እጮሃለሁ! – ብሩክ ነኝ

አባቴ ተሰቅሎ፣
ወንድሜ ተቃጥሎ።
እህቴ ታግታ፣
እናቴ ተቀልታ።
አያቴ ተሰ’ዶ
ህፃን ልጄ ታርዶ… አሞኛል!
ወገን ሞቶብኛል!
ሰው ተገ’ሎብኛል
በማያውቀው ጉዳይ ባልገባው ጨዋታ፣
በሌለበት ግንባር ባልዋለበት ሜዳ ቀድሞ እየተመታ፣
ተጨምቆ ተጨምቆ ጠብ ላይልለት የድላቸው ፋይዳ፣
መከራ የሚገፋው እየወደቀበት የማያውቀው እዳ…።
ሞት እያንዣበበ… ደክሞት ካረፈበት ከደሳሳ ቤቱ፣
ለማይሞላ ኑሮው ለማይነጋው ሌቱ።
ዛች ጥርስ እያፋጨ፣
ጥይት እያፏጨ።
ካራ እየተሳለ፣
ቀስት እየተሾለ…
አለ!
ከተፈጥሮ ታግላ፣
ጎታች ባህል ጥላ፣
ልትማር የተጋች ቀን ይወጣል ብላ።
መድረሻ ተነፍጋ መንገድ ላይ የቀረች
እህቴ…. የታለች?
አሞኛል!
ሰው ተገድሎብኛል!
ሰው ተሳዶብኛል! ተፈናቅሎብኛል! ከኖርበት ቀዬ፣
የአቅሜን እጮሃለሁ …
“የሰላም፣ ፍትህ፣ የህግ ያለህ!” … ብዬ።
“የኔ አቅም ለቅሶ ነው ድምፅ ልሁናቸው ልጩህላቸው” ስል
ይመጣል ሳይፈራ አሳ’ቆ ሊያፍነኝ ቃላቱን የሚስል
“ምንድነሽ?” ይለኛል “ለእገሌ ለእንትና” ጉዳቴ ሳይገደው
“የሟች ወገኑ ነኝ!” ንፁህ ሆኖ ሳለ ለሞት ‘ሚማገደው።
“የት ነበርሽ?” ይለኛል
“ለምን ዛሬ?” ይለኛል… ይሳለቅብኛል ድምፄን እየለካ
ስጮህም ዝምም ስል ለ’ሱ ፖለቲካ
“መርጠሽ ነው” ይለኛል…
መርጦ ገዳይ ካለ በየአደባባዩ፣
መርጬስ ባለቅስ ማን ይሆን ከልካዩ?
መርጬ አለቅሳለሁ ለተገፋው ህዝቤ ለሞተው ወገኔ
ቡድኑን አንተ አብጀው ንፁህ መሆኑ ነው የሚያገባኝ እኔ።
በፈለግኩት ጊዜ በፈለግኩት ቦታ
ስችል አለቅሳለሁ ሳልችል በዝምታ
ፈቃጅ አልፈልግም ለራሴ ስብራት ሀዘን አስተማሪ
አስታዋሽ አልሻም ላጣሁት ወገኔ የ’ጩሂለት’ ጥሪ
በፈለግኩት ጊዜ በፈለግኩት ቦታ
ስችል አለቅሳለሁ ሳልችል በዝምታ
“የማን ነሽ? ምንድነሽ? ከየት ነሽ?” ይለኛል ከየትስ ብመጣ?
ገድዬ አልፎከርኩኝ ሞቶብኝ ነው እንጂ አቅሌን የማጣ
ገዳይ ንፁህ ፈጅቶ በኮራበት ሀገር
ለተገፋ ማልቀስ ለምነው ‘ሚያስወግር?
ገድሎም አይበቃውም “እሰይ” ብሎ አይረካ
እንባዬን አድርቆ ሀዘኔን መቀማት አዲስ ፖለቲካ
እጮህለታለሁ…
ንፁሁ ሲጎዳ ባልመረጠው ደሙ ባልመረጠው መልኩ
ክርስቲያንም ሙስሊም ጥፋት ከሆነበት በምርጫ ማምለኩ
ለአማራ እጮሃለሁ በጅምላ ለሚያልቀው ለሚፈሰው ደሙ
ለትግራይ እጮሃለሁ ጦርነት ሲጎሰም በልቶት ሰቀቀኑ፣
ስደት ለመረጠው ከገዛ ሀገሩ፣ ከገዛ ወገኑ።
ለተደፈረችው፣ ለተሰበረችው እንግልት እህቴ፣
ላዘነች እናቴ
ለኦሮሞ ወንድሜ፣ ለደቡብ አባቴ፣ ለሀረሪ፣ ሱማሌ፣
ቤኑሻንጉል፣ አፋር፣ ድሬደዋ ላለው ወይ አዲስ አበቤ።
ለተበዳይ ህዝቤ፣ ለሞተ ወገኔ…
እጮህለታለሁ!
ቡድኑን አንተ አብጀው ንፁህ መሆኑ ነው የሚያገባኝ እኔ።
ትናንት ጮኼያለሁ፣ እጮሃለሁ ዛሬ፣ እጮሃለሁ ነገ
ሁሉም ወገኔ ነው ድምፅ የተነፈገ።
እጮህለታለሁ! … እጮሃለሁ!
ብሩክ ነኝ

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ““ነጻ”” ይወጣ ይሆን? ( ከአሁንገና ዓለማየሁ)

2 Comments

  1. አስራደው ከፈረንሳይ በግጥሙ ” አትሰቀል ይቅር ተጠየቅ ልጠየቅ” እንዳለን ሁሉ አንዳንዴ ጭራሽ ምድሪቱን ፈጣሪ የረሳት ይመስላል። ደግሞም ነው። ይህ ግን ከፈጣሪ ጥፋት ሳይሆን ከሰው ተንኮልና ሃጢያት ነው ይሉናል የቀኑ የሃይማኖት ሰዎች። ይህም ሁሉ ውሸት ነው። ችግሩ እኛው ራሳችን ነን። የጄ/ተፈራ ማሞ መሰወር ምን ያህል የአሁኖቹ አለቆቻችን በጊዜአቸው እንደ ከፉ ያሳያል። ጄኔራሉ ከጠላት ጋር ሲፋለም ሰውነቱ ውስጥ ሳይወጣ ነው የት እንዳደረሱት ያልታወቀው። ፍትህ በሃበሻው መሬት ድሮም አልነበረም። አሁን ግን የእንስሳት ዘመን ሆኗል። ሻለቃ ዳዊት ወልደጌዎርጊስ “Red Tears” በተሰኘው መጽሃፉ ላይ እንዳስነበበን ያኔ ኤርትራ እንደዛሬው ሳትሆን በአስመራ በየጊዜው እየታፈሱ ለእስር ይዳረጉ የነበሩት ወገኖቻቸውን ፍለጋ ቤተሰቦች ሲሄድ እዚህ የለም እዚያ ጠይቁ ወይም ደግሞ አልፎ ተርፎ ለትምህርት ውጭ ሃገር ተልኳል ይሏቸው እንደነበር ይታወቃል። የጄ/ተፈራ ማሞና የሌሎችም ቤተሰቦች በየፓሊስ ጣቢያውና በሌሎች መንግስታዊ መ/ቤቶች ስለ ቤተሰባቸው መሰወር ለማወቅ በሚያደርጉት ፈልጎ ማፋለግ የሚደርስባቸው ግፍ ይህ ነው አይባልም። እልፍ የኦሮሞ ጡሩንባ ነፊዎች መራራ ጉዲናን ጨምሮ አፍንጫው ስር ተቀምጠው እየዛቱና እያማቱ እውነቱን የሚናገሩ ጋዜጠኞችንና ወታደራዊ መኮንኖችን እየጠለፉ ማስደንገጥና መሰወር ምን የሚሉት የብልጽግና መንገድ ነው? ህዝብን በማሰቃየት፤ በማሰርና በመግረፍ በስልጣን የቆየ አወዳደቃቸው የሮም ሲሆን በታሪክ አላየንም እንዴ? ጋዜጠኛ ጎቤዜ ሲሳይ በቅርብ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ የታሰርኩት ” የሰው ደም ባጨማለቀው ቤት ውስጥ ነው” የእነማን ደም ይሆን? ይህ ከወያኔ አሰራር የሚለየው የቱ ላይ ነው? በአንድ በኩል ለሃገር ዝመቱ በሌላ በኩል ለሃገር አንድነት የቆሙና ሊቆሙ የሚችሉ ሃይሎችን በማሰርና በማፈራረስ ሙከራ ላይ ያለው የጠ/ሚ አብይና የአማራ ተቀጥላ ተኩላዎች ትርፋቸው ምን ይሆን? ያስፈራቸውስ ምንድን ነው? ትላንት የታሰረውን ዛሬ መልሶ የሚያስርና የሚያሰቃይ መንግስት ከወያኔው የዘር ፓለቲካ የሚለየው በቃሉ ቱልቱላ እንጂ በተግባሩ አይደለም። ወያኔ ሽዋ ድረስ እስኪመጣ ተጠብቆ የመልስ ምት የተባለው ከሴራው አንድ አካል ይመስለኛል።
    አሁን እንሆ ወያኔና ሻቢያ እንደገና ለመላተም ከፍተኛ ዝግጅት እያረጉ አልፎ አልፎም እየተቆራቆሱ ይገኛሉ። በዚህ መሃል አሜሪካ ለወያኔ ራሺያ ለኤርትራ እሳት እያቀበሉ ያገዳድሉናል። ሱዳን ወያኔ የሰሜን እዝን በመታ ማግስት የኢትዮጵያን ድንበር መውረሯ በአሜሪካና በግብጽ ታዛ እንጂ ሱዳን ዳቦ ካረረባት ቆይቷል። በሱዳን የኢትዮጵያ የሰላም ጠባቂ ጦር ከሃገሬ ይውጣልኝ ያለቸው በሱዳን ውስጥ ወያኔን የማሰልጠንና የማስታጠቅ ሥራቸው እንዳይደረስበት በመፍራት ነው። ግን የተራቀቀውና ውስብስቡ የሻቢያ የስለላ መረብ ይህን ሁሉ ጠንቅቆ ደርሶበታል። ኢሳያስን የራሳቸው አገልጋይ ለማረግ ለዘመናት የጣሩት ምዕራባዊያን እምቢታው ዘላቂ ሲሆንባቸው አሁን የአስመራውን መንግስት ለመገልበጥ ወገባቸውን ታጥቀው ተነስተዋል። ይሁን እንጂ የኩባውን ፊደል ካስትሮን ማውረድ እንዳልቻሉ ሁሉ የአስመራንም መንግስት አያነቃንቁትም። የሴራቸው መረብ ለማስፋት አሁን በሱማሊያ የሰላም ጠባቂ ጦር እንደገና ለመላክ ተነስተዋል። ይህ ነው ፓለቲካ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ። አንድ ጋ ትፈረጥጣለህ፤ ሌላው ጋ ተመልሰህ ትሄዳለህ። አሁን አሁን የሚገርመው ነገር የኤርትራና የኢትዪጵያን በሃሳብ መግባባት ተጸይፈው እርስ በእርሳችን እንደገና እንድንገዳደል የሚሰሩ ሃይሎች ብዙዎች ናቸው። ለዚህም ነው ወያኔን እየጋለቡ አስመራ ለመግባት ያሰቡት። የእብድ ሃሳብ ነፋስ እንደነካው ድቄት ነው። የወደቀበት አይታወቅም።
    በምንም ዓይነት የወታደራዊ ስሌት ወያኔ ሻቢያን የማሸነፍ እድል የለውም። ሻቢያ የወያኔ የነፍስ አባት ነውና! የዛሬን አያርገውና አብረው ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ወታደር ወግተዋል። ግን ደም ያፈሰሰ ደሙ ይፈሳል አይደል የሚለው መጽሃፉ ወያኔ ” የትግራይ ህዝብ ተከቧል” እያለ ምድሪቱን ሰው አልባ ለማረግ በየስፍራው እሳት ይጭራል። ቀድሞ ባረሰበት በሬ ዛሬ የሚያርስ የለም። ወታደራዊ ጉልበቱና ጉራው ዋጋ ቢስ ነው። ይልቅ ለሰላም መፍትሄ የሚሆኑ ነገሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ላይ አቅርቦ መወያየት በተገባ ነበር። ለወያኔ መኖር ጦርነትና ግርግር ደም መፋሰስና የዘር ፓለቲካ አስፈላጊ በመሆኑ የትግራይን ህዝብ ለዘመናት እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ያምሰዋል። የሚገርመው የጳጳሱም አብሮ ማበድ ነው። በቅርቡ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲህ አሉ። “የትግራይ ቤተክርስቲያን ተወልዳለች። ከጠላቶቿ ተለይታለች” ይህ ነው ጳጳስ? ግን በአንድ እጅ መስቀል በሌላው ሽጉጥ የታጠቁ ስመ መንፈሳዊያን ምን እንጠብቃለን። ትግራይ ከጎረቤቷ ሁሉ ተጣልታ፤ ከኢትዪጵያም ተገንጥላ ሃገር መሆን አትችልም። ያው ግን ሲተኩሱና ሲያታኩሱ ዝንተ ዓለም ይኖራሉ እንጂ።
    እኔም የናፈቀኝ ዘሩን፤ ቋንቋውን፤ ሃይማኖትና የኢኮኖሚ ስኬትና ማጣቱን ሳይደገፍ ሰውን በሰውነቱ አይቶ ፍትህ ሲጓደል የሚጮህ ነው። ግን አሁን ባለችው የሃበሻ ምድር ሰው በሰውነቱ ሳይሆን በዘሩና በሃይማኖቱ ብሎም በሚናገረው ቋንቋ እየተፈረጀ አላቅሰው ሲያለቅሱ የምናያቸው ስመ ምሁሮች ስሜን የቀየረው አማራ ነው፤ ክርስቲያን ያረገኝ አማራ ነው፤ መሬትን የቀማኝ ነፍጠኛ ነው ይሉናል። የፓለቲካ ውሾች እነዚህ ናቸው። ዓለም ፍትሃዊ ሆና አታውቅም ከብራዚል በስተቀር ደ/አሜሪካ ስፓንሽ ይናገራሉ፤ ብራዚል ፓርችጊዝ ትናገራለች። ይህን ቋንቋ መርጠው ነው? ዛሬ በአርጀንቲና ከጀርመንና ከጣሊያን በመጡ ሰዎች ተጥለቅልቃለች። ብዙው ሃብትና ንብረት በእነርሱ የተያዘ ነው። ውጡ ማለት ይቻላል? እስቲ ለዚህ ጉዳይ የጫቱ የኦሮሞ ፕሮፌሰር የሚለው ምን አለ? ግን ፓለቲከኞችና የእሳት ራት አንድ ናቸው። እሳቱ ውስጥ ገብተው እስኪንቀለቀሉ ድረስ በእሳቱ ዙሪያ መደነሳቸው አይቀሬ ነው። እኔ ግን ሰው ለሆነ ሁሉ ” እጮሃለሁ”. የሰው መለኪያው ያ ነውና። በቃኝ!

  2. ነገርን ነገር ያነሳዋል ህዝቅኤል ፕሮፌሰር ማእረጉ ነው ስሙ ነው? አሁን በርዶለት ከሆነ አላውቅም እንጅ አንድ ሰሞን መላውን አሳጥቶት ነበር ዋቄ ፈታ ከውሀ ውስጥ ወጣ ብሎ ህዝቡን ሲያስቀው ነበር። መንግስት ይሄን ጫት የሚሉትን ቢያግድ ግማሽ ችግር ይቀነስ ነበር አቶ ህዝቅኤል ጋቢሳም በጤነኝ አእምሮው ማሰብ ይችል ነበር።አቶ ያልኩት በቅርበት መድረክ ላይ አታካራ እንጅ ምሁራዊ ትንተና ሲሰጥ ባለመስማቴ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share