ተኝቷል ፣ መች ነቃ – ታዛቢው

የምዬ ሚኒሊክ ፣ የበላይ ዘለቀ
ባለማተብ ጀግና ፣ ዝናር የታጠቀ
ባድዋ ፣ በማይጨው ላይ ፣ እየተናነቀ
ጎራዴውን መዝዞ ፣ እየሞሸለቀ
ኃያሉን ደቁሶ ፣ በክርኑ ያደቀቀ
ዝናው በዓለም ላይ ፣ ናኝቶ የታወቀ
ምን ነካው አማራ ፣ ጦሩን አልሰበቀ
ወገኑ በመንጋ ፣ ታርዶ እያለቀ ።

ሁሉም በየዘውጉ ፣ እየተጠራራ
ባራቱም ማዕዘን ፣ እየሳለ ካራ
እየደገሰልህ ፣ ቀን ከሌት ሲያቅራራ
ጠላት ወዳጅ ላይሆን ፣ አርገህ ባልንጀራ
አብሮህ ይታደማል ፣ ይጎርሳል እንጀራ
ፈንጂ ፣ ታቅፎ እንቅልፍ ፣ አይበጅም አማራ

በደሉ ስቃዩ ፣ ምነው አልተሰማህ
ቸልታው በዛብኝ ፣ ምን ይሆን አላማህ
ዙሪያህን እያየህ ፣ ምኑ ነው ያልገባህ
አብሮህ እየሳቀ ፣ ሲዶልት ከጀርባህ
ወርቅ ላበደረ ፣ ጠጠር ሲሆን ዋጋህ
አስደገሙብህ ወይ ፣ ምነው ተዘናጋህ ?

እንደ ገና በሬ ፣ ካራጅህ እየዋልክ
ሃያ ሰባት ዓመት ፣ ሲገፉህ አልተማርክ
ዐይንህ እንዲገለጥ ፣ ጊዜ ሰጥቶህ አምላክ
ሃቁን እያወቅከው ፣ ዕውነታን እየካድክ
ከትላንቱ ዛሬ ፣ ምነው አልማር አልክ ?
ወርዶ ይንገርህ ወይ ፣ ከሰማይ መልዐክ ።

ወትሮ የምናውቀው ፣ ጠርጣራ ጠንቃቃ
እንኳንስ እራሱን ፣ ወገን አያስጠቃ
የሐገር መከታ ፣ ዋስና ጠበቃ
ዛሬ ላይ ተሳነው ፣ ማለት በደል ይብቃ
ተዘናግቷል እንጃ ፣ ተኝቷል ፣ መች ነቃ
ማጣፊያው እንዳያጥር ፣ ኋላ ጀምበር ጠልቃ ።

ታዛቢው
February 10, 2020

ተጨማሪ ያንብቡ:  እጮሃለሁ! - ብሩክ ነኝ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share