው? ማለቴ what do you do for living? ብንላቸው ምን መልስ ይሰጣሉ?
    በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ለማስገንባት ህዝቡ ገንዘብ እንዲያዋጣ ቅስቀሳም/ትዛዝም ተላለፈ አሉ። ታዲያ በጊዜው ንጉሱን የሚቃወሙ “ተራማጆች” ምን ብለው ቀሰቀሱ መሰላችሁ፣ “ንጉሱ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው መታከሚያ ፈልገው ነው እንጂ ሰፊው ደሃው ህዝብማ በምን አቅሙ?” ብለው። አይፈረድባቸውም፤ ምናልባትም ንጉሱ ሆስፒታሉን በልጃቸው ልኡል መኮንን ስም ስለሰየሙትም ጥርጣሬው ክፋት የለውም። በተለይ በዚያን ወቅት። ታዲያ አስቡት ከረዚም አመታት ጀምሮ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባይኖር [በተለይ በደርግ አመታት!] እንዴት እንሆን ነበር? አባቴ ነው የነገረኝ።
    ሆስፒታል እና ቤተመንግስት ለየቅል ቢሆኑም፣ መሪዎች በዘመናቸው የሚያደርጉትን ሁሉም ሰው ይደግፋል ማለት አይደለም። ጥቁር አንበሳ ፊት ለፊት ባለው ሃውልት አጠገብ ሲያልፍ የሚያመው ሰው አለ እኮ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን በመጥላት! ያሁኑ ትውልድስ? የካራመራን ድል ያከብርበታል። የአቢይ አህመድ ፕሮጀክቶችም ወደፊት በታሪክ ከዚህ የተለየ እጣ አይገጥማቸውም። እናም አቶ ነአምን፣ “አቢይ የቅንጦት ቤተመንግስት ሰራ” ብሎ መክሰሱ ግፋ ቢል የቤተ መንግስት ስራውን ያስቀረዋል እንጂ ለደሃው የሚጠቅመው ምንም ነገር የለም። እንዲያውም ብዙ ሰዎች የገቢ ምንጭ ያጣሉ። ቀላል ነው፣ የቤተመንግስቱን ስራ ወጪ የሚሸፍኑት “እንዴ ገንዘቡን እኮ የሰጠንህ ለቤተ መንግስት ሥራ ነው” ይላሉ። ባይሆን ሰጪው ማነው? እንዴት? ለምን? የሚለውን ጠሚው እንዲነግሩን ጫና ማድረጉ አይከፋም።
    “ዶላር አትላኩ” ላሉት፣ “በባንክ በኩል አትላኩ” ብለው ቢያስተካክሉት ይሻላል። ምክንያት አብዛኛው ዲያስፖራ ገነዘብ የሚልከው በጥቁር ገበያ ነው። ኑሮውንም ያስወደደብን አንዱ ይሀው የዲያስፖራ ድርጊት ነው። ሌላው ደግሞ አሁን አሁን አዲስ አበባ ላይ የወላጆቹን ትንሽ የከተማ መሬት የሚወርስ ዲያስፖራ እድሜ ልኩን ዉጭ አገር ያላገኘውን ገንዘብ ያገኛል። እናስ? ብሩ በጥቁር ወደ ዶላር ተመንዝሮ ባለበት ሃገር ላይ ሞርጌጅ ይዘጋበታል። ዲያስፖራ ሃገሩን ለራሱ ጥቅም ሲል ይውደድ፤ እንጂ እንደ ዉለታ ባይቆጥረው ጥሩ ነው። አቶ ነአምን ያስተላለፉት ጥሪ “ተሳካ” ቢባል እንኳን ተራው ዜጋ ላይ ችግር ከማባባስ ባለፈ አቢይን ከስልጣን ያወርድልናል የሚሉ ከሆነ በኢኮኖሚ ማአቀብ የወደቀ መንግስት ምሳሌ ቢሰጡን ጥሩ ይሆን ነበር። በነገራችን ላይ አቶ ነአምን እና የቀድሞ ድርጂታቸው አርበኞች ግንቦት 7 ተመሳሳይ ጥሪ በወያኔ ጊዜ አስተላልፈው ስለነበር፣ “ወያኔ የወደቀው የዲያስፖራ ዶላር ስለቀረበት ነው” ብለው አስበው ይሆን? ቢዬም ጠረጠርኩ።
    ሰላማችንን ያብዛልን!

  2. በአመዛኙ የሃበሻ ፓለቲካ የሚመራው በስማ በለው ባጭሩ በደንበር ገተር ነው። ያኔም ወያኔ እያለ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አትሂድ፤ ገንዘብ በዚህም በዛም አትላኩ፤ ከዚህ ሱቅ ከዚያ መደበር እቃ አትግዙ ተብለን ነበር። ይኸው አሁን ዞሮ ተመልሶ እንዲህ ያለ የወረደ ህሳቤ መስማትና ማንበብ በዘርና በቋንቋ በተሰመረችው አፓርታይድ ሃገር የቀን ወሬ ሆኗል። ዝም ብሎ ራሱን ላዳመጠ ሰው የኢትዮጵያ ፓለቲካ ከድጡ ወደ ማጡ እንጂ ምንም የሚሻል ነገር የለውም። በቅርቡ ወያኔን የምርጫ ቦርድ አልመዘግብም ማለቱ የቱን ያህል ነገርየው እንደላሸቀ ያሳያል። የወያኔን ጭኸት ካወጣው ረጅም መግለጫ ይመልከቱ። ለነገሩ ኢሠፓም አይሆንም ተብሎ የለ። ደርግም ሆነ ወያኔ እልፍ ሃበሳ ፈጽመው በሃገሪቱ ታሪክ ያለፉ ናቸው። ተወደደም ተጠላም እነርሱን ከታሪክ መፋቅ አይቻልም። የሁለቱ ድርጅቶች በምርጫ ቦርድ መመዝገባቸውም መብታቸው ነው። ግን እኛ ብቻ እናውቃለን የሚሉን ተረኛ ፓለቲከኞች እንዲህ ያለው አካሄድ ነገርን እያከረረ ህዝብ ለመከራና ለሽብር ዳግም ይዳርጋል እንጂ የተሻለ ነገር አያመጣም። እናም የሚጠበቅባቸውን እንዲያሟሉ በማድረግ ሊመዘገቡ ይገባል እላለሁ።
    ወደ ዋናው ሃሳብ ስንመለስ የጠ/ሚሩ አዲስ ቤ/መንግስት ለመገንባት መታገል እሰየው ያሰኛል እንጂ ለቅሶ አያስቀምጥም። ሲጀመር ገንዘቡ ከአረብ ሃገራት በልመና የተገኘ እንጂ ኢትዮጵያ በምን አቅሟ ነው እንዲህ ያለ ወጭ ማድረግ የምትችለው። በእኔ እምነት የትም ፍጭው ድቄቱን አምጭው እንዲሉ ጠ/ሚሩ ከተሳካላቸው በጎ ሃሳብ እንጂ ክፋት የለበትም። የሃበሻው ድህነትና በቀን አንድ ጊዜም በልቶ አለማደር ያኔም የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚኖር ነው። ለዚህ ዋናው ምክንያት የህዝቡ ብዛትና የዘራፊ ነጋዴዎች፤ በብሄር ስም የታጠቁ አሸባሪዎችና ሌሎችም በምድሪቱ በየቀኑ የሚፈልቁ ግፈኞች የሚያስከትሉት ጉዳት ነው። በፈጠራ ወሬ ህዝቡን የሚያሸብሩትና ቤቱ በራፍ ላይ ቆሞ ጥይት እየተኮሰ በረሃ ገብቻለሁ ብሎ ከሚያምን የሰው የበታቾች ጋር ግብግብ ውጤቱ ባዶ ነው። እብደቱ ከላይ ወደ ታች ከታች ወደ ላይ የተሰባጠረ እውነትና ህልምን መለየት በማይቻልበት ሁኔታ ሁሉንም ቅጀት ውስጥ የከተተ የቀን እንቅልፍ ላይ ነን። ሰበር ዜናው እግር የሌለው በውሸት የተዘገበ፤ የሰው የሶሻል ሚዲያና የሌላውን አካውንት በመጥለፍ ለመክበር ወይም ግለሰቦች እይታቸውን እንዳያካፍሉ ነገርን ማጨለም የሃበሻ የስልጣኔ ምልክት ነው። ጊዜው የተማረ የደነቆረበት፤ በአላሚ ተኳሽ መሳሪያ ወገኑን ገድሎ አልሞ ተኳሽ ብሎ የሚፎከርበት፤ እንደ ድር አራዊት በዘርና በቋንቋው ሰው የተሳከረበት ሰው በሰውነቱ የማይከበርበት ዘመን ላይ እንገኛለን። የሥራ ቋንቋው ቋንቋየ ይሁን ይላል የበድን ክምችት። ቋንቋ ሰው ከሰው የሚግባባበት ለዚህም ለዚያም የማያደላ ነው። በተሳከረው የዘርና የቋንቋ ፓለቲካ ግን ቋንቋ ዳቦ ሆኖ ይገመጣል። ወንድምና እህቱን ገድሎ ከሚፎከር ጋር ስለ ሰላምና ብልጽግና ለመነጋገር እጅግ ይከብዳል። ባጭሩ እውነት የተባለውና የውሸቱ መስመር ተቀይጠዋል። ከቀን ወደ ቀን እውነትና ውሸትን ለመለየት እየከበደ መጥቷል። ይህ ሂደትም ለወደፊት የከፋ ይሆናል።
    በቅርቡ አንድ ጓደኛዬ የኤርትራው መሪ በቻይና ስለተደረገላቸው አቀባበል ከአስመራ ሆኖ ቪዲዪ ላከልኝና ተመለከትኩት። ቻይና እንዲህ ያለ የንጉስ አቀባበል ያደረገቸው (21 ጊዜም መድፍ ተተኩሷል) በዓለም ላይ ቻይናና ሌሎች ሃያላን መንግስታት ያልተቀራመቷት ብቸኛዋ ሃገር ኤርትራ ብቻ ነበረች። ይኸው ቻይናዊያን ዓለምን ለመቆጣጠር ባላቸው ህልም መሰረት አፍሪቃ ቀንድ ላይ ሰራዊታቸውንና እግራቸውን ለማስገባት ያደረጉት የቁልምጫ አቀባበል ነው። ይህ ደግሞ ከፕ/ኢሳያስ የተሰወረ እውነታ አይሆንም። የቻይና አፍሪቃ መግባት ባርነት እንጂ ለሃገራት ልዕልናን አያመጣም። ቻይና ልክ እንደሌሎቹ ሃገራት በምዝበራ የታወቀች ከገባች ውጭልኝ የማትባል በሚሊዪን የሚቆጠር ህዝቧ በዓለም ዙሪያ በንግድና በስራ በመሰማራት ወታደራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ የሳይንስና ምርምር ወዘተ ጉዳዪችን በስለላ መረቧ የምታፍስ ሃገር ናት። ዛሬ ላለችበት ሁኔታ የደረሰችው በዚህ የስለላ መረብ የተገኘውን በReverse Engineering በመጠቀም ነው። ለዚህም በአፍሪካ፤ በእስያና በላቲን አሜሪካ ጥሬ ሃብቶችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልክ በመዝረፍ ላይ ትገኛለች። ቻይና ወደ ኤርትራ ከገባች የምታደርገው ይህኑ ነው። የኤርትራ ህዝብ ከቻይና የሚያተርፈው ነገር አይኖርም። ይህ ግን ቀን የሚያሳየን በመሆኑ እንጠብቅ!
    ለማጠቃለል ለአቶ ነአምን ዘለቀ ያኔም ዛሬም አክብሮት አለኝ። ይህ በስማቸው የተጻፈ ይሁን ከራሳቸው የወጣ አላውቅም። በዚህም ይሁን በዚያ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መገዳደል፤ መዝረፍ፤ መሰደድና እስራት ለማቆም በእውነት ላይ ተመርኩዞ ድምጽን ማሰማት ተገቢ ነው። ይሰራል ስለሚባለው የጫካ ቤተ መንግስት ግን ጫካውም ሆነ ህንጻው ቆሞው ብናይ ደስ ያሰኛል እንጂ አያስከፋም። ስለሆነም በጎ ሃሳብ ነው ብሎ ነገሮችን መተው እንጂ እንዲህና እንዲያ እያሉ በነገር ግብ ግብ መግጠሙ ትርፉ ለእኔ አይታየኝም። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share