October 22, 2013
31 mins read

እዚህም አዚያም ጩኸቱ ተበራክቷል . … ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ (ጋዜጠኛ)

ያን ሰሞን አንድ ጋዜጠኛ ወዳጀ ከወደ አማሪካ የሚያየውን የስደተኛ ህይወት በጨረፍታ በሚያስቃኝበት መጣጥፉ “ስሞት ሬሳየን አቃጥሉት !” ብሎ የተናዘዘን ወንድም አሳዛኝ የህይወት ታሪክ ከእነ ህልፈት ኑዛዜው ፍጻሜ እንደ መረጃ አቀበለን። በአስገራሚው ታሪክ ተደምሜ “ነብስ ይማር !” ብየ ሃዘኔን በገለጽኩ ቅጽበት ከቀናት በፊት የሰማሁት እንዳስታውስ አደረገኝ… የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ግዛቶች በእህቶቻችን ላይ ደረሱ የተባሉ የሞት አደጋዎችን አስታውሸም የአሜሪካው ስደተኛ አሟሟት አልገርም አልደንቅህ አለኝ…ይህን ማለቴ ክቡሩን የሰው ልጅ በአጭር መቀጨት ሳያሳዝነኝ ቀርቶ አይደለም ። “ከሞቱ አሟሟቱ !” እንዲሉ በአረብ ሃገር በወጣት እህቶቻችን ኑዛዜው ቀርቶ ወርቅ አድናፍስ ብለው በቀቢጸ ተስፋ መጥተው ማንነታቸው በውል ሳይታወቅ ደፋ ብለው የመቅረታቸውን እውነታ በቅርብ አውቃለሁና ነው። ለረጅም አመት በምኖርበት በጅዳ ብቻ ሳይሆን በዋና ከተማዋ በሪያድ ፣ በደማም ፣ በአብሃ ፣ በከሚስ ምሸት ፣ በአርአር ፣ በጣይፍ በመዲናና በመካ አካባቢ እና በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች የምሰማ የማያቸው አዛኝ የኮንትራት ሰራተኞች ህልፈት ታሪክ ታውሶኝ በወዳጀ ጽሁፍ ግርጌ የሚከተለውን አስተያየት አስቀመጥኩ “…የስልጡኑ ሃገራት ስደተኛ ለኑዛዜ በቅቶ ቢሞትም ያሳዝናል! እኔ ባለሁበት ሃገር በቅርብ የማውቀው የምሰማው አሟሟት ግን ከሞቱ አሟሟቱ ያስብላል! ብዙ አልልም! ወደ አረብ ሃገራት መጥተው ታመውም ሆነ በሰው እጅ ነፍሳቸው ስታልፍ የብዙዎቹ በማንነት አይታወቅም ! ወላጅ ሰርተው ህይዎታቸውን ይቀይሩልኛል፣ ይረዱኛል ብሎ ተበድሮ ስለላካቸው ልጆቹ መኖርና አለመኖር መረጃ ሳይኖረው ኑሮን በጸጸት በሰቀቀን ይገፋል! የሚቆረቆርለት መብቱን የሚያስከብርለት የሃገሩ ተወካይ ሆነ ዜጋ የለምና! የሃበሻ ልጅ ረክሷል! ብቻ የሁሉንም ነፍስ ይማር ! ሌላ ምን ይባላል: ( ” በማለት …በአስተያየቴን አስቀምጨ ትክዝ እንዳልኩ ስልኬ ጮኸች ፣ ቁጥሩን ተመለከትኩት ፣ ስሙ አይወጣም ፣ የማላውቀው ሰው መሆኑ ገባኝ ! አነሳሁት …
ስልኩ ቁርጥ ቁርጥ ይላል “አቶ ነቢዩ ሰላም ነህ አይደል ?” አዎ ነኝ ማን ልበል? ስልኩ ይቆራረጣል እኔ ልደውልልዎት? ” እከሌ እባላለሁ ፣ ችግር የለም ! ” በማለት የመለሱልኝ ወንድም የጅዳ ነዋሪ አንድ የቀድሞ ታጋይ መሆናቸውን ሰማቸውን ሲነግሩኝ ተረዳሁ። እናም የመንግስት ደጋፊው ወንድም ቀጠሉ …እኔም መስማት ጀመርኩ …በንግግራቸው መካከል እየገባሁ የኢትዮጵያና የሳውዲ መንግስት ሰራተኛን በማስመጣት የሁለትዮሽ ውል እንደሌላቸው ሌላው ቀርቶ ይህንን እውነታ የጅዳው ሃላፊ አቶ ዘነበ ከበደ በግላጭ ማመናቸውን አስረዳኋቸው። ሌላ እድል ሳገኝ ድግሞ ዜጎች በደል ሲደርስባቸው የመንግስት ተወካዮች በሰራተኛና አሰሪ መካከል ያለውንና ገንዘብ ተቀብለው የሚያጸድቁትን የስራ ኮንትራት ውል አለያም ሰብዕናን መሰረት አድርገው እንኳ መብታቸውን ሊያስከብሩ ይገባል የሚል ያልገባቸውን ለማስረዳት ብሞክርም አሻፈረኝ አሉኝ …
ዛሬ ማለዳ ዳሰስ ዳሰስ ያደረግኩት ሃገር ቤት የሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባቀረበው አንድ መረጃ ” ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው አረብ አገር የጠፉባቸው ቤተሰቦች ኤጀንሲዎችንና መንግስትን አማረሩ!” በሚለው ርእስ ስር “ኤጀንሲዎችና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እልባት ሊሰጡን አልቻሉም ”የቤተሰቦቻችንን አድራሻ እና ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ተቸግረናል” የሚሉት የወላጅ ቤተሰብን የሃገር ቤት ሮሮ ያትታል …

(ጸሐፊው ነብዩ ሲራክ)
እዚህም አዚያም ጩኸቱ ተበራክቷል . ... ነብዩ ሲራክ ከሳዑዲ አረቢያ (ጋዜጠኛ) 1
አማራጭ ሳጣ ደሜ እየተንተከተከም ቢሆን የሚሉትን መስማት ጀመርኩ ” ምነው ነቢዩ ዙሩን ታከረዋለህ ? የሰው ልጅ አላህ ካልጻፈለት አይሞትም! በኮንትራት መጥተው ሲሞቱ ነፍሳቸውን ይማር ማለት እንጅ የኢትዮጵያ መንግስት ምን ያድርግ? ለዚህ ሁሉ ያበቃን እኮ ድህነት ነው! ድህነትን ለመዋጋት ሌሎች ወደ ሃገር ቤት ተመልሰው በልማት እንዲሳተፉ መገፋፋት እንጅ ማማረር ምን ዋጋ አለው! የምትለው ችግር እንዳለ ማንም ያውቃል ። የመንግስት ሃላፊዎች እንደኔና እንዳንተ ሰዎች ናቸው ያዝናሉና የሚቻለውን ያደርጋሉ! አሰሪዎች ዜጎችችን አበዱ ብለው በር ላይ ጥለዋቸው ይሔዳሉ ፣ ሞቱ ብለው ሬሳቸውን ቅበሩ ብለው ይመጣሉ ፣ ተወካይ የምትላቸው ምን ያድርጉ? በዚህ ሳምንት ብቻ ከአስር ያላነሱ አዕምሯቸው የተዛባ ፣ በህመም የተለከፉ ፣ የተደበደቡና የተደፈሩ እህቶችን ጨምሮ ከ130 በላይ ተፈናቃዮች በጅዳ ቆንስል እንደሚገኙ ታውቃለህ። እነሱን ወደ ሃገር ቤት ለመላክ ስራ እየሰሩ እንደሁ አውቃለሁ! ታዲያ ከዚህ በላይ ምን ያድርጉ ትላለህ! ከዚህ መሰል አስከፊ ስደት የምንወጣው የአምስቱ አመት ትራንስፎርሜሽን እንዲሳካ ሁላችን ስንተባበር ፣ አንተም ገጽታ ማጠልሸቱን ትተህ በልማቱ ስትሳተፍ ነው! ” ብለው እንደጨረሱ ስልኩን ልመልስላቸው ስዳዳ “ያንተ መልስ ምን ያደርግልኛል፣ የምትሰማ ከሆነ ስማ … !” ብለውኝ ስልኩን ዘጉት … የወንድሜን ቁጣ የተቀላቀለበት ጭብጥ የሳተ ምክር በሉት አስተያየት የለምድኩት በመሆኑ አልገረመኝም አላናደደኝም ! ብቻ ከተራው የግል ህይዎት እንቅስቃሴ ወጋወግ ትኩረት ወደ ቋሚ የስደተኞች ህይዎት አጀንዳየ ፊቴን አዞር ዘንድ ግን ረዳኝ …
በያዝነው ሳምንት ለተወካዮች ምክር ቤት መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማሪያም ደሳለኝ የዛሬ ሶስት አመት ገደማ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እያሉ ሳውዲዎች 45000 (አርባ አምስት ሽህ ) ሰራተኛ በወር ይፍ ጋሉ ብለው የምስራች እንዳበሰሩን አስታውሳለሁ። ይህን ሲያደርጉ ግን በሁለቱ ሃገሮች ማካከል መደረግ የነበረበትን የሁለትዮሽ ውል ፈርመው አልነበረም። “ሰራተኞችን እያሰለጠንን እናቀርባለን!” በማለት ቃል ገብተው የተመለሱት የያኔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ድሳለኝ ከጥቂት አመታት በኋላ ዛሬ ሌላ መረጃ እየሰጡን ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ሃላፊነት ተቀምጠው ለምክር ቤቱ በሰጡት መግለጫ በሳውዲ አረቢያ የዜጎች ችግር መባባሱን አስታውቀው ወደ ሳውዲ አረቢያ በሚሔዱ ላይ እገዳ እንደተጣለ መናገራቸውን ሰምቻለሁ። እኔ እስከ ማውቀውና እስከ ምረዳው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ትናነትም ሆነ ዛሬ በሰጡን መረጃዎች ምሉዕ ሆነው አላገኘኋቸውም … የእገዳውን ጉዳይ ሲነሳ እኔ እስከማውቀው ከኢትዮጵያ ሰራተኛ ማስመጣቱን ያገዱት ሳውዲዎች መሆናቸውን ነው ። ይህም የሆነበት ምክንያት በኮንትራት የመጡት ሰራተኞች በሳውዲ አሰሪ ቤተሰቦች ላይ ተደጋጋሚ “የግድያ ወንጀል ፈጽመዋል !”በሚል ሰፊ የማጥላላት ክብረ ነክ ፕሮፖጋንዳ ከተሰራ በኋላ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኘ መናገር እችላለሁ ። ይህን ከስር መሰረቱ ከዚህ በፊት ባቀረብኳቸው መጣጥፎቸ ገልጨዋለሁ እና አልደግመውም። በተረፈ ይህ መሰሉ የተዛባ መረጃ እያነሆለለኝ በመቸገሬ በሃገር ቤት ለዜና ሽፋን በሚለቀቅ የመንግስት ሃላፊዎች መግለጫዎች ተስፋ የቆረጥኩት ሰው ነኝና በዚህ ዙሪያ ብዙ ማለት አልሻም ። ይህን ለማለት ምክንያቴ ብዙ ቢሆንም በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ ” ስደት ይብቃ !” ተበሎ ብዙ ቃል ተገብቶ ከዚያ ወዲህ እንኳ የተባለውን ያህል ቀርቶ ከቆየው የከፋ አደጋ እየተመለከትኩ በመሆኑ በሚደሰኮረው ላይ እምነት አጥቻለሁ ! በአንጻሩ በመንግስት የሚለቀቁ መረጃዎች ባያረኩኝም በመንግስት ደጋፊነትና በለዘብተኛነት የሚወቀሱ ሃገር ቤት የሚወጡ መጽሄትና ጋዜጦች በአረብ ሀገር ስደተኞች ዙሪያ እየሰጡት ያለው ተደጋጋሚ መረጃ ውሃ የሚያነሳ ለመሆኑ እማኝ መሆኔን አልክድም ! በቅርቡ ዳሰስ ዳሰስ ያደረግኩት ሃገር ቤት የሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ባቀረበው አንድ መረጃ ” ልጆቻቸውና ሚስቶቻቸው አረብ አገር የጠፉባቸው ቤተሰቦች ኤጀንሲዎችንና መንግስትን አማረሩ!” በሚለው ርእስ ስር “ኤጀንሲዎችና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እልባት ሊሰጡን አልቻሉም”“የቤተሰቦቻችንን አድራሻ እና ያሉበትን ሁኔታ ለማወቅ ተቸግረናል” የሚሉት የወላጅ ቤተሰብን የሃገር ቤት ሮሮ ያትታል …
“በተለያዩ ኤጀንሲዎች በኩል በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ህጋዊ ውል ፈፅመው ወደተለያዩ የአረብ አገራት ለስራ የሄዱ እህቶቻችን፣ ልጆቻችን እና ሚስቶቻችን በችግር ላይ ሆነው አቤት የምንልበት አጥተናል ሲሉ የተጓዥ ቤተሰቦች አማረሩ፡፡ ” በማለት እማኞችን ሲያቀርብ ” ከአምቦ ከተማ የ5 ወር ህፃን ልጇን አዝላ የእህቷን ጉዳይ እልባት ለማግኘት የምትመላለሰው ፋጤ ኑሬ ራህመት ኑሪ ሞሳ እህቷ “ይጠቅለን” በተባለው ኤጀንሲ በኩል ወደ ሳውዲ ሄዳ ጉልበቷ ያለ ደሞዝ እየተበዘበዘ እንደሆነ ደውላ እንደነገረቻች ገልፃለች፡፡ “ህፃን ልጄን ይዤ አንዴ ወደ ኤጀንሲው፣ አንዴ ወደ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ስመላለስ ብቆይም ምላሽ የሚሰጠኝ አጥቻለሁ” በማለት አማራለች፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ የተባለው ግለሰብ በበኩሉ፤ ከጋምቤላ ክልል መዠንገር ዞን እንደመጣ ገልፆ፣ እህቱ ጨረቃ ታደሰ ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሄደች ገና ሶስት ወር ቢሆናትም በሁለተኛው ወሯ ደውላ “ድረሱልኝ ከሞት አድኑኝ” የሚል ቃል ተናግራ ስልኩን መዝጋቷን ተናግሯል፡፡ “
በራሴ ጥረት ደውዬ አገኘኋት፤ ወንድሜ ከሞት አድነኝ ሶስት ቦታ እያሰሩኝ በጣጥሰው ሊገድሉኝ ነው፡፡ ወደ ኤጀንሲ እሄዳለሁ ስል ጩቤ አውጥታ እቆራርጥሻለሁ ትለኛለች መሞቴ ነው” ብላ በጭንቀት ላይ ነን” በማለት ተናግሯል፡፡ አልጀዚር በተባለው ኤጀንሲ በኩል እንደሄደች የሚናገረው አቶ ቴዎድሮስ ኤጀንሲው ቦታ ይቀየርላታል ቢልም እስካሁን አለመየቀሯንና በስቃይ ውስጥ መሆኗን ኤጀንሲውም ሆነ የመንግስት መ/ቤት የሆነው ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጉዳዩን ችላ እንዳሉበት ተናግሯል፡፡ ከትግራይ ክክል አዲግራት የመጡት አቶ መሰለ መሀሪ የ70 አመት አዛውንት ሲሆኑ ልጃቸው ፊዮሪ ሲሆኑ ልጃቸው ፊዮሪ መሰለ ቦሌ ሩዋንዳ በሚገኘው ናይል ኤጀንሲ በኩል ሪያድ መሄዷን ጠቁመው በሄደች በ4 ወሯ ደውላ ከዚያ በኋላ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች፣ ትኑር ትሙት የሚያውቁት እንደሌለ ጠቁመው ላለፉት 20 ወራት የልጃቸውን ሁኔታ ማወቅ እንዳልቻሉ በእንባ ገልፀዋል፡፡ “ለረጅም ጊዜ ወታደር ቤት ነበርኩኝ አካል ጉዳተኛም ነኝ ሰባት ልጆቼንና ባለቤቴን የማስተዳድረው በጡረታ ደሞዝ ነው” ያሉት አቶ መሰለ ልጃቸው ቤተሰቧን ለመርዳት ብላ ሄዳ ትሙት ትኑር አለማወቃቸውን ተናግረዋል፡፡ “ናይል ኤጀንሲ ለበርካታ ጊዜ ከትግራይ ስደውል የተለያየ ምክንያት ሲሰጡኝ ቆይተው በመጨረሻም ሪያድ ካለው ኤጀንሲ ጋር ያለን ግንኙነት ስለተቋረጠ ለመገናኘት ተቸግረናል የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል” ሲሉ አማረዋል፡፡ ኤጀንሲው አክሎም ሪያድ ያለውን ኤጀንሲ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ክስ መስርተን እየተከራከርን ነው የሚል ምላሸ እንደሰጣቸውና በመጨረሻም ከትግራይ መጥተው ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አቤት ብለው ምላሽ እስካሁን አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።አቶ ተሰማ ጉታ የተባለውና ከሰበታ ከተማ እንደመጣ የተናገረው ሌላው ባለ ጉዳይ ባለቤቱ ሞሚና አብደላ አራት ኪሎ በሚገኘው ተፈራ ኤጀንሲ በኩል ነሀሴ 2003 ዓ.ም ሳውዲ መሄዷንና በሄደች በዘጠኝ ወሯ እዛው በሚገኘው ቢሮ ደውላ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ከቤት አውጥተው ጥለውኛል በማለቷ ተጨንቆ እንደነበር ገልፆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሚስቱን ጉዳይ መስመር ለማስያዝ ወደ ተፈራ ኤጀንሲና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሲመላለስ ቢቆይም መፍትሄ አለማግኘቱን ገልጿል፡፡ “አንድ ቀን ደውላ ሁለት የሌላ አገር ዜጐች አብረውኝ ይሰሩ ነበር ምን እንዳጠፉ ባላውቅም ታስረው የሶስት ሰው ስራ ተከምሮብኛል ብላ መስከረም 15 ቀን 2006 ዓ.ም ደውላ ነበር” ያለው አቶ ተሰማ የ10 ወር ደሞዝ ሳትቀበል ያንንሁሉ መከራ ስትቀበል ከርማ በመጨረሻም ለአሰሪዋ ስንደውል “ልጆች ት/ቤት ልታደርስ ወጥታ በዚያው ጠፍታለች” የሚል ምላሽ ማግኘታቸውንና በጭንቀት ላይ መሆናቸውን አቶ ተሰማ ተናግሯል፡፡ ከምስራቅ ጐጃም የመጣውና የእህቱን መጥፋት ለኤጀንሲውና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አቤት ሲል ለአንድ አመት የቆየው አቶ ሱሌይማን ጋሹ ኤጀንሲና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሲመላለስ “ዛሬም አለህ እንዴ?” የሚል ምላሽ እንደሚያገኝ በምሬት ገልጿል፡፡ አሊማ ጋሻው የተባለችው የ29 አመት እህቱ ሰኔ 15 ቀን 2003 ዓ.ም ወደ ሳውዲ እንደሄደችና በሶስተኛው ወር ደውላ እስር ቤት መግባቷን እንደነገረችው ገልጿል፡፡ “ለምን እንደታሰረች ኤጀንሲውን ስጠይቅ አሰሪዋ ሪያድ ሄዷል ስራ ትገባለች እያለኝ ፉአድ ኤጀንሲ ሲያታልለኝ ቆይቷል” ያለው አቶ ሱሌይማን መጀመሪያም ደላላ 13 ሺህ ብር ወስዶባታል አሁን የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለች አላውቅም በማለት ተናግሯል፡፡ “በወቅቱ ዶ/ር ዘሪሁን የተባሉ ባለስልጣን ጋር አቤት ብዬ ነበር” ያለው አቶ ሱሌይማን ዶ/ር ዘሪሁን የኤጀንሲውን ባለቤት አስደውሎ ጠርቶ ስለ ጉዳዩ ሲያነጋግረው በጥሩ ሁኔታ ስራ ላይ እንደምትገኝ ነገረው ሲል ገልጿል፡፡ “እህቴን ለመላክ የሚያስፈልገውን ብር ከአማራ ብድርና ቁጠባወስደን ነበር ብድሩን ክፈል እያሉ ሲያስጨንቁኝ ወደ ኤጀንሲው መጥቼ ማልቀስ ጀመርኩ” ያለው አቶ ሱሌይማን አድራሻዋን ማግኘት እንደማይችል ነገር ግን በጥሩ ስራ ላይ እንደሆነች ኤጀንሲው ነግሮት የሶስት ወር ደሞዟ ነው በሚል ወደ ስምንት ሺህ ብር እንደሰጠውን ልጅቷን ማግኘት እንጂ ብር አልፈልግም በማለቱ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊዎች ብሩን ፈርሞ መቀበል እንዳለበት ሲነግሩት መቀበሉን ተናግሯለ፡፡
ከዚያም አድራሻዋ ሳይገኝ በተጨማሪ የ1 ወር ደሞዟን ኤጀንሲው ቢሰጠኝም የእህቴን አድራሻ እስካሁን አላገኘሁም ያለችበትን ሁኔታ ለማወቅ ስመላለስ አንድ አመተ አለፈኝ፡፡ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ለምን እንደተቋቋመና ለምን እንደማይዘጋ አልገባኝም ሲል አማሯል፡፡ አቶ ቃሲም ይመር ከካራ ኮተቤ መምጣቱንና ሚስቱ ነኢማ ይመር ያሲን በሳውዲ አረቢያ በችግር ላይ መሆኗን ተናግሯል፡፡ ሰኔ 4 ቀን 2005 ዓ.ም በሁለት ወሯ ደውላ አሰሪዬ እናቱ ቤት ሊቀይረኝ ነው ከአሁን በኋላ እኔ ካልደወልኩ አታገኙኝም ማለቷን የተናገረው አቶ ኡመር፣ ከ20 ቀን በኋላ ደውላ ሰውየው እናቱ ጋር እንዳልወሰዳትና ወደ አንድ ጭለማ ቤት ወስዶ በየቀኑ ሁለት ወንዶች እየተቀያየሩ እየደፈሯት እንደሆነ የደወለችውም በአንድ አጋጣሚ ሲፈቷት ስልክ ሰርቃ መሆኑን ገልፃልኛለች” ብሏል፡፡ “ወይ ወደ አገሬ አሊያም ወደ ቀድሞው ቤት ሰውየው ካልመለሰኝ ራሴን አጠፋለሁ ብላ በጭንቀት ላይ ነኝ” ያለው አቶ ኡመር ነፍሷን ለማትረፍ ቢሯሯጥም በኤጀንሲውም ሆነ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ በኩል ምንም ምላሽ እንዳላገኘ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ “ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ 15 ቀን ወደ ኤጀንሲው 14 ቀን ብመላለስም ምንም እልባት አላገኘሁም” ብሏል፡፡ አቶ ተመስጌን ወርቂቾ ከጉራጌ ዞን ማረቆ ወረዳ፣ አበበ አየለ ከወልቂጤ፣ ፈይሳ ቱሉ የተባሉ ከአርሲ የመጡ አባት፣ እና በርካታ ወላጆች የልጆቻቸውን አድራሻ እንደማያውቁና በኤጀንሲም በኩል ሆነ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መፍትሄ አጥተው እየተንገላቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ “አንድ ሰው አልጋ ከያዘ እየተደበቅን አምስትና ስድስት ሆነን ሲሚንቶ ላይ እያደርን እየተንገላታን ነው ” በማለት ባለጉዳዮቹ በሃገር ቤት የምሬት ጩኸት ገኖ መሰማቱን የአዲስ አድማስ ዘገባ ጠቁሟል።
እኔም ጭንቀት መከራን እንደቀረው የአረብ ሃገር ስደተኛ ለመሰማት ለማት የተፈረደብኝ ጋዜጠኛ ነኝና እንደ ወላጅ ቤተሰብ ተመሳሳይና የከፋ ጮኸት ፣ ሌላ ግፍ ፣ ሌላ ሮሮ በየእለቱ በአካልና በስልክ ይደርሰኛል . .. ግፍ በደሉ በትክክል መፈጸሙን የተጎዳውን ገላ ፣ የታወከውን አዕምሮ ተመልክቸ አዝኘ አልቀርም ፣ ላለሰሙት አሰማለሁ፣ ከቅን በጎ አድራጊዎች ጋር በመሆን መፍትሄ ለማፈላለግ እሞክራለሁ ፣ አልሆንልህ ሲል ሃገር ህዝብ ይወቀው ብየ እጽፈዋለሁ ፣ አትቅረበን የሚሉትን ተወካዮቻችን ቀርቤ አቤት እላለሁ! ሰምቶ መፍትሄ የሚያመጣ የመንግስት ተወካይ ግን የለም …ከቀናት በፊት ከቤተሰብ ጋር ለእረፍት ቆይታ አንድ ቅዳሜ ወደ ስራ ገብታ በበነጋው እሁድ “ሞታለች እና ሬሳዋን ሆስፒታል ውሰዱ !” የተበሉ መያዣ መጨበጫው የጠፋባቸው ቤተሰቦች ተጨንቀው ተጠበው አጫውተውኛል። ያን ሰሞን በእስር ቤት በአሰሪዎችዋ ላይ ” የግድያ ለማድረግ የሞከረች ” የተባለች እህት እስር ቤት ውስጥ ራሷን መግደሏን ሰምተን ከንፈር በመጠጥን ማግስት ሌላኛዋ እህት ራሷን በአሰሪዎችዋ ቤት ሰቅላ መግደሏን ያው የአረብ ጋዜጦች ነግረውናል ። መዘርዘር በማይቻለኝ ደረጃ የአረብ መገናኛ ብዙሃን የእህቶቻችን ህይዎት መቀጠፍ መርዶ በተደጋጋሚ አርድተውናል ። ዜጎች ተቆርቋሪ ጠያቂ የላቸውምና “ራሳቸውን አጠፉ” ብለው የአረብ መገናኛ ብዙሃን ሲነግሩን የሚሰጡት አበዱ የሚል ምክንያት ተቀባዮች ሆነናል ። ያሳዝናል ! ብዙዎች አሰቃቂውን የእህቶቻችን የሞት መርዶ ለምደነው “ገደሉ ፣ ተገደሉ፣ ሞቱ !” ሲሉ አቤት የሚባልበት ቦታ ቅጥ አምባሩ ጠፍቶን እና የመንግስ ተወካዮች “ከተቃዋሞ” እና ” አሸባሪ” ጋር ስማችን ለካልከው ወደ ሃገር ቤት መግቢያ መንገዱን ያሳጡናል ብለን እንፈራለንና ዝምታን መርጠናል ! ጥቂት የማንባል ተማርን ተመራመርን የምንል እንኳ ሌላው ቀርቶ በመረጃዋ ልውውጥ መንግስት ለህዝብ ተቆርቋሪ ወኪሎችን እንዲያሰማራልን ከማጠየቅ ይልቅ በየማህበራቱ የምስረታ ልደት ጥሩ ለብሰንና አምሮብን መታየትን መርጠናል። ብዙዎች በከንቱ ለሚያልፈው የእህቶቻችን ህይዎት መፍትሄ ሳንመክር ሳንዘክር በተራ ፖለቲካ ዘባተሎ ሁካታ ተለያይተን ለሰብዕናው እንኳ በአንድነት መቆሙ ገዶናል። ብዙዎች አድርባይነቱ በርትቶብን የመንግስት ሃላፊዎችን ለዜጎች መብት ጥበቃ ቁሙ ማለት የመንግስት ግልበጣ ወንጀል አድረገው ስለሚስሉብን ፍርሃቱ እያራደን ሽሽትን መርጠናል። በጣም ብዙዎች ለመብት ጥበቃው አቤት እንዳንል የሚደሰኮረውን ማስፈራሪያ እንደ ፍርሃትን ፈርተን “የእህቶቻችን መብት ይከበር!” ብለን ብንጠይቅ ሃገር ቤት ስንገባ ኑሯችን እንዳይሰምር ይሰናከላል ፣ ቤት እንዳንሰራ ንብረት እንዳናደርግና እንዳንቀሳቅስ ያደርጉናል፣ እንሳደዳለን ፣ እንታሰራለን እና ያለ ጠያቂ ወህኒ ተዘፍዝፈን እንቀራለን ፣ በሚል ፍርሃት ተቀፍድደናል ! ጨኸት ሮሮው እዚያም እዚህም በርትቷል ፣ ሰሚ ግን አልተገኘም ! ፍርሃትን ፈርተን ፣ በፍርሃት ተቀፍድደናልና የትንሳኤው ቀን ርቆናል !
እስኪ አንድየ ይታረቀን !
ነቢዩ ሲራክ

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop