እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በፍርድ ቤት ረታች

በጋዜጣው ሪፖርተር

ታሪክዊቷ እንጦጦ ማርያም ቤ/ክ (አዲስ አበባ)

ርዕሰ አድባራት የመንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን በይዞታዋ ስር የሚገኘውን የባሕር ዛፍ በሕገ ወጥ መንገድ ጨረታ በማውጣት ለመሸጥ ሲንቀሳቀስ የነበረውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ላይ የመሰረተችውን የሁከት ይወገድልኝ ክስ ረታች።
ቤተክርስቲያኗ በጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም በመሰረተችው ክስ ላይ እንደሰፈረው፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ወደ ቤተክርስቲያኗ ይዞታ በመግባት ዛፎችን ቆርጦ ለመሸጥ ጨረታ ያወጣ በመሆኑ እና ዛፎቹም የቤተክርስቲያኗ ንብረት ናቸው ብንልም ሊቀበሉ ባለመቻላቸው፤ እንዲሁም በጥር 12 ቀን 2003 ዓ.ም ሁከት የፈጠሩባቸው መሆኑን በመጥቀስ ዛፍ እንዳይቆረጥ በሕግ ይወገድልን በማለት ለልደታ ምድብ 7ኛ ፍትሐብሔር ችሎት ክስ መስርታ ነበር።
ተከሳሽ በበኩሉ በ14/06/2003 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ ከሳሽ በዛፎቹ ላይ መብት የለውም። ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ የተከሳሽ ሀብት ሆኗል። አሁን ከሳሽ ይዞታ ነው ያለው ቦታ እና ዛፍ ከ1988 ዓ.ም በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን፤ ከመጋቢት 4 ቀን 1988 ዓ.ም ጀምሮ የተከሳሽ ሆኗል። ከመስተዳደሩ በመረከብ ያሉትን ዛፎች በጨረታ በመሸጥ በአገር በቀል ዛፎች በመተካት ወደ ብሔራዊ ፓርክነት የመለወጥ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። ሕጋዊነትን በተላበሰ መልኩ ያወጣነው ጨረታ በመሆኑ የሚደናቀፍበት ምክንያት የለም፤ ቤተክርስትያኗ ምንም መብት ሳይኖራት ባለመብት በመምሰል ያቀረበችው ክስ በመሆኑ ልንከሰስ አይገባም በማለት መከላከያ ቀርቦ ነበር።
ጣልቃ የገባውም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ፤ በ26/12/03 ዓ.ም ባቀረበው አቤቱታ ከሣሽ መብት የለውም ጉዳዩን ማየት የሚችለው የከተማው ፍርድ ቤት ነው። በተሠጠኝ ካርታ መሠረት ዛፎችን ለመቁረጥ ጨረታ ማውጣቱ ተገቢ ነው። በይዞታው ያለው ዛፍ ለመቆረጥ ጨረታ ማውጣቱ ሁከት አይደለም። የከሳሽ ይዞታ ስላልሆነ ሁከት የለም በማለት መልስ ሰጥቷል።
የከሳሽና የተከሳሽን ክርክር ማስረጃ በማስቀረብ የተመለከተው የልደታው ፍርድ ቤት በሰጠው ብይን ላይ እንደሰፈረው፤ ጣልቃ ገብም ሆኑ ተከሳሽ እንዲሁ በወረቀት ላይ የሠፈረ ካርታ ይዘው የከሳሽ ይዞታ ራሱ ተጠቃሎ ባለበት ሁኔታ ዛፍ እንቆርጣለን በሚል ጨረታ ማውጣታቸውን ተገቢ ነው መባሉ የሚያደርጉት ነገር ኃላፊነት የጎደለው በመሆኑ ያቀረቡት መቃወሚያም ሆነ ክርክር በማይታበል ሁኔታ ለመብታቸው የሚናገርላቸው ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በቁጥር 184150 መዝገብ በሰጠው የፍርድ ውሣኔ መሠረት፤ 1ኛ. ተከሳሽም ሆነ ጣልቃ ገቡ በያዙት ካርታ ብቻ ተመርተው የከሳሽ ይዞታ በሆነው በተከሳሽ በአግባቡ ተለይቶ ባልተሰጠው ይዞታ ላይ ያለውን ዛፍ በመቁረጥ ያወጣውን ጨረታ እንዲቆም እና በጥር 12 ቀን 2003 ዓ.ም ያደረገውን ይህንኑ ሁከት እንዲያስወግድ ታዟል። 2ኛ. ተከሳሽ በራሱ ይዞታ ለመጠቀም ከፈለገ በመጀመሪያ በካርታው መሠረት የራሱን ይዞታ በመሬት ላይ በማስፈር የወሰን ድንጋይ እንዲለይ ታዟል። 3ኛ. ከሳሹ ወጪና ኪሳራውን ማቅረብ ይችላል።
ይህን የልደታ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመቃወም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 118925 ሰኔ ቀን 2004 ዓ.ም አቤት ቢልም፤ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሐምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በሰጠው ብይን የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ የሚነቅፍበት ምክንያት ስለሌለ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 337 መሰረት ተዘግቷል ሲል መዝገቡ ወደ መዝገብ ቤት እንዲመለስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በመቀጠልም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር በጣምራ ለሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 83743 የካቲት 25 ቀን 2005 ዓ.ም አቤቱታ አቅርበዋል። ሰበር ችሎትም በሰጠው ውሳኔ፤ የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 184150 መጋቢት 13 ቀን 2004 ዓ.ም ተሰጥቶ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁጥር 118925 ሰኔ 05 ቀን 2004 ዓ.ም የፀናው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 348 (1) መሰረት ፀንቷል ብሏል። እንዲሁም የአመልካች የሰበር አቤቱታ የመሰረታዊ ሕግ ስህተት መመዘኛን የሚያሟላ ባለመሆኑ ተቀባይነት የለውም ብለናል ሲል መዝገቡን ዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት መልሶታል።
ርዕሰ አድባራት የመንበረ ፀሐይ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያ የተመሰረተችው 135 ዓመታት በፊት ነው። ኅብረተሰቡን በማስተባበር እስከ አሁን ድረስ አካባቢዋን በባሕር ዛፍ በመሸፈን የአካባቢውን የአየር ንብረት በመጠበቅ ላይ ትገኛለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰማያዊ ፓርቲ ላይ የተወሰደውን ህገ-ወጥ ርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን!!! ከአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ (አንድት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

 

ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ የረቡዕ ኤፕሪል 3 ዕትም

1 Comment

Comments are closed.

Share