‹‹ዳጉ የአሸባሪ ኃይሉን ሐሰተኛ መረጃ ያጨለመ ቱባ ባህላችን ነው›› – አቶ አህመድ ኑርሳሊ

አቶ አህመድ ኑርሳሊ የካሳጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ

257895393 2141438769340793 4029940926631139397 nዳጉ የአሸባሪ ኃይሉን ሐሰተኛ መረጃ ያጨለመ ቱባ ባህላችን ነው ሲሉ የአፋር ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ እና የካሳጊታ ግንባር ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ አቶ አህመድ ኑርሳሊ ተናገሩ።

አቶ አህመድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የአፋር ሕዝብ በመረጃ የደረጀ የዳጉ ስርዓት መለያው የሆነ ሕዝብ ነው። ዳጉ ለአፋሮች የጀርባ አጥንት በመሆን እንደ ውሃና መጠለያ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው።

ከጥንት ከአባቶቹ የወረሰው ይህ አገር በቀል ባህል በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ ተቀባይነት ያለውና አሁንም ድረስ የአፋር ሕዝብ እየተጠቀመበት ያለ በመሆኑ የተዛቡ መረጃዎች በኀብረተሰቡ መካከል አይዘዋወርም ብለዋል። በመሆኑም የአፋር ሕዝብ በአሸባሪውና ወራሪው የትህነግ ኃይል ፕሮፖጋንዳ የመጋለጥ ዕድሉ እጅግ የመነመነና ማኀበረሰቡም ወደ ሌሎች የማኀበረሰብ ክፍሎች የተዛቡ መረጃዎችን ባለማስተላለፉ በአሁኑ ወቅት በጦር ሜዳ ድል በመቀዳጀት ላይ ይገኛል።

የአፋር ማኀበረሰብ በአብዛኛው አርብቶ አደር በመሆኑ በባህለዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ መረጃዎችን በተገቢ መልኩ ይጠቀምበታል ያሉት የኮማንድፖስቱ ሰብሳቢ፣ የሚተላለፉ መረጃዎች በዘፈቀደ መልኩ ሳይሆን መረጃዎች ግልጽ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው ሰው ብቻ በጥንቃቄ ስለሚተላልፍ የመረጃ መፋለስ የመፈጠር ዕድሉ እጅግ አናሳ ነው ብለዋል።

ሐሰተኛ መረጃ ቢያስተላልፍ እንኳ በዳጉ ባህል ስለሚወገዝ ፈጽሞ እንደማያደርገው ገልጸው፣ ያየውን ሁነት ሁሉ በትክክል ሳይሸማቀቅ በማስተላለፍ የሚታወቅ ማኀበረሰብ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪው ኃይል ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ሳይታለል በራሱ መረጃዎችን እየተለዋወጠ አካባቢውንና ክልልሉን ብሎም አገሩን ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ከወራሪ ኃይሉ በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

እንደ ኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ የአፋር ሕዝብ ለመከላከያ ኃይሉ ደጀን በመሆንና ትክክለኛ መረጃ በመስጠት በተጨባጭ የባህሉን ጠቀሜታ ያሳየበት፣ ማኀበረሰቡ ለፕሮፖጋንዳ እጅ ባለመስጠቱ ምክንያትም ካለበት ቦታ ሳይፈናቀልና ሳይሸሽ አሸባሪ ኃይሉን እየተፋለመ ይገኛል። ይህ የቁርጥ ቀን ልጅ ባለው ጀግንነት ስለሚታወቅ ችግሮች ቢከሰቱ እንኳ ተቋቁሞ ይኖራል እንጂ ከአካባቢው ተሰዶ የማይሄድ፤ ባለበት ቦታ ሆኖ አገሩንና አካባቢውን በንቃት የሚጠብቅ፤ በየትኛውም ጊዜ ችግሮችን ተቋቁሞ የሚጸና ማኀበረሰብ ነው ብለዋል።

አሸባሪውና ወራሪው ኃይል ክልሉን ለመውረር ከደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ከሚሴና ከተለያዩ አካባቢዎች ኃይሉን በማሰባሰብ በተለይም የኢትዮ-ጅቡቲን መንገድ ለመያዝ ጥረት ሲያደርግ ቢቆይም በባለሽርጦቹ ህልሙ ባዶ ሆኖበታል ብለዋል። በተለይም ሚሌን ተቆጣጥሬያለሁ በማለት የሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ መቀሌ በሚገኙት ከፍተኛ አመራሮቹ ቢያስነግርም በተግባር በዚህ ግንባር ያጋጠማቸው ፈተናና የሞራል ውድቀት በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መምከኑን አስረድተዋል።

ጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና የአፋር ሚሊሻ በቅንጅት በሠሩት ሥራ ጥቂት ተቆራርጦ የቀረ የአሸባሪ ኃይሉ ርዝርዥ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመደምሰስ ከፍተኛ የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

እንደ አቶ አህመድ ኑርሳኒ ገለጻ፤ የአፋር ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደር በመሆኑ ይህን የኢትዮ ጅቡቲ መንገድን ለመቆጣጠር የሚመኙ ኃይሎች አገሪቱን ለማፍረስና የህልውና አደጋ ላይ ለመጣል መሆኑን በመረዳት ተጋድሎ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ፍቃዱ ዴሬሳ

አዲስ ዘመን ህዳር 11 ቀን 2014 ዓ.ም

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.