እኔን የሚገርመኝ የአለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ፣ በተለይም የምእራባውያኑ አፈቀላጤዎች የግብዝነት ጫጫታ ነው፡፡
አሁን የነዳጅ ዝርፊያ ለወሮበላው ጉጅሌ ቁምነገር ሆኖ ነው ያን ያህል የተካበደው?
የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ት.ህ.ነ.ግ) ገና ሲፈጠር አንስቶ ጥርሱን ነቅሎ ያደገውና እዚህ ደረጃ የደረሰው ባንኮችን በጠራራ ፀሀይ እየዘረፈ፣ የካዝና ቁልፍ ገንጥሎ የህዝብ ገንዘብ እየመነተፈ፣ መንገድ እያፈረሰና ድልድይ እየደረመሰ አይደለም እንዴ?
ዝርክርክና አይቶ አያውቆቹ የት.ህ.ንግ ጀሌዎች እኮ ሰብኣዊ ማእበልን ተጠቅመው የዛሬ ዓመት አማራ ክልልን በግፍ በወረሩበት ወቅት በውድ ዋጋ የሚሸጠውን ነዳጅ ይቅርና አርሷ-ደሯ እመቤት አቡክታ በቡሆ እቃዋ ያስቀመጠችውን ያደረና ሊጋገር የደረሰ ሊጥ እየገለበጡ በመጠጣት ጠኔያቸውን ለጊዜው ሲያስታግሱና የደረቀ ጉሮሯቸውን ሲያርሱ አስተውለናል፡፡ ለወራት የቤተ-ሰብ ፍጆታ የተቀመመና በጉሽጉሻ የተቀመጠ ሽሮ፣ ወይም በርበሬና የተደቆሰ ድልህስ መች ቀራቸውና፡፡
እነሆ ሰሞኑን በመቀሌ ከተማ ተከማችቶ ይጠበቅ ነበር የተባለውን የአለም ምግብ ፕሮግራም ማእከላዊ መጋዘን በሀይል ጥሰው በመግባት በዚያ የተቀመጠውን 570000 ሊትር ነዳጅ ዘይት የተሞላባቸውን 12 ታንከሮች ጭነው ወሰዱ ተብሎ በሰበር ዜናነት ሲስተጋባ መሰንበቱ ለማያውቁሽ ታጠኚ ያሰኛል፡፡
ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፣ ይላሉ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን፡፡
ይህንን ጀሮ የሚበክል ዜና በመጀመሪያ ወደአደባባይ አውጥተው ያሰጡት David Beasley ሲሆኑ እርሳቸው ከፍ ብሎ የተጠቀሰው፣ ማለትም የአለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡
በርግጥ ዎሬውን ከርሳቸው ቀበል አድርገው የተ.መ.ድ ዋና ጸሀፊ የAntonio Guterresቁጥር አንድ ቃል አቀባይ የሆኑት Stephan Dujarricበይፋ ደግመው አስተጋብተዉታል፡፡
ቀድሞ ነገር ት.ህ.ነ.ግ ራሱ በጫረውና አለቅጥ በተራዘመው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ክፉኛ ለተሽመደመዱትና ኑሯቸው ለተናጋባቸው የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የእርዳታ እህል፣ መድሃኒትና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ያገለግል ዘንድ ታስቦ የተቀመጠ ነበር የተባለለትን ብዛት ያለው ነዳጅ እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር August 24 ቀን 2022ዓ.ም ሊነጋጋ አካባቢ በዝርፊያ ጭነው ወስደዉታል፡፡ መጋዘኑን በኀላፊነት ይጠብቁ የነበሩትና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ሊከላከሉ ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው እንደቀረ ሁለቱ ባለሥልጣናት ከገለጹ በኋላ በዝርፊያ የተወሰደው ነዳጅ ባፋጣኝ እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡
ድንቄም ተመለሰ፡፡
ወገኖቼ ሆይ፤
ይህ አጋጣሚ ለጊዜው በመጠኑ ፈገግ ያሰኝ እንደሆነ ነው እንጂ ክፉኛ ያሳዝናል፣ ያማልም፡፡
ከልባቸው ይሁን ከአንደበታቸው ባይታወቅም ዋና ስራ አስፈጻሚው ራሳቸውም ቢሆኑ አስነዋሪውን የት.ህ.ነ.ግ ዎንበዴዎች አድራጎት ፍጹም አናዳጅና አሳፋሪ (outrageous and disgraceful) ሲሉ ነበር በወቅቱ የተበሳጩ መስለው የገለጹት፡፡
አጅሬ ት.ህ.ነ.ግስ ምኑ ሞኝ ነው ታዲያ?
ነዳጁን እንደተወራው እኔ አልዘረፍኩም፤ ያበደርኩትን ነው በራሴ ሥልጣን መልሼ የወሰድኩት ብሏቸው እርፍ አላለም መሰላችሁ?
ቡድኑ እንደሚያላግጠው በመካከላቸው የብድር ውል ከነበረ በአበዳሪው የተናጠል ስርቆት ወይም ድፍረት የተመላበት ቅሚያ ሊፈጸም መቻል አለመቻሉን የሚያውቀው ራሱ ት.ህ.ነ.ግ ብቻ መሆንይኖርበታል፡፡
የሌባ አይነ-ደረቅ መልሶ ልብ ያድርቅ እንዲሉ የለየለት ሹፈትና ቅጥፈት ይሏችኋል ይህ ነው እንግዲህ፡፡
ለነገሩ የነዳጅ ዝርፊያው እንኳ የአንድ ሰሞን ጫጫታ ነው፡፡
እነርሱም ቢሆኑ ነውረኛው ቡድን ለምን ይህንን አስጸያፊ ድርጊት እንደፈጸመ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ሳይተባበሩት እንዳልቀሩ ብንጠራጠርም እኮ አይፈረድብንም፡፡
ያንኑ አይን ያወጣ ዝርፊያ ተከትሎ ክልፍልፉና አረመኔው የት.ህ..ነ.ግ ሰራዊት በአማራና በአፋር ክልሎች ላይ በበርካታ ግንባሮች ሶስተኛ ዙር ጥቃት ለመክፈት ቀናት አልወሰደበትም፡፡ አንቶኒዮ ጉተሬስና የበታች ሹሞቻቸው ግን ወራሪውን ለይቶ በጽኑእ ከመኮነን በመታቀብ አጥቂና ተጠቂ ያካሂዱታል ያሉትን ወታደራዊ ግጭት አቁመው በጠረጴዛ ዙሪያ ለሠላማዊ ድርድር ይቀመጡ ዘንድ ያለመታከት ሲመክሩና አልፏልፎም ሲገስጹ እንሰማቸዋለን፡፡
በርግጥ እነኚሁ ወገኖች ብለን ነበር ለማለት ያህል ብቻ ከተራ ውግዘት ባለፈ ተፋላሚ ሀይሎች በሰብኣዊ እርዳታ አቅርቦት ረገድ ያሉባቸውን ግዴታዎች እንዲወጡ በማለት የተለመደውን የቁራ ጩኸታቸውን ከማሰማት ቦዝነው የሚያውቁበትን ጊዜ በበኩሌ አላስታውስም፡፡
እዚህ ላይ አለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ በጭራሽ ሊስተው የማይችለው ጥሬ ሀቅ ቢኖር ኢትዮጵያ ሉኣላዊት ሀገር ብቻ ሳትሆን በማቋቋሚያ ቻርተሩ አንቀጽ 3. መሰረት የራሱ የመንግሥታቱ ማሕበር መስራች አባል ጭምር መሆኗን ነው፡፡ ትግራይ ግን በአንጻሩ የዚህቺው ሀገር ክፍለ-ግዛት እንጂ በአለም-አቀፍ ደረጃ ሕጋዊ ሰውነት ያላት ምድር አይደለችም፡፡
በአሁኑ ወቅት በፈላጭ-ቆራጭነት ተቆጣጥሮ የሚያስተዳድራት ቡድንም በመጥፎ ጠባዩ ምክንያት በሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አማካኝነት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ተሳዳጅ ድርጅት እንጂ በመንግሥታቱ ማሕበር እውቅና ተሰጥቶት የተመዘገበ ነጻና ሉኣላዊ አካል እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ታዲያ ይህ መሆኑበሚገባ እየታወቀ ተወደደም ተጠላ ሕጋዊውን ማእከላዊ መንግሥትና በሽብርተኝነት ተፈርጆ ሳለ ይህ አልበቃው ብሎ አስቀድሞ በፈጸመው ወንጀል ከመጸጸት ይልቅ በሀገሪቱ ህልውናና የግዛት አንድነት ላይ እንደገና ጦር ሰብቆ የተነሳውን አጉራ-ዘለል ድርጅት እኩል በአንድ ሚዛን ላይ አስቀምጦ አርፋችሁ ተቀመጡና ለሠላም ተደራደሩ በማለት ማላገጥና የተዛባ ብያኔ መስጠት ከነውሮች ሁሉ የላቀ ነውር መሆን አለበት፡፡
መቸም ምእራብ አውሮፓውያኑና አሜሪካውያኑ ለብሔራዊ ጥቅሞቻቸው መከበር ይበልጡኑ በማጋደል እንዲህ ያለውን የወገናዊነት ዝንባሌ ቢያሳዩ እኮ እምብዛም ላይገርም ይችል ይሆናል፡፡ የዋና ጸሃፊውን ሴክሬታሪያት ጨምሮ በሀያላኑ መንግስታት ምሪትና ተጽእኖ ስር ወድቆ በዚህ ደረጃ ባይዘወር ይመረጥ የነበረው የተ.መ.ድ ልዩ ልዩ ተቋማት ጭፍን ፍርደ-ገምድልነት ግን ድርጅቱ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ፍጻሜ ማግስት ከተቋቋመበት መሰረታዊ ፍልስፍና አኳያ ቅቡልና ተገማች ሊሆን ከቶ አይችልም፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ ተ.መ.ድ የነጻና ሉኣላዊ አገሮች ማሕበር ሲሆን በቻርተሩ አንቀጽ 4 ንኡስ አንቀጽ (1) ስር በተደነገገው መሰረት በአባልነት ተቀብሎ የሚመዘግበው ሠላም-ወዳድና ማሕበሩ የሚጥልባቸውን ግዴታዎች ለመፈጸም ዝግጁና ፈቃደኛ ሆነው የተገኙትን መንግሥታት እንጂ እንደት.ህ.ነ.ግ በብሔራዊም ሆነ በአለም-አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት የተፈረጁ ሕገ-ወጥና ተሳዳጅ የአመጻ ድርጅቶችን አይደለም፡፡
የወቅቱ ዋና ጸሀፊ ግን የቻርተሩን መንፈስና ሀይለ-ቃል በግልጽ በሚቃረን ያፈነገጠ አቀራረብ ሕጋዊውን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የወሮበላውን ቡድን መሪ እኩል በሆነ አቋም ሲገናኟቸውና ሲያዋሯቸው ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አጽንኦት ሰጥተን የምንከታተለው፡፡ ይህ መቸም የዲፕሎማሲ ሀሁን ላልቆጠረ ሰው እንኳ የሚመጥን ዘይቤ አይደለም፡፡
በዚህ አይነቱ የተወላገደ የውጭ አካላት እይታ ጭምር የተደፋፈረው ት.ህ.ነ.ግ እንደልማዱ የአማራና የአፋር ክልሎችን እንደገና ማተራመስ፣ ሠላማዊ ዜጎችን በጭካኔ ማረድ፣ አንጡራ ሀብታቸውን መዝረፍ፣ ማውደምና ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀል ከጀመረ እነሆ ሁለት ሳምንታትን ሊደፍን ትንሽ ነው የቀረው፡፡
ለሰብኣዊ እርዳታ ፍሰትና ተደራሽነት ሲባል ከአምስት ወራት በፊት የፌደራሉ መንግሥት በተናጠል ወስዶት የነበረውንና ት.ህ.ነ.ግ ራሱ ዘግይቶ የተቀበለውን የተኩስ ማቆም እርምጃ ያለአግባብ ተጋፍቶ በከፈተውና የመጨረሻው መጀመሪያ በሚመስለው በዚህ ሶስተኛ ዙር እብሪት-ወለድ ወረራው ከትግራይ ጋር ተዋሳኝ በሆኑት የሁለቱ ክልሎች አካባቢዎች ላይ እየወረደ ያለው የመከራ ዶፍ መጠኑ የበዛና ሊቋቋሙት የማይቻል ሆኗል፡፡
ይሁን እንጂ ካለፈው ነሃሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እንዳዲስ ተቀስቅሶ ቁጥር ስፍር ወደሌላቸው የከተማና የገጠር ቀበሌዎች በተስፋፋው ጦርነት እየደረሰ ካለው የንፁኃን ወገኖቻችን እልቂት፣ የማሕበረ-ሰቦቻችን ከየመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀልና መጠነ-ሰፊ የሀብት ውድመት ይልቅ በምስኪኑ የትግራይ ክልል ነዋሪ ወገናችን ስም በየብስና በአየር ማጓጓዣዎች ለዋልጌው የት.ህ.ነ.ግ ሰራዊት ሊተላለፍ የሚገባው ወታደራዊ ቀለብ መቋረጥ አብዝቶ የሚያስጨንቃቸው ግብዞቹ እነAntonio Guterres፣ እነሳማንታ ፓዎርና እነአንቶኒ ብሊንከን በግፍ እየተጠቃም ቢሆን መንግሥት የተከፈተበትን ወረራ ከመከላከል ይታቀብ ዘንድ በተገላቢጦሹ አጥብቀው ሲወሰውሱት ይደመጣሉ፡፡
እንግዲህ ጫፍ የረገጠና ከዚህ የባሰ ፍርደ-ገምድልነት ከየት ሊመጣ እንደሚችል ለመረዳት ጨርሶ ያዳግታል፡፡
ወያኔ ከውልደቱ ጀምሮ ሌላው ይቅርና ራሱ በበቀለበት የትግራይ ህዝብ ችጋርና ስቃይ ሲነግድና ሲበለጽግ የኖረ መሰሪ ድርጅት እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ በአስከፊው የረሃብና የቸነፈር ወቅት እንኳ ለተረጂዎች የሚለገሰውን ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆነ እህልም ሆነ ሌላ ቁሳቁስ በሱዳን ገበያ በግላጭ እየቸረቸረ የጦር መሳሪያ ይሸምትበት እንደነበር፡፡ በጊዜው አብረዉት የሰሩ ሁሉ እስኪበቃን ድረስ ነግረዉናል፡፡ ለዚህ ደግሞ እነአቦይ ገብረ-መድህን አርኣያ ህያዋን እማኞች ናቸው፡፡
ዛሬም ቢሆን የኢትዮጵያ ጥምር ጦር በሚያካሂደው የመከላከል ፍልሚያ በሚደረምሳቸው የት.ህ.ነ.ግ ምሽጎች ውስጥ እንደተከማቸ በቁጥጥር ስር እየዋለ ያለው የስንዴና የበቆሎ ዱቄት፣ ሀይል ሰጪ ብስኩትና መድሃኒት ለሰብኣዊ አገልግሎት ከተላከ የአቅርቦት መጋዝኖች በዝርፊያ የተሰባሰበ ወይም ከእኩያን አጋሮቹ በትብብር የተገኘ እንጂ ወንበዴው ሀይል ጻድቅ ሆኖ ከሰማይ የወረደለት መና ነው ሊባል ከቶ አይችልም፡፡ ይህንን ቅሌት በሚገባ ለማረጋገጥ በየመባልእቱና የነፍስ-አድህን መድሃኒቶቹ የማሸጊያ ከረጢቶች ላይ የታተመውን የለጋሽ ኤጀንሲዎች ስምና አርማ በጨረፍታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል፡፡
አለም በሚገባ ይወቀው እንጂ ታዲያ ይህ በቡድኑ ዘንድ አሳፋሪ ተግባር ነው ተብሎ አይወሰድም፡፡
ከሳምንታት በፊት እንኳ ለርዳታ የሚላክን የምግብ አቅርቦት ለተዋጊ ሀይሎች ቀለብ ታውላላችሁ በሚል ለቀረበለት አሸማቃቂ ጥያቄ የወያኔው ፕሬዚደንት ነኝ የሚለው የቡድኑ ፊታውራሪ እየተቅለሰለሰም ቢሆን የሰጠው ምላሽ ፍጹም አስተማማኝና ታዳምያኑን በሰፊው ያስደመመ ሆኖ ነበር የተደመጠው፡፡
ሰውየው የቡድኑን ምግባረ-ብልሹነት በጽንአት ለመከላከል እንብዛም አላቅማማም፡፡ ይልቁንም አይኑን በጥሬ ጨው አጥቦ ሰራዊታችን ምን በልቶ እንዲዋጋ ነበር የምትጠብቁት፣ ሲል በፖሊሲ የተደገፈ የሚመስለውንና በጄኔቫ ስምምነቶች ጭምር የተወገዘውን ድርጅታዊ ሌብነት በአደባባይ ለማስተጋባት አንዳች አይነት ሀፍረት አልተሰማውም፡፡