መጋቢት 10፣ 2020
መግቢያ
የአደዋን ድል ምክንያት በማድረግ ሰሞኑን በአገር ቤት፣ በተለይም በአዲስ አበባና በውጭ አገሮች አንዳንድ ከተማዎች በድምቀት ተከብሯል። ይህንን የመሰለውን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ህዝቦችና ለሌሎችም በቅኝ አገዛዝ ስር ይማቅቁ ለነበሩት ህዝቦች ምሳሌ የሆነውን ታላቅ የድል በዓል ስናከብር ብዙ ዐመታት አልፎቷል። በተለይም በአለፉት አስር ዐመታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የአደዋ በዓል በየዓመቱ መከበሩ የሚያረጋግጠው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ የቱን ያህል አዲስ የአገር ወዳድ ስሜት እንዳደረበት ብቻ ሳይሆን፣ ከእንደዚህ ዐይነቱ ታላቅ ድምልም የሚጠብቀውም ነገር እንዳለ ነው የሚያመለክተው።
እንደሚታወቀው በተለይም የህወሃት አገዛዝ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በተቆጣጠረበት ዘመን በጊዜው የነበረውን የዘመናዊነትና የተሃድሶ ክፍተት ከማሻሻልና አገሪቱን በአዲስና በፀና መሰረት ላይ ከመገንባትና ከማጓዝ ይልቅ የታሪክን ሂደት ለመቀልበስ ሲል አገራችንን በዘጠኝ የብሄረሰብ ክልሎች ሽንሽኖ አዲስ ፈተና ውስጥ እንደከተተን የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የኤርትራ መገንጠልና፣ በተለይም ደግሞ የአሰብ ወደብን እንዳንጠቀምበት ማድረጉ የብሄራዊ ነፃነታችንን ማናጋቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ደግሞ በህዝባችን ዘንድ ውስጣዊ አንድነትና የጋራ እሴት እንዳይኖር በማድረግ በህዝባችን ዘንድ አለመተማመን ሊፈጥር ችሏል። የጋራ እሴትና ምንም የሚያገናኘን ነገር የሌለ ይመስል ሁሉም በየፊናው የራሱን አርቲፊሻል ማንነት በመለጠፍ ተባብሮ አገሩን እንዳይገነባ ሊደረግ በቅቷል። ይኸው እንደምናየው በዛሬው ወቅት የህዋሃት አገዛዝና ግብረ-አበሮቹ በዘሩት የመርዝ ዘር ህዝባችን ይሰቃያል፤ በአዳዲስና በአረጁ የጽንፈኛ ኃይሎች ግራ በመጋባት ወዴት እንደሚጓዝ የሚያውቅ አይመስልም። ከዚህ ጋር ተያይዞ አገሪቱን በክልል ከልሎ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በሚያካሂድበት ወቅትና፣ ለአገር የመከለካያ ኃይል ጥንካሬ የሚሰጠውንና መሰረት የሚሆነውን የጋፋት የጦር መሳሪያንና የማሽን ፋብሪካ ከበታተነ በኋላ አባይን ልገድብ ብሎ መነሳቱ ዛሬ እንደምናየው በቀላሉ ልንወጣ የማንችልበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ከቶን አልፏል። ከዚህም በላይ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ሊያስገነባና የአገር ውስጥ ገበያ ሊያሳድግና ሊያስፋፋ የማይችል የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተሉና ተግባራዊ ማድረጉ በተለይም በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ብሄራዊ ስሜት እንዳይዳብርና ህዝባዊ እሴትም እንዲበጣጠስ ለማድረግ በቅቷል።
ዶ/ር አቢይ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ለጊዜው የተስፋ ጭላንጭል ቢታይም በዛሬው ወቅት የአገራችን አንድነት በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል። አገሪቱ በፖለቲካ ስም ማንም የሚፈነጭባት ሆናለች። የተገለጸላቸውና አዲስና ብሩህ ሃሳብ ያላቸው ኃይሎች ሳይሆኑ ሜዳውን ያጠበቡት በፖለቲካ አክቲቪስት ስም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች እንድ አሽን በመፍለቅ ከፍተኛ ውዝንብር በመንዛት ላይ ይገኛሉ። ያልተገለጸላቸውና ሰፋ ያለ ዕውቀት የሌላቸው የክልል አስተዳዳሪዎች በሚከተሉት ፖለቲካ-አልባ ፖሊሲ በየክልሉ የሚኖሩ ሰዎች ግራ ተጋብተው ይገኛሉ። ክልሎችን የሚያረጋጋና የፈጠራ ችሎታን የሚያዳብር ሰፋ ያለ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፖሊሲ ከመንደፍ ይልቅ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሚሊሺያኖችንና ፖሊሶችን በማሰልጠን አንደኛው ክልል ከሌላው ክልል ጋር ይፋለም ይመስል ቀንን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ ዐይነት የተዘበራረቀና ወደ ኋላ የሚጓዝና ወደ ኋላ የቀረ ፖለቲካዊ አካሄድ ስንነሳ በአደዋ ላይ የተገኘውን ድል በሙሉ ስሜት አይደለም ያከበርነውና አሁንም የምናከበረው። በእኔ ዕምነት ይህ ዐይነቱ ታላቅ የድል በዓልና አፄ ምኒልክ የተከተሉት የዘመናዊነት ፖሊሲ(Modernization Policy) ጽንፈኛ ለሆኑ ወይንም ተጨቁነን ነበርን ለሚሉም ሆነ ለኢትዮጵያ አንድነት እንታገላለን፣ የሶስት ሺህ ዓመት ታሪክ አለን ለሚሉት ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ግልጽ ያልሆነላቸው ነገር አለ። ስለሆነም ይህ ጸሀፊ እንደተለመደው ከዚህ ዐይነቱ ውዥንብር ለመውጣትና በአዲስ መንፈስና በአገር ወዳድ ስሜት ለመታገል ይቻል ዘንድ በተለይም የአፄ ምኒልክን የዘመናዊነት ፖሊሲ ምንነትና ተልዕኮውን ለማሳየት ይሞክራል። በዚህ ጸሀፊ ዕምነት ዘመናዊነትና የዘመናዊነት ፖሊሲ ትርጉምና መሰረታዊ ዓላማቸው እስካልታወቀ ድረስ ዘለዓለማችንን እየጮህንና እየተደነባበርን እንደምንኖር ግልጽ መሆን አለበት።
አፄ ምኒልክ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የኢትዮጵያ ፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ
ምን ይመስል ነበር?
በተለይም የኢትዮጵያ ታሪክ አከራካሪ የሚሆነው አብዛኛውን ጊዜ ስለ አገራችን ታሪክ ሲጻፍ አጻጻፉ የኢትዮጵያን ህዝብ የማይመለከትና በምንስ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር በፍጹም ግንዛቤ ውስጥ የሚያስገባ በመሆኑ ነው። በአብዛኛዎቹ የአገራችን ታሪክ ጸሀፊዎች የአጻጻፍ ስልት የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ግኑኝነትና (Social and Economic Relationship) የባህል ሁኔታዎች (Socio-Cultural Conditions) ምን እንደሆኑ የሚታወቁ አይመስሉም። በአገራችን የታሪክ አጻጻፍ ልምድ የሚታወቁት ንጉሶች እንጂ፣ ንጉሶችና የአገዛዞቻቸው መሰረት በምን ዐይነት የኢኮኖሚ መሰረት ላይ እንደቆመና የገበሬውና የተቀረው ህዝብ የአኗኗር ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር በግልጽ ቀርቦ ውይይት ሲደረግበት አይቼም ሰምቼም አላውቅም። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ በተበጣጠስ መልክ ካልሆነ በስተቀር በየታሪክ ኤፖክ ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ መልክ ነበር የሚኖረው፣ ከተፈጥሮ ወይም ከመሬት ጋር የነበረው ግኑኝነት ይህንን ይመስል ነበር፣ ከዚህም በላይ በነገስታትና በተቀረው የአሪስቶክራሲው መደብና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በገበሬውና በተቀረው ህዝብ መሀከል የነበረው ግኑኝነት ይህንን ይመስል ነበር ተብሎ ያስተማረኝ አልነበረም፤ ወይም በጽሁፍ ቀርቦ እንድንወያይበት አልተደረገም።
አውሮፓ ውስጥ ከመጣሁና ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኋላ ግን ልገነዘብ የቻልኩት የአውሮፓው የታሪክ አጻጻፍ ከእኛው ለየት ያለና ብዙም ጉራ የሚበዛበት አይደለም። የታሪክም አጻጻፍ ከህብረተሰብአዊ ድርጊቶችና ግኑኝነቶች ተነጥሎ አይታይም፤አይጻፍምም። ህብረተሰብአዊ ታሪክም በተለያዩ መልኮች የሚገለጽ ሁለ-ገብ ዕድገት ነው። እነዚህም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሲሆኑ፣ በዚያው መሰረትም በሰው አስተሳሰብ ላይ የሚኖራቸውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚዳስስና የሚተነትን ነው። ስለሆነም በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ አጻጻፍ ውስጥ ሁለት ዐይነት የአቀራረብና የአጻጻፍ ስልቶች አሉ። አንደኛው መንፈስንና የማቴሪያል ሁኔታዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የማቴሪያል ሁኔታዎችን ብቻ የሚመለከት የአጻጻፍ ስልት ነው። የመጀመሪው የአጻጻፍ ስልት በተለይም በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የነበረውን የአገዛዞችም ሆነ የህዝቡን የመንፈስ ወይም የአስተሳሰብ ሁኔታና የሚመኩበትን የማቴሪያል መሰረት (Production and Reproduction Base)የሚመረምር ሲሆን፣ በጊዜው ከነበረው ሁኔታ በመነሳት ለዕድገትና ለአስተሳሰብ ለውጥ ማነቆ የሆኑ ነገሮችን በመመርመርና በትንተና መልክ በማቅረብ መሰረታዊ ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ ማሳየት ነበር። ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ፣ በተለይም በአገዛዞችና በሰፊው ህዝብ መሀከል የነበረውን የምርት ግኑኝነት የሚመለከትና፣ በዚህ ዐይነቱ የምርት ግኑኝነት አማካይነት የሚደረገውን ብዝበዛ የሚመረምር ነው። ስለሆነም የምርት ኃይሎችን ማደግና አለማደግ፣ የሀብት ክፍፍልን ሁኔታና፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ከሚመረተው ምርት አብዛኛው ምርት ለየትኛው የህብረተሰብ ክፍል እንደሚደርስ በመመርመር የዕድገትንና የፀረ-ዕድገትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው። ይሁንና በሁለተኛው አጻጻፍና የአተናተን ስልት መሰረት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለካፒታሊዝም ወይም ለገበያ ኢኮኖሚ መሰረት የተጣለው በጊዜው አባባል ፊዩዳል በመባል በሚታወቀው የህብረተሰብ አወቃቀር ውስጥ እንደነበር በግልጽ ተቀምጧል። በሌላ አነጋገር በጊዜው የነበረው ስርዓት ባለበት ቆሞ የሚቀር ሳይሆን ከውስጡ በሚፈልቁ አዳዲስ ኃይሎች ጋር በመጋፈጥ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ይገደዳል። በድሮ አስተሳሰብና የአመራረት ስልት መኖር እንደማይቻል በመረዳት አዲስና ውስጣዊ ኃይሉ ከፍ ባለ ኃይል መተካት የታሪክ ግዴታ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ይገባል።
በመሰረቱ በሁለቱም የአተናተን ዘዴዎች መሰረት የማንኛውም አገር ታሪክ አንድ ቦታ ላይ ረግቶ የሚቀር ሳይሆን ከዝቅተኛ ሁኔታ በመነሳት እያደገ የሚሄድ ነው። ይሁንና የዕድገቱ ፍጥነት በየጊዜው በሚፈጠሩት የአገዛዝ መዋቅሮችና የፖለቲካ ሁኔታዎች የሚወሰን ነው። ሀብትን የሚቆጣጣሩና የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች በኃይላቸውና በሀብታቸው ብቻ የሚመኩ ከሆነ ዕድገትና መሻሻል አይኖርም። በመሆኑም በአውሮፓ ምድር ውስጥ ብዝበዛንና የጭቆናን ስርዓት አስመልክቶ በየቦታው በገበሬውና በባላባቱ መሀከል ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዷል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ የግዴታ የጥገና ለውጥ እንዲመጣ ለማስገደድ በቅቷል። የፖለቲካ ስልጣንን የጨበጡና መሬትን ይቆጣጠሩና ከገበሬውም ከፍተኛ ምርት ይጠይቁ የነበሩ በድሮው የብዝበዛ ስርዓታቸው ለመቀጠል ባለመቻላቸው የግዴታ የጥገና ለውጥ እንዲያደርጉ ተገደዱ። በተለይም በአንዳንድ በተገለጸላቸው የሃይማኖት መሪዎች የተካሄደው ያልተቋረጠ ትግል በዕውቀት አካባቢ ዕምርታን ማሳየት ቻለ። ቀደም ብሎ የመማርና የማወቅ ዕድል ያልነበረው ገበሬ ፊደልን የመቁጠር ዕድል በማግኘቱ አዕምሮውና ዐይኖቹ መገለጥ ቻሉ። የኑሮን ትርጉም መረዳትና የተፈጥሮን ምንነት መገንዘብ ቻለ። የመጠየቅና የማሰብ ኃይሉ ከፍ እያለ መምጣት ቻለ። በራሱ ላይም ለመተማመን በቃ። ይህ ዐይነቱ ጥገናዊ ለውጥና በምሁሮች ዘንድም ይደረገ የነበረው ያልተቋረጠ ምሁራዊ ትግል በአውሮፓ ምድር ውስጥ በጊዜው ሰፍኖ የነበረውንና የዕድገት ጠንቅ የሆነውን ዲስፖታዊ አገዛዝን መጋፈጥ ቻለ። ጊዜው የኢንላይተንሜንት ዘመን በመሆን ለሲብል ማህበረሰብ መሰረት እየተጣለ መጣ። የግለሰብ ነፃነት ሲያብብ፣ የፈጠራ ስራዎችም መዳበርና የኢኮኖሚ ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር በመሆን ሁለ-ገብ ዕድገት ሊመጣ ቻለ። ይህ ዐይነቱ ለውጥ ሊመጣ የቻለው በጊዜው በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተስቦ በሽታ በመስፋፋቱና በገዢ መደቦችም መሀከል የማያቋርጥ ጦርነት በመካሄዱና በዚህም መቀጠል የማይቻል መሆኑን በተረዱ በተገለጸላቸው ምሁራን አማካይነት ነው።
በአውሮፓ ምድር ውስጥ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የተንሰራፋውን በሽታና የማያቋራጥ ጦርነትን የተመለከቱ ምሁራን ምክንያቱን መመርመርና ማጥናት ተገደዱ። በየጊዜው የሚከሰተውን የተስቦና ሌላ የወረርሽኝ በሽታዎችና በመሳፍንቶች መሀከል የሚደረገውን የእርስ በእርስ ጦርነትም ሆነ በአገሮች መሀከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማቆምም ሆነ በሽታዎችን ለማስወገድ የግዴታ የችግሩን ዋና ምክንያት በመረዳት መፍትሄ መፈለግ አስፈላጊ ነበር። በጊዜው የነበረውም መፍትሄ የመንፈስ ተሃድሶንና የፖለቲካ ዘመናዊነትን ተግባራዊ ማድረግ ነበር። በዚህ መሰረት ደጋግሜ በተለያዩ ጽሁፎቼ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአውሮፓው ማህበረሰብ በጊዜው ሰፍኖ ከነበረው የጭቆናና የነፃነት ጠንቅና ኋላ-ቀር አገዛዝ ለመላቀቅ ታውቆም ሆነ ሳይታወቅ በሶስት መሰረታዊ የባህል ለውጦች ሂደት ውስጥ ማለፍ ነበረበት። ሶስቱም የመሰረታዊ ለውጥ ሂደቶች የየራሳቸውን ማህተም በማስረገጥ በአውሮፓ የማህበረሰብ አወቃቀር ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ፣ እንዲያም ሲል ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታ ፈጥረዋል። እነዚህም መሰረታዊ ለውጦች በሁለ-ገብ የሚገለጹ ሲሆኑ፣ ለከተማዎች ዕድገት፣ ለንግድ እንቅስቃሴና ለኢንዱስትሪ ዕድገትና በተለይም ለገበሬው የኑሮ ለውጥ አመቺ ሁኔታዎችን ሊፈጥሩ ችለዋል። ስለሆነም በአውሮፓ ምድር ውስጥ እንደዚህ ዐይነቱ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ፈላስፋዎች፣ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች፣ የቲዎሎጂ ምሁራን፣ ሰዓሊዎችና የአርክቴክቸር ሰዎች፣ ደራሲዎችና የሊበራልን አስተሳሰብ የሚያሰተጋቡ ታላላቅ ምሁራን፣ እንዲሁም በጊዜው እያደገ የመጣውን የከበርቴውን መደብ የበላይነት የሚያረጋግጥ መልዕክት የሚያስተላልፉና በዚያው መጠንም የፊዩዳሉን መደብ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ የሚታገሉ…ወዘተ. በመካፈል የመጨረሻ መጨረሻ ካፒታሊዝምና የሊበራል አስተሳሰብ በአሸናፊነት ሊወጡ ችለዋል።
ወደ አገራችን ስንመጣ በተለይም ከ13ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የፊዩዳሉ ስርዓት የተዘረጋ መሆኑን ቢታወቅም፣ ይህ ዐይነቱ ስርዓት የቱን ያህል ለዕድገት ወይም ለካፒታሊዝም መነሳት ማነቆ እንደነበር በደንብ ተተንትኖ አያውቅም። በተለይም ደግሞ አፄ ምኒልክ ጠቅላላውን ኢትዮጵያን በአንድ አገዛዝ ስር እስካጠቃለሉበት ድረስ በተቀሩት የፊዩዳሉ ስርዓት ባልተዘረጋባቸው ቦታዎች ምን ዐይነት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት እንደነበር በሰፊው የተጠናና ለህዝብ ቀርቦ ውይይት አልተደረገበትም። በዚህ ጸሀፊ ጥናት መሰረት በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ድረስ በጊዜው የነበረውን ከመሬት ጋር የተያያዘ የአኗኗር ስልትና፣ የንግድና የዕደ-ጠበብ ስራዎችን አለማበብ አስከትሎ የተደረገ የፖለቲካና የማህበራዊ እንቅስቃሴ አልነበረም። በመሆኑም በጊዜው የነበረው የአኗኗር ስልት እንደ ተፈጥሮአዊ ነገር በመታየቱ ለቴክኖሎጂና ለከተማዎች ዕድገት መሻሻል የሚታገል ምሁራዊ ኃይል በኢትዮጵያ ምድር አልነበረም ማለት ይቻላል። በአውሮፓ ምድር ውስጥ በተለይም ከአስራሶስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ መንፈስን የሚያድሱና የማቴሪያል ሁኔታዎች እንዲለወጡ አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን ትግል ሲያደርጉ የእኛው ህብረተሰብ አፄ ምኒልክ እስከነገሱበት ጊዜ ድረስ የተኛ ወይም የአንቀላፋ ነበር ማለት ይቻላል። ንግድና የቤተሰብ ኢንዱስትሪዎች አይታዩም ወይም አይታወቁም ነበር። ገበሬውም ሆነ የተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ተገልለው የሚኖሩ እንጂ አንድ የሚያገናኛቸው የመገበያያና የሃሳብ መለዋወጫ መድረክ አልነበራቸውም። ስለሆነም እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ኢንዱስትሪ ወይም በዕደ-ጥበብና በንግድ ላይ የተመሰረተ የአገር ቤት ውስጥ (Home Market) በፍጹም አይታወቅም ነበር። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ደግሞ የተገለጸለትና ለሊበራል አስተሳሰብ የሚታገል ኃይል ብቅ እንዳይል ከፍተኛ መሰናክል ሊፈጥር ችሏል። በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥና ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ ፊዩዳላዊ ሽኩቻዎች መኖራቸው የሚገርም አይደለም። በሌላ ወይም በፈጠራ ስራ የማይያዝ ህብረተሰብና የገዢ መደብ ዋና ተግባራቸው ጦርነትና የእርስ በእርስ ሽኩቻ ብቻ ነው።
አፄ ቴዎድሮስም ሆነ አፄ ምኒልክ ሲነግሱ ለዚህ ዐይነቱ የፊዩዳል ሽኩቻና የእርስ በእርስ ጦርነት ዋናው ምክንያት የአገሪቱ ኋላ መቅረት እንደነበር ግልጽ የሆነላቸው ይመስላል። ሁለቱም መሪዎች በጊዜው የኢንዱስትሪ አብዮትን አስፈላጊነት የተመኙና ተግባራዊም ለማድረግ የታገሉ ታላላቅ ንጉሶች ነበሩ። ይሁንና በተለይም የአፄ ቴዎድሮስን የዕድገት ፍላጎት ለመገንዘብ ያልቻለው የባላባቱ መደብና የቤተክህነት ሰዎች የጥገና ለውጥ አካሄዳቸውን አጥብቆ መዋጋት ጀመሩ። በሰፊው ህዝብ እንዲጠሉ የሚሆን የማይሆን ነገር በማስወራት እንዲገለሉና እንዲበሳጩም ለመደረግ በቁ። በተከተሉትም ጥበብ ያልታከለበት ፖለቲካ ድጋፋቸው እየቀነሰ መጣ። ይህ ዐይነቱ ፖለቲካቸውም ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ከተታቸው። ነገሩን ሊያበርዱ የሚችሉበትን ዘዴ ከመፈለግ ይልቅ በመካረር የመጨረሻ መጨረሻ ህይወታቸውን ለመሰዋት ተገደዱ። በሳቸው አለጊዜያዊ መሞት ህልማቸውም በዚያው ተቀጨ። የዘመናዊነት ሂደት ጊዜን እንዲጠባበቅ ተደረገ። በታሪክ አጋጣሚና በነበረው የእርስ በእርስ ሽኩቻ አማካይነት አፄ ምኒልክ በአሸናፊነት በመውጣት አዲስ የዘመናዊነትን ፈለግ እንዲከተሉ አስቻላቸው፤ አስገደዳቸው።
ከዚህ ስንነሳ ስለአገራችን ታሪክ በምንጽፍበትና ስለዛሬው ሁኔታ በምንነጋርበት ጊዜ በመጠኑም ቢሆን በየኤፖኩ በአጠቃላዩ የአገራችን ምድር የነበረውን የማቴሪያልና የመንፈስ ሁኔታ መመርመርና ማጥናት ያስፈልጋል። ይህንን ሳናደርግ ዝም ብሎ በጭፍን ትግል ለማድረግ መነሳት እጅግ አደገኛና ለሌላ የትግል ዙር የሚጋብዘን ይሆናል ማለት ነው። በሽታውን ያላወቀ ወይም የደበቀ መድሃኒት አይገኝለትም እንደሚባለው፣ በሽታችንን በሚገባ ማወቅ እስካልቻልን ድረስ በጭፍን ፖለቲካ እያሉ መጮህ የኋላ-ቀርነቱን ዘመን ማራዘም ነው። እንደዚህ ስል ግን ሁኔታውን እዚህ ላይ በተሟላ መልክ ለማቅረብ ችያለሁ ማለት አይደለም። ይህንን ለመረዳት የሚፈልግ ወደ 500 ገጽ የሚጠጋ ስለኢትዮጵያ ህብረተሰብ አወቃቀርና ለዕድገት ማነቆ የሆኑ ምክንያቶችንና፣ በተለይም አገራችን ለምን ወደ ካፒታሊዝም ስርዓት ለመሸጋገር አልቻለችም የሚለውን የዶክትሬት ስራዬን ቢያነብ አንዳንድ ጠቃሚ ማስረጃዎችን ማግኘት ይችላል። በተጨማሪም አሁን በቅርቡ የአፍሪካን ኢኮኖሚ ሁኔታ አስመልክቶ፣ „African Predicaments and the method of solving them effectively“ በሚለው መጽሀፍ ውስጥ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መከተልና የተበላሽ መንግስታዊ አወቃቀር እንዴት የዕድገት፣ በተለይም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ማነቆዎች በመሆን አንድን ህዝብ ደሃና አገርንም ደካማ ለማድረግ እንደሚበቁ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ከዚህም በላይ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በ60ኛውና በ70ኛው ዓ.ም በማርክሲስት ጸሀፊዎችም ሆነ በከበርቴው ጸሀፊዎች በአውሮፓ ውስጥ ስለተደረገው የህብረተሰብአዊ ለውጥ ክርክር (Transformation debate) ዕድል ያጋጠመውና ፍላጎትም ያለው ክትትል ቢያደርግ ጠቃሚ ትምህርቶችን መቅሰም ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም የመንፈሳዊ ለውጥ አስፈላጊነትና ግልጽነትን አስመልክተው የተጻፉትን መጽሀፎች ማገላበጥ ቢቻል ማንኛውም ሰው ጠቃሚ ትምህርቶች ሊቀስም ይችላል። ካፒታሊዝም በአውሮፓ ምድር ውስጥ እንዴት ማደግ ቻለ? ከተማዎችና መንደሮችስ እንዴት ሊገነቡ ቻሉ? ዕውቀትስ እንዴት ሊፈልቅና ሊዳብር ቻል? በተስተካከለ ዕድገት ላይም ምን ዐነት ሚና ይኖራቸዋል? የመንግስት መኪናና የመንግስት ሚና በዕድገትና በአገር ግንባታ ላይ ምን ዐይነት ሚና ይኖራቸዋል? እነዚህን የመሳሰሉትና ሌሎች ለህብረተሰብ ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች በሰፊው ሳይጠኑና ክርከር ሳይደረግባቸው በጭፍን በገበያ ኢኮኖሚ ስም ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎች እንደምናየው ዝብርቅርቅና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮችን ነው የሚያስከትሉት። በአቦ ሰጡኝ ወይንም በውጭ ኃይሎችና አማካሪዎቻቸው ግፊት ተግባራዊ የሚሆኑ ፖሊሲዎች የተስተካከለ ሀብትን ከመፍጠር ይልቅ ድህነትን ነው የሚፈለፍሉት። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ንፅፅራዊ ጥናት(Comparative Studies) ተግባራዊ ለሚደረግ ለውጥ በጣም ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ። በተለይም የብሄረሰብ ነፃነትን አርማ ይዘው የጽንፈኝነትን ፖለቲካ የሚያራምዱ ኃይሎች በእንደዚህ ዐይነት ጥናት ውስጥ ሳይሳተፉ የሚያካሂዱት የጭፍን ጉዞ የመጨረሻ መጨረሻ ልንወጣ የማንችለው ማጥ ውስጥ ነው የሚከተን። የጨለማውን ዘመን ነው የሚያራዝመው። ስለሆነም በእኔ ዕምነት ንፅፅራዊ ጥናት ሳያካሂዱና የዛሬውን የግሎባል ካፒታሊዝምን ሁኔታ ሳያጠኑ በጭፍን የሚወሰድ ፖለቲካና ተግባራዊ የሚሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ፋሺዝም ነው የሚያመራን።
የአፄ ምኒልክ የዘመናዊነት ፖሊሲ ትርጉምና መልዕክቱ!!
አፄ ምኒልክ ከነገሱና ስልጣናቸውን ሲጨብጡ ኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫ ወደ ኋላ የቀረች አገር ነበረች። ይህ ነው የሚባል ከተማና የመንደሮች ቅርጽ አልነበራትም። በየክፍለ-ሀገራት ውስጥ ዘመናዊ የሚባሉ ቢሮክራሲያዊ ተቋሞች አልነበሩም። ንግድና የዕደ-ጥበብ ሙያዎች ይህንን ያህልም አልበለጸጉም ወይም የኢኮኖሚና የባህል መሰረት መሆናቸው አይታወቅም ነበር። የተገለጸለት ምሁራዊና ከበርቴያዊ ኃይል አልነበርም። በአጭሩ በአገሪቱ ውስጥ ዘመናዊነት የሚባልና፣ በተለይም የገጠሩን ህዝብ ከነበረበት ኋላ-ቀር አኗኗር ሁኔታ ውስጥ ሊያላቅቀው የሚችል እንቅስቃሴ አልነበረም። የሊበራሊዝም አስተሳሰብ በፍጹም አይታወቅም ነበር። በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የቤተክህነት ትምህርት ከመስፋፋቱ በስተቀር ለስልጣኔ የሚያመች የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ዕውቀት አይታወቅም ነበር። በአንፃሩ በአውሮፓ ምድር ከአስራ አራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ስለኢኮኖሚ ቲዎሪና ፍትሃዊነት ስለሚኖረው ዋጋ ክርክር ይደረግ ነበር። በተለይም ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የፖለቲካ ኃይልን የሚያንጸባርቁ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎችና ፖሊሲዎች በመፍለቅ ክርክር ይደረግባቸውና ነገስታትም ተግባራዊ እንዲያደርጓቸው ግፊት ይደረግ ነበር። በአውሮፓ ውስጥ ህብረ-ብሄሮች ሲመሰረቱ ነገስታቶች ሆን ብለው የያዙት ወደ ውስጥ ያተኮረ የአገር ግንባታ ፖሊሲን መከተል ነበር። ስለሆነም ህዝቡን እንደማህበረሰብ የሚያያዘውን ከተማዎችን መገንባትና የተለያዩ ከተማዎችን በመርከብም ሆነ የኋላ ኋላ ደግሞ በባቡር ማያያዝና ማገናኘት የተለመደና አስፈላጊም ጉዳይ ነበር። በዚህ መልክ በመንግስታት ፖሊሲ አማካይነት ብቻ የረቀቀው እጅ ተግባራዊ እየሆነ መጣ። የገበያ ኢኮኖሚ ወይም ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ማደግ ቻለ። ባጭሩ ይህንን ዐይነቱን ወደ ውስጥ ያተኮረ ግንባታ ለማካሄድ የሚችል ምሁራዊ ኃይልና የተገለጸለት ከበርቴያዊ መደብ ብቅ ማለት በመቻሉ ህብረተስብአዊ ለውጥ ሊመጣ ቻለ። አዲሱ የከበርቴ መደብ ደግሞ በክልል ደረጃ የሚያምን ሳይሆን በአገር ደረጃ ነበር። የገበያ ኢኮኖሚም በክልል ደረጃና አንድ ወጥ የሆነ አስተሳሰብ በነገሰበት አካባቢ ለማደግ በፍጹም አይችልም። ዕውነተኛ ዕድገት የብዙ ነገሮች ጭምቅ(Synthetic) ነገር ነው። ውድድር ሲኖር ብቻ ነው ቴክኖሎጂ ሊያድግና አገራዊ ባህርይ ሊወስድ የሚችለው። የብሄረሰብ አስተሳሰብ በነገሰበት ዓለም ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በፍጹም ሊያድጉ አይችሉም። ስለሆነም በዚህ አማካይነት ብቻ ነበር በአውሮፓ ምድር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመዳበር የቻለውና ማኑፋክቱር የኢኮኖሚው መሰረት በመሆን የኢንዱስትሪ አብዮት ሊካሄድ የቻለው።
ወደ ኢትዮጵያችን ስንመጣ እነዚህ ለዘመናዊነት የሚያገለግሉና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች በሙሉ ይጎድሉ ነበር። በጠቅላላው አገሪቱ ውስጥ ዕድገት የሚባል ነገር አይታውቀም ነበር;፡ ከዚህ ሁኔታ በመነሳት የአገራችንን ኋላ-ቀርነት የተገነዘቡት አፄ ምኒልክ ዘመናዊ የሚባለውን ፖሊሲ መከተላቸው የታሪክ ግዴታና ሞራላዊ ኃላፊነታቸውም ነበር። ዋና ከተማን መቆርቆር ወይም ያለውን ማስፋፋት፣ ለመገበያያ የሚያገለግል ገንዘብ ማተምና የማዕከላዊ ባንክ ማቋቋም፣ ፖስታ ቤት መክፈትና ቴምብር ማተም፣ በተወሰኑ ቦታዎች ድልድዮችንና መንገዶችን መስራት፣ ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የባቡር መንገድ መዘርጋት፣ ቤተመንግስት ድረስ የመጀመሪያውን ውሃ ቧንቧ መዘርጋት፣ የመጀመሪያው ጋዜጣ መታተም፣ ሆቴል ቤት መከፈት፣ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል በአዲስ አበባ መዘርጋት…ወዘተ. እነዚህን የመሳሰሉት በሙሉ የዘመናዊነት ፖሊሲዎች ምልክቶች ነበሩ። አገዛዙ ወደ ተስፋፋበት ወደ ደቡቡ ክፍል ስንመጣ ደግሞ የአገዛዝ ተቋማትን መዘርጋት እንደዘመናዊነት ሊቆጠሩ የሚችሉ ነበሩ። ይሁንና እንደ አውሮፓው ዐይነት የማዕከለኛው ዐይነት ከተማዎችና ቤተ-ክርስቲያናትና የዕደ-ጥበብ ሙያዎች ባለመስፋፋታቸው ጠቅላላውን የአገሪቱን ግዛት በዘመናዊ አስተዳደር ለማዋቀር በጣም አስቸጋሪ ነበር። የነበረው አማራጭ የቤተክህነት ትምህርት የተማሩ ሰዎችን በየቦታው ማሰማራት ግዴታ ነበር። ያም ሆኖ አገሪቱ በአፄ ምኒልክ ዘመን ለማየት የበቃችው የዘመናዊነት ፖሊሲ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ አገራዊ ስሜትን ማዳበር ችሏል። ህዝቡ ልሰራና ልኖርበት እችላለሁ ወደ ሚለው ቦታ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር። በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ በሰው ብዛት ሞቅ ሞቅ ማለት ጀምሮ ነበር። በዚያው መጠንም መጠነኛ የፈጠራ ስራዎችና ራስን መቻል አስፈላጊ እየሆኑ በመምጣት ላይ ነበሩ።
ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ ከላይ በተነፃፃሪ መልክ ለማሳየት እንደሞከርኩት የራሱ የሆነ ገደብ ነበረው። ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመታወቁ የመንፈስ ተሃድሶ ማካሄድ አልተቻለም ነበር። ስለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ በመንፈስ ተሃድሶ አማካይነት መደረግ የነበረበት የዘመናዊነት አካሄድ የመተግበር ዕድል ማግኘት አልቻለም። ዘመናዊ ፖሊሲው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ በአማዛኝ ጎኑ በማቴሪያል ለውጥ ላይ ብቻ እንዲያተኮር ለመገደድ በቅቷል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ የግዴታ በደቡቡ ክፍል አዲስ ዐይነት የፊዩዳል ኢኮኖሚ ግኑኝነትን እንዲመሰረት አስቻለ። በሌላ አነጋገር፣ የአፄ ምኒልክ የዘመናዊነት አካሄድ እርስ በእርሱ የሚቃረንና ለፈጣን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚያግዝ ነበር ብሎ መናገር ያስቸግራል። ይህም የሆነበት ምክንያት በሳቸው ስህተት ሳይሆን በየቦታው የተገለጸለት ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ ብቻ ነው። በተጨማሪም ከኋላ ወይም ከበስተጀርባቸው ሆኖ ምክር የሚለግሳቸውና የሚገፋፋቸው ህብረተሰብአዊ ኃይል(Social Forces) አልነበረም። በእሳቸው ዙሪያ የተሰበስበው አሪስቶክራሲ በፊዩዳል ሽኩቻ የተያዘ ነበር። ምህራዊ ኃይሉ በጣም ደካማ ስለነበር ስትራቴጂካሊ ለማሰብና ሰፋ ያለ የአገር ግንባታ ፖሊሲ ለመቀየስ የሚያስችል ኃይል አልነበረውም።
ለማንኛውም ዛሬ የሚያጨቃጭቀንና ግራ ያጋባንን ሁኔታ ለመረዳት የነገሮችን ሂደት ወይም የህብረተሰብአችንን አወቃቀር የግዴታ ወደ ኋላ መለስ ብለን ማየትና መመርመር አለብን። ምን ምን ነገሮች ለዕድገት ማነቆ እንደነበሩ በሰፊው ማጥናት አለብን። ይህንን ሳናደርግ በጭፍን የምናስተጋባው ውንጀላ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክና ህዝብ አጉዝፎ ማየት ለጤናማ ውይይትና ለሁለ-ገብ ዕድገት እንቅፋት ይሆናል። ይሁንና የአፄ ምኒሊክ የዘመናዊነት ፖሊሲ ገደብ ቢኖረውም በተለይም ደግሞ በአደዋ ላይ በወራሪው ጣሊያን ላይ ድልን መቀዳጀት የራሳቸው መልዕክት አላቸው። ይኸውም ነፃና ጠንካራ አገር መመስረት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያመለክት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ የህዝቡ ነፃነት የሚረጋገጥበትን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማስፋፋትና ማዳበር ሊታለፍ የሚችል አይደለም ብሎ የሚጋብዝ ነው። ከዚህም በላይ ከተማዎችንና መንደሮችን በመገንባትና በተለያዩ የመገናኛና የመመላለሻ ዘዴዎች በማገናኘት ብሄራዊ ስሜትን ማዳበር የዘመናዊነቱ ዋና መልዕክት ነው። የአደዋ መልዕክትና የዘመናዊነት ዋናው ዓላማው የቅኝ አገዛዝን በተዘዋዋሪ መንገድ ወይም በጓሮ ማስገባት ሳይሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ፣ በጥሩ አርኪቴክቸሮች የሚገለጽ ከተማዎች መገንባትና ብሄራዊ ድራማና ቲአትር በአገሪቱ ምድር ማስፋፋት ነው። አፄ ምኒልክ የመጀመሪያውን የዘመናዊነት መሰረት ሲጥሉ ዕይታቸው የሚቀጥለው ትውልድ እያሻሻለ ብሄራዊ ነፃነቷ የተከበረችና የማንም አገር ተገዢ ያልሆነች አገር ለመመስረት ይቻላል ብለው በማመናቸውና በማሰባቸው ነበር። ስለሆነም ዋናውንና ፍጻሜ ማግኘት ያለበትን የህብረ-ብሄር ግንባታ ለሚቀጥለው ወይም ለተከታታዩ ትውልድ ጥለው መሄዳቸው ታሪካዊ ግዴታ ነበር።
ይሁንና ይህንን ህልማቸውን ሊያሟላ የሚችል ኃይል ሊፈጠር አልቻለም። አፄ ኃይለስላሴ ስልጣን ዚይዙና ከስደት ሲመለሱም ይህንን ዐይነቱን የአፄን ምኒልክን ህልም በአገሪቱ ምድር ማዳረስና ማሳካት ይችላሉ የሚል ግምት ነበር። በሌላ ወግን ግን አፄ ኃይለስላሴ ንጉስ ይሁኑ አይሆኑ ለአፄ ምኒልክ ቀድሞ ሊታያቸው የሚችል ጉዳይ አልነበረም። የአፄ ኃይለስላሴ ስልጣንን መጨበጥ የኃይል አሰላለፍና የሽኩቻ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ያም ሆኖ ይህ አፄ ኃይለስላሴ አፄ ምኒልክ የተጓዙበትን ብሩህና ሰፋ ያለ የዘመናዊነት ፈለግ መከተል አልቻሉም። የሳቸው የጥገና ለውጥ በዓለም አቀፍ የተስፋፋው የተኮላሸ ዘመናዊነት ለውጥ አካሄድ እንጂ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ነጻ እንድትሆንና በሁለት እግሮቿ እንድትቆም ሊያደርጋት የሚችል አልነበረም። አፄ ኃይለስላሴ አምስት ዓመት ያህል በስደት እንግሊዝ አገር በኖሩም ከዚያ ቀስመው የመጡት የዕድገት ፈለግ አልነበረም። በተጨማሪም እ.አ.አ በ1954 ዓ.ም ጀርመንን የመጀመሪያው የውጭ አገር መሪ በመሆን ሲጎበኙ ከጀርመን መንግስት ጋር ልዩ ዐይነት የዕድገትና የቴክኖሎጂ ስምምነት ማድረግ በቻሉ ነበር። አፄ ኃይለስላሴ በጊዜው የነበራቸውን ወርቃማ ዕድል ለመጠቀም አልቻሉም። በተበጠጣሰ የጥገና ለውጥ ብቻ እንደ ኢትዮጵያ የመሰለን ሰፊ አገር መገንባት የሚችሉ መስሏቸው ነበር። በሌላ ወገን ግን በአፄ ምኒልክ ዘመን የነበረው ምሁራዊ ክፍተት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመንም ይታይ ነበር። በተለይም በኢኮኖሚ ቲዎሪና ፖሊሲ ላይ ክርክር ሊያደርግ የሚችል ምሁራዊ ኃይል ባለመኖሩ አገራችን የኢምፔሪያሊስቶች፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዚም መስዋዕት ልትሆን በቃች። በአሜሪካን ሶስዮሎጂስቶች የረቀቀውና በተለይም በሶስተኛው ዓለም አገሮች የተስፋፋው በአማዛኝ ጎኑ በፍጆታ አጠቃቀም ላይ ያዘነበለ የዘመናዊነት ፖሊሲ ልዩ ዐይነት ለሁለ-ገብ ዕድገት የማያመች ህብረተሰብአዊ ኃይል ብቅ እንዲል ለማድረግ በቃ። ሳይንስና ቴክኖሎጂ በመስፋፋት የውስጥ ገበያ ከማደግ ይልቅ የተዘበራረቁና እርስ በራሳቸው ያልተያያዙ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች እንደ አሸን በመፍለቃቸው የተነሳ ህዝቡ ሊተሳሰር አልቻለም። ወደ መንግስቱም መኪና ጋ ስንመጣ መንግስታዊ መዋቅሮች በውጭ ኃይሎች በመሰልጠናቸው አገዛዙ የተረጋጋና በራሱ ፍላጎትና ዕምነት እንዳይራመድ ለማድረግ በቅቷል። ይህንን ሁኔታ ከጃፓን፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከሶቭየት ህብረት ወይም ራሺያና ዛሬ ደግሞ ከቻይና ጋር ካለው ሁኔታ ጋር ማነፃፀሩ ለምን የአገራችን ሁኔታ በዛሬው መልክ ሊገለጽ እንደቻለ ከሞላ ጎደል ግንዛቤ ሊሰጠን ይችላል።
ለማንኛውም የአደዋን ድል 124ኛ ዓመት ስናከብር ለአብዛኞቻችን ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። የአደዋን ድልና የዘመናዊነትን ተልዕኮና መልዕክቱን በሳይንሳዊ የዘመናዊነት ወይም በፍልስፍና የዘመናዊነት መነፅር ሳይሆን የምናየውና የምናከብረው በፊዩዳላዊ አመለካከት ነው ማለት ይቻላል። በጀግነንት መነጽር እንጂ በዚያን ጊዜ የተካሄደውን ብልህነት የተሞላበትን ትግል ግንዛቤ ውስጥ በማካተትና የዘመናዊነትን ፖሊሲ ምንነት በመረዳት አይደለም። የአፄው ምኒልክ የዘመናዊነት ዕቅድ ቀስ በቀስ የህግን መጠበቅ የሚያበስር መልዕክት ነበረው። በዚህም መሰረት ንቁና በመርሆች (Principles) ላይ የተመሰረተ ምሁራዊ ኃይል ማፍለቅና ማዳበር ነበር። የአደዋ ዋናው መልዕክት ለሰፊው ህዝብ ጠበቃ የሆነና አገሩን የሚያስከበር ትውልድና ምሁራዊ ኃይል ማፍራት ነበር። ከዚህም ጋር በማያያዝ በሁሉም አኳያ የሚገለጽ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን የሚቀበል ዜጋ በማፍራት ተከታታይና ሰላም የሰፈነባት ዜጋ ማፍራት ነበር የአደዋና ድልና የዘመናዊነት ዋናው መልዕክት። የአደዋ መልዕክት ይህ መሆኑ ቀርቶ አገሩን የሚበታትንና በህዝቡ ላይ ጦርነት የሚያውጅ ትውልድ ብቅ ሊል ችሏል። አገሩንና ህዝቡን ሳይሆን ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚሰግድና የእሱን የተበላሽ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል ኃይል ብቅ ሊልና የፖለቲካውን መድረክ ሊሞላው በቅቷል። የዛሬው የአገራችን ሁኔታ የዚህ ዐይነቱ የታሪክ ግንዛቤ ጉደለትና ታሪካዊ ኃላፊነትን ያለመገንዘብ ነፀብራቅ ነው። ዕይታችንና አስተሳሰባችን በሙሉ ዘመናዊነትን የሚያስተጋባ ሳይሆን ወደ ኋላ ተመልሰን እዚያው እንድንቀር የሚያደርገን ሰመመን ዐይነት ይመስላል። የትላንትናውንና የዛሬውን ሁኔታ በመረዳት ወደፊት የሚያራምደን የፖለቲካ ሂደት አይደለም የሚያነታርከን። ስልጣኔን የሚያስተጓጉልና በውጭ ኃይሎች እንድንጠቃ የሚያደርገን የፖለቲካ አመለካከት ነው ከራሳቸን ባሻገር እንዳናይ ያደረገን። ለዕድገት በሚጠቅሙ እንደ ሶስዮሎጂ፣ የኢኮኖሚክ ታሪክ፣ ፍልስፍና፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ የህሊና ሳይንስና ሌሎች ለአገር ግንባታ በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ጥናት ከማድረግና ከመከራከር ይልቅ በትናንሽ ነገሮች ላይ በመነታረክ የጨለማውን ዘመን እያራዘምነው ነው። በ21ኛው ክፍለ-ዘመን እየኖርንና ዘመናዊ መኪናዎችም ብንነዳምና ስማርት ፎንን ብንጠቀምም አካሄዳችን አመለካከታችን የተገለጸለትና ዘመናዊነትን የተላበስ አይደለም። አመለካከታችንና ፖለቲካችን ሰብአዊነት የጎደለው፣ ተፈጥሮን እንድናከብር የማያደርግና ወደ ውስጥ እንድንመለከት የሚያደርገን አይደለም። ስለሆነም የአደዋን ድል በጀግንነት ስሜት ብናከብረውም ተልዕኮውን ወይም ውስጣዊ ይዘቱን ለመረዳትና ተግባራዊ በማድረግ ነፃ አገር ለመመስረት ብዙ ዐመታትን መጠበቅ ይኖርብናል ማለት ነው። መልካም ግንዛቤ!!