ፋኖን ከኦነግ ሸኔ ጋር ማመጣጠኛ ለማድረግ የሚኬድበት ክፉ ፖለቲካ መቆም አለበት

ስለፋኖ በግልፅ መታወቅ ያለባቸው ጉዳዮች!

1) ፋኖን ከኦነግ ሸኔ ጋር ማመጣጠኛ ለማድረግ የሚኬድበት ክፉ ፖለቲካ መቆም አለበት:_

ፋኖ የራሱን መሳርያና ስንቅ ይዞ ከጠላት ጋር ሲተናነቅ የከረመ ኃይል ነው። በርካቶች በዚህ ሂደት ሕይወታቸውን ገብረዋል። አካላቸው ጎድሏል። ቤተሰባቸው ተበትኗል። በርካቶቹ ቀድሞ እንደጠፋው አንዳንድ ባለሀብት፣ አሊያም እንደሸሸው ባለስልጣናት አገር ሸሽተው አገር ቤትም ውጭ አገርም መኖር የሚችሉ ናቸው። እነ ምሬ ወዳጆ ሀብት ንብረታቸውን ጥለው ነው ትግል የገቡት። ሌሎች በርካቶች ተመሳሳይ ዋጋ ከፍለው ነው ለአገር የቆሙት። ፋኖዎች ላበረከቱት መከበር እያለባቸው ግን የሚጠሏቸው አካላት አሉ። ለአብነት ያህል አንድ የለመድነው ክፉ ፖለቲካ አለ። የኦሮሞ ብልፅግና የሆነ አጥፊ ኃይል ላይ ሕግ አስከብር ሲባል አማራ ክልል ላይ ማመጣጠኛ ይፈልጋል። የኦሮሞ ፅንፈኞችን ግፊት በፈራ ቁጥር አማራ ክልል ውስጥ አሊያም አማራ ኀይል ያለው ላይ የጦስ ዶሮ ይፈልጋል። እነ ጃዋር ሞሃመድ ሲታሰሩ እስክንድርና ሌሎችን አማራ ናቸው ብለው በማመጣጠኛነት አሰሩ። ኦ ኤም ኤን በቀጥታ ስርጭት ሕዝብን እርስ በእርስ የሚያጋጭ ዘገባ ሰርቶ ይጠየቅ ሲባል ምንም ያላደረገውን አሥራትን አሽገው ሰራተኞቹን አሰሩ። ኦነግ አጣዬን ያቃጠለ ሰሞን ሽፋን ተሰጥቶታል። ለሕግ ይቅረብ ሲባል ማመጣጠኛ አማራ ተፈለገ። ወለጋ ላይ ኦነግ ሸኔ በንፁሃን አማራዎች ላይ ጭፍጨፋ ሲፈፅም አማራ ታጣቂ ተብሎ በሀሰት አማራ ስሙ ተነስቷል። መምቻ ነበር። ይሄ የተለመደ ነው። ምንም ይሁን ኦሮሚያ ክልል ውስጥ አንድ እርምጃ ይወሰድ ሲባል ዘወር ዘወር ብለው ንፁሃ አማራን የጦስ ዶሮ የማድረግ ክፉ አባዜ ተለምዷል።

ሰሞኑን እንደ አዲስ ኦነግ ሸኔን እናጠፋለን ብለው ዘመቻ ጀምረዋል። ለኦነግ ማመጣጠኛ ፋኖ ላይ ትኩረት ያደረጉ አካላት እንዳሉ መገመት ይቻላል። ወሎ አካባቢ እየታየ ያለው ይህን መሰረት ያደረገ ይመስላል። ኦነግ ሸኔ እና ፋኖ የተለያየ ዓለም ሰዎች ናቸው። እናቀራርብ ካልን ከፋኖ መከላከያና የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ለኦነግ ሸኔ ይቀርባል። ምክንያቱም ከመከላከያና ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል ኦነግን የሚቀላቀሉ እንዳሉ ይታወቃል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት በርካታ የፀጥታ ኃይሉ አባላት ኦነግ ሸኔን የሚያግዙ ብሎም የሚቀላቀሉ መሆናቸውን በይፋዊ መግለጫ ነግሮናል። ኦነግ ሸኔ ፋብሪካ ሲያቃጥል ፋኖ ፋብሪካ የሚዘርፈውንና የሚያወድውን ትህነግን እየታገለ ከርሟል። ኦነግ ሸኔ ንፁሃንን ሲገድል ፋኖ ንፁሃንን ከሚገድለው ትህነግ ጋር እየተፋለመ ነበር። ትህነግና ኦነግ ሸኔ አንድ ሆነናል ብለው መግለጫ ሲያወጡ ፋኖ ኢትዮጵያን ለማዳን ጥሪ ተቀብሎ የዘመተ ኃይል ነው። ይህ የማመጣጠን ክፉ አባዜ ከፋኖ ላይ የሚሰራ አይደለም። የሀገር ክህደት ነው። ውለታቢስነት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ ውስጥ ስነስርዓት ሊይዝ የሚገባው የፖለቲካ ሃይል ቢኖር ብልፅግና ፓርቲ ነው!!!

መንግስት በፋኖ ጉዳይ የሚያነሳው ቅሬታ አለ። ይህን ቅሬታ ከመንግስት በላይ ፋኖን ያሳስበዋል። ፋኖ በስሙ የሚግድበት አይፈልግም። የሚጎዳው ራሱን ነው። ፋኖ ስሙ የተከበረ ስለሆነ በየትኛውም አካባቢ በስሙ ሊነግድ የሚሞክር አይጠፋም። ትግሉን ለገንዘብ የሚያስመስል አይጠፋም። መንግስትም በራሱ ተቀናቃኝ ፋኖ ለመፍጠር ሙከራ ያደረገበት ጊዜ አለ። ይህ ሁሉ ለትክክለኛው ፋኖና ለሕዝብ ጎጅ ስለሆነ መንግስት ከፈለገ ከፋኖ ጋር ሆኖ ማስተካከል ይችላል። መሰል ችግሮችን ማስተካከል የፋኖ ፍላጎት ይሆናል እንጅ አይከፋውም።

2) ለትህነግ የሚጠቅመው መንገድ መቆም አለበት:_

ትህነግ በራሱም በዓለም አቀፍ ወዳጆቹም ሲያስወቅስ የከረመው ፋኖን ነው። የውጭ ተቋማት የሚረግሙት ለአገር ዘብ ሆኖ የከረመውን ፋኖን ነው። ስለሚፈራው ነው። ያኔ ስንወረር ወዲያውኑ የጠራነው ፋኖን ነው። በመንግስት ሚዲያ “ኧረ ፋኖ ፋኖ” እየተባለ ሲዘፈን ነው የከረመው። ፋኖ ሲጨንቅህ የምትዘፍንለት፣ ሲደላህ የምትዘምትበት ኃይል አይደለም። አሁንም ጠላት እየተዘጋጀ ነው። ነገ ደራሹ ፋኖ ነው። ፋኖ ላይ የሚደረገው የትኛውም ትክክል ያልሆነ ነገር መከላከያንም ልዩ ኃይሉንም፣ አርሶ አደሩንም ያስከፋል። ሕዝብን ያስከፋል። ምክንያቱም መከላከያው አቅም ሲያጥረው የደረሰው ፋኖ ነው። ለልዩ ኃይል ደጀን የሆነው ፋኖ ነው። ከአርሶ አደሩ ጋር የዘመተው ፋኖ ነው። በፋኖ ላይ የሚደረግ የትኛውም ትክክል ያልሆነ ነገር የፀጥታ ኃይሉ ውስጥ ይገባል። የሚጠቅመው ለትህነግ ነው። ይህ እርስ በእርስ የሚያጋጭ አካሄድ መቆም አለበት።

3) ፋኖዎች እንደ ፀጥታ ኃይል መሆን አለባቸው:_

ድምፃቸው የማይሰማ፣ በቻሉት ለቀጣዩ ትግል እየተዘጋጁ ያሉ ፋኖዎች ብዙ ናቸው። በአንዳንዶቹ አልፎ አልፎ የሚታየው የሚዲያ አጠቃቀም ግን አውዳሚ ነው። በቀናነትም ቢሆን የሚናገሩት እየተመነዘረ ለብዙ መቀስቀሻ የዋለበትን ጊዜ ብዙ ነው። ፋኖ እንደ ልዩ ኃይል፣ እንደ መከላከያ የፀጥታ ኃይል እንጅ አክቲቪስትም፣ ገዥ ፓርቲም፣ ተቃዋሚም አይደለም። ዩቱዩበሩ በሄደ ቁጥር፣ የሚያደንቀው ስላገኘ በየአጋጣሚው የሚሰማውን መናገሩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ፖለቲከኛ ሞልቷል።አክቲቪስት ሞልቷል። ፌስቡከኛ ሞልቷል። ፋኖ በየሚዲያው መገኘት የለበትም። በተለይ ስልጠናውንም ዝግጅቱንም ማሳየት ወገንን የሚያስደስተውን ያህል የሚያሰጋቸው ኃይሎች እንዳሉ መታወቅ አለበት። ሁሉም ነገር በሚዲያ ሊነገር አይችልም። የገንዘብና ወዘተ ችግር ስለሚኖር አሊያም መታወቁ ይጠቅማል በሚል ብቻ የስልጠና ፎቶ ሲያልከሰክሱ መዋል፣ ታዋቂ ከተባለው ጋር መታየት፣ የፓርቲ ፖለቲካን ሲተነትኑ መዋል ለፋኖ አይጠቅምም። ስለሆነም ፋኖ ሚዲያና ታይታ የሚያበዙትን “ከአይን አታስገቡን” ብሎ መምከር፣ መውቀስ አለበት። ታይታ ፋኖን ይጎዳዋል። የሚዲያ ሞቅታ ስሙን ያጠፈዋል። የፋኖ ሙያ መተኮስ ነው። ፀጥታ ማስከበር ነው። ፖለቲካ ለመተንተኑ በርካቶች አሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢህአዴግ የዝምታ ፍራቻ (Sedatephobia) እና ስርወ-ምክንያቱ

4) ፌስቡከኛው ለፋኖዎች ማሰብ አለበት:_
የስጋ ዘመዱ ቢሆን እንዲለው የማይፈልገውን በፋኖ በኩል እንዲነገርለት የሚፈልግ፣ አንዳንዴም ፋኖ ያላለውን በሀሰት ሲለጥፍ የሚውል ፌስቡከኛ አለ። “ፋኖ አመረረ፣ ፋኖ ወጥር” እያለ ነገሮችን ከማብረድ ይልቅ የሚያጋግል ሞልቷል። ፋኖዎቻችን በዚህ ሁኔታ ቢሰው ፎቷቸውን ከመለጠፍ የተለየ ነገር ሊያደርግ አይችልም። ፋኖ ላይ የሚደረገውን ጫና በመቃወም፣ ችግሮች ሲፈጠሩ መፍትሄ መፈለግ፣ እንዳይጎዱ ለፋኖዎቹ ማሰብ ያስፈልጋል። ለሚናገሩት፣ አጀንዳ ለሚሆኑበት ነገር መጨነቅ ያስፈልጋል። ይጎዱብናል ብሎ ሊሳሳላቸው ይገባል። ይሳሳቱብናል ብሎ ሊሰጋላቸው ይገባል። በጠላት፣ በሰርጎ ገብ፣ ስሜታዊ ለማድረግ በሚፈልጉ አካላት አንዳይሳሳቱ ድጋፉ ያስፈልጋቸዋል። ፌስቡከኛው ቢችል ድጋፍ፣ ካልሆነ ለደሕንነታቸው መጨነቅ ይጠበቅበታል።

5) የአማራ ክልል መንግስት ጥርት ያለ አቋም መያዝ አለበት:_

የአማራ ክልል ባለስልጣናት በየሚዲያው ስለ ፋኖ መልካም ነገር ሲናገሩ ተደምጠዋል። ይህ ግን በተግባር መታየት አለበት። ሲጨንቃቸው የጠሩት ፋኖን ነው። የቀበሌና ወዘተ አመራር ሲሸሽ ፋኖ ሲፋለም ከርሟል። ስለሆነም ፋኖ ላይ የሚደረጉ ያልተገቡ ጉዳዮች ላይ አቋም መያዝ አለበት። ችግር ካለ ራሱ በምክክር፣ በመነጋገር መፍታት ይችላል። ሕግ አስከብሩ ሲባሉ ፋኖን ማመጣጠኛ የሚያደርጉ አካላት ጋር በሚኖረው ግንኙነት የአማራ ክልል መንግስት የሚቀርበውን መምረጥ አለበት። የሚቀርበው ፋኖ ነው።

6) መንግስት የሕዝብን ስሜት ማወቅ አለበት በራያና በወልዲያ ፋኖን አትንኩት ያለው ሰራዊቱ ጥሎት ሄዶ ፋኖዎች የደረሱለት የተጠቃ ሕዝብ ነው።

ጌታቸው ሽፈራው

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share