አምባገነን መንግስታት፤ ስልጣን ላይ ሳሉ ከሚያደርሱት በደል በላይ የከፋ ጠንቃቸው፤ በግዝፈታቸው ልክ ተገርድሰው የወደቁ እለት ፍርስራሻቸው የሚያስከትለው ሀገራዊ ምስቅልቅል ነው። ሕወሃት በውጫዊ ግፊት ከሥሩ ተመንግሎ ሀገር አብሮ ይዞ ከመውደቁ በፊት፤ እዛው ኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገ የኃይል ሽግሽግ፤ ጥግ የሚይዝበት አጋጣሚ ሲፈጠር የተሰማን ትልቅ እፎይታም ይህን ታሳቢ ያደረገ ይመስለኛል። ደስታው ግን ብዙም አልዘለቀም። በሕወሃት እና በአዲሱ የዶ/ር አብይ መንግስት መካከል እያደር የተፈጠረው ፍጥጫ ጡዞ ጡዞ ወደ ለየለት ጦርነት አድጏል።
የዶ/ር አብይ መንግስት ጦርነቱን አጠናክሮ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ሕወሃት መደምሰስ ላይ የማይቀለበስ አቋም የያዘ ይመስላል። የሀገር መከላክያ ሰራዊት ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተመርኩዘን ብይን ከሰጠን፤ የጦርነቱ ፍትሀዊነት ብዙም አጠያያቂ አይሆንም። ነገር ግን፤ የዶ/ር አብይ መንግስት፤ በሦስቱ አመታት የስልጣን ዘመኑ ያሳየውን ባህሪ ከግምት ውስጥ ካስገባን፤ አሁን መንግስት ለግጭቱ እየሰጠ ያለውን ምስል እንደወረደ መቀበል አስቸጋሪ ይሆናል።
በመንግስት በኩል፤ የጦርነቱ መንስኤ ሕወሃት መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረው ጥቃት እንደሆነ ነው የተገለጸው። ቆይተው፤ የሕወሃቱ ሴኮቱሬ፤ “ቀድሞ እራስን የመከላከል እርምጃ” ያሉትን ጥቃት የሰሜን እዝ ላይ መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ መልክት ሲያስተላልፉ ተስምተዋል። ያም ሆኖ ግን፤ ይሄን ግጭት የአንድ ክስተት ውጤት አድርጎ መደምደሙ ትክክል መስሎ አይታየኝም። ለሦስት አመት ሲታሽ ሲጎሽ ከርሞ የፈነዳ ጦርነት ነው። ወደ ኃላ ተመልሰን አጠቃላይ በሕወሃት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተፈጠረው ትንቅንቅ የተጓዘበትን መንገድ ከቃኘን፤ ዉጥረቱ ከሮ ከሮ እዚህ ለመድረሱ ዶ/ር አብይ የነበራቸው አስተዋጾ ከሕወሃት ቢበዛ እንጅ የሚያንስ አይደለም።
ሕወሃት ከአራት ኪሎ የተነሳው በደረሰበት የፖለቲካ ጫና እንጅ በጦር አልነበረም። በቀጣይም፤ ከሕወሃት በኩል ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ሊመጣ የሚችል ስጋትን ለመከላከል አዋጩ እና ዘላቂው መፍትሄ፤ በለውጡ የተፈጠረውን የስምምነት መንፈስ አጠናክሮ፤ ሁሉን አቀፍ የብሄራዊ ውይይት መድረክ በማመቻቸት፤ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መንገድ መጥረግ ነበር። ይህን ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ ሕወሃት ወይ አመሉን አስተካክሎ አብሮ ይጓዝ ነበር፤ ያለዚያም በአጠቃላይ ሀገራዊ ፖለቲካው ተጽኖ ውስጥ ወድቆ በግዜ ሂደት ተፈጥራዊ የፖለቲካ ሞቱን ያገኝ ነበር። ዶ/ር አብይ ቃል የገቡበትን ሀገርን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የማሻገር አጀንዳ ወደ ጎን ገሸሽ አድረገው፤ የግል ስብዕና የመገንባት እና የራስን ስልጣን የማደላደል ተግባር ላይ መጠመድ ስለመረጡ ይህ የሰላም መንገድ እድል አላገኘም።
ለውጡ ሦስትኛ አመቱን እየደፈነ ነው። በዚህ ግዜ ውስጥ አንድ የረባ ሀሳብ ላይ ፍሬ ያለው ውይይት እና ክርክር አልተደረገም። አንድም ነገር ውል ያለው መቋጫ አልተበጀለትም። ለውጡ ዶ/ር አብይ ጭንቅላት ላይ ብቻ በተቀመጠ ፍኖተ ካርታ ነው እየተንጠራወዘ የሚጓዘው። ቀጥለው ወዴት አቅጣጫ እንደሚቀዝፉ እርግጠኛ መሆነ አይቻልም። በዚህ ምክንያት፤ ሌላው ወገን የሳቸውን እጥፋቶች እየተከተለ ወዲያ እና ወዲህ ከመላተም ውጭ፤ ግልጽ አቅጣጫ ተከትሎ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ አልቻለም። ተቀራርቦ በመነጋገር ልዮነቶችን ማስታረቅ የሚቻልበት መንገድ ሲዘጋ መጣላት የማይቀር እዳ ይሆናል። ዶ/ር አብይ ሀቀኛ እና ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት እንዲደረግ መንገድ መዝጋታቸው በራሱ፤ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ለውጥ ሀዲዱን ስቶ ወደ ግጭት እና ጦርነት ለመግባቱ ዋና ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።
በሀያ ሰባቱ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ዘመን የደረሱ የሰባዓዊ መብት ጥሰቶችም ሆነ ሌሎች አስተዳደራዊ በደሎች በተመለከተ መጀመርያ ላይ በለውጥ ኃይሉ የተንጸባረቀው አቋም በይቅርታ ይታለፍ የሚል ነበር። ዶ/ር አብይ እራሳቸው፤ “ባለፉት ዓመታት ለደረሰው ጥፋት ወንጀለኞችን እንቅጣ ብንል፤ ሌላ ስራ መስራት አይቻልም፤ ለሰላም ሲባል ያን ምዕራፍ በይቅርታ ብንዘጋው የተሻለ ነው” የሚል ሀሳብ አስረገጠው መናገራቸውን አስታውሳለሁ። በኋላ ላይ ግን፤ ድንገት ቃላቸውን አጥፈው፤ ለዛውም ትግርኛ ተናጋሪውን የሚቆነጥጥ ፕሮፖጋንዳ የታጀበ እስር እና ክስ በሜቲክ እና በደህንነት ሰዎች ላይ አነጣጥረው ጀመሩ።
በግሌ፤ ተቃርኖ ላይ የተመሰረተው የኢሕአዴግ ፖለቲካ ያስከተለው ሀገራዊ ኪሳራ ላይ መግባባት ላይ መድረስ ከተቻለ፤ የእርቅ እና ይቅርታው መንገድ የተሻለ ነበር የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ። ወደ ፍትህ መሄድ አስፈላጊ ነበር ከተባለም፤ መጀመሪያ ሂደቱ ምን ሊመስል እንደሚችል በጥናት መፈተሽ ነበረበት። የብሔር ማንነት፤ ከፖለቲካ ፖርቲ ጋር አብሮ በተለወሰበት በዚህ ዘመን፤ እንደ ደርግ ግዜው፤ የፓርቲውን አውራዎች ሰብስቦ በማጎር፤ ሒሳብ በቀላሉ ማወራረድ አይቻልም። በዚያ ላይ፤ አዲሱ መንግስት፤ ከቀደመው መንግስት መህጸን የወጣ እንደመሆኑ፤ የከሳሽ እና ተከሳሹን መስመር መለየቱ ሌላ ፈተና ነው የሚሆነው። ዶ/ር አብይ፤ እኒህን እና መሰል ጥያቄዎችን ሳያገናዝቡ በዘፈቀደ ወደ እስር እና ክስ መግባታቸው እጅግ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነበር።
መንግስት፤ የሰኔ 16ቱን የመስቀል አደባባይ የቦንብ ፍንዳታ ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎች ላይ ለደረሱ አደጋዎች የሕወሃት ሰዎች እጅ እንዳለበት መረጃው ማቅረብ ከቻለ፤ ከሁኔታው ጋር የቀጥታ ንኪኪ ያላቸው ሰዎችን አጣርቶ፤ በዛ ወንጀል ዙርያ የታጠረ ክስ መመስረቱ ተገቢ ነው። አልፎ ሄዶ፤ በይፋ ተዘግቷል የተባለን የኋላ ፋይል መምዘዙ ግን አላስፈላጊ ጠብ አጫሪነት ነበር። በዚህ ድርጊታቸው፤ ዶ/ር አብይ ሕወሃቶችን ለህልውናቸው የሞት ሽረት ሲወራጩ ይባስ ሀገር ወደሚያተራምሱበት መንገድ ገፈተዋቸዋል። እግረ መንገዳቸውን፤ የትግራይ ህዝብንም፤ ከሕወሃት ጎን ከመሰለፍ ውጭ ለደህንነቱ ሌላ ዋስትና እንደሌለው እንዲሰማው አድርገውታል። አጠቃላይ በለውጡ ተፈጥሮ የነበረውን የመተማመን መንፈስም አላግባብ ክፉኛ ጎድተዋል።
ዶ/ር አብይ ኢሕአዴግን አፍርሰው ብልፅግናን የመሰረቱበት መንገድ፤ ሌላው በዶ/ር አብይ እና በሕወሃት መካከል የነበረውን ግንኝነት ላይጠገን የሰበረ ክስተት ይመስለኛል። ኢሕአዴግን አዋህዶ አንድ ወጥ ፓርቲ የመመስረቱ ሀሳብ፤ በመርህ ደረጃ የተቀደሰ ቢሆንም፤ ተጨባጭ አተገባበሩ ግን ግዜውን የጠበቀ እና እውነተኛ መግባባት ላይ የተመሰረተ ነበር ለማለት አያስደፍርም። ውህደቱ ነጻ እና ግልጽ ውይይት ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን የዶ/ር አብይ ፍላጎት ላይ ተንጠልጥሎ የተቀናበረ ነው የሚመስለው። የልዮነት እጥረት በሌለበት ሀገር፤ ምንም እሰጣ ገባ ሳይሰማ ውህደቱ ተጠናቀቀ መባሉ በራሱ፤ መድረኩ ነጻ እንዳልነበር አንዱ አመላካች ነው። በውህደቱ ዙርያ በለማ መገርሳ እና በዶ/ር አብይ መካከል የተፈጠረው ልዮነት የተስተናገደበት ሁኔታም፤ በተመሳሳይ ውህደቱ ምን ያህል የዶ/ር አብይ ጡንቻ ያረፈበት እንደነበር ሌላ ማሳያ ነው።
ምንም እንኳን ይህን ለማድረግ የግድ ኢሕአዴግን ማፍረስ ያስፈልግ የነበረ ባይመስለኝም፤ አጋር ይባሉ የነበሩት ድርጅቶች አዲሱ ፓርቲ ውስጥ መጠቃለላቸው የውህደቱ አንድ በጎ ጎን ሆኖ ሊጠቀስ ይችል ይሆናል። ከዛ በተረፈ ግን፤ የብልፅግና መመስረት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ሌላ ረብ አልነበረውም። “መደመር” የሚለውን ቋንቋ መሬት ወርዶ የፈጠረውን ታአምር አላየንም። በኦዲፒ እና በኦሮሚያ ብልፅግና ወይም በአዴፓ እና በአማራ ብልፅግና መካከል፤ ከስም ለውጡ ውጭ፤ የታየ የርዕዮትም ሆነ የመዋቅር ለውጥ የለም። የተለወጠ ነገር አለ ከተባለ፤ ውህደቱ ለሊቀመንበሩ ዶ/ር አብይ፤ ሁሉም ድርጅቶች ውስጥ እንደፈለጉ ጣልቃ ለመግባት የሚሰጣቸው ህጋዊ ሽፋን ነው። የውህደቱም ዋና አላማም ይሄው ይመስለኛል። ኢሕአዴግን በዶ/ር አብይ አምሳል እንደገና ማዋቀር።
ሕወሃቶችን አለቃ ሆነው በኖሩበት ድርጅት ውስጥ እኩልነትን ማላመዱም ቀላል ስራ ይሆን የነበረ አይመስለኝም። ዶ/ር አብይ ግን ጭራሽ ኢሕአዴግን አፍርሰው፤ እሳቸው እንደ አዲስ በቀረጹት ፓርቲ ውስጥ ሎሌ የመሆን ምርጫ ነው ያቀረቡላቸው። ሕውሃቶች ይህን አሜን ብለው ሊቀበሉ አይችሉም። ዶ/ር አብይም፤ በነበረው ሁኔታ ሕወሃት ውህደቱን እንደሚቃዎም እና እራሱን እንደሚያገል ቀድመው የሚገምቱ ይመስለኛል። ምን አልባትም፤ የውህደቱ አንዱ አላማ፤ ሕወሃትን ከውስጥ የፓርቲ ስራቸው የማስወገጃ ሽፋን ፍለጋ ሳይሆን አይቀርም። ዶ/ር አብይ ብልፅግና በተመሰረተ ሰሞን ባሌ ላይ አደረጉት በተባለ የኦሮመኛ ንግግር ያሰሙት “ከኦሮሞ ጠላቶች ጋር አብረን ላለመስራት ነው ብልጽግናን የመሰረት ነው” የሚል ሀሳብ ይህን መላምት የሚያጠናክር ሆኖ ነው ያገኘሁት። በእርግጥ “ለኦሮሞ ብለን” የሚለው አላምንበትም፤ ሕወሃት ጋር መፋታት እውነትም የእቅዳቸው አካል እንደነበር ግን ይሰማኛል።
ሕወሃት ለውጡን አሜን ብሎ ይቀበላል? ወይስ ያልሞት ባይ ተጋዳይ ሆኖ ሀገር ያተራምሳል? የሚለው ጥያቄ በለውጡ ዋዜማ ትልቁ ጭንቅ ነበር። ቀላል ላይሆን ይችላል፤ የተፈራው ሳይሆን ሕወሃቶች አንዴ በሰላም ስልጣን አስረክበው ከለቀቁ በኃላ ግን፤ ቢያንስ ቋሚ ሀገራዊ ስርአት መሰረት እስኪይዝ ድረስ፤ ልዮነትን አስታሞ አብሮ መቀጠሉ ለሀገር መረጋጋት የተሻለው መንገድ ነበር። የቀሩት ሦስቱ ድርጅቶችን እና አጋር ድርጅቶችን ተናበው መስራት ከቻሉ ሕወሃትን የሚኖረው ተጽኖ ዞሮ ዞሮ ያን ያህል አይሆንም ነበር። እንዲያዎም የድርጅቱ አካል ሆኖ መቀጠሉ እንቅስቃሴውን በቅርብ ለመቆጣጠር እና በፓርቲ ህገ ደንብ ማዕቀፍ ውስጥ ለመገደብ የተሻለ አቅም ይፈጥርላቸው ነበር። ዶ/ር አብይ፤ ያለምንም ተገዳዳሪ እንዳሻቸው የሚያዙት ፓርቲ ከመፈለግ ይመስለኛል ይህን መንገድ አልመረጡም።
በግልባጩ፤ ዶ/ር አብይ፤ ሕወሃትን ፈተው ሜዳ ላይ በመልቀቃቸው፤ ሕወሃት ከወደቀበት ተነስቶ፤ የኢሕአዴግን መፍረስን የብሔር ተኮር ፊደራሊዝሙ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው የወሰዱ ሌሎች ወገኖች ጋር ኃይል አስተባብሮ ነፍስ እንዲዘራ መንገድ ከፍተዋል። ምንም ብልፅግና የዶ/ር አብይን የአገዛዝ እቅድ ከማሳካት ውጭ ሌላ ፋይዳ ባይኖረውም፤ በወቅቱ “አህዳዊ መንግስት ሊመለስ ነው” የሚል ውጥረት እና ዘመቻ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። በኢሕአዴግ መፍረስ እና በብልፅግና መመስረት የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ አሁንም ጦሱ አልቋል ብየ አላስብም። ሆኖም፤ ዶ/ር አብይ የእሳቸውን መንግስት በመቃዎም በሕወሃት ዙርያ መፈጠር ጀምሮ የነበረውን ስብስብ በትኖ ሕወሃትን እንደገና ብቻውን ማስቀረት ተሳክቶላቸዋል።
ከእስካሁኑ አያያዛቸው፤ ዶ/ር አብይ ሀገር ጠቅልለው መዳፋቸው ለማስገባት ደፋ ቀና እንደሚሉ እንጅ፤ መጀመሪያ ላይ ተስፋ እንደተጣለባቸው ቋሚ ሀገራዊ ስርአት ለመገንባት እየታተሩ እንደሆነ የሚጠቁም ነገር እያሳዮን ነው ብየ አላስብም። የለውጡ መጀመርያ ላይ፤ ኢሕአዴግ ውስጥ፤ በተለይ ኦህዴድ እና ብአዴን አካባቢ ብዙ ተስፋ ሰጭ ነገሮች አይተን ነበር። ባለስልጣኖቹ የሚያስተላልፉት መልክት፤ በግድ ወጥ እንዲሆን ያልተጨፈለቀ፤ ግን ደግሞ ከሞላ ጎደል የተናበበ ነበር። በኢሕአዴግ ታሪክ ታይቶ በማይታዎቅ መልኩ፤ ድርጅቶቹ ለህዝብ ቅርብ መሆን ጀምረው ነበር። አዲሱ የነጻነት እና የግልጽነት መንፈስ ግን ብዙም አልዘለቀም። ቀስ በቀስ ነገሮች መልካቸውን መቀየር ጀመሩ።
አሁን ላይ ፓርቲው ከዶ/ር አብይ አብይ የተለየ ህልውና አለው ለማለት አያስደፍርም። በርግጥ፤ ዶ/ር አብይ እና የበታች አመራሮች እርስ በእርሱ የሚጣረስ መልክት የሚሰጡበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ይህ ግን የዶ/ር አብይ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ስትራቴጅ ነጸብራቅ እንጅ የፓርቲው ዲሞክራሲያዊነት መገለጫ አይመስለኝም። ዶ/ር አብይ ምንአልባትም፤ እምቢ ባዮን አስወግደው፤ የሚበረከከውን አምበርክከው እና የሚደለለውን ደልለው ፓርቲያቸውን ሙሉ ለሙሉ በእሳቸው እዝ ሰንሰለት ሥር ማስገባት ተሳክቶላቸዋል። ሀገር በብቸኘነት የሚስተዳድረው ብልፅግና እስከሆነ ድረስ፤ ፓርቲያቸውን ጠቀለሉ ማለት፤ የመንግስት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በእጃቸው አስገቡ ማለት ነው። የቀረው ትግራይ ነው። ሕወሃትን ትግራይን በተቆጣጠረበት ሁኔታ፤ የዶ/ር አብይ መላ ሀገሩ ላይ አራጊ ፈጣሪ የመሆን እቅድ አይሞላም። ኦህዴድን እና ብአዴንን በጠለፉበት መንገድ በውስጥ በኩል ገብተው ሕወሃትን ሊያንበረክኩ አይችሉም። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ ሕወሃትን ከውጭ በኩል አዋክቦ ማሽመድመድ ነው። የዚህ ጦርነት ፋይዳ ከዚህ የገዘፈ መስሎ አይታየኝም።
በሕወሃት እና በዶ/ር አብይ መንግስት የተፈጠረው ትንቅንቅ ወደ ጦርነት ከማደጉ በፊትም፤ በሁለቱም በኩል ጠባቸውን ለመርህ እና ለህገ መንግስት መከበር የሚደረግ ትግል አድርጎ የማቅረብ ሁኔታ ይታይ ነበር። ምርጫ አድርግ አደርጋለሁ ግብ ግቡን ጨምሮ፤ አንዳቸውም ሲወዛገቡባቸው የነበሩ ጉዳዮች፤ በዶ/ር አብይ በኩል ሕወሃት ለማንበረከክ፤ በሕወሃቶች በኩል ለዶ/ር አብይ ጫና ላለመበገር ከሚደረግ ትንቅንቅ ባለፈ፤ የኢትዮጵያን መጻየ እድል ከመወሰን ሆነ ህግን ከማስከበር አንጻር ሚዛን የሚደፉ አልነበሩም። ይህን ጦርነት፤ ለሀገር እና ለህዝብ የሚደረግ ጦርነት አድርጎ ለመቀበል የምቸገረው ለዚህ ነው።
ይህን የምለው መከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት አቅልሎ ከማየት አይደለም። ሕወሃት እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ነበር የሚል ሀሳብም የለኝም። ሌላው ቢቀር፤ ጎንደር አካባቢ ከቅማንት የማንነት ጥያቂ ጋር በተየያዘ በተደጋጋሚ ለተቀሰቀሰው ግጭት ያቀብሉት የነበረው ግብአት ብዙም የተደበቀ አልነበረም። ነገር ግን፤ በሕወሃት በኩል ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶችን ለመዝጋት የጦርነትን ያህል ዋጋ የማያስከፍሉ ብዙ አማራጩች ነበሩ። እየዘነጋን ካልሆነ፤ ቀድሞውኑ ሕወሃት ከስልጣን የለቀቀው በተፈጠረበት ፖለቲካ ጫና እንጅ በጦር አልነበረም። አሁንም ያዋጣ የነበረው በጠንካራ የወንጀል መከላከል ስራ የታገዘ ፖለቲካዊ መፍትሄ ነበር። ሆኖም፤ ዶ/ር አብይ ተስፋ እንደተጣለባቸ ሀገራዊ መግባባት የሚፈጠርበትን መደላድል ከማመቻቸት ይልቅ፤ የግል ስልጣናቸውን ማደላደል ላይ በመጠመዳቸው ሁኔታው ወደ አደገኛ አቅጣጫ ገፍተውታል።
ዶ/ር አብይ የተሰጣቸውን አደራ አክብረው ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር እየሰሩ ቢሆን ኖሮ ፤ ሶስት አመት ሙሉ ባለበት የሚረግጥውን የይስሙላ ውይይት ሳይሆን፤ በሀቅ ሃሳቦች የሚፈተሹበት ሁሉን አቀፍ የብሄራዊ ውይይት እየተካሄደ ቢሆን ኖሮ፤ ወደ ዲሞክራሲ የሚታሰበው ጉዞ ተስፋ የሚሰጥ ወጤት እያስገኘ ቢሆን ኖሮ፤ በሕወሃት በኩል ለሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት መንግስት የሚወስደው ህግ የማስከበር እርምጃ ፍትሀዊነትን ላይ ብዙም ጥያቄ የሚያስነሳ ነገር አይኖርም ነበር። ያለንበት ሁኔታ ግን ይህን አይመስልም። የህግ አላማ የዜጎችን ደህነነት ማስከበር ነው። ዶ/ር አብይ ግን ህግን የህዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ ሳይሆን ስርአት አልበኝነት መረን እስኪለቅ ጠብቆ የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸውን ለማስወገድ ሲጠቀሙበት ነው ደጋግመን የታዘብነው። በዚህ ሁኔታ እስከመቸውም ከግጭት አዙሪት እንወጣለን ብየ አላስብም።
እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የግጭት መንስኤዎችን ከምንጫቸው ማድረቅ እስካልተቻለ ድረስ፤ የሆነ ቡድንን ወይም እገሌ እገሌ የሚባሉ ግለሰቦችን ለቅሞ በማስወገድ ሰላም እና መረጋጋት ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም። በተለይ ስልጣን ላይ ያለው አካል እራሱ የፖለቲካው ትርምስ ዋና ተዋናኝ በሆነበት ሁኔታ ሌሎቹ ላይ መዝመቱ ብዙም ትርጉም አይኖረውም። አፍራሽ የሚባሉ ኃይሎችን ጥግ ለማስያዝ ሆነ የደህንነት ስጋቱ ለመቀነስ አዋጩ መንገድ ተለዋጭ እይታ እያቀረቡ መተማመን እንዲጎለብት መስራት ነው። አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላም አብሮ መኖርን አይጠላም። ይህም ለውጥ የተገኘው ህዝብ አዲስ ተስፋ ማየት በመቻሉ ነው። አሁንም ህዝብ የተሻለ ተስፋ ከተሰጠው፤ የጥፋት እንቅስቃሴዎች ብዙም ቦታ አያገኙም። አለበለዚያ፤ እንደ ሀሳባችን መዘበራረቅ፤ በጉልበት ይዋጣልን ማለት ውስጥ ከገባን፤ እጣፈንታችን ተጨራርሶ ማለቅ ነው የሚሆነው።
በጦርነት ቀጠና ውስጥ መኖር ከባድ ሰቀቀን ነው። ትግራይ በጦርነት እየተናወጠች፤ ጦርነቱ ከሕወሃት ጋር ነው የትግራይ ህዝብን አይመለከትም የሚለው አባባል ብዙም ውሃ የሚያነሳ አይመስለኝም። ወዶም ይሁን ተገዶ ሕወሃትን ለመመከት ጦርነት ውስጥ የሚማገደውም ያው የትግራይ ወጣት ነው። በግጭቱ ጦስ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይዎታቸው አጠዋል። በጦርነቱ ምክንያት ከቀየው ተነቅሎ ወደ ጎረቤት ሀገር ለመሰደድ እየተገደደ ያለው ህዝብም ቁጥሩ በየቀኑ እየጨመረ ነው። ግጭቱ በግዜ ካልተገታ ከዛም አልፎ ወደ ሊላው የሀገሪቱ ክፍል እንደማይዛመት እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በመንግስት በኩል ተሰልፎ ህይወት እና አካሉን የሚያጣው ወታደር ቁጥርም ጦርነቱ እያስከፈለን ካለው ሰባዓዊ ጥፋት የሚደመር ነው።
በጦርነቱ ሳቢያ ከባድ ሰባዓዊ እና ቁሳዊ ጥፋት እየደረሰ ነው። ዛሬ ባይሆን ውሎ አድሮ፤ የጦርነቱ ትኩሳት በመላው የሀገሪቱ ክፍል የሚቀሰቅሰው ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ የሚያስከትለው ጥፋት ግን ከዚህም እንዳይብስ ያሰጋል። በብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ተቀስፋ የተያዘች ሀገር ውስጥ፤ አንድ አካባቢ ላይ የሚፈጠር ቀውስ መላ ሀገሩን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የመጎተት እድሉ ከፍተኛ ነው። ምንም እንኳን፤ የጦርነቱ ፍጥነት እና ለድርድር የሚደረገው ግፊት እስካሁን ተጠናክሮ አለመምጣት ብዙም ተስፋ የሚሰጥ ባይሆንም፤ አሁንም ጥፋቱን ለመቀነስ ያለው የተሻለ አማራጭ ጦርነቱን በድርድር መቋጨት ነው።
ፌደራል መንግስቱ ካለው የኃይል ሚዛን ብልጫ አንጻር ጦርነቱን በድል ማጠናቀቁ አይቀሬ ይሆን ይሆናል። ሆኖም የሕወሃትን አቅም አሳንሶ ማየት አይቻልም። በውስን ግብአት ጦርነት የመግጠም ልምድ ያላቸው ሰዎች ናቸው። ተስፋ በቆረጠ ስነልቦና እስከ መጨረሻ ሕቅታቸው ሊታገሉ ይችላሉ። ይህ ግጭቱን ከምናስበው በላይ አስከፊ እና አሰቃቂ ያደርገዋል። ድርድሩ ቢያንስ የለየለት ደም መፋሰስ ውስጥ ሳይገባ ጦርነቱን ለመግታት ያግዛል። ከምንም በላይ ግን፤ ግጭቱ ቀጥሎ የሚያስከትለውን ማክበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ለመቀነስ ያለው ብቸኛ መንገድ ነው።
ሚዛኑ የትናንትና ቁጣ ሳይሆን የነገ የሀገር እጣፋንታ ከሆነ፤ ጦርነቱ ሰላማዊ መቋጫ ቢያገኘ የተሻለ መሆኑን መገንዘብ አዳጋች አይመስለኝም። የድርድር ግዜ በሚሰጠው ፋታ፤ ሕወሃት ትንፋሽ አግኝቶ መልሶ ያጠቃል የሚለውን ስጋት ለማስቀረት፤ የሶስተኛ ወገን የሰላም አስከባሪ ኃይል መኃል ገብቶ አካባቢውን የሚቆጣጠርበትን መንገድ ማመቻቸት ይቻላል። ይህ ጦርነት መጀመሪያውኑ መከሰት አልነበረበትም። የዶ/ር አብይ በመላ ሀገሩ አዛዥ ናዛዥ የመሆን ምኞት ያመጣው ጣጣ ነው። አሁንም የዶ/ር አብይን ለድርድር ፍንክች አልልም ማለት፤ ከሀገር እና ከህዝብ ደህነነት ይልቅ የግል ድል አድራጊነትን ያስቀደመ ተግባር አድርጌ ነው የማየው።
ለሰላም ቁርጠኝነቱ ቢኖር፤ አሁንም ለድርድር ረፍዷል ብየ አላስብም። ነገር ግን፤ በፌደራል መንግስቱ እና በሕወሃት መካከል ብቻ በታጠረ ድርድር ዘላቂ መፍትሄ ይገኛል የሚል እምነት የለኝም። ፈር የለቀቀውን የለውጥ ሂደት እንደገና መስመር የሚያስዝ፤ ሁሉንም ወገን ያሳተፈ ብሄራዊ የምክክር ጉባኤ ማዘጋጀቱም ቀጥሎ ሊታሰብበት ይገባል። የዶ/ር አብይ እና የሕወሃት ትንቅንቅ የመርገብ እድል የሚኖረው በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከተደረገ ብቻ ነው።
ሕወሃት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሰ ቡድን መሆኑ አይካድም። የእነሱ የስልጣን ምኞት እንዲሳካ አሥራ ሰባት አመት የኢትዮጵያ ህዝብ በጦርነት ታምሷል። ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላም፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በስንት ሀገር ወዳድ ዜጎች የዘመናት ልፋት የተገነቡ የሀገሪቱን ተቋማት አውድመዋል። ለእነሱ አገዛዝ የተመቸ ሀገር ለመፍጠር፤ የሀገር መሰረት የሚያናጋ ብዙ ተግባር ፈጽመዋል። የሀገር ሀብት ዘርፈዋል። ትውልድ አቆርቁዘዋል። ህዝብ አንገላተዋል። ካደረሱት በደል ሁሉ ግን፤ በህዝቡ መካከል የዘሩትን የመፈራራት እና ያለመተማመን መንፈስን ያህል ውስብስብ እና አስጊ ፈተና የሰጡን አይመስለኝም።
ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት፤ የኢትዮጵያዊነት ውሉ ተዛብቶብናል። ይህ ብሔርተኛውን ብቻ የሚመለከት አይደለም። ኢትዮጵያዊነትን አስቀድማለሁ የሚለውን ወገን ጨምሮ ሁላችንም በመፈራራት እና ባለመተማመን በሽታው ተጠቅተናል። የሕወሃት ሰዎችን በኃይል ማስዎገድ ይቻል ይሆናል። እኛው ልቦና ውስጥ ያነጹትን መፈራራት እና መቃቃር ግን በፉከራ እና በቀረርቶ ማባረር አይቻልም። ቁጣን በመተሳሰብ፤ ፉክክርን በትብብር፤ ቁጭትን በተስፋ፤ የመቀየር አቅም መፍጠርን ይጠይቃል። ተቃርኖዎችን የሚያስታርቅ የመፍትሄ ሀሳብ ማፍለቅን ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ብልሀቱን እና የመንፈስ ብርታቱን እስኪያድለን ድረስ ግን፤ የሕወሃት ሰዎች እጣ ፈንታ ምንም ይሁን ምን፤ የተዘራው የመለያየት መንፈስ ሀገር እያሳመሰን እኛው ጋር አብሮ ይቆያል።
ከናፍቆት ገላው