ዛሬ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳቅ የወያኔውን ብርሀነክርስቶስ በመጋበዘ ለተለያዩ የቀድሞ አምባሳደሮችና ታዋቂ ሰዎች ብርሀነ አደገኛ መርዙን የዘራበትን ቪዲዮ ዮቲውቡን ሁሉ አጨናንቆት ተመለከትሁ፡፡ ይሄን ቪዲዮ መጀመሪያ ያወጣው እንደገባኝ የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆነው ካናዳዊው ጋዜጠኛ ጄፍ ፒርስ ነው፡፡ በጄፍ ገጽ እንደተመለከትኩት በሚስጢር እነ ኤፍሬም ይሳቅ በኢትዮጵያ ላይ እየዶለቱ ነው ይመስላል፡፡
የዚህ ቪዲዮ እውነታ ግን ምን ይሆን? እኔ የተረዳሁትንና የተወሰነም ስለ ጉዳዩ የማውቀውን ልናገር፡፡ ይሄ ስብሰባ በድብቅ የተካሄደ ሳይሆን Peace and Development Center International (PDCI) https://www.ethiopiapdci.org/ ወይም የአለም ዓቀፍ የሠላምና የልማት ማዕከል የተለመደ በወቅታዊ ጉዳዮች የሚመለከታቸውን ጋብዞ ውይይት ማድረግ የሚለውን አላማ የያዘ ነው፡፡ በአጋጣሚ በዚህ ቪዲዮው እየተሰራጨ ባለው መድረክ በተጠያቂነት የቀረበው የወያኔው የውጭ ክንፍ ዋነኛ አንቀሳቃሽ የሆነው ብርሀነክርስቶሰ መሆኑና ሰውዬውም የተሰጠውን አጋጣሚ እንደተለመደው አደገኛ የሆነ መርዙን መርጨቱ ነው የዚህ ስብሰባ ለየት የሚያደርገው፡፡ ለብዙዎች በዚህ ስብሰባ የተገኙ በቪዲዮዎውም እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ላይ ሴራ እየሸረቡ ያሉ ብቻ ተመርጠው መስሏቸዋል፡፡ እውነታው ግን ምን አልባትም አሁን ያለው የአብይ መንግስት ሁነኛ ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦችም በዚህ ሥብሰባ የተገኙ መሰለኝ፡፡ አስተያየት ወይም ጥያቄ አላነሱም እንጂ፡፡
ስብሰባው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ላይ የሚዶልቱ ሰዎች ስብሰባ ሳይሆን የአለም አቀፍ የሠላምና የልማት ማእከል ከሚያደርጋቸው ሥብሰባዎች አንዱ ነው፡፡ የዚህ ማዕከል የቦርድና የሥራ ዓስፈጻሚ አባላት ከላይ ባስቀመጥኩት ድረ ገፅ እንደምትመለክቱት ነው፡፡ ስብስቡ ከሞላ ጎደል የተለያየ ማንነት ያላቸው ግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡ እሌኒ ገብረመድህን የዚህ ማዕከል አባል ነች፡፡ በቪዲዮው ባየንው ስብሰባ የተገኘችውም እንደ አባልነቷ እንጂ በልዩ ግብዥም አይደለም፡፡ ሌሎች የምናውቃቸው ከትግሬ ያልሆኑ ይልቁንም አሁን ያለውን የአብይ መንግስት ከሚደግፉ በስብሰባው አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሥማቸው ሲጠራ የሰማኋቸውም አሉ፡፡ ከእነሱ ውስጥ ጥያቄ ስታቀርብ የታየቸው ኢሌኒ ብቻ ነበረች፡፡ በስበሰባው በተጋባዥነት የመጡት የቀድሞ የተለያዩ አገራት የውጭ አምባሳደሮችና ራሱ በርሀነ ነበሩ፡፡
የወያኔው የውጭ ክንፍ ዋናው ዘዋሪ የሆነው ሰውዬ መድረኩን ሁሉ ለሴራው እንደተጠቀመበት አይተናል፡፡ ብዙዎቹ ተጋባዥ ጠያቄዎችም በእግጥም ለወያኔ ያላቸውን ወዳጅነት አሁን ታዲያ እንዴት ነው ወያኔን ማትረፍ የሚቻለው አይነት የጭንቀት የሚመስል ጥያቄ ነበር ሲሰነዝሩ የሚታዩት፡፡ በዛው ልክ በቅንነት ኢትዮጵያን ብቻ ማዕከል ያደረገ አስተያየታቸውንና ጥያቄያቸውን ሲያነሱ የሰማናቸውም አሉ፡፡ ለምሳሌ ከጀርመን ተጋባዥ የሆነችው አምባሳደር አስተያየቷ በግልጽ በቅንነትን እንደውም ዛሬ በኢትዮጵያ እየሆነ ባለው ነገር በማዘን ነው፡፡ ይህች አምባሳደር የወያኔው ሰውዬ ውሸት የተሞላበት ዲስኩር ብዙም የጣማት አይመስልም፡፡
በመጨረሻ የሰማንው የፕሮፌሰሩ ማጠቃለያም የብርሀነገብረክርስቶስን መርዘኛ አነጋገር የሚያረክስ እንጂ እንደተባለው የሚያበረታታና ዱለታ አልነበረም፡፡ ኤፍሬም ይስሀቅ በማጠቃለያቸው ሲናገሩ የኢትዮጵያ ችግር አንድ በመቶ በማይሞሉ ተማርን በሚሉ የመጣብን እንጂ ሕዝቡ ጋር አንዳች ችግር የለም፡፡ ይልቁንም በምዕራቡ አለም የተምህርት እድል አግኝተው ተማርን የሚሉ አንድ በመቶ የማይሞሉት ናቸው የኢትዮጵያ የችግር ሁሉ ምክነያት ብለው በዛው የጀርመንንና የፈረንሳይን የድሮ ጠላትነትና ዛሬ ያሉበትን የጃፓንና የአሜሪካን የድሮ ጠላትነትንና ዛሬ ያሉበትን ጠቅሰው፡ ኢትዮጵያውያን ግን እነዚህ ተማርን የሚሉ ካመጡብን ችግር በቀር በጠላትነት የመተያየት ችግ የለብንም፡፡ አሁንም ያለው ይፈታል በሚል ተስፋን የሚያጭር ንግግር ነበር፡፡
ሆኖም ዛሬ በየዩቲዩቡ እንደተመለከትኩት የስብሰባውን መሠረታው ዓላማ መረዳት ይቅርና ፕሮፌሰሩ በመጨረሻ ያስተላለፉትንም መልዕክት የሰማ ያለ አይመስለኝም፡፡ መስማትም የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ ችግሩ እንዲህ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያውያን ነገር በወያኔ ጥላቻ ብቻ የተሳከረ በመሆኑ አገራችን ዛሬ ያለችበትን ቀውስ ሁሉ በወያኔ እየተሳበበ ብዙ የከፋ ነገር እየደረሰ ነው፡፡ ወያኔን በመጥላት ብቻ የሚመጣ ነገር የለም፡፡ ወያኔን በመጥላት ብቻ በሆነው ምልከታችን ለወያኔ ጨምሮ ለብዙ የኢትዮጵያ ጠላቶች ትልቅ እድል እየፈጠረላቸው እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ይሄን ዛሬ እየተሰራጨ የሚገኘውን ቪዲዮ ከበስተጀርባ ሴራ እየተዶለተ ነው በሚል የመበርገጉም ምክነያት ይሄው ነው እንጂ ቪዲውን በደንብ አስተውሎ ለተመለከተው የወያኔው ሰውዬ አስተያየቱን እንዲሰጥ እድል ማግኘቱ እንጂ የተለየ ሴራ እንዳለው ምልክት የለም፡፡ እንግዲህ እንዲህ በትንሹ በትልቁም እየበረገግን መሠረታዊ ጉዳዮችን ማስተዋል ባለመቻላችን ወያኔንን ጨምሮ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንን ወደፈለጉት እያዘወሩን እነሱ ሴራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ለማንኛውም የቪዲዮውን የመጨረሻ መልዕክት በደንብ አስተውሉት፡፡ ፕሮፌሰሩ ለወያኔው ሰውዬም ለተጋባዥ አምባሳደሮችም የነገሯቸው ችግሮቹ እናንተ ናችሁ እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አደሉም ነው፡፡ የምዕራባውያን አስተሳሰብ ነው ያስቸገርን አይነት መልዕክት ነበረው፡፡ በምዕራባውያን አገር የተማሩ ጥቂት ግለሰቦች በሚል ነበር የጠቀሱት፡፡ እንግዲህ ይሄን መልዕክት የሰማን ስንቶቻችን እንሆን? አሁንም ቢሆን በድንብ እናስተውል፡፡ ኢትዮጵያኖች ሆይ በነገሮች ስሜተኞች እንደሆንን የተረዱን ሴረኞች አጀንዳ እየፈጠሩ መጠቀሚያ እያደረጉን እንደሆነ አስተውሉ፡፡ ይሄ ስብሰባ ብርሀነ የተባለው ግለሰብ እድል አግኝቶ የተለመደ መርዙን ከመርጨት በቀር ለልዩ ሴራ የተካሄደ ሥብሰባ አደለም፡፡
ይልቁንስ ሚዲያዎች ስበሰባውን ሲመሩት የነበሩትን የማዕሉ ሰብሳቢን በማነጋገር እውነቱን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ የተሻለ ግንዛቤ ይሰጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዲሁ በመሰለኝ ከማውራትም ያድናል፡፡ በእርግጥም ሴራም ካለበት ፊት ለፊት ማውጣት ያስችላልና፡፡ ይልቁንስ ኤፍሬም ይሳቅ ዛሬ እንኳን በዚህ በ80ዎቹ አድሚያቸው ለኢትዮጵያ ትልልቅ ነገሮችን እያቀዱ እንደሆነና በቅርቡም አንደ ትልቅ ነገር ሊያበረክቱ እየሰሩ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ፕሮፌሰሩ ነገሮችን የሚያዩበት አተያይ እኛ እንደምናየው አደለም፡፡ በተለይ ለሰላምና ይልቁንም ለአገራቸው ኢትዮጵያ ያላቸው ቦታ ትልቅ ነው፡፡ ይሄ ቪዲዮ ፕሮፌሰሩ በቅርብ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ለመስራት እየሰሩ ያለውን ለማበላሸት ነው ወይ የሚል ነገር አጭሮብኝ ነበር፡፡ ሆኖም ጄፍ ፕርስም በቅንነት በእርግጥም ሴራ እንደሆነ ስለተረዳው ይበልጠውንም የወያኔው የውጭ ክንፍ ዋነኛው መርዙን ሲረጭ ስለሰማው ስለሆነ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ወዳጆች ሴራውን ማጋለጡ ነው፡፡ ከወያው መረዘኛ መርዝ ስርጭ በቀር ግን የስብሰባው አላማ ሴራ አልነበረብም፡፡ ሚዲያዎችም በመሰለኝ ከምታወሩ ፕሮፌሰሩን ወይመ ሌላ የማዕሉን ሥራ አሰፈጻሚ ጠይቁ፡፡ የሆነ ሆኖ እኛ በሆነው ባልሆነው መበርገጋችንን ትተን እናስተውል፡፡
ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
አሜን!