ክልፍ ሶስት
“The worst type of tribalism is groups aligned to destroy other groups, such as through ethnic cleansing and genocide. We have heard the word tribalism used a lot today in reference to our politics. Today in our political world, we have “bad tribalism.” Bad tribalism is a group identity that fosters the bullying and scapegoating of others not like you.”
Dr. Elizabeth Segal, in “When tribalism goes bad,” Psychology Today, March 20. 2019
“እስልምናም ይሁን ክርስትና ምእመኑ ለእምነቱ አጅግ ቀናዒ ነው። እነዚህን ሁለት ሃይማኖቶች መቆጣጠር ሕዝቡን ለመቆጣጠር አመች እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ያ ሕገ ወጥ ቡድን (ማለትም ትህነግ/ህወሃት) ችግር እንዳይገጥመው፤ የተለያዩ ስትራተጅዎችን ነድፎ በሃይማኖት ተቋማቱ ላይ እጁን ሲያስገባ ነበር። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን የጳጳሳትና የፓርትያርክ ምርጫ ላይ እጃቸውን በመንከር መጀመሪያ የራሳቸውን ሰዎች እንዲሾሙ አደረጉ፤ ከዚያም ሁለት ቦታ በመክፈል ለማዳከምና ለመቆጣጠር ሞክረዋል።”
ዐብይ አሕመድ፤ የመደመር መንገድ ገጽ 153
ይህ ትንተናና ምክረ ሃሳብ ኢላማ ያደረገው የብልፅግናን ፓርቲ የበላይ አመራር፤ አማካሪዎችና አባላትን ነው። ብትስማሙም፤ ባትስማሙም ለተከታታይ ትውልድ ደህንነትና ለኢትዮጵያ ዘላቂነት ስትሉ ራሳችሁን ገምግሙ፤ ህሊናችሁን ፈትሹ። የመንግሥታችሁ የመጀመሪያ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የዜጎችን ደህንነት መታደግ መሆኑን ተቀበሉ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከላይ የጻፉት ትክክል ነው። ህወሃት ሃይማኖትን የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎት ነበር።
በተመሳሳይ፤ በአሁኑ ቀውጢ ወቅት፤ ዖነጋዊያን በተቀነባበረ ደረጃ የሚመሩት የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ ለፖለቲካ የበላይነት ሲሉ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን አይጠቀሙም ለማለት አልችልም። በተጨማሪ፤ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ እስካልተፈታ ድረስ በሴራው የግብፅ ኦርቶዶክስ ተቋም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተቋም መደገፉ እንዳለ ሆኖ፤ የግብጽ መንግሥት ግን በኦርቶዶክሱ ኃይማኖት ክፍፍል ሴራ እንደሌለበት በምን እናውቃለን?
የግብጽ መንግሥት ህወሃትን፤ ኦነጋዊያንና ሌሎችን ጽንፈኞች/ሽብርተኞችና ተገንጣዮች እንደሚደግፍ አልጠራጠርም። ዋናውና መሰረታዊው የኢትዮጵጵያ ችግር ግን የውጭ ሴራ ሳይሆን የውስጥ ዘረኛንት፤ ብሄርተኛነት፤ ወንበዴነት፤ ሌብነት፤ ሙሰኛነትና የአገዛዝ ውድቀት ነው (failed governance)።
የሕዝብ ድምጽ ዘገባ አልተለመደም እንጅ፤ ዛሬ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በመንግሥት አመራር ላይ እምነት የለውም። ለዚህ ዋናው ምሳሌ የብልጽግና መንግሥት አመራር ለዜጎች ህይወትና ደህንነት ደንታ ቢስ መሆኑ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ የመምህራን ጉባኤ ስለ ዜጎች እልቂት ተደጋጋሚነት ምክንያት ሲጠየቁ “መንግሥት በግድያው ውስጥ የለበትም” ያሉት ማዘናጊያ ብቃትን ሆነ ሃላፊነትን አያሳይም። አንድ መምህር የመንግሥቱን አመራር “ያልበሰለ/ያልጎለመሰ/ያላደገ (immature)” ያሉት ትክክል ነው።
የብልፅግና ፓርቲ 70 ሚሊዮን አባላት ባለው በኦርቶዶክ ሃይማንት ተቋም ላይ በተከሰተው ከፋፍለህ ግዛውና ብላው ስትራተጅ እጁ የለበትም ወይ? የሚለውን ጥያቄ በማያሻማ ደረጃ መመለስ ያለበት ገዢው ፓርቲ፤ በተለይ ጠቅዋላይ ሚንስትሩ ናቸው።
በአንድ አገር ሁለት አይነት መርህ፤ ሁለት አይነት ፍትህ ወዘተ ሊኖር አይችልም። ህወሃትን ተችቶ የኦነጋዊያንን ጽንፈኞች ሴራና ተንኮል ለመካድ ወይንም ለመደበቅ ወይንም ለመሸሽ አይቻልም።
በኦሮሞ የብሄር ጽንፈኞችና ሽብርተኞች ቀስቃሽነት በኦርቶዶክስ ኃይማኖት መርህ (ሲኖድ) ላይ የተካሄደው ክህደትና ውንብድና ትህነግ/ህወሃት ከሰራው ሴራ ሊለይ አይችልም። እንዲያውም የባስ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በመጽሃፋቸው ላይ እንዳስቀመጡት፤ “ምእመኑ ለእምነቱ ቀናዒ ነው።” ራሱን መስዋእት ለማድረግ ይችላል ማለት ነው።
እኔን በባሰ ደርጃ የሚያሳስበኝ ከጀርባው ያለው ሁኔታ ነው። በተገላቢጦሽ ችግሩን የሚያባብሱት ራሳቸው በኦርቶክስ ሃይማኖት በውስጥና በውጭ የተሰገሰጉት “የአማራ ጽንፈኞች ናቸው” የሚለውን አሳዛኝና አሳፋሪ የፈጠራ ትርክት መስማቴ ነው። የዚህ ትርክት ዋና የጥቃት ኢላማ የአማራው ብሄረሰብ መሆኑ አይካድም።
ወደ ኋላ ዞር ብለን ብንመለከት፤ ይህንን የፈጠራ ትርክት ህወሃቶች በተቀነባበረ ደረጃ ያሰራጩት “ትግራይ ጀኖሳይድ፤ ትግራይ ፋሚን፤ ትግራይ ከበባ” የሚለውን ፕሮፓጋንዳ ለመጥቀስ ይቻላል። በተመሳሳይ፤ ኦነጋዊያን ኦርቶዶክስን በሚመለከት ይህንን ሃይማኖት “የሚመሩትና የሚያስተጋቡት ሃበሻዎች ናቸው” የሚለው ከተሰበከ ብዙ አስርት ዓመታት ሆኖታል።
ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ ሹክሹክታው ለኢትዮጵያ አለመረጋጋትና በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖር የሚያደርገው የኦርቶዶክስ አመራር ነው። ይህንን የአማራ ብሄር ጽንፈኞች ምሽግ ለይቶ ማጋለጥ፤ ማስፈራራትና ማሳደድ አስፈላጊ ነው የሚል አደገኛ ስትራተጅ መኖሩ ይነገራል። በበክሌ ይህ እንደማይሆን እመኛለሁ።
የኢትዮጵያ ብልጽግና መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኦርቶዶክስ እምነት ላይ የተከሰተውን የመከፋፈል ሴራ ለምን አላወገዙትም? ለምን የማያሻማ እርምጃ አልወሰዱም? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ ብናስብበት መልካም ነው እላለሁ። ማሰብ ብቻ ግን በቂ አይሆንም። ድጋፋችን የማሳየት ግዴታችን መወጣት አለብን። ድጋፍ ስል ለኦርቶዶክስ አመራር የአንድነት ጥሪና አቋም ሙሉ ድጋፍ እንስጥ ማለቴ ነው።
የኦርቶዶክስ ቤተከርስቲያን የአማራ ጽንፈኞች ምሽግ ናት የሚለው አደገኛና ከፋፋይ ትርክት መሰረት አንድ ነው። ይኼውም፤ የአማራውን ሕዝብ ለመጨፍጨፍና ለማዋረድ ከሚደረገው አጠቃላይ ሴራ የተለየ አለመሆኑ ነው። በአጣየ፤ በደራ፤ በወለጋ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ (መተከል) ወዘተ የሚካሄደው እልቂትና ውድመት መሰረታዊ ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል?
ኢላማ የሆነው የአማራው ሕዝብ ከእንቅልፉ ቢነቃ ይሻለዋል። በተለይ፤ በረባ ባልረባው የተከፋፈለው የአማራ ምሁር፤ ሊቀሊቃውንት፤ ሜድያ፤ ጫና ፈጣሪ ነኝ ባይ፤ ዲያስፖራ፤ ስብስብ ወዘተ መቀበል ያለበት ይህ ክፍፍል አማራውን የሚያስጠቃ መሆኑን ነው።
ሕገ መንግሥቱና የአስተደር መዋቅሩ ጸረ-ፍትህ፤ ጸረ-ዲሞክራሲ ነው።
ዋናው፤ መሰረታዊው ስርአት ወለዱና መዋቅራዊው ችግር የአማራው ብቻ ሳይሆን የኢትዮያም ጭምር ነው። አማራውንና እምነቱን ኢላማ ያደረገው ክስተት፤ ግፍና በደል፤ ዘውጋዊ እልቂት ለምን ተከታታይ ሆነ? ብሎ መጠየቅ አግባብ አለው።
እኔ ይህንን ክስተት የምመለከተው ከሃይማኖት ባሻገር ነው። በኦርቶዶክስ እምነት ላይ ያንዣበ\በው አደጋ ከተጠነሰሰ ውሎ አድሯል። በኔ ግምገማ ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው፤
አንደኛ፤ ኢትዮጱያን በአዲስ መልክ ለመቀየስ፤ ለማዋቀር፤ ለማስተዳደር፤
ሁለተኛ፤ ጥንታዊዋ ኢትዮጵያ የተመሰረተችውና የምትታወቀው በአማራ ብሄረሰብና በመሰረታቸው ተቋማት አማካይነት ነው ተብሎ ስለሚለፈፍ፤ ፈረንጆችም ይህንን ትርክት ይጋራሉ የሚል እምነት ስላለ፤ እንደ ኦርቶዶክስ እምነት፤ እንደ አማርኛ ቋንቋ ያሉትን እሴቶች ሙሉ በሙሉ እንዳልነበሩ ለማድረግና፤
ሶስተኛ፤ የአማራው ብሄረሰብ መሬት አልባ፤ እሴት አልባ፤ ተቋም አልባ፤ አገር አልባ፤ ሽባ እንዲሆን ለማድረግ የሚደረግ የተቀነባበረ ሴራ ነው።
ስለሆነም፤ ትህነግ/ህወሃት የተከተለውን መርህ የኦነግ ጽንፈኞች፤ ብሄርተኞች፤ በተተኪነት የሚያያምኑ ኃይሎች ከሚያደርጉት ሊለይ አይችልም። ይህ ተግዳሮት ለአማራው ሕዝብ ብቻ ስይሆን፤ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሳሳቢ አደጋ እንደሚሆን መገመት ያስፈልጋል።
ማንነቴ ይከበር የሚለው እንዳለ ሆኖ፤ ግን በማንነት ስም ሕገ ወጥነት፤ ሽብርተኛነት እየነገሱ ይታያል። ባጭሩ፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ማንነት እንዳለው/እንዳላት አያከራክርም። አከራካሪው ጉዳይ ግን በማንነት ስም ወይንም ምክንያት ሕገ ወጥነት፤ ተተኪነት፤ የበላይነትና አገር አፍራሽነት ሲነግሱ ዝም ብሎ ከመመልከቱ ላይ ነው። ብልጽግና በበላይይነት የሚመራውን የኢትዮጵያን መንግሥት ለትችት የሚያጋልጠው ይኼው ነው።
ብልጽግናዎች ሌላውን ከመውቀስና ከመተቸት ይልቅ ምን አይነት ስርዓተ መንግሥትና የአመራር ክፍተት ቢኖር ነው የዜጎች ደህንነት፤ ሰላም፤ እርጋታና አብሮነት እየተሸረሸሩ የሄዱት? የሚለውን የመጠየቅ ግዴታ አለባቸው።
ኦርቶዶክስን ክልላዊ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ከጀርባው ማን አለበት?
በዛሬዋ ኢትዮጵያ ጥሩውን እሴትና ተቋም ከመጥፎው ለመለየት የማይቻልበት ሁኔታ በግልጽ ይታያል።
ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ድንቃማ ከሚያደርጓት መለያዎች መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትና ይህች ሁሉን አስተናጋጅ የሆነች እምነት ለሶስት ሽህ ዓመታት የሰጠችው የመለያ በረከት ወይንም እሴቶች ናቸው ብል አልሳሳትም። የራሷ የቀን መቁጠሪያ፤ የራሷ ፊደል፤ የራሷ ድንቃማ በዓለት ወዘተ መለያዎች ናቸው። ይህ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን መተኪያ የሌለው መልካም ጎን ነው።
ሰሞኑን የመላው ዓለም ያደነቀውን የጥምቀት፤ የቃና ዘገሊላ እና ሌሎች የደመቁ የክርስትና ተከታዮች በዓላት ስከታተል ተስፋ ያደረግሁት ይህች ጥንታዊ አገር አሁንም ቢሆን ተስፋ አላት የሚል ነበር።
ይህንን የምልበት መሰረታዊ ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ለኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና አገራዊ ነፃነት የማይካድ ሚና ስላለው ጭምር ነው። ይህንን የቆየ መለያችንን ልክ እንደ ክልል መለያ በዘውግ መከፋፈል ሊያስከትል የሚችለው አደጋ እጅግ በጣም ያሳስበኛል። ኦሮሞውንም፤ ጉራጌውንም፤ ትግራዩንም፤ አኟኩንም፤ ወላይታውንም ወዘተ ሊያስስበውና ሊያስጨንቀው ይገባል።
የሚሰሙ ከሆነ ክፍፍሉ እንዲከሰት ያደረጉትን ግለሰቦች፤ የብልጽግና መሪዎችንና አባላትን የምመክራቸው ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ከመድረሱ በፊት እውነተኛውን የኦርቶዶክ አመራርንና ያወጣውን አቋም እንዱደግፉ ነው።
በተለይ ኦርቶዶክስን ክደው የወጡትን ወደ እናቷ ቤተከርስቲያን እንዲመለሱ አሳስባለሁ። ለዚህ ስህተትን አምኖ ይቅርታ መጠየቅና ኑዛዜ (Regret and Repent) መግባት ሂደት አርአያ የሆኑትን መጋቢ ሐዲስ አባ ጸጋ ዘአብ አዱኛን እያመሰገንኩ በፖለቲካ ውሳኔ የተሾሙት ጳጳሳት ሁሉ ይቅርታ እንዲጠይቁ አደራ እላለሁ።
የኢትዮጵያ ሲኖድ አመራር የወሰደውን ጠንካራ አቋም አደንቃለሁ፤ እደግፋለሁ።
የመንግሥት ሜድያ ሚናውን ያስተካክል እላለሁ። የኦርቶዶክስ አመራር ያወጣውን የአቋም መግለጫ የገዢው መንግሥት ሜድያ—Ethiopian Broadcasting Corporation..በወቅቱ ሽፋን ለምን እንዳልሰጠው ምንም ሊገባኝ አልቻለም። ሌላው ቢቀር ተቋሙ የሚደገፈው ከሕዝቡ በሚከፈለው ታክስ መሆኑን ዘንግቶታል።
በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት ችግሩን በድርድር ልንፈታው እንችላለን የሚሉትን አቋም እቃወማለሁ።
ምክንያቱም፤ ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ስለሆነ ችግሩን ሊፈታው የሚችለው የሲኖዱ አመራር እንጅ የብልጽግና የፖለቲካ መሪዎችና አማካሪዎች ስላልሆኑ ነው።
ስህተት የሰሩት ሁሉ ይቅርታ እንዲጠይቁ መምከር አግባብ አለው። ለድርድር ይቅረቡ የሚለው ግን አፍራሽ ነው። የብልጽግና ፓርቲ አመራር በኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና ሕጋዊውን የመንግሥት ስልጣን በኃይል ለማስወገድ ሴራ ቢካሄድ ድርድር እንደማይፈቀድ ሁሉ፤ በኦርቶዶክስ እምነት ላይም ድርድር አድርጉ ማለት ተገቢ አይደለም።
በመጨረሻ ለብልጽግናዎች ለማሳሰብ የምፈልገው ሕገ ወጥነትን፤ ወንበዴነትን፤ ስርአት አልበኝነትን፤ ሌብነትን፤ ሙሰኛነትን፤ ከሃዲነትን፤ የእርስ በእርስ ግጭትን፤ በትምህርት ጥራትና ብቃት የተከሰተውን የወጣቱን ትውልድ መማከንን፤ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር ካልቻላችሁ ሚናችሁ ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ እንድትመልሱልኝ ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
ሕግና ፍትህ ይከበሩ!
ዘረኝነትና ብሄርተኝነት ይቁም!
ይቀጥላል
January 28, 2023
8