ፍኖተ ነፃነት
መምህርትና ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የወህኒ ቤቱን አስተዳደርና ጥበቃዎች ትንቅያለሽ የሚል ክስ እብደቀረበባት ቤተሰቦቿ ለፍኖተ ነፃነት አስታወቁ፡፡ የወህኒ ቤቱ ምንጮቻችን ቃል መስጠቷን አረጋግጠዋል፡፡ ጋዜጠኛ ርዕዮት የተከሰሰችበት አንቀፅ በቤተሰብና ወዳጅ እንዳይጠይቃትና ለብቻዋ እንድትታሰር የሚያስደርግ ነው፡፡
ርዕዮት አለሙ ላይ የቀረበው ክስ ሆነተብሎ የህሊና እስረኛዋን ለማንገላታት እንደሆነ የሚጠቅሱት የፍኖተ ነፃነት የወህኒቤት ምንጮች “ርዕዮት ህክምና ከመከልከል አንስቶ ከቤተሰቦቿ የሚላክላትን ምግብ እንዳታገኝ ለመከልከል ተዘጋጅተዋል” ብለዋል፡፡
የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እህት ወ/ት እስከዳር አለሙ ለጋዜጣችን እንዳስረዳችው በቃሊቲ እስር ቤት የሚገኙትን የአስተዳደር እና የጥበቃ ሰራተኞች ትንቂያለሽ፣ትሰደቢያለሽ እንዲሁም “የምትሰሩትን በሚዲያ እና ድረ ገፆች አጋልጣለሁ” ብለሽ ትዝቺያለሽ በሚል ክስ ቀርቦባት መጋቢት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ቃሏን ሰጥታለች፡፡ ወ/ት እስከዳር አክላም “ርዕዮት ላይ የቀረበባት ክስ በፌደራል ታራሚዎች አያያዝ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999 አንቀፅ 36 መ እና ሠ በመሆኑ እህቴን ጥፋተኛ ነሽ ካሉዋት ከአንድ ወር ላላነሰና ከአራት ወር ላልበለጠ ጊዜ በጎብኚዎቿ እንዳት ትደረጋለች” ስትል ስጋቷን ለፍኖተ ነፃነት ገልፃለች፡፡
በጋዜጠኛዋ ላይ የቀረበውን ክስ አስመልክቶ አስተያየት የሰጡን የወህኒ ቤቱ ምንጮቻችን፣ “ክሱ የርዕዮት ያለጥፋቴ ይቅርታ አልጠይቅም በማለቷ እልህ ውስጥ የገባው የኢህአዴግ መንግስት የበቀል እርምጃ ውጤት ነው” ካሉ በኋላ “ርዕዮት አመክሮ እንዳታገኝ ታስቦ የቀረበ ክስ ነው” በማለት አጋልጠዋል፡፡
ፍኖተ ነፃነት የአንድነት አመራር የሆኑት አቶ ናትናኤል መኮንንም ለአንድ ወር ከቤተሰብ እንዳይገናኑ መደረጋቸውንና የወህኒ ቤቱን ውሳኔ ተቃውመው ከሳምንት በላይ በርሀብ አድማ ላይ መሆናቸውን መዘገቧ አይዘነጋም፡፡
ምንጭ፡ ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ