ውዴ ሆይ ! እስከቀራኒዮ እዘልቃለሁ
ለንፁህ ፍቅርሽ አንገቴን እሰጣለሁ
ውዴ ህይ ! አልከዳሽም
ለሥጋ ተገዝቼ በሆድ አላውጥሽም ።
አመኚኝ ውዴ ሆይ !
እኔ አንቺን ነኝ ፣ አንቺ እኔነሽ
ሥጋዬ፣አጥንት ፣ ደሜ …
መላ ህዋሴ ነሽ
ውዴ ሆይ !
ከቶ ማንም አይለየን ፤ በጅንጉርጉርነታችን
ውበትን በተጎናፀፈው ነብራዊ መልከችን ።
ቢለያይ አፍ የፈታንበት ቋንቋችን
አንድ ነን እኮ በኢትዮጵያዊነታችን ።
የማይበጠሥ እኮ ነው ፤
የአደዋ ማተብአችን ?
ውዴ ሆይ !
በጭራሽ !
አልክድሽም ፤ …
በህይወት እሥካለሁ ።
የወደድሺኝ …ሰው በመሆኔ
የወደድኩሽ …ሰው በመሆንሽ …
እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁ ።
ውዴ ሆይ !
የእኔ ብርሃን እኮ ነሽ …
ጨለማን የምትገፊልኝ …
እንዳልሰናከል
ምርኩዝ የምትሆኚኝ …
ሊነጣጥለን ቢቃጣ ፣ ዘረኝነት ገኖ …
ውዴ ሆይ ! …
ለአንቺ ስል እዘልቃለሁ ፤ እሥከቀራኒዮ !
እሥከሚሰቅሉኝም ሥለፍቅርሽ አዜማለሁ
ውዴ ሆይ ! ሥለ ሰውነትሽ እሰዋልሻለሁ ።
ከመሰዋቴ በፊት የማዜምልሽን ዜማ
እሥቲ ለአፍታ አገር ይሥማ ።
” ውዴ ሆይ ! ፈፅሞ አትሥጊ
አየነጣጥለንም ብሽቁ ፕለቲካ
ቋንቋን በሰብዓዊ መብታችን ላይ እየተካ ።
ነገ ተነገ ወዲያ ዜጎች ይነቃሉ
‘ እኛ ሰው ነን !
እኛ ሰው ነን !
ቋንቋ አይደለንም !
ቋንቋ አይደለንም ! ‘
የሚል መፈክር ይዘው
የቋንቋን ጣዎት ለመከስከስ
እስከ ቀራኒዮ ይዘልቃሉ ። ”
ውዴ ! ሆይ !
መሰዋትነት በከንቱ እንደማይቀር አውቃለሁ ።
ውዴ ሆይ !
ለፍቅር ብለሽ ፣
ደጋግመሽ …
መሰቃየትሽን እያየሁ
ዘወትር አነባለሁ ።
ውዴ ! ፍቅሬ ! አካሌ ! …
እጅግ እወድሻለሁ …
አንቺ ከጎኔ ሆነሽ ባታፅናኝኝ …
ባትደግፊኝ …
አጋር ና ሀገር ባትሆኚኝ
እንዴት እንዲህ
ጀግና ኢትዮጵያዊ
ሆኜ እገኛለሁ ።
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
ታህሳስ 12 / 2015 ዓ/ም ተፃፈ