እንደ ማንኛውም ለራሱ ክብር እንዳለው የትውልዱ አካል በእጅ ላይ ላለ ትውፊትና በደገኛ አባቶቻችን ተጋድሎ ለተሰመረ ማንነት ቀናኢ መሆን አንድ ነገር ነው፤ ብዙዎች ለእለታዊ ነገር ተገዥ እየሆኑ ወቅት ባመጣው አድርባይነት እየተገፉ ከራእያቸው ጎድለው ከመንገድ ቀርተዋልና።
አንዳዶች ደግሞ ለታሪክ ይፈጠሩና ከዚህም ባሻገር አልፈው ሄደው የተሸፈነው ገልጠው ያሳያሉ፤ በአይነስጋ ያልያተየና ያልተዳሰሰ ነገር በአይነ ህሊና እንዲታይ፤ ይመጣል ያሉትንም ተስፋ በጽናት እንዲጠብቅ ስንቅ የመሆን አቅም ይፈጥራሉ።
ከሌሎች ተሞክሮ የምንማረውን መልካም ነገር ወንዝ ተሻግረንም ቢሆን መማር ክፋት የለውም፤ ስንት አንድ ፍሬ ወጣቶች ከመሃል አገርና ከደጋው የኤርትራ ክፍል አልፈው ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሳይቀር የከፍተኛ ትምህርታቸውን እየተው በዚያን ዘመን ወደ ሳህል በረሃ የኮበለሉት; ያልነበረችን ኤርትራ ቀድመው በአይነ ስጋ ማየት የቻሉት ሻቢያ ሲነዛው በነበረው የዘመኑ የብሄር ፖለቲካ ዝባዝንኬ አልነበረም። ይልቁንም በረከት መንግስተ አብና የማነ ባሪያው የሚባሉ ኤርትራውያን በረሃ ገብተው ከቃሮራ ሆነው በሚለቁት እንጉርጉሮ ስካር እንጅ። በየትኛውም ዘመን ይሁን በየትኛውም የአለም ክፍል የሙዚቃን ያህል ተጽእኖ ፈጣሪ መሳሪያ አለ ማለት አይቻልም። ዛሬ ህዋውን በስነ ፊዚክስ ቀመር ከሚመዘውሩት ልሂቃን በላይ ሰው ለማየትም ለመምሰል ሲራኮት የምናየው ፣ የእለት ዉሎና አዳራቸውን ሁሉ እንደግለ ታሪኩ ሲያወጣ ሲያውርድ የሚኖረው የሆሊውድ አክትረሶችን መሆኑ የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
ያለነው በስር ነቀል አብዮት ዋዜማ ላይ እንደመሆኑ መጠን ከግዜው ባቡር ጋር አብረው መፍጠን አቅቶዋቸው “ከቅንድቡ ያማረ “እስከ “ኢትዮጵያዊው ሙሴ ” ቀረርቶ ገብረው ሙያቸውን በምስር ወጥ ከሸጡት የኤሳው ልጆች ጀምሮ “አገራችን ነጻ ሳትወጣ ስለ ሴት ልጅ አፍንጫና ጸጉር ላልዘፍን” ብሎ እራሱን ከግዝት በታች ካኖረው ሸምበል በላይነህና በየደረጃውም እስከ ፋሲል ደመወዝ ድረስ ያሉ ከያኒያን በሁለት ጽንፍ ሲሄዱ ኑፋቄና ሽንገላ በነገሰበት ማተብ በተበጠሰበት በዚህ በዘመነ ጃርት የታዘብነው መራር እውነት ነው።
የገባንበት ትግል የምር ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ነው። ለዚህም አንዱ ማስረጃ ትግሉ በአይዲዮሎጅ ሳይገደብ፣ እድሜ፣ ጾታና የሙያ ደረጃ ሳይል ዳር እስከዳር በሁሉም የአገሪቱ አጽናፍ ያለውን ህዝብ ሁሉ ማካተቱ ነው። ከአምስት አመት ህጻን ልጅ እስከ ሰባ አመት መነኩሲት ያሉ ዜጎቻችን ሁሉ ተደምረው ያለፈውን ክረምት ጀምሮ ያስነሱትን ሱናሜ ስንታዘብ ከርመናል ።ዛሬም ያ ሁሉ እልህና ቁጭት መልኩን ቀይሮ ሊመጣ ቀን እየጠበቀ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ነገሮች ከእጃችን እንዳይወጡ የትግራዩ ገዥ ጉጅሌ ከሚሄድበት የክፋት መጠን በላይ መሄድ እንዳለብን ነፍስያው ያልነገረው ሰው ያለ አይመስለኝም።
ከአናታችን ላይ ያሉት የኒሮ ቄሳር የልጅ ልጆች እንደ መሆናቸው ዛሬ “ፍቅር ያሸንፋል ! ” ብሎ ማንጎራጎር ለዚህች አገር ትንሳኤ ዋስትና በቂ አይደለም። አዎ የተደፋብን ጥቁር ሰማይ ነው፤ ጨለማውም ድቅድቅ ነው። ከዋክብት የሚያስፈክልጉንም ለዚህ ነው፤ ያን ግዜ ደግሞ ይህ አስፈሪ ጽልመት የግለኝነትን ሰንሰለት ሰብረው ለሚወጡት ከዋክብቶቻችን ሁሉ ሞገስ መሆን ይጀምራል። ከዋክብት በቀን ብርሃን ቢወጡ አያምሩምና። ቴዲ አፍሮ የዚህ ዘመን ኮከብ ነው።ነገር ግን ከኮከብ ኮከብ ክብሩ እንዲለያይ የገርማሞ ልጅ ከትውልዱ ጋር በርቶ ከትውልዱ ጋር የማይከስም ዘመን ተሻጋሪ ኮከብ መሆን ቢፈልግ እንደነ የማነ ባሪያውና በረከት መንግስተ አብ ተከዜ ይውረድ። ከዚያም ወርዶ እንደ መጥምቁ ዮሃንስ ያለ ነጎድጓድ ድምጹን ያስተጋባ፤ ቀኑ መቅረቡን፤ ሁሉም ሊመጣ ላለው እውነት እራሱን እንዲያዘጋጅ የአዋጅ ነጋሪውን ቃል ይናገር፤ ያኔ ታዲ አፍሮ ታሪክ ሰሪ ሳይሆን እራሱ ታሪክ ይሆናል።መጥምቁ ዮሃንስ ሰውን ህይወት በሆነ ቃል አንጾ ለሰማያዊ እርስት የሚያዘጋጀውን ያህል ከክፋት የተሰሩትን እርጉማን ደግሞ “እናንተ የእፉኝት ልጆች” ለማለት የማይገደው የእውነት መንገድ መሪ ነበረና…”ወንድሜ ሆይ ወንዝ ሁን” ያለው ቅኔ አዋቂ ደብተራ ማን ነበር? መነሻንህን ሳትለቅ ልብህ ወደ ፈቀደው ፍሰስ ለማለት ነው።