ጳጳስ መስቀል ጨብጦ ከሳጥናኤሉ ተከታይ ድርድር ሲያደርግ ውል ሲያስር፣
ተመልካች ውሉ እንደሚጠና በማመን “እንኳን ደስ አለን” እያለ ሲጨፍር፣
የሚመለከት መለኮት በአንክሮ የትዝብት መስኮት በርግዶ ከጠፈር፣
ምን በጎ ነገር አይቶብን መስልጦ ያውጣን ከገባንበት መቀመቅ ከችግር?
ሳጥናኤል ሰውን ለመጥለፍ እባብን መርጦ አፉን አስልቶ ሲልከው፣
ሄዋን አዳምም የበለስ ፍሬ መጋጡ ገደል የሚከት መሆኑ ሳይገባው፣
በቀለበት ውስጥ አዙሪት ስንሽከረከር አምስቱን ዘመን ደፈነው፡፡
የጥፋት ውሀው ቅጣቱ ምልክት ልምድና ትምህርት ሳይሆነው፣
ቃል ኪዳን ብሎ ያሳየው ቀስተ ደመና ወይም ደመ ነፍስ ሳይገታው፣
ጫካ ተሚኖር አውሬ አንሶ አንዱ ሌላውን በአገሩ ምድር አረደው፡፡
የጭራቅ የእርጉሞች ተንኮል በክፋት የሚልቅ ሰዶም ገሞራን፣
ሕዝብን ተሕዝብ አናክሶ በደም አበላ የሚያለብስ መሬቱን፣
የቅጣት እሳት በማምጣት አቃጥሎ አሁንም እንዳያነዳት ምድሪቱን፣
የእውነት የፍትህ ሰዎች በገዳማት ውስጥ ታላችሁ በፀሎታችሁ ታደጉን፣
አንድም የእውነት ሰው ቢገኝ መለኮት ቁጣዬን አስታግሳለሁ ስላለን፡፡
ሰውን በሥራው መዝን እያለ ደጋግሞ እያስተማረ መጣፉ በአዲስ ኪዳኑ ብሉዩ፣
በማያልቅ የውሸት ስብከት እየተነዳ ምሁር ተብየው ካህኑ ሼሁ መንጋው፣
የሙሴ ኢያሱ የዳዊት ዓይነት መሪዎች እንዴት ባገር ተዘርተው ይብቀሉ?
ተፈሪሳውያን አብረው እስጢፋኖስን በድንጋይ ወግረው የገደሉቱ፣
ተዳር ቆመውም ብትር እያቀበሉ በለው እያሉ በጩኸት ያስወገሩቱ፣
ዛሬም ተስልጣን ወንበር ቁጭ ብለው ፀፀት ሱባኤ ንስሃ ገዳም ሳይገቡ፣
ፍትህ ፍቅርና ሰላም እንዴት ተዘርተው በቅለው አብበው ለፍሬ ይብቁ?
በሐሰት ከሳሽ ነፍሰ ገዳዮች በድሎት ተወንበር ዙፋን ያለ ነቅናቂ ቁጭ ብለው፣
ስመው ጠቁመው ሰጪዎች አሁንም እንደ ፍልፈሎች ተራብተው በርክተው፣
ፍርድ አጣማሚ ዳኛዎች ፍትህ መግደሉን እንደቀጠሉ በመዶሻቸው ጨፍልቀው፣
ሕዝብም እየተገዛ ዝምብሎ ተሸክሟቸው በጫንቃው እየተደፋም ተግራቸው፣
እግዜር ይቅር የሚለን ምን በጎ ተግባር የእውነትን መንገድ ስንከተል አይቶ ነው?
በእባቡ ምላስ እየተሰበክን መቼ የበለስ ፍሬ ግጦ መብላቱን ትተን ነው?
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
የካቲት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.