ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ የዕለቱን ንግግራቸውን የጀመሩት በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የታወቀውን የሩስያ ሥነ ጽሑፍ ሰው አሌክሳንደር ኸርት ሰርን አባባል በማስቀደም ነበር። ይህ ጸሐፊ ‹‹ታሪክ ከውርስ የሚገኝ ማብቂያ የሌለው እብደት ነው›› ይል እንደነበርና ይህ ብቻ ሳይበቃም “ታሪክ የእብዶች ግለ-ታሪክ ነው” ማለቱን አስታውሰዋል። ለዚህ አባባሉም ምሳሌዎች ያቀርብ ነበር ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፣ የፐርሺያ ጦር አቴንስን ሊይዝ ሲመጣ ካርቲዬስ የተባለው ጀግና ጦሩን ለማቆም ዘሎ ገደል ይገባል። ካርቲዬስ ገደል የሚገባው የዘመተበት ጦር ይቆማል በሚል እሳቤ ነበር። ኤፍጂኒያ ላይ ንጉሡ መርከቡ ከአቴንስ የባሕር ዳርቻ ለመልቀቅ ሲፈልግ ንፋስ ከሌለ ንፋስ እንዲመጣ በማሰብ የ13 ዓመት ሴት ልጁን ሰውቷል። ይህም እብደት ነው።
በሦስተኛ ደረጃ፡- የፕራሺያ ንጉሥ የተወሰነ ውቅያኖስ አስቀይሞኛል በማለት ወደ ሦስት መቶ ሺሕ ወታደር ሰብስቦ ውቅያኖሱን በጅራፍ ያስገርፈው ነበር። ይህም እብደት ነው። አራተኛ፡- አቴናውያን ከአእምሮ የፈለቀ ነገር ሲያስቸግራቸው የሶቅራጠስን አንጎል በሄሞሎክ አጥበው ገደሉት። አምስተኛ፡- ክርስትና ገና ብቅ ብቅ በሚልበት ጊዜ የሮማው ግዛተ ዐፄ ቄሣሮች የክርስትና አማኞችን ለአውሬ በመስጠት እምነቱን ይፈታተኑት ነበር። በመጨረሻም ክርስቲያኖቹ ደግሞ የበላይነትን ሲቆጣጠሩ ነገሥታቱ ካደረጉት አስከፊ ሥራ በላይ እርስ በርስ ጭከና በሞላበት አኳኋን ተበዳድለዋል። እንግዲህ አሌክሳንደር ኸርት ሰርን ‹‹ታሪክ የእብዶች ግለ-ታሪክ ነው›› ያለው ይህን ሁሉ ካለ በኋላ ነው።
ዶ/ር ዳኛቸው የአሌክሳንደር ኸርት ሰርን አባባል ወደ ሀገራችን ሲያመጡት አንድ ምሳሌ ጠቅሰዋል። “አንድ ሺሕ አራት መቶ ማይልስ የሚያህል የውኃ ጠረፍ ካስረከብን በኋላ አራት መቶ ኩንታል ድንች ለማያመርት ቦታ ከ50 እስከ 60 ሺሕ ወጣት በጦርነት ገብረናል። ይህ ደግሞ የእኛ ሀገር የታሪክ እብደት ነው” ሲሉ ከዐሥራ አራት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተደረገውን ጦርነት “የእብደት ታሪክ ነው” ብለዋል።
ዛሬ ከ21 ዓመታት በኋላ
ዶ/ር ዳኛቸው ከላይ የተጠቀሰውን የ“እብደት ታሪክ” ከተረኩ በኋላ አሁንስ ሲሉ ጠይቀዋል። በዚህ ንኡስ ሐሳብ ሥር “የት ነው ያለነው? ምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው? ሥርዐቱ ምን ላይ ነው?” በማለት አንዳንድ ነጥቦችን አጋርተዋል።
ከሁሉም በላይ ኢሕአዴግ “አብዮታዊ ፓርቲ ነኝ” የሚለውን አገላለጽ በንግግራቸው ያስቀደሙት ዶ/ር ዳኛቸው፣ “አብዮት ብዙ ጊዜ ስለ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚያወራ ነገር ነው። የፈረንሳይን፣ የአሜሪካን፣ የራሺያን እንዲሁም የእኛንም አብዮት ብናይ ሄዶ ሄዶ መሠረቱ ማኅበራዊ ፍትሕ ነው፤” ብለዋል።
“ማኅበራዊ ፍትሕ ደግሞ የሚገለጸው ፍትሐዊ የነዋይ ክፍፍል ላይ ነው” የሚሉት ዶ/ር ዳኛቸው በእኛም ሀገር “ገበሬው ደኃ ነው” በሚል “መሬት ለአራሹ” መባሉንም በማስታወስ የአብዮት ማዕከላዊ ማጠንጠኛ (focal point) ማኅበራዊ ፍትሕ እንደሆነ አስረድተዋል።
ኾኖም ግን አብዮት በተፈጥሯዊ ሂደቱ የሚሸጋገርባቸው ደረጃዎች እንዳሉት ዶ/ር ዳኛቸው ተናግረዋል። ይህም ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ እየተባለ ሊከፋፈል ይችላል። ምሁሩ ደረጃዎቹን ከመግለጻቸው በፊት አብዮት በምን መልኩ ሊነሣ እንደሚችል ጠቁመዋል። አብዮት የሚነሣው በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያለ የመንግሥት መዋቅር መቀጠል ሲያቅተው፣ ሕዝቡም ባለው ሥርዐት ርካታ ሲርቀው ጉሩምሩምታ ያሰማል። ከዚያም ወደ ቀውስ ይገባል። በአንፃሩ የተለያዩ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ፤ እናም ቀውሱ ለፍትሕና ለንዋይ አቅርቦት ያለው ተነሳሽነት ምንም የማይላወስ ይኾንና ሥርዐቱ ሲዳከም በተቃራኒው በትይዩ የሚቋቋሙ ኃይሎች ተጠናክረው “ይህን መንግሥት ብንሽረው ይሻላል” ብለው መንግሥትን ይለውጣሉ ብለዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው መንግሥትን ለመለወጥ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላሉ። አንደኛው “ብንለውጠው በጎ ነገር እናገኛለን” የሚል እምነት ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ መሥዋዕትነት ነው። እነዚህ ሁለቱ ነገሮች ሲቀናበሩ መንግሥት ይለወጣል። ይህ የአብዮታዊ ሂደት የመጀመሪያው ደረጃ ሲኾን ሁለተኛው ደረጃ የመንግሥት ለውጡ ከተሳካ በኋላ የሚያጋጥመው ከባድ ነገር ነው።
ሁለተኛው ደረጃ ከባድ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት ዶ/ር ዳኛቸው ሲያስረዱ፤ “አዲስ ሥርዐት ሲዘረጋ ጎበዝ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ፈሪ ሰዎችም አሉ። አገር ወዳዶች እንዳሉ ሁሉ አጋጣሚውን መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ባለተስፋዎች እንዳሉ ሁሉ ኪሳቸውን መሙላት የሚፈልጉ አሉ። አንድ አብዮት እነዚህን ሁሉ አቅፎ ነው የሚመጣው። በኻያኛው መቶ ክፍለ ዘመን በድኅረ አብዮት መንግሥት ተብሎ ከተዘረጋ በኋላ የበላይነት የሚይዙት ሆዳሞቹ ናቸው። ክላሽ ሲተኩስ የነበረው ተወርውሮ አንድ ቦታ ቂብ ይላል። በዚህ ጊዜ በመካከላቸው ግጭት ይመጣል። ሕዝባዊነታችን ላላ፣ ርእያችን ግቡን አልመታም የሚሉ ይነሡና ከጥቅመኞቹ ጋራ ውዝግብ ይጀመራል” ብለዋል።
ሦስተኛው የአብዮት ደረጃ አብዮቱ ሕዝባዊ መኾኑ ያበቃና በ(Thermadorial) ወይም ራስን ማዳን ዋነኛው አጀንዳ ይኾናል ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፤ “አብዮቱ ተረስቶ ተመልሶ ራሱን ወደ መከላከል ያመራል። በዚህ ጊዜ ምንም ዐይነት የነፃነት ጥያቄዎችንና ንቅናቄዎችን አይታገሥም፣ የማዕቀብ ኃይሎቹ ይጠናከራሉ፣ ተቀናቃኝ ቡድኖች ጫና ይበዛባቸዋል፤” ብለዋል።
ሌላው ሦስተኛው የአብዮት ደረጃ (Thermadorial) ጊዜ ማዕቀብን ከማጠናከር ባለፈ አዲስ ነገር የለም። አዲስ አነጋገር የለም። ሁልጊዜ ወደኋላ ይኬድና ያለፈውን ስርዓት እንዴት መጥፎ እንደሆነ የሚነገርበት ጊዜ ነው ብለዋል። እንደምሳሌም ዶ/ር ዳኛው ስለሀገራችን ሁኔታ ሲጠቅሱ የአቦይ ስብሐትን ንግግር አስታውሰዋል። አቦይ ስብሃት “የድሮውን ስርዓት ማስታወስ አለብን” ማለታቸውን ጠቅሰዋል። አፄ ኃይለስላሴ ከነገሱ ግን 72 ዓመት ሆኗቸዋል። ያም ሆኖ የአብዮቱ ሕዝባዊነት ሲያበቃ (Thermadorial ደረጃ ሲደርስ) አንድ ክፍለ ዘመን ወደኋላ ሄደህ ታወራለህ፤ ምክንያቱም አሁን ባለህበት ሁኔታ የምታቀርበው አዲስ ነገር የለም። አዲስ ነገር አምጥቼ ላውራ ብትል “ያው የርግብ አሞራ” ብለህ ነው የምትዘፍነው፤ ያልቅብሃልና፤ አስደማሚ ፕሮጀክቶችን እየፈጠርህ እንዲህ አደርጋለሁ በማለት የሕዝባዊነት መሸርሸር (Thermadorial) ደረጃ መድረስ ነው። የራሺያ አብዮተኞች ይህን ሁኔታ ያውቁታል ሲሉ አስረድተዋል።
የአብዮቱ ሕዝባዊነት ሲያበቃ (Thermadorial ደረጃ ላይ ሲደርስ) ዐምባገነናዊ መሆን ይከተላል ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው፣ “ይኸውም ፍጹማዊ ዐምባገነን አገዛዝ (Absolutism, Absolutist) መሆን ማለት ነው። በፍፁማዊ ዐምባገነንነት ከተቀናቃኞች ባለፈ አብዮቱን ታግለው ባመጡ ታጋዮች ላይ ሳይቀር የማይመለስ እንደኾነና ሕዝባዊነት የሚረሳበት ወቅት እንደኾነ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ደረጃም ከዚህ አንፃር በመመዘን ፍርዱን መስጠት እንደሚቻል አመላክተዋል።
ፉፁማዊነት (Absolutism) ምንድን ነው?
ዶ/ር ዳኛቸው የአብዮትን አመጣጥና ምንነት እንዲሁም የደረጃዎቹን ባሕርይ ከጠቀሱ በኋላ ‘ፍጹማዊነት’ (Absolutism) የሚለውን ጥቅል ሐሳብ አብራርተዋል። በዶ/ር ዳኛቸው እምነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መንግሥታዊ ሥርዓት ‘Authoritarian’s’ ነው ወይስ ‘Dictatorial’ ከሚለው ሁሉ የሚስማማቸው “Absolutism” የሚለው ነው።
የዐፄ ኀይለ ሥላሴ የፈረስ ስም “ጠቅል” ነበር። ሥርዓታቸውና የፈረሳቸው ስም የተዋሃደ ነበር። ፈረሱን ተምሳሌታዊ ያደርጋሉ “ጠቅል” ሲሉ ፍፁማዊ ስርዓት (Absolute State) እየፈጠሩ ነበር። የሰሜኑን ባላባቶች ተራ በተራ በፖለቲካ ራቁት ካስቀሩ በኋላ “ጠቅል” ነው የሆኑት። እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ “አገር በእጄ” ነው ያሉት። ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ቢያንስ ግልፅ ነበሩ። አሁን ግን ለየት ያለ “ጠቅል” ነው የመጣብን ብለዋል።
በዶ/ር ዳኛቸው አነጋገር አሁን ያለው “ጠቅል” ስሙን የደበቀ ፈፁማዊነት (Absolutism) ነው። ስሙን የደበቀ ያሉትን (Absolutism) ሁለት መሠረታዊ ባሕርያት እንዳሉትም አስረድተዋል።
አንደኛው Absolutism የሚባለው “It is a power that is not oppose in fact by adequate countervailing powers” እንደሆነና ምንም ዐይነት ተቀናቃኝ ኀይል የሌለው ነው። የተደራጀውንም ሆነ ያልተደራጀውን የማይታገስ ፍፁማዊ ነው። ከተደራጀህ ትካተታለህ፣ ካልተደራጀህ አትችልም ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው “አንዲት የፍልስፍና ማኅበር እንመሰርታለን ብለን ስንሯሯጥ አንድ ቅፅ ሰጡን። ቅፁ ከዘጠኙም ክልል አንድ አንድ ሰው ከሌላችሁ “ኢትዮጵያ” የሚባል ቃል አትጠቀሙም ተባልን እና ወሰዱንና በነርሱ ቅፅ አካተቱን። ወደፊት ደግሞ ምን አይነት የፍልስፍና ውይይት እንደምናደርግ ቅጂውን ትልኩልናላችሁ ይሉን ይሆናል” ብለዋል። እና በአሁኑ ወቅት አፀፋዊ ኃይል የለም (No countervailing Force) ሲሉ ገልፀውታል። በአሁኑ ወቅት ነጻና ራሱን ችሎ የቆመ ሲቪል ማኅበረሰብ አይፈቀድም። የሃይማኖት ተቋማት፣ እንደ ዕድር ያሉት ማኅበራዊ ተቋማት ሳይቀሩ ተገብቶባቸዋል። ምናልባት ዕቁብ አምልጦ ይሆናል በማለት የመጀመሪያውን የ‘Absolutism’ ምልክት አብራርተዋል።
አሁን ባለንበት ወቅት የብዙኃን መዋቅር (pluralistic structure) የለም፤ ሁሉም ነገር አሃዳዊ ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው ስልጣን ከአንድ ምንጭ ነው የሚመነጨው። ያ ስልጣን ደግሞ መጠን የለውም። “ከድንጋይ ጠረባ አንስቶ እስከፈለጓት ድረስ ተደራጅተህ ና” ነው የሚለው “የምትደራጀው በእኔ ስር ነው። አውቅሃለሁ እመዘግብሃለሁ፤ የምርጫ ቀን ደግሞ ተሰልፈህ ትወጣታለህ ነው የሚለው” ሲሉ አስረድተዋል።
ሌላው የAbsolutism ፀባይ የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት (Centralized Democracy) መሆኑን ያብራሩት ዶ/ር ዳኛቸው በአሁኑ ወቅት ሊራቡና ሊበራከቱ የሚችሉ ቡድኖች (multiplied groups) እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም። በጥቅሉ “Uni-centric Power” ወይም ሁሉን ነገር ያካተተ ኃይል ነው ብለውታል።
በተጨማሪም የAbsolutism መንግስት ባሕርይ በሕግ የማይገሠጽ (a State that is not disciplined by law) የሚሉት ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው አገዛዙ ሕግ የማይገሥጸው ነው። አጥፊዎቹን እየቀጣ እራሱ ግን ሕጉ በማይደርስበት ቦታ ነው ያለው ብለዋል። በኢትዮጵያም ሕግ የማይገሰፀው ሹመኛ በየቀበሌው መኖሩን አስረድተዋል። ሀገሪቱም ቢሆን በስም ካልሆነ በስተቀር ሕገ-መንግስታዊ ሀገር አይደለችም። በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ሕግ ያልገራው ፈረስ ነው ብለዋል።
የፍጹማዊ ዐምባገነን አገዛዝ የፖለቲካ ኃይል ምን ላይ ነው ያረፈው?
ዶ/ር ዳኛቸው የAbsolutism ስርዓትን ምንነትና ሁኔታ ካስረዱ በኋላ ስርዓቱ በምን አይነት የፖለቲካ ስልጣን ላይ እንዳረፈም አብራርተዋል።
“ስልጣን ዝም ብሎ አይኖርም። አንድ ቦታ ላይ ማረፍ አለበት። ምርኩዝ ያስፈልገዋል። በመጀመሪያ ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን ከኢኮኖሚ ኃይል ጋር የተቆራኘ ነው። በፊውዳል ሥርዓት ጊዜ አስገባሪዎቹ የፖለቲካ ሥልጣን ነበራቸው። ስለዚህ ሥልጣን በሁለት ነገር ላይ ያርፋል። አንደኛው ሥልጣን በተፈጥሮ ላይ ሲሆን ሁለተኛው ሥልጣን በሰው ላይ ያርፋል። ሥልጣን በተፈጥሮ ላይ የልሂቃን ሥልጣን ነው። ዛፉ አይፈራገጥም፣ ወንዙም አይፈራገጥም። ስልጣን በሰው ላይ ሲሆን ግን አስቸጋሪ ይሆናል።
አንድ መንግስት ሥልጣኑን ሲያፀና ሦስት ወሳኝ ነገሮችን ይተገብራል። አንደኛው በማጥመቅና በማሳመን (Persuasion) ሰዎች በእውቀተና በስሜት ያንን የበላይ ሥልጣን እንዲቀበሉ ማስገደድ። ለዚህ ነው ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሃያ አራት ሰዓት ሲያወራ የሚውለው:: ሁለተኛው ቁሳዊ ጥቅማ ጥቅም (material Benefit) ነው። ለምሳሌ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እናደርሳችኋለን፣ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሁሉም ነገር አረንጓዴ ይሆናል … እንደዚህ ሲሆን እንደዚህ ይሆናል … ወዘተ እያሉ እኛ ከቆየን ትጠቀማለችሁ ይሉናል። ሦስተኛው ደግሞ አጅሬ ጉልበት (violence) ነው ብለዋል።
የሦስቱ ጣምራ ሂደት ሥልጣን በሰው ላይ (Power over men) እንደሚባል ያወሱት ዶ/ር ዳኛቸው ዴሞክራሲያዊ በሆኑና ባልሆኑ አገራት ከሦስቱ የሥልጣን ሂደቶች የትኛው የበላይ ይሆናል የሚል ነው። ርዕዮተ ዓለሙን እያሳመነ የሚሄድ ስርዓት ሊቆይ ይችላል። ቁሳዊ ጥቅም የሚሰጥ ሥርዓት የሚደራደርበት ነገር አለው። ጉልበቷ ግን ለአጭር ጊዜ “ቀጭ” ለማድረግ ትረዳለች። እና በፍፁማዊነት አገዛዝ ወቅት የማሳመንና ቁሳዊ ጥቅማ ጥቅም የመስጠት ሁኔታ እየቀነሰ ጉልበት እየጨመረ ይሄዳል” ብለዋል።
ሌላው በabsolute state ስርዓት በኢትዮጵያ ለየት የሚያደርገው power over other men derived from power over nature ነው ብለውታል። ይሄንንም ሲያብራሩ ፍፁማዊነቱ በተፈጥሮ በምጣኔ ሀብት ላይ የተመረኮዘ ነው። ነገር ግን ተፈጥሮን ምን አመጣው ብሎ መጠየቅ ይቻል ይሆናል። በኢትዮጵያ 60 ሚሊዮን ገበሬ ተፈጥሮ ላይ እየሰራ ነው። ተፈጥሮ ላይ የሚሰራን ሰው (ገበሬ) ተፈጥሮውን በመቆጣጠር የበላይ መሆን ነው። ይህ ደግሞ መሬት የመንግሰት ነው በማለት በ60 ሚሊዮን ገበሬ ላይ ስልጣንን ማፅናት ነው። ይህ ደግሞ (power over men derived from power over nature) የሚባለው እንደሆነ አስረድተዋል።
ይህ ደግሞ በዶ/ር ዳኛው አገላለፅ “የሚገርም መቆጣጠር” ነው ብለውታል። በሌላ አነጋገር ይህ የሚገርም ቁጥጥር 26 ሚሊዮን ገበሬ አውጥቶ ተራራ እና ወንዝ እያስቆፈረ መሆኑን አስረድተዋል። ዶ/ር ዳኛቸው “የቁጥጥር አባዜ” ያሉት ይህ አሰራር “ካድሬዎች በሚያወጡት ፕሮግራም መሠረት 26 ሚሊዮን ገበሬ ምንም ሳይከፈለው አርባ ቀን ማስቆፈር ማለት የሚገርም ነው። ፈውዳሎቹም እንደዚህ ያደረጉ አይመስለኝም። ሴት ልጇን አዝላ፣ ገበሬዎች ከቀሩ 60 እና 70 ብር እየተቀጡ፣ ከሁሉም ደግሞ የሚገርመው በቴሌቪዥን ሲቀርብ ባንዲራ ተይዞ አታሞ እየተመታ እልል እየተባለ… እንዴት ነው? የሰው ልጅ ሳይከፈለው፣ አርባ ቀን ለመስራት እየዘፈነ፣ እየዘለለ ጣራ እየመታ የሚሰራው? ምን አይነት የሰው ስነ-ልቦና ነው? የማይሆን አይነት የ‘ሕዳሴ ፕሮጀክት’ ይያዛል፤ ይፈርሳል …” ሲሉ አስረድተዋል።
ፍፁማዊነት እና ምስጢራዊነት
በዶ/ር ዳኛቸው አገላለፅ በ‘Absolutist State’ ትግል ስልታዊ ውሳኔዎች (tactical Decisions) አሉ። እነዚህ (tactical Decisions) ሁልጊዜ የሚሰሩት በምስጢር ነው። ይህ አሁን ያለው አገዛዝ absolutist ብቻ ሳይሆን Secretive (ምስጢራዊም) ነው። ለ‘Absolute’ ሥርዓት ምስጢር ጠቃሚና ወሳኝ ማሳሪያ ነው። ምስጢራዊ ሥርዓት ደግሞ ሄዶ ሄዶ የለየለት ‹ኦሊጋርኪ› ነው። ጥቂት አርስቶክራስት ናቸው ሀገር የሚመሩት። ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም፤ ስፋታቸው ብዙ ነው። ሁለት ሚሊዮን አባል …. ሦስት ሚሊዮን አባል…. “አባል አባል … ይሄንን አባባል በጣም ያፈቅሩታል። ነገር ግን ከላይ የኦሊጋርኪ ማነቆ አለ። ምስጢር ጠብ አትልም። እያዞሩ ግን የሰው ምስጢር በቴፕሪከርደር ይሰበስባሉ። ይሄ ዝም ብሎ አባል ነኝ እያለ የሚሽከረከረውን ተውት ማነቆው እላይ ነው። ማነቆው ጠባብ ናት’’ ብለዋል።
ነፃነትና ሕግ
ፍፁማዊ ስርዓትን የተነተኑት ዶ/ር ዳኛቸው ይሄው ስርዓት ከነፃነትና ከሕግ ጋር ስላለው ግንኙነትም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ነፃነትና ሕግ በጣም ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን በሰፊው አውስተዋል። ሕግና ነፃነት ወይም ነፃነትና ሕግ ያላቸው ዝምድና እንዲሁም ከህግ የበላይነት (Rule of law) ወደ Rule by law ‘‘ሕግ እያወጡ ማሸት’’ እያነፃፀሩ አሳይተዋል።
ሕግ እያወጡ መግዛት (Rule by law) የተወሰኑ ሰዎች እንደፈለጉ ሕግ እያወጡ ‘‘ተከተለኝ’’ ማለት ሲሆን የህግ የበላይነት (Rule of law) ግን በህግ መመራት መሆኑን አብራርተዋል።
ዶ/ር ዳኛቸው ነፃነትና ሕግ ያላቸውን ግንኙነት ሲያብራሩ ያለሕግ ነፃነት እንደሌለ ገልፀዋል። ሕግ በውስጡ ትእዛዝ ብቻ ሳይሆን መብትና ፍትህ ያዘለ መሆን አለበት ብለዋል። ትልቁ የእንግሊዝ ፈላስፋው ጆን ሎክ “ስልጣን በአንድ ቦታ ከተከማቸ በዚያው መጠን ነፃነት ይሞታል” ማለቱንም አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ በአቶ አበራ ጀምበሬ መጠናቱን ያስታወሱት ዶ/ር ዳኛቸው፣ ሕግ ዝም ብሎ ትእዛዝ አይደለም። ሕግ ሰዎች በር ዘግተው የሚያወጡት ትእዛዝ አይደለም። ሕግ መብት የሚል ፅንሰ ሐሳብ አለው። ፍትሕ ከሚባለው ነገር ጋራ አብሮ ተጣምሮ የሚገለጽ ነገር ነው። በኢትዮጵያ በሕግ አምላክ ሲባል ሕግ ፍትሕን ማቀፉን ያመለክታል። ‘‘ሕጉ ይከለክላል’’ ሲባል ፓርላማ ያወጣው ሕግ ማለት ብቻ አይደለም።
አሁን ሕግ መብት ፍትህ የሚለው ቀርቶ ሰዎች አንድ ቦታ ተሰብስበው የሚያወጡት ትእዛዝ ሆነ፤ እነ እገሌ… አሸባሪ ናቸው እየተባለ ሕግ ይወጣል። የውጭውን መሬት ሸጬ ጨርሻለሁ አሁን ደግሞ የግቢህን እሸጣለሁ የሚል ሕግ ይወጣል፤ የኻያ አራት ወይም የኻያ አምስት ዓመት ወጣት ርእዮት የምትባል ትንሽ ልጅ አነበበች ነው ምናምን ተብሎ 14 አመት ሽብርተኛ ተብላ ይፈረድባታል። ታዲያ ይሄ ሕግ ፍትህ አለው?’’ ሲሉ በመጠየቅ በሀገራችን ላይ ሕግና ነፃነት የተራራቁ ሆነዋል። ሕጉ አለ ብለን እንቅልፍ እንዲወስደን ነበር ነገር ግን ሕጉ ጥበቃ ሊያደርግልን አልቻለም። ምክንያቱም ከሰዋዊ ሥልጣን አልተላቀቅንም (Power depersonalized) መሆን አልቻለም። የሕግ አመራር (Rule by law) ሳይሆን የሰው አመራር ነው ያለው ብለዋል።
ፍትህና ህግ እየተጋጩ መሆኑንም ዶ/ር ዳኛቸው አብራርተዋል። ፍትሃዊ ያልሆነ ሕግ፤ ሕግ አይደለም ብለዋል ‘Just Law’ እና ‘Unjust Law’ የሚባል ነገር እንዳለም አብራርተዋል። ማርቲን ሉተር ኪንግ ታስሮ አንድ ቄስ ‘‘አንተ ሰላማዊ ሰልፍ እያስወጣህ ሕግ እየሰበርክ ነው’’ አሉት እሱ በበኩሉ ‘‘እኔ ሕግ ሰባሪ አይደለሁም። እርስዎም ሆኑ እኔ ሴንት ኦገስቲንን አንብበናል። ‘Just Law’ የሚባል ነገር አለ Unjust Law የሚባል ነገር አለ። እኔ እየተቃወምኩ ያለሁት ዘረኛውን (Unjust Law)ን ነው። Unjust Law ደግሞ ሄዶ ሄዶ ህግ አይደለም አላቸው። እና ሕግ ዝምብለው ሰዎች የደነገጉት ትእዛዝ ማለት አይደለም። ቢያንስ ፍትሃዊ መሆን አለበት። ሂትለርም ሕግ እያወጣ ነበር የሚያሻው። እና አሁንም ሕገ መንግስቱን ተፃራችኋል፣ ሕጉ አይፈቅድም የሚባለው የሕግ Fetish (ልክፍት) ነውያለው’’ ብለዋል።
ሌላው የ‘Absolute State’ ባሕርይ የቃላት ቅየራ መሆኑን ዶ/ር ዳኛቸው አብራርተዋል። የድሮ ቃላቶች እንደ ወለቀ ሱሪ ይዘቀዝቁትና በውስጣቸው ያለው ሳንቲምና መሐረባቸው ይወጣና ሌላ ስያሜ ይሰጣቸዋል። ቃላቱ የሐሳብ ይዘታቸው ከወጣ በኋላ የራስህን ጫና ታሳርፍባቸዋለህ። በኢሕአዴግም ሁለት አይነት ቃል ነው ያለው። በኢህአዴግኛ ‘‘ኪራይ ሰብሳቢ’’ መጥፎ ቃል ‘‘ልማታዊ ባለሃብት’’ ጥሩ ቃል ነው። ይህ ማለት ከቃል ጋር ያለውን ሃሳብ እንዳንፈትሽ ቃሉን መጠቋቆሚያ ንቅሳት (ሲግናል) ያደርጉታል፤ ‘‘ኪራይ ሰብሳቢ’’ ሲሉህ ትደነግጣለህ፤ “Bad Boy” ነህ ማለት ነው።
‘‘እኔ የኮራሁ ኪራይ ሰብሳቢ ነኝ። እኔ የማውቀው ቤት ሲከራይ፣ ብስክሌት ሲከራይ፣ መኪና ሲከራይ ነው። እኔም ከደረግ የተረፈ ቤት እያከራየሁ እንጂ የዩኒቨርሲቲው ደመወዝ አይበቃኝም። ታክስ ግን እከፍላለሁ። እና ኪራይ ሰብሳቢ እያሉ ለምን ሞራሌን ይነኩታል። በአምስትና ስድስት ሺህ ዶላር ቤታቸውን የሚያከራዩ ጎበዞች እያሉ ዞረው እኔን ኪራይ ሰብሳቢ እንዴት ይሉኛል’’ ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው የተሰጠንን ቃል ብቻ ይዘን እንድንቀጥል ነው የሚፈልጉት ሲሉ አስረድተዋል።
በመጨረሻ ኢህአዴግን የሚገልፅልኝ ከአንድ ጣሊያናዊ ፈላስፋ የወሰድኩት ሁለት ቃል አለኝ ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው ሁለቱ ቃላትም Noviticsm and Beyond-ism የሚሉ ናቸው። Noviticsmየሚለው ቃል Novices ከሚለው ቃል የመጣ ነው። Novice ደግሞ አዲስ ጀማሪ ማለት ነው። Beyond-ism ያው Beyond መሄድ ማለት ነው።
Noviticsm ማለት ሁሉን ነገር እኛ እንደ አዲስ ጀመርነው ማለት ነው ያሉት ዶ/ር ዳኛቸው ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም አንድ ቀልድ አለው ‘‘ለቤተሰቤ አራተኛ ልጅ ለመሆን የመጀመሪያው ነኝ’’ ይላል። ይሄ Noviticsm ነው፤ Original ማለት ነው ብለዋል።
ወደ ጣሊያኑ ፈላስፋ (ሳርቱሪ) ሲመለሱ ሁሉም ትውልድ በዘመኑ Original ለመሆን ይሞክራል። ያልተባለና ያልተደረገ ነገር አደረኩ ለማለት ይሞክራል፤ “But it is not easy to be original”፤ ነገር ግን የታሪክ ቅጥያ የሚባል ነገር አለ። አልፌዋለሁ ስትል ይመጣል። ተሻግረነዋል ስትል የመጣል። አሁን ለምሳሌ በፊውዳል ጊዜ የነበሩት እንደ “ቀዳማዊ እመቤት” የሚባሉ አባባሎች እየመጡ ነው። ወደፊት ደግሞ ራስ፣ ደጃዝማች… እያለ ይቀጥላል’’ ብለዋል።
ይህን ካሉ በኋላ ዶ/ሩ ወደ ፈላስፋው ሲመለሱ “The easy way of being original” ማለት ብዙ አለማወቅ ነው። ብዙ አለማወቅ ደግሞ ታሪክን አለማንበብ ነው። ይሄ ደግሞ “Arrogance of Ignorance” ማለት ነው። ይህም ማለት አለማወቅ የራሱ የሆነ ‘Ignorance’ አለው። ስታውቅ ትሑት ትኾናለህ፤ ትሕትናን ታዳብራለኽ፤ ካላወቅኽ ግን ጣሊያናዊ ፈላስፋ በዚህ ዓለም ላይ አልፎ አልፎ ‘‘እኛ እስከመጣን ድረስ ዓለም ጨለማ ውስጥ ነበረች ዕድሜ ለእኛ ችቦ ብርሃን ታየ የሚሉ ጎበዞች ይመጣሉ’’ ብሏል። ጣሊያኑ ስለኢትዮጵያ የሚያውቀው ነገር ባይኖርም እስቲ ከኢትዮጵያ ጋ አዛምዱት ሲሉ ጠይቀዋል።
ባለሥልጣናት “በኢትዮጵያ ስንመጣ ብርሃን ሆነ” ማለት የተለመደ ነው። ስለህግ ሲወራ ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ምንም አይነት ሕግ ያልነበራት ትመስላለች። ጎበዞቹ ሲመጡ ሕግ እንዳመጡለት ነው የሚያወሩት። ጎበዞቹ [ኢህአዴጎቹ] ሁሌ ስንገዳደል አግኝተውን እነሱ ባመጡት ሕግ እንደ አዳኑን ይነግሩናል። ነገር ግን ይሄ አገር ስንት ሺህ አመት የኖረ ሕዝቡም ያልተፈራረመው ማኀበራዊ ውል (social contract) ያለው ሕዝብ ነው። ሕዝቡ ለዚህ ነው የማይፈርሰው። እንደአካፋው ብዛት ባለፉት 21 ዓመታት ይሄ አገር (ስቴት) መናድ ነበረበት። ከመንግስት ውል በላይ በማኀበራዊ ውሉ የጠነከረ ሕዝብ ነው። የሶማሌ ሕዝብ ማኀበራዊ ውሉ በጎሳ የላላ ስለሆነ ቢሉት ቢሉት አንድ መሆን አልቻለም ብለዋል።
ሁለተኛው የጣሊያናዊ ፈላስፋ አባባልና ከኢሕአዴግ ሁኔታ ጋራ ያዛመዱት ‹Beyond-ism› (ተሻግረዋል) የሚለውን ፅንሰ ሐሳብ ነው። ይህ ሐሳብ እብሪት ነው ብለዋል። በየቴሌቪዥኑ ‘‘በንጉሱ ጊዜ’’ የሚባለው አሁን አሁን ደግሞ ‘‘በሁለቱ ስርዓቶች’’ እየተባለ ነው። እና ‘‘ተሻግረነዋል’’ የሚለው አገላለፅ እብሪት ይወልዳል። ‘‘እኛ ነን የሁሉም ጀማሪ’’ ይባላል። ‘‘ድሮ እንዲህ ነበር አሁን እንዲህ ነው የማለት አባዜ ነው።’’ ብለዋል።
በመጨረሻም ዶክተር ዳኛቸው፣ አዲስ የመሆን ጥልቅ ፍላጎት ሁሉን ነገር አልፌአለሁ በሚል ሐሳብ ቢወጠርም ታሪክ ግን እንደ ሲሲፒየስ ሊመስል ይችላል በሚል ተዘምዶ ንግግራቸውን ቋጭተዋል። እንዲህ ሲሉ፡- “ሲሲፒየስ ማለት ትልቅ ቋጥኝ ይዞ ከገደል አፋፍ ላይ ይወጣና ልክ ገደሉን ወጣሁ ሲል ቋጥኙ መልሶ ይወርድበታል። የሀገር ታሪክ ማለት በከፊል እንደዚያው ነው። ይህም እነኾ 26 ሚሊዮን ገበሬ አሠማርቼ የኢትዮጵያን መልክአዊ ምድራዊ ገጽታ እለውጣለኹ የሚለው እብሪታዊ ፕሮጀክት መገለጫ ነው!!”