የጸረ-ኦርቶዶሱ ብልጽግና ቁማርና ደጋፊ ሚዲያዎቹ – ሰርፀ ደስታ

/

ከትላንት ወዲያ አንዳንድ ቦታዎች ላይ በቤተክህነት መሣሪያ ተገኘ የሚለውን ወሬ ሰምቼ ምን ተገኝቶ ይሆን ብዬ ነበር፡፡ ጉዳዩን ግን የዛን ያህል ትኩረት አልሰጠሁትም ነበር፡፡ አንድ ራሱን የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ የሚያደርግ አደባባይ የተባለ ሚዲያም ጉዳዩን አንስቶ ሲያወራ በጨረፍታ ሰምቼ የሆነ ነገር ተገኝቶ ይሆናል ብዬ ያው በወያኔ ዘመን የተቀበረ ሊሆን ይችላል ከሚል ግምት ያለፈ ብዙም ቦታ አልሰጠሁትም፡፡ ትላንትና ነበር የብልጽግና ልሳን የሆነው ኢሳት የአዲስ አበባ ከንቲባዋን ኢንተርቪው የሰማሁት፡፡ የሴትዮዋን ንግግር ላስተዋለ በኦርቶዶክስ ላይ ያላትን ጥላቻ ያሳበቀ እንጂ አንድ በዛ ደረጃ ያለ ባለስልጣን የሆነው ነገር በእርግጥም እንደተባለው ለልዩ ወንጀል የተከማቸ መሳሪያ ቢሆን እንኳን ገና በምርመራ ላይ ያለን ጉዳይ በሚዲያ መናገር በራሱ ሕገ ወጥነት ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ደግሞ ፍተሻ የተባለውን ሒደት ሚስጢራዊነት ሊኖረው ሲገባ በእርግጥም ለልዩ ዓላማ መሳሪያ ያከማቹ ካሉ እንዲያሸሹና እንዲሸሽጉ ከወዲሁ ጥቆማ መስጠት ነው፡፡ ኢሳት የተባለው የብልጽግና ልሳን እንዲህ ከብልጽግና ሹማምንት ጋር ባለው ቅርበት የተነሳ ከፍተኛ የተባሉ የጦር መኮንኖችን ሳይቀር በማንጋገር በወታደራዊ ተቋሙ ብቻ ሥር መሆን ያለባቸውን ጉዳዮች ሳይቀር ለገበያው እየሸቀጣቸው እንደሆነ በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ የዛሬውም አዳነች አቤቤን ያነጋገረበት ሂደት ይሄው ነው፡፡ አዳነች አቤቤ በቤተክርስቲያ ላይ ያላት ውስጠ ወራዊ ጥላቻ በግልጽ ያሳየችበት ምን አልባትም እግረ መንገዷን ሌላ ቦታ የሚጠረጠሩ በእርግጥም ለልዩ ወንጀል መሳሪያ የደበቁ ካሉ ተጠንቀቁ፣ አሽሹ ያለችበት አደገኛ የሆነ ንግግር ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው ፍተሻው ፍተሻ ሀኖ አዲስ አበባን የሚያድነው? ብሎ መጠየቅ ወሳኝ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በለገጣፎ -ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ቤታቸው የፈረሰባቸው ወገኖች ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ አቶ ለማ መገርሳን ማነጋገር አትችሉም ተባሉ

በትላንትናው እለት በቤተክህነት ተገኘ የተባለውን ከተለያየ ሚዲያ ሳይ በግልጽ በወያኔ አድጎ ራሱን ብልጽግና ያለው ቡድን መሪ ነኝ የሚለው አብይ አህመድ የጻፈውን የጸረኦርቶዶክስ የብልጽግና ማኒፌሽቶ እንደገና እነዳስተውለው ግድ ብሎኛል፡፡ ወያኔ በግልጽ የአማራ ጠል ማኒፌስቶ ጽፋ እንደተነሳች ብልጽግናም በግልት የኦርቶዶክስ ጠልነቱን በማኒፌስቶ ጽፎ አንደመጣ አይተናል፡፡ ማንም ግን ስለዚህ በአብይ አህመድ የተጻፈ የብልጽግና ጸረኦርቶዶክስ ማንፌስቶ ትኩረት ሰጥቶ ለምን ብሎ የጠየቀ አላያሁም፡፡ ዛሬ በቤተክህነት መሳሪያ ተገኘ በሚል በግልጽ ቤተክርስቲያኒቱን ለማጠልሸት አዳነች አቤቤ የሄደችበት ርቀት ትልቅ ደወል ሊሆን ሲገባ ይባስ የቤተክርስቲያን ነን የሚሉት እንደነ አደባባይ የመሰሉት ሚዲያዎች ሳይቀር ተቀብለው ሲያራግቡት በአግራሞት ተመልክቻለሁ፡፡ ለመሆኑ ማን ነው ለእውነት የሚታመነው?

በቤተክህነቱ ግምጃ ቤት ተገኘ የተባለው መሳሪያ ሳይሆን 1800 ጥይትና የጥይት ሳጥን እንዲሁም የክላሽንኮቭ ካዝዘና (ማለትም የጥይት ማስቀመጫው ቀፎ) ነው፡፡ እንደው እንኳንስ ፖሊስን የሚያህል ትልልቅ ሚስጢራዊ ወንጀሎችን ያወጣል ተብሎ የሚገመት አካል ይቅርና ለማንም ተራ ሰው 1800 ጥይት በቤተክህነት ግምጃ ቤተ መገኘቱ አዲስ ነገር ይሆንበታል? ጭራሽ እንደ ልዩ የምርመራ ውጤት በእነ አዳነች አበቤና በብልጽግና ሚዲያዎች በስፋት ሲሰራጭ ተመለከትን፡፡ ሊያም እውነት የተገኙት ጥይቶች ለልዩ ሴራ ተደብቅ የተገኙ እንኳን ቢሆን የቤተክርስቲያኒቱን ክብር መጠበቁን ይተውትና በዚህ ወቅት ሚስጢራዊነትቱን መጠበቅ ለቀጣይ ፍተሻ ወሳኝ መሆኑ እየታወቀ፡፡ ተገኙ የተባሉት 1800 ጥይቶች እንግዲህ በአንድ ትልቅ የአገሪቱ ታሪካዊና ተምሳሌታዊ በሆነችው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ግምጃ ቤት ውስጥ ነው፡፡ 1800 ከዛም በላይ ጥይት ለጥባቃ ሥራም ይሁን በተለያዩ ጊዜ በታሪክ ሊሰበሰቡ የሚችሉም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ደግሞም የሆነው ይሄው ነው፡፡ በቤተክርስቲያኑ ግምጃ ቤት ለጥበቃ ሥራ የሚሆኑ ጥይት ብቻ አደለም መሳሪያም ይገኛል፡፡ ለብ በሉ ተገኘ የተባለው 1800 ጥይት ነው፡፡ እንደው አንድ 20 ክላሽንኮቨ ቢያገኙ ምን ሊሉ እንደሚችሉ አስቡት፡፡ በእርግጠኝነት በጠቅላይ ቤትክህነት ብቻ ከ20 በላይ ለጥበቃ ሥራ የሚውል የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ይኖራል፡፡ በጠቅላይ ቤተክህነቱ ግን ለሌሎች ቦታዎችም ሊሆን የሚችል በርከት ያለ መሣሪያም ሊከማች ይችላል፡፡ ሆኖም ያ እንኳን ያለ አልመሰለኝም፡፡ እንዲህ ያለን እውነት በመካድና ሆን ተብሎ ቤተክርስቲያኒቱን ለማጠየም እየተሰራ ያለውን የብልጽግና ቁማር ምዕመኑ እንደ ዋዛ ማለፍ ያለበት አይመስለኝም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አብይ በአማራ ላይ ከከፈተው ጭፍጨፋ ድርድር ነጻ አያደርገውም | Hiber Radio Special Program

አደባባይ የተባለው በዋናነት የቤተክርስቲያን ነን የሚሉ የሚሰሩበት ሚዲያ ጉዳዩን ከቤተክርስቲያን በቀጥታ በማጠራት ለሕዝብ ግልጽ ማድረግ ሲገባው ጭራሽ በቤተክርሲቲያን ሰዎች ነን በሚል ሽፋን የብልጽግናን ሴራ በሕዝብ ተቀባይነት እንዲያገኝ አንድ ቀን ሳይሆን ሁለት ቀን ሥራዬ ሆይ ብሎ ሲያሰራጭ አይቼ አዝኛለሁ፡፡ አደባባይ የሚባለው ሚዲያ በተደጋጋሚ በኦርቶዶክሳዊነት ሽፋን ለጸረ ኦርቶዶክሱ ብልጽግና የኮንቪንስና ኮንፉውዝ ሥራ ሲሰራ ታዝበናል፡፡ የዛሬውም ዝግጅቱ የዚሁ አንድ አካል እንደሆነ ስናስተውል እጅግ በማዘን ነው፡፡ ባለማወቅ ቢሆን ጥሩ በሆነ፡፡ በተደጋጋሚ ያየንው እውነት ነው፡፡ የዛሬው ደግሞ የለየለት የብልጽግናን ጸረኦርቶዶክሳዊነት በይፋ ደግፉ መርዝ ሲረጭበት ያየንበት ነው፡፡ ይህ በእውነት ያሳዝናል፡፡ ማንን ማመን ይቻልል? ኢሳት በግልጽ የብልጽግና ልሳን ስለሆነ ብዙም አልገረመኝም፡፡እንደምናየውም የአገሪቱ ትልልቅ ሚስጢራዊ ተቋማትን ባለስልጣ ሳይቀር ቃለ መጠይቅ የሚያደርገው ከመንግስትም ሚዲያ በላይ ኢሳት ነወ፡፡ የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ ነኝ የሚለው አደባባይ ግን በዚህ መልኩ የጸረኦርቶዶክስን መርዝ ሲረጭ ማየት አሳዛኝ ነው፡፡

ለማንኛውም 1800 ጥይት በቤተክህነት ግምጃ ቤት (የቤትክርስቲያኒቱ ትልቁ ግምጃ ቤትም ሊሆን ይችላል) መገኘቱ ስህተት ሳይሆን ከዛም በላይ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዛ ይልቅ በሺዎችና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጦር መሳሪያዎች በብልጽግና ለኦነግሸኔ እየተላለፉ እንደሆነ ማንም አይናገርም፡፡ ዛሬም ቢሆን በአዲስ አበባ ሳይቀር ሌላውን በፍተሸ በሚል እያሸማቀቁ በጎን ለኦረሞ ብልጽግና ጠባቂዎች ማስታጠቅ እንደተስፋፋ እንታዘባለን፡፡ የብልጽግና ስልት ከወያኔ እንደወረደ የተቀዳ ብቻም ሳይሆን እንደወያኔ እንኳን ጥንቃቄ ባለበት ቀስ እየተባለ ሳይሆን በወረራ ምልክ ነው ነገሮች ሁሉ በኦሮሞ ኦነጋውያን ቁጥጥር ስር እንዲሀገቡ እየተደረገ ያለው፡፡ ግን አዋጣም፡፡ ከምንምና ምንም በላይ ይሄ አደጋው ለኦሮሞ ሕዝብ ለራሱ ነው፡፡ የኦሮሞ ፖቲከኞች የወያኔ መንፈስ የተጠናወታቸው የሚየስቡት እንኳ እንደ ሶፈትዌር ወያኔ በጫንችላቸው አስተሳሰብ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ማሰብ ቢችሉ 27 ዓመት የተበላበትንና ሕዝብ አንቅሮ የተፋውን የወያኔን ሥልት እንደወረደ ዛሬ በብልጽግና ሥም ባልመለሱት ነበር፡፡ ሁሉም ይጠፉ ዘንድ ግን እየሆነ ያለው ሁሉ እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሀሉ አስተውሉ፡፡ በተለይ ኦርቶዶክሳውያን አስተውሉ፡፡ በአለፉት ሶስትና ከዛ በላይ በሆኑት ዓመታት የሆነውን ሁሉ አስተውሉ፡፡ ሰዎች በወያኔ ጥላቻ ብቻ ስለታወሩ ከወያኔ የከፋውን የኦሮሞ ኦነግ/ብልጽግናን ሴራና አረመኔነት እያስተዋሉት አይመስልም፡፡ በአለፉት ሶስት አመታት የሆነውን ደጋግማችሁ አስተውሉ፡፡ ግን አያዋጣም፡፡ ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም ሆኖ ነው፡፡ ሁሉም በሴራቸው ተጠልፈው የሚጠፉበት ጊዜ ሩቅ አይመስለኝም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከባድ ውሳኔ አዎን! ማይክና ብዕር ሰቅዬአለሁ

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ

አሜን

3 Comments

  1. ሰርጸ እየተስተዋለ እንጅ። እኛን ሳይገባን አንተን በተለየ መልኩ የገባህ ነገር ያለ አልመሰለኝም አደባባይ ሚዲያ አንተ ባልከው መልኩ ትችት የሚገባው አልመሰለኝም።

  2. እነዚህ የሴጣን ቁራጮች ቤተ-ክህነትን ካዋረዷት፣ የሌባ ስብስብ፣ የዘር ሰንሰላት የተዘረጋበት እና የጦር ማስፈፃሚያ ካደረጓት እኮ ስንት ዓመታት ተቆጠረ አሁን ያለው መንግስት በጉዳዩ ላይ ቢዘገይም አልረፈደም አሁንም ይፍጠን፡፡ እነዚህ የቅዱስ ቦታን ያዋረዱ እና ተባባሪ የነበሩ የቤተ-ክህነት አስተዳደር ነን ተባዮች እና የውሸት ቆብ የሚያደረግጉ ተለይተው በደንብ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ቤተ-ክህነትማ የተዋረደቸው በቀድሞው ጳጳስ ተብዬ ጊዜ ነበር እኮ ኮልት እና መስቀል ይዞ ሴራ ሲዘረጋ የነበረው፡፡ ኡሁንም ከባድ እርምጃ እና አሰሳ በአዲስ አበባ ውስጥ መቀጠል አለባት፡፡

    ኢትዩጵያ ለዘላለም ትኑር!!

  3. በዚህ የጣር ጊዜ በየቦታው ሃገርና ወገን እንወዳለን በሚሉ ወገኖች የሚጎፈጫጨሩቱን ሃሳቦች ልብ ላለ ከጠቀሜታቸው ጉዳታቸው ያመዝናል። ትግል፤ የሃሳብ ፍጭት፤ ቡራ ከረዪም ቢሆን ጊዜ መርጦ ነው። አሁን ከሞላ ጎደል ጥቃቅን የሚባሉ ነገሮችን እየሰነጠቅንና እያባዛን እሳት የምንጭርበት ወቅት ላይ አይደለንም። ወያኔና ተባባሪዎቻቸው የጫሩትና በመንደድ ላይ ያለው እሳት ከመቀሌ ተነስቶ ሽዋ ሮቢት ደርሷል። አሁን ይህ እንዲህ ባለበት ጊዜ ጸረ – ኦርቶዶክስ፤ ብልጽግና እያሉ መወሻከቱ ጭራሽ ሊገባኝ አይችልም። እርግጥ ነው ወያኔና ኦነግ ሸኔ ተጣምረው የአምልኮ ቤቶችን እያወደሙ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን፤ የመስጊድ ስፍራዎችን እያፈረሱና እየዘረፉ እንደሆነ ተጨባጭ መረጃ አለ። ግን ያለምንም መረጃ የከንቲባዋን ፎቶ በመለጠፍና ብልጽግና ጸረ – ኦርቶዶክስ እንደሆነ መሳል ጉንፋናም መሆን ነው። መወገዝና መመከት ያለበት የወራሪ ሃይል እያለ ዝም ብሎ ባልተጨበጠ ነገር ላይ ማላዘን ምን ይባላል? ግን አንድ ነገር ለእኔ ግልጽ ነው። የራሱን የቀትር ጥላ ከሚፈራ ትውልድ ምንም አይነት ጭብጥ ነገር አይገኝም። ባጭሩ ትውልድ ህክምና ያስፈልገዋል። ታመናል። ይህ ሲባል የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን የውስጥና የውጭ ውጊያ የለባትም ማለት አይደለም። የእምነት ቤቶችና የዚህም የዚያም የማምለኪያ ስፍራዎች የጦር ማከማቻ፤ የሌቦች መደበቂያ፤ በእይታ የዘገዪትን በማታለል የመኖሪያ ብልሃት ፍለጋ ከሆኑ እድሜ ቆጥረናል። ያልዳነውን ዳነ፤ ሰይጣን ያልያዘውን ወጣለት፤ሞቱ እንደ ነገ የሆነውን እድሜ ልክ ትኖራለህ፤ አያሌ መድሃኒት ያላዳነውን በጠበል ትድናለህ እየተባለ ሊጠመቅና ሊጸለይለት ሂዶ ብሶበት ወይም አሸልቦ የሚመለሰው የሰው ቁጥር እትየሌሌ ነው። ግን ይህን ማን ሳይንሳዊ ጥናት አድርጎ ለህዝባችን ያስታውቅ? ባህሉም፤ ወጉም ወሬውና ተግዳሮቱም ይህን እንድናረግ አይፈቅድም። ፈጣሪን ከጥያቄ ውስጥ ማስገባት ነው ይሉናል። እኔ የማይጠየቅ አምላክ ማምለክ አልፈልግም። ብዙ ብዙ ጥያቄ አለኝና።
    የምወዳቸውና የማከብራቸው የወያኔን የበፊት ሃበሳ ሲጋፈጡ የታሰሩ፤ የተገረፉ፤ ዳግም ተፈትተው የሚጽፏቸውን ስመለከት ወ ቀጣፊ ይደልዎ ጥፊ ያሰኛል። ከእነዚህም መካከል ኤርሚያስ ለገሰ፤ ሃብታሙ አያሌው፤ መ/ር ዘመድኩን በቀለን መጥቀስ ይቻላል። በምድሩ ላይ ቆሞ ሃገሬ ናፈቀኝ ከሚልና በውጭ ሃገር ሆኖ በለው ያዘው ጥለፈው አለንልህ የሚሉ የውጭ አታኳሾች ጋር በምን አይነት ሂሳብ ነው ሰው በሰውነቱ ቆሞ የሚሟገታቸው? በቅርቡ አሜሪካ ያዋቀረቻቸው የዘር ጥርቅሞች 9 ኙ ተቃዋሚ ሃይሎች ውስጥ አንድ የአገው ህዝብ ተወካይ ነኝ የሚል ሲለፋደድ መስማት በፊትም ዛሬም ምን ያህል የነጭ ተላላኪዎች እንደሆን ያሳያል። አሁን ማን ይሙት የአገው ህዝብ ነጻ መውጣት ይፈልጋል? ግን ወያኔ ለዘመናት በዘረጋው የሴራ ፓለቲካ የአሜሪካም እጅ እንዳለበት የምናውቀው አሁን አይደለም። ቆይቷል። ነገሩ ሽርፍራፊ ሳንቲም ፍለጋ በየድህረ ገጽና በሶሻል ሚዲያ ላይ ወሬ አራጋቢዎች ከሚዘግቡት ጋርም አይገናኝም። ጥልቅ ነው። አሜሪካ ሊያስቡ የሚችሉ የጥቁር ልጆችን ጭንቅላትን በሚስጢር የምትቀላ ሃገር ናት። አሁን የምናየውንና የምንሰማውን ሁሉ ለማመን የኋሊት ሂዶ የአሜሪካ የስለላ መረብ በሃገራት ላይ የፈጸመውን በደል መፈተሽ መልካም ይሆናል። በዲሞክራሲና በሰላም ስም የስንት ሰው ህይወት ተቀጠፈ? ስንቶችሽ ለስደትና ለመከራ ተዳረጉ? ይህን ማየት የሚሳነው ሃበሻ ራሱን የሸጠ የውጭ ተላላኪና ሃገር አፍራሽ ተልዕኮ የተቀበለ ነው። በየጊዜው በሰርፀ ደስታና በመሰሎቹ የሚለጠፉልን መጣጥፎችም ቢሆኑ ከሚያጠናክሩት የሚንድት ጉዳይ ይልቃል። ይህ ሲባል የብልጽግናው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተለጣፊ ድርጅቶች ችግር ፈጣሪ አይደሉም ማለት አይደለም። እኔ ራሱ ብልጽግና የሚለው ቃል ያስጠላኛል። ሶስት ጊዜ ተበልቶ በማይታደርበት ሃገር መበልጠግ ምኞች ብቻ ነው። የማንም የፓለቲካ ሾተላይ ደጋፊም አይደለሁም። ግን ዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት ሳልል ለሃገሬና ለወገኔ በምችለው ሁሉ በዚህም ቢዚያም አለሁ ብያለሁ እላለሁም። ለሰርፀ የምለው ነገር ቢኖር “ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር” ብለሃል። ግን ለዘላለም የሚኖር ነገር የለም። በህበረት ካልነቃንና ካልሞገትን እንኳን ለዘላለም ልትኖር በዘመንህ ራሱ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ላትኖር ትችላለች። ጠብቀን እንይ! በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share