ብሊንከን ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተወያዩ

#image_title

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋራ ዛሬ ረቡዕ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ብሊንከን ከአቻቸው ደመቀ መኮንን ጋር ውይይታቸውን ከማካሄዳቸው በፊትም በጋራ የኢትዮጵያን ባህላዊ ቡና ሲጠጡ ታይተዋል።

በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት ብሊንከን “ወደ አፍሪካ መመለስ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፣ በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የታየው ሰላም ዘላቂ ሆኖ ወደፊት እየተራመደ ባለበት በዚህ አስፈላጊ ወቅት።

በዚህ እና ሌሎች አብረን የምሰራባቸው፣ እርስዎም እንደተናገሩት በኢትዮጵያ እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክሩ በርካታ ጉዳዮች ዙሪያም ከእርስዎ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመነጋገር በጉጉት እጠብቃለሁ” ብለዋል።

ብሊንከን በንግግራቸው የጠቀሱት የሰላም ሥምምነት፣ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው የትግራይ ክልል የተካሄደውን ግጭት ለማስቆም ባለፈው አመት የተደረሰውን የሰላም ሥምምነት ነው። አክለውም፣ ይህን ሰላም የማስጠበቁ ስራ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፀዋል።

“ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ግን በሰሜን የዘለቀውን ሰላም ማስጠበቅ እና ወደፊት የሚኖረንን ግንኙነት ማጠናከር ነው።” ብለዋል።

በትግራዩ ግጭት ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን የንግድ ስምምነቶች አቋርጣ የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ያንን ስምምነት ወደቦታው ለመመለስ ዝግጁ ናት።

ብሊንከን በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ ከፌዴራል እና ከትግራይ ክልል ባለስልጣናት ጋር አዲስ አበባ ላይ ለመገናኘት እቅድ ይዘዋል።

በቀጣይ ወደ ኒጀር በሚያደርጉት ጉዞም፣ በአካባቢው በሚገኙ ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው ቡድኖች ላይ ያነጣጠረውን የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ ያስተናገደችውን ሀገር በመጎብኘት የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይሆናሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከሃረር እስከ ጎዴ እንዲሁም ሃርጌሳ አፈሳው እና አፈናው ተጥውጡፏል

VOA

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share