በፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ላይ ስለቀረበው ትችት- ጥያቄ ለተከበርከው ለአቶ አኒሳ አብዱላሂ !

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

ጥቅምት 17፣ 2022

በተከታታይ በፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦና አንዳንድ በኢህአፓ ላይ ቅሬታ ባላቸው ሰዎች ላይ የሚቀርበው እንደዚህ ያለ ትችት የሚመነጨው፣ ማንም ሰው እንደዚህ ያለን ድርጅት የመተቸት መብት የለውም ከሚለው የሚነሳ አደገኛ አስተሳሰብ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የቀድሞ የኢህአፓ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩና አሁን ከድርጅቱ ተገልለው የሚኖሩ ራሳቸው ሳይቀሩ በኢህአፓ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፤ በተሰራው ስህተት ላይም የሚያሳምን መጽሀፍ ጽፈዋል። ትችታቸውም በአመራሩ ላይ እንጂ በየዋሁ የኢህአፓ አባላት ላይ አልነበረም። በትክክልም መተቸት ያለበት ምንም ሳያውቅ ዝም ብሎ ሰተት ብሎ በመግባት የኢህአፓ አባል በሆነው ሳይሆን አመራሩ ነው። በማንኛውም አገር ሁልጊዜ የሚሰሩ ስህተቶች የሚመነጩት የፖለቲካን ትግል ከሚያካሂዱ ወይንም በአወቁኝ ባይነት ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሚሆን የማይሆን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ አገርንና ህዝብን በሚያተረማምሱ ነው።  እንደሚታወቀው አንድ ግለሰብም ሆነ በአንድ ርዕዮተ-ዓለም ዙሪያ ተሰባስቦ የሚታገል ድርጅት  በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ስህተት ሊሰራ ይችላል። ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በቂ ሳይንሳዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ ሶስዮሎጂያዊና ሌሎችም ለአንድ አገር ግንባታ የሚያገለግሉ ዕውቀቶች በደንብ ሳይጠኑና ከአንድ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ሳይገናዘቡ የሚወሰዱ እርምጃዎች የግዴታ አንድ ድርጅት የሚጠበቅበትን ተግባር እንዳይወጣ ያግዱታል። በውስጡም ዲሞክራሲያዊ ውይይቶችና ክርክሮች እንዳይዳብሩ ያግዳሉ። ለዚህ ነው ከጥንቱ የግሪኩ ፍልስፍና እንቅስቃሴ ጀምሮ በፖለቲካ ዙሪያ ትግል ሲካሄድ በትችታዊ መነጽር ይመረመር የነበረው። የፖለቲካ መሰረትም ፍልስፍና ስለሆነ ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ፖለቲካ የግዴታ ስህተት እንዲሰራ ያስገድዳል።  በትችታዊ መነጽር እየተመረመረ የማይካሄድ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ ወደማያስፈልግ ግብግብ ሊያመራና  አገርን ወደማፈራረስ ያደርሳል። ስለሆነም ነው የአውሮፓው ካፒታሊዝም እዚህ ዐይነቱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ  ዕድገት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአምስትና ከስድስት በላይ የእርስ በርስ ጦርነቶች የተካሄዱት። የመቶ ዓመት ጦርነት፣ የሰላሳ ዓመት ጦርነት፣ የሰባት ዓመት ጦርነት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ አንደኛውና ሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች በሙሉ በአውሮፓ ምድር የተነሱና ለብዙ መቶ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት ሊሆኑ የቻሉት በጊዜው የዳበረውን ሰፋ ያለ ፍልስፍናዊ ዕውቀት መሰረት´ና መመሪያ ለማድረግ ካለመቻል የተነሳ ነው። ለዚህም ነው የኋላ ኋላ ሂትለርና ተከታዮቹ የአይሁዲዎችን ታላቅና ሳይንሳዊ ግንዛቤና አስተዋጽዖ ሳያጤኑ የሚሆን የማይሆን ነገር በማውራትና በጥላቻ መንፈስ በመታወር ለብዙ ሚሊዮን አይሁዳዊያነ እልቂት ምክንያት ሊሆኑ የቻሉት። በእነ ሂትለርም ዕምነት ከአርያን ዘር በስተቀር ማንኛውም ሰው ዝቅተኛና ለሳይንና ለቴክኖሎጂ የተፈጠረ አይደለም። እንደዚህ ዐይነት ዝቅተኛ የሆነ ዘር ደግሞ ደማችንና ዘራችንን ስለሚያባክል የግዴታ መጥፋት ያለበት ዘር ብለው የተነሱት።  ከእነዚህና አሁንም ካለው ዓለም አቀፋዊ ፍጥጫና በአገራችንም ከሚካሄደው እልክ አስጨራሽ ትግል ስንነሳ እነ ሶክራተስና ፕሌቶ የሚሉት አንድ መሰረታዊ ነገር አለ። በስግብግብነትና ስልጣንን በመያዝ መንፈሱ የተሳከረ ቡድንም ሆነ ግለሰብ አንድን ህዝብ ፍዳውን ያሳየዋል፤ ለዝንተ-ዓለምም በጦርነት ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል የሚሉት። ስለሆነም ይላሉ ሶክራተስና ፕሌቶ  ፖለቲከኞች አይ ፈላስፋዎች መሆን አለባቸው፣ ካሊያም ደግሞ ፖለቲኞች በፈላስፋዎች መመከር አለባቸው ይሉናል።

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ኢህአፓ የቱን ያህል ፍልስፍናዊ ግንዛቤ ያለው ለመሆኑ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ኢህአፓ ማርክሲስት ሌኒንስት ነኝ ብሎ የተነሳ ድርጅት ነው። የማርክስን ስራዎች ስናነብ ደግሞ ማርክስ ከግሪክ ፍልስፍና ጋር የተዋወቀ፣ የዶክትሬት ስራውም የኤፒኩሪያንና የዲሞክሪተስ ፈላስፋዎች በተፈጥሮ ላይ ያላቸውን የተለያየ አመለካከት አስመልክቶ ነው የጻፈው። ዳስ ካፒታል የሚለውን ስለ ኢኮኖሚና ስለሶሲዮሎጂ የሚያትተውን ታላቅ መጽሀፉንና ግራውንድ ወርክ የሚባለውን ግሩም ግሩም ስራዎችን ላነበበ ሰው ማርክስ ሰፋ ያለ የተፈጥሮ ሳይንስና የህብረተሰብ ሳይንስ ዕውቀት እንዳለው ነው መረዳት የሚቻለው። ለዚህም ነው ማርክስና ኢንግልስ አንድ ላይ በመሆን ሰፋ ያለ ዕውቀት ሳይኖርና፣ በተለይም ደግሞ ሰፈው ህዝብ ሳይነቃና ሳይደራጅ የሚካሄድ የፖለቲካ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ ጥፋትን እንደሚያመጣ ያስጠነቅቁ የነበረው። ለዚህም ነው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የግዴታ የማቴሪያልና የንቃተ-ህሊና መሰረቶች መጣል እንዳለባቸው ያስተምሩ የነበረው። የማቴሪያልና የንቃተ-ህሊና ጉዳይ ባልተሟሉባቸው አገሮች ደግሞ መሰራት ያለባቸው ነገሮች በመጀመሪያ ደረጃ በዕውቀት አኳያ ሰፋ ያለ ጥናትና ትግል እንደ´ሚስያፈልጉ ያስተማሩት። እነ ሌኒንም ይህንን መሰረተ-ሃሳብ በመረዳት ነው በተለይም በጊዜው በራሽያ ምድር የሰፈነውን የሶሺዮ-ኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ያጠኑና ይከራከሩ የነበረው። ስለሆነም ሌኒን The Development of Capitalism in Russia በሚለው ግሩም መጽሀፉ ለማመልከት እንደሚሞክረው፣ ካፒታሊዝም በአንዳንድ ቦታዎች የገባ ቢሆንም የምርት ኃይሎችን ይህንን ያህልም ለማዳበር አልቻለም ብሎ ለመጻፍ የበቃው። በሌላ ወገን ደግሞ ቀደም ብለው በታላቁ ፔተርና በካታሪና የተወሰዱት የጥገና ለውጦች በምሁራዊ ጥልቅ አስተሳሰብ ላይ  ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳላቸው የማይታበል ሀቅ ነው። እነ ቶልስቶይ፣ ማክሲም ጎርኪ፣ ፑሽኪን፣ ዶስቶይቪስኪ፣ ፕሌክሃኖቭና ሌኒን ሊፈጠሩት የቻሉ በዚህ ዐይነቱ የጥገና ለውጦች ምክንያት ነው። ከዚያም በመነሳት ነው የኋላ ኋላ አብዮት ተካሂዶ፣ ብዙ ስህተቶችም ቢሰሩ የመጨረሻ መጨረሻ ሶቭየት ህብረት ታላቅና ኃያል መንግስት ለመሆን የበቃችው። ስለሆነም ነው እነ ፕሬዚደንት ፑቲን ይህንን መሰረት በማድረግ አገራቸውን ከወራሪው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በሚመራው የኔቶ ኃይል ጋር ትንቅንቅ ውስጥ የገቡት። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው የተወሰዱት ጥገናዊ ለውጦችና የኋላ ኋላ ደግሞ የሶሻሊስት አብዮት መካሄዱ የራሽያን ህዝብና አመራሮችን የአገር ወዳድነት ስሜት እንዲያዳብሩ አስችሏቸዋል። ለማንም ኃያል ነኝ ለሚል ወራሪ ኃይል እንደማይገበሩ እያረጋገጡ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዘሀበሻ ላይ የወጣውን የቅዳሜ ዕለት የደብረሰላም መድሐኒአለም ውሎ ተከታትዬ በጣም አዘንኩኝ (ታዛቢ)

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ በአገራችን ምድር በአብዮቱ ዘመን የተሰራው ስህተት ዋናው ምክንያት በጊዜው የነበረው ያልበሰለ ምሁራዊ ጉዳይና ህብረተሰብን በሚመለከት ጠለቅ ያለና የሰፋ ክርክርና ትምህርት አለመኖሩ ነው። በተለይም የሶሽዮ-ኢኮኖሚክስን፣ ወይም ደግሞ የህብረተሰብአችንን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መሰረቶች፣ እንዲሁም የፖለቲካና የመንግስትን አወቃቀር አስመልክቶ ጥናትና ውይይት፣ እንዲሁም ክርክር ባለመኖሩ ጭንቅላታችንን ማዳበር አልቻልንም። በጊዜው የፍልስፍናና የማህበራዊ ሳይንስ ዕውቀቶች በሚገባ ስለማይታወቁ፣ እንዲሁም ስለካፒታሊዝም አፀሰናነስና ዕድገት ጥናትና ክርክር ስለማይካሄድ የአብዛኛዎቹ ታጋይ ነን ባዮች ጭንቅላት ውስጥ ይብስለሰል የነበረው የመደብ ትግል፣ የብሄረሰብ ጥያቄና ጭቆና የሚሏቸው ጉዳዮች ነበሩ። በመሆኑም ሁሉም ነገር በአብዮታዊ አመጽ መልስ ያገኛል የሚል ድምዳሜ ውስጥ ሊደረሰ ችሏል።  የሌኒንንም ቀላል ፎርሙላ በመውሰድ፣ “የአብዮት ዋናው መሰረታዊ ጥያቄ የልጣን ጥያቄ ነው” የሚለው አብዛኛዎችን ታጋይ ነን ባዮችን ወደ ስልጣን መያዝ ላይ እንዲያተኩሩ አስገድዷቸዋል። ይህን ያህልም የህብረተሰብን ችግሮችና ጥያቄዎች ለመመለስ በሚያስችሉ ሰፋ ባሉ ዕውቀቶች ላይ ርብርቦሽ ለማድረግ እንዳይችሉ ታግደዋል። ሰፋ ያለ ዕውቀት ባልዳበረበትና ጭንቅላት ጠለቅ ባለ በፍልስፍና ላይ በተመሰረተ ሳይንሳዊ ዕውቀት(Scientific Knowledge)  በማይቀረጽበት ህብረተሰብ ውስጥ ደግሞ አርቆ-አሳቢነትንና ሎጂካዊ አስተሳሰብን በፍጹም ማዳበር አይቻልም። የዚህ ውጤት ደግሞ አክራሪነትና ሌላ አስተሳሰብ ያለውን እንደዋና ጠላት በማየት ማግለል፣ ካሊያም ደግሞ በመግደል አስተሳሰብን ማዳፈን ነው። ይህንን አካሄድ አብዛኛዎች በማርክሲዝም ሌኒንዘም ስም ይነግዱ የነበሩ ድርጅቶችና ራሱ ኢሰአፓ የሚባለው በደርግ የሚመራው ፓርቲና መንግስት ሁሉ የሚከተሉት ፀረ-ሳይንይስ፣ ፀረ-ዕውቀት፣  ፀረ ሁለ-ገብ ዕድገትና፣ ፀረ አገርና ፀረ-ህዝብ የሆነ አካሄድ ነበር። ለዚህም ነው “ በኢትዮጵያ ትቅደም ፈንታ ደም ሳይፈስ አብዮት አይሰምርም”  እየተባለ ወንድም ወንድሙን፣ እህት እህቱን እንዲገል የተደረገው። መግደልና መገዳደል የጊዜው ፋሽን እንደነበር የማይታበል ሀቅ እንደነበር የታወቀ ጉዳይ ነው። በአንድ ጊዜ በአንድ ቤት ውስጥ ተከብረውና ተደስተው ይኖሩ የነበሩ ልጆቻቸው በአንዳንድ ማርክሲስት-ሌኒንስት  ነን በሚሉ ድርጅቶች ስለተመለመሉ እንዳለ በደርግ ካድሬዎች ሊገደሉ በቅተዋል። በዚህም ዐይነቱ ጭፍን አካሄድ የተነሳ ተከብረው የነበሩና ለአካባቢዎቻቸው እንደ ግርማ ሞገስ የሚታዩና ህዝቡንም ያስተባብሩ የነበሩና፣ ከህዝቡም ጋር አብረው ይበሉ ይጠጡ የነበሩ አባቶችና እናቶች ፊዩዳሎች እየተባሉ ተገድለዋል።  ጥራዝ-ነጠቅ በሰፈነበት አገር የመጨረሻ መጨረሻ ባህልና መከባበር እንዳሉ እንደሚወድሙ በአብዮቱ ዘመን የተለመደና የተረጋገጠ ለመሆን በቅቷል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሃላፊነት የጎደለው ስር አትን  ሃላፊነት በጎደለው መንገድ ለማስወገድ መሞከር አደገኛነቱ  አጠያያቂ አይደለም - ጊሸይ ጊሻ

ለዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የገባው የትምህርት ስርዓት ጭንቅላትን በሁሉም መልክ የመቅረጽና የማዳበር፣ ከዚህም በመነሳት አርቆ የማሰብ ኃይል እንዳይዳብር ለማድረግ የበቃ ነው። ስለሆነም በአገራችን ምድር ሎጂካዊ አስተሳሰብ፣ አርቆ-አስተዋይነትና ዲያሌክቲካዊ እንቅስቃሴዎች ግንዛቤ ውስጥ ሊገቡ አልቻሉም፤ አይታወቁምም። በአንጻሩ መካረርና የደም ፍላት ጭንቅላታችንን በመወጠር አሁንም ድረስ እንድንከሳከስ እያደረጉን ነው።  ስለሆነም በአብዮቱ ዘመን ስህተት አልሰራንም፤ ለተከታታዩም ሁኔታ አሉታዊ አስተዋጽዖ አላደረግንም የሚል ካለ ግብዝ ብቻ ነው። ትችትን የማይቀበልና፣ ትችት ሲሰነዘርበት ቡራ ከረዩ የሚል እንደዚህ ዐይነት ኃይል ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ ሊያስከትል የሚችለውን ዕልቂት መገመቱ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ እኔ ባለፉት ሰላሳ ዐመታት እጽፋላሁ። አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ትችቶች ይደርሱኛል። አንድና ሁለቴም ዘለፋ ነገር ደርሶብኛል።  በመሰረቱ በተለይም አሉታዊ ትችቶች በሚደርሱብኝ ጊዜ ደስታውን አልችለውም። ምክንያቱም አንድ ሰው አሉታዊ ትችት ሲጽፍ ከምድር ተነስቶ ሳይሆን የበለጠ ግንዛቤ ያለው ስለሆነ እንደዚህ ዐይነቱ ትችት የበለጠ እንድመራመርና እራሴን እንድጠይቅ ዕድል ይሰጠኛል። የሳንይንስንና የፍልስፍናን ዕድገት ስንመለከት ሊዳብሩ የቻሉት በትችት አማካይነት ብቻ ነው። ለምሳሌ አርሲቶለስ ፕሌቶንን ይተቸው ነበር። ፕሌቶ ደግሞ የአርስቲቶለስ አስተማሪ የነበረ ሰው  ነው። የአርስቲቶለስም ትችት ዕውቀት የሚመነጨው ከምናያቸው ነግሮች ነው ሲል፣ ፕሌቶ ደግሞ ከጭንቅላታችን ውስጥ የሚፈልቅና በምርምርና በአርቆ አስተዋይነት፣ እንዲሁም መላልሶ በመጠየቅ የሚፈልቅና የሚዳብር ነው ይላል። ታዲያ ፕሌቶ ተማሪዬ ስለነበርክ የእኔን አስተሳሰብ መቃወም የለብህም፣ አንተ ማን ነህና ብሎ ከመቃብሩ ብንን ብሎ በመነሳት አላሳደደውም። ይህንን የፕሌቶንን አስተሳሰብ የፈረንሳዩ ፈላስፋ ዴካንና የጀርመኑ ፈላስፋ ላይብኒዝና እነ ካንትም የሚጋሩት ነው። ካንት በበኩሉ ደግሞ ህለቱንም አስተሳሰብ፣ ከውስጥ የሚፈልቀውናና ከውጭ የሚገኘውን በማስታረቅ ዕወቀት በዚህ መልክ ሲይንቴሳይዝ በመሆን የሚደረስብት ነው ይላል፤ ትክክልም ነው።  እንደዚሁም በኒውተንና በላይብኒዝ መሀከል የጦፈ ክርክር ይደረግ ነበር። ሄገልም በካንት አንዳንድ አስተሳሰቦች ላይ አይስማማም ነበር። ለዚህም ነው ማርክስ ራሱ በተለይም ለንደን ከሰላሳ ዓመት በላይ በኖረበት ጊዜ በእንግሊዞች የክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ምርምርና ጥናት ባለመደሰቱ፣ አንዳድን ነገሮችን በመቀበል የራሱን ዳስ ካፒታልና ሰርፕለስ ቫልዩ የሚባሉትን ስራዎችን መጻፍና ማስፋፋት የቻለው። ስለሆነም ትችት እንደጭንቅላት ምግብ መቆጠር ያለብት እንጂ እንደስድብ መወሰድ ያለብት ጉዳይ አይደለም። ካለትችትና ካለክርክር የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ሊኖር በፍጹም አይችልም።

ወደ ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ ስንመጣ ደግሞ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የሚታገለውና ዋና ዓላማውም ስልጣን ላይ ለመውጣት ነው የሚለው አስተሳሰብ በጣም አደገኛ ነው። የአንድ የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ የሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ዋና ዓላማ ሰፋ ያለ ዕውቀትን በማስፋፋትና ህዝባዊ ኃይልን በማስተባበር፣ እንዲሁም ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ቅራኔዎችን በማቀዝቀዝ የህዝብ አትኩሮው በተሟላ ወይንም በሁለ-ገብ ዕውቀት ላይ እንዲሰማራ በማድረግ ሰፋ ያለ ዕድገትን ማምጣት ነው። ከዚህም በመነሳት የማያስፈልጉ ሽኩቻዎች እንዳይነሱና ቡድናዊ ስሜት እንዳይዳብር በማድረግ ሁሉም በወንድማማችና በእህትማማች መንፈስ በመታነጽ አገርን በጋራ መገንባት ነው።  ማንኛውም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሰፋ ባለ ዕውቀት ላይ እንዲመሰረት ማድረግ ነው። ከዚህ በመነሳት የፖለቲካ ትግል ዋና ዓላማው የአንድን ህብረተሰብ ችግር ከሁሉም አቅጣጫ በመመርመር አንድ ህዝብ መስራት ያለበትን ነገር እንዲሰራ ማድረግ ነው። ለዚህም ነው ፖለቲካ ሳይንስ ነው የሚባለው። በጉልበት ላይ የሚያተኩርና ቡድናዊ ስሜትን የሚያመጣ ፖለቲካ ሳይንስ መሆኑ ቀርቶ ድንቁርናን ማስፋፊያ ይሆናል። ዕድገት እንዳይመጣ ያደርጋል። ስለሆነም በፖለቲካዊ ትግል ውስጥ የተሰማራ ግለሰብም ሆነ ድርጅት ዋናው ዓላማው አንድ ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊወጣ የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የምርት ኃይሎች ወይም ደግሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚዳብሩበትን ሁኔታ መፍጠር፣ ለህዝብ ልዩ ልዩ ግልጋሎቶችን የሚሰጡ ተቋማት እንዲገነቡ ማድረግ፣ ቆንጆና መንፈስን የሚያድሱ ባህላዊ መንደሮችና ከተማዎች የሚገነቡበትን ሁኔታ መፍጠርና ማመቻቸት ነው። ጠቅላላው ህዝብ እንደ አንድ ኃይል ሆኖ በመነሳት ለተከታታዩ ትውልድ አዲስና መንፈስን የሚያድሱ ሁኔታዎች መፍጠር እንዲችል ማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ፖለቲካዊ ትግል የግዴታ ብጥብጥን የሚፈጥር፣ ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ቀዳዳ የሚሰጥ፣ የመጨረሻ መጨረሻ ድህነትና ኋላ-ቀርነት ስር እንዲሰዱ በማድረግ አገርን የሚበታትን ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም ፖለቲካን ከፍልስፍና፣ ከማህበረሰብ ሳይንስ፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ፣ ከኢኮኖሚክስ፣ ከአርክቴክቸርና ከከተማ ዕቅድ፣ እንዲሁም ከሌሎች ነገሮች ነጥሎ ማየት እጅግ አደገኛ አስተሳሰብ ነው።  ፖለቲካ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን ችግርን መመርመሪያና መፍቺያ ዘዴ ነው የሚባለው ለዚህ ነው።  ስልሆነም ትችትን መቀበልና በስነ-ስርዓት ማስተናገድ አዋቂነት ነው። በዕድሜ የገፋን ሰው ማንቋሸሽ ወይም መስደብ የፖለቲካ ሳይንስ መሰረተ-ሃሳብን የሚጻረር አደገኛ አካሄድ ነው። የመጨረሻ መጨረሻ ይህንን በፖሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ላይ ትችት ያቀረበውን ሰው የምጠይቀው ነገር ኢህአፓ ትላንትና የማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅት ነኝ የሚልና፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሶሻሊሳታዊ ስርዓት መጣል አለበት ብሎ የሚታገል ድርጅት ነበር። አብዮቱ ከሸፈ ከተባለበት ከዛሬ አርባት ጀምሮ ኢህአፓ የሚከተለው ርዕዮተ-ዓለም ለመሆኑ ምንድን ነው? አሁንም ሶሻሊስታዊ አስተሳሰብ ወይስ ሌላ አስተሳሰብን ነው የሚያራምደው? አይ ሶሻሊስቶች አይደለንም የሚባል ከሆነ ደግሞ የሚከተለውንና የሚመራበትን ርዕዮተ-ዓለም መናገር አለበት። ያሁኑን የአገራችንን የተወሳሰበና ጥልቀት ያለው ችግርስ በምን ዐይነት ፍልስፍናና ርዕዮተ-ዓለም መፍታት ይቻላል ብሎ ድርጅታችሁ ያምናል? የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች የሚያትቱ ሳይንሳዊ ጽሁፎችንስ ጽፋችኋል ወይ? ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ተግባራዊ ያደረገውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በሚመለከት የጻፋችሁት ሀተታ አለ ወይ? በተጨማሪም ባለፉት 40 ዓመታት ኢትዮጵያ እንደ አገርና ህብረተሰብ እንድትገነባ የሚያስችል መሰረተ-ሃሳቦችን አዳብራችኋል ወይ? በአጠቃላይ ሲታይ የህብረተሰብንና የኢኮኖሚ ዕድገትን በሚመለከት የጻፋችሁት ነገር አለ ወይ? ስለሳይንስና ስለቴክኖሎጂ ያላችሁስ ግንዛቤ ምን ይመስላል? እንዴትስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአገራችን ምድር ሊገነቡ ይችላሉ?  ስለመንግስት አወቃቀርና ተግባር፣ ስለፖለቲካ ጉዳይ፣ እንዲሁም በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮችና በአገራችንም ምድር ስለሚታዩት መንግስታዊና የፖለቲካ ቀውሶች ምክንያቶቻቸውን በማጥናት የጻፋችሁትና ለታዳጊው ትውልድ ያስተማራችሁት ነገር አለ ወይ?  እነዚህንና ሌሎች አያሌ ጥያቄዎችን የመመለስ ግዴታ አለባችሁ። ይህንን ሳታደርጉ ዝምብላችሁ ፓርቲ አለን፣ አሁንም ቢሆን ለኢትዮጵያ ህዝብ የምንታገልና ብቸኛውና ማራጭ የሌለው በህይወት የምንገኝ ድርጅት ነን፣ ከእኛም በላይ ደሙን ለአገሩ ያፈሰሰ የለም፣ ወደፊትም ለሚቀጥሉት 150 ዓመታትም የምንኖር ነን የሚለው አባባል የትም አያደርሰንም። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ፈቺን እንጂ ችግር ፈጣሪን አይፈልግም። አርቆ አሳቢንና ሎጂካዊ አስተሳሰብ ያለውን ነው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚናፍቀውና የሚፈልገው። ሰላምንና እንዲሁም የተሟላ ዕድገትን የሚያመጣለትን ምሁራዊ ኃይል ብቻ ነው የሚመኘው። አንድ ህዝብ በህልምና በምኞት ብቻ ሰለማይኖር አፍጠው አግጠው የሚታዩ ችግሮች እንዴት በተግባር ከታች ወደ ላይ እንደሚፈቱ የሚያሳየውን ምሁራዊ ኃይል ይፈልጋል። ስለሆነም ጊዜው የጎጠኝነት፣ ቡድናዊ ስሜት የሚያይልበትና ካለኔ ብቻ ታጋይ የለም የሚባልበት ዘመን አይደለም። አገራችንን ለማፈራረስና ህዝባችንም ለዝንተ-ዓለሙ በድህነት እንዲቀር የውስጥና የውጭ ኃይሎች ተባበረው በሚሰሩበት ወቅት ህዝባችን የጠራና ሳይንሳዊ፣ እንዲሁም ፍልስፍናዊ አመለካከት ያለው ሰፋና ጠለቅ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴን ይፈልጋል። ከዚህ ውጭ የሚፈልገው ምንም ነገር የለም።  መልካም ግንዛቤ!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ህዝብ የህልውና ስጋት አለበት ሲባል…..…. መስከረም አበራ: ከቃሉቲ ማጎሪያ

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

www.fekadubekele.com

3 Comments

  1. እናመሰግናለን አኒሳንም እናመሰግናለን አንተ ባትሳደብ እንዲህ ያለ እውቀት ከየት ይመጣል። በአንድ ውይይት ላይ ከኢህአሰ ከአምስቱ ሶስቱ ትግሬዎች እንደነበሩ ሰምተናል። እንግዲህ የጎሳ ነጻ አውጭ የሆነው ኢህአፓ በምን ምጥጥን ነው ሶስቱን ትግሬ ያደረገው? አባላቱ ኢህአፓን መተቸት ቃል ኪዳናቸውን ማፍረስ እየመሰላቸው ስህተት ላይ ስህተት ይሰራሉ። የኢህአፓ የነካ ነካ ትግል በጠላት ተመርቶ ኢትዮጵያን አሳክሮ ዛሬ ሰው ዘቅዝቀው የሚሰቅሉ እንደ ዶሮ አጋድመው የሚይርዱ አውሬዎች ላይ አድርሶናል። 1500 የሀገሩ ዜጎች ሲታረዱ በኢትዮጵያ ፓርላማ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ዜጎች ተነፍገዋል ኢትዮጵያን የምታክል አገር ሹመኞቹ የሚገርሙ ሁነዋል። ብሽሽቅ በመሰለ መልኩ ጠሚኒስተሩ የሚሾማቸው ወይ ችሎታ የሌላቸው ወይ ህዝብ የጠላቸውን ነዉ ። ኦሮሞ ኦሮሞን አይገድልም በሚለው መርህ የኦነግ ሀይሎች አማራን እንዲያርዱ ፍቃድ ሲሰጣቸው ነገዳቸውን ከመታረድ ለማዳን የሚውተረተሩትን ፋኖዎች በእንኩቶ አማራዎች ያሳድዳል። ባጠቃላይ ተደጋግሞ እንደተነገረው ኢህአፓ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ በኢትዮጵያ ጠላቶች እንክብካቤ ተልእኮውን ጨርሶ የከሰመ ግልብ ድርጅት ነው። አባላቱ አሁንም የበቀል ስሜታቸው እንደተንቀለቀለ ነው። ባለማወቅ ሀገር ጠቀምን ብለው በጠላት መሰሪ ሴራ ተጠልፈው ለሞቱት ዜጎች ከልብ እናዝናለን።

  2. ለዶ/ር ፍቃዱ የተለመደ ሚዛናዊ ትንታኔ ክብር መስጠት ፈልጋለሁ:: ቢረጋ የሚሉህ ግን ማስተዋል የጎደለህ መካሪ ይስጥህ:: የኢህአፓ አባላት ቂም በቀለኛ ናቸው ብለ በጅምላ ስትፈርድ በጣም ታሳዝናለሁ:: ያኔ ምሁራን ሲገደሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተን ነው ብሎ ዛሬም የሚከራከረውን ፋሲካን ማውገዛችንን ካልሰማህ ስማ:: ያ ትንታግ በህይወቱ ተወራርዶ ለገባር ህዝቦች መብት መሬት ላራሹ የዲሞክራሲ መብት ይከበር ያለን ትውልድና በቅንነት ያለፉ ሰማእታቱን በጎ ህሊና ያለው ሁሉ ያከብራል ያንተ ቢጤዎች ተራ ስድብና ነቀፋ ግን ምንም የሚፈይደው የለም

    “አባላቱ አሁንም የበቀል ስሜታቸው እንደተንቀለቀለ ነው”

  3. Degone Moretew
    ወዳጄ ስድብ ጥሩ አይደለም ትውልዱ በኢትዮጵያ ጠላቶች ተጋልቦ ኢትዮጵይን እዚህ ያደረሰ ነው፡፡ ተቆጣኸኝ እንጅ ከኢሃሰ አመራር ክአምስቱ ሶስቱ ትግሬዎች መሆናቸውን ትግሬዎች ነግረውናል፡፡መሬት ላራሹ ላልከው ዶር ምናሴ ለማ በቃለ መጠየቃቸው እንደነገሩን ባለ መሬቱ በአንድ ጋሻ 25 ብር መክፈል አቅቶት ግምሹ መሬት ተመልሶ ለህዝብ ተከፍሏል፡፡ የሰው ደም ካልጠማችሁ በስተቀር ሃገርን መክተው ያበቁትን ዜጎችን ደም ማፍሰስ ለምን አስፈለገ ነው ጥያቄው፡፡ ዝም በሉ አዳምጡን እውነት እኛ ዘንድ ነው የምትሉትን ለመቀበል እንገደዳለን ፖለቲካ ገበያ ነው ተቀባይነት ካጣችሁ ማላዘን ጥቅም የለውም፡፡ በጠላት ተገፋፍተው የተደገሰላቸውን ሳያውቁ ጭዳ ለሆኑ ዜጎች ዛሬም እናዝናለን አመራሩ ግ ን ልዩ የጥፋት ተልእኮ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው የሚለውን ሃሳብ ጊዜ ሰጥቶ ማጤን መልካም ነው ፡፡ለአኒሳ ከስር የተጻፈለትን ምላሽ ሳትመለክት አልቀረህም ከዛ ምን ተረዳህ? የኤርትራ ጥያቄ የኮለኒያሊዝም ጉዳይ ነው በሃሳቡ እንስማማለን አላላችሁም? የሱማሌ ወራሪን አትውጋ ዋናው ጠላትህ የኢትዮጵያ ወታደር ነው ስትሉስ አልነበረም? ለጅብ አሳልፋችሁ የሰጣችሁን እናንተ ናችሁ ምናልባት በህይወት የቀራችሁ ምስጢሩ ሳይገባችሁ ቀርቶ ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share