ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ዓ/ም
ቀሲስ አተርአየ [email protected]
ዘንድሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስታና የተዋህዶ ኦርቶዶክስ እምነት አካላት በተለይም አማሮችና ተጋሩወች በመልካሙ ዘመን እንደሚያደርጉት ግብረ ሕማማት የሚባለውን መጽሐፍ ዘርግተው ለማንበብ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያስፈልጋቸው አይደለም፡፡ ራሳቸው ግብረ ሕመም የሚባለውን መጽሐፍ ሆነዋል፡፡ ምድራቸውም ግብረ ሕማማቱ የሚነበበት ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ተቀይሯል፡፡ እንዴት? የሚል ጥያቄ መከተሉ ስለማይቀር ተባብረን ለመመለስ የግብረ ሕማማቱን ሐተታ አብረን እንቃኘው፡፡
“ግብረ ሕማማት” የሁለት ቃላት ጥንቅር ነው፡፡ ግብር ማለት በስራ የተተረጎመ ሐሳብ ማለት ሲሆን፦ ሕማማት ማለት በሽታወች ማለት ነው፡፡ ግብረ ሕማማት ተብለው አንድ ላይ ሲነበቡ፡ በሰወች ላይ የተለያዩ አስጨንቀው የሚገሉ በሽታወች ሲከሰቱ በህብረተ ሰብ መካከል ያሉ አዋቂወች ሰውን ለማዳን የሚያደርጓቸውን የርብርብ ጥረቶች የሚገልጽ ነው፡፡
በጾማችን መጨረሻው ባለው ሳምንት ላይ የምናከናውናቸውን የጸሎት አይነቶች ሰብስቦ የያዘውን መጽሐፍ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ግብረ ሕማማት ብላ ሰይመዋለች፡፡ ግብረ ሕማማት ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ ራዕየ ዮሐንስ ባሉት ማጻሕፍት ውስጥ ሰው በሰው ላይ የሚያደርሷቸውን የመከራ አይነቶች ሰብስቦ የያዘ ነው፡፡ በወንድሙ ከተገደለው ከአቤልና ወንድሙን ከገደለው ከቃኤል ጀምሮ የገዳይንና የተገዳይን የሕሊና ልዩነቶችን የምናይበት የምናሰላስልበት መጽሐፍ ነው፡፡
በሰው ላይ የሚደርሱትን መከራወች የምናይበትና የምናሰላስልበት ወቅትም ከመጽሐፉ ስም ጋራ በማያይዝ አባቶቻችን ሰሙነ ሕማማት ብለው ሰይመውታል፡
- ይህም ማለት፦ የመከራ የስቃይ የጭነቀት ሳምንት ማለት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት በዚህ ዓለም ለመኖር ሕይወታችን የሚጥይቁንን ሁሉ ተግባርት ርግፍ አርገን ተትን በክርስቶስ ላይ የደረሱትን መከራና ስቃይ በግብረ ሕማማቱ የሚተነተኑባትና
የምናስብባት ስለሆነች የሕማማት ሳምንት ተባለች፡፡ በየእለቱ በምንቆርብበት ሰአት የምናነባቸው መጻሕፍት የምንቀኛቸው ቅኔወቻችን በግብረ ህማማቱ ከሚነበቡትና ከሚዜሙት ልዩነት ባይኖራቸም፤ ከሆሣዕናው በኋል ባለችው ሳምንት የሚዘረጋው መጽሐፍ (ግብረ ሕማማት) በመከራ በዋይታና በሰቆቃው ብቻ የተሞላ ነው፡፡
በሰሙነ ሕማማት በግብረ ሕማማት የሚታወሱት በክርስቶስ ላይ የደረሱት መከራወች ብቻ አይደሉም፡፡ ዛሬ እንደ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያንች በማንነታቸው እየተወጉ እየታረዱ እየተቃጠሉ ያለቁት በስንክሳር የተመዘገቡት ጻድቃን ሰማእታት ሁሉ የሚታወሱበት ነው፡፡ በየዕለቱ የምንደግማት ውዳሴ ማርያም እንኳ ብትሆን፤ አባቶቻችን “ሰአሊ ለነ ቅድስት” የሚለውን ስለጨመሩበት ጸሎት ይመስላል እንጅ፡ እንደ ይዘቱና እንደተማርነው ከሆነ “ኀበ ዘትካት መንበሩ” እንዲል ክርስቶስ ሰውን ወደቀደመ ክብሩ የመለሰባቸውን መከራና ስቃይ እንዳንረሳቸው ማስታወሻችን ናት፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ባዘቦት በንባብና በማዜም የምናደርጋቸው በህማማት ሳምንት ከምናደርጋቸው የተለዩ ባይሆኑም ይህች ሰሙነ ሕማማት “ክርስቶስ የኛን መከራ በመስቀል ተሽክሞ ያደረገልንን ጽድቅ ምክንያት አድርገን የማዳኑን ሥራ የኃጢአት ማስፋፊያ ማድረግና አለማድረጋችንን የምንፈትሽባት ሳምንት ናት፡፡(ገላ 2፡17) ፡፡ በያመቱ ተለምዶን በመከተል በሰላም ዘመን በክርስቶስ ላይ የተፈጸመበትን መከራወችሥቃዮች ሁሉ የስቅለቱን ስእል በፊታችን አርገን በመጽሐፉ የተገለጹትን እያነበብን በዐይነ ህሊናችን እያየን በእዝነ ልቡናችን እየሰማን ሰውነታችንን በማስጨነቅ በስግደት በማክፈል ስሜት መከራውን በመሳተፍ እናሳልፈዋለን፡፡
ዘንድሮ ግን አማራና ኦርቶዶክስ ሁሉ በመልካሙ ዘመን እንደሚያደርገው ግብረ ሕማማት የሚባለውን መጽሐፍ ዘርግቶ ለማንበብ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡ ራሱ ወደ ግብረ ሕማምነት ተቀይሯል ፡፡ ምድሩም የራሱ ሕመምና ስቃይ የሚነበበት ወደ ቤተ ክርስቲያንነት ተቀይሯል፡፡
ራሱ ሕዝቡ ወደ ግብረ ሕማምነት ተቀይሮ በየቤቱና በየደረሰበት እየተነበበ ሳለ በቤተ መቀደስ ቆሞ እንደ ሰላሙ ጊዜ “ንዑ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ እለትሳተፉ ሕማመ ቢጽክሙ ወእለትትዌከፉ ሕማመ ፍቁራኒክሙ”(ጎር ቁ 40) ማለትም፦ በወገናቻችሁ ላይ እየደረሰ ያለውን ግርፋቱን በጦር መወጋቱን በቀኖት መቸንከሩንና መሰቀሉን ኑና ተመልከቱ እያለ በቤተ መቅደስ የሚያዜም ቄስ ካለ ያልበትን ወቅትና ቦታ ያልተገነዘበ ይመስለኛል፡፡
በግበረ ሕማሙ መጽሐፍ የተገልጸው የመከራ አይነት ሁሉ ኦርቶድክሶች ባሉበት ቤትና በየመንደሩ እየተካሄደ እያለ የዘንድሮውን ግብረ ሕማማት ለማንበብ ወደ ቤተ መቅደስ የሚሄድ ቄስ “ማስተዋሉ በተወሰደበት አንተን በመሰለ ቄስ እንዴት እጠየቃለሁ” የሚለውን የእግዚአብሄርን መጸየፍ የተገነዘበ አይደለምና ከቤተ መቅደስ መባረር አለበት፡፡(ህዝቅ 14፡3)፡፡
የዘንድሮው ግብረ ሕማማት ወደ ሰውነት ተቀይሮ በየመንደሩ እየተነበበ ሳለ ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ግብረ ሕማማት መዘርጋት የሕዝቡ ፈጣሪ አምላክ “የቤተ መቅደሱን በር የሚዘጋልኝ ምነው በተገኘ! (ሚልክ 1፡10) የሚያሰኘው እየመሰለኝ በመሰቀቅ ላይ ነኝ፡፡ ኦርቶዶክሱ ሕዝብ የቤተ መቅድሰን በር በመዘጋት ተሰጥኦውን ለአምላኩ መመለስ ያለበት ይመስለኛል፡፡
በግብረ ሕማማቱ መጽሐፍ የተገለጹት የመከራ አይነቶች፡ በክርስቶስ ማንነቶቹ ላይ በየዘመናቱ የሚፈጸሙትን ገሸሺ አርገን ከሁለት ሽህ ዐመታት በፊት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በተፈጸሙት መከራወች ላይ ብቻ እንድናተኩር አይደለም፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያዊት ኦርትዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄሶች ከሆን፤ ሰለስቱ ምዕት “ኢታንኅ ወኢትክላህ ፈድፋደ እማአቅሙ፡፡ አላ ዘምር በሕቁ ወበመጠን ከመ ኢይዘንግዑ አኀው (ሃይ 24፡38፡፡ ብለው የተናገሩትን መነሻ በማድረግ ሊቃውንት አባቶቻችን አንድም እያሉ ተንትነው ያስተማሩንን የምንረሳው አይመስለኝም፡፡ ይህም ማለት፦ “አንተ ራስህ በክርስቶስ ማንነቶች ላይ የሚደርሰውን መከራ ዘንግተህ ህዝበ ክርስቲያኑንም በሚደርስበት መከራ ላይ እንዳያተኩር የሚያደርግ ዝማሬህን አታርዝም ከጣሪያ በላይም በመጮኽ ሕዝቡን አታደንቁር” ፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኮነ ከማነ ዘእንበለ ኃጢአት ባሕቲታ” ማለትም፦ በመለኮታዊ ውህደቱ ከኛ የተለየ ቢሆንም እንደኛ በወንድ ዘር ከመወለድና ስህተት ከመስራት በቀር እንደኛ ፈጽሞ ሰው ነው፡፡ እኛ በምድር ያለን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ማንነቶቹ ነን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የመጣበትን የማዳን ስራ ፈጽሞ በማረጉ በአካሉ የተለየን ቢመስልም፤ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ከኛ ጋራ መስራቱ እንዳለ ሆኖ፤ በተዋህዶ እምነታችን እኛ የሱ ማንነቶቹ እንደሆን በአማኑኤልነቱ ገልጾልናል፡፡
ቅዱስ ጵውሎስ የቀደመ ማንነቱን በክርስቶስ ማንነት ከመተካቱ በፊት ክርስቲያኖችን (የክርስቶስ ማንነቶችን) በማስደድ ላይ ሳለ፡፡ ጌታችን በመለኮታዊ መብረቁ በገታው ጊዜ “አንተ ማነህ ? ብሎ ክርስቶስን ጠየቀው፡፡ ክርስቶስም “እኔማ አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ (የሐዋ 9፡5) ብሎ የመለሰለት መልስ በስሙ የተጠመቁት ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሶች ማንነቶቹ እንደሆኑ አጽንቶ ያረጋግጣል፡፡ በሰሙነ ሕማማቸው ወናፍ እሳትን ከብረት ጋራ ከሚአዋህደው ውህደት እጅግ በላቀ ወላፈኑ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖቹን ከሱ ጋራ ያወህዳቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንዳልኩት ወገኖቻችን ኢትዮጵያውያን የሆኑት ማንነቶቹ ባራት ማንነቶቻቸው ምክንያት በእስጢፋኖስ ዘመን በክርስቲያንች ላይ ከተደረገው የከፋ ስደትና መከራ እየደረሰባቸው ወደ ግብረ ሕማማትነት ተቀይረዋል፡፡
1ኛ፦ በኦርቶዶክስ ክርስትናቸው
2ኛ፦በኢትዮጵያዊነታቸው
3ኛ፦ባማራነታቸው
4ኛ፦በአማረኛ ቋንቋቸው እየተገደሉ ናቸው፡፡
የሕዝብ አመጽ በማነሳሳት በነፍስ ግድያ አሸባሪ የተባሉት ለፍርድ መቅረብ የሚገባቸው ኢትዮጵያውያን በርባኖች ሲፈቱ፡ እንዲያውም ወደ ሹመት እየተመለመሉ ሲገቡ እየተመለከት ነው፡፡ ጲላጦስ በኢየሱስ ላይ ጠላቶቹ እንዳሻቸው እንዲያደርጉት አሳልፎ እንደሰጠው፡፡የክርስቶስ ማንነቶች ኦርቶዶክሳውያን ለገደሏቸውና ለሚገድሏቸው ተላልፈው እየተሰጡ ናቸው (ሉቃ 23፡25) ፡፡
ከአማራው ህብረተ ሰብ ውጭ ያሉት ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ክርስቲያናዊ እምነታቸውና ኢትዮጵያውነታቸው ከብልጽግና ወጥመድ ባያመልጡም፡ የክርስቶስ ሰቃዮች ስምዖን የተባለው የቀሬና ሰው ከገጠር ሲመጣ አግኝተው፤ ለክርስቶስ ያዘጋጁትን መስቀል አሸክመው ኢየሱስን ተከትሎ ወደ ቀራንዮ እንዲሄድ እንዳስገደዱት፡ ብልጽግናወችም ለአማራው ያዘጋጁትን መስቀል እነ አቶ ታዴዎስ ታቶና አቶ ታየ ቦጋለን አሸክመው ከአማራው ጋራ ወደቀራንዮ እየነዷቸው ነው”(ሉቃ 23፡26)፡፡ በሕማማቱ ሰሞን ግብረ ሕማማት የሚባለውን መጽሐፍ የምንዘረጋው በክርስቶስ ላይ የተነገረገውን እንድንነጋገርበት ስእለ ስቅለቱንም በፊታችን የምናቆመው በሱ ላይ የተፈጸመውን ባይናችን እንድናይበት ነው፡፡
ዘንድሮ ራሱ ማንነቱ እየተገረፈ በጦር እየተወጋ በቀኖት እየተቸነከረ፡ በእሳት እይተቃጠለ እየተሰደደ እየተራበ እየተጠማ ነው፡፡ ሐሞትም ሲቀረብለት በተግባር እያየን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን መከራ ሲያስብ “ልብ ይትከፈል ወሕሊና ይዘበጥ ወንፍስ ትርዕድ ወሥጋ ይደክም ሶበ ይትነገር ሕማማቲሁ ልፍቁር”( አፈ 57) እንዳለው፦ ማለትም “በተወዳጁ ጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የደረሱት የመከራ አይነቶች ልብ የሚሰነጥቁ ነፍስን የሚያስጨንቁ ኩላሊት የሚወጉ ሥጋን የሚያንቀጠቅጡ መከራወች ናቸው” አለ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ባሉት ምንነቶቹ በኦርቶዶክስ ልጆች ላይ እየተፈጸሙ ያሉት የመከራ አይነቶች የከፉ እጅግ የሚዘገንኑ እንደሆኑ በገሀድ በመታየት ላይ ናቸው፡፡
ዮሐንስ አፈውርቅ “ብክየዎ ወላህውዎ እለ ታፈቅርዎ”(59) ማለትም፦ የምትወዱት ሁሉ አልቅሱለት ያለው ራሱ ክርስቶስ “ለኔ አታልቅሱልኝ ለራስችሁ አልቅሱ” (ሉቃስ 23፤ 28) ያለውን ዝንግቶት አይመስለኝም፡፡ በመገደል ላይ ላሉት እንደ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ለመሳሰሉት ማንነቶቹ እንዲለቀስ የተናገርው ይመስለኛል፡፡
ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ጎርጎርዮስም “ንዑ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ እለትሳተፉ ሕማመ ቢጽክሙ ወእለትትዌከፉ ሕማመ ፍቁራኒክሙ”(ጎር ቁ 40) ብሎ የጻፈውን ማለትም፦ በወገናቻችሁ ላይ እየደረሰ ያለውን ግርፋቱን በጦር መወጋቱን በቀኖት መቸንከሩን መሰቀሉን ኑና ተመልከቱ” ያለውን የሆሣዕና ዕለት ያዜምነው በመገደል ላይ ላሉት ማንነቶቹ እንጅ ከሁለት ሺ አመታት በፊት ለተፈጸመበት ለክርስቶስ ብቻ ነው ማለት የሚቻል አይደለም፡፡
“ንዑ ትርአዩ ዘንተ ቅስፈተ” ማለትም፦ “ይህን ግርፋት ይህን መከራ ታዩ ዘንድ ኑ” ተብለን የተጠራነው ከሁለት ሺ አመታት በፊት በክርስቶስ ላይ የተፈጸመበትን ብቻ እንድናይ የሚመስለን ከሆነ ጥሪያችንና ቅዳሴያችንን የተረዳን አይመስለኝም፡፡ “እናንተ የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ! በፊታችሁ የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዳታዩ ማን አዚም አደረገባችሁ! (ገላ 3፡1_5) እንደተባሉት እንደ ገላትያ ሰዎች በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን እንዳናይ ብልጽግናወች አዚማቸውን ያደረጉብን መሰለኝ፡፡
ግብረ ሕማማቱን እያነበባችሁ የስቅለቱን ስእል ብቻ የምትመለከቱ ቀሳውስት በተለይም ጳጳሳት ሆይ! በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን መከራ እንዳያዩ ብልጽግናወች በካድሬወቻቸው ላይ ያደርጉባቸው አዚም ወደናንተ እንዳይደርስ ተጠንቀቁ! ይህ በዚህ አመት ኦርቶዶክሳውያን በየቤታቸውና በየደረሱበት የሚፈጸሙባቸው ግብረ ሕማማት በፖለቲከኞችና በሐኪሞች የሚወገድ በሽታወች አይደሉም፡፡ የኛ የኦርቶዶክሳውያን ቀሳውስት እዳ እኛን የሚመለከቱ ናቸው፡፡
ግብረ ሕማማቱን መተርጎምና መተግባር የሚመለከትን እኛን ነው፡፡ የዘንድሮውን ግበረ ሕማማትና ሰሙነ ሕማማት በክርስቶስን ስእለ ስቅለት ፊት ስገደንና በጾም አክፍለን እንድናሳልፈው ለራሳችሁ አልቅሱ ያለን ክርስቶስ የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡
በመግቢያየ ላይ እንደገለጽኩት ግብር ማለት በስራ የተተረጎመ ሐሳብ ማለት ሲሆን፦ ሕማማት ማለት በሽታወች ማለት ነው፡፡ ግብረ ሕማማት ተብለው አንድ ላይ ሲነበቡ፡ በሰወች ላይ የተለያዩ ሕማማት ሲከሰቱ በህብረተ ሰብ መካከል ያሉ አዋቂወች ሰውን ለማዳን በሽታወቻን ለማስወገድ የሚያደርጓቸውን ጥረቶች የሚገልጽ ነው፡፡
በሕብረተ ሰባችን መካከል “የማይፈታውን ችግርና መከራ እንፈታ ዘንድ” ተሰይመናል (ኪዳን) እያልን ያላንዳች መወላወል በህዝቡ ፊት ቆመን በየቀኑ ከምንፎክረው ከኛ በቀር ሌላ ጥረት የሚያደርግ የለም፡፡
“ከኃጢአት ጋራ ስትታገሉ ገና ደማችሁን እስከ ማፍሰስ አልተቃወማችሁም” (12፡4) እንደተባለው ማንነቶቹ የሆኑትን ኦርቶዶክሳውያንን ከሚሰቅሉት ኃጢአተኞች ጋራ በመታገል እኛ ቄሶች ደማችን እንዲፈስ ክርስቶስ ይጠበቃል፡፡
እኛ የኦርቶዶክስ ቄሶች አፋችንን በፈታንበት መጽሐፉ አማካይነት ዳዊት “ነገሥታታቸውን በሰንሰለት መኳንንቶቻቸውን በእግር ብረት ያስራሉ፡፡ በነሱ ላይ የተጻፍወን ፍርድ ለመፈጸም ለቅዱሳኑ ሁሉ ይህች ክብር ናት” መዝ 149፡8 9)፡፡ ብሎ የነገረንን በተግባር የማዋል ግዴታ አለብን፡፡ በተለይም ብጹዐን ቅዱሳን የሚለውን ስም መጥሪያችሁ በማድረግ በግንባር ቀደም የተሰለፋችሁ የህዝብን ደህንነት አስጥብቃለሁ ብሎ የተሰለፈ እንደ ብልጽግና የመሰለ መንግሥት የህዝቡን እልቂት እያየ እየተመለከተ በማስተናገድ ላይ ሲሆን በተጠያቂነቱ ተፈርዶበት እጁ በሰንሰለት እግሩ በእግር ብረት እንዲታሰር በዓለም አለ ለሚባለው ምድራዊ ዳኛ ከሳችሁ የማቅረብ ግዴታ አለባችሁ፡፡
ነቢዩ ዳዊት የተናገረውን ከብዙ ዘመናት በኋል ክርስቶስ በዮሐንስ አማካይነት “ማንም በሰይፍ የሚገድል ቢኖር እርሱ በሰይፍ ይገደል፡ የቅዱሳን እምነትና ትእግስት የሚገለጸው በዚህ እንደሆነ ያስገነዝባል (ራእይ 13፡10) ብሎ የተናገርውን ጽድቅ ልትፈጽሙ የገባችሁበት ተልእኮ ያስገድዳችኋል፡፡ ወዳችሁ የገባችሁበትን ብትፈጽሙ ራሳችሁንም የክርስቶስን ማንነቶች (ኦርቶዶክሳውያን ) ታድናለችሁ፡፡ ባትፈጽሙ ግን ፍሬ ያማያፈራውን ዛፍ ለመቁረጥ የተዘጋጀው ምሳር በናንተ አንገት ላይ መደገኑን ግብረ ሕማማቱ ያስጥነቅቃችኋል!
ይቆየን