ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አልጀመርኩኝም – “በኢትዮጵያ ስለ ብሄረሰቦች ጥያቄ” (On the Question of Nationalities in Ethiopia – Walleligne Mekonnen – HSIU, Nov. 17, 1969))” የሚለውን ታሪካዊ ጽሁፍ ዋለልኝ መኮንን ባወጣ ጊዜና የልዑል መኮንን ባለቤት የሆኑት የልዕልት ሳራ ግዛው ወንድም የሆነው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዴንት ተማሪ ጥላሁን ግዛው መንግሥቱን ሲያወግዝ። በወቅቱ የቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደርጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ክፉኛ ይሞግቱ ነበር።
“ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” ለሚለው ክፉ ፖለቲካ ሰበብና ምርኩዝ የሆነችውን የዋለልኝን አነስተኛ ወረቀት (pamphlet) በወፍ በረር እስቲ እንቃኛት፣ ምን ተጽፎባታል?
ይህች መጣጥፍ ወደ ዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያንደረድረን፣ ጊዜና ቦታን እንድንመረምር ብሎም ለውይይትና ክርክር መነሻ እንዲሆን የተዘጋጀች ሙከራ ነች። ጸሃፊው ዛሬ ላይ የተዘፈቅንበት ትልቅ ተግዳሮትና መጠነ ሠፊ ችግር የሚቀረፈው በሕዝባዊ ውይይት መሆኑን ያምናል።
– የዋለለኝ ጽሁፍ በወፍ በረራ ዕይታ –
ዋለልኝ የአራተኛ ዓመት የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ያቀረባት አጭር ጽሁፍ ከትልቅ መጽሃፍ የምትበልጥ እምቅ ሃሳብ አዝላለች። ይህች ወረቀት የኢትዮጵያ አንድነትና አርበኝነት እንዲሁም የሃገሪቱን በአፍሪካ ብቸኛ የነጻነት አምሳል መሆኗ ተነግሮት ላደገው ተማሪ ድንገተኛ ክስተት ነበረች። ወረቀቷ ከመቅሰፍት የተማሪውን ትግል ፍላጎት የምታፈረጥምና ክርክር የምታስነሳ (provocative)እንደ አቶም ንጥረ ነገር ረቂቅ እንደ አቶሚክ ቦንብ ግዙፍ ሆነች። በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው የቀ.ኃ.ሥ. መንግሥት ለመገልበጥ ከፍተኛ ጦር ይዞ ከተንቀሳቀሰው ብ/ጄ መንግስቱ ነዋይ ይልቅ ይህች ትንሽ ወረቀት የንጉሡም ሆነ ዘውዳዊ ሥርዓቱ ትልቅ ተግዳሮት (challenge)በመሆን ድንገት ሳይታሰብ ባፈነዳችው አብዮት (revolution)ጉልታዊውን ሥርዓት (feudalism)ገርሰሰች።
የዋለልኝን ሃሳብ በራሴ አተረጓጎም ነውና ያቀረብኳቸው ማረም ይቻላል። ዋለለኝ ወደ ዋናው ሃሳቡ ሲንደረደር “የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምን ከምን የተውጣጣ ነው?(What are the Ethiopian people composed of?) ሲል ይጠይቅና፣ “ኢትዮጵያ በአሁኑ ደረጃ አንድ ብሄር (one nation) ብቻ አይደለችም፣ የየራሳቸው ቋንቃ፣ የአለባበስ ዘይቤ፣ ታሪክ ማህበራዊ አደረጃጀትና የየራሳቸው ክልል ያላቸው ከደርዘን በላይ በሆኑ ብሄሮች የተሰራች ነች” (made up of dozen nationalities) በማለት ያብራራል። ጨምሮም “በኢትዮጵያ ውስጥ ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ አደሬ/ሃረሬ ብዙዎቻችሁ ባትቀበሉትም ሶማልያን ጨምሮ ብሄሮች ይገኛሉ። ይህ ትክክለኛው የሃገሪቱ ገጽታ ሆኖ ሳለ ነገር ግን በገዥው መደብ የሚራመድ አስመሳይ ኢትዮጵያዊ ብሄረተኝነት” (fake Ethiopian Nationalism) አለ ሲል በአጽንዖት ይናገራል።
ዋለልኝ “የውሸት ብሄረተኝነት ምንድነው?(What is fake Nationalism?!) የአማራ ወይንም የአማራና ትግሬ የበላይነት አይደለምን?(Is it not simply Amhara and to a certain extent Amhra-Tigre supremacy?) የሚል አነጋጋሪ ሃሳብ ያነሳና – “ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ፣ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ፣ ብሄራዊ ልብስ ምን እንደሆን ማንንም ጠይቁ የአማራ ወይም የትግሬ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳል።
ይህም ብቻ አይደለም፣ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን አንድ ግለሰብ አማርኛ ማውራት፣ አማርኛ ዘፈን ማዳመጥ፣ የአማራና ትግሬ ኃይማኖት የሆነውን ኦርቶዶክስ ክርስትና መቀበልና በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የአማራና ትግሬን ሸማ ለብሶ መቅረብ አለበት” የሚል ሃሳብ ያክላል።
ዋለልኝ “ትክክለኛው ብሄራዊ መንግሥት ምንድነው?” ሲል ይጠይቅና “ብሄራዊ መንግሥት ሁሉም ብሄረሰቦች በመንግሥት ጉዳይ እኩል የሚሳተፉበት፣ ሁሉም ብሄረሰቦች ቋንቋቸውን፣ ሙዚቃቸውንና ታሪካቸውን እኩል የሚጠብቁበትና የሚያዳብሩበት ተመሳሳይ እድል ማግኘት ነው” የሚል መልስ ይሠጣል። “ብሄራዊ መንግሥት አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አደሬ/ሃረሬ፣ ሶማሌ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ወዘተ፣ እኩል የሚታዩበት ነው። ብሄራዊ መንግሥት በምጣኔ ኃብትም ይሁን ባህል አንዱ ብሄር ሌላኛውን ብሄር የማይጫንበት መንግሥት ነው” በማለትም ያብራራል።
“ወደ መዕከላዊው ጥያቄ ስንመለስ” ይላል ዋለለኝ፣ “እንደምን ሃቀኛ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ብሄራዊ መንግሥት መመስረት እንችላለን?(How can we form a genuine egalitarian national-state?) ሲል ይጠይቃል። “በእርግጥ በአመጽና በአብዮታዊ የትጥቅ ትግል (through revolutionary armed struggle) እዚህ ግብ ላይ እንደርሳለን ቢሆንም ግን ከመንግሥት ሃሰተኛ የብሄር ፕሮፖጋንዳ (pseudo-nationalist propoganda) ልንጠበቅ ይገባናል። አብዮቱ የትም ሊጀመር ይችላል የመገንጠል ዓላማም አንግቦ ሊነሳ ይችላል ይሁንና ግን በተራማጅ ኃይሎች፣ አርሶ አደሮችና ሠራተኞች እስከተመራ ድረስ የመጨረሻ ግቡ የኢትዮጵያን ሠፊ ህዝብ ነጻ ማውጣትና ብሄሮችን ምጣኔ ኃብታዊና ባህላዊ ነጻነት ማጎናጸፍ ነው” የሚለውን እምነቱን ያክላል (has the final aim the liberation of the Ethiopian mass with due consideration to the economic and cultural independence of all nationalities)።
የዋለልኝ ጽሁፍ “የሁሉም አብዮተኛ ሚና ንቅናቄው ሶሺያሊስታዊ ነው ወይንስ አድሃሪያዊ ብሎ መጠየቅ እንጂ ንቅናቄው የመገንጠል ዓላማን ያቀፈ ነው ወይንስ አይደለም ብሎ መጠየቅ አይደለም። ሶሺያሊዝም ዓለማቀፋዊነት (internationalism) ስለሆነ ሶሺያሊስት ንቅናቄ የግንጠላ (secessionist)ዓላማን በፍጹም አያራምድም” የሚለው ተስፋውም ብርቱ ነበር። (In the long run Socialism is internationalism and a Socialist movement will never remain secessionist for good)
ዋለልኝ ሠፊው ሕዝብ – ስለ መልክዓ–ምድራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ትስስር እንዲሁም ስለ ሠፊ ግብይትና ትልቅ ከተማ ጥቅሞች ግንዛቤ እንዳለው በማመን (the value of geographical and economic ties and the advantage of big market and a big state) ከሌኒን ትንሽ ሃሳብ ይጠቅስና “የብሄሮች ንቃተ ኅሊና ልዩነት ባለበት ሁኔታ የነቃው ብሄር (conscious nationality) ሌላውን በማገዝ ለሕዝቡ ሙሉ ነጻነት (total liberation) መጎናጸፍ መትጋት አለበት” ይላል።
– የዛን ዘመን ነባራዊ ሁኔታ –
የዋለልኝን ጽሁፍ ስናነብ በዛን ዘመን የነበረውን የዓለም ዓቀፍ ሁኔታና በሃገር ውስጥ የነበረውን ሁኔታ ማጤን ያስፈልጋል። በተማሪው እንቅስቃሴ ዘመን አለም በሁለት ርዕዮተ–ዓለም ተከፍላ ነበር። የነ ፊደል ካስትሮ፣ ቼ ጉቬራ፣ ሆ ቺ ሚንህ ታላቅ ገድል ብዙዎች ወጣቶችን አነሳስቷል። ሁሉም በዱር በገደል ተሰማርቶ እንደነሱ መሆን ነበር ምኞቱ። ተማሪው ሶሺያሊዝምን እያወደሰ ኢምፔርያሊዝምን ያወግዛል። ኢትዮጵያ የርስት አገርና የገባር አገር ተብላ የተለያየ የመሬት ይዞታ ሥርዓት ከማስተናገድዋም በላይ የሜጫና ቱለማ እንቅስቃሴና የመሪዎቹ መታሰር፣ የኤርትራ ሁኔታና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በጎጃምና ጌዴዎ የነበረው የገበሬዎች አመጽ እንዲሁም ደሃው በድህነቱ የሚሸማቀቀበትና የሚያዝንበት ወቅት መሆኑን በሚል ጥላሁንን እንደጠየቁት የሠማሁት “የብሄሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ” በሚል አርዕስት በተዘጋጀ ውይይት ላይ ነው።
ከዋለልኝ ወረቀት በፊት ተማሪውን ያስተባበረውና የሚያታግለው የመሬት ላራሹ ጥያቄ ዋነኛ ነው። ተማሪ ዋለልኝ በጀማሪዎች መርሃ ግብር ላይ እንዲናገር በተሠጠው ዕድል መሠረት ያነበባት ይህች ትንሽ ወረቀት ነገሩን ሁሉ ገለባበጠች። እያደር “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እስር ቤት ነች” የሚለው አመለካከት እየጎላ ሄደ። ትግሉ በዘመን ተንሰራፍት በነበረው የመደብ ጭቆና ላይ ያነጣጠረ ሲሆን የዋለልኝ ጽሁፍ ደግሞ ታጋዩንና አብዮተኛውን (Revo) ይበልጥ ደፋር አደረገው።
በዚያን ወቅት አድርባይነት ብዙም ቦታ የላትም። ቀደም ሲል ኢብሳ ጉተማ “ማነው ኢትዮጵያዊ ብሎ ያቀረበውን ግጥም ዋለልኝ ዘረኛነትን የሚያንጸባርቅ ግጥም ነው ብሎ ወርፎት ነበር። ይሁንና ግን ይህ ባለ ትንሽ ወራት ውስጥ ዋለልኝ “በኢትዮጵያ ስለ ብሄረሰቦች ጥያቄ” የሚለውን ጽሁፍ አወጣ። የዋለለኝን ወረቀት ብዙዎች ሲቀባበሉት በወቅቱ ተማሪ የነበሩት የሶማልያ ብሄር ተወላጁ ዶክተር አብዱል መጂድ ሁሴን “እንዴት ያማራን ሕዝብ በበዳይነት ትከሳለህ” በሚል ጥላሁንን እንደጠየቁት የሠማሁት በውይይት ላይ ነው። ፕሮፌሰር ባህሩ የዋለልኝ ጽሁፍ ተማሪዎችን የከፋፈለ ነው ሲሉ አውግዘውታል። አንዳንዶች ጽሁፉ ጂዎርጅያ የተወለደው ስታሊን በታህሳስ 1913 የጻፈው (Marxism and the National Colonial Question) ጽሁፍ ቃል በቃል ትርጋሜ ነው ሲሉ ኮንነውታል።
– ጊዜና ቦታ (Time and Space) –
ፖለቲካ ወይንም የአንድ መንግሥት ፖሊሲ መሬት ላይ ወርደው ይፈኩ ዘንድ የጊዜና ቦታ ግጥምጥሞሽን ይሻሉ። እንቁላል ዝም ብሎ ቢቀመጥ እንቁላል ነው። እንቁላል ተስማሚ ወይም ምቹ ሁኔታ (favourable condition) ሲታደል ሕይወት ያለው ጫጩት ይሆናል። አንድ እንቁላል በቂ ሙቀት ቢያገኝም አየር ላይ ወይንም ውሃ ውስጥ ሆኖ ጫጩት ሊፈለፍል አይችልም። አንድ የዶሮ እንቁላል ለመፈልፈል ቦታው ምድር ሲሆን ጊዜው 21 ቀን ምቹ ሁኔታው ደግሞ ከ35 እስከ 40.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ወይም ከ 84.5 እስከ 104.9 ደግሪ ፋራንሃይት ሙቀት ነው። ፖለቲካና ፖሊሲም ከባብያዊ ምቾት፣ ጊዜና ቦታ ይፈልጋሉ። ፖለቲካ በሕዝብ ጠባይና ባዳበሩት የፖለቲካ ባህል (character and political culture) ላይ የሚታነጽ ነው። በርካቶች አርሶ አደሮች በሆኑባት ኢትዮጵያ የዋለልኝ ጽሁፍ እንደምን ከጊዜና ቦታ ጋር እንደምትቀናጅ አይታወቅም። ከፖለቲካው ይልቅ ውትድርና ጊዜና ቦታን በማቀናጀቱ ረገድ ስኬታማ ሊሆን ይችላል። ፖለቲካ ሳይንስ የሚሆነው ጊዜና ቦታና ሲያገናኝ፣ ሲያቀናጅና ሲያጣምር ነው። ፖለቲካ ትምህርትን፣ ልምድንና ተሞክሮን ማጣመር አለባት። ፖለቲካ ከዚህም በላይ ጥበብን፣ ትዕግስትን፣ ፍላጎትን፣ ክህሎትን፣ በጎነትን፣ ግብረገብን፣ ሥነ–ምግባርን፣ ወዘተ ማካተት አለባት።
ፖለቲካ ወይንም ፖሊሲዎች ጭብጣቸው መልካም ቢሆንም እንኳን የአተረጓጎም ሂደቶች (processses of interpretation) ውስጣዊ ይዘቶቻቸውን ያመሰቃቅላሉ። የአንድ አገር ተጨባጭ ሁኔታና የዓለም አቀፉ ፖለቲካ አሰላለፍ ፖለቲካና ፖሊሲዎች እግር አውጥተው እንዳይራመዱ ያሰናክሏቸዋል። ይህ ብቻ አይደለም ፖለቲካውን በባለድርሻነት የያዙት የልህቃኑ የፍላጎቶች ልዩነት (perception of interests) ተግባርን ያሸሻሉ። እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ደሃው ላይ መከራ ያዘንቡበታል።
የወጣቱ ሶሻሊስታዊ ስሜቱ ከፍ ያለ በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያው የከበርቴው መደብ ገና ያልተፈጠረባት ኋላ ቀር አገር ነች። ሾሺያሊዝም በኢትዮጵያ ውስጥ ለመተግበር ምቹ ሁኔታ አልነበረውም ጊዜና ቦታንም አያቀናጅም። ሌኒንና ስታሊን የሚናገሩት የሃገራቸውን ወቅታዊ ሁኔታ ተመርኩዘው ሲሆን እኛ ደግሞ እንደነሱ የመሆን ችኮላችን ነገሮችን ሁሉ ግልብጥብጥ አደረገ። የብሄር ጥያቆች በብዙ የዓለማችን ክፍል ላይ ይነሳል ቢሆንም ግን ሊበራሎቹም ሆኑ ሶሺያሊስቶች የሃገራቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ተመርኩዘው ይህን ቁልፍ ጉዳይ (key issue) የማስተናገድ የራሳቸው ብሂሎች አሏቸው። የሕዝቡም የዳበረ ፖለቲካ ባህል ጥያቄውን ያቻችላል እንጂ አያጋግልም።
በርካታ ደሃ አገሮች ከተዘፈቁበት ችግር ለመላቀቅ ሶሺያሊዝምን እንደ አማራጭ ብቻ ሳይሆን እንደ ነጻ አውጭ ርዕዮተ ዓለም ይመለከቱት ነበር። ዋለልኝ ሶሺያሊዝም የተማሪው ርዕዮተ ዓለም (a level where socialism as a student ideology) መሆኑን ጠቆም አድርጎ ዋነኛ የሆነውን ለማንሳት የሚፈራውን “አንዳንዶች ሰዎች ጎሰኝነት (some people call it ridiculosly tribalism) ነው የሚሉትን እኔ ግን ብሄራዊነት (nationalism) የሚለውን ጉዳይ” አነሳለሁ ይላል።
ዛሬ ላይ የተንሰራፋው ዘረኝነትና ጎሰኝነት ከየት ፈላ? እኔ እንደተረዳሁት ከሆነ ዋለልኝ ሶሺያሊዝምን እንደ አማራጭ መፍትሄ ከመመልከቱ በቀር በጽሁፉ ላይ የዘረኝነትንም የመገንጠልንም ሃሳብ ሲደግፍ አይታይም። እርሱም ቢሆን ጽሁፉን ሲቋጭ “አንዳንዴ በሹክሹክታ አንዳንዴ ደግሞ በግልጽ የሚነገረውን “ይህ ሁሉ የዘረኝነት፣ የመገንጠል፣ ወዘተ ወሬ ምንድነው?ሲል ይጠይቃል። (What is this talk of tribalism, secessionism, etc,,,?)
የሆነ ሆኖ ግን “ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ፣ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ፣ ብሄራዊ ልብስ ምን እንደሆን ማንንም ጠይቁ የአማራ ወይም የትግሬ ነው” የሚለው የዋለልኝ ድምዳሜ አማራው ነገድ ተነጥሎ እንዲፈረጅ ምክንያት ሆነ። ዘረኞች ይህንኑ ጽሁፍ ተመርኩዘው ፀረ–አማራ አመለካከቶችን (anti-Amhara attitude) በማጉላታቸውና በማቅለማቸው አማራውን የተሳሳሳተ ፍርጃ ዒላማ አደረገው (bias toward categorizing targets as Amharas)። ዋለልኝ ቋንቋው፣ ሙዚቃው፣ ብሄራዊ ልብሱ የአማራና የትግሬ ነው” ብሎ ነው የጻፈው። እነሆ ታድያ ፍረጃው አማራው ላይ ብቻ ለምን በረታ?ጥቂት የውሸት ፌደራሊዝሙ ሥርዓት የጠቀማቸው ዘረኞች – ህወሃት የብሔር ብሄረሰቦችን ጥያቄ መመለሱ፣ ቋንቋዎች በየክልሉ እንዲነገሩ ባህሎች እንዲከበሩ በማድረጉ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷልና የብሄር ብሄረሰቦች ውዳጅ ነው ሲሉ – ይህን ያልተቀበሉት ደግሞ “ፌደራሊዝሙ የይስሙላ ነው – አማራም ትግሬዎችም አንድ ናቸው” ይላሉ።
ያም ሆነ ግን ዋለልኝ ስለ ብሄረሰቦች ጥያቄ ያነሳው የወቅቱ አይነኬ (sensitive) ሃሳብ ለፖለቲካ ዘረኞች (political tribalists /political ethnicists) ፍረጃ ሠበብና ምርኩዝ ሆነች። የባቡሯን አቅጣጫና መዳረሻ ያላስተዋሉት የዋሆች ሶሺያሊዝም ቅብ እሆነችው ባቡር ላይ ተሳፈሩ። ዘረኞች አዘናግተው ባቡሯን ፌደራሊዝም መሰል ቀለም ቀቧት፣ መዳረሻዋም የአማራ እልቂት ማስተናገጅያ ያደረገው – የክፉ ፖለቲካው ጥግ – የውሸት ፌደራሊዝም ሆነ።
– ዛሬስ፣ ጉደኛዋ ዛሬ! –
ክፉዎች የዋለልኝን ዲስኩር መቼ፣ እንዴት ወደ ዘረኝነትና መገንጠል እንደጠመዘዙት ባላውቅም ከያ በኋላ ግን ኢትዮጵያ በክፉ ፖለቲካ ምትሃት በግናለች። ተደኮሰረም፣ ሥልጣኑ ተቀያየረም – ድህነቱ አልተቀረፈም፣ መከራው አልነጠፈም፣ ፍጅት ግድያው ጋብ አላለም። “መሬት ላራሹ” የተጮኸለት ደሃው አራሽ አይኑ እያየ መሬቱን በመሬት ወራሪዎች እስኪቀማ ድረስ ትርጉም ያጣው ፖለቲካ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁም አዋረደ፣ አማራውንም አስፈጀ። ዋለለኝ የዛች ቀን የጻፋትን አስደማሚ ጽሁፍ ከሃምሳ ሶስት ዓመት በኋላ ዛሬ ላይ ስንመዝናት ከጊዜም ከቦታም ጋር አለመገጣጠሟንና አለመቀናጀትዋን እንገነዘባለን።
ሀ. ታጋዩ ኢትዮጵያ ህዝቦቿ በእኩልነት ይኖሩ ዘንድ በልማት ጎዳና እንድትራመድ በሙሉ ልቡ ሲታገል ጥቂቱ ጮሌው ደግሞ የዋለልኝን ጽሁፍ ተመርኩዞ ወደ ለራሱ ግለሰባዊ ጥቅም መቃረምያ አደረገው። ጥቅሙ – ሥልጣን፣ ገንዘብ፣ ዝና፣ ወዘተ፣ ሲሆን አማላዮቹና የጥቅማ ጥቅሞቹ አስጠባቂ (safeguarding) ክቡር ዘበኞች ምዕራብያውያኖቹ ናቸው።
ለ. ዋለለኝ የውሸት ብሄረተኝነት (fake nationalism) አለ ባለባት ኢትዮጵያ የውሸት ፌደራሊዝም (fake federalism) ነገሠ። ያለፉት መንግሥታት የብሄሮችን መብት ለመጠበቅ አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን ለማስተካከል ሞክረው ነበር። ንጉሡ ቋንቋዎች በየአካባቢው እንዲነገሩ ጥረት አደረጉ። ደርግ ራስ ገዝ (autonomous) አካባቢዎች በመፍቀድ የራስን እድል በራስ መወሰን (self-determination)በሚለው መርህ ችግሩን ሊፈታ ሞከረ። ህወሃት የተሻለ ፖሊሲ መንደፍ ሲገባው የውሸት ፌደራሊዝም (fake federalism) በመቅረጽ ባህላዊም ሆነ ምጣኔ ኃብታዊ ነጻነትን የማያጎናጽፈውን የቋንቋ ክልሎችን በማካለል ለዛሬይቱ ጉደኛዋ ዛሬ አደረሰን።
ሐ. ዋለልኝ “ሕዝቡ የአማራና ትግሬ ኃይማኖት የሆነውን ኦርቶዶክስ ክርስትና በግድ እንዲቀበል ይደረጋል” ባለባት ኢትዮጵያ ዛሬ የኃይማኖት ነጻነት ፈር ለቆ አስመሳይነትንና ሸንጋይነትን አበዛ። አስመሳይነትን ተመርኩዞ በሚመጣው ሃሰተኛ ነብይ ደሃው እየተበዘበዘ ይገኛል። የኃይማኖት ነጻነት የግለሰብ መብት መሆኑ እርግጥ ነው – ነገር ግን እንደ መጨቆኛ መሳርያ የተፈረጀችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ–ክርስትያን በመጥላትና በማስጠላት ትርክት ብዙዎች ቀኖናን ሳይመረምሩ ፈረንጆች ለእኩይ ዓላማ የቀረጹትን ጥልቀት በሌለው (superficial)ኃይማኖት አፈና ውስጥ እንዲወድቁ አደረገ። ይህ ሴራ በሃገሪቱ ክብር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል። ዛሬ ይህ ሁሉ ሃይማኖተኛ ባለበት አገር ሥነ–ምግባርና ግብረገብ ወርደው የእግዚአብሄር ቃል በአቋራጭ ጥቅም ማግኛ ዘዴ (means) ተደረገች። ሃሰተኛ ነብይነትና ሸንጋይ ፓስተርነትም ሆነ ቄስነት በማስመሰል ዘይቤ የሚመሩ የራስ ወዳድነት መገለጫዎች ናቸው። ማስመሰልና ሽንገላው ከመንግሥት የበለጠ የሚፈሩ ጮሌዎችን አፈላ ።
መ. ዋለልኝ – “የሁሉም አብዮተኛ ሚና ንቅናቄው ሶሺያሊስታዊ ነው ወይንስ አድሃሪያዊ ብሎ መጠየቅ እንጂ ንቅናቄው የመገንጠል ዓላማን ያቀፈ ነው ወይንስ አይደለም ብሎ መጠየቅ ሊሆን አይገባም” ይላል። ዋለልኝ ሶሺያሊዝም ዓለማቀፋዊነት (internationalism) ንቅናቄ ነውና የግንጠላ (secessionist)ዓላማን አያራምድም የሚል እምነት ነበረው። (በእርግጥ አቶ ኢሳያስ በወያኔ ሻጥር ተገፍተው ሊሆን ይችላል ኤርትራን ያስገነጠሉት)የሆነ ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆናለች። ዛሬም ትምህርት ያልቀሰሙ ግንጠላ አፍቃሪዎች አካቢያባቸውን ገንጥለው ያገሬውን መከረኛ ደሃ የግፍ ውሃ ሊግቱት እየጠበቁ ነው። መገንጠል ወርቅ የምትወልደዋን ዶሮ እንደማረድ ነው። ሁሉንም ወርቅ ባንዴ ሰብስቦ ለመውሰድ የቋመጠው ስግብግብ ዶሮዋን አርዶ ወርቁን ቢፈልግ የለም። መገንጠል ሲያወሩት ማር ማር ይላል በገሃድ ሲያዩት ግን መራር ነው።
ሠ. ዋለልኝ እኔ እንደተረዳሁት ከሆነ “የቅራኔው ኃይሎች አብዮትና ጥገናዊ ለውጥ መሆናቸው ቀርቶ በሳይንሳዊው ሾሻሊዝምና ነገሮችን በማዛባትና ዝንጉ በሚያደርጉ ትዕይንቶች ዙርያ ነው” ይላል። (The contradictory forces are no more revolution versus reform, but correct scientific Socialism versus perversion and fadism) ብዥታ የፖለቲካ ማነቆ መሆኑን ዋለልኝ ገና ድሮ አውቆታል። በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተካሄደውን የፋሽን ትርዒት ባህልን የሚጠወልግ አቅጣጫ አስለዋጭ (diversion)ነው ሲባል ተነቅፏል።
ብዙዎቹ ፖለቲካን ከጊዜና ቦታ ውጭ ለመተግበር ብዥታን ይጠቀሙበታል። ብዥታ ትክክልና ትክክል ያልሆነውን ክስተት መለየት እንዳይቻል ወይም ጥሩና መጥፎውን መለየት እንዳይቻል የምታደርግ፣ አቅጣጫን የምታስት ግትሮች ምትሃት የሚሰሩባል አስማት ነች። ሰው ሁሉ ብዥ ሲለው ጮሌው እንደ ልብ ይራመዳል፣ ይሠርቃል፣ ይከብራል። ዛሬ ጊዜ “አቅጣጫ ተቀምጧል” እየተባለ ሲወራ ይሰማል። መንገዱ በብዥታ እሾህ ታጥሮ ምን አቅጣጫ አለና።
ረ. ዋለልኝ “የማን አለባበስ፣ የማን ሙዚቃ፣ የማን የአምልኮ ባህል ነው ይልቁንም ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ፣ ኢትዮጵያዊ ሙዚቃ፣ ብሄራዊ ልብስ ምን እንደሆነ ማንንም ጠይቁ – የአማራ ወይም የትግሬው አይደለምን” ብሎ ያቀረበው ጥይቄ የጮሌውን ሩጫ ፈጣን አደረገው።
ወገኖቼ! ዛሬስ፣ ጉደኛው ዛሬ ላይ ቆመን ሁኔታዎችን እንደምን እናያቸዋለን?ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸውን አለባበስ፣ የአምልኮ ባህልም ሆነ ሙዚቃ በቅጡ አዳብረዋል ወይንስ ወደ ምዕራብያውያኑ አለባበስ፣ የአምልኮ ባህልና ሙዚቃ ተስበዋል?ምዕራብያውያኑ ሃገር በቀሉን ሸማ አስወልቀውን ሰልቫጆቻቸውን ሲያራግፉብን ምን ተሰማን?እነሱ እንደሆን ምጣኔ–ኃብታቸው ብቻ ሳይሆን አለባበሳቸውም ድንበር ዘለል (transnational) ሲሆን ጮቤ ይረግጣሉ። በቅኝ በተገዙት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ በሙሉ ልብስና ከረባት ማጌጥ የሥልጣኔ ምልክት ነው። በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው እንግሊዘኛ ብቻ እንዲናገሩ፣ እንግሊዘኛ ዘፈን ብቻ እንዲሰሙ አድርገዋል። ወይ ዛሬ፣ ወይ ጉደኛው ዛሬ – አንዳንድ የማስታወቅያ ንግድ ሠራተኞች የፈረንጅ አገሮችን ስም ሲጠሩ በማቆላመጥ ብቻ ሳይሆን በኩራትም ጭምር ነው። የሆነስ ሆነና የብሄረሰቦች ጥያቄን በአግባቡ መፍታት አቅቶን “ጉደኛው ዛሬ” ላይ ያደረሰን አባዜ ምን ይሆን?ግብዝነት (vanity) ወይንስ አላዋቂነት (ignorance)?
– ዘረኛ ፖለቲከኞች – ሃሰተኛ ፌደራሊስቶች (pseudo federalists)፣ ንዑስ ብሄረተኞች (petty nationalists) –
ዘረኛ ፖለቲከኞች ግብዝነትን አጥልቀው ድንቁርናን ተመርኩዘው በእግዚአብሄ አምሳል የተፈጠረውን የስውን ልጅ በዘር ፖለቲካ እያመሱትና እየገደሉት ነው። ዘረኛ ፖለቲከኞች “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ–ክርስትያንና አማራ አንድ ናቸው” በሚል ክፉ ፖለቲካ እየተመሩ የዘርና የኃይማኖት ጥላቻን ኮትኩተው አሳድገዋል። ፈጣኖቹ ዘረኛ ፖለቲከኞች አድዋ ድረስ የዘመተችውን ቤተ–ክርስትያን በማንቋሸሽና ሥራዋን በማጠልሸት ቅኝ ገዥዎችን ያስደስታሉ። ግብጽ ቃል የገባችላቸው ኢትዮጵያ ጠል ፖለቲከኞች – ዘረኝነት፣ ድህነት፣ ዝርፊያና ግድያን – ሥርዓት ለማድረግ ቀን ሌት በመሥራት እጅግ ዘግናኝ የሆነውን የፍጅትና እልቂት ዓይነት በበደኖና አርባጉጉ እንዲሁም በማይካድራና በወለጋ–ቶሌ በገሃድ ለዓለም አሳይተዋል። ፈጣኖቹ ዘረኛ ፖለቲከኞች ከፍጅትና ማስፈጀት ፖለቲካ ውጭ ሂሳብ አይቀምሩም፣ ግንባታ አይወጥኑም፣ ብረት አያቀልጡም ወይንም የመስኖ እርሻ አይሸነሽኑም።
“የብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ” የሚለውንም ፖለቲካ ለመበዝበዣና የኃብት መዝረፍያ ምንጭ ያደረጉት በፌደራሊዝ ስም የተደራጁት ሃሰተኛ ፌደራሊስቶች (pseudo federalists) ጭምብሉን ንዑስ ብሄረተኝነት (petty nationalism) ሳያወልቁ እንደምን በኢትዮጵያ ሠላም ይሰፍናል?
– የብሄረሰብ ጥያቄውና ኃይማኖት –
በፈሪሃ እግዚአብሄር የተሞሉት መላው የኢትዮጵያ ኃይማኖቶች – ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ እስልምና፣ ወዘተ፣ ታላቅ ሥርዓትና አስተማሪ ግብረገብ ይታይባቸዋል። ከዓመታት ወዲህ ግን የተንሰራፋው የአምልኮ ዘይቤ ባህልንና ጨዋነትን የሚጻረር የሥነ–ልቦና ጫና ሆኗል። የሥነ–ልቦና ጫና እየበዛ ተመራማሪ መሆን፣ አዋቂና ፈላስፋ መሆን፣ የጠፈር ሳይንቲስት መሆን አይቻልም።፡የፖለቲካን ሁኔታ ለራሱ ክብር የሚያዞሩ አስመሳይና አጭበርባሪ (imposter)እንዳለ ሁሉ ኃይማኖትንም የራሳቸው የኃብት ምንጭ መዛቅያ አካፋ የሚያደርጉ የበግ ለምድ ለባሾችም አሉ።
ትክክለኛው የኃይማኖት መምህር – በኦሮሞው፣ ትግራዩ፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው፣ አደሬ/ሃረሬው ሶማልያው፣ ወዘተ፣ መካከል ያለው ተፈጥሯዊ አንድነትና ፍቅር ይለምልም – የሚል ትምህርት እንዳይሰጡ የእምነት ቤቶች በብዥታ ታጥረዋል። ዛሬ እንደ አሸን የፈሉት የኃይማኖት ቤቶች “ሞትና ግድያ” ይቅር ብለው ክፉዎችን ቢያወግዙ ኖሮ ይህን ያህሉ መጠነ ሠፊ ግፍ በአገሪቱ ላይ አይታይም ነበር። “ጌታ ኃብታም ያደርግሻል – የሞቀ የደመቀ ትዳር ይሠጥሻል” ተብላ በሃሰተኛ ነብይ የሥነ–ልቦና ሃሴት የተጎናጸፈችው ደሃይቱ ሴት አገር ሠላም ካጣች ኃብቱን የት ሆና ልትበላው ነው?ጎረቤቶቿ በሞት እየተነጠቁ የሞቀ ትዳሩስ እንደምን ይሞቃል?
ለኃይማኖተኛ አጭበርባሪዎች መፍላት ምቹ ወይም አስፈላጊ ሁኔታዎቹ (necesssary conditions) መከራ፣ ስቃይ፣ ጦርነት፣ ቸነፈር፣ ፈተና፣ ደዌ፣ ድህነት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ሥራ ማጣት፣ ወዘተ ናቸው። የዳበረ የፖለቲካ ባህል፣ የምጣኔ ኃብት እኩልነት፣ እውቀት፣ ፍትህ፣ ነጻነት፣ የነቁ ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ መልካም አስተዳደርና መስተዳድር፣ መቻቻልና መግባባት፣ ወዘተ፣ በሰፈኑበት ቦታ ማስመሰልና ሽንገላ አቅም የላቸውም። ከኃብቱ፣ ከቪላው፣ ከሞቀው ትዳር ወይንም ከቀበጠው ኑሮ ትንበያ በፊት ኢትዮጵያ በመጀመርያ ሞትና ግድያ የሚቀርባት አገር እንትሆን ምዕመኑን ወይንም ወደየ ኃይማኖት ቤቶቹን የሚመጣውን አማኝ ማስተማሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የተንሰራፋውና የሠፈነውን ክፉ ፖለቲካ ይቀረፉ ዘንድ አስተዋጽዖ ያደርጋል።
– ሁኔታ ማርሽ ቀያሪ ነች –
ሁኔታ ክስተት ነች፣ ሥነ–ልቦናን ታማልላለች። አንድ ሃሳብ ድቅን ሲል ሁኔታ የሥነ–ልቦናን ቀልብ ታነቃለች። ሁኔታ ሃሳቡ ይተግበር አይተግበር ጉዳይዋ አይደለም፣ ሥነ–ልቦንና ስሜትን በማሟቁ ረገድ ግን ሚናዋ ቀላል አይደለም። “ባህሉም፣ ምኑም ምኑም ከሰሜኑ ክፍል የመጣ አይደለምን” የሚባለው አነጋገር የጮሌውን ሩጫ ፍጥነት ጨመረለት። “የአማራውንና የትግሬውን ሸማ አትልበሱ የራሳችሁን የባህል ልብስ ልበሱ” የሚለውን የዛሬው ፖለቲከኛ ተጠቃሚ ያደረገችው ሁኔታ ነች። ፖለቲከኛው ወⷈዋለሁ የሚለውን ወገን በባህል ልብሳቸው እያስጨፈረ እርሱ በቴሌቪዝን ለጥያቄ ሲቀርብ ምዕራብያውያኑ እንዲወዱት ሙሉ ልብስና ከረባት አድርጎ ገጭ ይላል። ለዚህም ነው በቶሎ ቪዛ የሚያገኘው። የስንቱን አፍሪካዊ ምሁር፣ ተዋናይና ከያኔ ዓዕምሮና ጉልበት የበላው ቪዛ ሰጥቶ መቀበያ ስልት ነው።
ይህ ብቻ አይደለም። ስለ ዲሞክራሲና ሠብዓዊ መብት ሲነሳ ምዕራቡን ዓለም እንደ ምሳሌ መጠቀም የጮሌነት ምግባር ሆኗል። ይህ ውብ መሰል የብዥታ ገጽታ ነው። ውዳሴ–ምዕራብ ወይንም ከምዕራቡ ዓለም ጋር መሞዳደጀያ ስልት የአስመሳዩ ፖለቲከኛ ሥልጣን ላይ የመውጫና የመዝረፍያ ስልት ነው። ብዥታን አቅጣጫ ማስቀየርያ ወይንም ማርሽ ቀያሪ ማድረግ የቻለ ጮሌ ፖለቲከኛ በለስ ቀንቶት እሥልጣን ወንበሩ ከተጠጋ የዓለም ባንክ ለሃገሪቱ ከሠጠው ገንዘብ ገሚሱን ሞጭልፎ እምዕራብያኑ አገሮች ኢንቨስት ያደርጋል።
ዛሬ ምዕራብያውያኑ አገር መሽጎ ስለ መገንጠል የሚያወራው የምዕራቡ ብሄራ ፍላጎት አሳላጭ – መድረክ ላይ ሲቆም እንደ ምዕራብያውያኑ ኃብታሞች በሙሉ ልብስና ከረባት አጊጦ ነው። አስገንጣዩ – አስገነጥለዋለሁ የሚለውን ክልል ባህላዊ ልብስ ለብሶ ቢሆን ኖሮ የሚደሰኩረው ቢያንስ ሞራሉን እናደንቅለት ነበር።
የአፍሪካን ፖለቲከኛ ቱሪስት ያደረገው ለፖለቲከኞቹ እንደልብ የሚታደለው የአውሮፓና የአሜሪካ ቪዛ ነው። “ዛሬ ነገ መፍትሄ ይገኛል” ብለው ተስፋ የሠነቁ በሃገር ቤት ዘመዶች ያሏቸው የውጭ ነዋሪዎች – ለፖለቲከኛው ቱሪስት ጭብጨባና ዶላር ካለገደብ የሚለግሱት – ድህነቱ እንኳን ቢቀጥል በአህጉሪቱ ሠላም ይሰፍናል በሚል ተስፋ ነው።
– “ክፉ ፖለቲካ” –
ኢትዮጵያን አሁን ላይ ለተዘፈቀችበት አሳፋሪ ችግር የተዳረገችው ዋለልኝ ከጻፈው ጽሁፍ ያፈነገጠው፣ ነገር ግን ጽሁፉን ምርኩዝ ያደረገው “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” የሚለው ክፉ ፖለቲካ የተወለደ ዕለት ነው።
ይህ ክፉ ፖለቲካ ለግብጽ ጣልቃ ገብነት ደልዳላ መንገድ ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ሱዳን ብርታት አግኝታበታለች። ይህ ክፉ ፖለቲካ የመስፋፋት ዓላማ ላላት ሶማልያና የመገንጠል ዓላማ ላላቸው ሁሉ አንደርዳሪ ኃይል ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ለሃገራቸው የሠሩትን የቀኃሥ ባልሥልጣናት ለህልፈት የዳረገ በርካታ ውጣቶች በቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እንዲያልቁ መንስዔ ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ሕወሃትን ከደደቢት ተሸክሞ እምኒሊክ ወንበር ላይ አስቀምጧል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ለሆዳም አማሮች የኢህዴን/ብአዴን አባልነት እጅ መንሻ ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ አማሮች በበደኖና አርባጉጉ ላይ የዘር ፍጅት እንዲፈጸምባቸው አድርጓል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ወያኔ ለቀረጸው ህገ መንግሥትና የዘር ክልሎች ማካለል ታላቅ ምሰሶ ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ለሌብነት፣ ምዝበራ፣ ህገ–ወጥነትና ብልግና ጽኑ መሠረት ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ መጠነ ሠፊ ለሆነው ስደት ዋነኛ መንሥዔ ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ባለሥልጣናትና ዘመዶቻቸው የኢትዮጵያ ኃብት ወደ አውሮፓና አሜሪካ እንዲያግዙ ድልድይ ሆኗል። ይህ ክፉ ፖለቲካ እጅግ በርካቶችን ለእስርና ዘግናኝ ሰቆቃ ዳርጓል። ይህ ክፉ ፖለቲካ አሳፋሪ ባህል ወደ ሃገር አስገብቷል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ቅኝ ገዥዎችን አስቦርቋል። ይህ ክፉ ፖለቲካ ዛሬም ወገን ከወገን ጋር እያላተመ፣ ፍርሃትና ስጋት እየጫረ ጮሌውን ወደ ሥልጣኑ ወንበር ማድረሻ ስልት መሆኑ ቀጥሏል።
ክፉ ፖለቲካ ዘለቄታዊ ጥቅም ባያስገኝም “ሥልጣን ይዤ ልዝረፍ” ለሚሉ ክፉዎች ወርቃማ ስልት ነው። ስልት መሆኑ ባልከፋ – ክፋቱ ግን ከተራራም ይከብዳል። ክፉ ፖለቲካ – ኅዳሴውን ግድብ አፍርሶ ግብጽን እፎይ እስኪያሰኝ፣ ነጻዪቱን ኢትዮጵያን የምዕራቡ ዓለም ተገዢ እስኪያደርግ አልያም ተጠባባቂውን–ተረኛ ዘረኛ እሥልጣኑ ወንበር አድርሶ – ድንበሩን እስኪያካልል፣ ቋንቋውን እስኪያውጅ፣ እምነቱን እስኪያጸና፣ ባህሉን እስከሚያስከብር፣ ጥሬ ኃብቱን ቆጥሮ እስከሚረከብ ድረስ – ዕለት ተዕለት አማሮችን ያግታል፣ ከቀዬአቸው ያፈናቅላል፣ አስቀቃቂና ዘግናኝ በሆነ ምግባር ይገድላቸዋል።
“ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” የሚለው ፖለቲካ ከዚህ በኋላ ምን ያህል አማሮችን እንደሚያግት፣ እንደሚያፈናቅልና እንደሚገድል ማንም ሊተነብይ አልቻለም። በየዕለቱ አቅጣጫ ማስቀየርያ ፖለቲካ እየተፈበረከ፣ ትኩረት መሳብያ አጀንዳ እየተቀረጸ፣ የሃሰት ማስረጃ እየቀረበ አልያም የሃሰት ፕሮፖጋንዳ እየተለፈፈ ደሃው አማራ ይህን ከተራራ የሚከብደውን ክፉ ፖለቲካ በምን ጫንቃው ይሸከም? የማደናገሩ ዲስኩር አማራው ላይ ለሚፈጸመው ዘር ተኮር ጅምላ ፍጅት (genocide) ፈጻሚው እንዳይታወቅ የመደበቅያ ስልት ሆኗል። አቤቱ አምላኬ ሆይ! ምነው ዝም አልክ?
– የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት ጠንካራ ሊሆን ይገባል –
የመንግሥት ደካማነት አይበጅም። የመንግሥት ደካማነት የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ውስጥ ይጥላል። ትልቅ ሕዝባዊ ድጋፍ የነበረው ብልጽግና የሌብነት ማሳለጫ፣ የክፉዎች ሥልጣን መውጫ መሰላል የሆነውን ህገ መንግሥት የመቀየር ወይም የማሻሻል አቅምም ፍላጎትም ለምን አጣ? ተዋጊ ጄት፣ ታንክ፣ ሞርተርና መድፍ የታጠቀ መንግስት ስልታዊውን የምዝበራ ስልት ገድቦ በጠራራ ፀሃይ የሚፈጀውን ምስኪን አማራ ከእልቂት መከላከል እንደምን አቃተው? መላ ኢትዮጵያ የዘር ፍጅት ቀጠና የሆነችበት ብልጽግና ፓርቲ በመሃል አገሪቱ ሌብነትና ዝርፊያን ወደ አራተኛ ደረጃ እስኪያሻቅብ ድረስ ምነው ዝም አለ?
ፍርድ ቤቶች፣ ጉምሩኮች፣ ማዘጋጃ ቤቶች፣ ገቢዎችና ቀበሌዎች መሥሪያ ቤቶች መሆናቸው ቀርቶ ሰው ዓይኑ እያየ ገንዘቡን የሚሰለብበት የምትሃት ቤቶች ሆነዋል። በትህነግ የሠለጠኑት የብልጽግናዎቹ ባላ ቪ8 ቶቹ መንታፊውች ካላንዳች ርኅራሄ የብርን የመግዛት ኃይል ሠብረው ደሃውን እሲዖል ደጃፍ ወርውረው አሜሪካ ውስጥ ዘመናዊ ቪላ ወይም ጋዝ ማደያ ለመግዛት በውጭ ምንዛሬ ከደበቁት የድሆች ገንዘብ ውስጥ መዘዝ አድርገው ያሻቸውን ይሸምታሉ።
ሌብነትና ምዝበራ ጣራ በደረሱባቸው ከተሞች ኢትዮጵያዊነት ኃጢዓት ሆኖ ባንዲራዋ መሸማቀቅያ ሆናለች። ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ ባንዲራ የሌቦችና መዝባሪዎች የቀን ቅዠትና ሰቆቃ ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዘረኝነትና የቋንቋ ፖለቲካ ከፍ ባሉባቸው ከተሞች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ባንዲራዋን እንዳይዙ እግዚአብሄር የሠጣቸው ተፈጥሯዊ መብት ተገድቧል። ገዳዮችና አስገዳዮች ፖለቲካውን እዚህ ጫፍ እስኪያደርሱት መንግሥትና ህግ የት ሄዱ?
የዩክሬንና ሩስያ ጦርነት፣ የዓለም የፖለቲካ ኃይል ሚዛን መዛባትና የወቅቱ የዓለም ነባራዊ ፖለቲካ ሽግሽግ ለመንታፊዎችና ለምጣኔ ኃብት አሻጥረኞች መልካም አጋጣሚ ቢሆንስ? ለፍቶ አደሮች ለታክሲና ባጃጅ ነዳጅ ለመቅዳት ሌት ተነስተው ሲሰለፉ ሙሰኞችና ሁኔታን አዋቂዎች ረቂቅ የምዝበራና ምንተፋ ቀመሩን እያሰሉ ቢሆንስ? በ WFPስም ምግብ ዘይት፣ የቅባት እህሎች ሲጓጓዙ ክፉዎች ከፊሉ በሽርክና በሚሠሩት ዘረኞች እጅ እንዲወድቅ ቢያደርጉስ? የወያኔ ዘመን ሙሰኞችና የእኩይ ዓላማ አራማጆች “አይዟችሁ፣ ማንም አይነካችሁም፣ በርቱ” እየተባሉ እንደምን ምጣኔ–ኃብታዊ ፍትህ ትሰፍናለች?
የኢትዮጵያ መንግሥት እንዳለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት ጠንካራ ሊሆን ይገባል። ሞት እንደ መንፈስ ነግሶ፣ ገዳዮች ከቦታ ቦታ እንደልብ እየተንፈላሰሱ መንግሥት አል ሊባል አይችልም። መንግሥት “አሜሪካ ውስጥ በየቀኑ ሰው ይገደላል” ብሎ ማካካሻ ከማቅረብ ይልቅ የጋናን አስተዳደር ዘይቤ እንደ ምሳሌ ቢጠቀምበት አዋቂነት ነው። በእርግጥ ቅኝ ገዥዎችን ያንበረከክችዋ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለየት ያለ ቀጠናዊና መልክዓ–ምድራዊ ችግሮች ቢኖርባትም ቅሉ ፖለቲከኞች ዘወትር አሜሪካ አሜሪካ ከማለት ይልቅ ማውሪሽያ፣ ቦትስዋና፣ ታንዛንያ፣ ናሚቢያ የተባሉት የአፍሪካ አገራት ከሞላ ጎደል እንደምን ሰላም ሰፈነባቸው? ብለው መጠየቅ አለባቸው።
የአሜሪካ የግድያ ወንጀል (crime against humanity) ምንጩ የምጣኔ ኃብት ያራራቀው ማህበራዊ መደብ የፈጠረው ልዩነትና ሠፊ ማኅበራዊ ቅራኔ (social contradictions) ሲሆን የኢትዮጵያ ችግር ምክንይት ደግሞ ዘረኝነትን የሚደግፈው ህገ መንግሥትና በዘረኞች የሚፈጸመው ዘር ተኮር ጅምላ ፍጅት (genocide) ነው። ከፍተኛ ማኅበራዊ ቅራኔ (social contradictions) ያጨናነቃት አሜሪካ የጥቂት ከበርቴዎች መታያና የቀበጡ የተዋንያን መድመቅያ እንጂ ለአፍሪካ የሚጠቅም መልካም ፖለቲካ አይታፈስባትም።
ማለፍ አይቀርም – ነገር ግን ሠላምን፣ አንድነትን፣ ሉዓላዊነትን፣ ጠብቆ ለሕዝባዊ መንግሥት አሸጋግሮ መሰዋት ክብር ነው። መንግሥት ቢያንስ ቢያንስ ሕዝብ በሠላም ወጥቶ በሠላም እንዲገባ፣ መብታቸው እንዲከበር፣ በጉልበተኞችና በዘረኞች እንይበደሉ፣ በቀማኞችና ሌቦች እንዳይጠቁና እንዳይዘረፉ፣ ከየቦታው እንዳይታገዱና እንዳይገደሉ፣ ወዘት፣ ተገቢውን ጥበቃና ከለላ ማድረግ አለበት። የመንግሥት ሥልጣን እንዲጨብጡ ዕድል (chance)በሯን የከፈተላቸውም ሆነ ታሪክ አደራ የጣለባችባቸው (responsible) ባለሥልጣናት በእጃቸው በጨበጡት ኃይል ሠላምን ሊያስጠብቁ ይገባል። መንግሥት ኢትዮጵያ ቀድሞ ወደ ነበራት ክብሯ፣ ሉዓላዊ ቁመናዋና አቃፊነትዋ እንድትመለስ ጥረት ማድረግ አለበት።
– የሕዝብስ ሚና ምንድነው! ሕዝብ በዘረኞች የተበተነውን ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብን መቅበር አለበት –
ገናናዋና የእግዚአብሄር መንግሥት መቀመጫዋ ኢትዮጵያ የገዳይና አስገዳይ ፖለቲከኞች መንፈላሰሻ ብቻ ሳትሆን የሌቦችና መዝባሪዎች መቦረቅያ ሆናለች። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ግለሰብን በገቢው መጠን መመደብ አይቻልም። ኢትዮጵያ የሁለት ሠፊ ልዩነት ያላቸው ማህበረሰቦች ማለትም (ሀ)የጥቂት መዝባሪ ተጠቃሚዎች (ለ)የብዙሃን ተመዝባሪ ደሆች አገር ሆናለች። ብዙሃን ተመዝባሪ ደሆች ለመብታቸው እንዳይታገሉ ክፉዎች በብሄር–ብሄረሰብ ክፉ ፖለቲካ ከፋፍለዋቸዋል። ጉራጌው፣ ኦሮሞው፣ አማራው፣ ጋምቤላው፣ ሺናሻው፣ ወላይታው፣ ትግራይዋ፣ ሲዳማው፣ ወዘተ፣ ተመዝባሪ ደሃ – ለፖለቲክና ምጣኔ–ኃብት መሻሻል እንዳይታገል አጠገቡ ያሉት መዝባሪ ሃብታሞች ያሰማሯቸው ኃይሎች ያዋክቧቸዋል። የዘር ፌደራሊዝሙ (ethnic federalism) የጥቂት መዝባሪ ዘረኛ ተጠቃሚዎች ፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ጥቅም ማስጠበቅያና መጨቆኛ ሲሆን ለብዙሃኑ ተመዝባሪ ደሆች ደግሞ መበዝበዥያና መገደያ ነው።
ገዳይ አስገዳይ ፖለቲከኞች “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” የሚለውን ፖለቲካ ካላራመዱ በቀር ግባቸው ይጨናገፋል። ፖለቲካ እውቀትን ሲጠይቅ ዘረኝነት ደግሞ በባዶ ዓዕምሮ ውስጥ ትንፈላሰሳለች። ሕዝብ በማስተዋል ከተነሳ ድንቁርና ትከስማለች። የእስከዛሬው እኩይ ሥራ እንዲቆም ሁሉም የታጠሩበትን የክልል አጥር በጣጥሰው መውጣት አለባቸው። ጉራጌው፣ ኦሮሞው፣ ጋምቤላው፣ ሺናሻው፣ ወላይታው፣ ትግራዩ፣ ሲዳማው፣ ወዘተ፣ ባንድነት “አማራውን አትግደሉ” ሊሉ ይገባል። ኦሮሞውም ቢገደል ሁሉም “ኦሮሞውን አትግደሉ” ሊሉ ይገባል። ትግራዋዩም፣ ጋምቤላም፣ ጉጂውም፣ ወዘተ፣ ቢገደል ሌሎች መጮህ ይገባቸዋል። ለኢትዮጵያ ህልውና የሚተጉና የሚታገሉ ወገኖች በክልል አጥር ታጥረው ዘመን ሙሉ በድንቁርና ጅራፍ መገረፍ አይገባቸውም።
ከሠላሳ ዓመት በላይ በተግባር ያየነው “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” – የተባለው ክፉ ፖለቲካ – ምግባረ ብልሹ፣ እምነተ ቢስ፣ እውቀተ–አልባ፣ ግብረገብ–አልባ፣ ውሸታም፣ ጨቋኝ፣ ገዳይ አስገዳይ፣ የምዕራቡ ዓለም ተንበርካኪ፣ ሆዳም፣ ዋልጌ፣ እፍረተ–ቢስ፣ ተኮፋሽ፣ – ሲያደርግ እንጂ ጉራጌውን፣ ኦሮሞውን፣ አማራውን፣ ጋምቤላውን፣ ሺናሻውን፣ ወላይታውን፣ ትግሬውን፣ ሲዳማውን ባጠቃላይ ኢትዮጵያውያኑን ሲጠቅም አልታየም።
ዛሬ ላይ ሥነ ሥርዓትና ግብረገብ (ethics and moral) እየጠወለጉ ነው። ጉቦ መጠየቅ እፍረት መሆኑ ቀርቷል። ጠጅ የጠማው የመብራት ኃይል ሠራተኛ መብራትና ውሃ አውቆ ቆርጦ ለማስቀጠል ገንዘብ ሲጠይቅ ትንሽ እንኳን ሃዘኔታ የለውም። የትምህርት ቤቱን ሂሳብ ለመክፈል ነዋይ ያጠረው የገቢዎች ሠራተኛ ግብሩን አብዝቶ “ይህን ያህል ስጠኝና ላስቀንስልህ” ሲል እፍረት አይሰማውም። የማዘጋጃ ቤቱ ሰው ቦታ እየመተረ ለባለገንዘቡ ሲሸጥ የሚቆጣ አለቃ የለም። እረ ስንቱ ተወርቶ! ለኃጢዓታችን ሲል ራሱን በሠዋልን የዓለም አዳኝ በሆነው ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ስም መነገድና ገንዘብ መሰብሰብ ፍርሃት መሆኑስ ቀርቶ የለ? ክፉው ፖለቲካ ፈሪሃ እግዚአብሄርን እንኳን ያደበዘዘ የዲያብሎስ ታናሽ ወንድም ነው።
ለሶስት አሥርት ዓመታት የጠላት የሥነ–ልቦና ጥምዘዛና ብዥታ ብዙዎችን ፈር እያስለቀቀች ጮሌውን ደግሞ የራሱ ጥቅም ዓላማ መጮለፍያ አድርጋለች። ቶክ ሾው፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ልዩ ልዩ አዝናኝ ትዕይንቶች የሥነ–ልቦና ጥምዘዛና ብዥታ እንጂ ወደ ሳይንሳዊ እውቀት መሸጋገርያ አልሆኑም። እነዚህ ሁኔታዎች ለበግ ለምድ ለባሹና ለአስመሳዩ ኃብት ማደኛ (fortune hunting) ሆነው እርሱን ባለ ሕንጻና ፋብሪካ ደሃውን ደግሞ ተበዝባዥና ተሰዳጅ አድርገውታል።
ክፉው ፖለቲካ ሆን ብሎ ድህነትን፣ እርዛትን፣ ጭቆናንና በደልን በማስፋፋት ሥነ–ምግባርን እያወረደ ጥቂቱን ባለገንዘብ ብዙሃንን ለማኝ እያደረገ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ልቅ ሆኖ የተንሰራፋው ህገ–ወጥነትና ሥርዓተ–ቢስነት ምንጩ “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” የሚለው ክፉ ፖለቲካ ያነገሰው የዘር ፌደራሊዝም ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተተበተበትን የዘር ፌደራሊዝም ሥርዓተ–ሠንሠለት በጣጥሶ – ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ሺናሻ፣ ወላይታ፣ ትግርይዋ፣ ሲዳማ፣ ወዘተ፣ ሳይባባል ዘረኞች አምጠው የወለዱትን “ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰብ ጭቆና ሃገር ነች” “አማራው ጨቋኝ ነው” የሚለው ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብ መቅበር አለባቸው። መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተነስተው ይህን አስተሳሰብ ላንዴና ለመጨረሻ ሊያወግዙ ይገባል። ይህ ክፉ አስተሳሰብ ከሰዎች ዓዕምሮ እስካልተወገደ ድረስ አንድነት ዘበት ነው። መምህርት መስከረም አበራ “አማራው የሚገደለው በአስተሳሰብ እንጂ በአስተዳደር አይደለም” ያለችው ይህን ማሳያ ነው።
የተሳሳተ ማህበራዊ ፍረጃ (biased social categorization)የተሳሳተ ማህበራዊ ግንዛቤን (biased social cognition)እያዳበረ የተሳሳተ ፍረጃን (biased categorization) ያጎለብታል። ዘረኝነት (ethnicism)እንደ ባህል አድጎ አድጎ የፖለቲካ ርዕዮተ–ዓለም (political ideology) ከሆነ ወደ ኢ–ሠብዓዊ የፖለቲካ ሥነ–ልቦና (inhuman political psychology) ይቀየራል። እነሆ በግለሰብ ወይንም በጎሳ ላይ ያነጣጠረ ወደ ጥፋት ያጋደለ ፍረጃ ወይም በዘረንነት ላይ የተመረኮዘ ያልተገባ ጥላቻ (prejudice)ከሰዎች ዓዕምሮ ውስጥ መውጣት አለበት። ክፉ አስተሳሰቦች ዓዕምሮን በማጽዳት ይወገዳሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ትልቁን ድራሽ የተሸከሙት መንግሥት፣ የኃይማኖት ቤቶችና አቃፊዋን ኢትዮጵያ የሚያውቋት ታላላቆች ናቸው።
– ምሁራን፣ ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ ሃቀኛ የፖለቲካ ሰዎች፣ ጋዤጠኞች፣ ተራማጆች – ተነሱ፣ ምከሩ! –
የኢትዮጵያ ችግር ዋነና መንሥዔ የምዕራቡ ዓለም ብሄራዊ ፍላጎት (national interest) ነው። ግብጽ የምዕራቡ ዓለም ተላላኪ ስትሆን በአገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ መከራውንና ግፉን፣ መፈናቀሉንና ግድያውን የሚያፋፍቡን የግብጽ ተላላኪዎች ናቸው።
የዓለም አቀፍ ሁኔታው ዘወትር በኢትዮጵያ ላይ መከራ ያዘንባል። የኃያላን አገሮች ፉክክርና ሽኩቻ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ፖለቲካና የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ኢትዮጵያን ያምሳታል፣ ፖሊሲዎች በትክክል እንታይተገበሩ ምቹ ሁኔታን አጥፍተው ጊዜና ቦታን አራምባና ቆቦ ላይ ያስቀምጣሉ። የዓለም አቀፍ ፖለቲካው ሁኔታው ችግር ጋብ የሚለው ወይንም የሚገደበው ሕዝብና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው ተባብረው ሲመክቱ ነው።
ከላይ እንደተገለጸው ክፉ ፖለቲካ ከቀን ወደ ቀን ክፋትዋ የሚበረታው ብዙሃኑን ገድላ ገድላ ፈሪ ማድረግ በመቻሏ ነው። ብዙሃኑ “በቃ ሁላችንንም ግደሉ እንጂ እንወያያለን” ብሎ መከራውን ተጋፍጦ ለምክክርና ውይይት ከወጣ ክፉ ፖለቲካ ትደነባበራለች፣ እውቀት በጥበብ (knowledge in wisdom)፣ ተግባር ደግሞ በመልካም እሴት (action in virtue) ይታጀባሉ። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ሊፈታ የሚችለው በውይይትና ምክክር ብቻ ነው። ክፉዎች እንድንወያይና እንድንመካከር አይፈልጉም። ክፎዎች ፍላጎታቸው እንዳይታነቅ ሲሉ የውይይትና ምክክሩን መድረክ ያበላሹታል።
በሌብነት የሚተዳደረውም የመንግሥት ሠራተኛም ሆነ “ዘረኝነት ነገ ሥልጣን ላይ ያደርሰኛል” የሚለው ዘረኛ ውይይትና ምክክር አይፈልጉም። ግብጽና አድህሮት ኃይላት ምክክርና ውይይቱ እንዲደናቀፍ ሱዳንን ይልኳታል፣ ገዳዮችንም አስማርተው አማራ ያስገድላሉ። ምዕራብያውያኑ አገሮች የተረጋጋች ኢትዮጵያ እንዳትኖር ምክክሩንና ውይይቱን ለማጨናገፍ ይሞክራሉ። ቢሆንም ግን የፍርሃቱን ሠንሰለት በጣጥሶ ክርክር፣ ውይይትና ድርድር ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው።
ማስተዋል መግባባትን ታመጣለች – በውይይት የማይፈታ አንዳች ነገር የለም። ሰቆቃና ግድያ፣ ፍጅትና እልቂት እንዲቀር እስካሁን በድፍረት የሚንቀሳቀሱት፣ አድርባትነት ያላስጎበደዳቸው፣ ጥቅም ያልገዛቸው፣ ጭብጨባ ያላዘናጋቸው፣ ለአገሪቱ ሠላም የሚታገሉ፣ ለሞቱት በአደባባይ የሚያለቅሱት፣ ወዘተ፣ ሃቀኛ ምሁራን፣ የጥበብ ሰዎች፣ ጋዜጠኞች፣ አስተማሪዎች፣ የፍትህ ታጋዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች – በሃገር ቤት በገጠር፣ በከተማ በገበያ ቦታዎችና በአደባባዮች፣ በትምህርት ቤቶችና በስብሰባ አዳራሾች፣ ወዘተ፣ የውይይት መድረክ ሲያዘጋጁ መንግሥት ተገቢውን ጥበቃና ከለላ ያድርግ።
አለበለዝያ ግን መወያየት እያቃተን ከማስተዋል (prudence)፣ አመክንዮ (logic)፣ እውቀትና (knowledge)መልካም እሴት (virtue)እየራቅን – ተስፋ ቆርጠን ብንዳክር ትርፉ የችግራችንን ዕድሜ ማራዘም አልያም ተሰዶ ዓዕምሮንና ጉልበትን ለሃብታሞች ገጸ–በረከት አድርጎ ማቅረብ ወይም የጥቂት ዘረኞች ተገዢ፣ ተመዝባሪና ተገዳይ ሆኖ መቅረት ነው።
ወገኖቼ!
ዓለም እዚህ ሳይደርስ እግዚአብሄር በታላቅ ክብር የሚመለክባት ኢትዮጵያ ቀርቶ የትም ቢሆን ሃቀኛ ለሕዝብና ለሃገር የቆሙ ደፋር ታጋዮችና የሕዝብ አገልጋዮች አይታጡም። እነዚህ ሃቀኛ ኢትዮጵያውያን የገዳዮችንና አስገዳዮችን እኩይ ድርጊት ገድበው ዘመን አመጣሹን ምዝበራንና ሌብነትን ለታሪክ ተመራማሪዎች ትተው፣ እፍረተ–ቢስነትንና ሥርዓት–የለሽነትን በሃይማኖት አባቶች አስገስጸው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀና ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ኅልውና በደጋጎችና መልካም ዓላማን ባነገቡ ቆራጦች ይቀጥላል። ክፉ ፖለቲካ ትደበዝዛለች – ባለቤቶችቿም፣ ደጋፊዎቿም አሽቃባቶችዋም ይቅበዘበዛሉ። ጥቂት ቀን ነው – ወገኖቼ! ኢትዮጵያ ወደ ቀድሞ ክብሯ ትመለሳለች።
ትላልቆች ታናናሾችን ያስተምሩ፣ ሁላችንም ለሕዝባዊ ውይይት እንነሳ!
እግዚአብሄር ይመስገን!