የአማራ ክልል ውሎ፣ መጋቢት 30 ቀን 2015 ዓ/ም
ችግርና ቀውጥ በተነሳ ቁጥር ህዝብ መረጃ እንዳያገኝ ኔትዎርክ መዝጋት የለመደው፣ የአብይ አህመድ አገዛዝ በብዙ ቦታዎች የኦንተርኔትና የኔትዎርክ አገልግሎቶች እንዲቆራረጡ የማድረግ አሳፋሪና አፋራሽ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡
እንደዚያም ሆኖ ግን፣ የአብይ አገዛዝ ትልቅ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊና ወታደራዊ ክስረት እየደረሰበት እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡
የህዝብ አመጽና ቁጣ
ከመጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ፣ ህዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ ፣ እንዲሁም የአማራ ልዩ ኃይልንና ፋኖዎችን ትጥቅ አስፈታለሁ ያለውና፣ ለኦነጋዊው አብይ አህመድ አገዛዝ የሚታዘዘውን ጦር እንደልቡ እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ ፣ መንገዶችን የመዝጋት ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች በበርካታ የአማራ ክልል አካባቢዎች እየተደረጉ ነው፡፡
– በዋገመራ ዞን ፡ በኮረም፣ ኦፍላ፣ ዛታ፣ ሰቆጣ ከተሞች፣
– በሰሜን ወሎ ዞን ፡ በቆቦ፣ ወልዲያ፣ መርሳ፣ ኡርጌሳ፣ ጎብዬ፣ ጋሸና፣ መቄት፣ ዓላማጣ፣
– በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በይፋት/ራሳ፣ ምንጃር/አረርቲ፣ ሸዋሮቢት፣
– በምዕራብ/ደቡብና ሰሜን ጎንደር፣ በመተማ፣ ገንዳ ውሃ፣ ዳባት፣ ወረታ ፣ ፎገራ እንዲሁም ጎንደር ዙሪያ፣
– በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ በደብረ ማርቆስ፣ ደጀን፣ አባይ በረሃ፣ ቢቸና፣ ግንደ ወይን፣ ደብረወርቅ፣ ሉማሜ አዋበል፣
– በምእራብ ጎጃም ዞን፣ በደምበጫ፣ ቡሬ፣ ጅጋ፣ መራዊ፣ ፍኖተ ሰላም፣
እና ሌሎች ቦታዎች፣ ባመረረ መልኩ ነው በብልጽግና አገዛዝ ላይ፣ ያለውን ብሶት፣ ምሬትና ተቃውሞ ህዝብ እየገለጸ ያለው፡፡
ጀነራል አበባው ታደሰ፣ በቴሌቪዥን መስኮት በመቅረብ፣ “ከትግራይ ተማሩ፣ እምቢ ያለ ካለ (አብይ አህመድን የማይታዘዝ ማለቱ ነው) ፣ ልክ እናስገባቸዋለን” በሚል ህዝቡን ለማስፈራራት የሞከረ ቢሆንም፣ የህዝቡ ግብረ መልስ ግን ተቃውሞዉን የበለጠ ማጠናከር ሆኗል፡፡
በጎንደር ከተማ ፣ “አብይ ኦነግ ነው”፣ “አማራ ተነስ” ፣ “ከልዩ ኃይላችን ጎን ነን”፣ “ብልጽግና ይውደም” የሚሉ መፈክሮች በትልቁ ተጽፈው በብዙ ቦታዎች ተለጥፈዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ የህዝብ መዓበል የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ማዕበል፣ ውስጥ ይሰሙ ከነበሩ ድምጾች መካከል “ዘመነ ካሴ፣ ያሳምነው ልጅ”፣ “ይለያል ዘንድሮ”፣ ” አብይ አህመድ ይውረድ” የሚሉ ነበሩ፡፡
የአማራ ልዩ ኃይሎች ሁኔታ
============
እስከ አሁን በተገኘው መረጃ፣ በብዙ ቦታዎች ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት የታቀደውና የታሰበው ሙሉ ለሙሉ ከሽፏል፡፡ ባህር ዳር ከተማ ጨምሮ ትጥቁን የፈታን አንድም የልዩ ኃይል አባል የለም፡፡
በአንዳንድ ቦታዎች ተኩስ የነበረ ቢሆንም፣ በብዙ ቦታዎች የመከላከያ አባላት የህዝቡን ቁጣ አይተው፣ እንዲሁም አብረውን በየጦር ሜዳው ሲዋጉ የነበሩ ወንድሞቻችን ላይ አፈሙዝ አናዞርም ብለው የተመለሱበት ሁኔታም እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ ህዝቡን ልዩ ኃይሎችን፣ ፋኖዎች፣ እንዲሁም የመከላከያ አባላት በማነጋገር ፣ መረጋጋት እንዲመጣ ማድረጋቸውን እየሰማን ነው፡፡የአማራ ልዩ ኃይል የተለያዩ ብርጌዶችም አንድነታቸውንና ትስስራቸውን እያጠናከሩ ሲሆን፣ ከፋኖ ህዝባዊ ኃይል ጋር በመናበብና በንቅጀት መስራት ጀምረዋል፡፡
በጎንደር፣ በሰቆጣ፣ በመተማና በርካታ ቦታዎች የአማራ ክልል እናቶችና እህቶች፣ ለአማራ ልዩ ኃይሎች ያላቸውን ድጋፍና አጋርነት በማሳየት፣ እንጀራ፣ ዳቦ ፣ ስንቅ እየያዙ በመምጣት፣ ለልዩ ኃይል አባላት ድጋፋቸውንና አጋርነጋቸው እያሳዩ ነው፡፡
የአማራ ክልል መንግስትና ፊዴራሉ አገዛዝ
====================
የአማራ ክልል መንግስት ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ በርካታ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ሸሽተው፣ ወደ አዲስ አበባና ናዝሬት እንደሄዱ ይነገራል፡፡ የክልሉ ርእስ መስተዳደር ዶር ይልቃል ከፍያለ ፣ ለስራ ጉብኘት ወደ አውሮፓ ከሄዱበት የተመለሱ ሲሆን፣ ወደ ባህር ዳር ሄደው እንደነበረ፣ ሆኖም ግን ባህር ዳር ይቆዩ፣ ወደ አዲስ አበባ ሌሎችን ለመቀላቀል ይሄዱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡
አንድ ግልጽ የሆነው ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአማራ ክልል ብልጽግና መንግስት ፣ እንደ መንግስት በባህር ዳር እየተንቀሳቀሰ እንዳልሆነ ነው፡፡ ከታችኛው የዞን አመራሮች ጋር ያለው የ ዕዝ ሰንሰለት ተበጥሷል፡፡
በፌዴራል መንግስቱና በመከላከያ አመራሮች ውስጥ ከፍተኛ የርስበርስ ውዝግቦች እንደተነሱም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መንግስት የወሰደውን አፍራሽ ውሳኔ እንዲያነሳና የህዝቡን ጥያቄ በማዳመጥ ያለውን ችግር በውይይት መፍታት፣ ነገሮችን ማለዘብ ያስፈልጋል የሚሉ አመራሮች ቢኖሩም፣ አብይ አህመድ እነርሱም ሊሰማቸው አልቻለም፡፡ “አሰለጠንኩ፣ አደራጀሁ” ባለው ጦር በመመካትና፣ ምን አልባትም ህወሃቶች ያግዙኛል በሚል፣ የኃይል እርምጃ መውሰድ ፣ የተነሳዉን ተቃውሞ በጉልበት ለመጨፍለቅ፣ ከሰኞ ሚያዚያ 2 ቀን ጀምሮ፣ በኦነግ ጀነራሎች እንድትመራ ለማድረግ፣ በአማራ ክልል ኮማንድ ፖስት ለማቋቋም እንዳሰበ ምንጮ እየተናገሩ ነው፡፡
ማጠቃለያ
====
በአማራ ክልል ሕዝባዊ አመጽ ከተቀሰቀሰ አንድ ሳምንት ሆነው፡፡ ቀን በሄደ ቁጥር ተቃውሞው እየተጠናከረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም፡፡
አብይ አሀመድ ጎንደር፣ ጎጃም እያለ የአማራውን ማህብረሰብ ለመከፋፈል ብዙ ሞክሯል፡፡ ሆኖም ሙከራዎቹ ከሽፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመላው የአማራ ክልል ፣ ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር ህዝቡ አንድ ሆኖ የተነሳበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በአማራ ክልል ያለው ህዝብ፣ አማራው ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በአማራ ክልል እየተደረገ ላለው የሰላም፣ የፍትህ፣ የእኩልነት፣ በህይወት የመኖርና ኢትዮጵያን ከጥፋት የማዳን ትግል አጋርነቸውን እየገለጹ ነው፡፡
አገዛዙ የህዝብን ጥያቄ ከመስማትና ከመቀበል ውጭ ሌላ ምርጫ የለውም፡፡ ብረት ይዞ ህዝቡን ለማንበርከክ ከመጣ የሚገጥመው እድል መደምሰስ ነው፡፡ አገዛዙ ካልሰማ፣ ህዝባዊ ሰላማዊ እምቢተኝነት ከማድረግ ባለፈ ፣ የህዝብን ጥያቄ ለማፈን በተነሱት ላይ እርምጃዎች ለመውሰድ ማህበረሰቡ ሊገደድ እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ አብይ አህመድና የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች፣ ከእሳት ጋር ባይጫወቱ ይሻላቸዋል፡፡ ህዝቡ እኮ ለሰላም፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎ እንጂ እየተጎዳም እስከአሁን የታገሳቸው፣ አንዴ ተነስቶ እፍ ቢላቸው ድራሻቸ አይገኝም፡፡