የተጠያቂነት ልቃቂት መቋጫው የት ነው ?! – መስፍን ማሞ ተሰማ

1. ሰኔ 11/2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ  ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በኦነግ ሰራዊት በአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ በተካሄደ የዘር ፍጅት ከ1500 በላይ ዜጎች በአሰቃቂ ጭፍጨፋ ህይወታቸውን አጥተዋል።
2. ሰኔ 23/2014 ዓ.ም ምዕራብ ኦሮሚያ በመንግሥት ፀጥታ ሀይሎች ቁጥጥር  ስር በመሆኑ የደህንነት ችግር አይኖርም ሲል የብልፅግና መንግሥት በኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ ይወቅልኝ ሲል መግለጫ አወጣ።3. ሰኔ 27/2014 ዓ.ም (የብልፅግና መንግሥት መግለጫ ባወጣ በአራተኛው ቀን) በምዕራብ ወለጋ ቄለም ወረዳ በኦነግ ሰራዊት በተካሄደ ከአራት ሰዐት በላይ በዘለቀ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ከ300 በላይ የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ህይወታቸው ጠፍቷል።

4.  በግንቦት? (2014) የኦሮሚያ ፕሬዚደንት አቶ ሺመልስ አብዲሳ ኦነገ/ሸኔን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከወለጋና ከሌሎች ከሚንቀሳቀስባቸው ወረዳዎች ጠራርጌ  አጠፋዋለሁ ሲሉ በአደባባይ ተናገሩ።  ኦነገ ግን በተቃራኒው  እጅግ ተደራጅቶ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋውን በየሳምንቱ አድርጎታል። አቶ ሺመልስ ህፃናትን እናቶችን አረጋውያንን እና ወጣቶችን ያስጨፈጨፈ ውሸት ዋሽተዋል። ስለ ዕልቂቱም እንደ ክልል መንግሥት ተጠያቂነትን አልወሰዱም።

5. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሰኔ 11 በግፍና በገፍ ለተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን እውቅና እንኳን ሳይሰጡ ችግኝ ሲተክሉ ዋሉ።  መፅሀፉ ለሁሉም ጊዜ አለው ይላል፣ ችግኝ ለመትከልም ቢሆን ጊዜ ነበረው። ተከተል አለቃህን ሆነና እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሚያው ፕሬዚዳንትም የዘር ፍጅት በተፈፀመበት የሰኔ 27 ጭፍጨፋ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው የብሎኬት ፋብሪካ ሲመርቁ ዋሉ። [ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰኔ 27ቱን ጭፍጨፋ ዘር ተኮር  መሆኑን ሳይገልፁ በደፈናው በመሸሽ ላይ ያለው(?!!) ኦነግ ሸኔ ጭፍጨፋ ፈፅሟል ባሉበት ቅፅበት ከተወካዮች ምክር ቤት እስከ ቀበሌ የብልፅግና ፓርቲ  ካድሬዎች ሁሉም ‘ሀዘን ላይ ን’ እያሉ የቁራ ጩኸት መጮኻቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር የሚያሳዝነው የዘር ጭፍጨፋን ለማውገዝና ሀዘንን ለመግለፅ የፓርቲውን መሪ አንደበት መጠበቃቸውና እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባታቸው እንደ ሀገር እጅግ አሳሳቢ የሆነ ሰዋዊና ማህበረሰባዊ  አረንቋ ውስጥ መዘፈቃችንን ያሳያል። ]

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኤርምያስ ለገሰና የመሳይ መኮንን መንገዶች፤ ቀጣዩ የኤርምያስ እሥሥታዊ እርምጃ

6. የብልፅግና መንግሥት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 11 ቀን ለተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን ዕውቅና በመስጠት የሀዘን መግለጫ ማውጣት ቀርቶ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዳይደረግላቸው በአፈ ጉባኤው አፍ አገደ።

7. የብልፅግና መንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር የሀሰት መግለጫ በመስጠትና ህዝብን ያለጥንቃቄ ለኦነግ ፍጅት በማጋለጥ፣ የኦሮሚያ መንግሥት እና ፕሬዚደንቱ በተደጋጋሚ በክልሉ የዘር ፍጅት የሚፈፀምባቸውን የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን መታደግ ባለመቻሉ/ባለመፈለጉ፣ የአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ባለሥልጣናት እና የፓርቲው መሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የሚወክሉት የአማራ ህዝብ በተደጋጋሚ እየደረሰበት ያለውን መጠነ ሰፊ ግፍና የዘር ፍጅት ከቶም መከላከልና ማስቆም ባለመቻላቸው ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ከሰብአዊ ርህራሄ ውጪ በግፍ ለተጨፈጨፉት የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ዕውቅና በመንፈግና የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዳይደረግ በማድረጋቸው፣ የኒህ ሁሉ የበላይ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዓመታት የዘለቀውን የዘር ፍጅት ማስቆም ባለመቻላቸውና በተደጋጋሚ በግፍና በገፍ በዘር ተኮር ጭፍጨፋ ህይወታቸውን ላጡ ኢትዮጵያውያን የሀዘን መግለጫም ሆነ እውቅና ሳይሰጡ ለተደጋጋሚ ዓመታት በመቆየታቸው፤ እኒህ ሁሉ እንደ ሀላፊነታቸውና እንደ ተሳትፏቸው መጠንና ስፋት በህግ ሊጠየቁና ሊዳኙ ይገባል!!! ተጠያቂነትን የማይቀበልና በራሱ ላይ መተግበር የማይችል መንግሥት የሀገርን ሰላምና የህዝብን ደህንነት መጠበቅ ከቶም መቼም አይችልም !!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share