ዛሬ አሀዱ ያለነው ሳምንት ሰሞነ-ህማማት ነው፡፡ ክርስቶስ፣ ወገኖቹ በሆኑ ጻሕፍት እና ፈሪሳውያን በሐሰት ተከስሶ፣ በሐሰት ተፈርዶበት በግፍ እንዲሰቀል ለሮማውያን ጌቶች ተላልፎ የተሰጠበት ነው፡፡ ዕለቱም ሆነ ክስተቱ በዚህ ዐውድ ለምናነሳው አጀንዳ ‘ትዕምርት’ (Symbol) ነው፡፡ ዛሬም ሀገር-በቀል “ሮማውያን” አሉና፡፡ ሮማውያን ካሉ ደግሞ “ጸሐፍት” እና “ፈሪሳውያን”ም ይኖራሉ፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ከ“ተደመሩ” ተላልፎ የሚሰጠው የመሰዋት በግ መኖሩም ሆነ “በርባን” በነፃ መለቀቁ ርግጥ ነው፡፡
…ለመሰዋት የቀረበውን የዐማራ ልዩ ኃይል በተመለከተ ባለፉት ሦስት ተከታታይ ቀናት ሦስት ከፍተኛ ሹማምንት “ዓይናችሁን ተጨፈኑና ላሞኛችሁ” ዓይነት መግለጫ ሰጥተዋል። ጄነራል አበባው ታደሰ፣ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ እና ዶ/ር ይልቃል ከፋለ…
የጄነራሉ ግድፈቶች
ጀኔራል አበባው የዛሬ ሠላሳ ዓመት በገዛ ጓዶች ላይ የተፈፀመውን ግፍ፣ ከሠላሳ ዓመት በኋላ በስማቸው ሥልጣን በጨበጠባቸው ወገኖቹ ላይ ለመድገም አስፈፃሚ ሆኖ መምጣቱ የታሪክ ምፀቱን ማጉላቱ አልቀረም።
ወያኔ (የዛሬዋ “በርባን”) ጠንካራ የኢሕዴን አዋጊዎችን መመንጠር የጀመረችው ገና አዲስ አበባን በጦር ሜዳ መነጽር ማየት በጀመረችበት ርቀት እንደሆነ በትግሉ ዙሪያ የተሰናዱ ድርሳናት ነግረውናል፡፡ ለምንጠራው የተመዘዙት ካርዶች ደግሞ “ነፍጠኛና ትምክህተኛ” የሚሉ እንደነበረ ለጄነራሉ ማስታወስ፣ ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ትሕነግ ከተጠቀመባቸው በኋላ የወረወራቸውን የጦር አዋጊዎች በስም መዘርዘሩ እንኳ “ኪስ ይቀዳል” ብለን እንለፈው፡፡
አዲስ አበባ ከተገባ በኋላ የኢሕዴን አራት ክፍለ ጦሮች “ተቅሊጥ-ብወዛ ይግቡ” ተብለው በሺሕ የሚቆጠሩ ታጋዮች ከሠራዊቱ ተጠርገው፣ የተዋጉበትን ዩኒፎርም መለመኛ ሲያደርጉት ‹ጄነራል አበባው ልጅ ነበረ› ቢባል እንኳ፤ በምርጫ-97 ማግስት ከ21 ሺሕ በላይ የዐማራ ተወላጆች የመከላከያ አባላት (ከተራ ወታደር እስከ ጄነራል) “ቅንጅትን ትደግፋላችሁ” ተብለው ሲመነጠሩ የእሱ ተሳትፎ ግዘፍ-የሚነሳ ነበር፡፡ ምክንያቱም፣ የምዕራብ ዕዝ አዛዥ በመሆኑ፣ ከእዚህ ዕዝ የተባረሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ዐማራ የሠራዊቱ አባላት በፊርማው የተሸኑ ናቸውና፡፡
ይህ ኀጢያቱ ግን የትሕነግ የበላይነት በመኖሩና ታዝዞ ያስፈጸመው በመሆኑ በሕዝባዊ ይቀርታ ታልፏል፡፡ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በድጋሚ ወደ ሠራዊቱ ከመመለሱ በፊትም ሆነ ከተመለሰ በኋላ የዐማራ ሕዝብ ስሙን በበጎ ሲያነሳው የነበረው “ይቅር” በማለቱ ነውና፡፡
ዛሬ፣ ያውም በተግባርና በልምድ በተፈበነበትና የተሰሚነት ሚናው በእጅጉ በጨመረበት ወቅት፣ ተረኛው ቡድን (“ሮማውያኑ”) ሊተገብሩት ያቀዱትን መሰል የፖለቲካ ፕሮጀክት ሊያስፈጽም ከፊት መገኘቱ፣ ከታሪክ የማይማር የተረገመውን ዘመን ለመድገም ያለመ አስመስሎታል።
መቼም፣ በመከላከያ ውስጥ የአንድ ብሔር አዛዦች ፍፁማዊ የበላይነት መንሰራፋቱን ለጄነራሉ ማስታወስ፣ አሁንም “አውቆ የተኛ…” በመሆኑ ብናልፈው እንኳ፤ የኦሮሚያውን ግዙፍ የልዩ ኃይል ግንባታንም፣ ‹ለተሰጠው ሥልጣን ማካካሻ ነው› ብለን ብንተወው እንኳ፤ ዛሬም ሆነ ነገ ሞቱን የሚመኙለት የሰሜን ወንበዴዎች ትግራይ ላይ ጉምቱ የጦር መኮንኖች የሲቪል አስተዳደሩን ተረከበው፣ ወታደራዊ መንግሥት እየመሰረቱ፣ መጠነ-ሰፊ ልዩ ኃይል እያሰለጠኑ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ግና፣ ይህን ደረቅ ሃቅ ወደ ጎን ብሎ፤ ለለማ መገርሳ ያልበጀውን፣ ዐቢይ አሕመድ ከወሬ ማድመቂያ ያላዘለለውን “ኢትዮጵያዊነት” በማስጮህ፣ ዐማራን ለእርድ ለማቅርብ “አንዱ አብጦ ሌላው የሚዳከምበት አሠራር በኢትዮጵያ አይኖርም” በማለት ለማጃጃል የሞከረበት ፈሪሳዊነት እጅግ አስተዛዛቢ ነው፡፡ሰው አንዴ ይሳሳታል፡፡ ሁለቴም ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ሦስተኛ… ግን ይከብዳል፡፡ በግሌ የኢሕዴኑ ወታደራዊ “ፍሬ” የአበባው ጉዳይ ወጥቶልኛል!!
የዐቢይ የደፈረሱ መስመሮች
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ በፋላሲ የታጀቡ፣ በተቃርኖ የተሞሉ፣ በአፋዊነት የተሸሸጉ፣ በስሁት ፕሮፓጋንዳ የተጀቦኑ… መግለጫዎችን ሰጥተዋል፤ ዲስኩሮችን አሰምተዋል፡፡ በብዕር ሥምም ሆነ በእውነተኛ ሥማቸው የጻፎቸው መጽሐፍትም አንድም በ“ከፋፍለ ግዛ”፤ ሁለትም፣ በፕሮፓጋንዳ ሸንግለህ (በእሳቸው አገላለጽ “የሚፈልጉትን እየነገርካቸው፣ የምትፈልገውን አድርግ፤” ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ በበቂ ተረድተናል፡፡
እነዚህን አደገኛ “ፍሬ ከናፍርቶቻቸውን” በሙሉ ለመጥቀስ በፌስቡክ ቀርቶ፣ በደለቡ ጥራዞችም የሚቻል ባለመሆኑ፤ ከአጀንዳችን ጋር በተያያዘው ሰሞነኛው ረዥም ሀተታቸው ላይ ብቻ እናተኩራለን፡፡ የልዩ ኃይሎችን ፈረሳ በተመለከተ ያስነበቡን ጽሑፍ አሁናዊውን የኢትዮጵያ የፀጥታ ሁኔታ የካደ፣ በቅጥፈት የተሞላ ከመሆኑም በላይ፤ እንደተለመደው ታሪክን አጣሞ ያቀረበ ነው።
በተለይ፦ “የኢትዮጵያ ሠራዊት በብሔራዊ ደረጃ የተደራጀበትን ታሪክ ከተመለከትን የተለያዩ ወታደራዊ አደረጃጀቶችን ወደ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት በማዋሐድ የተከናወነ መሆኑን እናያለን፤” የሚለው የጽሑፋቸው አንቀጽ ድኀረ-1983 ያለፍንበትን እውነታ የማይገልፅ ስለመሆኑ ራሳቸው “ገና በ16 ዓመቴ ተቀላቀልኩት” የሚሉት ተቋም ህያው ምስክር ነው።
ምክንያቱም፣ በጅምላ የተባረረውን የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት በወያኔ ፍረጃ የ”ደርግ ሠራዊት”ን እና ከላይ የተጠቀሰውን የኢሕዴን ተዋጊዎችን ምንጠራ ብንተወው እንኳ፤ ዛሬ መንገዳቸውን ለመደልደል ምክረ-ሃሳብ በመስጠት የሚያገለግሏቸው ሌንጮ ለታ ይታዘቧቸዋል፡፡
በወቅቱ የሽግግር መንግሥቱ ምክር ቤት ወታደራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ሌንጮ ራሳቸው በመሩት መድረክ ነውና፤ የኦነግ ሠራዊት እንዲበተን እና ኢሕዴግ ብቻ የአገሪቱ ሠራዊት እንዲሆን በድምጽ የተወሰነው፡፡ ያኔ እሳቸው ምናልባት በሕወሓት አጠራር “ማንጁስ” ስለነበሩ፣ ስለጉዳዩ አያውቁ ከሆነ እንጃ?! እኛም አድገን ታሪኩን አንብበን ነው ያወቅነው፡፡
የእርሳቸው ሿሿ… ግን ተለየ፡፡
በተረፈ፣ በመግለጫቸው የነገሩን ደረቅ ሃቅ የትላንት አለቃቸው፣ የዛሬው ጁኒየር ፓርትነራቸው “ጠንካራውን ማራገፍ፣ ቀሪውን በመዋቅር መቆጣጠር” ይሉት የነበረውን የገዥነት መንገድ መደገም ነው።
ለዚህ ደግሞ፣ ራሳቸው የሚመሩት መንግሥት በ2011 ዓ.ም “በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን” በሚል ያወጣውን አዋጅ መጥቀስ እንችላለን፡፡
“የአገር መከላከያ ሚንስቴር” በሚለው አንቀጽ 14 ሥር፣ ቁጥር 7 ላይ የሰፈረው እንዲህ ይነበባልና፡-
“የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች፣ የብሔረሰቦችና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋጽዖ ያካተተ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡”
እናሳ፣ እሳቸውም ሆኑ ጄነራል አበባው ይሄ ጠፍቷቸው ነው?
የፌዴራል-ኦሮሚያ መሪዎች፣ በቅድሚያ በአዋጅ ያደራጃችሁትን ብሔር-ተኮር ተቋም ወይ አፍርሳችሁ አስተካክሉ፤ አልያም በአዋጁ መሰረት የብሔር ውክልናን አመጣጥኑ፡፡
የኦሮሚያ ልዩ ኃይልም ለተሾመ ቶጋ እንደተነገረው፣ አበባው እንደደሰኮረው ወደ መከላከያም ሆነ ፌደራልና መደበኛ ፖሊስ የመቀላቀሉ ሽታውም የለም፡፡ በትግራይማ የግዳጅ ምልምላው ከመቼውም በላይ ደርቷል፡፡
የፕሪቶሪያውን ስምምነት የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መከላከያ ሠራዊት እንደሆነ ተጠራርጎ ወጥቶ ወደ ዐማራ ክልል ከመዝመቱ በተጨማሪ፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እና ማሰልጠኛዎች የነበሩ የሠራዊቱ አባላትም ዐማራ ክልል እንዲርመሰመሱ መታዘዛቸውን ዐቢይ እና አበባው ብቻ ሳይሆኑ፤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቀጥሎ ረዥሙን ዓመት በሥልጣን የሰነበቱት አቶ ደመቀም ሆኑ ሌሎቹ የዐማራ ከፍተኛ አመራሮች ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡
በተረፈ፣ ይች “ትጥቅ ፍታ አላልንም” የሚሏት ጨዋታ ተራና መናኛ ማደናገሪያ መሆኗን ለመረዳት ምንም ዓይነት የፖለቲካም ሆነ የፀጥታ ዕውቀት የሚጠይቅ አይደለም፡፡ “ብሔራዊ ጦር” እያሉ የሚሸነግሉበት ተቋምም ቢሆን፣ የሱዳን ወራሪን ቀርቶ፤ በኦነግ-ሸኔ ከሚመራው የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን እየተንደረደረ የሰሜን ሸዋ ከተሞችን የአመድ ቁልል ሲያደርግ የነበረውን የሽብር ቡድን እንዳይከላከል የበዙ አሻጥሮች ሲፈጸምበት ታዝበናል፡፡
ዶ/ር ይልቃል እና ጓዶቹ
(“ጸሐፍት” እና “ፈሪሳውያኑ”)
የዐማራ ክልልን ልዩ ኃይል በማፍረሱ ረገድ በርዕሰ-መስተዳደሩ ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የተላለፈው መግለጫ ሁሉንም ከፍተኛ አመራር የሚወክል ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ምክንያት አለኝ ላስረዳ፡- ፌደራል ላይ የተቀመጡት የብልፅግና ሥራ-አስፈጻሚዎችን ጨምሮ፤ በክልሉ ላይ እስካሉት የካቢኔ አባላት ድረስ በዚህ ጉዳይ አንድነት እንጂ፤ ልዩነት እንዳላቸው የሚያመላክት ምንም ነገር አላየንምና፡፡
(የአቶ ጣሂር መሀመድንን አቋም ቀደም ብዬ ገልጨዋለሁ፡፡)
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=6003617003090080&id=100003255189402&mibextid=Nif5oz
የሆነው ሆኖ፣ ይህ አመራር ከአዲሱ ለገሰም የከፋ የተላላኪነት ሚና ለመውሰድ መጣደፉ ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻም፡፡ ሰፊ የድጋፍ መሰረት ነበረው፡፡ የዘመኑን የፖፕሊዝምን መንፈስ በመከተልም ለሕዝቡ ስላለው ውዴታ ደጋግሞ ምሏል፤ ተገዝቷል፡፡ (በዛው ሰሞን ስለታሪክ ምርኮኝነት ያወጣት መጣጥፍ መሰል መግለጫ ሰብስባለት የነበረችውን የሕዝብ ድጋፍ መጠን ያስታውሷል)
ዛሬ ግን በተገላቢጦሽ፣ አንድ ጋንታ ልዩ ኃይል እንኳ በሌለው ዐዲሱ የደቡብ-ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ “የልዩ ኃይሎች መልሶ ማደራጀት ሥራ በመጠናቀቅ ላይ ነው፤” ተብሎ የተሰራጨውን “ዜና” ይዞ፣ ‹ሁሉም ክልሎች እየተገበሩት ነው፤ የእኛም መፍረስ አለበት፤› እስከማለት የተለጠጠ ክህደት እየፈጸመ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ያልገባቸው ነገር ብዙ ነው፡፡ … ነገሩ ነው እንጂ፣ ሕዝብ ካልፈለገ የቱንም ያህል ሠራዊት ብታዘምት አታሸንፍም፡፡ ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ የዐማራ ሕዝብ ያለው ሥነ-ልቦና እና እሴት (Value) ደግሞ፣ አቶሚክ ቦንብ ነው፡፡
እመነኝ፣ ሰፊ ቁጥርና የሥነ-መንግሥት ልማድ ያለው ሕዝብ ቀርቶ፤ በመቶ ሺሕዎች ብቻ የሚቆጠረው ሀረሪ እንኳ ሞትን ንቆ ከወጣ አታንበረክከውም፡፡ እነ ሽመልስ አብዲሳ ጉራጌን በቁጥርና በጆግራፊ መዝነው የጀመሩት ጨዋታ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ጊዜው ሲደርስ ታየዋለህ፡፡ የዐማራ ልዩ ኃይልን መበተን፣ የአዴፓን 35 የአመራር አባላት እንደመበተን የሚቀል አድርገህ ከወሰድከው ስህተት ነው የምልህም ለዚህ ነው፡፡
በቀጭን መስመር የገባች መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፡- የክልሉን ርዕሰ-መስተዳደር እንዳሻህ መቀያየር ትችላለህ፡፡ አድርገኸውማል፡፡ ለገሰ ቱሉን ወይም ሬዲዋን ሁሴንን ለዐማራ ክልል ፕሬዚዳንትነት ብትሾም፣ አጠገብህ ያሉ አመራሮች አጨብጭበው እንደሚያስፈጽሙ አልጠራጠርም፡፡ ልዩ ኃይሉ የተሰባሰበው ግን ለገዱም ሆነ ለአገኘው፣ ለይልቃልም ሆነ ለግርማ አጃቢነት አይደለም፤ ለሕዝብ ህልውና እንጂ፡፡
ሥነ-ቃሉም የሚነግርህም፡-
“ግፋ በለው፣ ይገፋል በግዱ
የአገሩ ገመገም፣ ሲጠፋው መንገዱ፤”
በማለት ነውና፡፡
እንደ መውጫ
***
ይህ ሳምንት ለኦርቶዶክሳዊያን በነብያቱ አንደበት የተነገረውን ለመፈጸም ‹ረቢው› ያለፈበትን ስቅየት እያሰብን የምንሰግድበት፣ የምንጸልይበት፣ ምህላ የምናደርግበት ሰሞነ-ህማማት ነው፡፡ የሳምንቱ መጨረሻ ደግሞ ተንሳኤ ነው፡፡ የድል ቀን ነው፡፡
የሐሰት ከሳሾች፣ እብሪተኞች፣ ግፈኞች፣ ተረኞች… ተሸንፈው ከሞት የምትነሳበት ተምሳሌት ነው፡፡ ለሃቅ እስከቆምክ፣ እውነተኛ ምክንያት እስካለህ፣ ሕዝባዊ እስከሆንክ… የሁሉም ነገር ሂደት መቋጪያው እንዲህ ነው፡፡
“ጸሐፍት” እና “ፈሪሳውያን”፡- ለስቃይ፣ ለመከራ፣ በሐሰት ተከሰህ በሐሰት እንዲፈረድብህ፣ በጅምላ እንድትጨፈጨፍ… ለ“ሌሎች” ወጋሪዎችህ አሳልፈው ይሰጡሃል፡፡
ዛሬ የምትሰማውም “እሰረው፣ ፍለጠው፣ ቁረጠው፣…” የሚሉ ፍርደ ገምድል ድምፆችም የዚህ ውርስ ናቸው፡፡
በተከታዮቹ ሳምንታት ወይም ወራት ሞትንም፣ የሞትንም ወሬ፣ ስደትንም እስርንም አብዝተህ ልትሰማ ትችላህ፡፡ ጦርነትንም የጦርነትንም ወሬ ትሰማ ይሆናለህ፡፡
በርባንን በነፃ ያሰናበቱት፣ ሮማዊያኑ አንተንና ሕዝብህን በጅምላ ለመጭፍጨፍም አያመነቱ ይሆናል፡፡
በመጨረሻ ተንሳኤው ግን የአንተ ነው፡፡ ዳግማ ተንሳኤም አለ፡፡ኦርቶዶክሳዊ መእምናን፣ እየሰገዳችሁ!!
ሙስሊም ወገኖች በረመዳን ዱዓችሁ ፅኑ!!
መልካም የህማማት ሳምንት!!!
(ማስታወሻ፡- በክፍል ሁለት የዐማራን ልዩ ኃይል ለማፍረስ የተጠቀሱት ሰባት ምክንያቶች እንዴት ዱቄት እንደሆኑ እናያበታለን፡፡
ይህች ጽሑፍ ከሰሞኑ በጅምላ ለሚታሰሩ የዐማራ ልጆች መታሰቢያ ትሁንልኝ)
ሙሉዓለም ገ/መድኀን
ከሁመራ-ጎንደር