April 3, 2013
9 mins read

መኢአድ ከቤኒሻንጉል ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ጉዳይ ለአለም ፍርድ ቤት ሊያቀርብ ነው

*ሁለት ነፍስጡር ተፈናቃዮች መኪና ላይ ወልደዋል
በመስከረም አያሌው

በቤኒሻንጉል ክልል የሚኖሩ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ያፈናቀለውን አካል ጉዳይ ለአለም ፍርድ ቤት ለማቅረብ ማቀዱን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አስታወቀ።
የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ወንድማገኘኝ ደነቀ እንደገለፁት በቤኒሻንጉል ክልል የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው ብቻ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈፀመባቸው በመሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ ክስ ለመመስረት ታስቧል። ባለፈው ሳምንት ከቤኒሻንጉል ቡለን ወረዳ ብቻ 5ሺ 530 የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወደ ባህርዳር፣ ጐንደር፣ ደጀን እና ቻግኒ እንደተሰደዱ የገለፁት አቶ ወንድማገኝ፤ ከትናንት በስትያም ከከማሼ ዞን ያርሶ ወረዳ 2ሺ 500 ተጨማሪ ሰዎች ተሰደው ፍኖተሰላም ሰፍረዋል ብለዋል። እነዚህ የአማርኛ ቋንቋ በመናገራቸው ብቻ ከ30 አመት በላይ ከኖሩበት አካባቢያቸው እንዲሰደዱ የተደረጉ ሰዎችም ከሆቴል ባለቤት እስከ የቀን ሰራተኛ የሚደርሱ መሆናቸው ተገልጿል። በተለይ በከማሼ ዞን እነዚህ ሰዎች የኖሩበት ነባር አካባቢያቸው መሆኑን እና አንዳንዶቹም አማራ ብቻ ሳይሆኑ ቅልቅል መሆናቸው ተገልጿል።
በተለይ ከትናንት በስትያ ወደ ፍኖተ ሰላም እንዲሰደዱ ከተደረጉት ሰዎች መካከል ሁለት ነፍሰጡሮች መኪና ላይ መውለዳቸውንም አቶ ወንድማገኝ ገልፀዋል። እነዚህ ሰዎች ኃላፊነት በጐደለው ሁኔታ በአንድ መኪና እየታጨቁ እና እየተደበደቡ ወደነዚህ አካባቢዎች በመጓዝ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ለረጅም አመት የኖሩበትን ቀዬ እና ሀብት ንብረት ትተው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰደዱ የተደረጉት እነዚህ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ለተለያዩ ችግሮች እየተዳረጉ ከመሆናቸውም በላይ ህፃናት እና ታዳጊዎች ለጐዳና ህይወት እየተዳረጉ መሆናቸው ተገልጿል።
በየጊዜው በዜጐች ላይ እየተከሰተ ያለውን ከቀዬ የማፈናቀል ሂደት ለማስቆም የፓርቲው አመራሮች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል። የውይይቱ ዋና አላማ እነዚህ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጐች አስቸኳይ እርዳታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነበር። ለተፈናቃዮቹ ከተለያዩ አካላት ገንዘብ የማሰባሰብ እና የተሰበሰበውን ገንዘብም በአግባቡ አገልግሎት ላይ ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪም በእነዚህ ሰዎች ላይ በቋንቋቸው ምክንያት ብቻ እየተወሰደባቸው ያለው እርምጃ የዘር ማጥፋት እርምጃ በመሆኑ በአለም አቀፍ ህግ ለመጠየቅ የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
‘‘አንድን ሰው በቋንቋ፣ በእምነቱ ወይም በሌላ ብቻ መግደል፣ ማሰር፣ ማሰቃየት፣ ማፈናቀል ዘር ማጥፋት ነው። በቻርተሩ የተቀመጠ ነገር ነው። እነዚህ ሰዎች የራሳቸው መረጃ ስላላቸው የህግ አማካሪዎችም ያሉን ይሄንኑ ነው። ስለዚህ ጉዳዩን ወደ አለም ፍርድ ቤት ለመውሰድ አስበናል’’ ያሉት አቶ ወንድማገኝ፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን እንዲቃወሙ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ‘‘የቀረው ነገር ቢኖር እንደ ሒትለር በሞተር መፍጨት ብቻ ነው’’ የሚሉት አቶ ወንድማገኝ ያ ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል።
እነዚህ ከቦታቸው የተፈናቀሉ ዜጐች ህይወታቸው መቀጠል ስላለበት እና ህፃናት የምግብ፣ የጤና እና የመጠለያ አገልግሎት ማግኘት ስላለባቸው የመላው ኢትዮጵያዊያን ርብርብ እንደሚያስፈልግ ነው የተገለፀው። ተፈናቃዮቹ ያረፉባቸው አካባቢዎችም የምግብ አቅርቦቱ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በዚሁ ጉዳይ በተመሳሳይ የተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል። አንድነት በመግለጫው ‘‘የከዚህ በፊቱን የማፈናቀል ግፍ ትተን በቅርቡ እንኳ በጉረፈርዳና በሌሎች አካባቢዎች በቀጥታ በክልሉ ባለስልጣናት በተፃፈ ደብዳቤ ይሄ ሀገራችሁ አይደለም ተብለው፣ ሃብትና ንብረታቸው ተዘርፎ፣ የወለዱ አራሶች እንኳን የማገገሚያ ጊዜ ሳይሰጣቸው ደማቸውን እያዘሩ ሲባረሩ ከመንግስት የተሰጠው ምላሽ ‘‘ሞፈር ዘመቶች ናቸው (ማረሻውን ብቻ ተሸክሞ ወደ ሌላ ሀገር የሚሰደድ ለማለት ይመስለናል)’’ የሚል ነበር። ይሄም ቢሆን የማንኛውም ዜጋ መብት ነው። መንግስት እነዚህ ዜጎች ‘‘ሃገራችን የት ነው?’’ በማለት ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ የለውም።
ገዥው ፓርቲ ሃላፊነትን መዘንጋትንና ስህተትን በማረም ፈንታ አፋፍሞ በመቀጠል ዜጎች ሃብትና ንብረታቸው እየተዘረፈ መባረራቸውን ቀጥለዋል። ይህም በጋምቤላና ቤኒሻንጉል በከፋ መልኩ ቀጥሏል። በተለይ ከቤኒሻንጉል ክልል የአማራ ተወላጅ የሆኑትን ዜጐች የዘመናችን ሹመኞች ከኢ-ሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ ለእቃ ከሚሰጥ ክብር ባነሰ ሁኔታ ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ በጅምላ እየተጫኑ መጣላቸውን ቀጥለዋል። በርካታ ህፃናትም የዚህ ግፍ ሰለባ ሆነዋል፤ እየታፈኑ የሚሞቱትም ቁጥራቸው በርካታ ነው፤ በጣም የሚያሳቅቀው ደግሞ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት 59 ሰዎች ሞት ጉዳይ ነው። ካላግባብ በጭካኔ ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት፣ ከወለዱበትና ከከበዱበት ስፍራ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በአንድ መኪና እየታጨቁ እንዲወጡ በማድረግ ገደል ውስጥ ገብተው እንዲሞቱ የተፈረደባቸው ዜጎችን ህይወት እንዲቀጠፍ ያደረገውም በቸልታ እየገዛ ያለው የኢአዴግ መንግስት ነው። መንግስት በነዚህ ዜጎች ላይ ለደረሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ህይወት ማጣት ተጠያቂ ነው በማለት ፓርቲያችን ያምናል’’ ሲል በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

 

ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ ኤፕሪል 3 ዕትም

Latest from Blog

የኦህዴድ መራሹ ብልፅግና  መንግስት  በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በንጹሀን  ዜጎች ላይ እየወሰዳቸው ያሉ የነፃ እርምጃ  ግድያዎች  መንግስት ያሰበውን የፖለቲካ ግብ ያሳካለታል  ወይ ? በኔ አመለካከት እነዚህ የንፁሃን ዜጎች  የጅምላ ግድያዎች  በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላዎ (double edge sword) ናቸው:: ፩- መንግስት እያሰላው

 የኦህዴድ መራሹ ጅምላ ግድያዎች ስሌት (ሸንቁጥ- ከምዕራብ ካናዳ)

January 24, 2025
እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

Go toTop