ይህንን አውቃለሁ !… -መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ይህንን አውቃለሁ !…
( የግጥሙ ደራሲ መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ )

ሰዎች ሁላችን…
ሥጋን እንወዳለን…
ሥጋን እናፈቅራለን…
ለሥጋ እንሞታለን…
ለሥጋዬ ለዘመዴ… ሁሌም እንላለን።
ከቶ ምን ይሆን ይህ ሥጋ ማለት ?
በዘር፣በቋንቋ በጎሣ ተቧድኖ የሚሞትለት ?
…………………………….
ይህንን አውቃለሁ…
ይኽ የሰው ሥጋ ይለያል ከከብት
በአዋዜ አጥቅሰው አይመገቡት።
የእንስሳን ስጋ ነው የሰው ልጆች ምግብ
ይህንን ይገነዘባል በሰውነቱ ያለ ፣ እነደ አውሬ የማያስብ፡፡
እርግጥ ማንም ያውቃል…
ከብት ታርዶ፣ ሥጋው ተበልቶ፣በውዛ እየበራበት የሚሰቀለው በየሉካንዳ ቤቱ
ሰው ገዝቶ እንዴያነክተው ነው፣ እዛው ከሉካንዳ ወይ ወስዶ ከቤቱ፡፡
……………………………
እርግጥ ነው፤ አለሰማሁም …
ከቶም አላየሁም…
የሰው ሥጋ ታርዶ ባይቀርብ ለገበያ
ሲሆን ግን አውቃለው በሰብቅ ፣የእንጀራ መብያ
ለብዙሃኑም የቡና ማህበርተኛ ፣ይሆናል የሰው ስጋ ቁርስ
ተነስቶ የሚቦጨቅ…ሺ ጊዜ የሚነሳ የሚጣል.. ደሞም የሚታፈስ፡፡

………………………..
ይህንን አውቃለሁ፣
ሰው ለእንሥሣ ሥጋ፣ ባልትና እየሰጠ
ጣፍጦ እንዲገባ በበልተናው ጣእሙን እያጣፈጠ
ክትፎ፤ጎረድ፣ጎረድ፤ቁርጥና ዱለት
ምንቸት፣ ቀይ ወጥ፣ አልጫ- ፍትፍት
ቅቅል፣ ጥብሥ፣ ክትፎ፣ ምላሥና ሰንበር
አውቃለሁ…እጅ እያስቆረጣሚ ሆኖ
እየተጎረሰ፣ በአፍ ገብቶ በከርስ እንደሚቀበር።
……………………………
ይህንን እውቃለሁ …
የስጋን ሥጋነት
የእንሥሣን … ከብትነት
የስጋውን…መብልነት።
ይህንን ማንም ያውቃል፣እኔም አውቃለሁ…
ግና ጥቂት ሰው ነው ፣የስጋን ክቡርነት በጥልቅ የሚረዳወ
በመንፈሣዊ ጥበብ ተክኖ ሥጋውን ከሐጥት የሚጠብቀው፡፡
ይህንን አውቃለሁ…
የህ የእኛ የነፍስ ልብሥ …ከሰማይ እንደመጣ
በክብር እንደሚኖር ነፍሳችን እሥክትወጣ።
ሰው ከሞተ በኋላ ልብሱ ሬሳ እንደሚባል
ሥጋው ለዘላለም ከአፈር እንደሚቀላቀል።
ይሁን እንጂ ተራ ሞች…
በህይወቱ ሣለ የፈጣሪ ቤተመቅደስ መሆኑንን ይዘነጋል
በስጋው እየተደሰተ በሐጥያት ይኖራል ፡፡
በሐጥያትም ይከብራል፡፡
……………….
ይህንን አውቃለሁ
ብዙ ሰው ክቡሩነቱን ፈፅሞ እንዳልተረዳ
ዋጋ የከፈለለትን እያሳዘነ፣ እንደሚኖር፣ራሱን እየጎዳ።
ማነው የሚረዳው ሰው “ህዋዊ ” ፍጥረት እንደሆነ
እንደፕላኔት ፣እንደከዋክብት፣እንደጨረቃ በምድር ገዝፎ እንደገነነ ።
የተከበረ ታላቅ ፍጡር መሆኑን ባለማወቁ፣ይኖራል ሰው፣ሰውን እያሳዘነ ።
በሆድ፣ለሆድ ለስጋ ምቾት በመኖር ግላዊ ደሥታን እያቀነቀነ።
እንሆ ለሦሥት ሺ ዘመን ኖሯል የህዋው አካልነቱን እንደረሳ
ዛሬም ይኖራል፣በአልጠግብ ባይነት በእብሪት እያገሳ ።
የራሴ ዜጋ ፣የራሴ ጎሣ ፣የሚለውን ብቻ በማቀፍ
የእኔን ቋንቋ አይናገርም ብሎ ሌላውን በመንቀፍ
ሁሌ፣ሥጋዬን፣ዘሬን ፣ጎሳዬን፣ቋንቋዬን ብሎ
ለሥጋው ምቾት የመንፈሥ አንድነቱን ጥሎ
ከጥንት እሥከዛሬ ሥጋዬ ዘመዴ እያለ
በአውዳሚ መሣሪያው ብዛት እየፎለለ
ሥለሥጋ፣ ለሀብትና ንብረት ሁሌም እየተጨነቀ
ወገኔ፣የአገሬ ዜጋ የማይለውን እያደቀቀ ፤፡
ይህንን አውቃለሁ ! …
ሰው ያለማወቁን እንደማያውቅም እረዳለሁ።
ሀ ሲል ከላይ ከአርያም እንደመጣ
ከሄዋን መሐፀን እንደወጣ
አዳም እነደሆነ አባቱ
ፈፅሞ በመዘንጋቱ…
በመራቅ ከመንፈሳዊ እውቀት
መዳረጉን ለሥጋ እስር ለህሊና ውድቀት።
………………………………..
ይህንን አውቃለሁ !
የምናዋድደው ይህ ሥጋ …
እያየን እኮ ነው ፣ነፍሳችንን ሲወጋ።
በዘርና በጎሣ ሰውነታችንን እየለካ ?!
ሥጋን በማግዘፍ በቅድስናላይ እያስካካ
ክቡሩ ሰውነት ተቆጥሮ እንደእንሥሣ ሥጋ
ሰው በሰው ላይ ማድረሱን ቀጥሎል እየተቧደነ በመንጋ።
…………………………………………..
ይህንን አውቃለሁ !
ሰው ሁሌ ቢበላ የከብት ሥጋ
አወፍሮ ይዳርገዋል እንጂ ለህመም፣ለአደጋ
ጥቂቱን ያጋድለዋል እንጂ ይህ የሥጋ ጥጋብ
በማይረባ ትርኪ ምርኪ፣ በሰበብ ና አሥባብ።
የከብት ሥጋ መብላት ከብት አያደርግም…
የከብት ሥጋ ሥለ በላ ሰው ማሰቡን አያቆምም፡፡
ህሊና የሚበላውን ዓይነት የእንስሳ ሥጋ ሆኖ አያውቅም።
ይህንን አውቃለሁ …
ሰው መሆኑን ለዘነጋ…
ሰው መሆኑን እንዲረዳ
ዛሬም እፀልያለሁ፡፡
……………………………

ተጨማሪ ያንብቡ:  "ተጠጋ ወደ እሳቱ" አገር ሳያጠፋ በቅጠል

አመሰግንሃለሁ።
ፈጣሪዬ ሆይ ቸሩ የእኔ አምላክ
(እየሱስ ክርስቶስ )
አንተ ፍፁም ነህ ፣እኔ ባልሆን ልክ።
የልቤን ፀሎት ፣ፈጣሪዬ ሰምተህ
በማሥተዋል ሞላኸኝ ፣ በጥበብ አሥታጥቀህ ።
ህሊናዬ እንዳይዋዥቅ ፣በመንፈሥህ ገዝተህ…
በፍቃድህ አደርገህኛል የሃሳብህ መልዕከተኛ
ሰለፍቅር እና እውነት እንድፅፍ ዘወትር ሳልተኛ።
በአንተ መሪነት ዘወትር እውነትን ፅፌያለሁ
ለዚህም ውለታህ… አመሠግንሃለሁ ።

ማስታወሻ

እነዚህ ሁለት ግጥሞቼ ታህሣሥ 26/2013 ሌሊት፣8:30 ላይ ፈጣሪዬ ከእንቅልፊ ቀሥቅሶኝ የፃፍኳቸው ግጥሞቼ ናቸው። በፈጣሪ ቁጥጥር ውሥጥ የተገጠሙ…። በዛው ሌሊት 10:43 ላይ ግጥሞቹ ተጠናቀቁ። እናም ” የገና ሥጦታ ለአንባቢዎቼ ለምን አላደርጋቸውም ?” አልኩና ዛሬ “እንሆ በረከት ! ” አልኳቸዋ !
እንኳን ለጌታችን ለመድሃኒታችን ለእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡

1 Comment

  1. ሰማ ወገኔ – አንድ የዘፈን አቀንቃኝ እንዲህ ብሎ ገጥሟል (ወይም ከህዝብ ተውሶቷል)። ወንድሙን ገደለው አይቶት እንደ ጠላት፤ በደም የተቦካ እንጀራን ለመብላት። እኮ በል ሌላ ልጨምር – በአንድ ወቅት ሰው ሲሞት እንዳይለቀስ በተለይም ምሾ በማውጣትና መንግስትን በሚጎንጡ ነገሮች ዙሪያ ክልክል ነበር። በዋጋ የተቀጠረቸው አስለቃሽ እንዲህ ብላ ሰውን አላቀሰች። ያን ማዶ ተራራ እርጥቡ ጋረደው ገብቶ የነደደው ደረቅ ደረቁ ነው አለች። ሰው ከእንስሳ መጣ የሚለው ሃሳብ የአዳምና የሂዋንን የገነት ኑሮና ከዚያም ያለልባቸው ተሽቀንጥረው መጣል ህሳቤ ስለሚቃረን የሰማይ አምላክ አለ ለሚሉ አይስማማቸውም። ግን ሰው ከሰውነት ተራ ወጥቶ አውሬ ሆነ የሚለው ግን የሚያከራክር ጉዳይ አይሆንም። አይናችን እያየ ነውና! ሰው አውሬ ሆኗል! እንተማመን በዚህ፡
    አንድ ያነበብኩት መጽሃፍ ትዝ ይለኛል። ካልተዘነጋኝ ደራሲው ታደሰ ዘውዴ ይመስለኛል። አርዕስቱ ” ቀሪን ገረመው” ይሰኛል። በንጉሱ ጊዜም ሆነ በደርግ የመከራ ዘመን፤ አለያም በወያኔ የባርነት ጊዜ ወይ በአንድ ወይም በሁሉም የኖረ ሰው በሃገራችን በተፈጠረውና በተሰራው ነገር ሁሉ አልተገረምኩም የሚል ካለ ከእንቅልፉ ያልነቃ ነው። እኮ በል የወያኔ ውድቂያ የሮም አወዳደቅ አይደለም የሚል ይኖር ይሆን? ከዙፋን ወደ ዋሻ? ለዘመናት የሰሩትን በደል ሁሉ ይቅር ተብለው አብረን እንኑር ሲባሉ አካኪ ዘራፍ ሲሉ እንዲህ መንኮታኮት ምን ይሉታል? ሥጋን ሥጋ ሲበላው ሰው ማየት እንዴት ይሳነዋል? ይህ የፓለቲካ እሽክርክሪት አይደለም ብሎ ለመናገር የሚደፍር ይኖራል። የኢትዮጵያን ሰራዊት ሲያፈራርሱና የራሳቸውን እንደ አዋቂ አናጢ ሲገነቡ በሰፈሩት መስፈሪያ መሰፈር እንደማይቀር እንዴት መገመት ያቅታል። እንኳን ፊደል የቆጠረ የሃገራችን ቃልቻ ጠንቅቆ ያውቀዋል። በጅምላ ፓለቲካ ሰው በዘርና በቋንቋው እንዲሁም በክልሉ መሰፈር ከጀመረ ወዲህ የፓለቲካ አዙሪቱ ሰውን በሰውነቱ መመዘኑ ቅርቶ አማራው ተበደልኩ ሲል ኦሮሞው እኔም፤ ሌላውም እኛ እሳ የሚባልባት ፍርድንና ፍትህን ስንጠይቅ በሰውነት ደረጃ ሳይሆን ከዚሁ አሻጥረኛ አሰላለፍ ጋር በመጎዳኘት በመሆኑ ሰው ሁሉ አውሬ ሆኗል ማለት ይቻላል። አንድ የትምህርት ቤት መጽሃፋችን አርዕስት ትዝ ይለኛል። “አብሮ መኖር በአለም ዙሪያ” ይል ነበር። ወያኔ ያደረሰው ግፍ ሰማይ ጠቀስ ነው። የሚጓዝበት ጎዳናም የማያዋጣና ለውድቀት የሚዳርግ ለመሆኑ ብዙ ምልክቶች ነበሩ። ለምሳሌ የኢህ አደግ የቁልቁለት ጉዞ (2005 -2010) የስብሰባዎች ወግ የተሰኘውን መጽሃፍ ላነበበ ዘመናቸው ሁሉ የቧልት እንደነበር ያመላክታል። አሁን ወህኒ ያለው አቶ በረከት አልፎ አልፎ ይህ ውድቀት እንደሚመጣ ይሟገት እንደነበር በዚህ መጽሃፍ ላይም ሆነ በሌላ ስፍራ ተመልክቻለሁ። አሁን ማን ይሙት አቶ በረከት ከአቶ ስዬና ከሌሎቹ በአዲስ አበባና በውጭ ከሚኖሩ የወያኔ ባለስልጣኖች የበለጠ በደል ፈጽሟል? አይመስለኝም። ግን የፓለቲካ አተካራ እንዲህ ነው በወረፋ መበቃቀል። የወያኔውን የክፋት አለቃ የአቶ መለስን መቃብር በዘብ የምታስጠብቅ ሃገር ኮ/መንግስቱ ሃይለማሪያም ሃገራቸው ገብተው እንዳይቀበሩ የሚከለክል ድርቡሽ ስርዓት ነው። መንግስቱና ጓደኞቹ በለጋ ዘመናቸው በመጤ ርዩተ ዓለም ተጠምቀው በአሃዝ የማይተመን በደል ፈጽመዋል። ለወያኔና ለሻቢያ ድል 100% በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ረድተዋል። ግን ያ ያለፈ ታሪክ ነው። ዛሬ ደግሞ ሌላ ነው። ሃገር እንገነጥላለን ያሉ ግቡ ሰላም እንፍጠር ሲባሉ እሺ ብለው ገብተው አይደል እንዴ አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብለው ህዝባችንን የሚያጫርሱት። ምህረት ከተባለ ለሁሉም መሆን አለበት። ብቻ ተተራምሰን ስናተራምስ፤ መራን ብለን ስንደናበስ፤ ኖርን ብለን መኖራችን ሳናውቅና ሳናጣጥም ሁሉም ወደ እማይቀርበት አለም እንጓዛለን። እንዲህ ነው ያለውን ነገር። አምናው ካቻምናውን ሲመስል፤ ካቻምናው አምናውን ሲመስል። ልብ ብላችሁ ያዙልኝ። በሚቀጥለው በዚህ ሰአት ስንቶች ቆመው ስንቶች ይሞቱ ይሆን? ምንስ ተሰርቶ ምን ይፈርስ ይሆን። ህይወት ወራጅ ወንዝ ነው። ይነጉዳል። ዘረኝነት በሽታ ነው። መኖርን ለመኖር አለም አቀፋዊ እይታ በሰውነት ሚዛን ይኑረን። የቀረው የገለባ ክምር ነው። እሳት የሚበላው። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share