አቻምየለህ ታምሩ
አማራ በአማራነት የሚደራጀው እንደ ኦነግ አይነት ኦሮሞነት ወይንም እንደ ወያኔ አይነት ትግሬነት ለመፍጠር አይደለም። እኛ የአማራ ወጣቶች በአማራነት የምንደራጀው ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማያት ቆራሄ ላይ መስዕዋት የሆኑባትን ኢትዮጵያ፤ ጀኔራል ለገሰ ተፈራ ዋቤ ሸለቆ ደማቸውን ያፈሰሱባትን የአባቶቻችን ምድር ረስተን አይደለም። አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው አፈወርቅና ለገሰ ዋጋ በከፈሉባት አገር በሰፊዋ ኢትዮጵያ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በእኩልነት ለመኖርና የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ ለመከላከል ብቻ ነው።
አንዳንዶች አማራ በአማራነቱ የሚደራጀው እንደ ኦነግና ወያኔ የራሱን መንግስት ለመመስረትና ለፖለቲካ ስልጣን እየመሰላቸው የአማራን መሰባሰብ በጥርጣሬ ሲመለከቱት ይስተዋላል። በርግጥ በብሔረሰብ መደራጀት ማለት እንደ ወያኔና ኦነግ አገር ለማፍረስ መሆኑን በተግባር ያየ ማህበረሰብ አማራው በአማራነቱ ይደራጅ ሲባል በጥርጣሬ አይን መመልከቱ ባይፈረድበትም፤ አማራው በአማራነቱ የሚደራጀው ከሌላው ጋር የሚያስተሳስረውን የወንድማማችነት ሰንሰለት የበለጠ ለማጠናከር እንጂ ለመበጣጠስ አለመሆኑንና ከኢትዮጵያም ሆነ ከህዝቧ አንጻር ለመቆም እንዳልሆነ ሲነገዘብ ግን የአማራውን መደራጀት ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ አኳያ በጥርጣሬ ሊያየው አይገባውም።
ከፍ ብሎ ከቀረበው የአማራ መደራጃት አስፈላጊነት በተጨማሪ እኛ የአማራ ወጣቶች በአማራነት የምንደራጀው የግራ ፖለቲካ ያጠየማቸውን የአማራ ሰብዓዊ እሴቶች፤ምግባርና አስተሳሰቦች፤ አማራው ለፍቅር ገር፣ የቅንነት አሽከር መሆኑን አንደበት አውጥተን፤ ግዝፍ ነስተን መልክዓ ልቡናውን ልናሳይለትም ጭምር ነው።
ስለዚህ በአማራነት ስንደራጅ ሰብዓዊ የሆኑትን የአማራውን መሰረታዊ እሴቶች ተሸክመን፤ የአማራው የኑሮ አድማስ በስነ ምግባር ደንቦች የታሸ፤በስሜት የበሰለ፤ በእውቀትና ግንዛቤ የላቀ መሆኑን ማስመርከርና አማራው በሰርክ ህይወቱ ማህበራዊ ስርዓት ሳይናጋ፤ አገራዊ ቀውስ ሳይፈጠር ማህበራዊ ለውጥ የሚጠነስስ፤ የራሱንና የሌሎችን ባህልና ታሪክ ጠብቆና አክብሮ የሚኖር፤ በትህትና፣ በቸርነትና በይቅር ባይነት የተገነባ የምር ኢትዮጵያዊ መሆኑን እንድናሳይም ይጠበቅብናል።