በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረው አስቸኳይ ምልዐተ ጉባኤ በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ቅዱስ ሲኖዶስ በሚል በሕገ ወጥነት በቀድሞ ስማቸው አባ ሳዊሮስ የተባሉ ግለሰብ መሪነት ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ቀን ድረስ በተለያዩ ክልሎች እና የፌዴራል መንግሥት በሚመራቸው ቦታዎች ውስጥ በሚገኙ የቤተ ክርስቲያኗ አህጉረ ስብከት የሆኑትን ሥርዓተ አምልኮዋን የምትፈጽምባቸው በየመዋቅሩ የሚገኙ አስተዳደር ቢሮዎችን ከሕግ አግባብ ውጭ የቤተ ክርስቲያኗ እምነት ተከታይ ያልሆኑ ግለሰቦችን በማካተት በመንግሥት ልዩ ኃይል ድጋፍ በመውረር እና በመስበር የሕግ አግባብነት በሌላቸው እንዲሁም መብት እና ጥቅም ሳይኖራቸው በማሸግ ቤተ ክርስቲያን ላይ ወረራ እየተፈጸመባት የሚገኝ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ለመረዳት ችሏል፡፡
መንግሥትም ሰላም እና ደህንነትን ከማስጠበቅ ባለፈ የሕይወት እና የአካል ደህንነት መብትን እንዲሁም የመንቀሳቀስ መብትን በመገደብ ያለአግባብ ታግተው መቆየታቸውን ከሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ከዚህ ቀደም መግለጻችን የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ ድርጊታቸውም ሳይታቀቡ በጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ያሬድን በሕገ ወጥ መልኩ የዜግነት መብታቸው ተጥሶ በደረቅ ሌሊት በማሰር እና በማዋከብ ከሀገረ ስብከታቸው ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን እንዲሁም የተለያዩ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳትን ወደየ አህጉረ ስብከታቸው እንዳይሄዱ ማስፈራሪያ በመላክ የቤተ ክርስቲያችንን ክብር እና ልዕልና እጅጉን የሚጎዳ እና አሳዛኝ ድርጊት እየተፈጸመባት ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የየሀገረ ስብከት ሥራ አኪያጆችንና ሠራተኞችን፤ አገልጋይ ካህናትንና ምእመናን በሕገ ወጥ መልኩ በማሰር እንደ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ባለመወጣቱ ቤተ ክርስቲያናችን እጅጉን አዝናለች፡፡
ከዚህም አልፎ መንግሥትም በቤተ ክርስቲያችን በኩል በተደጋጋሚ የተሰጠውን ማሳሰቢያ ችላ በማለቱ ምክንያት በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ ሕገ ወጦቹ መንግሥትን ተገን በማድረግ የቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጥ መልኩ ወረራ ለመፈጸም ባደረጉት እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያንችንን ለመጠበቅ በወጡ ምእመናን ላይ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የአደባባይ የግድያ ወንጀል ተፈጽሟል፡፡ ሌሎች በቁጥር ያልታወቁ ምእመናንም ላይ ከፍተኛ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ይህንንም ሕገ ወጥ ተግባር በተመለከተ ተገቢውን ሕጋዊ የሰላም እና የደህንነት ከለላ እንዲያደርጉ ለሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቤተ ክርስቲያናችን ብትሰጥም ይህንን ማሳሰቢያ ወደጎን በመተው መንግሥት ሕገ ወጡን ቡድን በመደገፍ እና በማስፈጸም ከላይ የተገለጹትን አሳዛኝ ድርጊቶች በይፋ በአደባባይ ፈጽሟል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጠራው አስቸኳይ ጉባዔ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡
- በብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት እና የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፤ የክፍል ኃላፊዎች፤ ካህናት፤ አገልጋዮች እና ምእመናን ላይ የተፈጸመውንና እና እየተፈጸመ ያለውን ሕገ ወጥ እስር እና ወከባ ቅዱስ ሲኖዶስ በፅኑ አውግዟል፤
- በጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም በምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት በሻሸመኔ ከተማ በደብረ ስብሐት ቅዱስ ሚካኤል አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፤ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ የወጡት ምዕመናን ላይ ጭካኔ በተሞላ ሁኔታ የተፈጸመው ሕገ ወጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የተፈጸመው አሰቃቂ የሞት ድርጊትን ፍጹም ታወግዛለች፤ ተገቢውን ሲኖዶሳዊ እና ሃይማኖታዊ ጸሎት በማድረግ በሁሉም አጥቢያ ሥርዓተ ፍትሐት እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
- ቅዱስ ሲኖዶስ በጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ባስተላለፈው ውሳኔ እና በሰጠው መግለጫ መላው የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ጾመ ነነዌን ሙሉ የሱባዔ ጊዜ በማድረግ ጥቁር ልብስ ያለውን ትርጓሜ በመግለጥ እንድንሰነብት መግለጫ መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
3.1. ለዚህም ዝርዝር አፈጻጸም መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 3 ቀናት በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የምትገኙ ማናቸውም ካህናት እና ምዕመናን ሙሉ ጥቁር ልብስ በመልበስ በየአብያተ ክርስቲያናት እና በገዳማት ያለውን ሥርዓተ ጸሎት እንድትመሩ እና እንድትከታተሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3.2. በየትኛውም እንቅስቃሴ ይህንን ጥቁር ልብስ በመልበስ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ ንቁ በመሆን እንድትፈጽሙ፤ ሆኖም ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ዓለም አቀፍ የጸሎትና የምህላ መርሐ ግብር ካወጀበት ቀን በኃላ በተለያዩ ከተሞች የጥቁር ልብስን ሆነ ተብሎ ከገበያ እንዲወጣ እየተደረገ መሆኑን በመረዳታችን ምዕመናን ያላችሁን ተመሳሳይ አልባሳት በመጠቀም የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን በእንቅስቃሴያችሁ ሁሉ እንድትፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3.3. በነዚህ ቀናት ውስጥ አገልግሎቱ በድምጽ ማጉያ እንዲከናወን እና የሙሉ ጊዜ ሆኖ በሰባቱ የጸሎት ሰዓታት እየተጠበቀ በተመሳሳይ ሰዓታት ለአምስት ደቂቃ ያህል በማያቋርጥ ደወል በመደወል የማስተጋባት ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
3.4. ይህንንም የየአህጉረ ስብከት፤ የወረዳ ቤተ ክህነት እና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤያት በመከታተል እንድታስፈጽሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
3.5. የአኃት አብያተ ክርስቲያናት፤ የኦርቶዶክስ ዓለም፤ እውነቱን የምታውቁና የምትደግፉ ማናቸውም ኃይማኖታዊም ሆነ ማህበራዊ ተቋማት እና ግለሰቦች የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ በመደገፍ በአንድነት ትቆሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላፋለን፡፡
- በነዚህ የጸሎትና የምሕላ ጊዜያት የደነደኑ ልቦች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥሪ ሰምተው የማይፈጽሙ እንደሆነ
4.1. በየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምእመናን ከጠዋቱ 11፡00 ጀምሮ በየአጥብያቸው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ጠዋቱ 1፡30 ድረስ ሥርዓተ ቅዳሴው ከተፈጸመ በኃላ ከጠዋቱ 2፡00 ላይ ሁሉም ገዳማት፣ አድባራት እና አብያተ ክርስቲያናት በተመሳሳይ ሰዓት ደወል በመደወል ምእመናን በሙሉ እስከ ጠዋቱ 2፡30 ድረስ እንዲሰባሰቡ በማድረግ ከየአጥቢያው በመነሳት የጥምቀተ ባህር ወይም የመስቀል አደባባይ ላይ ታቦተ ሕጉን በማክበር፤ በማጀብ በዝማሬ እና በእልልታ በአንድ ቦታ በመሰባሰብ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
4.2. የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ዝርዝር አፈጻጸም መመሪያን በተመለከተ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምናሳውቃችሁ መሆኑን አውቃችሁ ዝግጅት እንድታደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
- ማንኛውም የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ቤተ ክርስቲያን ያዘዘችውን ሰላማዊ ጥያቄ በሚከወንበት ማንኛውም የአገልግሎት ጊዜ ተግባራቱ ሰላማዊ መሆናቸውን በመገንዘብ ተገቢውን ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት አውቆ እንዲያስፈጽም ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ
ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ