“እኛ በሕዝብ በአርጩሜ እየተገረፍን የሰጠነውን ድጋፍ እነሱ አላግባብ ተጠቅመውበታል” አንዱዓለም አራጌ

May 28, 2022

Andualem Aragieአቶ አንዱዓለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ ናቸው። አንዱዓለም በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ጉምቱ ከሚባሉ ፖለቲካኞች መካከል ይጠቀሳሉ። አሁን ፓርቲያቸው ኢዜማ በመጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ያካሂደዋል ተብሎ በሚጠበቀው ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ለመሪነት ለመወዳደር ማክሰኞ ግንቦት 08/2014 ዓ.ም. በዕጩነት ተመዝግበዋል።

በዚህም አቶ አንዱዓለም በርግጥም የፓርቲውን የመሪነት ስፍራ ለመጨበጥ እንጂ እንዲሁ ለውድድር ያህል የገቡበት እንዳልሆነም ይናገራሉ። ባለፉት ጥቂት ወራት በፓርቲው ውስጥ ተከስተዋል ተብለው ስለሚነሱ ክፍፍሎች ብሎም በአጠቃላይ ለፓርቲው ዋና መሪነት ስለሚያደርጉት ውድድር አቶ አንዷለም ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ የፓርቲውን መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን እንደ አቶ አንዱዓለም ሁሉ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የስልክ ሙከራዎችን ቢያደርግም ሳይሳካ ቀርቷል። እንደተሳካ ለእርሳቸውም ተመሳሳይ እድል ይሰጣል።

እንዲሁም በቦታው ለመወዳደር የተመዘገቡ ሰዎችን ዝርዝር ለማወቅ እና ተመሳሳይ ዕድል ለተወዳዳሪዎቹ ለመስጠት ለፓርቲው ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን ለጊዜው ዝርዝሩ በሚመለከታቸው ኮሚቴዎች ተገምግሞ ባለማለቁ ይፋ ለማድረግ እንደሚቸገር ኢዜማ ለቢቢሲ ገልጿል።

ቢቢሲ፡ የፓርቲዎን መስራች መሪ ለመገዳደር ያበቃዎ ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ አንዱዓለም፡ በየትኛውም ጤነኛ ፓርቲ ውስጥ ልዩነት እንዳለ ሁሉ ኢዜማ ውስጥም ታክቲካል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች አሉ። ነገር ግን ምሰሶ በሆኑ ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ ልዩነት የለንም። ስለዚህ በተለይ በእኔ እና በመሪው (ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ) መካከልም ብዙ የሃሳብ ፍጭቶች ነበሩ።

ነገር ግን ያንን ይዤ ወደ ሕዝብ በመውሰድ ሚዲያ ላይ ማራገብ ወይም ጋዜጣ ላይ የመጻፍ ፍላጎት አልነበረኝም። ፓርቲው ለሕግ የበላይነት የሚተጋ ፓርቲ ስለሆነ ጊዜውን ጠብቄ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ሃሳቤን ተከራክሬ ለማሳመን ይህንን ወቅት ስጠብቀው ነበር። ስለዚህ ያሉኝ የሃሳብ ልዩነቶች ናቸው ለመሪነት እንድወዳደር ያደረጉኝ።

ቢቢሲ፡ ፓርቲያችሁ ሲመሰረት ገዢውን ፓርቲ በመፎካከር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል ተብሎ ተጠብቆ ነበር። ፓርቲው ከተመሰረተ በኋላ ይህ የሚጠበቅባችሁን ሰርተናል ብለው ያምናሉ?

አቶ አንዱዓለም፡ በአጠቃላይ አሁን ያለንበትን ዘመን የሚመስል ክፉ ዘመን አለ ብዬ አላስብም። ቅስም የሚሰብር፣ ወንድም በወንድሙ ላይ የሚጨክንበት እና ዘረኝነት የነገሰበት ዘመን ነው። ውሉ የጠፋበት ዘመን ነው። በዚህ የፖለቲካ መስተጋብር ውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚተጋ ፓርቲ ምን ያህል ችግር ውስጥ እንደሚገባ መገመት አያስቸግርም። እንደ ማኅበረሰብ የታመምን እና ነገ ምን እንደሚፈጠር ባለማወቅ ስሜታዊነት ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።

በዚህ ሁሉ ግራ መጋባት ውስጥ አገሩን አስክኖ ወደፊት ለመሄድ የሚደረግ ትግል ከብዙ አቅጣጫ ሲታይ አስቸጋሪ እንደሚሆን ማሰብ አይከብድም።

ፓርቲያችን ሕዝቡን አረጋግቶ እና በኢትዮጵያዊነት ዙሪያ በማሰባሰብ ወደፊት ለመሄድ ያደረገው ትግል አስቸጋሪ ነበር። ይህንን ለማሳካት የብሔር ፖለቲካ አገሩን በዋጠበት ዘመን ላይ መሆኑ ትልቅ ችግር ገጥሞን ነበር ማለት ይቻላል።

ባሰብነው መጠን ባይሆንም በቻልነው ልክ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጨርሶ እንዳይጠፋ እና እንዳይሞት አርማውን አንግበን ብንቆይም፣ በአጠቃላይ ብዙ ተሳክቶልናል ብዬ አላስብም። በውጫዊም በውስጣዊም ምክንያቶች።

ቢቢሲ፡ ከሚቀርቡባችሁ ወቀሳዎች አንዱ ገዢውን ፓርቲ ይሞግታል ተብሎ የተጠበቀው ፓርቲያችሁ የመንግሥት ፎቶ ኮፒ ሆኗል የሚል ነው። እሱ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ አንዱዓለም፡ በሕዝብ ደረጃ የሚነሱ ሃሳቦች በፓርቲ ውስጥም የተፋጭተንባቸው ናቸው። ከሃሳብ ልዩነቶቻችን አንዱ ከመንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት ነው። ግንኙነቱ መንግሥትንም አገርንም በሚጠቅም መንገድ እየሄደ ነው ወይስ ሁለቱንም የሚጎዳ ነው? የሚለው ሃሳብ ያከራከረን ነበር።

ከሃሳቡ ስንነሳ አገሩ ውጥንቅጡ በወጣ የፖለቲካ መስተጋብር ውስጥ እየሄደ በመሆኑ መጀመሪያ አገሩን ማረጋጋት ብሎም በሰከነ አገር ውስጥ ብቻ ነው ፖለቲካው ሊሰምር የሚችለው የሚል አጠቃላይ ሃሳብ ነበረን። አገሩ ከተረጋጋ በኋላ ምርጫን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን ማካሄድ ይቻላል የሚል እምነት ነበረን። ለመንግሥት የተወሰነ ድጋፍ ብንሰጠው አገርን ያረጋጋል የሚል ተስፋ ነበረን።

እኔን በግሌ ብጠየቅ መንግሥት ያንን አልተጠቀመበትም። ይልቁንም እንደ ቂሎች ነው የወሰዱን። መንግሥት እንዳታለለን እንዳሞኘን እንጂ ለአገር ብለን እንደምንከፍለው ዋጋ እና ሆደ ሰፊ ሆነን ነገሮችን እንደምናይ አልቆጠረውም።

በሌላ በኩል ይህ በሕዝቡ ዘንድ እንደተለጣፊነት ነው የተወሰደብን። ስለዚህ በሁለቱም በኩል አለመረዳቶች አሉ። እኛም በሕዝብ በአርጩሜ እየተገረፍን የሰጠነውን ድጋፍ እነሱ አላግባብ ተጠቅመውበታል። ይህ ነው ያለው ሁኔታ።

ቢቢሲ፡ ለፓርቲው መሪነት ውድድር የወጣው መስፈርት ሦስተኛ ዲግሪ ያለው እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ውስጥ ያገለገለ ሰው ከፍተኛ ነጥብ እንደሚያገኝ ያሳያል። ይህንን ጨምሮ ሌሎች የተጠቀሱ የመወዳደሪያ ነጥቦች የፓርቲውን መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የበለጠ የማሸነፍ እድል ለመስጠት የወጣ መስፈርት ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ አንዱዓለም፡ ኢዜማ በዕውቀት የሚመራ ፓርቲ እንዲሆን እንፈልጋለን። ግን ዕውቀት ደግሞ ከዩኒቨርሲቲ ብቻ ይገኛል ብለን አናስብም። እንደ አብርሃም ሊንከን አይነት ታላላቅ የዓለም መሪዎች ኮሌጅ ገብተው ወይም በዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነት የሚታወቁ አይደሉም። ይልቁንም በተግባር ተፈትነው ያለፉ፤ በመስዕዋትነት ቀልጠው፣ በዚያ ተገንብተው አገር የገነቡ ናቸው።

ለትምህርት ካለን ቦታ አንጻር መስፈርቱ አሁን ከተሻሻለው ነጥብ ከፍ ያለ ነበር። ነገር ግን ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት የምንሰጠው እውቅና በጣም የተጋነነ ነበር። የኢዜማ ውበቱ በክርክር ማመናችን ነው። ስለዚህ በዚህ መሰረት ለትምህርት የተሰጠው ነጥብ መጀመሪያ ከነበረው 50 ነጥብ አሁን ወደ 25 ወርዷል። ስለዚህ ይህ ከጀርባው ሌላ ነገር አለ ለማለት ይከብደኛል።

[መስፈርቶቹ በሥራ አስፈጸሚው ኮሚቴ ከመጽደቃቸው በፊት ክርክሮች ተደርገውባቸው በዚያም መሰረት መሻሻል የተደረገባቸው፤ ብሎም ማንንም በልዩነት ለመጥቀም ያላሰቡ ናቸው ሲሉ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ትዕግስት ወርቅነህ ተናግረዋል]

ቢቢሲ፡ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ነጥቦችም እኮ አሉ።

አቶ አንዱዓለም፡ እኔ ይሄ ፍጹም ነው እያልኩ አይደለም። ፓርቲው ገና እንደዚህ አይነት ሂደት እየጀመረ ነው። እኛ የጀመርነውን ልጆቻችን እና ወጣቶቹ ያስተካክሉታል ብዬ አስባለሁ። ይህ ክርክር አድርገን ለመነሻ ያህል የደረስንበት ነው።

ነገር ግን ከታች በጥረቱ ታግሎ፣ ማንነቱን አስመስክሮ እና መሪ መሆን የሚችልን ሰው ብዙ የሚደግፍ ነው ብለን አናምንም። በጉዳዩ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረግነው ክርክርም ከታች ላሉ ሰዎች እድሉን የበለጠ ለማስፋት ሙከራ አድርገናል። ነገር ግን ፍጹም ነው ብዬ አላምንም።

በትምህርትም በመንግሥትም ሥራ ያልታወቀ ግን በአባላቱ ዘንድ ከበሬታ ያለው እንዲሁም ራሱን በፓርቲው ውስጥ ሰርቶ ያረጋገጠ ሰው ነገ መሪ መሆን መቻል አለበት። በሚቀጥለው ጉባኤ ላይ ይሻሻላል ብዬ አስባለሁ። እያንዳንዱ መስፈርት ላይ አሁን እንነጋገርበት ከተባለ ብዙ ነገር ማንሳት ይቻላል።

ቢቢሲ፡ ፓርቲያችሁ ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸውን ከውጪ ሆኖ ለሚከታተል ሰው እንኳን መታዘብ ከባድ አይደለም። እነዚህ ከፍፍሎች ፓርቲውን እስከመፈረካከስ ያደርሱት ይሆን ብለው ይሰጋሉ?

አቶ አንዱዓለም፡ እዚያ ድረስ ይወስደናል ብዬ አላስብም። ኢዜማ ውስጥ መሰነጣጠቅ አለ የሚለውንም ብዙ አልገዛውም። ከዚህ በፊትም በሃሳብ እንፋጫለን። ነገር ግን ያን ፍጭት ወደ መገናኛ ብዙኃን አላወጣነውም። ፍጭቱን እንደ መሰነጣጠቅ አናየውም፣ ከዚያ ከወጣን በኋላም ጓደኝነታችን ይቀጥላል።

የምርጫ ጉዳይ ሲመጣ ደግሞ ነገሮች አስጨናቂ ሊሆኑ ብሎም ስሜታዊ መሆን ይኖራል፤ የተፈጠረውም ይሄ ነው። ፓርቲው ደግሞ በሕግ የሚመራ መሆኑን ያሳየበት ነው። ማንም ይሁን ማን በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ያየንበት ነው። ከሕግ እና ሥርዓት ውጪ ለመሆን የሞከሩ አንዳንድ አባላት ነበሩ፤ ጉዳያቸውን ለሕግ እና ለዲሲፕሊን ኮሚቴ መርተናል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምንም የኮሚቴውን ውሳኔ እንቀበላለን።

የምርጫ ወቅት እንደመሆኑ የተወሰነ መካረሮች ይኖራሉ፣ ይህም ጤነኛ አካሄድ ነው። ተስፋ አደርጋለሁ ከምርጫ በኋላ ለአገራችን ምሳሌ የሚሆን ነገር እንደሚኖር። እኔም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ካሸነፉኝ፣ አክብሬ ማስረከብ እሳቸውም እኔ ካሸነፍኳቸው እንዲሁ አድርገው ለአገራችንም ምሳሌ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ።

ቢቢሲ፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣዊ ክፍፍል ሲኖር ገዢውን ፓርቲ ተጠያቂ ያደርጋሉ። የእናንተ ፓርቲ ውስጥ ያሉ ልዩነቶችን በማስፋት ወይም ክፍተቶችን በመፍጠር የገዢው ፓርቲ እጅ አለበት?

አቶ አንዱዓለም፡ ወደፊት ሊኖር ይችላል ብዬ እሰጋለሁ። አሁን ባለኝ መረጃ ግን እንደዚያ አይነት ምልክት አላየሁም።

ቢቢሲ፡ ለምን ይሰጋሉ?

አቶ አንዱዓለም፡ ያው አይታወቅም፤ ፓርቲዎች ውስጥ ያለ ሁኔታ የመንግሥት ጥቅም ሊኖርበት ስለሚችል ያ አጋጣሚ አይፈጠርም ብዬ ሙሉ በሙሉ ለመናገር አልፈልግም። በተወሰነ መልኩ ጣልቃ ሊገቡ ይችሉ ይሆን ወይ ስል አስባለሁ። እስካሁን ድረስ ያየሁትም የሰማሁትም ነገር የለም። ምን አልባት እኔ ስላልደረስኩበት ሊሆን ይችላል ወይም ንጹህ ስለሆኑ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ መረጃ ስለሌለኝ ንጽህናቸውን እንውሰድላቸው።

ቢቢሲ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስፈርቶች የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንጥቀስ ቢባል ከሚጠቀሱት መካከል ኢዜማ አንዱ

ነው። ይህንን ፓርቲ አቶ አንዱዓለም በመሪነት ቢይዙት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚጠይቀው “ተንኮለኝነት ወይም ሴራ” ይጎድላቸዋል የሚል አስተያየት ይነሳብዎታል። ምን ምላሽ አለዎት?

አቶ አንዱዓለም፡ በርካቶች ይህንን ነገር ያነሳሉ። እኔ ግን የዋህ ነኝ ብዬ አላስብም፤ ይልቁንም ብልህ ነኝ ብዬ አስባለሁ። የኢትዮጵያ ችግር አብዛኛው መሰረቱ የፖለቲካ ባህላችን ነው።

አንደኛው ችግር ደግሞ ይህ አሁን የምትዪው ፖለቲካኛ ማለት ተንኮል የተሞላበት እና ሌላውን ጀርባውን መውጋት ያለበት ብሎም መጠፋፋትን እንደመፍትሄ የሚቆጥር ባህል ያለው ነው የሚል እምነት አለን። ይህ ባህል እስካልተቀየረ ድረስ የኢትዮጵያ ችግሮች አይፈቱም።

እኔ ያ የፖለቲካ ባህል እንዲቀየር ቀጥተኛ የሆነ እና ግልጽነት የተሞላበት ፖለቲካ ማራመድ ትክክል ነው ብዬ አምናለሁ። አሁን ሁሉም ሰው ለምሳሌ ለመወያየት ሲታሰብ ሸምቆ ነው የሚገናኘው። ስለዚህ ልብ ለልብ ሳንገናኝ እና ሳንነጋር ትሸውደኛለች፣ ይሸውደኛል በሚል ካብ ለካብ ስንሄድ አገራችንን እያጠፋናት ነው። እኔ ይህ የፖለቲካ ባሕል መቀየር አለበት ብዬ ስለማምን በዛ እገፋበታለሁ።

3 Comments

  1. Andualem,
    Your earlier struggles for freedom and justice were very much appreciated.
    However, at this time you have to come clean and just admit your party’s shameful collaboration with OPDO as it swallowed up Addis Ababa and crushed northern Ethiopia into the stone age.

  2. አንዱ አለም አራጌ ይሄ ጩሉሌ ሰው በምን ምትሃት አልፎ ሂዶ ፍሬ ሊያፈራ የሚችለውን ድርጅት እንዳሰናከለው ፈጣሪ ይወቅ። እንደ ጥጃ ስትታሰሩ ስትፈቱ ህዝብ እምነት የጣለባችሁ ዜጎች እያላችሁ ብርሃኑ ግምቦት ሰባትን ይዞ በምን ተአምር ነው ድካማችሁን የነጠቀው? አስመራ መሎቲ ቢራ ውስጥ መሽገው 2 ሳምንት ጠብቁን ነጻ እናወጣችሁዋለን ብለው እጥብ አድርገውን ዛሬ በላያችሁ ላይ ቁጭ ሲሉ ያሳዝናል። ብርሃኑም ሆነ አንዳርጋቸው የወያኔ ሰዎች እንጅ የኢትዮጵያ ስላልሆኑ በዚህ አትለሳለሱ ጥልፍልፍ ስራቸውን ግን አትችሉትም ነቅታችሁ ጠብቁ።

  3. ግርማ ሰይፉ ብርሀኑ ነጋ ኦሮሙማ ከሰጣቸው ሽራፊ ስልጣን መነሳትን እንኳን በውናቸው በህልማቸውም ማሰብ አይፈልጉም። አንዴንድ በብርሀኑ የናበዙ ወጣቶችም አሉ እነሱ ከጠሩ ኢዜማ ተሀድሶ ካደረገ ከአብን ባልደራስ መኢአድ ጋር ተቀናጅቶ መልክ ያለው ስራ ይሰራል ካልሆነ እንዳለፈው ምርጫ በመጣ ቁጥር በውርደት ይጠናቀቃል። ዶር አብይ አቶ ታዲዮስ ታንቱን አስረህ ነብስህ እንዴት እረፍት አገኘች?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

281773279 589624645852490 8570690513383339644 n
Previous Story

አሸባሪው ሕወሓት በግዳጅ ዜጎችን ለውትድርና በመመልመልና እርዳታን ለእኩይ አላማ በመጠቀም ተግባሩ እንዲጠየቅ ጥሪ ቀረበ

172513
Next Story

አውደ ሃሳብ – “በወያኔ ጊዜ የወልቃይት ሰው ሊቢያ ውስጥ እንደ ባሪያ ተሸጦአል”—“ሰብአዊ መብት ተሟጋች እና ጦማሪ አቶ ዳኛቸው ተሾመ

Latest from Blog

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

ከመጠምጠም መማርን እናስቀድም!

;በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com) አብዛኛው አንባቢ ተገንዝቧል ብዬ እንደምገምተው ሕዝብ ለቡና ቲራቲም፣ ለግብዣ፣ ለበዓል፣ ለሰረግ፣ ለሐዘን፣ ለእድር፣ ለእቁብ ለውይይትና ለሌሎችም ማህበረሰባዊ ጉዳዮች ሲገናኝ የሚበዛው አድማጭ ሳይሆን ተናጋሪ  ወይም ደግሞ ለመናገር  መቀመጫውን ከወንበር ወይም
Go toTop