February 11, 2023
ጠገናው ጎሹ
“እስከ ዛሬ ስለ ክርስቶስ አስተምሪያለሁ ። ተምሪያለሁ። ዛሬ ግን ራሱን ክርስቶስን አይቸዋለሁ” ይህን የሚነግረን የተሰጠውን የዲያቆንነትና የሙአዘ ጠበብትነት ስያሜ ለርካሽ የግል ዝና እና ፍላጎት ማርኪያነት ካዋሉት ጨካኝና አደገኛ የዘመናችን አድርባዮች አንዱ የሆነውዳንዔል ክብረት ነው።
እርግጥ ነው ከዳንኤል አይነት ህሊናውን ከሸጠና ሃይማኖታዊ እምነትን ልክ ለሌለው የግል ፍላጎቱ ማርኪያነት ሽፋን ከሚያውል (ከሚጠቀም) የበግ ለምድ ለባሽ ክፉ ተኩላ እንዲህ አይነቱን እጅግ የለየለት ቅጥፈት መስማት ወይም ማንበብ የሚጠበቅ እንጅ ከቶ የማይጠበቅ አይደለም። በራሱም ይሁን በሰዎች (ከተገኙ) አማካኝነት ተገልጦ ለዳንኤልና ለመሰሎቹ የሚታይ እውነተኛ አምላክ (ክርስቶስ) መኖሩን እንኳን ለማመን ለማሰብም በእጅጉ ይከብዳል ።
ለዘመናት እና በተለይም ከራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በንፁሃን የግፍ ደምና የቁም ሰቆቃ ክፉኛ የተመረዘው የቤተ መንግሥት ፖለቲካ ታማኝ አማካሪ (በሰው አምሳል ቆሞ የሚሄድ ዲያብሎስ ለሆነ ሰው) ሊገለፅ (ሊከሰት) የሚወድ (የሚችል) እውነተኛው ክርስቶስ በፍፁም የለም። ሊኖር የሚችለው በዳንኤልና መሰሎቹ እኩይ ህሊና (አእምሮ) ውስጥ የተቀረፀ ወይም የብልፅግና ወንጌል (የአብይ ነቢያት) እንደሚሉን ከአብይ ጋር በቤተ መንግሥት ተሰይሞ የመከራውንና የውርደቱን ሥርዓተ ፖለቲካ እያራዘመ ያለው እጅግ ክፉ መንፈስ ነው።
የመፀፀትና ከስህተት የመመለስ ሰብአዊ ባህሪ ላልፈጠረበት እና ይልቁንም ወደ አስከፊው የኢሰብዊ ቁልቁለት ለሚወርድ ፍጡር ሁሉ ጥሩ ማሳያ ከዳንኤል የተሻለ ፈፅሞ የለ። ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አገላለፄን ለግልብ ስሜት በማይጎረብጥ ሁኔታ ብገልፀው ደስ ባለኝ ነበር። ዳንኤል ክብረት አታሎ ፣ መስሎና አስመስሎ የመኖር ባህሪው አብሮት የኖረ (ምናልባትም አብሮት ያደገ) ሊሆን እንደሚችል በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም መገመት ግን አያስቸግርም። ይህ ግን የራሱና ምናልባትም በእርሱ ዙሪያ የነበሩና ያሉ ወገኖች ጉዳይ ነውና ለእርሱ/ለእነርሱ የሚተው መሆን እንዳለበት በሚገባ እረዳለሁ።
ይህ አይነት እጅግ አደገኛ ባህሪ አድጎና ጎልብቶ የፖለቲካውን ቤተ መንግሥትና መንበረ ሃይማኖትን እየቀላቀለ አገርንና ወገንን ለአስከፊና ማለቂያ ለሌለው መከራና ውርደት ሲዳርግ እየታዘቡ ማለፍ ግን ለሰማያዊውም ሆነ ለምድራዊ ህይወት ፈፅሞ ፀር ነውና በግልፅና በቀጥታ መነጋገሩ ነው የሚበጀው። የዳንኤል ክብረትን የቤተ መንግሥት አማካሪነት ምንነትና እንዴትነት ከመር ለተከታተለና ሚዛናዊ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው ይህንኑ መሪር እውነታ ፈፅሞ አይስተውም። እናም ለዚህ ነው አካፋን አካፋ ከማለት ይልቅ ልፍስፍስ ምክንያት እየደረደሩ የተለየ ለውጥ መጠበቅ ወይ ድንቁርና ወይም አድርባይነት ከመሆን የማያልፈው። እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት ተዋርዶ አዋራጆችና ክፉ ሰዎች ቢያንስ ነውር ነው ለማለት የፖለቲካና የሞራል ወኔው በእጅጉ የሚጎድለው ትውልድ ስለ ግዙፉና ጥልቁ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ለምንና እንዴት እንደሚደሰኩር (እንደሚያላዝን) ሲያስቡት በእጅጉ ያስጨንቃል።
አዎ! እንደ ዳንኤል ክብረት አይነት እጅግ አደገኛ አድርባዮች በዲያቆንነትና በሙአዘ ጥበባትነት ስም በአገርና በወገን ላይ እጅግ አስከፊና የማያቋርጥ የመከራና የውርደት ዶፍ ለሚያወርደው የሸፍጠኞችና የአረመኔዎች ሥርዓተ ፖለቲካ ራሳቸውን አሳልፈው የሸጡ ወገኖችን በአግባቡ ለመገሰፅና ለማረም ወኔው የከዳውን የሃይማኖት አባትነት በአግባቡና በአክብሮት ትክክል አይደለም ማለትን እንደ ሃጢአት ወይም ብልግና የሚቆጥር ትውልድ ስለ የትኛው የሃይማኖት ነፃነትና የሰብአዊ መብት መከበር እንደሚናፍቅ ለመረዳት በእጅጉ ይከብዳል።
የትናንቱና የዛሬው ለመግለፅ የሚያስቸግር አጠቃላይ ውድቀታችን መሪር ትምህርት ሆኖን የተሻለ ነገንና ከነገ ወዲያን ለመፍጠር እንደምንችል ተስፋ እያደረሁ አበቃሁ!