እንኳን ሰው የበግ መንጋ እንኳን “ብኣኣኣ!” እያለ ሀዘኑን በአንድነት ይገልጣል! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ተማሪ ልጆቻችን ተጠልፈው ከተወሰዱ ወራቶች አልፈዋል፡፡ ልጅ ጠፋብኝ ያልን ጩኸታችንን አሰምተን እንደገና ለሽ ያልን ይመስላል፡፡ ልጅ ያልጠፋባቸው ደግሞ ከፊላቸው በማፌዝ አብዛኞቹም በዝምታ እንኳን ህላዊ ባህሪ ደመነፍሳዊ ባህሪአቸውንም የፋቁ ፍጡራን መሆናችውን አሳይተዋል፡፡ የሕዝብን ጆሮ በመጥባትና በማፈን ተነቅሮ ያደገውን “ሙሴ” ማወናበጀ ትያትር በማናፈስ በሕዝብ ህይወት መቀለዱን ቀጥለዋል፡፡ ለአማራ እንቆረቆራለን የሚሉ ያልበሰሉ ውርጋጦችም አማራን ለዚህ ታበቃው ልሙጡ ገረድ ብአዴን የዝንጆሮ ቆንጆ ለመምረጥ ሲወላገዱ አንድ ባንድ ገደል መንከባለሉን ቀጥለዋል፡፡

ደመነፍሳዊ ባህሪአቸውን በበረኪና ተፋቁት ከርሳሞች፣ ጀሮ ጠቢ አፍቃሪዎችና ተገረዱ ብአዴን ቆንጆ መራጮች በተሻለ ሁኔታ ጠቦት እግሩን ተስቦ ለእርድ ሲወሰድ የበግ መንጋ በአንድነት “ብኣኣኣ!” እያለ  ሀዘኑን ይገለጣል፡፡ እኛ ሮጠው ያልጠገቡ ልጆቻችንን አዝጋሚ ለውጥን ላልጨረሱ ጭራቆች አስረክበን ቁርስ፣ ምሳና እራት ጥሽቅም አርገን እየበላን የድሎት ኑሮን ቀጥለናል፡፡ “ልጆቼ፣ እህቶቼ፤ ወንድሞቼ ወይም ራሴ” ብሆንስ የሚሉትን ጥያቄዎች እንዳንጠይቅ የሆድና እንደለገሰ ዜናዊ ትቢያ ስንሆን የሚቀረው የኑሮ ፍቅር ህሊናችንን እንደ ኩስ ጭምልቅልቅ አድርጎብናል፡፡ ልጆቹ የተጠለፉት እኛን ስለመሰሉና በእኛ ልሳን ስለተናገሩ የመሆኑን የግንዛቤ አልማዝ ሆዳምነት፣ መሀል ሰፋሪነት፣ አድርባዊነትና ወላዋይነት እንደ ጎርፍ ጠርገው ወስደውብናል፡፡

የአድርባዮችና የመሀል ሰፋሪዎቹ “ሙሴ” ተማሪዎችን ለጅብ አስረክቦ “ተማሪ ብሔር የለውም!” እያለ ይደሰኩርና በሰለጠነበት “የአኬልዳማ ድራማ” እርሱ በፈንታው ባሰለጠናቸው ጆሮ ላሾች ዛሬም ድራማ ይሰራብናል፡፡ የተጠለፉት ሳያንስ ሌሎች ልጆችን አስጠልፎ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየነፋ በሀዘን ወቅት ሰርጓ እንዳማረላት ሙሽራ ሲገለፍጥ ይውላል፡፡ አገሪቱን በቋንቋ ሰነጣጥቆ እርሱም በቋንቋ ፖለቲካ ተነቅሮ፣ በዚያው ተጠምቆና በተጠመቀበት እድፍም ተደራጅቶ ሌላውን እያጠቃ “ተማሪ ብሄር የለውም” ሲል መሀል ሰፋሪና ሆዳሙ አማራ አፉን ከፍቶ ያዳምጠዋል፡፡ ከርሳሙ ጋዜጠኛም ይኸንኑ ያንባርቃል፡፡

ከወራት በፊት እሬሳ አወርሞ ለአስከሬን ዘር የሰጠ እርጉም ጆሮ ጠቢ “ተማሪ ብሄር የለውም ሲል” ሆዳምና አለቅላቂ አማራ ዛሬም ለንቦጩን ጥሎ ያዳምጠዋል፡፡ ጆሮ ጠቢው ሙሴ እግዚአብሄር አያድርገውና እነዚህ የአማራ ቆዳ የለበሱና የአማራ ልሳን የሚናገሩ ልጆቹ አንድ ነገር ቢሆኑ ከፊሎችን ያወርምና በእርሱ ድውይ ስሌት የራሱ ብሄር ያደርጋቸዋል፡፡

ይህ አድግ እንደ ሳር ባጨደው የሬሳ ክምር ቆማችሁ የይህ አድጉን ጀሮ ጠቢ የተከተላችሁና ተብአዴን ቆንጆ በመምረጥ ላይ ያላችሁ በሰማይ እግዚአብሄርንና የንፁሐንን ህይወት አስቀይማችኋል፡፡ በምድርም ያለፈውን፣ የአለውንና መጪውን ትውልድ አፈር ድሜ አስግጣችኋል፡፡ ዘር እየለዬ በወንድ ብልት ኮዳ እያንጠለጠለ የሚሰልብ፣ ሴቶችን የሚያመክን፣ በወህኒ የሚያሰቃይ፣ የሚያሰድድና የሚረሽን ድርጅት ጆሮ ጠቢን “ሙሴ” በማለታችሁ ቀናተኛው አምላክ ይጠይቃችኋል፡፡

አማራ በወህኒ ሲማቅቅ፣ በመላ አገሪቱ ስደተኛ ሲሆን፣ በገጀራ ሲቀላ፣ የማምለክ መብቱን ሲነፈግ፣ ከዩንቨርስቲ እየተመረጠ ሲባበረር፣ ልጆቹ እየተጠለፉ የምድር ሲዖልን ሲያዩና ድራማ ሲሰራባቸው በጆሮ ጠቢው አሻጋሪ ሙሴ የተማምናችሁ ከንቱዎች አራጁን ለይቶ ተሚጮኸው የበግ መንጋ አንሳችኋል፡፡ ተብአዴን ቆንጆ ለመምረጥ እንደ ጥንዚዛ በፈናጠር ያችሁ ጉንዳኖችና ሆዳችሁን እየቆዘራችሁ ዝም ያላችሁ አማራዎች በደመ ነፍስ ተሚንቀሳቀሰው በግ እጅግ አንሳችኋል፡፡ እንኳን ሰው አቅም የሌለው የበግ መንጋ እንኳን “ብኣኣኣ!” እያለ ሀዘኑን በአንድነት ይገልጣል!

 

ህዳር ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

 

ቁማር በአማራ ነፍስ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share