ይሰጣታል ቢያንስም (ዘ-ጌርሣም)

ገና ጎህ ሳይቀድ በጥዋት ተነስታ
የምታድነውን ከወዲሁ አስልታ
የበሬውን እንትን መከተል መረጠች
ተስፋዋን ሰንቃ መኳተን ጀመረች

ዓይን ዓይኑን በማየት ስትባዝን ውላ
ከአሁን ወደቀልኝ ተስፋዋንም አዝላ
በውሃ ጥም ድካም ጉልበቷ ተጠቅቶ
ከንቱ ደክማ ሄደች ምኞቷ ተረቶ
ጉልበታሙ አንበሳ ሲቀናው ስላየች
በደካማነቷ የምር ተፀፀተች

ችግሯን ተረድቶ መዋሏን ስትደክም
ለሷ ያሰበውን መቸም አይነሳትም
እንደሰው አይደለም አምላክ ቸል አይልም
የማታ የማታ ይሰጣታል ቢያንስም

ለማይገኝ ነገር ከንቱ ከመጃጃል
ባገኙት ረክቶ መኖሩ ይበጃል
የጎደለ ካለ ጊዜን መጠበቅ ነው
አንድም ነገር የለም ለሱ የሚሳነው

ጊዜ እንደ ፈረስ ነው ያደርሳል ካሰቡት
ቁስሉ ተሎ አይድንም ከጣለ የኋሊት
ፈርስ ለመጋለብ ህግና ደንብ አለው
መሟላት ሲችል ነው ኮርቻና ዛቢያው
ጊዜን ያለአግባብ ልጠቀም ለሚሉ
ካሰቡት ሳይደርሱ መንገድ ይቀራሉ

ምስኪኗ ቀበሮ ስትባዝን ውላ
ሄደች ተመልሳ በድካም ነሁልላ
ምኞትና ተስፋ ተራራ ሲወጡ
አይቀሬ ጉዳይ ነው መውደቅ መላላጡ
ያሰቡትን ነገር ከግቡ ለማድረስ
ትንፋሽን ዋጥ አርጎ ይገባል መታገስ
እንደሰው አይደለም አምላክ ቸል አይልም
የማታ የማታ ይሰጣታል ቢያንስም

ተጨማሪ ያንብቡ:  በጦሙ ፈሰኩ! - በላይነህ አባተ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.