የብርሃኑ ዳምጤ (አባመላ) ቅልቅል (ከክንፉ አሰፋ) ጋዜጠኛ

ብርሃኑ ዳምጤ እንደገና ሲገለበጥ የአስር አመት ልጅ ሳለሁ ያጋጠመኝን አንድ ክስተት አስታወሰኝ። በሰፈራችን ውስጥ ልጆችን ሁሉ የሚጠሉ አንድ ሰውየ ነበሩ። አንድ ቀን በድንገት ተነሱና የሰፈሩን ሰው ሁሉ መሰናበት ጀመሩ። በእጃቸው 3 ሜትር የሚያህል ርዝመት ያለው ገመድ ይዘዋል። “የሰፈሩ ልጆች ስላስቸገሩኝ ራሴን ልስቅል ነው። ደህና ሁኑ…” እያሉ ሁሉንም ተሰናብተው ሲያበቁ ለመሰቀል መንገዳቸውን ጀመሩ። የእኝህ ሰው ውሳኔ ለመንደሩ ሰው ሁሉ ደንታ አልሰጠውም።

የሰፈር ልጆች ግን ተከተልናቸው። ብዙ ነበርን። ሰውየው ተራራ ሲወጡ አብረን ወጣን። ቁልቁል ሲወርዱም አብረን ወረድን። ጉዞው አሰልቺ ነበር። ግን ተስፋ ሳንቆርጥ ጉዱን ለማየት ስንል ተከተልናቸው። በመጨረሻ አንድ ዛፍ አገኙና የሚሰቀሉበትን ገመድ እዛፉ ላይ ማሰር ጀመሩ።

ሰው ሲሞት አይተን ስለማናውቅ ሁኔታውን እንደ ልብ አንጠልጣይ ፊልም ነበር በጉጉት የምንከታተለው። ሰውዬው በዚህ ሁኔታ ለመሞት መወሰናቸው ብዙም አላስደነገጠንም። ይልቁንም ከኛ እየቀሙ በግቢያቸው ያጠራቅሙዋቸው ኳሶቻችን ነጻ ሊወጡልን ነው ብለን ተደስተናል።

ገመዱን አስረው ራሳቸውን ለመሰቀል ካመቻቹ በኋላ ዘውር ብለው እኛን ተመለከቱን። «እባኮን ይተው!» የሚላቸው አንድ እንኳን ሰው አልነበረም። ለደቂቃዎች በአትኩሮት ከተመለከቱን በኋላ እንዲህ አሉ። «እንዲያውም ደስ አይበላችሁ። ሃሳቤን ቀይሬአለሁ። አልሰቀልም!»

ዛፉ ላይ ያሰሩትን ገመድ ፈቱትና ወደ ሰፈር አቀኑ። ካልተሳከው የጎልጎታ መሰውያ ሲመለሱ እመንገድ ላይ ያገኛቸው አንድ ሰው ሲመክራቸው ሰማን። «ሌላ ግዜ መሰቀል ከፈለጉ ለሰው አይናገሩ። ድምጽ አጥፍተው ለብቻዎ ያርጉት። የዚህ ሰፈር ልጆች አብዝተውታል። ሰው በሰላም እንኳን እንዳይሞት እያደረጉ ነው።»

ሰውየው ለመካሪያቸው ምንም ምልስ አልሰጡም- ግን ወደኛ እየተገላመጡ «እርሱት። አታገኙዋትም!» የማለት አይነት በአይናቸው እየዛቱብን እቤታቸው ገቡ።

ከልጅ ጋር የሚጫወቱት እንቁልልጬ መሆኑ ነው። ለዚያማ ማን አክሎን። የባሰ እልህ ውስጥ አስገቡን። … በመጨረሻ ብቻቸውን መንገድ ላይ እያወሩ መሄድ ሲጀምሩ ተውናቸው። …

የሳይበሩ አንበሳ የመታጠፉ ፍጥነት ሳይገርመን የድጋሚ ቅልቅሉን በከአዲስ ዜማ አከለበት። “እንደውም ደስ አይበላችሁ። ወያኔን ተቀላቅያለሁ!” የሚል ዜማ። የልጅነት እንቁልልጬ ጨዋታ ይመስላል። ለመዞርማ ምድርም ብርሃንና ጨለማን ለማፈራረቅ በራስዋ ዛቢያ ላይ ትዞራለች። የኋላውን ለማየት ሲል አንገትም ይዞራል። ብረትም ይዞራል – በእሳት ሲፈተን። … ቆርቆሮ ግን እንዲሁ ይጠመዘዛል።

«..እኔ እንኳን ትንሽ መቆየት ፈልጌ ነበር።» አለ ኦቦ ዳምጤ፤ ለሁለተኛው ዙር ከወያኔ ጋር ያደረገውን ቅልቅል ሲያበስር። ይህችን አነጋገር የተጠቀመባት ያለ ምክንያት አልነበረም። ወደዚህኛው ጎራ የገባው የጥምር ሰላይ (double agent) ስራ ለመስራት እንደሆነ ለማስመሰል መሞከሩ ነበር። ፈረንጆቹ (match fixing) ማች ፊክሲንግ የሚሉት በእግር ኳስ አለም ውስጥ ለተቃራኒው ተገዝቶ የመስራት ውስልትና አይነት መሆኑ ነው። እንዲህ የተራቀቀ ቢሆንማ ኖሮ እናደንቀው ነበር። ግና በዚያው ቃለ-ምልልስ ላጠፋው ጥፋት ይቅርታ ጠይቆ ጨዋታውን አበላሸው። ድንጋይ በትከሻው ባይሸከምም ህሊናውን ዝቅ አድርጎ ከአክራሪ ዲያስፖራ ጋር በመዋሉ በጣም ተሰምቶታት። ወያኔዎች ይቅርታ የሚላቸውን ለምን እንደሚወዱ አይገባኝም። ይቅርታ የሚጠይቋቸውን ሰዎች በጣም ሲወድዱ እንጂ ምህረት ሲያደርጉላቸው ግን አይተን አናውቅም። ታምራት ላይኔን በፓርላማ ካዋረዱት በኋላ ቀፈደዱት። ሰለሞን ተካልኝም ከይቅርታ አልፎ ከዲያስፖራው ርኩስነት ለመጽዳት ሲል አባን ጸበል እርጩኝ ብሎ ነበር – በዘፈን። መቀሌ ድረስ ሄዶ በኢህአዴግ ጸበል ቢጠመቅም፣ እነሱ ግን ቂማቸውን አልረሱም። ሁሉንም ማኖ እያስነኩ በአየር ላይ ያንሳፍፏቸዋል።

አባመላ ከነሱ ጋር ተጣልቶ ወደ ተቃውሞ ጎራ በሄደ ጊዜ ወያኔዎች አንድም ነገር አልተነፈሱም ነበር። ምክንያቱም ጸቡ የመርህ እንዳልነበር ያውቁታል። ጉዳዩ የግል ጥቅም ነው። መፍትሄውም ቀላል። በፈለጉት ግዜ እንደ ቆላ በሬ አሞሌ ጨው አልሰው እንደሚመልሱት አስቀድመው ያውቁታል።

በቃለ-ምልልሱ አባ መላ በካፒቴን ሀይለመድህን አበራ ዙርያ የተነሳውን ክርክር ሊቋቋመው እንዳልቻለ አልካደም። በክርክር ሲሸነፍ እንደመፍትሄ የወሰደው የወያኔን ጎራ መቀላቀል መሆኑም አዲስ ነገር አይደለም። ያኛው ጎራ በሃሳብ የተሸነፉ መሃይማን መሰብሰብያ ጎራ ከሆነ ሰንበትበት ብሏል።

ንግግር መቻል አንድ ነገር ነው። እየቀለዱ ሰውን ማሳቅም ቀላል ሊሆን ይችላል። በመናገር ሰዎችን ማሳመን መቻል ግን ሌላ ጉዳይ ነው። ይህ ጥበብን፣ ብስለትን እና አስተዋይነትን ይጠይቃል። በንግግር ሰዎችን ማሳመን መቻል ደግሞ ሮኬት ሳይንስ መሆንን አይጠይቅም። አንዳንዶች በትምህርት ያገኙታል። ሌሎች በማንበብ ይለወጣሉ። የህይወት ተመክሮም በራሱ ብዙ ነገር ያስተምራል። ከስህተታቸው እየተማሩ የሚበስሉ ሰዎችም ብልሆች ናቸው።

«አቶ መለስ ዜናዊ እድሜ ልካቸውን የአማራን ህዝብ ሲሳደቡ ሰንብተው፤ አንድ አማራ ሲሰድባቸው ግን ደግም ላይመለሱ አሸለቡ።» የሚል ቀልድ ሰምቼ በጣም ነበር የሳቅኩት። ነገሩ ልክ ነው። በሌላው ላይ የሚቀልዱ ሰዎች በራሳቸው ላይ ሲደርስ በቶሎ ይሰበራሉ ይባላል።

እናም በሃይለመድህን ጉዳይ «ከጽንፈኞች» ሳይስማማ በመቅረቱ የጠፋው በግ ወደ ቤቴ ተመለስኩ ነው እያለን ያለው። ይህ ሰው ግን ስንት ጊዜ ነው ከቤቱ የሚጠፋው?

ደግሞ ፍጥነቱ። የብርሃን ጉዞም እንደብርሃኑ ዳምጤ አይፈጥነም። ወደዚያኛው ጎራ ሲቀየስ የለበሰውን የዲያስፖራ ማልያ እንኳ ለመለወጥ ግዜ አልወሰደም። የቡናን ማልያ ለብሶ ለደደቢት የሚጫወት አይነት ሰው ነው የሆነው።

እንደዚህ አይነት ሰዎች ስብእናቸውን የሚሸከም አንገት ስለሌላቸው ወደግራም ሆነ ወደቀኝ፣ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ ለመተጣጠፍ ችግር የለባቸውም። ይህ ሰው ወደ ቀኝ ታጥፎ በነበረበት ግዜ ከአንዴም ሶስቴ ደውሎ በስልክ አናግሮኝ ነበር። አቀራረቡ፣ አነጋገሩና ጨዋታው ያራዳ ልጅ ይመስላል። ተግባሩ ግን የአራዳ ልጅ አይደለም። ያራዳ ልጅ ባልንጀራውን ይረዳዋል እንጂ በቁሙ ሊያርደው አይዳዳም።

ወያኔ የመሆን መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ለመሆን የሄደበት መንገድ ግን በጣም ይደብራል። ድርጊቱ ሰሞኑን በፈረንሳይ ሃገር ከተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ጋር ተመሳሳይ ነው የሆነብኝ። የክህደት ትንሽ የለውም። ልዩነቱ አባ መላ ያስጠጉትን ወገኖች በቁም አለመግደሉ ብቻ ነው።

አንዲት የዋህ ወይዘሮ፤ በፓሪስ ከተማ እመንገድ ላይ ወድቆ የሚለምን ኢትዮጵያዊ ወገን አግኝተው እጅግ አዘኑለት። እቤታቸውም ወስደው ማረፍያ ሰጡት። መሰረታዊ የሆነውን ነገር ሁሉ አሟሉለት። አምነው ያሳደሩት ይህ ሰው ግን ውለታቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ መለሰላቸው። አራት ወር እንደቆየ ይህንን የሶስት ልጆች እናት ከትንሽ ልጃቸው ጋር በሴንጢ አርዶ ተሰወረ። አባመላ አብረውት ሲሰሩ የነበሩትን በቢላ ባያርዳቸውም በአነጋገሩ ስጋቸውን እንደበላው ነው የሚቆጠረው። አምነው አስተጉት ይህ ሰው እንደጴጥሮስ ጎህ ሳይቀድ ካዳቸው። የክህደት ቁልቁለት ይሏል እንዲህ ነው። «የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ!» ይላሉ አበው። ቃልን ማጉደል ምን ያህል ከባድ ነው!

ታማኝ በየነ እና አበበ ገላው ከብርሃኑ ዳምጤ ጋር በሳውዲው ቀውስ አብረው መስራት ሲጀምሩ በፍጹም ቅንነት እና በየዋህነት ነበር። ይህንን በማድረጋቸውም በርካታ ትችት ቀርቦባቸዋል። እነሆ አባ መላ ዛሬ ለቅልቅሉ እጅ መንሻ እነሱን በመሳደብ እንደመስዋዕት አቀረባቸው።

የብርሃኑ ዳምጤ አካሄድ ያሳሰባቸው ሁለት ወዳጆቼ በዚያን ሰሞን በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰል ያለ አስተያየት ጽፈው ነበር። በልጅግ ዓሊ (ከፍራንክፈርት) እና እንግዳሸት ታደሰ (ከኦስሎ)። እነዚህን ጽሁፎች እንደገና እንድታነቧቸው እመክራለሁ። በልጅግ ዓሊ «ዘመንን ለማሰር» በሚለው ጽሁፉ ይህ ሰው እንደ ጴትሮስ ይክደናል ነበር ያለው።
…ለአንዲት የሰሙኑ የፖለቲካ ጥቅም ሲባል ብርሃኑ ደቡርን እላይ የሰቀላችሁት በኋላ እንደለመደው ሲክዳችሁ ስትንጫጩ መስማታችን አይቀርም። ትንቢት እንዳይመስላችሁ ደቡርን በደንብ አድርገን እናቀውቀዋለን። ቆዳችሁን ገፎ ይሸጠዋል፣ ደቡር ሃገሩን አይደለም እናቱንም ቢሆን ይደልላል። አታውቁት እንደሆን መርካቶ ላይ ሄዳችሁ የተሰራውን ግፍ ጠይቁ። እንኳን የቀይ ሽብሩን ፣ እነ ሽብሬን ረስተን የለም እንዴ !! ምን ይደንቃል።
ብሎ ነበር። እንግዳሸት ታደሰ ከኖርዌይ የጻፈውም ተመሳሳይ ነገር ነበር። «አባ መላ ልብ ሲበላ! » በሚለው መጣጥፉ «የዲያስፖራ ኃይል በአራዳ ስልትና በወያኔ ቆረጣ ለመሰንጠቅ ፣ የሚደረግም ጨዋታ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመትም የዋህነት አይመስለኝም።» ነበር ያለው። እነዚህን መጣጥፎች ደግሜ ሳነባቸው ትንቢት ነው የመሰሉኝ። በወቅቱ ግን እነዚህን ጽሁፎች በድረገጽ በማውጣቴ የስድብ ናዳ ወርዶብኝ ነበር። አንዱ የፓልቶክ ታዳሚ እንዲህ ብሎ ነበር የጻፈልኝ። «የማናውቅህ እንዳይመስልህ! አንተ የዳዊት ከበደ ወንድም!»
የትኛው ዳዊት እንደሆነ ግን ግልጽ አላደረገልኝም። የአትላንታው ወይንስ የአውራምባው?

እርግጥ ነው። በፖለቲካ ቋሚ ወዳጅ ወይንም ቋሚ ጠላት የለም – ጥቅም እንጂ። በመርህ ላይ ሳይሆን ይልቁንም ለግል ጥቅም ሲሉ የሚዋዥቁ ሰዎች ናቸው ሀገርን የሚያጠፉት። በተለምዶ መሃል ሰፋሪዎች ይባላሉ። እንደዚህ አይነቶቹ ሰዎች በተቃዋሚውም ጎራ ነፍ ናቸው። ደጋፊ ሳይሆን ተደጋፊ ሆነው ለመኖር ሲሉ ብዙ ጥፋት ይሰራሉ። የሃይል ሚዛኑ እስካዘነበለ ድረስ ለአለቆቻቸው እጅግ ታማኝ ይሆናሉ። የሃይል ሚዛኑ ሲዛባ ደግሞ ለመካድ የመጀመርያዎቹ ናቸው።

ይህ የመርካቶ ቁጭበሉ ሼም አያውቅም። ትንሽ ብትጠብቁት እንደገና ይመለሳል። በዚህ አይነት ሰው ላይ እምነት መጣል እና መስጋት ከየዋህነት ያለፈ ነው። አንድ ጅል ትምህርት ቤት ሲሄድ የሙዝ ልጣጭ አዳልጦት ወደቀ። ከትምህርት ቤት ሲመለስ ያችኑ የሙዝ ልጣጭ አይቶ ቆመ። ከዚያም ማልቀስ ጀመረ። ለምን እንደሚያለቅስ ሲጠየቅ ወደ ልጣጩ እያመለከተ እንዲህ አለ። «እንደገና ልወድቅ ነው።»

5 Comments

  1. Do not give a damn care for low life people. Who cares about Berhanu Damtie? No need to dwell on this idiot. Just laugh and relax

  2. I don’t understand why all these fuss about aba bela. By the way, aba mela refers to the great patriotic Ethiopian HabteGiworgis Denegde not opportunistic parasites like aba bela. I want to congratulate the opposition Diaspora that the tumor is removed. Now it is up to the woayne camp to keep an eye on him. Because everyone realizes that this dude can flip flop better than the Olympic gymnasts and available for sell for the highest bidder. Regarding ESAT, I do not believe that interviewing him is a mistake. ESAT interviewed him as a defector but never offered him a job that he was hoping for. We can use his own words and interviews to bash, trash, name and shame himself and as well as the regime. I am just wondering how he will blend the system he used to call racist and corrupt as well as in his own words, “fogariw” Meles and the “prostitute” Azeb camp…..kkkkk…..woayne camp, enjoy aba bela….hahahaha

  3. Honest God, if woyane is going to accept the so called Aba Mela, (in fact he has no Mela, rather belly), then woyane is really nothing, but mafia. I mean, at least for their moral, they have to ignore this guy. I knew several people who insulted senior woyane leaders and cadres, but no one like Birhanu. I never heard any one saying Prostitute Azeb, Fogariaw meles—he added to the insult lot of new words—-I mean didnot they have shame? how they will have a place for such type of people? i mean, if they have still space for people like aba mela, what type of people are leading our country? can you lead a family leave alone country, without having a moral? I am eager to see how woyane treat this issue!! Yekoye—alu emama tiru!

  4. በጣም ገረመኝ፡፡ ከገረሙኝ ነገሮች አንዱና ዋናው የጊዜ ርዝማኔው ነው፡፡ መገልበጡን መጠበቅም ከነበረብኝ ልጠብቀው ከምችለው እጅግ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ነው የተገለበጠው – የተዋጣለት አክሮባትና የአእምሮ ህመምተኛ መሆኑን አስመስክሯል፤ በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ ላይ አስመዝግቡት – እንደዚህ ያለ ፈጣን ተለዋዋጭ መኖሩን ሰምቼ አላውቅም፡፡ የለውጡ ዓይነት ደግሞ ከጨለማ ወደ ብርሃን ዓይነት subliminal ነው፡፡ የሰው ልጅ በባህርይው እንዲህም ነው፡፡ የርሱ ባሰ እንጂ፡፡ ሲናገር እኮ ያፈዛል፡፡ ለነገሩ “ሰይጣንም ለተንኮሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል” ይባላልና ሰውዬው የሚያደርገው ሁሉ ለእኛ ለሞኞች እንጂ ለርሱ መደበኛና ጤናማ ነው፡፡
    አንድ ግብረሶዶማዊ ወይም ሌዝቢያን ወይም ሌባና አጭበርባሪ ድርጊታቸው ለነሱ ለራሳቸው በጣም “ጤናማ” ነው፡፡ ጤናማ የማይሆነው እነዚህ ነገሮች ለማያደርጉ ሰዎች ነው፡፡ በሥነ ልቦና ትምህርት እነዚህ ሰዎች በሽተኞች ናቸው፡፡ በሽተኞች ተደማጭነትና ከበሬታን ካገኙ ግን ችግር ነው፡፡ አንደኛ አድማጩና አክባሪው በቅድሚያ ይጎዳሉ፡፡ አንድ ሰው ነበር – በእግዚአብሔር አያምንም አሉ፡፡ እሱ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን በእግዚአብሔር እንዲያምኑ የሚያደርግ የአነጋገር ለዛና ተሰጥዖ ነበረው፡፡ ዳምጤም መርዝ በተደበቀበት በማር የተለወሰ አንደበቱ አነሆለለንና “ሰው አገኘን” አልን፡፡ ግን ግን ድመት መንኩሳ ዐመሏን እንደማትረሳ ይህ በሽተኛ ሰውዬ የዋሆችን ጉድ ሠርቶ ወደካምፑ ተመልሷል ማለት ነው፡፡ በበኩሌ “ ይህ ክስተት መማሪያ ይሆነናል” ማለቱ ጅልነት ይመስለኛል፡፡ እስከመቼ እየተጃጃልን እንኖራለን፤ እስከመቼስ የአጭበርባሪዎች መናኸሪያ እንደሆን እንቀራለን፡፡ ይህን ሰው ጅባት ብሎ መተውና ወደፊት መቀጠል ነው፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው፡፡ እንዲህ ያሉ እስስቶችና አጋሰስ ጌኛዎች መኖራቸውን ማወቁ በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ ነገር ግን ትምህርት ይሆናል ከሚል ሞኝነት ማንንም አፈጮሌ እያስጠጉ ጓዳ ጎድጓዳን ማስቧጠጥ ደግ አይደለምና ለወደፊቱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ መጣጥፌ የአባ መላ ነፍስ መግዛት ጥሩ መሆኑን ጠቅሼ ነገር ግን ለተንኮል አለመሆኑ ይጤንበት ማለቴን አስታውሳለሁ፡፡ ለውጥ አለ፡፡ ነገር ግን የለውጥን እውነተኝነት መመርመር ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ሰውን ማመን ቀብሮ ነው እንዳለችው እመት ቀበሮ በውብ ቋንቋ እየከሸነ የሚናገርን አሰለጥ ሁሉ እንዳለ ተቀብለን ከፈዘዝን ኤድስ የያዘው ቆንጆ ሰው አነሁልሎ ቢተኛን የምንሆነውን መሆን ለመሆን መስማማት ነው፡፡ የዚህ ሰው በሽታ ሆድና በየትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ስመጥርነትን ማግኘት ነው፡፡ በሰይጣን ቤትም ይሁን በእግዚአብሔር ቤት ዋናው ሹመቱን ያግኝ እንጂ ስለምክንያታዊነቱ ሃሳብ አይገባውም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው የራሱ የሆነ አእምሮ የለውም – ማሕጸን እንደሚያከራዩት ዓይነት ድሆች የፈረንጅ ሀገር ሴቶች እርሱም ብልጣብልጥ አንደበቱንና ቀፎ ጭንቅላቱን በገንዘብ እያከራዬ መኖር ነው ሥራው፡፡ እንደተባለው ልጁንም ሸጦ ቢሆን ገንዘብ ከማግኘት ወይም በዝና ማማ ላይ ፊጥ ከማለት አይመለስም፡፡ የሰውን ባሕርይ አንዴ ማወቅ ነው፤ ከዚያ መጠንቀቅ፡፡ ከዚህ በኋላ ስለርሱ መነታረክ በፈሰሰ ውሃ መጨቃጨቅ ነው፡፡ ይልቁንስ ገና ያላወቅናቸው ብዙ በሽተኞችና እስስቶች አሉ፡፡

  5. Kinfe It is good to comment on things for construction.The comment helps to correct mistake .What do say on the one who is commenting on things you hate from the biginning .you hate ESAT from the biginning.please watch the utube esat when the Amestrdam esat station interviewed you. I watched how your face look like at that interview. i do not know why you hate it. It is a radio and televsion station that gives service to the oppostion forces. Do you oppose weyannae?if so why esat? this is not the only things you did. You were inviting your website to weyanaes like dawit kidanemariam who are spy and supporter of weyanae.On this writing you main object is not critising the abamela.it is aginst ESAT and their supporter. ESAT is growing it will continue flourshing. ESAT used Abamela and Dawit to their propaganda as far as against weyanae not against oppostions group.There may be others also; When they change thier mind to weyanae they will be throwen away by the people as wellas by ESAT. ESAT has journalists with well stablished aim ie for the freedom of ethiopian people.I believed ESAT may play a great roll in the dismantelling of weyanae.I do not belief on opposing the oppostion group as far as ethiopian people have strong enemy weyanae.it is old tactic. I may leave also a message to all the oppostion group who oppose the oppstion forces.Please see the big picture the oppressor of the 90 million people ie Weyanae .let us stand only against on weyanae .Let us not stop leaving the 90 million people and stand to few group of people in thier group or party at this time .Espsially the journalist has great responsblity. THANK YOU

Comments are closed.

13544
Previous Story

ስለሚኒሶታው መድሃኔዓለም ቤ/ክ አመሠራረትና አሁን ያለበት ሁኔታ ምናልባት እስካሁን ያልሰማናቸው ጉዳዮች – (ልዩ ጥንቅር ከኢትዮጵያ ድምጽ ራድዮ)

Next Story

አባ መላ እና መላ ያጣው ንግግራቸው (በዳጉ ኢትዮጵያ)

Latest from Blog

ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com ) እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት

የኢካን ዓላማ በኔዘርላንድ የሚኖረውን ትውልደ ኢትዮጵያውያንን እና ኢትዮጵያውያንን ኮምዩኒቲይ የማሰባሰብ ሳይሆን የመከፋፋልና የማዳከም ተልኮን ያነገበ ነው።

አገር ! ለየአንድ ሠው ቋንቋው፣ ልማዱ፣ ባሕሉ፣ እምነቱ፣ አስተሳሰቡ፣ ወጉና በአጠቃላይ እሱነቱና ማንነቱ የሚከበርበት ብቸኛ ሥፍራ ነው። ኢትዮጵያውያንም በስደት በሚኖሩባቸው አገራት ሁሉ እነኝህን በስደት ያጧቸውን የግልና የጋራ ማንነቶቻቸውን በአንድ ላይ ሆነው ለመዘከር

ፋኖ ምሽጉን ደረመሰው ድል ተሰማ | ” ስልጣን እለቃለሁ ” ፕረዚዳንቷ | ህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ | “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ

-966+9-የኦህዴድ ድብቅ ስብሰባ በአዲስ አበባ “ተመስገንን በመዳፌ ስር አስገብቼዋለሁ” አብይ – ስልኩ ተጠለፈ “እኛ የምን’ዘጋጀው ለፋኖ ሳይሆን ለኤር-ትራ ነው” አበባው|”በጊዜ ቦታ አዘጋጁልኝ” አረጋ

አንድ በኢኮኖሚና በሌሎች ነገሮች ወደ ኋላ የቀረች አገር አንድን ኃያል መንግስት በመተማመንና ጥገኛ በመሆን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማምጣትና የተሟላ ነፃነትን መቀዳጀት ትችላለች ወይ?

ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር) ሰኔ 4፣ 2016 (ሰኔ 11፣ 2024)   በዚህ አርዕስት ላይ እንድጽፍ የገፋፋኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑኑ ዶ/ር ዮናስ ብሩ የቻይንንም ሆነ የቬትናምን በኢኮኖሚ ማደግ አስመልክቶ ሁለቱ አገሮች እዚህ ዐይነቱ የዕድገት ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት ከአሜሪካ ጋር

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት

ፋኖ አንድ ሌሊት አያሳድረንም” የአማራ ብልፅግናየኢሳያስ ግዙፍ ጦር ወደ ወልቃይት አብይና ዳንኤል ክብረት ጉድ አሰሙ-|ጀነራሉ በቁ*ጣ ተናገሩ-‘ህዝቡ ጉድ ሰራን’-|“ብልፅግናን ራ*ቁቱን አስቀርተነዋል”-|ታዳሚው ባለስልጣናቱን አፋጠጠ
Go toTop