July 20, 2020
1 min read

አቤት ውበት! (ዘ-ጌርሣም)

አመለ ለስላሳ መልኳ የሚያሳሳ
ጉርብትና አክባሪ ወዳጅ የማትረሳ
ባለትልቅ ታሪክ ገድል ያስነበበች
ለጥቁር ዘር ሁሉ ትምሣሌት የሆነች
በቅዱስ መጽሐፍት ስሟን ያስከተበች

አቤት ውበት !

የብዙሃን እናት የቋንቋም ጎተራ
ሰፊ ጫካ ለባሽ በሚያኮራው ጋራ
ለልጆቿ ኩራት ጠላት የሚያስፈራ
የፏፏቴው ጩኸት ያስመታል ዳንኪራ

አቤት ውበት !

ፊደላትን ፈጥራ
ዘመናትን ቆጥራ

የግል ባህሏን አዳብራ ገንብታ
የመጣውን ጠላት በራሷ መክታ

የምትታይ ፈክታ እንደ አደይ አበባ
በሰማኒያ ዘሮች ደምቃና ተውባ

አቤት ዉበት !

ከሃያላኖቹ ዕኩል ተሰላፊ
ዓለም አቀፍ ህግን በጋራ ነዳፊ

ለሰው ልጆች መብት ዋቢና ጠበቃ
ቀድማ ተሰላፊ በግፍ ለተጠቃ

አቤት ውበት !

ይህችን ድንቅ ሀገር የኖረች ተከብራ
በህብረት እንገንባት አንደ ፀሃይ ታብራ

አድጋ ተመንድጋ በልጽጋ አንድናያት
እጅና ጓንት ሁነን ከፍ ከፍ አናርጋት

የውበቷ ድባብ ከሩቅ ለሰባችሁ
ኢትዮጵያ መሆኗን እኔው ላብስራችሁ

አቤት ውበት !

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop