ቪቫ ሲሪ ላንካ!  (ከአሁንገና ዓለማየሁ) 

እንዲህ ሹክ ይለኛል
የምኞት ፋብሪካ
አቢይ አህመድ አሊ
ሳይሞት ሳይነካ
ቪቫ ሲሪ ላንካ!
የካድሬን ኩይሳ
የተቦረቦረን ያለቀን ተበልቶ
ሕዝቡ እንደ ንብ ተምሞ
ይደርምሰው ገብቶ
ከውቅያኖስ ማዶ ላሰማችው ፊሽካ
ቪቫ ሲሪ ላንካ
አቢይ አህመድ አሊ
ሳይሞት ሳይነካ
የሌላ ደም ሳይፈስ መተከል ወለጋ
ኢትዮጵያ ሳትከፍል ተጨማሪ ዋጋ
በሩን ክፈቱለት ወደሚያሻው ይንካ
ቪቫ ሲሪ ላንካ!
የጠላትን ሴራ ሁሉም ይወቅ ይንቃ
የንጹሐኑ ደም የጎረፈው ይብቃ
ወታደሩ ይባል ማሎ ሳቂ ሳንቃ*
ለሁሉም በእኩል ይዘርጋ ሰደቃ
አንዴ ሳይቆረጥ አሥሬ ይለካ
መድሓኒትም ቢሆን አይለፍ ከማንካ
ሕዝብ እንጀራ ይጋግር
የራሱን ሊጥ ያቡካ
ቪቫ ሲሪ ላንካ!

*ሳቂ ሳንቃ = በሩን ክፈት
ሲሪ ላንካ = ሕዝብ መስዋእትነት ከፍሎ በሰላማዊ ማእበል መንግሥት የቀየረበት የJuly 2022 አብዮት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕዝብ ሆይ! - በላይነህ አባተ

1 Comment

  1. ሲጀመር መንግስት ገና አልተቀየረም። ትርምስ ተፈጠረ እንጂ። ቪቫውም ቢቆይ ይሻላል። ተማሪና ሥራ ፈት ያመጣው ለውጥ ሃገራትን አስጨነቀ እንጂ የተሻለ ነገር አምጥቶ አያውቅም። ቪቫ መንግስቱ ያሉ፤ ንጉሱን ሌባ ሌባ እያሉ የጨፈሩ ተማሪዎችና አውደልዳዪች ብዙዎቹ በዚያው እሳት ተለብልበው አልፈዋል። በሶስት የተለያዪ የነጭ ገዢዎች የተገዛችው የያኔዋ ሲሎን የአሁኗ ሲሪላንካ በዚህም በዚያም ሰበብ ከህንድ በ1948 ብሎም በ1970 ዎቹ ላይ ስሟን ከሲሎን ወደ ሲሪላንካ ሪፕብሊክ ቀይራ ብቅ አለች። ህዝብ እንደ ሰርዲን የታጨቀባት ይህች ሃገር አሁን በምግብ መወደድና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ ከመንግስት ጋር ግብግብ ተገጥሞ መሪያቸው በወታደራዊ አየር ሃይል ወደ ሌላ ሃገር ተጉዞአል ተብለናል። ግን የስሪላንካ ትርፍ ምን ይሆን? የሃገሪቱ መሪስ ሃገር መልቀቅ መሬት ላይ ያለውን መከራ ይለውጠው ይሆን?
    ለምሳሌ ጠ/ሚር አብይ ወደ ስልጣን ሲመጣ የጦዘው ድጋፍ ከዘፈን እስከ ቀረርቶ ደርሶ ነበር። አሁን ደግሞ የቀጥታ ስድብና የእንካ ስላንትያ ናዳ እየወረደ እንደሆነ እንሰማለን፤ እናነባለን። ፓለቲካ እውነትን ተላብሶ አያውቅም። በውሸት፤ በያዘው ጥለፈው በዚህም በዚያም የማይመስሉትን በማፈን እድሜን ለማስቀጠል የሚደረግ የአራዊቶች ትንቅንቅ ነው። ዛሬ በየሜዳው እንደ እንስሳት እየታደኑ የሚገደሉት አማሮች በደላቸው ሃገራቸውን መውደዳቸው ነው። ሌላው ሁሉ የፈጠራ አሻሮ ፓለቲካና የተለጠጠ የብሄር ነጻነት የፈጠረው የውሸት ትርክት ነው። አይተነዋል፤ ኑረንበታል። እርሻና አረም ያለን ሰው ለቅሞ የሚረሽን አውሬዎች በበቀሉት የሃበሻ መሬት ቪቫውንም እልፍ መፈከሩም ያመጣውን የመከራ ዝናብ እያየን ነው። ገና እንደማያባራም አመላካች ነገሮች በየቀኑ አሉ። ለዚህም ነው “የጊዜአዊ መንግስት ይቋቋም” የሚለውን የሙታን ፓለቲካ ጭራሽ የማላምንበት።
    ሲሪላንካ ገና ብዙ ውጣ ውረድ ይጠብቃታል። አሁን አለምን ያቆራኘው የኢንተርኔት አገልግሎት በሚነዛው የፈጠራ ወሬ ስንቱ ተረብሾ ስንቱ እንቅልፍ አጥቶ እንደሚያድር የሚቀምር የለም እንጂ ብዙዎች በበሽታው ተጠቅተው ስራቸውን አጥተዋል። የአዕምሮ በሽተኛ ሆነዋል፤ የሚዳሰሰውን ግዑዙን አለም ትተው በአተቴና በመተት፤ በኮከብ ቆጣሪዎችና በጠንቋይ፤ በውሸታም ነብያቶች የወደፊቱን ለማወቅ ጥረዋል። ግን የሚቻል አይደለም። በጸሎት ከሆዷ ውስጥ ዓሳ አወጣሁ ከሚል ሰባኪ ጋር እንዴት ባለ ሂሳብ የወደፊቱን መነጋገር ይቻላል? ሁሉ ነገር አስረሽ ምቺው ሆኗል። ሰርቶ አዳሪ ቀርቶ ሰርቆ አዳሪ በዝቷል። የስሪላንካውም ለውጥ ልክ እንደ ሊቢያው፤ እንደ ግብጽ፤ እንደ ቱኒዢያው ወዘተ አሁን አስጨፍሮ ቆይቶ የሚያስለቅሳቸው ነው የሚሆነው። አብረን ቆይተን እንይ። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share