September 4, 2013
39 mins read

“ቀጣዩ ፕሬዚዳንት ኦሮሞ ሙስሊም ይሆናል የሚል ግምት አለኝ” – የፓርላማው አባል አቶ ግርማ ሰይፉ

ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑት የተከበሩ ግርማ ሰይፉ ከሎሚ መጽሔት ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አውግተዋል፡፡ ዘ-ሐበሻ ለአንባቢዎች ግንዛቤ እንደወረደ አስተናግዳዋለች።

 
ሎሚ፡- የዘንድሮው ፓርላማ ምን ይመስል ነበር

 
ግርማ፡- ባለፈው አንድ ጋዜጣ ጠይቆኝ ነበረ፤ እንዴት ነበር ሲለኝ አሠልቺ ነው ስለው…እንዴት እንደዚህ ይላሉ ከሰለቸዎ ለምን ለቀው አይወጡም የሚል አስተያየት ሰምቼ ነበር፡፡ እንዲህ እያሉ ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ለምን ጥለውት አይወጡም? ከሰለቻቸው አዛ ቁጭ ብለው ደሞዝ ይበላሉ? የሚል ነገር አለ፡፡ የኔ አስተሳሰብ ግን ሌላ ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት አሠልቺ ሁኔታም ቢሆን ነጥብ ማስያዝ የምንችልበትን ስራ መስራት አለብን፡፡ እኔ አሠልቺ ነው ያልኩበት ምክንያት፣ ኢህአዴግን አውቀኸው ገብተህ ምንም ነገር እንደማይመጣ…ለምሣሌ አዋጅ ሲቀርብ እንደሚፀድቅ ታውቃለህ፤ አዋጁ ላይ የኔ የግሌ አስተያየቶች አሉ፡፡ እነዚህን አስተያየቶች ይዘህ ሄደህ ለመቀየር የሚያስችል አቅም አለመኖሩን ስታይ ትሰላቻለህ፡፡ ይህን ለመግለፅ ነው አሰልቺ ነው ያልኩት፡፡ ሦስቱም አመታት የመጡ አዋጆች በሙሉ የሚፀድቁበት ነበር፡፡ በዚህ አመት በነበረው ፓርላማ፣ ሀሣቦች መነሣት ጀምረው ነበር፡፡ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ ሣይሆን እንዲሁ ውይይቱን ሞቅ ደመቅ የማድረግ ሁኔታ ነበር፡፡ ከዛ በፊት ጠያቂው እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፤ እነሱም አንዳንድ ለታሪክ የሚሆኑ ነገሮች እያስመዘገቡ መሄድ ጀምረው ነበር፡፡ እንደዚህ አይነት ነገሮች ይመዘገባሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ልዩ ያደርጉታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በፓርላማው መዝጊያ አካባቢ አንድ የተወካዮች ም/ቤት አባል ያለመከሰስ መብት ለማንሣት የተደረገው ነገር “አስቆጭ” ነበር፡፡ እና ‹‹እንዳይከሰስ›› የሚለውን ነገር አስተካክለው እንዲመጡ፣ እንደዛ ካልሆነ እንዳይሆን ብለው ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃውሞ የተነሣበት ሁኔታ ነበር፡፡ በማግስቱ ባልታወቀና ባልተለመደ ሁኔታ ተገልብጦ ሌላ ነገር ተፈጠረ፡፡ ለምን ተከሰሱ ለምን እንደዚህ ሆኑ አይደለም፡፡ ፖለቲካው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅና የሚቆይ ነው፡፡ አንዳንድ ትንተና የሚሰጡ ሰዎች አሉ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ በስራ አስፈፃሚ ደረጃ እኩል ነው፡፡ በምክር ቤት ደረጃ ግን እኩል አይደለም፡፡ ስለዚህ እኩል በሆኑበት የስራ አስፈፃሚ ደረጃ የሚወሰነው ውሣኔ፣ በም/ቤቱ እኩል ያልሆነ ወንበር ያላቸው ሰዎች መወሰን አለባቸው የሚለው ነገር በትክክልም የህገ-መንግስትና የሕዝብ ውክልናን ይዘው ምክር ቤት የገቡትን ሰዎችን የሚጐዳ ነው፡፡ ባላቸው ድምፅ እኩል መልስ የማይሰጡበት ስለሚሆን ማለት ነው፡፡ እነዚህ የዚህ አመት የፓርላማ ጨዋታዎች ነበሩ፡፡

 
ሎሚ፡- ከጠ/ሚ መለስ ሞት በኋላ ፓርላማው መቀዝቀዝ ታይቶበታል ይላሉ;

 
ግርማ፡- መቀዛቀዝ ነው መነቃቃት…;

 
ሎሚ፡- እርስዎ ቢመልሱት አይሻልም?…

 
ግርማ፡- ጠ/ሚኒስትሩ ከሞቱ በኋላ ፓርላማው ተነቃቅቷል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ከሞቱ በኋላ ፓርላማው ተኝቷል የሚሉም አሉ፡፡ ተፋዟል የሚሉም እንዲሁ አሉ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ይሰጧቸው የነበሩ ትንሽ “ድምቀት” መሳይ መልሶች አንዳንዴ ፓርላማውን የሚያስቁ ወይም ደግሞ የሚያሸማቅቁ ነበሩ፡፡ ግን በሙሉ ልብና ስልጣን ባለመኖራቸው ተቀዛቅዟል የሚሉ ሰዎች አሉ፡፡ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ጠ/ሚ መለስ ከሞቱ በኋላ የፓርላማው አባላት የተለያዩ ሀሣቦችን በስፋት የማንሸርሸር አዝማሚያ ታይቶባቸዋል ይላል፡፡ እውነቱን ለመናገር በመለስ ጊዜ የስራ አስፈፃሚ አካሎቹ ትንሽ ሸምቀቅ ብሎ የመምጣት ሁኔታ ይታይባቸው ስለነበር አሁን ተነቃቅቷል የሚል ነገር አለ፡፡ ለኔ ሁለቱም ትርጉም የላቸውም፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ መጥተው ደመ ሞቃት የሆነ መልሣቸውን የሚናገሩበት ነገር አለመኖሩ ለኔ የተለየ አይደለም፡፡ “ለኔ የቀረብኝ ነገር ብዬ የማስበው ነገር የለም፡፡” የምጠብቀው ነገር ስላልሆነ ማለት ነው፡፡ እኔ ከኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር የምጠብቀው በእውነት የሚመጥን፣ ረጋ ያለ፣ ነጥብ ያለው መልስ እንጂ ተረት ተረት እያነሱ፣ የፈለጉትን እያሉ በተለይ ደግሞ ለልጆችም ጭምር የማይመጥን ቃላት እንዲናገሩ አልፈልግም፡፡ ከዚህ አንፃር የጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሣለኝን እመርጣለሁ፡፡ ያው እሣቸውም ሲናገሩ የሚፈልጉት ነገር ያለ ቢመስልም፣ እሱ እንዲታረም እየጠየቅኩ ቁጥብነታቸውንን ነው የምወደው፡፡ ፓርላማው ተቀዛቅዟል የሚለው ብዙም ትኩረት አይሰጠኝም፡፡ መሟሟቁ ትርጉም ከሌለው ተጠያቂነትን የማያመጣ ከሆነ ቢቀዛቀዝስ?…ፓርላማ ዋና ስራው የሕዝብን ተጠያቂነት ማምጣት ነው፡፡ የሕዝብ ወኪል የሆነ ፓርላማ ፈፃሚ አካሎችን መጠየቅ አለበት፡፡ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ያጠፉ ሰዎች አይ ምንም አይደለም እየተባሉ የሚታለፉበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እርምጃ መውሰድ እስካልቻለ ድረስ ሁሉም ጥያቄ ጠይቆ ቢወጣ፣ ምንም ለውጥ አልመጣም፡፡ እኔም አንዱ ሆኜ እጠይቃለሁ፡፡ እነሱም 300 ሆነው ጥያቄ ጠይቀው ለውጥ የማይመጣ ከሆነ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ስለዚህ አንድ እኔ እበቃ ነበር፡፡ ፓርላማው የሕዝብ ውክልና የሚኖረውው፣ ትክክል የሚሆነውም ተጠያቂነት ሲኖረው ብቻ ነው፡፡ እያንደንዳችን መታገል አለብን፡፡ በፀሎት ከሆነ በፀሎት፣ ሌላ መንገድም ካለ ደግሞ ሌላ መንገዶችን እየተጠቀሙ ፓርላማው በሚቀጥለው የተሻለ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ልንሰራ የሚገባን ይሄን ነው፡፡ አሁን ባለው ፓርላማ ግን ይሄ ይሻሻላል ብዬ አልጠብቅም፡፡

 
ሎሚ፡- በርግጥ ለብቻዎ ፓርላማ መግባትዎ የፈጠረው ተፅዕኖ አለ;

 
ግርማ፡- ምን ዓይነት ተፅዕኖ;

 
ሎሚ፡- ለብቻዎ ስለገቡ የተፈጠረ ነገር አለ;

 
ግርማ፡- እኔ ምንም እንዲፈጠር አይደለም ፓርላማ የገባሁት፡፡ ምክር ቤቶች ሁለት ዋና ዋና ተግባራት አላቸው፡፡ ህግ ማውጣት፣ አስፈፃሚ አካላትን መቆጣጠር ነው፡፡ የነዚህ ሁለቱ ስራዎች ሕግ በማውጣት አስፈፃሚ አካላትን መቆጣጠር ነው፡፡ ህግ በማውጣቱ ረገድ መቶም ሆነን ብንገባ ህግ የማውጣት ስልጣን የሚኖረው አብላጫ መቀመጫ የያዘው ነው፡፡ ግን ስምምነት ይደረጋል፡፡ ሌሎቹም ቢሆኑ ድምፃቸው ለአብላጫው ባይደርስም እንደዚህ አይነት ነገር ያደርጋሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ‹‹ብሎክ ስቲንግ›› በሚታሰብበት ቦታ ነው፡፡ ይህ በሌለበት ሁኔታ በፓርላማ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች በሕገ መንግስቱ መሠረት ተጠያቂነታቸው ለመራጩ ሕዝብ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ አይነት የሚመረጡ ቢሆን ኖሮ እኔ ጥሩ ሀሣብ ባቀርብ ለጥሩ ሀሣብ ይገዙና እዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ተፅዕኖ አሣድሪያለሁ ብዬ ላስብ እችላለሁ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ኢህአዴግ ድምፃችንን የመዝጋት ሁኔታ ነው የሚጠቀመው፡፡ የፓርቲውን ብቻ አይደለም፤ የአጋሮቹን ስብስብ ጭምር ነው የሚጠቀምበት፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ለውጥ አመጣለሁ ብዬ አስቤ አይደለም የገባሁት፡፡ ያመጡት ሁሉ ነው የሚፀድቅላቸው፡፡ ፓርላማው 15 ቋሚ ኮሚቴዎች አሉት፡፡ ከነዚህ 15 ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ እኔ ልሣተፍ የምችለው አንድ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ነው፡፡ የምሠራበት ቋሚ ኮሚቲ ውስጥ 16 ሰዎች አሉ፡፡ አንድ ነኝ፤ ስለዚህ እዚህም ውስጥ በድምፅ ብልጫም ይሁን… በእውነቱ እኛ ድምፅ ሰጥተን ስለማናውቅ አብዛኛው በስምምነት የሚያልፍ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ነው የሚባል ተፅዕኖ አመጣለሁ ብዬ ገምቼ አላውቅም፡፡ በዋነኝነት የኔ ስራ ኢህአዴግ አንድ ሕዝብን የሚመለከት ጉዳይ በሚያመጣበት ጊዜ፣ የሕዝብ ስሜት ይሄነው ብዬ ይኸኛውን ነገር ለማሣየት ነው፡፡ አላየንም ነበር እንዳይሉ፤ አልሰማንም ነበር እንዳይሉ ማለት ነው፡፡ ሰምተው በራሣቸው አንግል እንደወሰኑ እንዲያውቁት ነው ፓርላማ የገባሁት፡፡ ከዚህ አንፃር ተሣክቶልኛል፡፡ በታሪክ ውስጥ ሊመዘገቡ የሚችሉ ኢህአዴግ እየሰማ አውቆ ሳያስተካክላቸው ያወጣቸው አዋጆች አሉ፡፡ እንግዲህ የታሪክ ፍርድ ነው፡፡ ተፅዕኖውም የሚለካው ያኔ ነው፡፡

 
ሎሚ፡- ከፕ/ር በየነ ጋር ያለዎት ልዩነት ምንድን ነው;

 
ግርማ፡- በእኔና ፕ/ር በየነ መካከል አለ የሚባል ልዩነት ካለ እኔ ፓርላማ መግባቴ ነው፡፡ ፓርላማ መግባቴ ልክ ነው እላለሁ፡፡ ፕ/ር በየነ ደግሞ የኔ ፓርላማ መግባት ልክ አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡ ይሄም ልዩነት ተገቢ ነው፡፡ ችግር የለውም፡፡ ተገቢ የማይሆነው “ፓርላማ ግርማ የገባው ኢህአዴግ አስመርጦት ነው” የሚለው ነው፡፡ ኢህአዴግ አስመርጦኝ ከሆነ ፓርላማ የገባሁት፣ እሣቸው ፓርላማ ሲገቡ ኢህአዴግ አስመርጧቸው ነበር ወይ? ነው የምለው፡፡ እነዚህ ናቸው ልዩነቶቻችን፡፡ እኔ ደግሞ ለነዚህ ልዩነቶች ብዙ ጊዜ መልስ ሰጥቼ አላውቅም ነበርና በጣም ሲደጋገም መልስ መስጠት በነበረብኝ ጊዜ መልስ ሰጥቻለሁ፡፡ እንጂ ሌላ የሀሣብ ልዩነት የለንም፡፡ ፓርላማ መግባት አለብኝና ፓርላማ መግባት የለብኝም በሚለው ልዩነት እከራከራለሁ፡፡ ችግር የለብኝም፡፡ ያለስምህ ስም ሲሰጡህ ግን ትክክል አይደለም፡፡ የዛኔ ነው ፓርላማ የገባሁት በኢህአዴግ ድራማ አይደለም ያልኩት፡፡ ኢህአዴግ ብዙ ድራማ ይሰራል፡፡ ይህንን ድራማ ግን አልሰራም ስላቸው ማመን አለባቸው፡፡ ካለመኑ ግን እኔ የመድረክ አባል ድርጅት መሪ ነኝ፡፡ ያ ድርጅት የመድረክ አባል ነው፡፡ ስለዚህ መድረክ ውስጥ ኢህአዴግ አለ ማለት ነው፡፡ በኢህአዴግነት የሚያስፈርጀኝ መረጃ ካላቸው ለመድረክ አቅረበው ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ ጥምረት አንፈጥርም ብለው ወይ እኔ እንድወጣ ወይ ደግሞ ያ ፓርቲ እንዲወጣ ማድረግ አለባቸው፡፡

 
ሎሚ፡- በአሁኑ ወቅት ከመለስ ሞት በኋለ ያለውን ኢህአዴግ እንዴት ይመለከቱታል?…እንደሚታወቀው አንደኛ አመታቸው እየተዘከረ ነው፡፡ እናም የአንድ አመት ቆይታው ምን ይመስል ነበር;

 
ግርማ፡- ይሄ ጥያቄ ለኢህአዴግ ለራሱ አይሻልም ነበር? ….(ሳቅ)….እንዴት ከረማችሁ ማለት ለእነሱ ነው፡፡…. ጠ/ሚኒስትሩ ከሞቱ በኋላ ኢህአዴግ ቤቱን በጣም ይቆጣጠር የነበረበት አመት ነው፡፡ ሁሉን በእጁ ጠቅልሎ ይዞ ይመራ የነበረ አባት ሲሞት የሚፈጠር ቀውስ አለ አይደል፡፡ ውይ ቢዝነሱን ማን ይምራው; ልጆቹ እንዴት ይሁኑ; የውርስ ጉዳይ እንዴት ይሁን; ኢህአዴግ እንደዛ ነው የሆነው፡፡ ቤቱን ቀጥ አድርጐ የያዘ ጥሩ አባት የነበራቸውን እና ውርሱ ይሄ ይሄ ነው ብሎ በትክክል ሣያስረክብ ድንገት የሞተባቸውን ቤተሰቦች አስብና ኢህአዴግን በዛ መልኩ ተመልከተው፡፡ በይፋ ያልወጣ ይመስላል እንጂ በውርስ በምናምና የሚጣሉበት ሁኔታ አለ፡፡ እኔ ነኝ የአባትን ‹‹ሌጋሲ›› የምወስደው፤ እኔ ነኝ ይህን የማደርገው እያሉ የሚጣሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢህአዴግ እንዳለ ሆኖ ህወሓት የበኩር ልጅ በመሆኑ ብኩርናውን የሚመጥን ደረጃ ላይ አይደለም የሚገኘው፡፡ ድንገት ነው የሞቱባቸው፡፡
ሎሚ፡- የስልጣን አወቃቀሩን እንዴት ይመለከቱታል;

 
ግርማ፡- የፓርቲ መዋቅሩን ከዚህ በፊት በግልፅ ነው ያስቀመጥኩት፡፡ እውቀትን መሠረት አድርጐ አይደለም፡፡ ፓርርቲን መሠረት አድርጐ ነው እየተከፋፈለ ያለው፡፡ ይህንን ነው ቅድምም ያልኩህ፡፡ ‹‹ውርሱ›› በትክክል ያልተከፋፈለበት ሁኔታ አለ፡፡ በውርስ ጉዳይ ጠብ አለ፡፡ በትክክል የተከናወነ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ድሮ በኔ እምነት ጠ/ሚኒስትሩ በደንብ ጠቅላይ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በእውነት የቡድን አመራር ነው ያለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ የቡድን አመራር በሁሉም ስር ነው ያለው፡፡ ይሄን በቀጥታ የምታየው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ አዲስ አበባን የሚያስተዳድረው ኃላፊነት ያለው ከንቲባ አይደለም፡፡ ኮሚቴ የሚያስተዳድርበት ሁኔታ አይነት ነው ያለውና፡፡ ያው ኮሚቴ ደግሞ በማስ (በሒሳብ) ነው የሚሰራው፡፡

 
ሎሚ፡- የእናንተ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎችም በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች አሉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት እንቅስቃሴዎች እያደረጋችሁ ነው? እንቅስቃሴዎቻችሁስ ምን ዓይነት ምላሽ እያገኙ ነው (ከኤምባሲዎች);…

 
ግርማ፡- በመጀመሪያ ደረጃ ከኤምባሲዎች እኛ ምንም አንጠብቅም፡፡ ጉዳያቸውንም የሚከታተል ኤምባሲ መኖሩን አናውቅም፡፡ በኛ ደረጃ ሚና አላቸው ብለን አናምንም፡፡ አዎ! ያውቃሉ፡፡ ለዚህች ሀገር የሚሰሩት ነገር እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ ከዛ ውጭ ግን ሚና አላቸው ብለን አናምንም፡፡ ከኛ አንፃር ትግል ውስጥ ሲገባ እስር እንዳለ እናውቃለን፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች በሚታሰሩበት ጊዜ ምን እንደሚጠብቃቸው እናውቃለን፡፡ ተከታይም የሚገባው ሰው ምን እንደሚጠብቀው ያውቃል፡፡ ዋናው ስራ የእስረኞች ጉዳይ አይደለም፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የሁላችንም እስር ቤት ሆና ባለችበት ሁኔታ ላይ ሌሎች የተወሰኑ ሰዎች እስር ቤት ውስጥ ስለገቡ የተለየ የምናደርገው እንቅስቃሴ የለም፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞች የፖለቲካ እስረኞች መሆናቸው እንዲታወቅ፣ ያለጥፋት የታሰሩ መሆናቸው እንዲታወቅ ብዙ እንቅስቃሴዎች እናደርጋለን፡፡ በማህበራዊ ዘርፍ ደግሞ ሌላው ቀርቶ ቤተሰቦቻቸው ማህበራዊ ችግር ውስጥ እንዳይወድቁ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ እንዲቻል የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን እንሰራለን፡፡ ከዛ ውጭ ግን ዋናው መፍትሄ የሚገኘው እስረኞች ይፈቱ በሚል መፈክር አይደለም፡፡ አጠቃላይ የስርዓቱ፣ ስርዓት መያዝ ነው መፍትሄ የሚያመጣው ብለን ስለምናምን ነው ትግል የምናደርገው፡፡ እስረኛ የማስፈታት ትግል አናደርግም፡፡ ምናልባትም ይህን አቅጣጫ እንደ አቅጣጫም ያስቀመጠው አንዱአለም ነው ብል ስህተት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ብርቱካን ታስራ ፖለቲካው በሙሉ ‹‹ብርቱካን ትፈታ›› እስከሚመስል ድረስ የተደረገበት ሁኔታ ነበርና ነው፡፡ አሁን ፖለቲካችንን በሙሉ አንዱአለም ይፈታ የሚል ብናደርገው አንዱአለም ከኛ ጋር ይጣላል፡፡ ስለዚህ እኛ ደግሞ አንዱአለምን ማስቀየም አንፈልግም፡፡ የአንዱአለም ትግል ስርአቱ ስርአት እንዲይዝ እንጂ የተለየ ነገር በእስረኞች ላይ እንድናደርግ አይደለም፡፡ ግን የሕግ ጉዳዮቻቸውን እንከታተላለን፡፡ ለታሪክ የሚመዘገቡ ነገሮችን ማለት ነው፡፡

 
ሎሚ፡- የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ መብት ተወካዮች እንዲሁም የአሜሪካ ከፍተኛ ሹማምንት (የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሣደርን ጨምሮ) ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፤ እነሱን የማግኘት እድል አላጋጠማችሁም;

 
ግርማ፡- ያገኘናቸው ሰዎች አሉ፤ እኔ አልነበርኩኝም እንጂ፡፡

 
ሎሚ፡- ምን አዲስ ነገር ነበረው;

 
ግርማ፡- ምንም የለውም፡፡ በይፋ የሰጡት መግለጫ ነው፡፡ የተረጋገጠው ነገር ግን እኛ እስር ቤት ስንሄድ የሚደርስብን ውክቢያና እንግልት እነሱም ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ መከናወኑ ነው፡፡ እኛን አያምኑንም ነበር፡፡ እስረኞችን መጠየቅ ተከለከልን ስንል ውሸት ሊመስላቸው ይችላል-ውጭ ያሉ ሰዎች፡፡ አሁን ግን በትክክል በዘዴ እነሱንም እንዳይጐበኙ እንዳደረጓቸው አይተው ሄደዋልና ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እኛ ግን ዕለት በዕለት የምናየው ነገር ነው፡፡

 
ሎሚ፡- እንደሚታወቀው የሙስሊሙ ጉዳይ በጣም እየሰፋ መጥቷል፣ ላለፈው አንድ አመት የነበረው ሁኔታ በሰላማዊ ተቃውሞ የተገደበ ነበር፡፡ አሁን ግን ደም የፈሰሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የመንግስትን እርምጃ እንዴት ያዩታል? መፍትሔውስ ምንድን ነው ይላሉ;

 
ግርማ፡- መፍትሄው ውይይት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሌላ መፍትሄ የለውም፡፡ በኢሳት ቴሌቭዥን አንድ ቃለ-መጠይቅ በዚህ ጉዳይ ላይ እያየሁ ነበር፡፡ ልክ እኛ እዚህ ሀገር ውስጥ የሚገጥመንን አይነት የሙስሊም መሪዎችንም የሚገጥማቸው ሁኔታ አለ፡፡ በሙስሊሙ ውስጥ ያለውን የኃይማኖት ጥያቄ ለምንድነው ወደ ሕብረተሰቡ ወስዳችሁ ፖለቲካ የማታደርጉት ተብለው ይጠይቃሉ፣ ተጠይቋል፡፡ ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ እኛም ጋር የመጣ አለ፡፡ ለምንድነው የሙስሊሙን ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ አድርጋችሁ የማታራግቡት ተብለን ተጠይቀናል፡፡ እነዚህ ሁለቱም ትክክል አይደሉም፡፡ እኛም ይህንን አጀንዳ አድርገን የፖለቲካ ስራ ለመስራት እቅድም ፕሮግራምም የለንም፡፡ በጣም ደስ ያለኝ ነገር ከነሱም በኩል ይህ ነገር የለም፡፡ ይህንን ኮረንቲ ለማገናኘት ግን ኢህአዴግ ተግቶ እየሰራ ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን ገብተውበታል እያለ በሌለንበት ቦታ ውስጥ እያገናኘን ሰበብ መፍጠር ይፈልጋል፡፡ ከኛ አንፃር የመርህ ጉዳይ ነው፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ በሚነሣበት ቦታ ላይ ሙስሊሞች መብታችን ተጣሰ ብለው ሀሣባቸውን ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ አንድነት በጠራው ስብሰባ ላይ ለምን ሙስሊም ተገኘ ብለው ይንጫጫሉ፡፡ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ አይደለም እንዴ; አንድነት በጠራው ስብሰባ ላይ ሙስሊም መምጣቱ እኛን ያስደስተናል፡፡ ለምን ከዚህ በፊት በብዛት የማይሣተፉ የነበሩ ሙስሊሞች አሁን መብታቸው በደንብ እየተነካ ስለሆነ በፖለቲካ ፕሮግራሞች ላይ መንቀሣቀስ ጀምረዋል፡፡ ምርጫ በመስጊድ እናድርግ ማለት ምን ስህተት አለው; በመስጊድ አይደረግም የሚለውን ክርክር እነሱ ናቸው ከመጅሊሣቸው ጋር መነጋገር ያለባቸው፡፡ መንግስት ምን አግብቶት ነው በዚህ ላይ መግለጫ የሚሰጠው፡፡ መንግስት ምን አግብቶት ነው አህባሽ፣ ሰለፊ ምናምን እያለ ማብራሪያ የሚሰጠው?…ይሄንን እነሱ ያብራሩ፤ እነሱ ይህንን እንዲያደርጉ መተው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አሸባሪ ድርጅት ምናምን ሲሉ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የተወሰነ ማሻሻያ አድርገውበታል፡፡ “አክራሪ” ወደሚል መጥተዋል፡፡ አክራሪ ብለው አታክርሩ ተብሎ ለመነጋገር የሚቀል ከሆነ ወደ ቀለል ወዳለው መምጣታቸው ክፋት አለው ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን አክርረዋል የተባሉት ሰዎች ጋር አታክርሩ ተብለው መነጋገርና መፍትሄ ማበጀት ነው፡፡ መፍትሄው ሁሉንም ላያስደስት ይችላል፡፡ ግን መፍትሄ እያበጀንለት ነው ብለው መናጋር ቢጀምሩ አብዛኛው ሙስሊም ይሄ የመነጋገሩ ነገር ያበርደዋል፡፡ በሰላም ሶላታቸውን ሰግደው የሚመለሱበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ከዛ ውጭ አንዳንዶቹ ለምንድነው በሶላት ሰዓት ላይ ሌላ ጥያቄ የሚያቀርቡት ይላሉ፡፡ ሶላታቸውን በስርዓት ነው የሚሰግዱት፡፡ ሶላታቸው ካለቀ በኋላ ግን በአጋጣሚ የሚገናኙበት ቦታ ያ ስለሆነ መልዓክታቸውን ለማስተላለፍ ቢጠቀሙበት ጥፋቱ አይታየኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ፖለቲካ ርኩስ ነው ያለው ማነው; ስለዚህ መብታቸውን፣ የእምነት ጥያቄያቸውን ከመስጊድ ውጭ የት ያቅርቡ? የፖለቲካ መሪዎች ቢሮ መጥተው ነው የሚያቀርቡት; ቆይ መጂሊሱ ይለወጥ ብለው አንድነት ፓርቲ ቢሮ ቢሰበሰቡ ምንም ትርጉም የለውም? በእርግጠኝነት የምነግርህ አንድነት ፓርቲ እንደ ፓርቲ እንደዚህ አንድ አጀንዳን ይዞ እዛ ላይ ገብቶ የፖለቲካ ጉዳይ ለማድረግ አይፈልግም፡፡

 
ሎሚ፡- ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ከዋልታ ጋር ቃለመጠይቅ አድርገዋል፡፡ በቃለ መጠይቁ ላይ አንዳንድ ፓርቲዎችን ከሙስሊሙ ጉዳይ ጋር አያይዘው ተናግረዋል፤ ይህን እንዴት ያዩታል;

 
ግርማ፡- የፈለጉትን አንዳንድ ፓርቲ ሊገምቱ ይችላሉ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በፓርላማ ከሻዕቢያ ጋር እንደምትሰሩ ማስረጃ አለን፤ የእንትና ተላላኪ ምናምን ይሉ ነበር፡፡ የዛኔ ምን አይነት ደካማ መረጃ ነው ያላቸው ብለን ነው እንጂ የምንጠራጥራቸው ብዙም በዚህ ጉዳይ አንረበሽም፡፡ አሁንም እንደዚህ ያደርጋሉ የሚሉ ከሆነ እኛ በመርህ ነው የምንሰራው፡፡ ከመርህ ውጭ የምንሆነው ነገር የለም፡፡ ከዚህ መርህ ውጭ ሰዎች ቢጠረጥሩ፣ ሲጠራጠሩ ቢውሉ የሚደክሙት እነሱ ናቸው፡፡ ይሄ ማለት ግን እኛ ላይ እንቅፋት የለውም ማለት አይደለም፡፡ እንቅፋቶች ይፈጥራሉ፡፡ አሁን ፋንፍሌቶች እንበትናለን፤ የእለት ተእለት የፖለቲካ ስራዎች እየሰራን እያለ ፖሊሶች በየመንገዱ ላይ ይይዙህና ‹‹እናንተ አሸባሪዎች›› ምናምን ይላሉ፡፡ ቀልዴን እንዳይመስልህ፡፡ ‹‹አሸባሪዎች›› ይሉናል፡፡ በምን አይነት የፖሊስ አስተሳሰብ ውስጥ አንዳለን የሚያሣይ ነው፡፡ የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት የሚለውን ፕሮግራም መጀመራችን የኢትዮጵያን የፖሊስ ተቋም እንድንታዘብ አድርጎናል፡፡ እያንዳንዱ የፖሊስ ተቋም ሕገ መንግስቱን ጥንቅቅ አድርጐ ቃል በቃል ማወቅ አለበት፡፡ ትራፊኮች ታርጋ ቁጥር ለቅመው እንደሚይዙት ፖሊሶችም ሕገ መንግስቱን ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል፡፡ ግን ኮከብ ትከሻቸው ላይ ያደረጉ በሙሉ የፀረ ሽብር ህጉን ለምን ትቃወማላችሁ? ‹‹አሸባሪዎች›› ናችሁ ይሉናል፡፡ ይሄማ ህገ መንግስቱን መናድ ነው ይሉናል፡፡ ተመልከት፤ ህገ መንግስት እንዴት እንደሚናድ እንኳን አያውቁም፡፡

 

ሎሚ፡- በመስከረም ወር የፓርላማው የመጀመሪያ ስራ ርዕሰ ብሔር መምረጥ ነው፡፡ ሦስት ሰዎች ለፕሬዚዳንትነት ተገምተዋል፡፡ አንደኛ ዶ/ር አሸብር፣ ሁለተኛ ኃይሌ ገ/ስላሴ እንዲሁም ሶሎሜ ታደሰ፤ ይሄን እንዴት ያዩታል? በተለይ ኃይሌ እንደሚሆን ነው በርግጠኝነት እየተነገረ ያለው፡፡ እርስዎ በፓላማ ካለዎት ቆይታ ከሚያዩት የኢህአዴግ አሠራር ምን ይገምታሉ;

 
ግርማ፡- ዶ/ር አሸብር አይሆኑም፡፡ እኔ ድሮም ይሆናል የሚል ግምት የለኝም፡፡ በጣም ብዙ ሰዎች ናቸው በእሱ ጉዳይ የሚሳሳቱት፡፡ የአሁኑ ፕሬዚዳንት የግል ተወዳዳሪ ስለነበሩ አሁን ያለው የግል ተወዳዳሪ ዶ/ር አሸብር ስለሆነ፣ በዚህ ምክንያት እሱ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ይንጸባረቃል፡፡ ዶ/ር አሸብር ፕሬዚዳንት አይሆንም ስልህ እሱ አይፈልግም ማለት አይደለም፡፡ እሱ ሊፈለግ ይችላል፤ ግን አይሆንም፡፡ ቅድም እንዳልኩህ የስልጣን አወቃቀሩ ፓርቲን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ከደቡብ የሚሆንበት ሁኔታ ሚከብድ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ከደቡብ፣ ፕሬዚዳንቱም ከደቡብ ሲሆን የኃይል ሚዛኑ ወደታች ይወርዳል፡፡ በዚህ ቀመር ስለሚሰሩ ዶ/ር አሸብር የሚሆን አይመስለኝም፡፡ ይሄ የኔ ግምት ነው፡፡ ኃይሌ የመሆን ዕድል ይኖረዋል፡፡ ኃይሌ ለዚህች ሀገር ከዚህ የበለጠ ሊሣተፍ የሚችልበት ሌላ ቦታዎች አሉት፡፡ ባለፈው አንድ ጋዜጣ ላይ ሪዞልቱን ቢያስተዳድር ይሻላል ብሏል፡፡….አዎ ሪዞልት ማስተዳደር የበለጠ ለዚህች ሀገር የሚጠቅም ስራ ነው፡፡ ወይም በአመት አንድ ማራቶን የበለጠ ሊሆን ይችላል፡፡ በሚቀጥለው ምርጫ ተወዳድሬ ምክር ቤት እገባለሁ ብሏል፡፡ ኃይሌ ፕሬዚዳንት ከሆነ በፕሮቶኮል ታጥሮ ምንም ስራ አይሰራም ማለት ነው፡፡ በዶ/ር ነጋሶ ጊዜ አንበሳ ጊቢ ነበር የሚባለው፡፡ አንበሳ ጊቢ ገብቶ ከአንበሶች ጋር ተቀምጦ ምን አይነት ሕይወት እንደሚኖር አስበው እስኪ፡፡ ለኃይሌ ይሄ አይመጥነውም፡፡ ስለሰሎሜ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ግን ሌላ አማራጭ ሞልቷል፡፡ ኦህዴድ ብዙ ቦታዎችን አላገኘንም ከሚለው ቅሬታው አንፃር የፕሬዚዳንትነቱ ቦታ ለኦሮሞ ሊሰጥ ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ኦሮሞ ብቻም አይደለም፤…ፕሬዚዳንቱ የኦሮሞ ሙስሊም ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም አለኝ፡፡ ምናለ ለአንድ ሱማሌ ቢሰጠው? ለአፋር ቢሰጠው? ለቤንሻንጉል ቢሰጠው? ከአጋር ድርጅቶች ለአንዱ ቢሰጥ ምን አለበት? ልክ ለግል ተወዳዳሪ ለግርማ ወ/ጊዮርጊስ እንደተሰጠው ከአጋር ድርጅቶች ለአንዱ ቢሰጠውስ? ግን ፖለቲካዊ አማራጭ አለው፤ ትልቁ ግምቴ ግን ፕሬዚዳንት ሊሆን የሚችለው ኦሮሞ ሙስሊም ነው፡፡

 

 

 

Latest from Blog

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
Go toTop