ይህ ጽሑፍ በዚሁ ርእስ ከተጻፈ ረዘም ያለ ጽሑፍ ተቀንሶ የቀረበ ነው። የተጻፈበት ጊዜ ከአመት በላይ ቢያልፍም የጽሑፍን ፍሬ ሃሳብ በመሠረታዊነት የሚቀይር ለውጥ ስለሌለ እንዳለ ቀርቧል። እንዲያውም ባለፈው አመት ከምናምን የተፈጠሩ ሁኔታዎች በተወሰነ ደረጃ የጽሑፉን ድምዳሜ ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው። ሕወሃት/ትህነግ/ወያኔ ሁለት አማራጮችን ይዞ የተጓዘ ድርጅት መሆኑ የታወቀ ነው። በአንደኛው አማራጭ ማእከላዊ መንግሥትን ተቆጣጥሮ የነበረ እንደመሆኑ ወደፊትም ሊቆጣጠር ቢችል በመሠረታዊነት የተፈጠረበትን አስገንጥሎ የመገንጠል አማራጭ ያልተወና ዝንተዓለም የሚተው ድርጅት እንዳልሆነ ስላስመሰከረ ይህ ጽሑፍ በመገንጠሉ አማራጭ ላይ ብቻ አተኩሯል። (“ገ” ይጠብቃል)
መንደርደሪያ
እንግሊዝ የቀበረው ፈንጂ በዓለም ዙሪያ እየፈነዳ ለጎረቤት ሀገሮች እርስ በእርስ ግጭት ብቻ ሳይሆን ለሀገሮች መፍረስ፣ መከፋፈልና መበታተን መንስዔ እንደሆነ የተባለና፣ በስፋት የተለቀሰበት ጉዳይ ነው። በእንግሊዝ መንግሥት ፀሐይ አትጠልቅም ይሉ የነበሩበትን የመታበይ ደረጃ ለመልቀቅና የኤርትራን የቆዳ ስፋት ብቻ በምታክለው ሀገራቸው እንዲወሰኑ ታሪክ ሲፈርድባቸው፣ ፍርዱን በሰላምና በጨዋነት የተቀበሉ ሳይሆን በረገጡት የምድር ዳርቻ ሁሉ ውሎ አድሮ የሚፈነዳ የነገርና የጭቅጭቅ፣ የጦርነት መንስዔ የሚሆን ፈንጂ ቀብረዋል።
እንግሊዞች ይሄንን የነገር ፈንጂ ለምን ቀበሩ?
ነገ በቀሉ ወደ እነሱ እንዳይዞር፣ ይህም ሃብቱን የዘረፉት፣ የጨፈጨፉት፣ በባርነት የፈነገሉት፣ ያቆረቆዙት ሕዝብ ቢያንስ በወቃሽነት እና በከሳሽነት ጣቱን ወደ እነሱ እንዳያዞር፣ ጣቱን ቃታ ላይ አድርጎ ወንድሙ፣ ጎረቤቱ ላይ እንዲያነጣጥር ለማድረግ
ሌላው በልማት እንዳይደርስባቸው
ተመልሰው መጥተው በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር ሊበዘብዙት እንዲችሉ፣
በአሸማጋይነት ጣልቃ ለመግባት እና ለማራራቅ፣ የራሳቸውን አጀንዳም ለማራመድ እንዲመቻቸው።
እርስ በእርስ እያጋጩ ለመሳሪያና ለእርዳታ ሲል የነሱን ጥቅም የሚያስከብር ወገን ለማግኘት እንዲመቻቸው
ፈንጂዎቹ ምን ምን ዓይነት ናቸው?
እንግሊዞች ነባርና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ቅኝ ገዥዎች ስለነበሩ ከጥቂት ቅኝ ሀገሮች በጦር ሽንፈትና ውርደት ቢባረሩም ከብዙ ቦታዎች ግን ሙሉ በሙሉ በጦርነት ተሸንፈው ውርደት ሳይገጥማቸው በፊት ለመውጣት ሞክረዋል። በፈቃዳቸው የወጡና በቸርነታቸው ነጻነት የሰጡ ለማስመሰልም ብዙ የግብዝነት ድራማ ሠርተዋል። በዚህም በኋለኛው አማራጭ ነጻ የሚወጣውን ሀገር እጣ ፈንታ፣ የሚተዳደርበትን ሕገመንግሥትና ካርታ ሳይቀር በሚፈልጉበት መንገድ ለማጣመም፣ ለመቅረጽ፣ ለማበላሸት ችለዋል። ይህንን አማራጭ ተጠቅመው በለቀቁዋቸው ሀገራት የቀበሯቸው የጊዜ ፈንጂዎች እንዴት ያሉ ናቸው?
አንዱ ፈንጂ ከመውጣታቸው በፊት ቅኝ የያዙትን ሀገር ወዲያው ወይም ውሎ አድሮ ሁለትና ሦስት ቦታ እንዲከፈል በማመቻቸት ነው። እነዚህን ነባር የሃገሪቱ ክፍሎች አንድ ለማድረግ በሚፈልጉና ባዳዲሶቹ ሀገር ኤሊቶች መካከል የማያባራ ውዝግብ፣ ጦርነትና ውድመት ይከተላል። ይህንን ጦርነት አይቀሬ ለማድረግ ካርታውን ስትሰራላቸው የምትከፋፍላቸው አወዛጋቢ በሆነ ድንበር ወይም የተፈጥሮ ሃብት መስመር ላይ ነው። ሕንድን (ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ኔፓል)፣ የመንን ማየት ይቻላል።
ሁለተኛም በቀጥታ ከፋፍሎ ከመሄድ ይልቅ አንድ በሆነ ሀገር ውስጥ በባሕር በር፣ በነዳጅ ምንጭ ወይም በሌላ የተፈጥሮ ሃብት የይገባኛል ውዝግብን ተክለው ይወጣሉ። ይህም የፖለቲካ ኤሊቱን አእምሮ በደህንነት ተቋማቸው አማካኝነት ወይም በሥርዓተ ትምህርቱ መሣሪያነት በማጠብ ነው።
ያስተዳድሯቸው የነበሩትን ሁለትና ሦስት ታሪካዊ አንድነት ያልነበራቸው ሀገሮችን በአንድ ሀገር አጠቃልሎ ነጻነት መስጠት ነው። እነዚህ በጉርብትና ሲቆራቆሱ የነበሩ ሃገራት ሕዝቦች ባንድ ሀገር ውስጥ ለመኖር የጋራ ማንነት ያላዳበሩ በመሆናቸው ቀላል ለማይባል ግጭት ይዳረጋሉ። ናይጄሪያ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናት። ዮሩባ፣ ኢቦና ሃውሳ የተባሉ የተለያየ ሀገራዊ ማንነት የነበራቸውን ሕዝቦች በግድ፣ የአውሮፓ የጦር ድብደባ ተጨምሮበት ናይጄሪያ በሚል ሀገር ውስጥ እንዲጠረነፉ ተገድደዋል።
ይዘዋቸው በነበሩና በአጎራባቾቻቸው ሀገሮች ውስጥ አከራካሪና ያልተካለሉ የድንበር መስመሮችን ሆን ብለው በመተው በጎረቤታሞቹ ሀገሮች መካከል ውሎ አድሮ የሚቀሰቀስ የድንበር ግጭት መፍጠሪያ ሰበብ በማስቀመጥ።
በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ያንድ ቋንቋ ተናጋሪዎችን “ታላቋ ምንትስዬ” የሚል ሕልም አይሉት ቅዠት በኤሊቱ አእምሮ በማንበር ድንበር ዘለል ለሆነ ጦርነት እና የማያባራ ግጭት በመዳረግ። እነዚህም እንደወረርሽኝ የሚዛመቱ ሲሆኑ ታላቋ ሱማልያ፣ ታላቋ ትግራይ፣ ታላቋ ኦሮምያ እኛው ግቢ ያሉ ምሳሌዎች ናቸው። የሶማልያን ብናይ ጣልያን ተሸንፎ እንግሊዝ ኦጋዴንን ከሱማልያ ክፍሎች ጋር ደርባ ባስተዳደረችበት አጋጣሚ ከሞቃዲሾ እስከ ሐረርና ጅጅጋ የሱማሌ ወጣቶችን በማደራጀትና የታላቋ ሱማልያ ሕልም በማስታጠቅ ምሥራቅ አፍሪካን የሁከት ቀጠና አድርገውት ኖረዋል።
በአጠቃላይ ግን ኤርትራን ያስገነጠሉ ባእዳን ኃይላት ( የእንግሊዝ መንግሥት በዋናነት) ልምድ፣ አቅምና ትእግሥት ያላቸው ያሰቡትን ነገር በሰላሣና አርባ ዓመታት ርቀት የማስፈጸም በተሞክሮ የበለጸገ ችሎታ ያዳበሩ ናቸው። ይህንንም የሚያደርጉት የፖለቲካ፣ የወታደራዊና ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማስጠበቅ/ለማስቀጠል ነው።
መግቢያ
ለመንደርደሪያ ይሄንን ካልን እስኪ ከዛሬው ጉዳይ አኳያ በእንግሊዝ የተጠነሰሰውን የታላቋ ትግራይ ሕልም እንፈትሽ። ይህንንም ከኤርትራ በኩል እና ከትግራይ በኩል ብለን በሁለት አቅጣጫ እንክፈለው። እዚህ ላይ ሕወሃት ከፍጥረቱ ጀምሮ በራሱ የፖለቲካ ንድፍ እንዳልተንቀሳቀሰ በግልጽ የሚያመለክተው በለስ ቀንቶት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ሙሉ ኢትዮጵያን (ኤርትራን ጨምሮ ) የመቆጣጠር ያላሰበው ሰፊ እድል የገጠመው ቢሆንም ያንን ማድረጉ የተፈጠረበት ዓላማ ስላልነበር ያንን ወርቅማ አማራጭ ችላ ብሎ በተፈጠረበት እና በተተለመለት ቦይ ሲፈስ ኖሮ የነጻ አውጭ ስሙን እንደያዘ መቀሌ ተመልሶ ቀጣዩን መርሐግብር ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መገኘቱ ነው።
ሀ. የታላቋ ትግራይ ሕልም በኤርትራ በኩል
የኤርትራ ሕዝብ ዋነኛ ታሪካዊ ጠላት ከጣልያንም በከፋ መልኩ የእንግሊዝ መንግሥት ነው። እንዴት? ለሚል ማሳያው
ጣልያንን ወደ ምጽዋ አምጥቶ የቅኝ ግዛት መንግሥት እንዲመሠርት ያመቻቸው የእንግሊዝ መንግሥት ነው
ራስ አሉላ ጣልያንን ዶጋሊ ላይ ድባቅ ከመቱት በኋላ ከሥልጣን እንዲነሱ በማድረግ ጣልያን አሥመራ እንዲገባ መንገድ ያስጠረገለት የእንግሊዝ ሴራ ነው
ከዚህም በላይ አጼ ዮሐንስን የርሱን የእንግሊዝን ጦርነት በውክልና እንዲዋጉ በማድረግ ከሱዳኖች ጋር አጋጭቶ እሳቸው ከማህዲ ሲዋጉ አስመራም እንድትያዝ እሳቸውም እንዲሞቱ መንገድ አመቻችቷል።
ኤርትራ በኢትዮጵያ እገዛ ነጻ እንዳትወጣ ጣልያን ኢትዮጵያንም ጨምሮ ቅኝ እንዲገዛ መንገዱን በመጥረግ ጣልያንን ለወረራ በማደፋፈርና በወረራውም ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የመሣሪያ መግዛት ማእቀብ በመጣል ኢትዮጵያን ያስወረረ እንግሊዝ ነው። (ጣልያንን ማባበል በሚለው ፖሊሲው)
ጣልያን ከጀርመን ጋር በመሰለፉ እንግሊዝ ተጣልቶት ጣልያንን ከኤርትራ እንዲወጣ ካደረገ በኋላ ጣልያን እኖራለሁ ብሎ በኤርትራ የገነባውን ቁጥር ሥፍር የሌለው ፋብሪካ፣ ሕንጻና ሌላም ተቋም ሁሉ ነቅሎ የዘረፈ፣ ተሸክሞ የማይወስደውን ደግሞ በፈንጂ አውድሞ ኤርትራን ያራቆተ እንግሊዝ ነው።
ኤርትራን በገዛባቸው አሥር አመታት ኤርትራ በእስላምና በክርስትያን ለሁለት እንድትከፈል ያለድካም የታተረ እንግሊዝ ነው። በራሱ ሀገር የሌለ የሃይማኖት ፓርቲዎች በኤርትራ እንዲቋቋሙ አድርጓል።
ለአፍራሽ ዓላማው የቆላ ኤርትራን ሕዝቦች ኢትዮጵያን እንዲጠሉ ባጀትና የሰው ኃይል መድቦ ይሠራ የነበረ እንግሊዝ ነው።
ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለማስጠላት ውጤት ያለው ሥራ ሰርቷል።
የታጠቀ ጸረ ኢትዮጵያ ጸረ ክርስትያን ኃይል በቆላ ኤርትራ መሥርቷል
በእንግሊዝ ደህንነት ባጀት የሚንቀሳቀስ ጋዜጣ አሥመራ ውስጥ በመክፈት በሐሰተኛ የብእር ስሞች ኤርትራውያንን በሃይማኖት የሚያናቁሩ ጽሑፎችን በመጻፍ በየቦታው ከፍተኛ ግጭትና እልቂቶች እንዲከሰቱ አድርጓል።
(በነገራችን ላይ ይህ ክዚያ በፊት በኤርትራ እዚህ ግባ የማይባል የነበረ የሃይማኖት ግጭት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ እና እየተባባሰ ሄዶ ኋላ ላይ የኤርትራ ወጣት በጀብሃና ሻዕቢያ ተከፍሎ እንዲተላለቅ አንዱ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል)
እንግሊዝ ኤርትራን ለማፍረስ ለምን ፈለገ?
እንግሊዝ ኤርትራን ማፍረስ የፈለገበት ዋና ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ከሱዳን የቅኝ ግዛቱ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። እንግሊዝ ለመስኖ እርሻ ተስማሚ ነው ያለውን ቆላውን ኤርትራን ከሱዳን ግዛቱ ጋር ለመቀላቀል ከፍተኛ ምኞት ነበረው። መሬቱ የተበላ፣ የተቆራረጠ እና ለእርሻ ተስማሚ አይደለም የሚለውን ደጋ ኤርትራን ደግሞ አይፈልገውም ነበር። ይህን ዓላማውን ለማሳካት በአብዛኛው ክርስትያንና ትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነውን ደጋ ኤርትራ የክርስትያንና የትግሬ አገር ብቻ በማስመሰል ወደ ትግራይ ለመቀላቀል ቆላውን ደግሞ እስላም የሚበዛውን ወደ ሱዳን ለመጠቅለል ከፍተኛ ሥውርና ግልጽ ደባዎችን ሠርቷል። ምናልባትም በሁለተኛ ዓለም ጦርነት ምክንያት አቋሙ ባይዳከምና የዓለም ኃያላን አሰላለፍ ባይለወጥ ኖሮ ይህንን ዓላማ ከ50 አመታት በፊት አስፈጽሞት ነበር።
የእንግሊዝ ኤርትራን የማፍረስ ቁማር አምዶች
እንግሊዝ ኤርትራን ለማፍረስ ከተጠቀማባቸው ስትራቴጂዎች ዋነኛው ጣልያን ሲሸነፍ እንግሊዝ ኦጋዴንን ለመደራደሪያነት ይዞ መቆየቱ ነው። በዚህም ኃይለሥላሴ የኤርትራን ደጋ ወስደው ቆላውን ከተዉለት ኦጋዴንን ሊመልስላቸው ካለበለዚያ ደግሞ ኦጋዴንን ወስዶ ከበርበራ ጋር ሊቀላቅል ያለመ መሆኑ ነው።
ሌላው እንግሊዝ ከሆነለት ኤርትራን ራሷን አትችልም ብሎ በራሱ ሞግዚትነት ማስተዳደሩን መቀጠል ነው።
ሌላው ደግሞ በቆላው ተገንጣይ የእስልምና እንቅስቃሴ በመመሥረት ኤርትራን መገንጠል ወይም ማፍረስ ነው።
ይህ የእንግሊዝ ኤርትራን የመከፈል፣ የማፍረስ እቅድ በዋነኝነት የከሸፈው በሁለት ምክንያቶች ነበር።
የኤርትራ ሕዝብ ሁለት ቦታ ላለመከፈል ባደረገው ከፍተኛ ትንቅንቅ ነው። ብዙ ደም ፈሷል። ይህም በእንግሊዝ አስተዳደር በነበረችው ኤርትራ ይህንን ሃሳብ በመቃወም የተደረገ ነበር። የሕዝቡ ፍላጎት ነጻ መውጣትም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር መቀላቀልን በአንድነት ሆኖ እንጂ ሁለት ቦታ ተከፋፍሎ ወደ ተለያየ ሀገር እንዲመደብ አልነበረም።
ከዚህ በላይ ግን የኃይለሥላሴ መንግሥት በተጫወተው ከፍተኛ ጥበብ የተሞላበት እርምጃ ነው። ይህ ከፍተኛ ጥበብ የተሞላበትና ኤርትራን ከሁለት ከመከፈል ያዳነና ብሎም ወደ ኢትዮጵያ እንድትቀላቀል ያስቻለ እርምጃ ምን ነበር?
እንግሊዝ ኦጋዴንን እንደመደራደሪያ ይዞ በኤርትራ ያሰበው ሀገር ቆረሳ ካልተሳካለት ኦጋዴንን ከሱማሌ ጋር ደርቦ ቅኝ ግዛቱ ለማድረግ የወጠነውን ሴራ ባንድ በኩል የኤርትራ ምኞቱን በሌላ በኩል ሁለት ወፍ ባንድ ጠጠር የመቱበት የኃይለሥላሴ ስትራቴጂ ምን ነበር?
የእንግሊዝ ኤርትራን ሁለት ቦታ የመገንጠል ሴራ እንዴት ከሸፈ?
ዳግማዊ ሚኒልክ የዘመኑን የኃይል አሰላለፍ በውል በመረዳት ኢትዮጵያ ነጻነቷን የምታቆይበትን ብልህ የዲፕሎማሲያዊና የሚሊታሪ ጨዋታ መጫወት እንደቻሉት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም የዛሬ ሰማንያ ዓመት ይህንን የዘመኑን ኃያል የእንግሊዝ ድርብ ተንኮል ያመከኑት የወቅቱን የኃይል ሚዛን ትክክለኛ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ እርምጃ በመውሰድ ነበር።
በአጭሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ያን ጊዜ ያደረገው ነገር በኦጋዴን የነዳጅ ማውጣት ኮንሴሽንን ለአሜሪካን ኩባንያ ለሃያ አምስት አመት መስጠት ነበር። ይህ ኩባንያ (ሲንክሌር ኦይል) ነዳጁን ሲያወጣ ኢትዮጵያ በራሷ ወደብ ብታጓጉዘው ለኢኮኖሚም ለደህንነትም የተሻለ አማራጭ ስለሚሆን የአሜሪካ መንግሥት የኤርትራ ወደቦች በእንግሊዝ፣ በጣልያን ወይም በተገነጠለች ሀገር ሥር ሳይሆን በኢትዮጵያ እጅ እንዲቆዩ በዩናይትድ ኔሽንም ሆነ በማንኛውም በኩል ይሄንን የሚያመቻች ተጽእኖ እንዲያደርግ ኩባንያው የአሜሪካን መንግሥትን ይጠይቃል። የሲንክሌር ፕሬዚዳንት ለውጭ ጉዳይ ሚንስትር (Secretary of State) በማመልከት ማለት ነው። በዚህም እንግሊዝ አሥር አመት የማሰነችበት ኤርትራን የመክፈል ወይ የመገንጠል ሃሳብ ውድቅ ሆኖ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር ልትዋሃድ ችላለች።
አንባቢ ሲሰማው ከኖረው የኤርትራ ታሪክ ጋር ስለማይስማማ ይህንን አቋም ውድቅ ከማድረጉ በፊት በማጣቀሻው ያሉትን መረጃዎች እንዲመረምር በትሕትና አሳስባለሁ። ይህንን ውሳኔ እንግሊዝ እየጎመዘዛት የተቀበለችበት ምክንያት በሁለተኛ ዓለም ጦርነቱ ሁለንተናዊ ድቀቷ ምክንያት እንግሊዝ ኮከቧ እየተነሳ የመጣችውን የአሜሪካንን ውሳኔ የመቀልበስ አቅም ስላልነበራት ነው።
እንግሊዝ ያቋቋመችው የኤርትራ ተገንጣይ እንቅስቃሴም ሆነ የትግራይ ትግሪኝ (ታላቋ ትግራይ) ጥንስስ ከፌደሬሽን መመሥረትም ሆነ መፍረስ የሚቀድም መሆኑን አንባቢ ልብ ይበል። የእንግሊዝን የትግራይ ትግሪኝ ሃሳብ በዋናነት ያራምዱ የነበሩት በእንግሊዝ ደህንነት ባጀት የሚንቀሳቀሰው የመጀመሪያው የትግሪኛ ጋዜጣ እና የስለላ ቡድኑ ምልምል የነበረው የጋዜጣው አዘጋጅ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ነበሩ። ወልደ አብ ወልደ ማርያም ከትግራዋይ ወላጆች የተወለዱ ነበሩ። ይህ የትግራይ ትግሪኝ ሃሳብ ነው ግዘፍ ነሥቶ በአመራር ደረጃ ቁልፍ ቦታ የሚጫወቱ የሕወሃትና የሻዕቢያ መሪዎች ይህንን ሃሳብ የተቀበሉ፣ ወይም ለዚህ ሃሳብ እውን መሆን እንቅፋት የማይፈጥሩ እንዲሆኑ የረቀቀ ሥራ ሲሠራ የኖረው።
ሻዕቢያም በአብዮቱ መባቻ የኢሕአፓን ጦር ኤርትራ ከአመት በላይ አግቶ የሕወሃትን አስኳል አዘጋጅቶ ትግራይ የለቀቀበት ምስጢርም ይሄው ነው። የሕወሃት መሪዎች ግብ ትግራይን በመሬት፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ አጠናክረው፣ የተቀረውን ኢትዮጵያን ደግሞ አደህይተውና አፈራርሰው ከኤርትራ ጋር ታላቋ ትግራይን መመሥረት እንደሆነ ከሰላሣ አመታት በላይ የተባለ የአደባባይ ምሥጢር ነው። ይህንም የአስኳሉን ዓላማ ይቃወማሉ የተባሉ አመራሮች ተፈላጊነታቸው ሲያበቃ እየተወገዱ አስኳሉ ብቻውን ሁሉንም ነገር ሊቆጣጠር በቅቷል። ዘመንም ደረጃ በደረጃ በዚህ ጉዞ ላይ እንዴት እንደገሰገሱ ምስክርነቱን እየሰጠ እያለፈ ነው። ይሄ ስንኩል ዓላማ ግን በቆራጥነት የእድሜና የሕይወት መሥዋእትነት የከፈለው የኤርትራና የትግራይ ወጣትም ሆነ ልጆቻቸውን የገበሩት ቤተሰቦች የተስማሙበት ወይም የደገፉት ነው ማለት አይደለም። ከነማወቃቸውም ያጠራጥራል። ይልቁንም ነጻነት ለሚባል ሃሳብ ነው የተሰዉት። ሌላ ቀርቶ ከመሪዎቹም እንኳን ከሲሶ በላይ ይሄንን ዓላማ ይደግፉ ነበር ለማለት ያስቸግራል። ይሁንና ይህንን ዓላማ የማይደግፉት ወይም በግልጽ የተቃወሙት ተገድለዋል፣ ከሥልጣን ተገፍተዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰድደዋል።
እዚህ ላይ ኤርትራ ስንል የትኛዋን ኤርትራ ነው ትግራይ ትግሪኝ ታሳቢ ያደረገው? ብለን ልንጠይቅ የግድ ይለናል። የትግራይ ትግሪኝ ዓላማ አፍሪካዊ ሳይሆን አውሮፓዊ መነሻ ያለው እንደመሆኑ የዳበረች ትግራይ የምትዋሃደው ዛሬ ከምናውቃት ኤርትራ ጋር አይደለም። ይህ ቢሆን የእንግሊዝን ዘመን ተሻጋሪ ምኞት ያጨናግፋል። ይልቁንም ትግራይ ከክርስትያኑ የኤርትራ ክፍል ጋር ምናልባትም ወደቦቹን ጨምራ እንድትዋሃድ እንጂ ቆላ ኤርትራን እንድትጨምር አይደለም ኦሪጂናሉ እቅድ። የአካባቢውን ኑባራዊ ሁኔታ ካየንም ይህንን የሚደግፍ ነው።
ለ. የታላቋ ትግራይ ሕልም በትግራይ በኩል
ታላቋ ትግራይን ለመመሥረት የሥነ ልቡና ችግር እንዳይፈጠር የመሪዎቹ ቤተሰባዊ የጎሳ ጥንክር ታስቦበት በተመረጡ አመራሮች የበላይነት የተቋቋመ ድርጅት ነው ሕወሃት። ከዚህ ጥንቅር ውጭ ያሉ አባላት የነበሩ ሲሆን እነዚህ አባላት በጊዜ እና አገልግሎታቸው ሲያበቃ በተለያየ ስልት ገለል ተደርገዋል።
እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ የትግራይ ታጋዮች ትግል በሕወሃት አሸናፊነት ቢጠናቀቅም በገንጣይም ሆነ በኢትዮጵያ አንድነት ጎራ በተደረጉት ትግሎች ብዙ የትግራይ ልጆች ግንባር ቀደም መስዋእትነት የከፈሉ መሆናቸውን ታሪክ መዝግቦት ያለፈ ሐቅ መሆኑ ነው።
ወደ ፍሬ ሃሳቡ ስንመለስ ትግራይ ከኢትዮጵያ ያለ ችግር ለመገንጠል የሚያስፈልጓትን እርምጃዎች ሕወሃት ደረጃ በደረጃ ሲያስፈጽም መቆየቱን እንመለከታለን።
በትግራይ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ትግሎች እንዳይካሄዱ መዋጋት
በትግራይ ኢትዮጵያን የሚያስቀድሙ ግለሰቦችን እና ቤተሰቦችን ማደን፣ ማጥፋት፣ ማዳከም
ኤርትራን ማስገንጠል (በፕሮፓጋንዳ፣ በጦርነት፣ በዲፕሎማሲ፣ በፋይናንስ)
ኤርትራን ማዳከም
የተቀረችውን ኢትዮጵያን ማዳከም፣ መከፋፈል፣ ለታላቋ ትግራይ እንቅፋት እንዳትሆን ማድረግ
ትግራይን በመሬትና በገንዘብ ዘረፋ፣ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በማሕበራዊ ኃይል ማጠናከር
የኤርትራ ወደቦች ለምሳሌ አሰብ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይካለሉ መታገል።
የሱዳንን ጥቅም በማንኛውም መልኩ ማስቀደም (የድንበር፣ የግድብና ሌሎችም ሱዳን ተኮር እንቅስቃሴዎች)
ትግራይ ውስጥ ለዚህ ዓላማ ከተቋቋመው ከሕወሃት ሌላ የፖለቲካ ኃይል እንዳይፈጠር፣ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ።
ለታሳቢው ውሕደትም እንቅፋት እንዳይሆን በትግራይና በኤርትራ መካከል ያለውን ድንበር መሬት ላይ እንዳይካለል በተሳካ ሁኔታ ታግለዋል።
ታላቋ ትግራይ እንደ ሕወሃት ሃሳብ የምትመሠረተው በትግራይ የበላይነት ሥር የኤርትራን ትግሬዎች በማካተት ነው። ለዚህም አስፈላጊው የኢኮኖሚ በላይነት ነው በሚል ያለመታከት በዘረፋ አቅማቸውን ሲያዳብሩ ቆይተዋል።
ይሄ የትግራይ ትግሪኝ ዓላማ ምን ያህል የተፈጻሚነት እድል አለው?
አሁን የምሥራቅ አፍሪካን በጎሳና በሃይማኖት ፍጅት ለማፈራረስ አስፈላጊው መደላድል ሁሉ ተሠርቶ ያለቀበት ወቅት ነው። በተለይም በሃይማኖት ሽፋን አረቡን አለም ያተራመሱት ምዕራባውያን እና የአረብ ወኪሎቻቸው ከቀይ ባሕር ማዶ ወደ ኢትዮጵያ እያማተሩ ያሉበት እንደሆነ ዳር ዳርታው ያመላክታል። የተዋሕዶ ሃይማኖት ላይ ከአራት መቶ አመታት በላይ የዘመቱት ምዕራባውያንም ለዚህ የጥፋት ተግባር እንደ አክራሪ እስልምና የተመቸ መሣሪያ አያገኙምና ይህንኑ ስለው ሃይለኛ ጅራፍ እንደሚሰነዝሩ መጠበቅ ይቻላል።
ታድያ በዚህ የሃይማኖት ግጭት ጠርዝ በሚረግጥብት ሁኔታ ክርስትያኑ ኤርትራዊ ከእልቂት ለመዳን ከትግራይ ጋር ለመዋሃድ አይቸገር ይሆናል። የኤርትራ እስላሞች ግን የሃይማኖት አክራሪነት ወይም ጦርነት በተነሳበት ሁኔታ ማጆሪቲ ክርስትያን ወደ ሚሆነው የኤርትግራይ መንግሥት የመካተት ፍላጎት አይኖራቸውም። በዚህም መሠረት ትግራይ በተገነጠለች ማግሥት የተገነጠለችበት ዓላማ ያሰጋቸው የኤርትራ እስላሞች ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደሚጀምሩ መገመት ይቻላል። የመሳሪያና የዲፕሎማሲ ድጋፍን ደግሞ ደጉ የእንግሊዝ መንግሥትም ሆነ የተለመዱት አረቦች በተለይ ግብጽና ሱዳን የሚነፍጓቸው አይሆንም። ኤርትራ በሙስሊም ክርስትያን መስመር ትሰነጠቃለች ማለት ነው። ትግራይ ስትገነጠል የኤርትራ ፍጻሜ ይህንን ይመስላል።
ከመበጣጠስ የሚገኝ ጥንካሬም ስለሌለ ለአጠቃላዩ የምሥራቅ አፍሪካ ደሃ ሕዝብ የከፋ እጣ ወደቀበት ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ላይ ባጠቃላይ፣ በክርስትያኑ ሕዝብ ላይ ደግሞ በተለይ የተደገሰውን የእልቂት ድግስ ፈጣሪ ያምክንልን። እነዚህም አፍሪካን ለመውረስ የማይታክቱ ባእዳንን በዚያው በየሀገራቸው ያስታግስልን።
* ፍጻሜ = እጣ ፈንታ፣ እድል፣ መጨረሻ ወይም ማብቂያ የሚሉት ትርጉሞችን ያዘለ ነው።
**ከግብጽ እና ክሱዳን ጀርባ እንግሊዝ እንዳለች ቀድሞም የቅኝ ገዥያቸው እንደነበረች ብዙ ሰው እየተረዳው የመጣ ነው። በግብጽ ከፍተኛው ኢንቨስትመንት የእንግሊዝ ሲሆን ከፍተኛው እርዳታ ደግሞ የአሜሪካ መሆኑ የተባለለት ነው። ለግብጽ ሲያደሉ “ጥጃ ጠባ ሆድ ገባ” በመሆኑም ጭምር ነው። ሌሎቹም አረቦች እስልምናን በማስፋፋት ረገድ የነዳጅ ብራቸውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢያውሉትም እነዚህ ሁሉ ሀገሮች በተለያየ መንገድ የእንግሊዝ አሻንጉሊት በሆኑ የቁጩ ልዑላንና መሪዎች የሚመሩ ስለነበሩ በዚያ ቦይ እንዲፈሱ ተመቻችቷል። ማስታወስ የሚገባን የፈረሰውን የኦቶማን ቱርክ ኤምፓየር ወራሽ ሆና ያስተዳደረችና የዛሬውን የአረቦች ሀገሮች ፖለቲካዊ ካርታና ብዙ የፉገራ “ነጻ” የአረብ መንግሥታትንም የፈጠረች እንግሊዝ መሆኗን ነው።
ዋቢ ጽሑፎች
https://www.nytimes.com/1945/09/07/archives/ethiopia-concedes-her-oil-to-sinclair-50year-grant-of-exclusive.html
https://www.salon.com/2007/04/24/ogaden/
http://content.time.com/time/subscriber/printout/0,8816,854515,00.html#