በወያኔው የዘረኛ አስተዳደር ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን ይዘው በህዝብ እምባና ደም ሲቀልዱ የነበሩ በተለያየ ምክንያት የተባረሩ ሰዎች በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ሊያዩ የቻሉት ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ ነው:: ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ህዝባዊነታቸውን ሊያሰሙ ሀሳቡ እንኳ ያልነበራቸው የቀድሞ ባለስልጣናት ከስልጣን ከተባረሩ በኋላ አይናቸው ተገልጦ “ሕዝብ ተበደለ” እያሉ መንግስትን ሲነቅፉ እየሰማን ነው:: አንዳንዶቹ ደግሞ ከስልጣን ከተባረሩም በኋላ ጥቅማቸው ተከብሮላቸው ተንደላቀው እየኖሩ ለወያኔ መንግስት በስልት የመከላከል ስራ እየሰሩ ነው:: ወያኔ መራሹ አገዛዝ የሲቭል መንግሥት እንደሆነ የሚናገሩ እንደነ ጀኔራል አበበ ተ/ሀይማኖት ያሉ ሆን ብለው የሚያሳስቱ ሰዎች መንግስት አንዳንድ መሻሻሎችን አድርጎ እንከን የሌለው የሚሉትን ህገ-መንግሥት ለማስፈጸም እንዲንቀሳቀስ እየመከሩ ነው:: የመንግስት ባለስልጣኖች ሀገሪቱን ለመምራት ድክመት እያሳዩ መሆናቸውን በመግለጽ ጀኔራል ሳሞራ የኑስ ያደረጉትን ንግግር መሰረት አድርገው ጀነራል አበበ ሲያብራሩ የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ወታደራዊ ሀይሉ መፈንቅለ መንስት አድርጎ ስልጣን እንዳይዝ የኢትዮጵያ ህዝብ በንቃት እንዲጠብቅ መክረዋል:: እያሉን ያሉት አሁን ያለው የሲቭል አስተዳደር መፈንቅለ መንግስት ተደርጎበት ስልጣን ወደወታደሩ እንዳይገባ ህዝብ ጥበቃ ያድርግ ነው:: ብዙሀኑ የኢትዮጵያ ህዝብምን ቢሆን አሁን ያለው መንግሥት የወታደር መንግሥት መሆኑን የረሳው ይመስላል:: በ 1966 ዓ.ም ከጦር ሀይሎች: ከፖሊስና ከማረሚያ ቤቶች ተውጣጥቶ ሀገሪቱን በበላይነት የመራው ደርግ ከአመታት በኋላ የወታደራዊ መለዮውን አውልቆ የህዝብ አስተዳደር መስርቻለሁ ብሎ ማወጁ ይታወሳል:: ደርግ የወታደራዊ ልብሱን ሲቀይር ወታደራዊ ባህሪውን ግን ሊቀይር የሚቻለው አልነበረም:: ከሲቭል ማህበረሰቡ የተወሰኑ ሰዎችን መራርጦ ካስጠጋ በኋላ እየተገዛን ያለነው በወታደራዊ ኃይል ነው ሲሉ የሚሞግቱትን ሰዎች እንዲያው ክፋታችሁ ሆኖእንጅ እውነት አሁን ደርግ አለ? ሲል ነበር ምላሽ የሰጠው:: የአሁኑ ወያኔም ቢሆን የደርግን ፈለግ ተከትሎ ራሱን ከወታደር ወደ ሲቭል ቀይሮ ሕዝባዊ መንግሥት መስርቻለሁ እያለን ነው:: እንደእኔ እምነት ከሆነ ወታደር ማለት በውትድርና ሙያ ሰልጥኖ በየትኛውም ጎራ የሚሰለፍ ተዋጊ ሀይልነው:: በዚህ አረዳድ ስንሄድ ወያኔወችም ሆኑ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በውትድርና ሰልጥነው በሙያው ተጠምቀው ተዋግተው አሸንፈው ወደስልጣን የመጡ መሆናቸውን እንገነዘባለን:: ደርግ እንዳደረገው ሁሉ ወያኔም ከራሳቸው አልፈው ስለህዝብና ስለሀገር ማሰብ የተሳናቸውን ሰዎች በመብራት እየፈለገ በየብሄረሰብ ጉረኖ እንዲሰበሰቡ አድርጎ ሲያበቃ ከላይ ተቀምጦ እንደፈለገው እያሽከረከረ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ስርአት ተዘርግቷል ሲል ይቀልዳል:: እውነታው ግን ሀገሪቱ እየተመራች ያለችው በዘረኛ የወያኔ ወታደሮች ሲሆን ሌሎቹ ከወያኔ ጉያ የተወሸቁቱ በራሳቸው አስበውና አቅደው መስራት የማይችሉ የትእዛዝ ተቀባይናእንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ የማፈን ድርሻ ያላቸው ናቸው::
ለምሳሌ ያህል ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያምን ብናነሳ ከእምነትም ሆነ ከህግ ያፈነገጠ ስራ የሚሰሩት የታዘዙትን ብቻ የሚፈጽሙ በመሆናቸው ነው:: የመብት ጥያቄ ያነሱትን ኢትዮጵያውያን በሀይል እንዲያፍን ለፖሊስና ለመከላከያ ሀይል ትእዛዝ ሲያስተላልፉ የመናገርና የመቃወም መብት መኖሩን ረስተውት አይደለም:: በሰሞኑ የተመድ ስብሰባ ላይ ተገኝተው: የህዝብ ተቆርቋሪ እንደሆኑ የሚገልጹ ጽንፍ የረገጡ ቡድኖች በማህበራዊ ሜዲያ ሁከትን እየቀሰቀሱእንደሆነ ተናግረዋል። የህዝብ ጩኸት ተዳፍኖ ወያኔወች የፈለጋቸውን እያደረጉ ይቀጥሉ የሚል እንደምታ ያለው ይህ ንግግራቸው ምን አይነት ሰው እንደሆኑ የሚያሳይ ነው:: ወያኔወች በህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ጭፍጨፋና ዘረፋ በአለም አደባባይ ለመናገር ድፍረቱ የሌላቸው እኒህ ሰውየ በሚደርስበት ዘርፈ ብዙ ግፍ እየጮኸ ያለውን ህዝብና ተቆርቋሪወቹን ለማፈን የሚያደርጉት ድርጊት ሀገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ ከሚል ጤነኛ ሰው የሚጠበቅ አይደለም:: በወያኔ ግፍ እየተፈጸመብኝ ነው የሚለው ህዝብ ለምን ድምጹን አጥፍቶ መከራውን አልተቀበለም: የሕዝብን ጩኸት እያስተጋቡ ያሉት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና አለም አቀፍ ድርጅቶችም ለምን አይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ አልሆኑም በሚል መልኩ ሲወቅሱ ሰምተናል:: ድመት ወተት ሰርቃ ስትጠጣ አይኗን የምትጨፍነው እንዳትታይ ነው እንደሚባለው ሁሉ የወያኔው መልእክተኛ ኃ/ማሪያምም ጌቶቻቸውና ድርጅታቸው የሚፈጽሙትን በደልና ዘረፋ የአለም መንግስታት የማያውቁት መስሏቸው የህዝብ አመጽ የሚቀሰቅሱትና ዘረኝነትን የሚሰብኩት የሀገሮችን ሰላምና እድገት የማይፈልጉ ሀይሎች እንደሆኑ አርገው በማቅረብ ለጌቶቻቸው ሲከላከሉ ለወያኔ ያላቸውን ታማኝነት አስጠብቀው ጥቅማቸውን ለማስከበር አይናቸውን ጨፍነው ሲዋሹ ሰምተናል:: እውነት ህዝብ ማንም እንደፈለገ የሚነዳው በሆነ ባልሆነው ቅስቀሳ ለአመጽ የሚነሳ ነው? ቢያንስ አለ ብለው ያመኑትበመንግስት ባለስልጣናት የሚፈጸም የተቀናጀ ሙስና ሕዝብን ሊያሳምጽ አይችልም? ሌላው ቢቀር ጣራ የነካው የኑሮ ውድነት መንግስት ከስልጣን እንዲለቅ የሚያስጠይቅ ምክንያት አይሆንም? ቀደም ሲል የኢህአዴግ ባለስልጣን የነበሩ ሰዎች አልፎ አልፎ ብቅ እያሉ መንግስትን እየነቀፉ ሲናገሩ እየሰማን ነው:: እንደ ገብሩ አስራት: ታምራት ላይኔና ጁኔዲን ሳዶ ያሉት የቀድሞ ባለስልጣኖች ከኢህአዴግ ተወንጅለው ከተባረሩ በኋላ መንግስት እየተከተለ ያለው አካሄድ የተበላሸ ነው ብለው አውግዘው ለህዝብ ጥያቄ ትክክለኛ ምላሽ እንዲሰጥ እየጠየቁ የመፍትሀ አቅጣጫ እየጠቆሙ ነው:: እኒህ ሰዎች ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የተሰጣቸውን ተልእኮ ከመፈጸም ውጪ ሳት ብሏቸው ህዝብ እየተበደለ ነው ብለው መንግስትን ሲሞግቱ የተደመጡበት ጊዜ አልነበረም:: ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያምም እውነቱን እንዲናገሩ ከኢህአዴግ እስኪባረሩ መጠበቅ ይኖርብናል:: ሟቹ ጠ/ሚኒስትር እንዳሉት የኢህአዴግ ስልጣን ልክ እንደዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው:: ከአንቀላፉ የጨበጡትን ይለቁና መውደቅ ይከተላል:: ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ላያዘልቁት የወያኔ ባለስልጣናትን በሙስና ሲከሱ ከዛፍ ላይ ተኝተው የጨበጡትን ግንድ መልቀቅ መሆኑን የተረዱት አይመስልም::አንድ ቀን ስምና መልክ ተሰጥቶወት ይወረወሩና ከበታችወ ተኮልኩለው የርስዎን ስልጣን ከሚቋምጡት ሰዎች አንዱ በወንበሩ ተተክቶ እርስዎ ይሉ የነበሩትን ሲል: ሲያደርጉ የነበሩትን ሲያደርግ ያኔ በሀገር ውስጥም ይሁን በስደት ላይ ሆነው መንግስትን እያወገዙ ከወያኔ ጋር የቆዩባቸውን ጊዚያት እየረገሙ እውነቱን ይነግሩናል::
ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!