አባ መላ እና መላ ያጣው ንግግራቸው (በዳጉ ኢትዮጵያ)

አቶ ብርሃኑ ዳምጤ (አባ መላ) በቅርቡ ስላደረጉት የአቋም ለውጥ ለቢንያም ከበደ (ቤን) የሰጡትን ቃለ መጠይቅ አነበብኩት፡፡ ላልተጠበቀው የ180 ዲግሪ የአቋም ለውጥ በመንስኤነት ከጥቅመኛ ፖለቲከኝነት እስከ የጠበቁትን አለማግኘት በርካታ ምክንያቶች እየተጠቀሱ በብዙዎች ትንታኔ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡ እኔ በዚህ ረገድ ምንም ለማለት አልፈልግም፡፡ ይልቁንስ በቃለ ምልልሳቸው ኢሳትን በተመለከተ በሰነዘሯቸው አንዳንድ የተሳሳቱ ነጥቦች ላይ ጥቂት ብል እመርጣለሁ፡፡ የትኩረት ነጥቦቼን በተናጠል ተራ በተራ እዘረዝራለሁ፡፡

“ምንም አይነት የዜና ምንጭ የሌላቸው”
አቶ ብርሃኑ ስለኢሳት ከተናገሯቸው ነጥቦች የመጀመሪያው “ኢሳት ምንም አይነት የዜና ምንጭ የለውም” የሚል ነው፡፡ እውነት ለመናገር ራሳቸው አቶ ብርሃኑም በዚህ ንግግራቸው የሚያምኑበት ከሆነ አስቂኝ ነው፡፡ እንዴ አቶ ብርሐኑ፡- መቼም የጠቅላይ ሚኒስትርዎትን ሞት ቀድመው የሰሙት ከኢቲቪ አልያም ከፋና አይደለም፡፡ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምነውን አስፀያፊ ንግግር ከዝግ የካድሬዎች ስብሰባ ላይ ቀድቶ አየር ላይ ያዋለው የሰሞኑን ወዳጅዎ (መቼም እርስዎ በዚህ ተለዋዋጭ አቋምዎ ዘላቂ ወዳጅ አይኖርዎትም ብዬ ነው) አቶ ቢንያም አይመስለኝም፡፡ ኸረ ስንቱ ስንቱ… ከጉራ ፋርዳ የአማራ ተወላጆች መፈናቀል እስከ የኦህዴድ ውስጣዊ ህንፍሽፍሽ… ኢሳት ይህን ሁሉ ከህዝብ ተደብቆ የነበረ መረጃ አደባባይ ያወጣው ያለአንዳች የመረጃ ምንጭ ነው ካሉን በአመክኒዮ ሳይሆን በስሜት እንደሚነዱ በራስዎ ላይ እየመሰከሩ ነው፡፡
“የዜና ምንጫቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው”
ይህ ነጥብ ደግሞ አስቂኝነቱ ያመዝናል፡፡ ኢሳት የኢቲቪን ዜና “ትዊስት እያደረገ የመጀመሪያውን መጨረሻ የመጨረሻውን መጀመሪያ” አድርጎ የሚያቀርብ ከሆነ አራተኛው የኢቲቪ ቻናል ሆነ ማለት ነው፡፡ የኢቲቪን ዜና ዳግም የሚያሰራጭ (Rebroadcast) ጣቢያ ከሆነ ደግሞ እኔን ጨምሮ በሚሊዮን የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን አማራጭ የመረጃ ምንጭ ባላደረግነው ነበር፡፡ ለምን ቢሉ ኢቲቪን ዲሽ መትከል ሳያስፈልገን፤ አንዱ የስርጭት ሞገድ ሲዘጋ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠር ብር ከእለት ጉርሳችን ነጥቀን ለዲሽ አስተካካዮች ሳንከፍል መከታተል እንችላለን፡፡ እውነቱን ለመናገር የኢሳት የተሰሚነት ሚስጥር እርስዎ ከተናገሩት ተቃራኒው ነው፡፡ ከአሰልቺውና ከእውነት ከተጣላው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፕሮፖጋንዳ የሚያስጥል አማራጭ አድርጎ ኢሳት ራሱን ማቅረቡ ነው የተሰሚነቱ ምክንያት፡፡ እስኪ ለዛሬ ለእውነት ታማኝ ለመሆን ይሞክሩና የኢቲቪንና የኢሳትን የዜና ፕሮግራሞች ይከታተሉ፡፡ ኢቲቪ የሐረር የውኃ ችግር እንደተቃለለ “አንዳንድ ነዋሪዎችን” እማኝ አድርጎ ሲዘግብልዎት ኢሳት ግን በህዝቡ አዕምሮ ውስጥ የሚብሰለሰለውን የሐረር የግንብ መደዳ ሱቆች ቃጠሎ ክስተት ተጎጂዎቹን እያነጋገረ ያስደምጥዎታል፡፡ እርስዎ በሐረር ከተማ ቢኖሩ አሊያም በከተማው ውስጥ የሚኖር አንዳች የቅርብ ዘመድ ካለዎት የኢቲቪን “ሐረር ሠላም ነው ምንም አልተፈጠረም” የዘወርዋራ ፕሮፖጋንዳ ለመስማት የሚያስችልዎት አንዳች ፍላጎት ይኖርዎ ይሆን?
“ተአማኝነት የሌለው”
በቅርቡ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የአቶ አለምነውን ስድብ-አዘል ንግግርና የፓርቲያቸውን የዝምታ ስምምነት በመቃወም በባህር ዳር ከተማ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳተፉበት ደማቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዶ ነበር፡፡ ሠልፈኞቹ ለተቃውሞ የወጡበትን የአቶ አለምነውን ንግግር የሰሙት በሌላ በማንም ሚዲያ ሳይሆን በኢሳት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ500 ኪ.ሜ ርቀት የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በኢሳት የሰሙትን መረጃ አምነው ለተቃውሞ የባህር ዳር ከተማን ጎዳናዎች አጥለቅልቀዋል፡፡ ተአማኝነት ማለት እንግዲህ ከዚህ በላይ ምን ማለት ይሆን?
“ኢሳት ከግንቦት ሰባት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን አያስተናግድም”
አቶ ብርሐኑና እኔ የምንሰማው ሁለት የተለያዩ ኢሳቶችን ካልሆነ በቀር በየእለቱ የኢሳት ፕሮግራሞች የአንድነት፣ የሠማያዊ፣ የአረና ወዘተ እንቅስቃሴዎችና መግለጫዎች ሰፊ ሽፋን የሚያገኙት በኢሳት ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የባህር ዳር የአንድነት ፓርቲና የመኢአድ የተቃውሞ ሠልፍ የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኘው በኢሳት ነበር፡፡ ኢቲቪማ በሠልፉ ተደናግጦ ስለሰልፉ አንዳች ቃል ሳይተነፍስ ይልቁንስ “መድረክ አንድነትን ከአባልነት ማገዱን” እያጋነነ ሲዘግብልን ነበር፡፡ “ተቃዋሚዎች ተከፋፈሉ” ነው መልዕክቱ፡፡ ሁለት ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች (አንድነት ፓርቲና መኢአድ) በትብብር መሬት-አርዕድ የተቃውሞ ሠልፍ ማድረጋቸው ሳይሆን አንድ ፓርቲ ለጊዜው ከመድረክ መታገዱ ለገዢው ፓርቲ የሚጠቅም ዜና ስለሆነ ሽፋን ያገኛል- በኢቲቪ መስፈርት፡፡
“በኢሳት ከግንቦት ሰባት ውጪ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሽፋን አያገኙም” ለሚለው የአቶ ብርሐኑ አስተያየት ራሱ ገዢው ፓርቲ ከሳምንታት በፊት በሐገር ውስጥ በህጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች መሪዎች በኢሳት መግለጨ መስጠታቸው ህገወጥ ነው ሲል መክሰሱና አንድነትና ሠማያዊ ፓርቲም “ይህን ማድረግ መብታችን ነው” ሲሉ በጽኑ መቃወማቸው ጉልህ ማስተባበያ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ግንቦት ሰባት “ከኤርትራ በማገኘው ድጋፍም ጭምር ተጠቅሜ የአገዛዝ ስርዓቱን አወርዳለሁ” ሲል በሰጠው መግለጫ ላይ ጊዚያዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ተቃውሞ ማሰማቱን ከዋና ፀሐፊው አንደበት የሰማነው በዚሁ በኢሳት እንደነበት አቶ ብርሐኑ አይዘነጉትም ብዬ አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ የያዙትን የፖለቲካ አቋም በማናቸውም ምክንያት ትቶ የአቋም ለውጥ ማድረግ ሊከበርለት የሚገባ የማንም ሰው መብት ነው፡፡ ነገር ግን አዲስ የተቀላቀሉት ካምፕን ደስ ለማሰኝትና ድርጎ ቢጤም ለማግኘት በማሰብ የባሰ ትዝብት ላይ የሚጥል ንግግር መናገሩ ፋይዳው ብዙም አይታየኝም፡፡ አገዛዙ እንደሆነ ደጋፊህ ነኝ ብሎ ለሚመጣለት (በተለይም ከተቃዋሚው ጎራ) ከህዝብ አንጡራ ሐብት ላይ ዘግኖ ላለመስጠት የሚያስችል አንጀት እንደሌለው የታወቀ ነውና አቶ ብርሐኑም ያሰቡትን ለማግኘት ብዙ መቀባጠር የሚኖርብዎት አይመስለኝም፡፡ አበቃሁ!

7 Comments

 1. dagu (aka fasile yenealem):

  Why do you dwell on the fringe issues rather than tackle the most fundamental accusation he has made: which is ESAT does not have financial and political independence. It is financed and guided by foreign agenda namely Egyptian and its proxy shabiya?

 2. Unstable personality,flactuating mood, fight &flight of ideas, denial and a pathological lie and dropped eye lids of him tells me a psychiatric disorder and he better visit clinical psychologist or psychiatrist. Shame Tota -ABA-mela /’

 3. I don’t understand why all these fuss about aba bela. By the way, aba mela refers to the great patriotic Ethiopian HabteGiworgis Denegde not opportunistic parasites like aba bela. I want to congratulate the opposition Diaspora that the tumor is removed. Now it is up to the woayne camp now to keep an eye on him. Because everyone realizes that this dude can flip flop better than the Olympic gymnasts and available for sell for the highest bidder. Regarding ESAT, I do not believe that interviewing him is a mistake. ESAT interviewed him as a defector but never offered him a job that he was hoping for. We can use his own words and interviews to bash, trash, name and shame himself and as well as the regime. I am just wondering how he will blend the system he used to call racist and corrupt as well as in his own words, “fogariw” Meles and the “prostitute” Azeb camp…..kkkkk…..woayne camp, enjoy aba bela….hahahaha

 4. kkkk ABA MELA was praising ESAT in his interview with SISAY AGENA three months ago and this ABA MELA guy is the greatest traitor this country has ever seen he changes his side like his shirt kkkkk now nobody will believe him he is like a HORSE ABA MELA actually the HORSE of menilik ABA mela had one owner but this STUPID GUY has no one master he is simply KEHADI too bad WOYANES will never trust him again ABA MELA is good only for one thing SIM MATFAT he must have grown at SEBATEGNA he talks like A prostitute

 5. Setyowa ena Bergude PM tebiyewun titew ahunim eyasweredu new. Belew ke 8 a met befit be Aligarh yamenezerchiw endayibekat. Wet Romina!

 6. በጣም ገረመኝ፡፡ ከገረሙኝ ነገሮች አንዱና ዋናው የጊዜ ርዝማኔው ነው፡፡ መገልበጡን መጠበቅም ከነበረብኝ ልጠብቀው ከምችለው እጅግ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ነው የተገለበጠው – የተዋጣለት አክሮባትና የአእምሮ ህመምተኛ መሆኑን አስመስክሯል፤ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ላይ አስመዝግቡት – እንደዚህ ያለ ፈጣን ተለዋዋጭ መኖሩን ሰምቼ አላውቅም፡፡ የለውጡ ዓይነት ደግሞ ከጨለማ ወደ ብርሃን ዓይነት subliminal ነው፡፡ የሰው ልጅ በባህርይው እንዲህም ነው፡፡ የርሱ ባሰ እንጂ፡፡ ሲናገር እኮ ያፈዛል፡፡ ለነገሩ “ሰይጣንም ለተንኮሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” ይባላልና ሰውዬው የሚያደርገው ሁሉ ለእኛ ለሞኞች እንጂ ለርሱ መደበኛና ጤናማ ነው፡፡
  አንድ ግብረሶዶማዊ ወይም ሌዝቢያን ወይም ሌባና አጭበርባሪ ድርጊታቸው ለነሱ ለራሳቸው በጣም “ጤናማ” ነው፡፡ ጤናማ የማይሆነው እነዚህ ነገሮች ለማያደርጉ ሰዎች ነው፡፡ በሥነ ልቦና ትምህርት እነዚህ ሰዎች በሽተኞች ናቸው፡፡ በሽተኞች ተደማጭነትና ከበሬታን ካገኙ ግን ችግር ነው፡፡ አንደኛ አድማጩና አክባሪው በቅድሚያ ይጎዳሉ፡፡ አንድ ሰው ነበር – በእግዚአብሔር አያምንም አሉ፡፡ እሱ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በእግዚአብሔር እንዲያምኑ የሚያደርግ የአነጋገር ለዛና ተሰጥዖ ነበረው፡፡ ዳምጤም መርዝ በተደበቀበት በማር የተለወሰ አንደበቱ አነሆለለንና “ሰው አገኘን” አልን፡፡ ግን ግን ድመት መንኩሳ ዐመሏን እንደማትረሳ ይህ በሽተኛ ሰውዬ የዋሆችን ጉድ ሠርቶ ወደካምፑ ተመልሷል ማለት ነው፡፡ በበኩሌ “ ይህ ክስተት መማሪያ ይሆነናል” ማለቱ ጅልነት ይመስለኛል፡፡ እስከመቼ እየተጃጃልን እንኖራለን፤ እስከመቼስ የአጭበርባሪዎች መናኸሪያ እንደሆን እንቀራለን፡፡ ይህን ሰው ጅባት ብሎ መተውና ወደፊት መቀጠል ነው፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው፡፡ እንዲህ ያሉ እስስቶችና አጋሰስ ጌኛዎች መኖራቸውን ማወቁ በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትምህርት ይሆናል ከሚል ሞኝነት ማንንም አፈጮሌ እያስጠጉ ጓዳ ጎድጓዳን ማስቧጠጥ ደግ አይደለምና ለወደፊቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ መጣጥፌ የአባ መላ ነፍስ መግዛት ጥሩ መሆኑን ጠቅሼ ነገር ግን ለተንኮል አለመሆኑ ይጤንበት ማለቴን አስታውሳለሁ፡፡ ለውጥ አለ፡፡ ነገር ግን የለውጥን እውነተኝነት መመርመር ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ሰውን ማመን ቀብሮ ነው እንዳለችው እመት ቀበሮ በውብ ቋንቋ እየከሸነ የሚናገርን አሰለጥ ሁሉ እንዳለ ተቀብለን ከፈዘዝን ኤድስ የያዘው ቆንጆ ሰው አነሁልሎ ቢተኛን የምንሆነውን መሆን ለመሆን መስማማት ነው፡፡ የዚህ ሰው በሽታ ሆድና በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ስመጥርነትን ማግኘት ነው፡፡ በሰይጣን ቤትም ይሁን በእግዚአብሔር ቤት ዋናው ሹመቱን ያግኝ እንጂ ስለምክንያታዊነቱ ሃሳብ አይገባውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው የራሱ የሆነ አእምሮ የለውም – ማሕጸን እንደሚያከራዩት ዓይነት ድሆች የፈረንጅ ሀገር ሴቶች እርሱም ብልጣብልጥ አንደበቱንና ቀፎ ጭንቅላቱን በገንዘብ እያከራዬ መኖር ነው ሥራው፡፡ እንደተባለው ልጁንም ሸጦ ቢሆን ገንዘብ ከማግኘት ወይም በዝና ማማ ላይ ፊጥ ከማለት አይመለስም፡፡ የሰውን ባሕርይ አንዴ ማወቅ ነው፤ ከዚያ መጠንቀቅ፡፡ ከዚህ በኋላ ስለርሱ መነታረክ በፈሰሰ ውሃ መጨቃጨቅ ነው፡፡ ይልቁንስ ገና ያላወቅናቸው ብዙ በሽተኞችና እስስቶች አሉ፡፡

 7. ለዚህ ህሊና ቢስ እርካሽ ሰውዬ ሽፋን አትስጡት ለራሱ ክብር የማይሰጥ ደደብ ደግሞ አባ መላ ድንቄም

Comments are closed.

Previous Story

የብርሃኑ ዳምጤ (አባመላ) ቅልቅል (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ

Addis Ababa
Next Story

ትዝብት – ደርሶ መልስ ዲያስፖራ (ኢትዮጵያ ደርሶ የመጣ ዲያስፖራ የሚነግራችሁ እውነት) (አንደኛ)

Go toTop