የአፍሪካ የማያባራው ድህነት የሚዘወረው (የሚሽከረከረው) በአውሮፓና በአሜሪካ መንግሥታት አንጎል ውሥጥ ነው

መኮንን  ሻውል  ወልደጊዮርጊስ 

አፍሪካ ለምን ደሃ ሆነች የሚል ጥያቄ በዋነኝነት የሚነሳው በራሷ በህዝቦቿ ነው ።  በድሀ ህዝቦቿ ። የበለፀጉት አገሮች መንግሥታት አፍሪካ ለምን ደሀ እንደሆነቸ ሥለሚያቁ ይህንን ጥያቄ አያነሱም ። ከምር ተነሥቶ የመወያያ ርእስ እንዲሆንም አይፈልጉም ።

አፍሪካ በድኽነት አረንቋ ውሥጥ ዳካሪ የሆነችው በአሜሪካ ና በአንዳንድ የአውሮፖ አገራት መንግሥታት ያልተቋረጠ ብዝበዛ እንደሆነም አያምኑም  ።

አፍሪካ  እሥከዛሬ  ከድህነት  ያልተላቀቀችው ፣ ባልተቋረጠው የአሜሪካ ና የአውሮፓ ቱጃሮች ብዝበዛ እንደሆነ ግን ይታወቃል ። የአፍሪካ ብዝበዛ እንዳያበራ ዛሬም የሚጥሩት ፣የብዝበዛው  ፈጣሪዎች የአሜሪካና የአውሮፓ ቱጃሮች የሚመሯቸው ኃያላኑ መንግሥታት ናቸው ።  የአፍሪካውያኑ አሻንጉሊት መንግሥታትም ለብዝበዛው ቀንደኛ ተባባሪዎች ሆነው እናገኛቸዋለን ።

የአፍሪካውያኑ ፣  ድህነት ና የድህነት ሰቆቃ ለኃያላኑ መንግሥታት ብዝበዛ የተመቸ በመሆኑ ፣ የአፍሪካ ”  ህዝብ  ለምን ዘላለለም አለሙን ፣ በችግር ና በችጋር እየተሰቃየ አይኖርም  ! ለምን የአፍሪካ ህፃናት   በምግብ እጦት የተነሳ እንደቅጠል አይረግፉም  ?!   ለምን ህመምተኞች መድሀኒት አጥተው ተሰቃይተው አይሞቱም  ?! ለምን ዘላለም አለማቸውን ንፁሕ የመጠጥ ውሀ ና የኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት አጥተው  ከበሽታና ከድቅድቅ ጭለማ ጋር ተወዳጅተው አይኖሩም !? …” በማለት  የአፍሪካውያንን ሰቆቃ ባላየ በማለፍ  ብዝበዛቸውን  ያቀለጥፋሉ እንጂ  ፣ በድህነት እንዲኖር ለፈረዱበት አፍሪካዊ ቅንጣት ያህል ደንታ የላቸውም ።

የአውሮፓ ና የአሜሪካ መንግሥታት ፣ለአፍሪካዊያን ደንታ የሌላቸው ፣    የአፍሪካውያን ሰቆቃ የእነሱ ቱጃሮች ዶላር መሰብሰቢያ በመሆኑ ብቻም ሳይሆን ፣ አቅመ ቢሥ የሆነች አፍሪካ ለብዝበዛ ሥለምትመች አኽጉሪቱ ያለከልካይ ጥሬ ሀብቷ ይበዘበዝ ዘንድ ፣ በድህነት የተነሳ ራሶን መከላከል የማትችል አቅመ ቢስ መሆን አለባት ከአቅመ ቢስ ድኽነትም   እንዳትለቀቅ  በኃያል ጉልበታቸው ተጭነው በኃይል በመያዝ አድኽይተዋታል  ። ለአፍሪካ ሰጥን የሚሉት ብድር ባርያ የሚያደርጋት እንጂ የሚያበለፅጋት እንዳይደለም እየታየ ነው ። ምክንያቱም ዛሬ ታይቶ ነገ የሚጠፋ መሠረተ ልማት ላይ የሚውል ነውና !

እንደሚታወቀው ፣ የአሜሪካ ና የአውሮፓ መንግስታት ፣ በእጅ አዙር ለሚያሽከረክሩት ቱጃሮች ብዝበዛ አፍሪካ እንድትመቻች ሲሉ በእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር ጭንቅላቱ በዶ የሆነ ፣ በጠመንጃ የሚያምን በጥባጭና ያለመረጋጋት ፈጣሪዎች   ወኪሎቻቸውን ሰይፍ አሲዘው በህቡና በግልፅ አሰማርተዋል ።

እነዚህ ሰይፍ ያሥታጠቋቸውን አራጅ  በጥባጮች ፣ በየአፍሪካ አገሩ ፣ በፖለቲካ ፓርቲ ወይም በነፃ አውጪ ሥም ፈጥረዋል ። ነፃ አውጪ ምናምን እያሉ ።

እነዚህንም  ጥቅማቸው የሚነካ ሲመሥላቸው ሰይፍ እንዲያነሱ በሥውር ግንኙነት መረባቸው ያዟቸዋል  ። እናም ብዝበዛን የሚቃወሙ መሪዎች ሲከሰቱ ለነዚህ አጥፊ ቡድኖች  ይጥፋት መመሪያ ይሰጣሉ  ። ባዳዎችና ከሆድ ሌላ ህሊና የሌለቸውም ፣ የአሸባሪነት ሚናቸውን በህቡ በተቀናጀ ሤራ በማካሄድ የአገራቸውን መንግሥት እጅ በመጠምዘዝ በቱጃሮቹ መንግሥታት መዳፍ ውሥጥ  እንዲገባ  ያደርጋሉ ። ( ልብ በል ፣ ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ብቻ  ሱዳንን አተረማምሰው ደ/ሱዳን የፈጠሩ እነሱ ናቸው ። ኤርትራን ከኢትዮጵያ የለያዩትም ህነ  ሱማሊያን በውክልና ጦርነት ያሾቋት ቱጃሮቹ  የአሜሪካ ና የአውሮፓ መንግሥታት  ናቸው ። )

የአሜሪካ መንግሥት በአይጠረቄ ና ጨካኝ ቱጃር ነጮች የሚመራ መንግሥት ነው ። (አንባቢ ሆይ ፣ የአሜሪካ 98% ዜጎች ጨዋና ዴሞክራሲን አጥብቀው የሚሹ ፣ ጭቆና እና ጨቆኞችን ተፀያፊ እንደሆኑም አትዘንጋ ! )

አንዳንድ የአውሮፓ መንግሥታትም የአሜሪካንን የብዝበዛ መንገድ እንደሚከተሉ  ይታወቃል ። እናም አፍሪካ ደሃ ያደረጋት ዋነኛው ምክንያት በቀላል ና በጥቅል አማርኛ  የእነዚህ ቱጃር  በዝባዥ መንግሥታት መዥገር ና ትሆንነት ደምዋ እየተመጠጠ   መሆኑንን ልብ በል ።

ከዚሁ ጋር በተጓደኘ ደግሞ የአፍሪካ ድህነት ና ኋላቀርነት መንሥኤ ፣ በእያንዳንዱ የአፍሪካ መንግሥታት ዜጎች መካከል ፤  አንድነት ፣ ፍቅር ና ህብረት ያለመኖር ደግሞ ሌላው የአፍሪካ ድህነት መንሥኤ ነው ።

አፍሪካዊያን የዘውግ ፣ የነገድ ፣ የጎሣ፣ የቋንቋ ፣ የኃይማኖት አንድ ያለመሆን፣ ወደ  ግጭትና ያለመግባባት እንዲወሥዳቸው በቅኝ ገዢዎቻቸው በእጅጉ ተሰርቷል ።  ደም በመቃባት ቂም  እንድያያዙ እሥከ 20ኛው  መ/ ክ/ዘ በቅኝ ገዢዎቻቸው ያለሰለሰ ጥረት ተደርጓል ።   ዛሬም በሥልጡኑ 21 ኛው ክ/ዘ ይኸው ሸር በአንዳአንድ አፍሪካ አገሮች ገቢራዊ ሲሆን እናስተውላለን ። ( የኢትዮጵያን የዘውግ ና የቋንቋ ፖለቲካ መንስኤና ያደረሰውን ጥፋት መርምር ። )

በአፍሪካ አገሮች የእርስ ፣ በእርስ ያለመግባባት እየከረረ የሚመጣውም ከቱጃሮቹ የአውሮፓ በጥቅምና የአሜሪካ መንግስታት ጋር ያበሩ የአንድ ዘውግ ኢሌቶች በውክልና  በሚፈጥሩት የእርስ በእርስ ግጭት ነው ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሁለቱ ድርጅቶች ጥምር መንግስቱ ሊመሰረት ይችላል። ( በኤርሚያስ ለገሰ)

አንዱ ዘውግ ወይም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ዘር ብቻ    ለሥልጣን እንዲበቃ በማድረግ  ሌላው ዘውግ ወይም ቋንቋ ተናጋሪ  የበይ ተመልካች ወይም ፍርፋሪ በሊታ በማደረግ የማያባራ የእርስ በእርስ እልቂትን የሚፈጥሩት እነዚህ እጃቸው ረዢም የሆነ የአሜሪካ ና የአውሮፓ ቱጃሮች ናቸው ። ( ለእነሱ ሁሉም ነገር ሸቀጥ ነው ።  በሰው ህይወትም ይሸቅጣሉ ። )

እነዚህ ቱጃር መንግሥታት ለደሀው አፍሪካዊ ቅንጣት ያህል ርህራሄ የላቸውም ።ያቋቋሟቸው አሻንጉሊት መንግሥታት  ቀስ  በቀስ የብዙሃኑ ህዝብ ንቃተ ህሊና ጎልምሶ እንቢ ባርነት በሚል ፤ ለነፃነት ፣ ለፍትህ ፣ ለእኩልነት እና ለጋራ ተጠቃሚነት በተነሳ በተባበረ የህዝብ ክንድ  ከወንበራቸው ሲገፈተሩ ፤ በጠመንጃቸው እና በእሥር ቤቶቻቸው ተመክተው ሲበዘብዙ የኖሩ መሪዎች እግሬ አውጪኝ ብለው ወደእነሱ አገር እንደሚፈረጥጡ  ያውቃሉ  ። ቶሎ ብለው ካልፈረጠጡ በሰፈሩት ቁና ተሠፍሮላቸው በተራቸው  ወደ እሥር ቤት እንደሚወረወሩ ያውቃሉ ።

በህዝብ ና በአገር ሥም ምሎ ና ተገዝቶ መንበሩን የያዘው ወይም በእነሱ እግር የተተካው መንግሥትም ተመሳሳይ የአሻንጉሊት ሚናውን እሥከጊዜው  እየፈፀመ  በመንበሩ የሰነብትና እርሱም በተራው ለሌላው በዝባዥ ና አሥበዝባዥ ተራውን ይለቃል ። ይህንን የውድቀት ድግግሞሽ በአሜሪካ እና በአውሮፓ መንግሥታት  የሚደገፈው ቱጃር ለብዝበዛው ሲል        ይፈልገዋል ና በየዓመቱ በዝባዥ መንግሥታት በአፍሪካ መንግሥታትት መንበር ቢቀያየሩ ደንታ የለውም ።

እናም በሙሥና የገነኑ ፣ የአገርን ገንዘብ እየዘረፉ ወደ አውሮፓና አሜሪካ የሚያሸሹ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአፍሪካ እንዲበዙ በሥውር ያለመታከት ሴራውን ይጎነጉናል  ።

የቱጃር ዘጎቻቸው ጥቅም ጠባቂ የሆኑት የአሜሪካ ና የአውሮፓ መንግሥታት ፤  ለእነሱ አገር  ት/ቤቶች ፣ ዩኒቨርስቲዎች ፣ የህክምና ተቋማት ፣መዝናኛ ሥፍራዎች ረብጣ ዶላር የሚከፍሉ ሌባ የአፍሪካ ባለሥልጣናትን ከመደገፍም አልፎ ክብርና እውቅና ይሰጣሉ ። ጥቅሙን ብቻ የሚያሳድደው የአውሮፓ ና የአሜሪካ ቱጃር ከመንገሥታቱ ጋራ እጅና ጓንት በመሆኑ ለአፍሪካ  አንባገነን መሪዎች የሐሰት ፕሮፓጋንዳ በማዘጋጀት የገፅታ ግንባታ በሚዲያው የሚያደርጉላቸውም ለግል ጥቅማቸው ቀጣይነት ሲሉ እንደሆነ ከዚህ እውነት እንረዳለን  ።

ከብዝበዛው በተቃራኒ የቆሙና የአገራቸውን ጥቅም አሥቀድመው ለመላው ህዝብ ብልፅግና እንሰራለን እንጂ አምሥት ሣንቲም አንሰረቅም የሚሉ የህሊና ጥንካሬና የሞራል ልእልና ያላቸውን መንግሥታት  ደግሞ  ፤ በተቻለ ፍጥነት ከሥልጣን የሚወገዱበትን መንገድ  ፣ ቀደም ሲል ለዚሁ ተግባር ከዘጋጃቸው ፣ በብር ተገዢ ከሆኑ ፣ የውሸት የነፃ አውጪ ና የዘውግ ሥም ከሰጣቸው ቡድኖች ጋር ይቀይሳል ። አገርንም ተከታታይነት ባለው ትርምሥ ውሥጥ በመክተት የዜጎችን ሠላም ያደፈርሳል ። በመጨረሻም ዜጎች ደካማ መንግሥት እንዳላቸው በመቁጠር ፣ ኃቀኛውን መንግሥት የሰጠንህን ኃይል መጠቀም አቅቶህ እኛን የምታሥጠቃን ከሆነ ወረድ ይሉታል ። እናም ይወርዳል ። ህዝቡም ወደለመደው ድህነት ውሥጥ ይዘፈቃል ። የአሜሪካ ና የአውሮፓ መንግሥታት ደግሞ ወደብዝበዛቸው ።

በአጭሩ ፣ የአፍሪካ የማያባራው ድህነት የሚዘወረው ( የሚመራው )    በአውሮፓ ና አሜሪካ መንግስታት  አንጎል ውሥጥ ነው ። ጅራቱ (ተሣቢው ) ደግሞ አፍሪካ ውሥጥ  __ በታላቅ የአእምሮ ድህነት ውሥጥ ተወሽቋል ፤  ማለት እንችላለን   ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.