ደሴ እንደ ስታሊንግራድ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

dessie ደሴ እንደ ስታሊንግራድ  (ከአሁንገና ዓለማየሁ)ጦርነቶቹ ብዙ ቦታዎችና ውጊያዎችን ቢያካትቱም የሚጠሩበት መለያ ስም ከአንድ ወሳኝ ቦታ ጋር ተያያዥነት አለው። አድዋ፣ ማይጨው፣ ካራማራ በመባል ይታወቃሉ በተለምዶ። በአርባ በአርባ አመት ልዩነት የተደረጉ ነበሩ።

በካራማራ ስም በሚጠራው የሶማሌ ወረራ ጊዜ የሲያድ ባሬ ጦር ድሬዳዋ ከተማ ገብቶ አየር ማረፊያው ድረስ ዘልቆ ነበር። የጨበጣ ውጊያ ተከስቶ የኢትዮጵያና የሶማልያ ሠራዊት በመቀላቀሉ፣ “አየር ማረፊያውን ከሚቆጣጠሩት ይልቅ ካስፈለገ እኛንም ወገኖቻችሁን በአየር ውጊያ አብራችሁ ደምስሱን” በሚል ቆራጥነት የምድር ጦሩ  የተዋጋበት አኩሪ የመስዋእትነት ገድል ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ የሚያስደንቀው ውጊያው ከወታደራዊ የጨበጣ ውጊያ አልፎ የድሬዳዋ ሕዝብ ያለውን መሳሪያ ብረታ ብረት ድንጋይና ዱላ ሳይቀር ይዞ ወጥቶ ከጠላቱ ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ የተናነቀበትና የወረራው ማእበል ለመጀመሪያ ጊዜ በብቃት የተመከተበት ክስተት ነበር። በዚህ መልክ የተመከተው የሶማልያ ወራሪ ጦር እግሩን ነቅሎ እስኪፈረጥጥ ድረስ ተቀጥቅጦ ሲባረር ሕንድ ውቅያኖስም ያልተጨመረው በአሜሪካና ወዳጆቿ እዬዬ እና የኢትዮጵያ ሠራዊት ድንበሩን እንዳያልፍ በተደረገ ዛቻም ጭምር ነበር።

በዓለም ታሪክ እንዲህ ቤት ለቤት ደጃፍ ለደጃፍ ሰፈር ለሰፈር በተደረገ ውጊያ ያንድን ግዙፍ ጦርነት መልክ በመለወጥ ዝነኝነት ያተረፈችው የቀድሞዋ የስታሊንግራድ ከተማ ናት። ጦርነቱ አምስት ወር ነበር የፈጀው። በቀዝቃዛው ጦርነት የፕሮፓጋንዳ ማእበል ታሪኳ ተደፍቆ ብዙ አይዘመርላት እንጂ የሂትለር ናዚያዊ ቅስም የተሰበረበት ወሳኝ ውጊያ ሆሊውድ አብዝቶ እንደሚቀደደው ሳይሆን ሶቪየት ዩኒየን ውስጥ በስታሊንግራድ የተካሄደው አስደማሚ ተጋድሎ ነበር። ከስታሊንግራድ ድል በኋላ በተከታታይ አሥር ድሎች ተመዝግበው ሂትለርም ከነቅዠቱ ተቀብሯል። ዘመኑ የጠየቀውን የነጻነት ዋጋ የከፈሉት የስታሊንግራድ ነዋሪዎች ጀግንነትም ሲዘከር ይኖራል።

ሂትለር ስታሊንግራድ ላይ የተሟሟተበት አመክንዮ ብዙ ስትራቴጂካዊና ፕሮፓጋንዳዊ እሳቤዎችን የያዘ ነበር። ከደሴ ኮምቦልቻ ጋር አንዳንድ ገራሚ ተመሳሳይነት አለው። በሶቪየት በኩል ደግሞ  የስታሊንግራድን አስደናቂ ተጋድሎ እና የስታሊንን ከተማዋን ላለማስያዝ ያሳየውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ከተማው በስሙ መሰየሟን እንደ አንድ ታላቅ ምክንያት የሚያነሱ ጸሐፍያን አሉ።  ዐቢይ አህመድ የማሳ ጉብኝቱን ትቶ በሙሉ ኃይሉ ለደሴ እንዲደርስላት ስሟን በጊዜያዊነትም ቢሆን ዐቢይግራድ ወይም በሻሹካ ማለት ያስፈልግ ይሆን  ዛሬ ስታሊንግራድ ቮልጋግራድ ትባላለች። ስታሊን ሥልጣኑን እና ሩሲያን መታደግ ብቻ ሳይሆን እኛንም ጀርመንኛ ከመናገር አድኖናል። ያውስ ለዘር ብንተርፍ አልነበር?

በነገራችን ላይ ሂትለር ስታሊንግራድ ስትያዝ (ከተያዘች) ወንዶቿ በሙሉ እንዲገደሉ፣ ሴቶችና ልጆች በሙሉ እንዲፈናቀሉ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። የመንፈስ ልጁ ደብረ ጽዮንስ ስለደሴ ነዋሪዎች እጣ ፈንታ ምን ዓይነት ምስጢራዊ ትእዛዝ አውርዶ ይሆን?

ስታሊንግራድን ስናስብ በሕወሃት ፊታውራሪነት የሚደረገውም ወረራ በወሳኝነት ደሴ ላይ የመቀልበስ እድል አለውና ታሪክ የደሴን በሮች እያንኳኳ ይገኛል። ከአራቱ ማእዘን ተፈናቅሎ፣ በገዛ ቀዬው ባይተዋር የተደረገው እና እያለቀሰ ደሴ የገባውን የወሎ ሕዝብ እግዚአብሔር እንደሚረዳው ጥርጥር የለውም።

 

1 Comment

  1. አሁን ገና አለማየሁ ጥሩ ዘግበሀል ፈቃድህ ቢሆን ትንሽ ፈታ ብታደርገው መልካም ነበር። ስታሊንግራድ ሁለት ጉልበታም ዝሆኖች የተገናኙበት ነበር ።አለም ከዛ በፊትም ሆነ በሗላ አታየውም ነው የሚባለው። መሪው መሪ ነበር ህዝቡም ህዝብ ነበር። የጦር መሪዎች የጠላት ሀይል አይሏል ምን እናድርግ ብለው ንግድ ስታሊን ቴሌግራም ቢልኩ እኔም ካለሁበት ነቅነቅ አልልም አንተም ባለህበት ሳትነቃነቅ መክት የሚል ትእዛዝ ከመሪው ቢሰማ ተዋጊው ከመሪው ባገኘው ሞራል ጠላትን መልሶ እናቱ ጉዋዳ ቀብሮታል። ባንጻሩ የኛ መሪዎች በስንት መስዋእትነት የተገኘው ድል ላይ ሲያላግጡ የሆነውን አይተኸዋል። ስታሊንግራድ ላይ የተሳተፈ ወራሪ በህይወት የተረፈው የባቡር ሀዲድ ሰርቶ እዛው ማጠናከሪያ ሁኖ ቀርቷል።

    መከላከያ ሚኒስትራችን ዶር አብረሀም የጠሚኒስተሩ አማካሪ አርከበ እቁባይ የሰላም ሚንስትር ታየ ደንዳ የህዳሴው ሚኒስተር በለው አረጋዊ በርሄ በሆኑበት አገር ኢትዮጵያን ከጠላት ማጽዳት አስቸጋሪ ነው ሽመልስ አብዲሳን ከግምት ስብከት ማለት ነው።
    በስታሊንግራድ ጦርነት ሰርጎ ገብ አይታሰብ በደሴው ጦርነት አንዳንድ ቦታ አዋጊው ህወአት ነበር።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.