ለዘመኑ የሀገራችን ቤተ-መንግሥቱን ለተቆጣጠሩት መንደርተኛና ጎጠኛ ‘ቦልታኪዎች‘ /
እ’ስራና ቅል ……..
አፈጣጠራቸው፣ ቢሆንም ለየቅል፤
እንደ አቅማቸው፣ ሠርተው
በሀሳብ – ተግባር፣ ተግባብተው፤
ሰላም አግኝተው፣ አንድነት
ይኖሩ ነበር፣ በአንድ ቤት።
በፍቅራቸው፣ የሚቀናው
ዱባ ግን፣ ጉረቤታቸው፤
ያሴር ነበር ሴራ፣ የሚያሥር
ይሸርብ ነበር ነገር፣ የሚያደናግር፤
ያጠምድ ነበር፣ ወጥመድ
ባረፉበት ቤት፣ ሳይቀር በመንገድ።
እ’ሰራን ሲያገኘው፣ ብሎ ጎንበስ – ቀና
የሰላምታ አይነት፣ ያዥጎደጉድና፤
በማር የተቀባ፣ የመርዝ ቃላት
ይነግረው ነበረ፣ መስሎ ተቆርቅሪ፣ ለሱ ያዘነለት።
ቅልንም ሲያገኘው ወይም ቤቱ ሄዶ
ከአስረደው በኋላ፣ እንደሚፈልግው በፍቅሩ ተገዶ፤
ምክር ነው እያለ፣ ነገር ይነግረዋል
በማያውቀው ጉዳይ፣ ደሙን ያፈለዋል።
ከለ’ታት አንድ ቀን፣ ሥራ በፈቱበት
በነገር ተይዘው፣ ”በተሰለቡበት”፤
እ’ስራ ተክዞ፣ ወደ ቤት ሲሄድ
ቅልም በበኩሉ፣ ሲያስብ በምንገድ፤
ዓይን – ለዓይን ተጋጩ፣ እጅግ ተፋጠጡ
በሰላምታ ፋንታ፣ ንትርክ መረጡ።
ቅል ኮራ ብሎ፣ ምላሱና ሳለና
ዱባ ከነገረው፣ ብዙ አስታወሰና፤
”እኔ ከ’ንተ አላንስም፣ እንዲያው ባልበልጥህ ”
በማለት ጀመረ፣ “አንተ እ’ስራ ሆድ ነህ!”።
“ለሰው ልጅ አገልጋይ፣ ወሃ ለመያዝ፣ ተመራጭ እኔ ነኝ
እንደ አስፈለጋቸው፣ የሚሽከረክሩኝ።”
”እኔ ቅል ብቻ ነኝ፣ ቶሎ ውሃ በመሙላት የሚመርጠኝ ሰው
ይዘውኝ ቢዞሩ፣ የማልከብዳቸው፣ የምመቻቸው።”
ነገሩ ተካሮ፣ ዱላ መረጡና
ይጣለዙ ጀመር፣ በሰፊው ጎዳና።
ገላጋይ መስለው፣ የቀረቡት ሁሉ
ዘወር ብለው ሄዱ፣ ዱላ እያቀበሉ።
እነሱም ቀጠሉ፣ ቀጠሉ…. ቀጠሉ
እስቲ እናስብበት፣ ለነገም አላሉ
ጎዳናውን አልፈው፣ ሜዳውንም ሞሉ።
የመደባደቡ፣ ኃይል ቢያጥራቸው
ተያይዘው ወደቁ፣ ‘ርስ – በ’ርሳቸው
ብትንትንም አሉ፣ መሬት ብትነካቸው።
የእ’ስራና ቅል፣ ዱባ ጉረቤት
ጠቡን ሲከታተል፣ ቁጭ ብሎ በ’ርቀት፤
”ከቶ ማን ያሸንፍ፣ ፈሪ ማን ይሆን”
እያለ ሲደሰት፣ በማየት ፍልሚያውን፤
ወድቀው፣ ተበታትነው፣ ተፈረካክሰው
ሜዳውን ሞልተውት፣ ሲያስታውላቸው
”ለካስ ሁለቱም ባዶዎች ነበሩ!” በማለት ሳቀና
ቤታቸውን ሊወርስ፣ ሄደ እየተዝናና።
——-—–//———–ፊልጶስ
E-mail: philiposmw@gmail.com
*”ያለተጻፈ መጻፍ ” ከተሰኘው የግጥም መደብል መጻህፌ የተወሰደ::
One attachment • Scanned by Gmail